የጽርሐ ጽዮን ሐዋርያት ጎላ ቅዱስ ሚካኤል የፍኖተ ብርሃን ሰ/ት/ቤት (Official Channel)
2.58K subscribers
6.1K photos
67 videos
60 files
1.7K links
ይህ በጽ/ጽ/ሐ/ጎ/ቅ/ሚካኤል ቤ/ክ ፍ/ብ/ሰ/ት/ቤት እውቅና የተሰጠው የቴሌግራም ቻናል ነው።
Download Telegram
መስከረም 11/2014 ዓ.ም ወርሐዊ የቅዱስ ሚካኤል ጸሎት ተደረገ።

#ሚካኤል ብሂል /የቃሉ ትርጉም/ መኑ ከመ አምላክ እንደ እግዚአብሔር ያለ ማነው ማለት ነው ።
#ቅዱስ ሚካኤል የሰማይ ሰራዊት አለቃ ነው ኢያሱ 5 ÷ 14
#በዘመነ ብሉይ እስራኤላውያንን በበረሃ በስደት ጊዜ የተራዳ መልአክ ነው በዚህም (መጋቤ ብሉይ በመባል ይጠራል) ዘፀአት 23
#ለሰው ልጆች አዛኝ ተራዳኢ መልአክ በመሆኑም ሩሁሩህ መልዐክ ይባላል ።
#ዛሬም ምልጃውና ተራዳኢነቱ ለሐገራችን ለኢትዮጵያና ለህዝቦቿ ጋሻ መከታ ጥላ ከለላ ይሁንልን ጦርነቱን ረሐብ ስደቱንም ከአምላክ በተሰጠው ቃል ኪዳን እየተራዳ ያስታግስልን አሜን
#መስከረም_13

#ቅዱስ_ባስልዮስ_ዘቂሣርያ

መስከረም ዐሥራ ሦስት በዚህች ቀን ታላቅና ቅዱስ የሆነ የቂሣርያ ሊቀ ጳጳሳት ባስልዮስ ላደረገው ተአምር መታሰቢያ ሆነ።

ይህም እንዲህ ነው አንድ ጐልማሳ አገልጋይ የጌታውን ልጅ ስለወደዳት ልቡ እርሷን ወዶ እንደ እሳት እስከ ነደደ ድረስ እርሷንም ከመውደዱ ብዛት የተነሣ ወደ አንድ ከሀዲ ሥራየኛ ሔደ። ሥራየኛውም የክህደት ደብዳቤ ጽፎ ሰጠው። ወደ አረሚ መቃብርም ሒዶ በመንፈቀ ሌሊት ደብዳቤዋን ይዞ ወደላይ እጁን አንሥቶ በዚያ እንዲቆም አዘዘው።

ይህም አገልጋይ ይህን ነገር ተቀብሎ ያ መሠርይ እንዳዘዘው አደረገ። በዚያንም ጊዜ ከሰይጣናት አንዱ መጥቶ ወደ አለቃቸው ወስዶ አደረሰው ያቺንም የክህደት ደብዳቤ ከእጁ ወሰደ። እንዲህም ብሎ ጠየቀው "ንጉሥህ ክርስቶስን ትክደዋለህን? ፈቃድህን ከፈጸምኩልህ በኋላ ወደእርሱ አትመለስምን?" ይህም ጐስቋላ ባሪያ "አዎን ጌታዬ ያዘዝከኝን ሁሉ አደርጋለሁ" አለው። መስሐቲ ዲያብሎስም ይህን ልታደርግ በእጅህ ደብዳቤ ጻፍልኝ አለው። እርሱም በከበረ ደሙ የዋጀውን የክብር ባለቤት ክርስቶስን ክዶ በደብዳቤ ውስጥ የክህደቱን ቃል ጻፈለት።

በዚያንም ጊዜ ሰይጣን በጌታው ልጅ ልብ ውስጥ የፍትወት እሳትን አነደደ ይህንንም ባሪያ እጅግ ወደደችው ከእርሱም መታገሥ አልተቻላትም። ወደ አባቷ በመጮህ በግልጥ ከዕገሌ ባሪያህ ጋር ካላጋባኸኝ አለዚያ ራሴን እገድላለሁ ትለዋለች እንጂ መታገሥ አልተቻላትም። አባትና እናቷም ፈጽሞ አዘኑ በምንም በምን ሊያስታግሥዋት አልቻሉም። የዚያም አገልጋይ ፍቅሩ በየዕለቱ በልቧ ይጨመር ነበር እንጂ። ስለዚህም ራሷን እንዳትገድል አባቷ ፈራ ለዚያ ባሪያ ሰጠው። እርሱም የጌታውን ልጅ ተቀብሎ ወደቤቱ አስገባት። ከርሷ ጋር ያለውን ፍላጎቱንም ፈጸመ። ከእርሱም ጋር ረጅም ጊዜ ከኖረች በኋላ አባትና እናቷም ይቅር ብሎ ኀዘናቸውን ከላያቸው ያርቅላቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ኀዘንንና ልቅሶን አብዝተው ነበር።

ከዚህም በኋላ ክብር ይግባውና ጌታችን ክርስቶስ ጩኸታቸውን ሰማ ልመናቸውንም ተቀብሎ ይህ የወደደችው አገልጋይ ጐልማሳ ክርስቲያን እንዳልሆነ አስገነዘባት ከእርሷ ጋር በነበረበት በዚህ በረጅም ዘመን አንዲት ቀን እንኳ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲሔድ ሥጋውንና ደሙንም ሲቀበል ወይም አዳኝ በሆነ በመስቀል ምልክት ራሱን ሲአማትብ እርሷ አላየችውም።

ስለእምነቱም ጠየቀችው ግን አልገለጠላትም እርሷም እንዲህ አለችው "አንተ ክርስቲያን ከሆንክ ና በአንድነት ወደ ቤተ ክርስቲያን እንሒድና በፊቴ ቅዱስ ቊርባንን ተቀበል።" እንዲህም በአስገደደችው ጊዜ ስለርሷ ያደረገውን ሁሉ ወደ ሥራየኛ እንደሔደም በሰይጣንም አምኖ እምነቱንም በክርታስ ጽፎ ያንን ክርታስ ለሰይጣን እንደ ሰጠው ነገራት።

ይህንንም ነገር ከእርሱ በሰማች ጊዜ ደነገጠች መሪር ልቅሶንም አለቀሰች ራሷንም በማወዛወዝ እጅግ ተጸጽታ አዘነች። ያን ጊዜም ፈጥና ተነሣች የቤተ ክርስቲያን ምሰሶ ወደሆነው ወደ ሀገርዋ ሊቀ ጳጳሳት ወደ ቅዱስ ባስልዮስ ሔደች ከእግሩ በታችም ወድቃ ሰገደችለት በላይዋ የደረሰውን ሁሉ አስረዳችው ለሰው ልጆች ጠላት ከሆነ ከሠይጣን እጅ ፈጽሞ ያድናት ዘንድ ብዙ በማልቀስ ለመነችው።

ቅዱስ ባስልዮስም ባሏ የሆነውን ባርያ ወደርሱ ልኮ አስመጣውና ጠየቀው እርሱም የሠራውን ሁሉ አስረዳው ቅዱስ ባስልዮስም "ተመልሰህ ክርስቲያን ልትሆን ከሰይጣንም እጅ ልትድን ትወዳለህን?" አለው ያም ባርያ "ጌታዬ ይሆንልኛልን?" አለ ይህ ቅዱስ አባትም የፈጣሪህን ስም እየጠራህ ልብህን አጽና አለው።

ከዚህም በኋላ ከእርሱ ዘንድ በአንድ ቦታ ዘጋበት በመስቀል ምልከትም አማተበበት እንዲጸልይም አዘዘው ራሱ ቅዱስ ባስልዮስም ስለርሱ ጸለየ። ከሦስት ቀኖች በኋላም ጎበኘው እንዲህም አለው በእሊህ በሦስት ቀኖች የደረሰብህ ምንድን ነው እርሱም በላዩ በመጮህ ሠይጣናት ሲያስፈራሩት ያንንም ደብዳቤ ሲአሳዩትና በእርሱ ላይ ሲቆጡ በመከራ ውስጥ እንደኖረ ነገረው ቅዱስ ባስልዮስም ከእሳቸው ቁጣ የተነሣ አትፍራ እግዚአብሔር ይረዳሃልና አጽንቶም ይጠብቅሃል አለው።

ከዚህም በኋላ ጥቂት እንጀራና ውኃ ሰጥቶ ወደ ቦታው መለሰው ቅዱስ ባስልዮስም ስለዚያ አገልጋይ ሒዶ ይጸልይ ጀመረ። ዳግመኛም ከሦስት ቀኖች በኋላ ጐበኘውና በእርሱ ላይ ምን እንደ ደረሰበት ጠየቀው ያ አገልጋይም ጩኸታቸውን እሰማለሁ ግን አላያቸውም ብሎ መለሰለት። እንጀራና ውኃም ሰጠውና መከረው ወደ ቦታውም መለሰውና ስለርሱ ሊጸልይ ቅዱስ ባስልዮስ ሔደ። እስከ አርባ ቀኖች ፍጻሜ ድረስ እንዲህ አደረገ። በአርባውም ቀን ፍጻሜ ከእርሱ ስለ ሆነው ጠየቀው ያ አገልጋይም እንዲህ አለው ቅዱስ አባቴ ሆይ ስለ እኔ ሰይጣንን ስትጣላውና ድል አድርገህ ጥለህ ስትረግጠው በዛሬዋ ሌሊት አየሁ አለው።

ቅዱስ ባስልዮስም ይህን ነገር ከእርሱ በሰማ ጊዜ እጅግ ደስ አለው የገዳማቱን መነኰሳትና ካህናቱንም ጠርቶ ስለዚያ ሰው ያቺን ሌሊት መላዋን እንዲጸልዩባት አዘዛቸ። በነጋ ጊዜም ያንን አገልጋይ ወደ ቤተክርስቲያን እንዲአመጡት የዚያችንም አገር ሕዝብ ሁሉንም ሰብስቦ እጆቻቸውን ወደ ሰማይ አንሥተው አቤቱ ክርስቶስ ማረን ይቅር በለን እያሉ ወደ እግዚአብሔር ፈጽሞ እንዲማልዱ አዘዛቸው እንዳዘዛቸውም አደረጉ።

እንዲህም እያሉ ሲማልዱ ያ ሰው ጽፎ ለሰይጣን የሰጠው የክህደት ደብዳቤ ከሰይጣን እጅ በሕዝቡ ሁሉ ፊት ወደቀ ሁሉም ደስ ብሏቸው ምስጉን እግዚአብሔርን አመሰገኑት የከበረ አባት ባስልዮስም ባረካቸው ሥጋውንና ደሙንም አቀብሎ ወደ ቤቶቻቸው በሰላም በፍቅር አሰናበታቸው ። እነርሱም ስለ ኃጢአታቸው ስርየትና ስለ ድኅነታቸው ፈጽሞ ደስ እያላቸው እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ይህንን ቅዱስ አባት ባስልዮስን እያከበሩ ወደ ቤታቸው ገቡ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ አባት ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መስከረም)
አቡነ አረጋዊ ማለት የልጅ አዋቂ ማለት ሲሆን አባታቸው ይስሐቅ እናታቸው እጅና ይባላሉ ሀገራቸው ቆስጥንጥንያ ሲሆን በጥር 14 ቀን በ400 ዓ.ም ተወለዱ በ14አመታቸው ወደ ገዳም ገቡ ከአባ ጳጉሚስ ምንኩስናቸውን ተቀበሉ።

በጥቅምት 14 ቀን በ470ዓ.ም ወደ ታላቂቷ ሀገር ኢትየጵያ መጡ ደብረ ዳሞ የቀድሞ ቦታ ሃሌሉያ ይባል ነበር ከዚያ ተራራ ስር ሆነው ማን ያውጣኝ እያሉ ሲፀልዩ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ዘንዶውን ላከላቸው።

ዘንዶውም ቁመቱ 60ክንድ ነበር በወገባቸው ላይ ተጠምጥሞ ጥቅምት 12 ቀን መልአኩ ዘንዶውን እያዘዘው ተራራውን ወጥተዋል አባታችን በተወለዱ በ158 አመታቸው በሞት ፈንታ በጥቅምት 14 ቀን በ558 ዓ.ም ተሰውረዋል።

በረከታቸው ሁላችንን ይጠብቀን
👇የሰንበት ት/ቤታችንን Youtube ገጻችንን ሰብስክራይብ በማድረግ አገልግሎታችንን ይደግፉ 👇 https://m.youtube.com/channel/UCXMG9oO5j1M-lRbAn0OdVdQ
#መስከረም_15 በዚህች ቀን የዲያቆናት አለቃ የሰማዕታት መጀመሪያ ለሆነ #ቅዱስ_እስጢፋኖስ የሥጋው ፍልሰት ሆነ።

ይህም እንዲህ ነው ከአረፈበት ጊዜ ብዙ ዓመቶች ከአለፉ በኋላ ሦስት መቶ ዓመት ያህል ከዚያም የሚበዛ ጻድቁ ቈስጠንጢኖስ ሲነግሥ የቀናች ሃይማኖትም ተገልጣ የሕያው እግዚአብሔር አምልኮት በሁሉ ሲዘረጋ ያን ጊዜ የቅዱስ እስጢፉኖስ ሥጋ በአለበት አቅራቢያ የገማልያል ቦታ በትምባል በኢየሩሳሌም በአንዲት ቦታ አንድ ሰው ይኖር ነበር። የዚያም ሰው ስም ሉክያኖስ ነው ተጋዳይ የሆነ እስጢፋኖስም ብዙ ጊዜ በሕልም ተገለጠለት እንዲህም ብሎ አስረዳዉ እኔ እስጢፋኖስ ነኝ ሥጋዬ በዚህ ቦታ ተቀብሮ አለ።

ያም ሉክያኖስ የሚባል ሰው የኢየሩሳሌም ኤጲስቆጶስ ወደ ሆነው መጥቶ በራእይ ያየውን ይህን ነገር ነገረው ኤጲስቆጶሱም ሰምቶ እጅግ ደስ አለው ያን ጊዜም ሁለት ኤጲስቆጶሳትን፣ ካህናትንና፣ የቤተ ክርስቲያንን ሰዎች ሁሉ ከእርሱ ጋራ ይዞ ተነሣ የቅዱስ እስጢፋኖስ ሥጋ በውስጡ ወዳለበት ወደዚያ ቦታ ደርሰው ሊቆፍሩ ጀመሩ ታላቅ ንውጽውጽታም ሆነ የቅዱስ እስጢፋኖስ ሥጋ በውስጡ ያለበት ሣጥን ተገለጠ ከእርሱ እጅግ በጎ የሆነው የሽቱ መዓዛ ሸተተ።

በሰማያት ለእግዚአብሔር ምስገና ሆነ በምድርም ሰላም ለሰው ነፃነቱ ይሰጠው ዘንድ በጎ ፍቃድ እያሉ ሲያመሰግኑ የመላእክትን ቃሎች ሰሙ። እንዲህም መላልሰው ሦስት ጊዜ አመሰገኑ ኤጲስቆጶሳቱና ካህናቱም የቅዱስ እስጢፋኖስን ሥጋ በያዘ ሣጥን ፊት ለጌታ ሰገዱ ከዚያም በኋላ ወደ ጽርሐ ጽዮን እስኪያደርሱት ብዙ መብራቶችን አብርተው በመያዝ በማኀሌት ምስጋና እየዘመሩ ተሸከሙት።

ከዚህም በኋላ እንዲህ ሆነ በኢየሩሳሌም ነዋሪ የሆነ የቊስጥንጥንያ ተወላጅ ስሙ እለእስክንድሮስ የሚባል ሰው ነበር ለቅዱስ እስጢፋኖስም ውብ የሆነች ቤተ ክርስቲያንን ሠርቶለት ሥጋውን አፍልሰው ወደርሷ ወስደው አኖሩት ከአምስት ዓመት በኋላም እለእስክንድሮስ አረፈ ሚስቱም በቅዱስ እስጢፋኖስ አስከሬን ጕን ቀበረችው። ከሌሎች አምስት ዓመቶችም በኋላ የእለእስክንድሮስ ሚስት የቧላን አስከሬን ወደ ቊስጥንጥንያ አገር ይዛ ልትሔድ አሰበች ባሏንም ወደ ቀበረችው እርሱ ባሏ ወደ ሠራት ቤተ ክርስቲያን ሔደች የባሏ ሥጋ ሣጥን ግን የቅዱስ እስጢፋኖስን ሥጋ በያዘ ሣጥን አምሳል ነበር በእግዚአብሔር ፈቃድ የቅዱስ እስጢፋኖስን ሣጥን ወስዳ እስከ አስቃላን ከተማ ተሸከመችው ከዚያም ወደ ቊስጥንጥንያ ልትጓዝ በመርከብ ተሳፈረች።

በመርከብ ስትጓዝ ከሣጥኑ ጣዕም ያለው ምስጋናን የምትሰማ ሆነች እጅግም አድንቃ ያን ሣጥን ልታየው ተነሣች በውስጥ የቅዱስ እስጢፋኖስ ሥጋ ያለበት ሣጥን እንደሆነ ተረዳች ይህም የሆነው ክብር ይግባውና በእግዚአብሔር ፈቃድ እንደሆነም አወቀች ወደ ኢየሩሳሌም ትመለስ ዘንድ አልተቻላትም ይህንንም ታላቅ ጸጋ ስለሰጣት ልዑል እግዚአብሔርን አመሰገነች።

ወደ ቍስጥንጥንያ አገርም በደረሰች ጊዜ ያቺ ሴት ወደ ንጉሡ ሒዳ የቅዱስ እስጢፋኖስን ዜና ከእርሱ የሆኑትን ተአምራት ወደ ቍስጥንጥንያ አገር ወደብም እንደ ደረሰ ነገረችው ሰምቶም እጅግ ደስ አለው ንጉሡም ከሊቀ ጳጳሳቱና ከካህናቱ ከብዙ ሕዝቦችም ጋር ወጣ ከወደቡም በክብር አንሥተው ወደ መንግሥት አዳራሽ እስከ አስገቡት ድረስ በፍጹም ደስታ እየዘመሩና እያመሰገኑ ተሸክመውት ተጓዙ።

ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ከእርሱ ተአምራትን ገለጠ በሠረገላ ሥጋውን ጭነው በሁለት በቅሎዎች በሚስቡት ጊዜ ቍስጣንጢንዮስ ከሚሉት ቦታም ሲደርሱ የቅዱስ እስጢፋኖስንም ሥጋ በዚያ እንዲያኖሩ ስለ ፈቀደ የሚስቡት በቅሎዎች ቆሙ። አልተንቀሳቀሱም በቅሎዎችንም ይመቷቸው ጀመሩ የቅዱስ እስጡፋኖስን ሥጋ በዚህ ሊያኖሩ ይገባል የሚል ቃል ከአንዱ በቅሎ ሰሙ ይህንንም ያዩና የሰሙ ሁሉም አደነቁ።

እግዚአብሔርንም አመሰገኑት የበለዓምንም አህያ ያናገራት እርሱ እነዚህን የቅዱስ እስጢፋኖስን ሥጋ የተሸከሙትን በቅሎዎች ያናገራቸው እርሱ እንደሆነ አወቁ። ንጉሡም በዚያ መልካም የሆነች ቤተ ክርስቲያን ሠርተው ይህን የከበረና ንጹሕ የሆነ ዕንቈ ባሕርይ በውስጧ እንዲያኖሩ አዘዘ። ይኸውም ለተመሰገነና ለተባረከ ሐዋርያ የዲያቆናት አለቃና የሰማዕታት መጀመሪያ ለሆነ እስጢፋኖስ ሥጋው ነው።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን ።
#ፍኖተ_ብርሃን_ሰንበት_ት/ቤት

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መስከረም እና #ከገድላት_አንደበት)
#ፍኖተ_ብርሃን_ሰንበት_ት/ቤት
https://t.me/finotebirhan12
https://t.me/finotebirhan12
https://t.me/finotebirhan12
መስቀልን በመስቀል አደባባይ
✔️ ሁሉም ከአቅመ ደካማና ከህጻናት በስተቀር በመስቀል አደባባይ በድምቀት እንዲያከብር፣
✔️ ሁሉም የአፍ መሸፈኛ ጭንብል እንዲያደርግ፣
✔️ የቤተክርስቲያን አርማ ያለበትሰንደቅ አላማ እና ህጋዊው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ለበዓሉ ድምቀት የተፈቀደ ነው።
👇 በዕለቱ ወደ አደባባዩ ለመግባት የተከለከሉ 👇
👉 ሳኒታይዘር፣እስክሪብቶ፣ ቻርጀር እና ሌሎች ተቀጣጣይ ኤሌክትሮኒክስ እቃዎች!!!
👉 ሞባይሎን በፍተሻ ወቅት እንዲያበሩ የጸጥታ መስፈርቱ ስለሚጠይቅ የማይበራ ወይም ቻርጅ ያልተደረገ ሞባይል ይዞ ማምጣት ክልክል ነው!!!
#ሁላችንም_በዓላችንን_በከፍተኛ_ድምቀትና_በፍጹም_ሰላም_እንዲከበር_የድርሻችንን_እንወጣ
የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት
#መስከረም_20
#ቅዱስ_አትናቴዎስ_ካልዕ
መስከረም ሃያ በዚች ቀን ለሊቃነ ጳጳሳት ሃያ ስምንተኛ የሆነ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባት አትናቴዎስ አረፈ።
ይህም አባት አስቀድሞ የእስክንድርያ አገር ቤተክርስቲያን መጋቢ ነበር ከእርሱም በፊት የነበረ ሊቀ ጳጳሳት አባ ጴጥሮስ በአረፈ ጊዜ ይህን አባት ሊቀ ጵጵስና ይሾሙት ዘንድ ሁሉም ኤጲስቆጶሳት መኳንንቱና ሊቃውንቱ ሕዝቡም በአንድ ምክር ተስማሙ በእግዚአብሔር ሕግ በመጽናት ያደረገው መልካም ተጋድሎውና ቅድስናው ስለርሱ ስለተነገረ መንፈስ ቅዱስም እንደ አደረበት ስለ ተረዱ ያለ ፈቃዱም ወስደው ሊቀ ጵጵስና ሾሙት።
ከዚህም በኋላ ክብር ይግባውና የክርስቶስን መንጋዎች በምክሩ፣ በትምህርቱ፣ በጸሎቱ ከዲያብሎስ ተኵላዎች በመልካም አጠባበቅ ጠበቃቸው እሊህም ሃይማኖትን የሚለውጡ መናፍቃን ናቸው።
በሊቀ ጵጵስናውም ፯ት ዓመት ኖረ እግዚአብሔርንም አገልግሎ በሰላም አረፈ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን ።
(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መስከረም)
#መስከረም_21

መስከረም 21 በዚህች ቀን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት ዕፀ መስቀል በግሸን ደብረ ከርቤ የተቀመጠበት ዕለት ነው

#ዕፀ_መስቀል (#ግሸን_ማርያም)

በሌላ በኩል መስከረም ፳፩ ቀን የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በአምባሰል ተራራ በግሸን ደብረ ከርቤ የገባበትና በዓሉ የከበረበት ዕለት ነው፡፡ ታሪኩም በአጭሩ የሚከተለው ነው፤

ዐፄ ዳዊት መንፈሳዊና ደግ ንጉሥ ነበሩ፡፡ በዘመናቸው በኢትዮጵያ ቸነፈር ተከሥቶ ሕዝቡ ስለ ተሰቃየባቸው እጅግ አዘኑ፤ በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ቢያመለክቱም ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላኩ ባሕታዊ መጥተው "የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መስቀል አስመጥተህ በአገርህ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አሠርተህ ብታስቀምጥ ረሃቡ፣ ቸነፈሩ ኹሉ ይታገሥልሃል" አሏቸው፡፡ ዐፄ ዳዊትም ከብዙ ገጸ በረከት (ስጦታ) ጋር "የጌታችንን መስቀል ላኩልኝ" የሚል መልእክት አስይዘው መልእክተኞችን ወደ ኢየሩሳሌም ሰደዱ፡፡ መልእክተኞቹም በታዘዙት መሠረት መስቀሉን ይዘው መምጣታቸውን ዐፄ ዳዊት ሲሰሙ "ክተት ሠራዊት ምታ ነጋሪት" ብለው መስቀሉን ለመቀበል ጉዞ ጀመሩ፡፡

ዐፄ ዳዊት ስናር (ሱዳን) ደርሰው ከመልእክተኞቹ ጋር ተገናኝተው መስቀሉን በክብር አጅበው ወደ መካከል ኢትዮጵያ ለማስገባት ሲነሡም ከበቅሏቸው ወድቀው ጥቅምት ፱ ቀን ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፤ በዚህም ሠራዊታቸው ተደናግጠው የጌታችንን መስቀል እዚያው ትተው የዐፄ ዳዊትን አስከሬን ይዘው ተመለሱ፡፡ መስቀሉ በስናር ከቆየ በኋላ የዐፄ ዳዊት ልጅ ዘርዐ ያዕቆብ ሲነግሡ ወደ መሃል ኢትዮጵያ አምጥተው ቤተ ክርስቲያን አሠርተው ለማስቀመጥ ቢያስቡም ምቹ ቦታ ግን ሊያገኙ አልቻሉም ነበር፡፡ ንጉሡና ሠራዊታቸው ምቹ ቦታ ሲፈልጉ መስቀሉን በኤረር ተራራ፣ በደብረ ብርሃን፣ በመናገሻ ማርያም ዓምባ፣ በእንጦጦ ጋራ ብዙ ጊዜ አስቀምጠውት ቆይተዋል፡፡

መስቀሉ በእንጦጦ ጋራ ሳለ እግዚአብሔር አምላክ "አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል፤ መስቀሌን በመስቀለኛ ተራራ ላይ አስቀምጥ" የሚል ቃል ለንጉሡ በራእይ ነገራቸው፡፡ መስቀሉን ወደ ወሎ ሀገረ ስብከት እንዲወስዱትም አዘዛቸው፡፡ ንጉሡና ሠራዊታቸው በእግዚአብሔር መሪነት መስቀሉን ይዘው ወሎ ሲደርሱም ጌታችን ወደ አምባሰል እያመለከተ "አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል፤ መስቀሌን በመስቀለኛ ተራራ ላይ አስቀምጥ" ይላቸው ነበር፤ ንጉሡ መስቀሉን ይዘው ወደ ቦታው ሲያመሩ መስቀለኛው የግሸን ተራራን አገኙ፤ በዚያም ቤተ ክርስቲያን አሠርተው በ፲፬፻፵፮ (1446) ዓ.ም የጌታችንን መስቀል በክብር አስቀምጠውታል፡፡

ከዚህ በኋላ ንጉሡ ‹‹መካከሏ ገነት፤ ዳሯ እሳት ይኹን! የበረረ ወፍ፣ የሠገረ ቆቅ አይታደንባት! በድንገት ሰው የገደለ፣ ቋንጃ የቈረጠ ወንጀለኛ አይያዝባት!›› ብለው ዐዋጅ ነግረዋል፡፡ የእመቤታችን ጽላትም አብሮ በግሸን ደብረ ከርቤ እንዲቀመጥ አድርገዋል፡፡ ስለዚህም መስከረም ፳፩ ቀን በየዓመቱ በቤተ ክርስቲያናችን በድምቀት ይከበራል፡፡ ኀጢአታቸውን ለካህን ተናዘው፣ ንስሐ ገብተው በዚህ ዕለት ወደ ግሸን ደብረ ከርቤ በመሔድ የሚጸልዩና የሚማጸኑ ምእመናን ኹሉ እስከ ሰባት ትውልድ ድረስ የምሕረት ቃል ኪዳን እንደሚያገኙም ጤፉት በተባለችው መጽሐፍ ተጠቅሷል፡፡

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎታቸው ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

#ስንክሳር_ዘወርኅ_መስከረም
ቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ
https://t.me/finotebirhan12
https://t.me/finotebirhan12