የጽርሐ ጽዮን ሐዋርያት ጎላ ቅዱስ ሚካኤል የፍኖተ ብርሃን ሰ/ት/ቤት (Official Channel)
2.64K subscribers
6.38K photos
67 videos
82 files
1.72K links
ይህ በጽ/ጽ/ሐ/ጎ/ቅ/ሚካኤል ቤ/ክ ፍ/ብ/ሰ/ት/ቤት እውቅና የተሰጠው የቴሌግራም ቻናል ነው።
Download Telegram
ውድ የሰ/ት/ቤታችን አባላት
ዓመታዊ የአባላት የአንድነት ጉባኤ ነገ ነሐሴ 14 ቀን 2015 ከቀኑ 8:00 ሰዓት ጀምሮ የተዘጋጀ በመሆኑ እንድንገኝ ሰ/ት/ቤታችን የአክብሮት ጥሪዋን ታስተላልፋለች።
የፊታችን ማክሰኞ በእለተ ኪዳነ ምሕረት ምሽት ከ 11:00 ጀምሮ በአውደ ምሕረት በምናከናውነው በዚህ ልዪ ጉባኤ እንዲገኙልን በእግዚአብሔር ስም ተጋብዘዋል።
🔴#ስንክሳር ነሐሴ_16

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ነሐሴ ዐሥራ ስድስት በዚህች ቀን አምላክን የወለደች #የእመቤታችን_ድንግል_ማርያም ሥጋዋ ወደ ሰማይ ያረገበት መታሰቢያዋ ሆነ፣ የሰማዕታት አለቃ #የቅዱስ_ጊዮርጊስ ሥጋው የፈለሰበት ነው፣ #ቅዱስ_ጊጋር በሰማዕትነት ሞተ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ዕርገተ_ማርያም

ነሐሴ ዐሥራ ስድስት በዚህች ቀን አምላክን የወለደች የእመቤታችን ድንግል ማርያም ሥጋዋ ወደ ሰማይ ያረገበት መታሰቢያዋ ሆነ ። ከዕረፍቷም በኋላ ከእርሳቸው ስለመለየቷ ሐዋርያት ፈጽሞ እያዘኑ ነበር ።

ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ተገለጠላቸው እርሷን በሥጋ ያዩ ዘንድ እንዳላቸውም ተስፋ ሰጣቸው ። ወንጌላዊ ዮሐንስም እስያ በሚባል አገር እያስተማረ ሳለ በነሐሴ ወር ዐሥራ ስድስተኛ ቀን ተድላ ደስታ ወደአለባት ገነት በመንፈስ ቅዱስ ተነጠቀ ።

የክብር ባለቤት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን የእመቤታችን ማርያም ሥጋዋ ካለበት ከዕፀ ሕይወት ሥር ተቀምጦ አየው። የንጽሕት እናቱንም ሥጋ ታወጣ ዘንድ ምድርን እንዲጠሩዋት ሰባቱን የመላእክት አለቆች አዘዛቸው ። እነርሱም የንጽሕት እናቱን ሥጋ ታወጪ ዘንድ እግዚአብሔር አዞሻል አሏት ። ያን ጊዜም ከዕፀ ሕይወት በታች ካለ መቃብር የእመቤታችን ማርያም ሥጋዋ ወጣ ።

የክብር ባለቤት ጌታችንም እንዲህ እያለ አረጋጋት የተወደድሽ የወለድሽኝ እናቴ ሆይ ዘላለማዊ ወደ ሆነ መንግሥተ ሰማያት አሳርግሽ ዘንድ ነዪ ። ያን ጊዜም በገነት ያሉ ዕፀዋት ሁሉም አዘነበሉ መላእክት የመላእክት አለቆች ጻድቃን ሰማዕታትም እየሰገዱላትና ፈጽሞ እያመሰገኗት አሳረጓት ።

አባቷ ዳዊትም ንግሥት እመቤታችን ወርቀ ዘቦ ለብሳ ደርባ ደራርባ በቀኝህ ትቀመጣለች እያለ በበገና አመሰገናት ። በኪሩቤል ሠረገላ ተቀምጣ ከዐረገች በኋላ በልጁዋና በፈጣሪዋ ቀኝ በታላቅ ክብር ተቀመጠች ።

ወንጌላዊ ዮሐንስም ከእርሷ በረከትን ተቀብሎ ሰግዶላት ተመልሶ ከሰማይ ወረደ ሐዋርያትን ተሰብስበው ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሥጋ ፈጽሞ ሲያዝኑና ሲተክዙ አገኛቸው ። እርሱም እንደ አየ እንደ ሰማ ሥጋዋንም በታላቅ ክብር በምስጋና እንደ አሳረጓት ነገራቸው ።

ሐዋርያትም በሰሙ ጊዜ ዮሐንስ እንዳየና እንደሰማ ባለማየታቸውና ባለመስማታቸው እጅግ አዘኑ ። ከዚህም በኋላ እያዘኑ ሳሉ እነሆ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገለጠላቸውና የፍቅር አንድነት ልጆች ሰላም ይሁንላችሁ ስለ እናቴ ማርያም ሥጋ ለምን ታዝናላችሁ ። እነሆ እኔ እርሷን በሥጋ ላሳያችሁ ልባችሁም ደስ ሊለው ይገባዋል አላቸው ይህንንም ብሎ ከእርሳትው ዘንድ ወደ ሰማያት ዐረገ ።

ሐዋርያትም ዓመት ሙሉ ቆዩ የነሐሴም ወር በባተ ቀን ለሐዋርያት ዮሐንስ እንዲህ አላቸው አምላክን የወለደች የእመቤታችንን ሥጋዋን ለማየት የተዘጋጀን አድርጎ ያሰየን ዘንድ ኑ ይህን ሁለት ሱባዔ በመጾም የክብር ባለቤት ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን እንለምነው በልጅዋ በወዳጅዋ ቀኝ ተቀምጣ አይተን በእርሷ ደስ እንዲለን ።

በዚያን ጊዜም ዮሐንስ እንዳላቸው በጾም በጸሎት ሱባዔ ያዙ የነሐሴ ወር እንደ ዛሬ ዐሥራ ስድስተኛ ቀን በሆነ ጊዜ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉንም ሐዋርያት ወደ ሰማይ አወጣቸው ። በታላቅ ክብር በተወደደ ልጅዋ ቀኝ ተቀምጣ ከሥጋዋ ተዋሕዳ ተነሥታ እመቤታችን ማርያምን አዩዋት። እጆቿንም ዘርግታ የከበሩ ሐዋርያትን እያንዳንዳቸውን ባረከቻቸው በልባቸውም እጅግ ደስ አላቸው።

የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በከበረ ሥጋውና ደሙ ላይ ሠራዒ ካህን ሆነ ። እስጢፋኖስም አዘጋጀ ዮሐንስም በመፍራት ቁሙ አለ ። ሁሉም ሐዋርያት በመሠዊያው ዙሪያ ቆሙ በዚያን ጊዜ ከቶ እንደርሱ ሆኖ የማያውቅ ታላቅ ደስታ ሆነ።

ጌታችንም የቅዳሴውን ሥርዓት በፈጸመ ጊዜ ሥጋውንና ደሙን አቀበላቸው ። ከዚያም በኪሩቤልና በሱራፌል ሠረገላ ተቀምጣ በምታርግ ጊዜ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እናቱ እመቤታችን ማርያምን እንዲህ ብሎ ተናገራት።

በዚች ቀን የሆነ የዕርገትሽን መታሰቢያ በዓለም ውስጥ እንዲሰብኩ ልጆችሽ ሐዋርያትን እዘዣቸው ። መታሰቢያሽን የሚያደርገውን ሁሉ ተጠብቆም በዚች ቀን ቅዱስ ቁርባንን የሚቀበለውን ኃጢአቱን እደመስስለታለሁ ። የእሳትን ሥቃይ ከቶ አያያትም መታሰቢያሽን ለሚያደርግ ሁሉ በዚች ቀን ለድኆች በስምሽ ለሚመጸውት ቸርነቴ ትገናኘዋለች ይህም ሥጋሽ ወደ ሰማይ ያረገበት ነው።

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ክብር ይግባውና ጌታችንን እንዲህ አለችው ልጄ ሆይ እነሆ በዐይኖቻቸው አዩ በጆሮቻቸውም ሰሙ በእጆቻቸውም ያዙ ሌሎችም ታላላቅ ደንቆች ሥራዎችን አዩ ። እመቤታችንም ይህን ስትናገር ጌታችን ሰላምታ ሰጥቷቸው በታላቅ ደስታ ወደ ደብረ ዘይት ተመለሱ ።

የተወደዳችሁ ወንድሞች ሆይ በፍጹም ደስታ መታሰቢያዋን እናደርግ ዘንድ ይገባናል እርሷ ስለእኛ ወደ ተወደደ ልጅዋ ሁልጊዜ ትማልዳለችና ።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ይማረን ። በረከቷም ከርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ከአባ ማትያስ ከሁሉም ሊቃነ ጳጳሳትና ኤጲስቆጶሳት ጋራ ሐዋርያት ከሰበሰቧት ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆች ከሁላችን ጋራ ይኑር ለዘላለሙ አሜን ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#የቅዱስ_ጊዮርጊስ_ፍልሰተ_አጽሙ

በዚህችም ዕለት የሰማዕታት አለቃ የቅዱስ ጊዮርጊስ ሥጋው ከፋርስ አገር ወደ አገሩ ልዳ በክብር የፈለሰበት ነው። የሥጋውም ፍልሰት ከእመቤታችን ድንግል ማርያም የሥጋ ፍልሰት ጋር አንድ ሆኗል ስለዚህም እርሷን መውደዱን የሚያወቁ ሥዕሉን ከሥዕሏ አጠገብ ይሥላሉ በስሙ ለሚማፀኑ የድኅነት ወደብ ይሆን ዘንድ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ጊጋር_ሰማዕት

በዚህችም ቀን የሶሪያ መስፍን ጊጋር በሰማዕትነት ሞተ። ሰማዕት የሆነበትም ምክንያት ጌታችን ከእመቤታችን ከእናቱ ከድንግል ማርያም ጋራ በተሰደደ ጊዜ በሊባኖስ ተራራ ሳለ ኄሮድስ ሰምቶ ከበው ይዘው ይገድሏቸው ዘንድ ጭፍሮቹን ላከ ጊጋርም ጭፍሮች እንዳገኟቸው አሸሻቸው።

ስለዚህም ኄሮድስ ተቆጣ ጊጋርንም ይዞ ጽኑ ሥቃይን አሠቃየው ሕዋሳቱንም ሁሉ ቆራረጠ። ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጦለት ስሙን ለሚጠራ መታሰቢያውን ለሚያደርግ ገድሉንም ለሚጽፍ ቃል ኪዳን ሰጠው ከዚህም በኋላ ራሱን በሰይፍ ቆረጡት በሦስት አክሊሎችም ተጋረደ ሦስት አክሊላትን ተቀዳጀ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በአማላጅነቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን ።https://t.me/finotebirhan12
የዩቲዩብ ቻናላችን
https://youtube.com/@finotebirhan12
ዛሬ በእለተ ኪዳነ ምሕረት ምሽት ከ 11:00 ጀምሮ በአውደ ምሕረት በምናከናውነው በዚህ ልዪ ጉባኤ እንዳይቀሩ ተጋብዘዋል።