ፈለገ ጥበብ ሚዲያ felegetbeb media
991 subscribers
8.84K photos
102 videos
110 files
1.35K links
ይህ ቻናል የደብረ ዘይት ደብረ መዊዕ ቅዱስ ሚካኤል ወ ደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል ፈለገ ጥበብ ሰንበት ት/ቤት የመረጃ ሚዲያ እና ህዝብ ግንኙነት ክፍል ሲሆን ይህ ቻናል ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የሆኑ አስተምህሮቶች በየእለቱ የሚለቀቅበት ቻናል ነው ቻናላችን ስለተቀላቀሉ በእግዚአብሔር ፅኑ ፍቅር እናመሰግናለን ።

#የፈለገ_ጥበብ_ሰንበት_ትምህርት_ቤት_የመረጃ_ሚዲያ_እና_ህዝብ_ግንኙነት_ክፍል
#FTM
Download Telegram
🌻††† እንኳን ለቅድስት ጾመ ፍልሠታ ለማርያም እና ለቅዱሳኑ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅድስት ጾመ ፍልሠታ ለማርያም †††

††† ቸር #እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ከሰጠው ጸጋ አንዱ #ጾም ነው:: የሰው ልጅ ከፈጣሪው ክብር እንዲደረግለት ክፋትን መስራት የለበትም:: መልካም መሆንም ይጠበቅበታል:: ለዚህ ምንጮቹ ደግሞ ጾም: ጸሎትና ስግደት ናቸው:: ያለ እነዚህ ምግባራት መቼም ወደ #ጽድቅ መድረስ አይቻልም::

ይቅርና እኛ ክፉዎቹ የሰማይና የምድር ፈጣሪ: የክብር ሁሉ ባለቤት ጌታችን #ኢየሱስ_ክርስቶስ ሥጋችንን በተዋሐደ ጊዜ የመጀመሪያ ሥራው ያደረገው ጾምን ነው:: ስለዚህም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን 7 አጽዋማትን በጉባዔ ሠርታ: በአዋጅ እንዲጾሙ ታደርጋለች:: ከእነዚህም አንዱ ጾመ ፍልሠታ ነው::

"ፈለሠ" - ሔደ: ተጉዋዘ እንደ ማለት ሲሆን " #ፍልሠታ" ማለት የእመቤታችን ቅድስት #ድንግል_ማርያምን የዕርገት ጉዞ የሚያዘክር ቃል ነው:: #እመ_ብርሃን በዚህ ዓለም ለ64 ዓመታት ኑራ ካረፈች በሁዋላ ሥጋዋ እንደ እኛ አልፈረሰም::

ለጊዜው በዕጸ ሕይወት ሥር ቆይታ እንደ ልጇ ትንሳኤ ተነስታ ዐርጋለች:: እርሷ በሁሉ ነገሯ ቀዳሚና መሪ ናትና:: ጾመ ፍልሠታን የጀመሩት አበው #ሐዋርያት ሲሆኑ እንድትጾምም ሥርዓት የሠሩ ራሳቸው ናቸው:: ከ7ቱ አጽዋማትም እጅግ ተወዳጅና እየተናፈቀች የምትፈጸም ናት::

ካህናትና ምዕመናንም ጾሟን እንደየአቅማቸው ክብር በሚያሰጥ መንገድ ይፈጽሟታል::
*የቻሉ ወደ ገዳማት ሔደው ጥሬ እየቆረጠሙ: ውሃ እየተጐነጩ ክብርን ያገኛሉ::
*ሌሎቹ ደግሞ ባሉበት ደብር አካባቢ እያደሩ ሌሊት ሰዓታቱን: በነግህ ኪዳኑንና ውዳሴ ማርያም ትርጉዋሜውን: በሰርክ ደግሞ ቅዳሴውን ይሳተፋሉ::
*የኔ ብጤ ደካማ ደግሞ ጠዋት ማታ ወደ ደጇ እየተመላለሰ "አደራሽን ድንግል" ይላታል::

††† በእርሷ አምነን አፍረን አናውቅምና ነጋ መሸ ሳንል እንማጸናታለን::

††† #ጽንዕት_በድንግልና: #ሥርጉት_በቅድስና #እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሳን ለምኚልን:: አእምሮውን: ልበለብዎውን: ጥበቡን በልቡናችን ሳይብን አሳድሪብን:: <3
*ጾሙን የፍሬ: የትሩፋትና የበረከት ያድርግልን::*

††† ቅዱሳን ዮሴፍና ኒቆዲሞስ †††

††† እጅግ የተወደዱ: ሞገስ የሞላላቸውና ፈጣሪያቸውን በክብር ገንዘው የቀበሩ አባቶች ናቸው::

††† ቅዱስ ዮሴፍ ዘአርማትያስ †††

††† ቅዱሱ በእሥራኤል ምድር ተወልዶ ያደገ: ኦሪትን የተማረ ባለጠጋ ሰው ነው:: የተማረ ደግ ሰው ነውና የክርስቶስን መምጣት በተስፋ ይጠብቅ ነበር:: ባገኘውም ጊዜ በአዳኝነቱ (በመሲህነቱ) አምኖ በስውር ተከታዩ ነበር::

††† ቅዱስ ኒቆዲሞስ †††

††† ወንጌል እንደሚነግረን ይህ ሰው የአይሁድ አለቃ: መምሕር: ዳኛ እና ሃብታም ሰው ነበር:: እነዚህ ሁሉ ማነቆዎች ግን እርሱን ከፈጣሪው ሊያስቀሩት አልቻሉም:: ሌሊት እየመጣ ከጌታችን እግር ይማር ዘንድም አድሎታል:: በመካከልም ከአይሁድ ጋር ብዙ ተጋጭቷል::

ሁለቱ አባቶች መድኃኒታችን ስለ እኛ ሲል ሞቶ ባለበት ሰዓት ላይ በእርሱ የደረሰ ይደርስብናል ሳይሉ በድፍረት ሥጋውን ከዺላጦስ ተካሠው ለመኑ:: እንባቸው በፊታቸው እየወረደ ከመስቀል አውርደው በዮሴፍ በፍታና በኒቆዲሞስ ሽቱ ገነዙት::

እንዲህ እያሉ:-
"ሙታንን የምታስነሳ ጌታ አንተ ሞትክን?! ደካሞችን የምታጸና ቸር አንተ ደከምክን?!"
*በዚያች ሰዓት ጐልጐታ አካባቢ ዝማሬ መላእክትን እየሰሙ የክብር ባለቤትን ቀብረውታል:: ጌታችንም ከተነሳ በሁዋላ በንጹሕ አንደበቱ ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል::

"እየሳማችሁ አክብራችሁ እንደ ገነዛችሁኝ እኔም በሰማይ በእንቁ ዙፋን ላይ አስቀምጣቹሃለሁ" ብሏቸዋል:: "አነ አብረክሙ ዲበ መንበረ ሶፎር" እንዲል:: ጻድቃን አበው ዮሴፍና ኒቆዲሞስ በተረፈ ዘመናቸው ወንጌልን ሰብከው: ከአይሁድ መከራን ታግሰው: በበጐ ሽምግልና ዐርፈዋል::

††† ቅዱስ አቦሊ ሰማዕት †††

††† ቅዱስ አቦሊ የሰማዕታቱ #ቅዱስ_ዮስጦስና #ቅድስት_ታውክልያ ልጅ ሲሆን በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን ያበራ የቤተ ክርስቲያን ዕንቁ ሰማዕት ነው:: የሚገርመኝ ሦስቱ የግማሹ ዓለም አስተዳዳሪዎች ነበሩ:: ዮስጦስ ንጉሥ: ታውክልያ ንግሥት: አቦሊ ደግሞ ልዑል ነው::

ነገር ግን ይህንን ክብራቸውን #በክርስቶስ ፍቅር ጐን: ሚዛን ላይ ቢያኖሩት በጣም ቀሎ ታያቸው:: 3ቱም ከዙፋናቸው ወርደው: ወገባቸውንም ታጥቀው: ባሮቻቸው በነበሩ ሰዎች ስለ ክርስቶስ ብዙ ተንገላቱ:: መራራ ሞትንም ታገሱ::

በተለይ ቅዱስ አቦሊ ከአንጾኪያ ወደ ግብጽ (ብስጣ) ይዘው አምጥተው ክርስትናውን እንዲተው ያላደረጉት የለም:: በቁሙ ቆዳውን ገፈው: በቆዳው አቅማዳ ሰፍተው: ያንንም አሸክመው: የተገፈፈ አካሉን ጨውና ኮምጣጤ እየቀቡ አዙረውታል::

እርሱ ግን ጌታ በላከለት ድንቅ መልአክ #ቅዱስ_ሚካኤል ረዳትነት ሁሉን ችሎታል:: በዘመኑ ብዙ ተአምራትን የሠራ ሲሆን አንድ ጊዜ ቤት ተንዶ 16 ሰዎች ቢያልቁ የተገፈፈ ቆዳውን እየጣለባቸው ተነስተዋል:: በተአምራቱና በተጋድሎውም ብዙ ሺህ አሕዛብን ለክርስትና: ብሎም ለሰማዕትነት አብቅቷል::

እርሱም ከብዙ የመከራ ጊዜያት በሁዋላ በዚህች ቀን አንገቱን ተከልሏል:: ጌታችን "ዜናሕን የጻፈውን: ያነበበውንና የሰማውን ይቅር እለዋለሁ" ብሎ ቃል ኪዳንን ሰጥቶታል::

††† ፈጣሪ ከጻድቃንና ሰማዕታት በረከትን አይለይብን:: ወርሐ ነሐሴንም ለበረከት ይቀድስልን::

††† ነሐሴ 1 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.በአተ ጾመ ፍልሠታ
2.አበው ሐዋርያት ዮሴፍና ኒቆዲሞስ
3.ቅዱስ አቦሊ ሰማዕት
4.ታላቁ ቅዱስ ዸላሞን ገዳማዊ
5.ቅድስት ሐና (የእመ ብርሃን እናት)
6.ቅድስት ሐና ነቢይት (ወለተ ፋኑኤል)
7.ደናግል ቅዱሳት (የንግስት ሶፍያ ልጆች)

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ልደታ ለማርያም ድንግል እግዝእትነ
2.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
3.ቅዱስ ራጉኤል ሊቀ መላዕክት
4.ቅዱስ በርተሎሜዎስ ሐዋርያ
5.ቅዱስ ሚልኪ ትሩፈ ምግባር

††† "የጌታ ኢየሱስ ደቀ መዝሙር የነበረ የአርማትያስ #ዮሴፍ የጌታ ኢየሱስን ሥጋ ሊወስድ ዺላጦስን ለመነ:: ዺላጦስም ፈቀደለት:: ስለዚህም መጥቶ የጌታ ኢየሱስን ሥጋ ወሰደ:: ደግሞም አስቀድሞ በሌሊት ወደ #ጌታ_ኢየሱስ መጥቶ የነበረ #ኒቆዲሞስ መቶ ንጥር የሚያህል የከርቤና የእሬት ቅልቅል ይዞ መጣ:: የጌታ ኢየሱስንም ሥጋ ወስደው እንደ አይሁድ አገናነዝ ልማድ ከሽቱ ጋር በተልባ እግር ልብስ ከፈኑት::" †††
(ዮሐ. 19:38)

††† "በጽዮን መለከትን ንፉ:: ጾምንም ቀድሱ:: ጉባዔውንም አውጁ:: ሕዝቡንም አከማቹ:: ማሕበሩንም ቀድሱ:: ሽማግሌዎችንም ሰብስቡ:: ሕጻናቱንና ጡት የሚጠቡትን አከማቹ:: ሙሽራው ከእልፍኙ: ሙሽራይቱም ከጫጉላዋ ይውጡ::" †††
(ኢዩ. 2:15)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††

https://t.me/felegetibebmedia
✞✞✞ እንኩዋን ለቅዱሳት #እናቶቻችን #አትናስያ_እና_ኢዮዸራቅስያ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

✞✞✞ #ቅድስት_አትናስያ ✞✞✞

=>የዚህች ቅድስት ሕይወት በብዛት የእግዚአብሔርን ቸርነትና የንስሃን ፍጹምነት የሚያሳይ ነው:: ጥንተ ነገሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-

+ቅድስት አትናስያ ግብፃዊት ስትሆን የነበረችውም #መኑፍ በሚባል አውራጃ በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው:: ይህ ዘመን "ዘመነ ከዋክብት" ይባል ነበር:: ከቁጥር የበዙ ቅዱሳንም በዘመኑ ነበሩ::

+ቅድስት አትናስያም ከክርስቲያን ወላጆች ተወልዳ: እንደሚገባ አድጋ: ገና በወጣትነቷ ሁለቱም ወላጆቿ ሞቱባት:: ነገር ግን ብዙ ሃብት ትተውላታልና ምን እንደምታደርገው ሃሳብ ሆናት:: #መንፈስ_ቅዱስ ግን መልካሙን ሕሊና አደላትና አብርሃማዊ ሥራን ለመሥራት ቆረጠች::

+መጀመሪያ አገልጋዮችን አዘጋጀች:: እንደየ ወገኑ ለእንግዶችና ለነዳያን ቤትን ሠራች:: በጐውን እድል መርጣለችና ለብዙ ዓመታት ለነዳያን በማድላት: እንግዶችን በመቀበል ተጠመደች:: በዚህ ሥራዋም እግዚአብሔርንም ሰውንም ደስ አሰኘች::

+ግብሯ እንዲህ ነው:: በሌሊት ጸሎት: በመዓልት ግን እንግዶችን መቀበል: እግር ማጠብ: ማስትናገድ: ማስተኛት: ስንቅ አሰንቆ መስደድ ነው:: በዚህ ግብሯ ከምንም በላይ የወቅቱን ጻድቃን አስደስታለች::

+በዚያው ልክ ግን ዲያብሎስ ተቆጥቶ ይከተላት ጀመር:: በብዙ ጐዳና አልሳካልህ ቢለውም በክፉ ጐረቤቶቿ አማካኝነት ግን ተሳካለት:: የአካባቢዋ ሰወች ወደ እርሷ ተሰብስበው በብዙ ማታለል ከቅድስና ሕይወቷ ፈቀቅ እንድትል አደረጉ::

+እነርሱ መልካም ሥራዋን ያስተዋት በመልክ ቆንጆ ነበረችና ይህንን ተጠቅመው ነው:: "ውበትና ሀብትሽን አታባክኚ" ብለው ከጐዳና አስወጧት:: መጽሐፍ ክፉ ባልንጀርነትን የሚቃወመው ለዛ ነው:: መልካም #ክርስቲያን ማለት ባልንጀራውን የሚመርጥ ነው::

+የሚገርመው ያን ያህል እንግዳ ተቀብላበት ያላለቀ ገንዘብ አሁን ግን ተመናመነ:: ክፉዎቹ ምክራቸውን ቀጠሉ:: አካሏን እንድትሸጥ አሳምነው ሴተኛ አዳሪ አደረጉዋት:: ባንዴ ከዚያ የቅድስና ከፍታ ወርዳ አካሏን ለዝሙት የምትሸጥ ሆነች::

+ነገሩን የሰሙ ገዳማውያን ሁሉ አዘኑ: አለቀሱላት:: ይልቁኑ ለእነሱ የእናት ያህል ደግ ነበረችና ከዲያብሎስ ሴራ ሊታደጉዋት ቆረጡ:: ከመካከላቸውም #ቅዱስ_ዮሐንስ_ሐጺርን ለዚህ ተግባር መረጡ:: እርሱ በአጋንንት ላይ ስልጣን ያለው ሰው ነውና::

+እነርሱ ሱባ዗ ይዘውላት አባ ዮሐንስ ሐጺር ወደ መኑፍ ከተማ ሔደ: ወደ ቤቷም ደረሰ:: ጠባቂዋን አስፈቅዶ ሲገባ ለረከሰው ድርጊት የመጣ ሰው መስሏት ተዘጋጅታ ነበር:: አባ ዮሐንስ ሐጺር ግን አጋንንትን ያርቅ ዘንድ እየዘመረ ገባ::
"እመኒ ሖርኩ ማዕከለ ጽላሎተ ሞት . . . በሞት ጥላ ሥር እንኩዋ ብሔድ አንተ ከኔ ጋር ነሕና ክፉን አልፈራም" እያለ ቀረባት:: (መዝ. 22)

+ፈጠን ብሎ ከጐኗ ተቀምጦ ቅዱሱ ምርር ብሎ አለቀሰ:: አትናስያ ደንግጣ "ምነው?" አለችው:: "የአጋንንት ሠራዊት በራስሽ ላይ ሆነው እየጨፈሩኮ ነው" አላት:: አስከትሎም አጋንንቱን በጸሎቱ ቢያርቅላት በአንዴ ወደ ልቧ ተመለሰች::

+ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ሰው የሠራችውን ሁሉ ማመን አቃታት:: ተስፋም ቆረጠች:: ቅዱስ ዮሐንስ ግን "ግዴለሽም: ንስሃ ግቢ:: ፈጣሪ ይምርሻል" ብሎ አሳመናት:: "እሺ አባቴ" ብላ ከቀደመው ዘመን ሥርዓት ያለውን አንዱን ቀሚስ ለብሳ: ጫማ ሳትጫማ: ሌላ ልብስ ሳትደርብ: ምንም ነገር ሳትይዝ ከቤት ወጣች::

+ቤቷን አልዘጋችም:: ዘወር ብላ ወደ ሁዋላም አልተመለከተችም:: ቅዱሱን ተከትላ ጉዞ ወደ በርሃ ሆነ:: ያ በእንክብካቤ የኖረ አካል እሾህና እንቅፋት: ብርድና ፀሐይ ጐበኘው:: ሲመሽ እጅግ ደክሟታልና "እረፊ" ብሏት ሊጸልይ ፈቀቅ አለ::

+መንፈቀ ሌሊት በሆነ ጊዜ #መላእክት ከሰማይ የብርሃን ዓምድ ዘርግተው አንዲትን ነፍስ በዝማሬ ሲያሳርጉ አየ:: "የማን ነፍስ ትሆን" ብሎ ወደ #አትናስያ ሲሔድ መሬት ላይ ዘንበል ብላ ዐርፋ አገኛት:: ቅዱሱም "ጌታ ሆይ! ምነው ለንስሃ እንኩዋ ብታበቃት?" ብሎ አለቀሰ::

+ፈጣሪ ከሰማይ ተናገረ:- "ገና ከቤቷ ተጸጽታ ስትወጣ ነው ይቅር ያልኩዋትና ደስ ይበላችሁ" አለው:: ይህንን የአምላክ ቃል ሁሉም ገዳማውያን ሰምተው እጅግ ደስ አላቸው:: "ጻድቅ 7 ጊዜ ይወድቃልና: 7 ጊዜ ይነሳል::"

+"+ #ቅድስት_ኢዮዸራቅስያ ድንግል +"+

=>ይህቺ ቅድስት እናት የ4ኛው መቶ ክ/ዘመን ሰው ስትሆን ወደ ምናኔው የገባችው ገና በ6 ዓመቷ ነው:: አባቷ ገና በልጅነቷ የሞተባት ኢዮዸራቅስያ ከእናቷ ጋር ለሥራ ወደ ግብፅ ገዳማት ይሔዳሉ:: በዚያ #ደናግል ጌታችንና እመቤታችንን ሲያገለግሉ ተመልክታ ተደነቀች::

+ምክንያቱን ብትጠይቃቸው ስለ ሰማያዊ ተስፋ ነገሯት:: የሰማችው ነገር ቢመስጣት እዚያው ገዳም ውስጥ መኖርን መረጠች:: እናት ሥራቸውን ሲጨርሱ "እንሂድ" ብትላትም ያቺ የ6 ዓመት ብላቴና "እኔ ከእንግዲህ የክርስቶስና የድንግል እናቱ ንብረት ነኝና የትም አልሔድም" አለቻት::

+እናት የሕጻን ልጇን ነገር ሰምታ "ልጄ! አንቺ ያልፈለግሺው ዓለም ለእኔስ ምን ይሰራልኛል?" ብላ እርሷም እንደ ልጇ ገዳሙ ውስጥ ቀረች:: ከጥቂት ዓመታት በሁዋላም እናት ታማ ዐረፈች:: ቅድስት ኢዮዸራቅስያም ንጹሕ ተጋድሎዋን ቀጠለች::

+ትዕግስት: ትሕትና: ፍቅር: ደግነትና ታዛዥነት በእርሷ ሕይወት ላይ በዝተው መገለጥ ያዙ:: እህል የምትቀምሰው በ7 ቀን አንዴ ብቻ ሆነ:: ለጸሎት ስትቆምም እስከ 40 ቀናት በተመስጦ ትቆይ ነበር:: ያቺ ብላቴና ሰይጣንን ከነ ሠራዊቱ አሳፍራዋለችና ታገላት::

+በዱላና በመጥረቢያ ሳይቀር ይመታት ነበር:: እርሷ ግን ታገሰችው:: እጅግ ብዙ ድውያንን ከመፈወስ ደርሳ ድንቅ ተአምራትን ሠራች:: በዚህች ቀንም ዐርፋ ለክብረ መንግስቱ በቃች:: ድንግል #ኢዮዸራቅስያ ለገዳሙ ሞገስ ነበረችና በዕረፍቷ ታላቅ ሐዘን ተደረገ::

=>የቅዱሳት አንስት አምላክ ከንጽሕናቸው: ትጋታቸውና ማስተዋላቸው በረከትን ይክፈለን::

=>ነሐሴ 2 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅድስት አትናስያ ቡርክት
2.ቅድስት ኢዮዸራቅስያ ድንግል
3.ቅዱስ ዴሚና ሰማዕት

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት
2.ቅዱስ ኢዮብ ጻድቅ ተአጋሲ
3.ቅዱስ አቤል ጻድቅ
4.ቅዱስ አባ ዻውሊ ገዳማዊ (ታላቁ)
5.ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ
6.አባ ሕርያቆስ ዘሃገረ ብሕንሳ
7.ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ (ከ12ቱ ሐዋርያት)

=>+"+ ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው:: ከኃጢአተኞችም ዋና እኔ ነኝ:: ስለዚህ ግን የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት በእርሱ ያምኑ ዘንድ ላላቸው ሰዎች ምሳሌ እንድሆን #ኢየሱስ_ክርስቶስ ዋና በምሆን በእኔ ላይ ትዕግስቱን ሁሉ ያሳይ ዘንድ ምሕረትን አገኘሁ:: +"+ (1ጢሞ. 1:15)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
https://t.me/felegetibebmedia
" . . . ንግግራቸው #የቤተክርስቲያንን አንድነት እና ሰላም የሚያናጋ፣ ክብረ አበውን የሚሸረሽር፤ የሚያስከትለውም መዘዝ ለሀገር ሰላም አሉታዊ ተጽእኖ የሚያመጣ ነው " - የቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት

ከሰሞኑን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት መምሪያ ሓላፊ ለመገናኛ ብዙሃን የሰጡት መግለጫ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ እየተዘዋወረ ይገኛል።

መግለጫውን ሰጥተው የነበሩት ፤ መላከ ሕይወት አባ ወልደ ኢየሱስ ሠይፈ ሲሆኑ በመግለጫው ላይ በተለይ ቅዱስ ፓትርያርኩን በተመለከተ የተናገሯቸው ንግግሮች የበርካቶች መነጋገሪያ ሆኗል።

ይህም ቅዱስ ፓትርያርኩንና ፅ/ቤታቸውን ያስቆጣ ድርጊት መሆኑን እና እርምትም እንዲወሰድ መጠየቁን ለማወቅ ተችሏል።

ይህንን ጉዳይ በተመለከተ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት ለብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የባህርዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ደብዳቤ ፅፏል።

በዚህ ደብዳቤ ላይ የEOTC ቴሌቪዥንን ጨምሮ 4 ሚዲያዎች በተገኙበት በተሰጠው መግለጫ የመምሪያ ኃላፊው ፤ ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክና ከአንዳንድ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በተያያዘ ኢቀኖናዊ የሆኑ #የድፍረት_ቃላትን ተጠቅመው ሐሰተኛ መረጃ ማሰራጨታቸው ተገልጿል።

በተጨማሪ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤትን በተመለከተ መሠረተ ቢስ የሆኑ አሉባልታዎችን ማስተላለፋቸውን በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ከተሠራጨው ድምጽና ተንቀሳቃሽ ምስል (ቪዲዮ) መመልከት እንደተቻለ የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ገልጿል።

" የመምሪያ ሓላፊው ንግግር ከእውነት የራቀ " ነው ያለው ፅ/ቤቱ ንግግራቸው የቤተክርስቲያንን አንድነት እና ሰላም የሚያናጋ፣ ክብረ አበውን የሚሸረሽር፤ የሚያስከትለውም መዘዝ #ለሀገር_ሰላም አሉታዊ ተጽእኖ የሚያመጣ መሆኑን አስገንዝቧል።

በመሆኑም ፦

- የሥራ ድርሻቸው ከሚፈቅደው ውጭ በየትኛው የሕግ አግባብ እና የሥራ ኃላፊ ፈቃድ ሊያስተላልፉ እንደቻሉ ?

- በመግለጫው ውስጥ የተካተተው ሐሳብ ቀኖናዊ ይዘት?

- ያደረጉት ንግግር ከሕግ አንጻር ያለው ምልከታ በሚገባ ተመርምሮና ቀደም ሲል በተለያዩ ጊዜያት ከሰጧቸው መግለጫዎች ጋር ተገናዝቦ አፋጣኝ የሆነ እንዲሁም ሌሎችን ሊያስተምር የሚችል እርምት ቢወሰድ የተሻለ በመሆኑ በብፁዕነታቸው አባታዊ መመሪያ እንዲሰጥበት የቅዱስ ፓትርያርኩ ፅ/ቤት ለብፁዕነታቸው በፃፈው ደብዳቤ ጠይቋል።

@tikvahethiopia
††† እንኳን ለታላቁ አባት አባ ስምዖን ዘዓምድ እና ቅድስት ሶፍያ ቡርክት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ታላቁ አባ ስምዖን ዘዓምድ †††

††† በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ስም አጠራራቸው ከከበረ አባቶች አንዱ ይህ ቅዱስ ነው:: ተወልዶ ያደገው በሶርያ (ንጽቢን) ውስጥ ሲሆን ዘመኑም 4ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው:: አባ ስምዖን ዘዓምድ የቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ የልጅነትና የተማሪ ቤት ባልንጀራ ነው::

ሁለቱንም ያስተማራቸው ደግሞ ሊቁ ቅዱስ ያዕቆብ ዘንጽቢን ነው:: ቅዱሳኑ አባ ስምዖንና ቅዱስ ኤፍሬም ለአገልግሎት ከተለያዩ በኋላ አንድ ቀን ተገናኙ::
ቅዱስ ኤፍሬም ድንግል ማርያምን
"እመቤቴ" እያለ ደጋግሞ በጉባኤ ሲያመሰግናት በመስማቱ "ወንድሜ! ይህን ምሥጢር ማን አስተማረህ?" አለው::

ቅዱስ ኤፍሬምም "ተገልጾልኝ ነው" እንዳይል ውዳሴ ከንቱን ፈርቶ "ቅዱስ ያዕቆብ ነው ያስተማረኝ" ቢለው በአባ ስምዖን ጠያቂነት ወደ መቃብሩ ሔደው ቅዱሱን ከሞት ቀስቅሰውታል:: እርሱም የእመቤታችንን ክብርና የቅዱስ ኤፍሬምን ጸጋ መስክሮ ዙሮ ዐርፏል::

በዚህ የተገረመው ቅዱስ ስምዖን ለቅዱስ ኤፍሬም ሰግዶለት: እመቤቴን ስንቅ ይዞ ወደ በርሃ ሔደ:: ተጋድሎን: ጾምና ጸሎትን በእረኝነት ሕይወት (በሰባት ዓመቱ) የጀመረው ቅዱስ ስምዖን በርሃ ከገባ በኋላ በእጅጉ አሳደገው:: ቅዱሱ በወገቡ የሚሻክር ገመድ አሥሮ: ምግብ ሳይበላ ዕለት ዕለት ያጠብቀው ነበር::

ከጊዜ በኋላ ገመዱ ሆዱን ቆርጦት ወደ ውስጥ ገብቶ ነበርና ሲራመድ በእግሩ ደም ጠብ ጠብ ሲል ይታይ ነበር:: ይሕንን መመልከት ጭንቅ የሆነባቸው መነኮሳት ለአበ ምኔቱ ተናግረው ቁስሉን አድነውና ገመዱን አውጥተው ከገዳም አባርረውታል::

እርሱ ግን ይህንን የሚያደርገው ሕማማተ ክርስቶስን ለመሳተፍ ነው:: ከገዳም ከተባረረ በኋላ ቅዱሱ በበርሃ ውስጥ ወደ ሚገኝ ዋሻ ውስጥ ገብቶ አራዊት: እባብና ጊንጥ ከበውት ይጸልይ ነበር:: እግዚአብሔር ግን በራዕይ ለገዳሙ አበ ምኔት ተገልጾ "ወዳጄን ስምዖንን ካልመለስከው አልምርህም" አለው::

በዚህ ምክንያት መነኮሳት በጭንቅ ፈልገው አግኝተው: ከእግሩ ወድቀው ይቅርታ ጠይቀውታል:: እርሱ ግን ከመነሻውም የሚቀየም ልብ አልነበረውም:: ቅዱስ ስምዖን ወደ ገዳሙ ተመልሶ ለዘመናት በተጋድሎ ጸንቶ ቀጠለ::

እግዚአብሔር ግን ቅዱሱን ከገዳሙ ወጥቶ ወደ አንዲት ምሰሶ እንዲሔድ ስላዘዘው አሥራ አምስት ሜትር ያህል ርዝመት ባለው ምሰሶ ላይ ቆመ:: ከዚህች ቀን በኋላ ነው እንግዲህ "ስምዖን ዘዓምድ (የምሰሶው አባት)" የተባለው:: ቅዱሱ ከሃምሳ ዓመታት በላይ ያለ ምንም ዕረፍት እንቅልፍ እና መቀመጥ ቆሞ
ጸልዩዋል::

ቦታዋ ለከተማ ቅርብ በመሆኗ ብዙዎችን ፈውሷል:: በእርሱ ስብከት ወደ ሃይማኖት የተመለሱ: ንስሐ የገቡ ቁጥር የላቸውም:: አንዳንዴ ክፉ ሰዎች መጥተው እርሱን በማየት ብቻ ይለወጡ ነበር:: ከቆመባቸው ዘመናት አሥራ ሁለት ዓመታት ያህልን ያሳለፈው በአንድ እግሩ ቆሞ: ሌላኛው እግር ቆስሎ ነው:: ምክንያቱ ደግሞ የሰይጣን ዱላ ነበር::

ታላቁ አባ ስምዖን ዘዓምድ ከእነዚህ የተጋድሎ ዘመናት በኋላ በዚህች ቀን ዐርፏል:: የዕረፍቱ ዜናም ከቤተ መንግስት እስከ ቤተ ክህነት ሁሉን አስደንግጧል:: እርሱ ለመንጐቹ ዕረፍት ያልነበረው ታላቅ አባት ነበርና:: ሊቃነ ጳጳሳት ገንዘውት: መኳንንት ተሸክመውት ሥጋው በክብር ዐርፏል:: ብዙ ተአምራትም ተደርገዋል::

††† ቅድስት ሶፍያ ቡርክት †††

††† ይሕች ቅድስት እናት ኢጣሊያዊት (የአሁኗ ጣልያን አካባቢ) ስትሆን የነበረችው በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻ አካባቢ ነው:: ትውልዷ የነገሥታቱ ዘር ውስጥ እንደ መቆጠሩ እጅግ የተከበረች ሴት ነበረች:: ምንም ሥጋዊ ክብሯ እንዲህ ከፍ ያለ ቢሆንም መንፈሳዊነቷ የሚደነቅ ነበር::

ከነገሥታቱ ዘር ካገባችው ባሏም ሦስት ሴቶች ልጆችን አፍርታለች:: በሃይማኖት ምክንያት መከራ ሲመጣ ስለ ልጆቿ ስትል ሃገሯን ጥላ ተሰደደች:: ስለ ክርስትናም በባዕድ ሃገር መጻተኛ ሆነች:: ያም ሆኖ ክፉዎቹ እግር በእግር ተከትለው ደረሱባት::

ቅድስት ሶፍያ ከዚህ በላይ መሸሸትን አልፈለገችም:: ከልጅነታቸው ለተባረኩ ልጆቿ ገድላተ ሰማዕታትን ታስጠናቸው ነበርና አሁን የነገር መከናወኛ ደርሷል:: ልጆቿን ቁጭ አድርጋ አዋየቻቸው::

"ልጆቼ! ክርስቶስን የወደደ ክብሩ በሰማይ እንጂ በምድር አይደለም:: ገድላቸውን ያነበባችሁትን ቅዱሳት አንስትን አስቡ" አለቻቸው:: ሦስቱ ሕፃናትም "እናታችን አትጨነቂ:: እኛ ለአምላክ ፍቅር ተገዝተናል:: ስለ ስሙም ደምን ልንከፍል ቆርጠናል:: ብቻ የእርሱ ቸርነት: ያንቺም ምርቃን አይለየን እንጂ" አሏት:: ቅድስት ሶፍያ በሰማችው ነገር እጅግ ደስ አላት::

ከዚያ ጉዞ ወደ ምስክርነት አደባባይ አደረጉ:: ቅድስቷ እናት ሦስቱንም ሕፃናት በመኮንኑ ፊት አቀረበች:: አንድ በአንድ ጠየቃቸው:: ሁሉም ግን መልሳቸው የተጠናና ተመሳሳይ ሆነበት:: "እኛ የክርስቶስ ነን" ነበር ያሉት:: መኮንኑ በቁጣ ሦስቱንም እያከታተለ አስገደላቸው::

ቅድስት እናት ሶፍያ በእንባ እየታጠበች ልጆቿን
በየተራ ቀበረች:: ስለ ሃይማኖቷ ክብሯን: ሃገሯን: ሃብቷን: መንግስቷን ሰጠች:: ከምንም በላይ ግን ልጆቿን ሰጠች:: ከዚህ በኋላ ግን በመጨረሻው ወደ ልጆቿ መቃብር ሒዳ በእንባ ለመነች::
"ልጆቼን አይ ዘንድ ናፍቄአለሁና ጌታ ሆይ! ውሰደኝ" አለች:: ከደቂቃዎች በኋላም እዚያው ላይ ዐረፈች:: የአካባቢው ሰዎች ደርሰው እርሷንም ከልጆቿ ጋር ቀበሯት::

††† መድኃኔ ዓለም ከታላቁ አባ ስምዖንና ከቅዱሳት አንስት በረከትን ያድለን:: ትዕግስታቸውንም ያሳድርብን::

††† ነሐሴ 3 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ታላቁ አባ ስምዖን ዘዓምድ
2.ቅድስት ሶፍያ ቡርክትና ደናግል ልጆቿ

††† ወርኀዊ በዓላት
1.በዓታ ለእግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ
2.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
3.ቅዱሳን ሊቃነ ካህናት አበው (ዘካርያስና ስምዖን)
4.አባ ሊባኖስ ዘመጣዕ
5.አቡነ ዜና ማርቆስ
6.አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ዘደብረ በንኮል
7.ቅዱስ ቄርሎስ ሊቅ (ዓምደ ሃይማኖት)

††† "ጻድቅ እንደ ዘንባባ ያፈራል:: እንደ ሊባኖስ ዝግባም ያድጋል::
በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ተተክለዋል:: በአምላካችንም አደባባይ ውስጥ ይበቅላሉ::
ያን ጊዜ በለመለመ ሽምግልና ያፈራሉ:: ደስተኞችም ሆነው ይኖራሉ::" †††
(መዝ. ፺፩፥፲፪)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
https://t.me/felegetibebmedia
††† እንኳን ለጻድቅ ንጉሥ ሕዝቅያስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ ሕዝቅያስ †††

††† ቅዱስ መጽሐፍ እንደ ነገረን ከመድኃኒታችን ክርስቶስ ልደት ሰባት መቶ ዓመታት በፊት ሕዝቅያስ የሚባል ንጉሥ በይሁዳ ላይ ነግሦ ነበር:: ደጋጉ ዳዊትና ሰሎሞን ካረፉ በኋላ የሕዝቅያስን ያክል ቅን እና የእግዚአብሔር ሰው በእሥራኤል ላይ አልነገሰም:: ንጉሡ ጣዖት አምልኮን ነቃቅሎ አጥፍቶ ሕዝቡ እግዚአብሔርን ብቻ እንዲያመልክ አድርጐም ነበር::

ነገር ግን ቅዱስ ሕዝቅያስ በነገሠ በ14ኛው ዓመት የአሕዛብ (የአሦር) ንጉሥ ሰናክሬም በጠላትነት ተነሳበት:: ወደ አካባቢውም መጥቶ: ከቦ አስጨነቀው:: ሰናክሬም በጦር እጅግ ኃይለኛ ነበር:: በዚያውም ላይ ጦር የሚመዙ ከመቶ ሰማንያ አምስት ሺ በላይ ብርቱ ተዋጊዎች ነበሩትና ሕዝቅያስ እንደማይችለው ተረድቶ መልእክተኛ ላከበት::

"እገብርልሃለሁ: የፈለግከውንም እሰጥሃለሁ:: ነገር ግን ሃገሬን አታጥፋ:: ኢየሩሳሌምን አታቃጥል: ሕዝቤንም አትግደል" በሚል ለመነው:: እጅ መንሻ ግብሩንም ከከተማዋ የተገኘውን ወርቅና ብር ሁሉ ጭኖ ላከለት::

ሰናክሬም ግን ሰይጣን ያደረበት ነውና የሕዝቅያስን ልመና ወደ ጐን ብሎ የእሥራኤልን አምላክ: ቅዱስ ስሙንም ተገዳደረ:: ለሕዝቅያስም "ከእኔ እጅ የሚያድንህ ማነው? ሕዝቡንም እግዚአብሔር ያድናል ብለህ አታታልላቸው" ሲል ላከበት:: ቅዱስ ሕዝቅያስ በዚህ ጊዜ የፈጣሪው ስም ሲቃለል ሰምቷልና ፈጽሞ አዘነ::

መልእክተኞችን ወደ ነቢዩ ቅዱስ ኢሳይያስ ልኮ እርሱ ወደ ቤተ መቅደስ ገባ:: በእግዚአብሔር ፊት ልብሱን ቀድዶ ማቅ ለበሰ:: ስለ ኢየሩሳሌምና ሕዝቡም ፈጽሞ አለቀሰ::

በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር የሰናክሬምን መገዳደርና የሕዝቅያስን ልመና ሰምቷልና በኢሳይያስ አንደበት እንዲሕ አለ:- "ስለ ባሪያዬ ስለ ዳዊት ከተማዋን አድናታለሁ::"

በዚያች ሌሊትም ድንቅ መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ከሰማያት በግርማ ወረደ:: ወደ ሰናክሬም የጦር ሠፈር ደርሶ አንድ ጊዜ የእሳት ሰይፉን መዝዞ ቢያሳያቸው ከአሕዛብ ሠራዊት መቶ ሰማንያ አምስት ሺ ኃያላን እንደ ቅጠል ረገፉ:: በለኪሶ የነበረው ሰናክሬም በጧት ቢነሳ ሠራዊቱ ሁሉ ወደ አስከሬን ክምር ተቀይሯል::

በድንጋጤ ወደ ነነዌ ሒዶ ወደ ጣዖት ቤቱ ሲገባ የራሱ ልጆች (አድራማሌክና ሳራሳር) ገደሉት:: ትዕቢተኛው ሰናክሬም ለአሕዛብ ሁሉ መዘባበቻ ሆነ:: ቅዱስ ሕዝቅያስ ግን በፈጣሪው ታምኗልና ቅዱስ ሚካኤል ሞገስ ሆኖት የዓለም ነገሥታት ሁሉ ፈሩት:: (1ነገ. 18:13, 19:1)

ቅዱስ ሕዝቅያስ የነሐስ እባቡን በማጥፋቱ: ሕዝቡን ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር በመመለሱ ቢደነቅም ሰው ነውና አንዲት ጥፋት አጠፋ:: በዘመኑ ታላቁ ነቢይ ልዑለ ቃል ኢሳይያስ ነበረና ሐረገ ትንቢትን ያፈስ ነበር:: ከተናገራቸው ትንቢቶችም አንዱ "ድንግል ትጸንሳለች: ወንድ ልጅም ትወልዳለች" የሚል ነበር:: (ኢሳ. 7:14)

በወቅቱ የነበሩ አንዳንድ ክፉ መካሪዎች ቀርበው ንጉሡን በውዳሴ ከንቱ ጠለፉት:: "ንጉሥ ሆይ! ሺህ ዓመት ንገሥ:: እንዳንተ ያለ ማንም የለም:: ነቢዩ የተናገረው ትንቢትም እኮ ላንተ ነው:: "ድንግል" የተባለች ኢየሩሳሌም ስትሆን "ወልድ-ወንድ ልጅ" የተባልክ ደግሞ አንተ ነህ" አሉት::

ይሕንን ጠማማ ትርጉም እህ ብሎ የሰማቸው ቅዱስ ሕዝቅያስ አልወቀሳቸውም:: ይልቁኑ ልቡ ወደ እነሱ አዘነበለ እንጂ:: በዚህ ምክንያት እግዚአብሔር ተቆጥቶ ኢሳይያስን ላከው::
ነቢዩም በቀጥታ መጥቶ ንጉሡን አለው:- "ትሞታለህ እንጂ አትተርፍምና ቤትህን ሥራ::"

ወዲያውኑ ሕዝቅያስ ታመመ: ደከመ:: ነገር ግን ፊቱን ወደ ቤተ መቅደስ አዙሮ ሊያዝን: ሊተክዝም ጀመረ:: አባቶቻችን ለየት የሚያደርጋቸው ይኼ ነው:: በቅድስና ኑረው: ሰው ናቸውና ይሳሳታሉ:: ነገር ግን ንጹሕና ፍጹም ንስሐን ከማቅረብ አያቋርጡም::

ንጉሡ ቅዱስ ሕዝቅያስ ወደ ፈጣሪ:- "ጌታ ሆይ! እንደ ቸርነትህ በፊትህ በቅን መንገድ መሔዴን አስብና ይቅር በለኝ" ሲል ተማጸነ:: ይህ ሲሆን ቅዱስ ኢሳይያስ ገና ከንጉሡ አካባቢ አልራቀም ነበርና የእግዚአብሔር ቃል ወደ እርሱ መጣ::

ሕዝቅያስን በለው:- "ጸሎትህን ሰምቼ: ስለ ባለሟሌ ስለ ዳዊት ብዬ ምሬሐለሁ:: በዘመንህም ላይ አሥራ አምስት ዓመታትን ጨምሬልሃለሁ በለው" አለው:: ነቢዩም ወደ ንጉሡ ተመልሶ ይሕንኑ ነግሮ "እስከ ሦስት ቀን ድረስ ወደ ቤተ መቅደስ ድነህ ትመለሳለህ" አለው::

ቅዱስ ሕዝቅያስ "ይሕ እንደሚደረግ በምን አውቃለሁ?" አለው:: (ተጠራጥሮ ግን አይደለም: ድንቅ ተአምር ይገለጥ ዘንድ ነው እንጂ) ኢሳይያስም ፀሐይን ዓለም እያየ አሥር መዓርጋትን ወደ ኋላ መለሳት:: በወቅቱ ይህ ተአምር በመላው ዓለም ታይቶ: ተሰምቶም ነበርና ሕዝቅያስ ከፍ ከፍ አለ::

በቅን የሔደ: እግዚአብሔርም የወደደው እንዲህ ነው:: የዓለም ነገሥታት ሁሉ ለሕዝቅያስ አዘነበሉ: ገበሩለትም:: ለእርሱ ጌታ ድንቅ ነገርን አድርጐለታልና::

ቅዱስ ሕዝቅያስ በተጨመሩለት ዘመናት ሁሉ እግዚአብሔርን አመለከ:: በፊቱም በቅን ተጓዘ:: ከክርስቶስ የዘር ሐረግም በቀጥታ ተቆጠረ:: (ማቴ.1:10) ለአሥራ አምስት ዓመታት ሕዝቡን አስተዳድሮ በዚህች ቀን እድሜ ጠግቦ ዐርፏል:: በእርሱ ዙፋን ላይም ልጁ ምናሴ ተተክቷል::

††† አባ ማቴዎስ ገዳማዊ †††

††† እኒህ ቅዱስ ሰው በ4ኛው መቶ ክ/ዘ ፋርስ አካባቢ የነበሩ ጻድቅ ናቸው:: በወቅቱ ምንኩስና በአካባቢው ባለመስፋፋቱ ወደ ዱር እየወጡ የሚኖሩ አበው ነበሩና አባ ማቴዎስ አንዱ ናቸው:: እርሳቸው በበርሃ ልብሳቸው አልቆ አካላቸው የሚሸፈነው በጸጉራቸው ነበር::

የአቶር ንጉሥ የሰናክሬም ልጅ መርምሕናምን(እጅግ ታላቅ ሰማዕት ነው) ያሳመኑትና ያጠመቁት እርሳቸው ናቸው:: እኅቱን ሣራንም ከለምጿ አንጽተው ወደ ክርስትና መልሰዋል:: በዚህ ምክንያትም የፋርስ አውራጃ የሆነችው አቶር በሙሉ የክርስቲያኖች ቤት ሆናለች:: አባ ማቴዎስ ከዘመናት ተጋድሎ በኋላ በዚህች ቀን ዐርፈዋል::

††† አምላከ ቅዱሳን እድሜ ለንስሐ: ዘመን ለፍስሃ አይንሳን:: የጻድቃኑ በረከትም ይደርብን::

††† ነሐሴ 4 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ሕዝቅያስ ጻድቅ (ንጉሠ ይሁዳ)
2.አባ ማቴዎስ ገዳማዊ
3.ቅዱስ ዳዊት ሰማዕት

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ (ወንጌላዊው)
2.ቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያ
3.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
4.ቅዱስ ዮሐንስ ዘሐራቅሊ (ሰማዕት)

††† "አቤቱ በኃይልህ ንጉሥ ደስ ይለዋል::
በማዳንህ እጅግ ሐሴትን ያደርጋል::
የልቡን ፈቃድ ሰጠኸው:: የከንፈሩንም ልመና አልከለከልኸውም::
በበጐ በረከት ደርሰህለታልና::
ከከበረ ዕንቁ የሆነ ዘውድን በራሱ ላይ አኖርህ::
ሕይወትን ለመነህ ሰጠኸውም:: ለረጅም ዘመን ለዘላለሙ::
በማዳንህ ክብሩ ታላቅ ነው::" †††
(መዝ. ፳፥፩-፭)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
https://t.me/felegetibebmedia
††† እንኩዋን ለጻድቃን ቅዱሳን #አባ_አብርሃም: #ቅዱስ_ዮሐንስ እና #አባ_ፊልዾስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ †††

††† #አባ_አብርሃም_ክቡር ገዳማዊ †††

=>ጻድቁ ግብጻዊ ሲሆን በ4ኛው መቶ ክ/ዘ ከተነሱ ከዋክብት አንዱ ነው:: #ክርስቲያን ወላጆቹ በሥርዓት አሳድገው "ሚስት አግባ" አሉት:: እሺ እንዳይላቸው ከልጅነቱ ጀምሮ የተመኘው ምናኔ ሊቀርበት ሆነ:: እንቢ እንዳይላቸው ደግሞ ወላጆቹ ያዝናሉና የልቡን በልቡ ይዞ "እሺ" አላቸው::

+ሠርግ ተደግሶ: #ተክሊል ተደርሶ: ከአንዲት ክርስቲያን ጋር አጋቡት:: በጋብቻው ማግስት ግን ከነ ድንግልናው ጠፍቶ በርሃ ገባ:: በዚያም አንዲት በዓት አዘጋጅቶ ፈቃደ ሥጋውን እየቀጣ: ፈቃደ ነፍሱን እያለመለመ ለ10 ዓመታት ተቀመጠ::

+በነዚያ ሁሉ ዘመናት የሞቀ አልለበሰም: የላመ የጣመ ነገር አልበላም:: የፀሐይ ብርሃን እንኩዋ አልተመለከተም:: በዚያ ወራትም ወሬ ነጋሪ ወደ በዓቱ መጥቶ "ወላጆችህ ዐረፉ:: በቤት ውስጥ ከ6 ዓመት እህትህ ከማርያ በቀር ማንም የለምና የወላጆችህን ሃብት ውረስ" አለው::

+አባ አብርሃም የሚያደርገውን ያውቃልና ከበርሃ ወጥቶ ወደ ሃገር ቤት ሔደ:: ትንሽ እህቱን (6 ዓመቷ ነበር) ለቤተ ዘመድ አደራ ሰጥቶ: ሃብት ንብረቱን አንድ ሳያስቀር ለነዳያን በትኖ:ወደ በዓቱ ተመለሰ:: በዚያም እንዳስለመደ በጾምና ጸሎት ተወስኖ ለ10 ዓመታት ቆየ::

+ተጋድሎ በጀመረ በ20 ዓመቱ #እግዚአብሔር ለሌላ አገልግሎት ጠራው:: የግብጽ ሊቀ ዻዻስ #አባ_አብርሃምን አስመጥቶ ቅስናን ሾመውና "ሒደህ ወንጌልን ስበክ" አለው:: ችግሩ እርሱ የተላከባት ሃገር አንድም ክርስቲያን የሌለባት ከመሆኗ በባሰ እጅግ ጨካኝ ናቸው::

+ማንም ደፍሮ በዚያ ሃገር ውስጥ ነገረ እግዚአብሔርን የሚናገር ሰው አልነበረም:: አባ #አብርሃም ወደ ሃገር ገብቶ ወንጌልን ቢሰብክላቸው እንደ ልማዳቸው መሬት ላይ ጥለው ደበደቡት: አጥንቶቹንም ሰባበሩት:: ሞቷል ብለው ከከተማ ውጪም ጣሉት::

+እርሱ ግን በፈጣሪው ኃይል ጸንቶ ተነሳ:: ማስተማሩ ብቻውን መፍትሔ እንደማይሆን ተረድቷልና ስለ እነሱ ተግቶ ይጸልይ ጀመር:: አሕዛብ ጠዋት ቢመጡ በከተማዋ መሐል ላይ ሲጸልይ አገኙት:: ስለ ተናደዱ ድጋሚ አካሉን በዱላ ሰባብረው እየጐተቱ ከከተማ አስወጡት:: በዚያም ከነ ሕይወቱ ቀበሩት::

+ነገር ግን ጠዋት ሲመለሱ እዛችው ቦታ ላይ ሲጸልይ አገኙት:: ይሕ የሚደረገው ለእነርሱ ድኅነት መሆኑን አልተረዱምና እነርሱ በየቀኑ እየደበደቡና እያሰቃዩት እርሱ ስለ እነሱ እየጸለየ 10 ዓመታት አለፉ:: ቅዱሳን ተስፋ አይቆርጡምና በመጨረሻው ተሳካለት::

+የቅዱሱ የዘመናት ጸሎት ፍሬ አፍርቶ እግዚአብሔር በአሕዛብ ልቡና ያደሩ አጋንንትን አራቀለት:: አንድ ቀን ጠዋት የሃገሩ ሕዝብ ሁሉ (ወንዱ: ሴቱ: ትልቁ: ትንሹ) ወደ ጻድቁ መጸለያ መጡ:: ለእርሱስ የጠብ መስሎት ነበር:: እነርሱ ግን በአንድነት በፊቱ ተንበርክከው ሰገዱ:: ይቅር እንዲላቸውም ለመኑት::

+ቅዱሱ ይሕንን ሲመለከት ሐሴትን አደረገ:: ሁሉንም #በስመ_ሥላሴ አጥምቆ ክርስቲያን አደረጋቸው:: አብያተ ክርስቲያናትንም አነጸላቸው:: በሁዋላ ግን በጣም ሲወዱትና ሲያከብሩት ተመልክቷልና ከውዳሴ ከንቱ (#ስብሐት_ብጡል) መለየት ፈለገ:: ፈጣሪንም በቸርነቱ እንዲጠብቃቸው ለምኖ: በሌሊት ጠፍቶ ወደ ነበረበት በርሃ ገባ::

+እርሱ በበርሃ ሁኖ ስለ ትንሽ እህቱ #ማርያ ያስብ ነበርና አስጠራት:: "ምን ትፈልጊያለሽ?" አላት:: እርሷም "እንዳንተ መሆን" ስላለችው አስተምሮ: ፈትኖ አመነኮሳት:: ለጥቂት ዓመታት በሥርዓት ከኖረች በሁዋላ ግን ችግር ተፈጠረ::

+ከአንድ መነኩሴ ጋር በነበራት ያልተገባ ቅርርብ የዝሙት ፍላጐታቸውን መቆጣጠር ባለመቻላቸው በኃጢአት ወደቁ:: በዚህ ተስፋ ቆርጠው 2ቱም ቆባቸውን ጥለው ከተማ ገቡ:: ይልቁኑ እርሷ (ማርያ) ሴተኛ አዳሪ ሆነች::

+በዚያ ሰሞን ቅዱሱ አብርሃም ራዕይን ያያል:: ትልቅ ዘንዶ አንዲት ርግብን ሲውጣት: መልሶም ሲተፋት አይቶ እሕቱ መሆኗን ተረዳ:: ወዲያው ጥሩ ልብስና ፈረስ ተውሶ ተነሳና ወደ ከተማ ገባ:: የጦር መኮንን መስሎ እህቱ ቤት ገባ::

+ሸሽታ እንዳታመልጠው ቤቱን ዘጋና ራሱን ገለጠላት:: ደንግጣ እንደ በድን ብትሆንም እርሱ አረጋጋት:: "እህቴ! ንስሃ ግቢ: አምላክ ይራራልሻል" አላት:: ልቧ ወደ ምክሩ አዘንብሏልና የእህቱን ነፍስ ማርኮ ወደ ገዳም ተመለሰ::

+በዚያ በዓት ሠርቶላት: ቀኖናም ሰጥቷት ሔደ:: #ማርያም ስለ ኃጢአቷ ፈንታ የምትገርም የቅድስና ሰው ሆነች:: ያየ ሁሉ እየተደነቀባት ከዓመታት ተጋድሎ በሁዋላ ዐረፈች:: አባ አብርሃም በተረፈ ዘመኑ በንጹሕ ገዳማዊ ሕይወት ተጠምዶ ኑሯል::

+በዘመኑ ሁሉ በጥርሱ ስቆ: በከንፈሩም አልባሌ ነገርን ተናግሮ አያውቅም:: ልቡ በፈጣሪው ፍቅር የታሠረ ነበርና ሕማማተ ክርስቶስን እያሰበ እንባው ያለማቁዋረጥ ይፈስ ነበር:: ደግና ቅዱስ ሰው አብርሃም በዚህች ቀን ዐርፎ ተቀብሯል::

††† #ቅዱስ_ዮሐንስ_ጻድቅ †††

=>ይህ ቅዱስ የነበረው በዘመነ ሰማዕታት ቢሆንም እንደ ሰማዕታት ስቃይ አልደረሰበትም:: ክርስቲያኖችን እንዲገድሉና አብያተ ክርስቲያናትን እንዲያቃጥሉ ከተመደቡ ወታደሮች አንዱ ነበረ:: ታዲያ እንዲገድላቸው የሚሰጡትን ክርስቲያኖች እየወሰደ ይደብቃቸው ነበር::

+የመከራው ዘመን እስኪያልፍ ድረስም ይንከባከባቸው ነበር:: ሌሎች ወታደሮች እንዳይነቁበት ሁሌም "ክርስቲያኖችን በጣም እጠላለሁ" እያለ ያወራ ነበር:: እርሱ በሌሊት ሁሌም ለጸሎት ይተጋ ነበር:: በእንዲህ ያለ ግብር ኑሮም በዚህች ቀን በሰላም ዐርፏል::

††† #አባ_ፊልዾስ #ዘደብረ_ቢዘን †††

=>#ደብረ_ቢዘን በቀድሞ የኢትዮዽያ ክፍለ ሃገር (አሁን #ኤርትራ) ውስጥ የሚገኝ ታላቅ ገዳም ነው:: ገዳሙ #እመቤታችን_ድንግል_ማርያም በስደቷ ያረፈችበት: ጌታችን የባረከውና የመረጠው ቦታ ነው:: #አባ_ዮሐንስን: #አባ_ናርዶስንና ሌሎች ከዋክብት አበውን ያፈራ ሲሆን የአባ ፊልዾስን ያሕል ግን አልተገኘም::

+ጻድቁ በግል የተጋድሎ ሕይወታቸው: ገዳሙን በአበ ምኔትነት በመምራታቸውና በስብከተ ወንጌል አገልግሎታቸው ምስጉን ነበሩ:: እርሳቸው ቅዱስ ሆነው አልበቃቸውምና ብዙ ቅዱሳንን ወልደዋል:: ይሕች ዕለትም የዕረፍታቸው መታሰቢያ ናት::

=>አምላከ ጻድቃን ገዳማትን ከመከራ ይጠብቅልን:: ከአባቶቻችን ቅዱሳን ጸጋ በረከትንም ይክፈለን::

=>ነሐሴ 5 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ አባ አብርሃም ገዳማዊ
2.ቅድስት ማርያ እህቱ
3.ቅዱስ ዮሐንስ ጻድቅ
4.አባ ፊልዾስ ዘደብረ ቢዘን

=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ዼጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት
2.ቅዱስ ዻውሎስ ብርሃነ ዓለም
3.አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ
4.ቅዱስ ዮሐኒ ኢትዮዽያዊ
5.ቅዱስ አሞኒ ዘናሒሶ
6.ቅድስት አውጋንያ (ሰማዕትና ጻድቅ)

=>+"+ በድካም: አብዝቼ በመገረፍ: አብዝቼ በመታሠር: አትርፌ በመሞት ብዙ ጊዜ ሆንሁ:: በድካምና በጥረት: ብዙ ጊዜም እንቅልፍ በማጣት: በራብና በጥም: ብዙ ጊዜም በመጦም: በብርድና በራቁትነት ነበርሁ. . . የቀረውን ነገር ሳልቆጥር ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው:: +"+ (2ቆሮ 11:23)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
https://t.me/felegetibebmedia
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

✞✞✞ እንኩዋን ለቅድስት #እናታችን_ማርያም_መግደላዊት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

✞✞✞ #ቅድስት_ማርያም #መግደላዊት ✞✞✞

=>ይህችን ቅድስት "ማርያም" ያሏት ወላጆቿ ሲሆኑ "መግደላዊት" እያሉ የጠሯት ደግሞ ሐዋርያት (ወንጌላውያን) ናቸው:: ለምን እንዲህ ብለው ጠሯት ቢሉ:- በዘመኑ "ማርያም" የሚባሉ ብዙ ሴቶች ነበሩና ከእነሱ ለመለየት ነው:: አንድም ሃገሯ ከእሥራኤል አውራጃዎች በአንዱ (በመግደሎን) ተወልዳ ያደገች ናትና::

+ማርያም መግደላዊት ይህ ቀረሽ የማይሏት ቆንጆ ነበረችና ሰዎች ያደንቁዋት: ወንዶች ይከተሏት ነበር:: በዚህም 7 አጋንንት ተጠግተው 7 ዓይነት ኃጢአትን ያሠሯት ነበር:: በተለይ ደግሞ በዝሙት: በትውዝፍት (ምንዝር ጌጥ) እና ትዕቢት በእጅጉ የታወቀች ነበረች::

+በእንዲህ ያለ ግብር ጸንታ ለዘመናት ኖረች:: በዚያ ወራት የክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ሥጋችንን ተዋሕዶ ያስተምር ነበርና ስለ እርሱ ሰማች:: "ጌታ ኃጥአንን አይጸየፍም (ይቀበላል): አጋንንትንም ያስወጣል" ብለውም ነገሯት:: ጥሪው የእግዚአብሔር ነውና ማርያም መግደላዊት አልዘገየችም::

+ወደ እርሱ ሔዳ ጌታ ባያት ጊዜ ኩላሊትን የሚመረምር አምላክ ነውና አቀረባት:: በቸርነቱም ከራስ ጸጉሯ እስከ እግር ጥፍሯ የሞሉትን 7 የአጋንንት ነገድ አስወጣላት:: በዚያች ሰዓት ዕለቱኑ እንደተወለደ ሕጻን ከነበረባት ችግር ሁሉ ንጹሕ ሆነች:: ጌታም ከ36ቱ ቅዱሳት አንስት አንዷ ትሆን ዘንድ መርጦ ተከታዩ አደረጋት::

+ቅድስት ማርያም ከዚህች ቀን ጀምሮ ፍጹም ተቀየረች:: እርምጃዋ ሁሉ የተባረከና የንጽሕና ሆነ:: ጌታን እስከ ዕለተ ሕማሙ ድረስ በመዓልትም: በሌሊትም በቅን አገለገለችው::

ጌታችን ስለ እኛ መከራን በተቀበለባት በዚያች ዕለተ ዐርብም ከጠዋት ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ ከጐኑ ነበረች::

+ከግርፋቱ እስከ ስቅላቱ እያለቀሰች ተከትላዋለች:: በእግረ #መስቀሉ ያለቅሱ ከነበሩ ቅዱሳት አንስትም አንዷ እርሷ ነበረች:: (ዮሐ. 19:25) ቅዱሳኑ #ዮሴፍና #ኒቆዲሞስ ጌታን ሲቀብሩትም ከእሕቶቿ ጋር አብራ ተከትላ አይታለች::

+እሑድ በሌሊት: ገናም ሳይነጋ መቃብሩን ታይ ዘንድ: ሽቱም ልትቀባ ወደ ጐልጐታ ገሠገሠች:: ፍጹም የአምላክ ፍቅር አድሮባታልና ግርማ ሌሊቱንና የአይሁድ ጭፍሮችን አልፈራችም:: ጌታችንም #ክእመቤታችን ቀጥሎ ከፍጥረት ወገን ትንሳኤውን ያየች የመጀመሪያዋ ሰው ትሆን ዘንድ አደላት::

+በመቃብሩ ራስጌና ግርጌም 2 መላእክትን (#ሚካኤልና_ገብርኤልን) ተመለከተች:: ዘወር ስትል ደግሞ የክብርን ባለቤት አየችው:: አላወቀችውምና "ማርያም" አላት:: "ረቡኒ-ቸር መምሕር ሆይ" ብላ ሰገደችለት::

+ጌታም "ሑሪ ኀበ አኀውየ ወበሊዮሙ . . . ሒደሽ ለደቀ መዛሙርቴ በያቸው . . . " ብሎ የትንሳኤው ሰባኪ አደረጋት:: "ወሖረት ወነገረቶሙ ለአርዳኢሁ . . . " እንዲል ትንሳኤውን ለደጋጉ #ሐዋርያት ሰበከችላቸው::

+#ቅድስት_ማርያም መግደላዊት ከክርስቶስ ትንሳኤ በሁዋላ ለ40 ቀን #መጽሐፈ_ኪዳንን: #ትምሕርተ_ኅቡዓትን ተምራለች:: በዕርገቱ ተባርካ: በበዓለ ሃምሳ ከቅዱስ መንፈሱ ጸጋ ተካፍላለች:: በአዲሲቷ #ቤተ_ክርስቲያን ውስጥም ልዩ አገልግሎት ነበራት::

+ቅዱሱ #እስጢፋኖስ 8 ሺውን ማሕበር ሲመራ ሴቶችን ታስተዳድርለት ነበር:: ከሁሉ በላይ ግን ቅድስቲቱ የቅዱሳን ሐዋርያት መጋቢ ነበረች:: በዘመኑ #መንፈስ_ቅዱስ የሚባርከውን #አጋፔ (የፍቅር ማዕድ) የምታዘጋጀው እርሷ ነበረች::

+እንዲያውም አንዴ የሚበላ ጠፍቶ ለሐዋርያት ማዕድ ፍለጋ በሔደችበት እግሯ ቆስሎና ደምቶ መመለሷ ይነገራል:: እንዲህ አድርጋ ያዘጋጀችውን ማዕድ #ቅዱስ_መልአክ ወርዶ ወደ ሰማይ ወስዶታል:: ለቅዱሳን ሐዋርያትም እያመጣ ይመግባቸው ነበር::

+እናታችን #ማርያም_መግደላዊት በስብከተ ወንጌልም የተመሰከረላት ነበረች:: የመጀመሪያዋ የሐዲስ ኪዳን #ዲያቆናዊት ሴት ስትሆን ክርስትናንም ተዟዙራ ሰብካለች:: ስለ ቅዱስ ስሙም ሽሙጥን: ስድብን: መንገላታትን እና ግርፋትን ታግሳለች::

+በተለይ አይሁድ ብዙ አሰቃይተዋታል:: ቅድስቷ እናታችን መልካሙን ገድል ተጋድላ በበጐ እድሜ በዚህች ቀን ሔዳለች:: በዓለም የሚገኙ ክርስቲያኖች ሁሉ (ከአንዳንዶቹ በቀር) ያከብሯታል::

+"+ #ቅድስት_ኢየሉጣ_ዘቂሣርያ +"+

=>በቀድሞው የግሪክ ግዛት (ቂሣርያ ውስጥ) በዘመነ ሰማዕታት አካባቢ የነበረችው #ቅድስት_ኢየሉጣ ክርስትናን የወረሰችው ከወላጆቿ ነው:: ገና ወጣት እያለች ወላጆቿ በማረፋቸው የሃብታቸው ወራሽ ሆነች::

+ነገር ግን አንድ ክፉ ሰው መጥቶ ሃብቷን ነጠቃት:: በዚህ አዝና "የዳኛ ያለህ" ልትል ወደ ፍርድ ቤት ስትሔድ የጠበቃት ግን የሚገርም ነበር:: የተገፋችው እርሷ ተከሳሽ: ገፊው ደግሞ ከሳሽ ነበር:: የክሱ ጭብጥ ደግሞ "ክርስቲያን ነሽ" የሚል ነበር::

+በወቅቱ በመኯንንቱ ፊት ክርስትናዋን ብትክድ በቀጥታ ሃብቷን ማግኘት ትችል ነበር:: እርሷ ግን ለአፍታ አሰበች:: "እንዴት ዘላለማዊ ሃብቴን (ሃይማኖቴን) በኃላፊው ንብረት እለውጣለሁ" ብላ ሁሉም እየሰሙ ጮክ ብላ "#ክርስቲያን_ነኝ" አለች::

+ወዲያውም ሞት ተፈርዶባት ተገደለች:: ታላቁ #ቅዱስ_ባስልዮስ ስለ #ሰማዕታት በጻፈው ድርሳን ላይ በስፋት አመስግኗታል:: ለሴቶችም ታላቅ ምሳሌ ናት ብሏታል::

=>ቅዱሳት እናቶቻችንን ያጸና ቸር አምላካቸው እኛንም በሃይማኖትና በምግባር ያጽናን:: ከበረከታቸውም አብዝቶ ያድለን::

=>ነሐሴ 6 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅድስት ማርያም መግደላዊት (ከ36ቱ ቅዱሳት አንስት)
2.ቅድስት ኢየሉጣ ሰማዕት (ዘቂሣርያ)
3.አባ ዊጻ (የታላቁ ሲኖዳ ደቀ መዝሙር)

=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅድስት ደብረ ቁስቁዋም
2.አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን
3.አባታችን ኖኅና እናታችን ሐይከል
4.ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ
5.ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ
6.ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ
7.ቅድስት ሰሎሜ
8.አባ አርከ ሥሉስ
9.አባ ጽጌ ድንግል
10.ቅድስት አርሴማ ድንግል

=>+"+ #ጌታ ኢየሱስም:- "#ማርያም" አላት:: እርሷ ዘወር ብላ በእብራይስጥ:- "#ረቡኒ" አለችው:: ትርጉዋሜውም "መምሕር ሆይ!" ማለት ነው:: ጌታ ኢየሱስም:- "ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና አትንኪኝ:: ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ ሔደሽ . . . ዐርጋለሁ ብለሽ ንገሪያቸው" አላት:: #መግደላዊት_ማርያም መጥታ ጌታን እንዳየች ይሕንም እንዳላት ለደቀ መዛሙርቱ ነገረች:: +"+ (ዮሐ. 20:16)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

https://t.me/felegetibebmedia
በቢሾፍቱ ጋራ ብሩ ደብረ ፀሐይ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ለምዕመናን አመች ይሆን ዘንድ የመንገድ የኮብል እስቶን ንጣፍ እየተሠራ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡
----------------------------------------
ነሐሴ 2/2015 ዓ.ም ሐተሚ ( አዳማ- ኢትዮጵያ)

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት በአድኣ ወረዳ ቤተክህነት የቢሾፍቱ ጋራ ብሩ ደብረ ፀሐይ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ለምዕመናን አመች ይሆን ዘንድ የእግረኛ ረዥም የኮብልእስቶን ንጣፍ እየተካሄደ መሆኑ ተገለጸ፡፡

በደብረ ፀሐይ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ደብር ከዚህ ቀደም በቦታው ላይ ይስተዋሉ የነበሩ ቅራኔዎችን በመልአከ ሰላም አባ ዮሴፍ ሂርጶ የደብሩ አስተዳዳሪ መሪነት በውይይትና በንግግር በማጥፋት የደብሩ ሰበካ ጉባኤ ፡ ማኅበረ ካህናት፡ የጽ/ቤት ሠራተኞች ፡ የሰንበት ተማሪዎች ፡ መንፈሳዊ ማኅበራት አንድ በማድረጎ መልካም አገልግሎትና ሰፋፊ ልማታዊ ሥራ እየተሠራ ይገኛል፡፡

በአሁኑ ሰዓት ከከተማው ወደ ጋራው የሚያስወጣው መንገድ ከዚህ በፊት አስቸጋሪና ለደካማ አረጋውያን እናቶችና አባቶች የማይመች ሆኖ የቆየ ቢሆንም አሁን በመልአከ ሰላም ቆሞስ አባ ዮሴፍ ኢርጶ የደብሩ አስተዳዳሪ አስተባባሪነት በቅንጅት ሁሉም ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉበት የሚገኘውን የኮብል እስቶን ንጣፍ እየተሠራና ወደ መጠናቀቁ እየተቃረበ ይገኛል፡፡

በጌጠኛ ቤትህ ልማት ይሁን( መዝ 122:7)
ይህ ዘመን ተሻጋሪ ልማት ነውና በርቱ እንላለን፡፡
††† እንኳን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ የጽንሰት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቁጽረታ (ጽንሰታ) ለማርያም †††

††† ይህችን ዕለት አበው ሊቃውንት "ጥንተ መድኃኒት፤ የድኅነት መነሻ ቀን" ሲሉ ይጠሯታል::
ስለ ምን ነው ቢሉ:-
ለዓለም ድኅነት ምክንያት የሆነች የአምላክ እናቱ የተጸነሰችበት ዕለት በመሆኑ ነው:: አንድም ከአዳም ስሕተት በኋላ ያለ ጥንተ አብሶ የተጸነሰች የመጀመሪያ ሰው እርሷ ናትና እንዲህ ይላሉ::
"ለጽንሰትኪ በከርሥ: እንበለ አበሳ ወርኩስ: ወለልደትኪ እማኅጸን ቅዱስ::"
"ድንግል ሆይ! መጸነስሽ ያለ በደል (ያለ ጥፋት) ነው: የተወለድሽበት ማኅጸንም ቅዱስ ነው::"
(መጽሐፈ ሰዓታት, ኢሳ. 1:9, መኃ. 4)

ይሕች ዕለት ለኢያቄምና ለሐና ብቻ ሳይሆን ለፍጥረት ሁሉ የተስፋ ድኅነት ቀን ናትና ሐሴትን ልናደርግ ይገባል::
የእመቤታችን መጸነስስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-
ከነገደ ይሁዳ የሚወለድ ቅዱስ ኢያቄም የሚባል ደግ ሰው ከነገደ ሌዊ(አሮን) የተወለደች ሐና የምትባል ደግ ሴት አግብቶ: በሕጉ ጸንተው: በሥርዓቱ ተጠብቀው ይኖሩ ነበር:: ነገር ግን በዘመኑ ሰዎች "ልጅ የላችሁም" በሚል ይናቁ ነበር::

ኦሪታውያን ልጅ የሌለውን "ኅጡአ በረከት-ከጸጋ እግዚአብሔር የራቀ" ነው ብለው ያምኑ ነበር:: ኢያቄምና ሐና ልጅ እንዲሰጣቸው ሲያዝኑ: ሲጸልዩ ዘመናቸው አልፎ አረጁ:: እነሱ ግን የሚያመልኩት የአብርሃምና ሣራን አምላክ ነውና ተስፋ አልቆረጡም::

የለመኑትን የማይነሳ ጌታ በስተእርጅናቸው ድንቅ ነገርን አደረገላቸው:: አንድ ቀን ርግቦች ከጫጩቶቻቸው ጋር ሲጫወቱ የተመለከተች ቅድስት ሐና ፈጽማ አለቀሰች:: "እንስሳትና አራዊትን: እጽዋትን በተፈጥሯቸው እንዲያፈሩ የምታደርግ አምላክ ምነው ሐናን ድንጋይ አድርገህ ፈጥረሃታልን?" ብላ አዘነች::

ይህን የተመለከተ ቅዱስ ኢያቄም ወደ ተራራ ወጥቶ ሱባኤ ያዘ:: ለአርባ ቀናትም ሲጸልይና ሲማለል ቆየ:: በአርባኛው ቀን ሁለቱም ሕልምን ያልማሉ:: እርሱ:- ነጭ ርግብ ሰማያትን ሰንጥቃ ወርዳ: በሐና ቀኝ ጆሮ ገብታ: በማኅጸኗ ስትደርስ አየ::

እርሷ ደግሞ:- የኢያቄም በትር አብቦ: አፍርቶ: ጣፋጭ ፍሬውን ሰው ሁሉ ሲመገበው ታያለች:: ቅዱስ ኢያቄም ከሱባኤ እንደ ተመለሰ ያዩትን ተጨዋውተው "ፈቃደ እግዚአብሔር ይሁን" አሉ:: ለሰባት ቀናትም በጋራ እግዚአብሔርን ሲለምኑ ሰነበቱ::

በሰባተኛው ቀን (ማለትም ነሐሴ 7) መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ክንፉን እያማታ ወደ እነርሱ ወረደ:: "ዓለም የሚድንባት: የፍጥረት ሁሉ መመኪያ የሆነች ልጅ ትወልዳላችሁ" ብሏቸው ተሠወራቸው:: እነርሱም ደስ ብሏቸው እግዚአብሔርን አመሰገኑ::

እንደ ሥርዓቱም በዚህች ቀን አብረው አድረው እመ ብርሃን ተጸነሰች::
"ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ ደነስ ዘተጸነስኪ"
"ድንግል ሆይ! ኃጢአት ባለበት ሥጋዊ ፍትወት የተጸነስሽ አይደለም" እንዳለ ሊቁ::
(ቅዳሴ ማርያም)

††† ቅዱስ ጴጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት †††

††† ዳግመኛ ይህች ዕለት የቅዱስ ጴጥሮስ መታሰቢያ ናት:: ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ በዚህች ቀን ደቀ መዛሙርቱን ወደ ቂሣርያ ፊልጶስ ይዟቸው ሔደ:: በዚያም ጌታ ከእነሱ ራቅ ብሎ ተቀምጦ ነበርና የማይሰማቸው መስሏቸው እርስ በእርስ ይከራከሩ ገቡ::

የክርክራቸው መነሻ ደግሞ ጌታችን ነበር:: የዋሃን (ገና ምሥጢርን ያልተረዱ) ነበሩና አንዱ ተነስቶ "ኤልያስ ነው": ሌላኛው "ሙሴ": ሦስተኛው "ኤርምያስ ነው" በሚል ተከራከሩ:: ቅዱስ ጴጥሮስ ለብቻው ቆሞ ነበርና ጠርተው "ሃሳባችንን አስታርቅልን:: ለአንተስ ማን ይመስልሃል?" አሉት::

አረጋዊው ሐዋርያም ተቆጣቸው:: "እናንተ እንደምታስቡት እርሱ ከነቢያት አንዱ ሳይሆን "እግዚአ ነቢያት-የነቢያት ፈጣሪ ነው" አላቸው:: ወዲያውም ጌታ ጠርቷቸው ወደ እርሱ ቀረቡ::

ቸር አምላክ "ለምን ተጠራጠራችሁኝ" ብሎ መገሰጽ ሲችል እንዳይደነግጡ ጥያቄውን በፈሊጥ አደረገ:: "የሰውን ልጅ ሰዎች ማን ይሉታል?" አላቸው:: እነርሱም በልባቸው ያለውን የሌላ አስመስለው ተናገሩ::

ጌታችን "እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ?" ቢላቸው ጸጥ አሉ:: ገና ሃይማኖታቸው አልጸናም ነበርና:: በዚያን ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ተነስቶ "አንተ ውእቱ ክርስቶስ ወልደ እግዚአብሔር ሕያው-አንተ የሕያው እግዚአብሔር የባሕርይ ልጁ ክርስቶስ ነህ" አለው:: (ማቴ. 16:16)

ይህች ቃል የክርስትና ሃይማኖት መሠረት ናትና ጌታችን "አንተ ዓለት (መሠረት) ነህ" ብሎ የቤተ ክርስቲያንን በዚህ እምነት ላይ መመስረት ተናገረ:: ለቅዱስ ጴጥሮስም "መራሑተ መንግስት-የመንግስተ ሰማያት መክፈቻ ቁልፍ (ሥልጣን)" ተሰጠው::

††† ሊቀ ሐዋርያትነትንም ደረበ:: ዛሬ ለበርካቶቹ የጸነነባቸው ይሔው እምነት ነው::
ኢየሱስ ክርስቶስን "አምላክ ወልደ አምላክ:
ወልደ ማርያም:
አካላዊ ቃል:
ሥግው ቃል:
ገባሬ ኩሉ:
የሁሉ ፈጣሪ"ብለው ካላመኑ እንኳን ጽድቅ ክርስትናም የለም::

††† አፄ ናዖድ ጻድቅ †††

††† ሃገራችን ኢትዮጵያ ምስፍና ከክህነት: ንግሥናን ከጽድቅ ያጣመሩ ብዙ መሪዎች ነበሯት:: ከእነዚህ አንዱ ደግሞ አፄ ናዖድ ናቸው:: ጻድቁ ንጉሥ የነገሡት ከ1487 እስከ 1499 ዓ/ም ሲሆን ለእመቤታችን በነበራቸው ልዩ ፍቅር ይታወቃሉ:: ካህን እንደ ነበሩም ይነገራል::

ዛሬ ሁላችን የምንወዳትን ጸሎት (ሰላም ለኪ: እንዘ ንሰግድ ንብለኪ . . .)
የደረሷት እርሳቸው ናቸው:: ትልቁን መልክአ ማርያምም ደርሰዋል:: ይህ መልክእ ጣዕሙ ልዩ ነው::

የጻድቁ ንጉሥ ሚስት (ማርያም ክብራ): ልጆቻቸው (አፄ ልብነ ድንግልና ቡርክት ሮማነ ወርቅ) እጅግ መልካም ክርስቲያኖች ነበሩ:: ንጉሡ አፄ ናዖድ ከባለሟልነት የተነሳ ድንግል ማርያምን "እመቤቴ ስምንተኛው ሺ መቼ ይገባል? ጊዜውስ እንዴት ያለ ነው?" አሏት::

እመ ብርሃንም በአካል ተገልጻ የዘመኑንና የሰውን ክፋት ነገረቻቸው:: ንጉሡም አዝነው "እመቤቴ! ከዛ ዘመን አታድርሺኝ" አሏት:: በዚህ ምክንያት የስምንተኛው ሺህ ዘመን መስከረም 1 በ1500 ዓ/ም ሊገባ እርሳቸው ነሐሴ 7 ቀን በ1499 ዓ/ም ዐርፈዋል::

††† ጌታችን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ የድንግል እናቱን ጣዕም: ፍቅር: የቅዱስ ጴጥሮስን ሃይማኖትና የአፄ ናዖድን በረከት ያሳድርብን::

††† ነሐሴ 7 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.በዓለ ጽንሰታ ለእግዝእትነ ማርያም
2.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
3.ቅዱስ ገብርኤል መበሥር
4.ቅዱስ ጴጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት
5.አፄ ናዖድ ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮጵያ)
6.ቅዱስ ዮሴፍ ጻድቅ (ወልደ ያዕቆብ-ልደቱ)
7.አባ ጢሞቴዎስ ሊቀ ጳጳሳት

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ሥሉስ ቅዱስ (አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ)
2.አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
3.አባ ሲኖዳ (የባሕታውያን አለቃ)
4.አባ ዳንኤል ዘገዳመ ሲሐት
5.አባ ባውላ ገዳማዊ
6.ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ
7.ቅዱስ አግናጥዮስ (ለአንበሳ የተሰጠ)

††† "መሠረቶቿ በተቀደሱ ተራሮች ናቸው:: ከያዕቆብ ድንኳኖች ይልቅ እግዚአብሔር የጽዮንን ደጆች ይወዳቸዋል::
የእግዚአብሔር ከተማ ሆይ! በአንቺ የተደረገው ድንቅ ነው . . .
ሰው እናታችን ጽዮን ይላል::" †††
(መዝ. ፹፮፥፩-፮)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††

https://t.me/felegetibebmedia