ፈለገ ጥበብ ሚዲያ felegetbeb media
993 subscribers
8.92K photos
102 videos
110 files
1.38K links
ይህ ቻናል የደብረ ዘይት ደብረ መዊዕ ቅዱስ ሚካኤል ወ ደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል ፈለገ ጥበብ ሰንበት ት/ቤት የመረጃ ሚዲያ እና ህዝብ ግንኙነት ክፍል ሲሆን ይህ ቻናል ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የሆኑ አስተምህሮቶች በየእለቱ የሚለቀቅበት ቻናል ነው ቻናላችን ስለተቀላቀሉ በእግዚአብሔር ፅኑ ፍቅር እናመሰግናለን ።

#የፈለገ_ጥበብ_ሰንበት_ትምህርት_ቤት_የመረጃ_ሚዲያ_እና_ህዝብ_ግንኙነት_ክፍል
#FTM
Download Telegram
በሐረር መካነ ሥላሴ ካቴድራል በበጎ አድራጊ የተሰራዉ የአብነት ት/ቤት ተጠናቆ ተመረቀ።

በምስራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት በሐረር ከተማ ከሚገኙት ጥንታዊና አንጋፋ አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንዱ የሐረር መካነ ሥላሴ ካቴድራል መሆኑ ይታወቃል በዚህ ስፍራ በርካታ የአብነት ተማሪዎች የሚገኙ ሲሆን ለተማሪዎቹ ለመማርያ ብቁና ምቹ ቦታ ያልበረ ሲሆን በካቴድራሉ አስተዳዳሪ በመልአከ ሰላም ጥበቡ አስተባባሪነትና በሐረር ከተማ ተወላጅ በሆነዉ በአቶ ለማ ጌታቸዉና በባለቤታቸዉ በዶ/ር ገነት እንዲሁም በልጆቻቸዉ ስም ለአቶ ለማ እናትና አባት መታሰብያ ይሆን ዘመናዊ የሆነ የአብነት ት/ቤት መማርያ ሠርተዉ ለካቴድራሉ አስተዳደር ጽ/ቤት አስረክበዋል።
በዕለቱም የምስራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ገነት ቀሲስ ንጋቱ ደሳለኝ እና የሐገረ ስብከቱ የክፍል ኃላፊዎች ተገኝዋል።የካቴድራሉ አስተዳዳሪ መልአከ ሰላም ጥበቡም በዕለቱ እንግዶችን እንኳን በደሕና ወደ ካቴድራላችን በሰላም መጣችሁ በማለት ንግግር ከአደረጉ በኋላ የተሰሩ ስራዎችን ገለፃ አድርገዋል ይህንን በጎና መልካም ሥራ ለቤተሰባቸዉ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ለአሠሩት ለአቶ ለማ ጌታቸዉ እና ለባለቤታቸው ለዶ/ር ገነትና ልጆቻቸዉ የስጦታ እና የምስጋና እንዲሁም የዕውቅና ሠርተፍኬት መርሐ ግብር ከተከናወነ በኋላ ለተደረገላቸዉ አቀባበልና ስጦታ አቶ ለማና ባለቤታቸዉ ምስጋና አቅርበዉ በመጨረሻም የሐገረ ስብከቱ ስራ አስኪያጅ የተሰራዉን ስራ አስመልክቶ ምስጋና አቅርበዉ መልዕክት አስተላልፈዉ የመርሐ ግብሩ ፍፃሜ ሆኗል።
©ምስራቅ ሀረርጌ ሀገረ ስብከት
ብፁዕ አቡነ አብርሃም እና ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ/ር) የትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤትን ጎበኙ።

ብፁዕ አቡነ አብርሃም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤት ዋና ስራ አስኪያጅና የባህርዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ/ር) የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የኒውዮርክና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ  የትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤትን ጎብኝተዋል።  በጉብኝቱ ወቅት የማተሚያ ቤቱ አመሠራረት ታሪክ የተዘከረ ሲሆን ፫ኛው የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ብፁዕ አቡነ ተክለሃይማኖት ክርስትያን ያልነበሩ ወላጅ አልባ ታዳጊዎችን አሰባስበው አስተምረው በድርጅቱ ሥራ ሰጥተው ልጆቹ ቁም ነገር ላይ ያደረሱ መሆናቸው ተወስቷል።
ብፁዕ አቡነ አብርሃም እንዲህ ያሉ አባቶችን ተግባር አሁን ያለነው ምን መሥራት እንደሚገባን ትልቅ አስተማሪ ታሪክ መሆኑን ጠቁመው ቢቻል  በ፳፻፲፮ የበጀት ዓመት አለበለዚያ በ  ፳፻፲፯ ዓ.ም  በጀት ዓመት የድርጅቱ ሥራ መሠረታዊውን ለውጥ የሚያመጣ መሆን እንዳለበት ብፁዕ ጠቅላይ ስራ አስኪያጁ ጠቁመዋል።
የሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ በበኩላቸው በታሪክ የምንሰማውን የማተሚያ ቤታችንን ሥራውን በማየታችን ትልቅ ትምሕርት  ያገኘንበት ሲሆን ክርስቲያን ያልነበሩ እጓለማውታ እና  የካህናት ልጆችን በዚህ እያሠራችሁ እዚህ ማድረሱ  ተቋሙን የሚያስመሰግንነው በማለት ማተሚያ ቤትና ሰንበት ትምህርት ቤት ለግብጽ ቤተ ክርስቲያን የዕድገት መሠረት እንደሆኑ ጠቁመዋል ።
©EOTC TV
የቱለማ ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን ሕንጻ ቤተ መቅድስ ሥራ በጥሩ አፈጻጸም ላይ እንደሚገኝ ተገለጸ

 በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የወላይታ እና ዳውሮ ሀገረ ስብከት በኢሰራ ወረዳ በቱለማ ቀበሌ የሚገኘው የቱለማ ደብረ ነጉድጓድ ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን ሕንጻ ቤተ መቅደስ ግንባታ በጥሩ አፈጻጸም ላይ እንደሚገኝ አስተባባሪ አገልጋዮቹ ለዝግጅት ክፍላችን ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም መካናተ ደብረ ነጎድጓድ በተሰኘው ዓምዳችን ካስተዋውቅናችሁ በሀገራችን ከሚገኙ የሐዋርያው የቅዱስ ዮሐንስ አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንዱ የሆነው ይህ ቤተ ክርስቲያን ከአዲስ አበባ 555 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን በአጥቢያው የሚገለግሉ ምዕመናን ጥቂት በመሆናቸው ከአቅም ማነስ የተነሳ የለቅኔ ማሕሌት እና ቅድስት በሳር ክዳን የተሠራ እጅግ ጠባብ ቤተ መቅደስ ነበር ይህ ቤተ ክርስቲያን በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የሚቀደስበት አንድ አገልጋይ ዲያቆን ከአንድ ልብሰ ተክህኖ ጋር ብቻ ያለበት በአጽራረ ቤተ ክርስቲያን የተከበበ ቦታ መሆኑን በወቅቱ ወደ እናንተ ባዳረስነው ጥንቅር መግለጻችን ይታወሳል የአካባቢው ተወላጆች ለሚድያችን በላኩልን መረጃ መሠረት ስለ ቤተ ክርስቲያኑ ታሪክ እና ያለበትን ወቅታዊ ሁኔታ  ወድ እናንተ ተከታታዮቻችን ካደረስን በኃላ በልዩ ልዩ በጎ አድራጊ ምዕመናን እና አገልጋዮች ትብብር ቤተ መቅደስ እንደ አዲስ እየተሠራ የሚገኝ ሲሆን አሁን ያለበት ደረጃም እጅግ ተስፋ ሰጪ መሆኑን መረጃውን ያቀበሉን የአጥቢያው አገልጋዮች ይገልጻሉ የጀመሩትን ይህን ሕንጻ ቤተ መቅደስ ለመጨረስ አሁንም የእኛን ድጋፍ የሚፈልጉ ሲሆን ሥራው ለፍጻሜ እንዲበቃ በምንችለው ሁሉ እንድንረባረብ ሚድያችን ጥሪ ያቀርባል

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
1000309325428
††† እንኳን ለሐዋርያው ቅዱስ ሐናንያ እና ለሰማዕቱ ቅዱስ ቶማስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ ሐናንያ ሐዋርያ †††

††† ሐናንያ ቁጥሩ ከ72ቱ አርድእት ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስማቸው ተመዝግቦ ከተቀመጠልን ከጥቂቶቹ ዋነኛው ነው:: ከነገደ እሥራኤል ተወልዶ : በሕገ ኦሪት አድጐ : ከወጣትነት ዕድሜው ትንሽ እልፍ ሲል ጌታችን ወንጌልን ማስተማር ጀምሯልና ጠራው:: እርሱም በበጐ ፈቃድ ተከትሎታልና ከ72ቱ አርድእት ደመረው::

ለ3 ዓመታት ከጌታ እግር ተምሮ : ከዕለተ ስቅለት በፊት ሀብተ ፈውስም ተሰጥቶት ነበር:: ምክንያቱም ቅዱስ ሉቃስ እንደ ጻፈልን ሰብዐው አርድእት "ጌታ ሆይ! አጋንንት በስምህ ተገዙልን" ማለታቸውን አስቀምጦልናል:: (ሉቃ. 10:17) ቅዱስ ሐናንያ በበዓለ ዕርገት ተባርኮ በ50ኛው ቀንም መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ ለስብከተ ወንጌል ወጥቷል::

በሚያስተምር ጊዜ የሶርያዋን ደማስቆን ማዕከል አድርጐ ነበር:: በሁዋላም አበው ሐዋርያት የዚህች ከተማ የመጀመሪያው ዻዻስ አድርገው ሹመውታል:: ጌታ ባረገ በ8ኛው ዓመት ክርስቲያኖችን ያሰቃይ የነበረው ሳውል (የሁዋላው ቅዱስ ዻውሎስ) ወደ ደማስቆ የተጉዋዘው ክርስቲያኖችን በተለይም ቅዱስ ሐናንያን ለማሠር ነበር::

ለእግዚአብሔር ምርጥ ዕቃ ይሆን ዘንድ መብረቅ ዐይኑን አጠፋው:: ወዲያውም ጌታችን ሳውልን ወደ ሐናንያ እንዲሔድ ነገረው:: ከ3 ቀናት በሁዋላ ጌታችን ለሐናንያ ተገልጦ አነጋግሮታል::

ሳውል (ዻውሎስ) ወደ ሐናንያ የደረሰው በመሪ ነበር:: 2ቱ እንደተገናኙ ቅዱስ ሐናንያ ሳውልን አስተማረው : ፈወሰው : አጠመቀው : በጐ መንገድንም መራው:: በዚህ ምክንያት ቅዱሱ ሐዋርያ የቅዱስ ዻውሎስ የንስሃ አባቱ ይሰኛል:: (ሐዋ. 9:1-19)

ከዚህ በሁዋላ ቅዱስ ሐናንያ ለብዙ ዓመታት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ወንጌልን አስተማረ:: መከራንም ተቀበለ:: በመጨረሻም በዚህ ቀን ክፉዎች ከብዙ ስቃይ በሁዋላ በድንጋይ ወግረው ገድለውታል::

††† ቅዱስ ቶማስ ዘሰንደላት †††

††† በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን ከነበሩ ሰማዕታት አንዱ የሆነው ቅዱስ ቶማስ ወደ ሰማዕትነት ሕይወት የገባው በ11 ዓመቱ በመላእክት መሪነት ነው:: ገና ወደ ምስክርነት አደባባይ እንደ ቀረበ መኮንኑ "ክርስቶስን ካድና ልሹምህ" ቢለው ሕጻኑ ቅዱስ ቶማስ ተቆጥቶ : "አንተ ሰነፍ መኮንን" ብሎ ገስጾ : በጐችን ይመልስባት በነበረችው ጅራፍ ገርፎታል:: ይሔም በዘመኑ የመጨረሻው የድፍረት ደረጃ ነበር::

††† በዚህም ምክንያት በሕጻን ገላው ላይ የተቀበለው መከራ ሊናገሩት ይከብዳል::
¤ግርፋት:
¤እሳት:
¤አራዊት በእርሱ ላይ አልፈዋል::

አካሉ ተቆራርጧል:: አንድ ጊዜም "ለጣዖታችሁ እንድሰግድ አምጡት" ብሏቸው ልክ ከፊቱ ሲደርሱ ወደ ጌታ ቢጸልይ መሬት ተከፍታ ውጣቸዋለች::

እሱን ያሰቃየው የነበረውን መኮንንም ከደዌው አድኖ ከነ ሠራዊቱ አሳምኖታል:: ሕጻኑን ቅዱስ ቶማስን ግን ያላመኑ አረማውያን በዚህች ቀን አንገቱን ሰይፈውት በሰማዕትነት ወደ ወደደው ክርስቶስ ሔዷል::

††† አምላከ ቅዱሳን ከሐዋርያው በረከት : ከሰማዕቱም ምልጃ አይለየን::

+"+ #ቅዱስ_ያዕቆብ_ዘሥሩግ +"+

=>#በቤተ_ክርስቲያን_ታሪክ በደራሲነታቸው: በወንጌል አገልግሎታቸውና በቅድስናቸው ከተመሠከረላቸው ዐበይት ሊቃውንት አንዱ ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ ነው::

+ሊቁ የተወለደው መጋቢት 27 ቀን በ433 ዓ/ም ሲሆን ሃገሩ ሶርያ ነው:: ወላጆቹ ክርስቲያኖች ለዚያውም አባቱ ሊቀ ካህናት ነበር:: ቅዱስ ያዕቆብ ገና በልጅነቱ ጀምሮ ጸጋ እግዚአብሔር የጠራው ነውና በብዙ ነገሩ የተለየ ነበር::

+አንድ ቀን በዕለተ ሰንበት ገና በ3 ዓመቱ እናቱ አቅፋ ወደ #ቤተ_መቅደስ ወሰደችው:: ምዕመናን #ቅዱስ_ሥጋውንና #ክቡር_ደሙን ሲቀበሉ ሕጻኑ ያዕቆብም ይቆርብ ዘንድ ቀረበ:: ሊቀ ዻዻሱ ደሙን በዕርፈ መስቀል ሊያቀብለው ሲል መልአኩ መጥቶ "በጽዋው ጋተው" አለው:: የጌታን ደም በጽዋ ቢጠጣ ምስጢር ተገለጸለትና "#አንሰ_እፈርሕ_ሠለስተ_ግብራተ-እኔስ 3 ነገሮች ያስፈሩኛል" ሲል አሰምቶ ተናገረ::

+ዻዻሱና ሕዝቡ ወደ ሕጻኑ ያዕቆብ ቀርበው "ምን ምን?" አሉት:: እርሱም:-
1.ነፍሴ ከሥጋየ ስትለይ
2.ቅድመ እግዚአብሔር ለፍርድ ስቀርብ
3.ከፈጣሪየ የፍርድ ቃል ሲወጣ" አላቸው::
ያን ጊዜ ሕዝቡና ሊቀ ዻዻሳቱ "#እግዚአብሔር_በዚሕ_ሕጻን_አድሮ_ዘለፈን" እያሉ ለንስሃ በቅተዋል::

+ቅዱስ ያዕቆብ 7 ዓመት ሲሞላው ይማር ብለው ወደ ጉባዔ አስገቡት:: በ5 ዓመታት ብሉይ ከሐዲስ ጠንቅቆ በ12 ዓመቱ ሊቅ ሆኗል:: በዚህ ወቅት የነበሩ ታላላቅ ሊቃነ ዻዻሳት ወደ እርሱ ተሰበብስበው "እንግዳ ድርሰት ድረስልን: አዲስ ምሥጢር ንገረን" አሉት:: እርሱ ግን ሲቻለው ስለ ትሕትና "አልችልም" አላቸው::

+"እንግዲያውስ #ትንቢተ_ሕዝቅኤልን ተርጉምልን" ቢሉት ባጭር ታጥቆ አመሥጥሮላቸው ተደስተዋል:: ፈጣሪንም አመስግነዋል::

+ቅዱስ ያዕቆብ ከዚህ በሁዋላ ወደ ገዳም ገብቶ ትሕርምተ አበውን: ዕጸበ ገዳምን: ሕይወተ ቅዱሳንን በተግባር ተምሯል:: በድንግልናው ጸንቶ: #ጾምና_ጸሎትን እያዘወተረ ኑሯል:: በፈቃደ እግዚአብሔር የሥሩግ (በኤፍራጥስና ጤግሮስ ወንዞች መካከል የምትገኝ የሶርያ ግዛት ናት) ኤዺስ ቆዾስ ሆኖ ተሹሟል::

+በዘመኑም:-
1.የ451ን የኬልቄዶን ጉባኤ አውግዟል

2.ብዙ መናፍቃንን ተከራክሮ ምላሽ አሳጥቷል

3.በወንጌል አገልግሎት መልካም እረኝነቱን አሳይቷል

4.ዛሬ የምንገለገልበትን መጽሐፈ ቅዳሴውን ጨምሮ በርካታ መንፈሳዊ ድርሰቶችን ደርሷል::

+በመጨረሻም ከብዙ የተጋድሎና የቅድስና ዓመታት በሁዋላ በተወለደ በ72 ዓመቱ በ505 ዓ/ም በዚሕች ቀን አርፏል:: አንዳንድ ምንጮች ደግሞ ሰኔ 27 ቀን እንዳረፈ ይናገራሉ:: #ቅዱስ_ያዕቆብ_ዘሥሩግ ለቤተ ክርስቲያን የቁርጥ ቀን ተወዳጅ ልጇ ነውና በእጅጉ ታከብረዋለች::

=>#አምላከ_ቅዱሳን ከታላቁ ሊቅ በረከት ይክፈለን::

††† ሰኔ 27 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ሐናንያ ሐዋርያ (ከ72ቱ አርድእት)
2.ቅዱስ ቶማስ ሰማዕት (ዘሰንደላት)
3.ቅዱስ አልዓዛር ነዳይ (በነዌ ደጅ የወደቀ : ቀጥሎ ደግሞ በአብርሃም እቅፍ ውስጥ የተገኘ ጻድቅ - ሉቃ. 16:19)
4.ቅዱስ ማማስ

††† ወርኀዊ በዓላት
1.የጌታችንና አምላካችን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ በዓለ ስቅለት
2.አቡነ መብዐ ፅዮን ጻድቅ
3.ቅዱስ መቃርስ (የመነኮሳት ሁሉ አለቃ)
4.ቅዱስ ያዕቆብ ዘግሙድ
5.ቅዱስ ገላውዴዎስ ሰማዕት (ንጉሠ ኢትዮዽያ)
6.ቅዱስ ቢፋሞን ጻድቅና ሰማዕት
7.ማር ቅዱስ ፊቅጦር ሰማዕት

††† "በደማስቆም ሐናንያ የሚሉት አንድ ደቀ መዝሙር ነበረ:: ጌታም በራዕይ:- "ሐናንያ ሆይ!" አለው:: እርሱም "ጌታ ሆይ! እነሆኝ" አለ:: ጌታም:- ተነስተህ ቅን ወደ ሚባለው መንገድ ሒድ:: በይሁዳ ቤትም ሳውል የሚሉትን አንድ የጠርሴስ ሰው ፈልግ:: እነሆ እርሱ ይጸልያልና:: ሐናንያ የሚሉትም ሰው ገብቶ ደግሞ እንዲያይ እጁን ሲጭንበት አይቷል" አለው::" †††
(ሐዋ. 9:10-18)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
#በአንድ_ወቅት_እንዲህ_ሆነ

እግዚአብሔር #በአባ_ሙሴ_ጸሊም ላይ አድሮ ከአደረጋቸው ተአምራት መካከል ያለ ወቅቱ ዝናብ እንዲዘንብ ማድረጋቸው አንደኛው ነው፤ ከዕለታት አንድ ቀን በበዓታቸው ምንም ውኃ በሌለበት ቀን አረጋውያን በእንግድነት መጡባቸው፡፡ ውኃ የሚቀዳበት ቦታ በጣም ሩቅ ነበርና የሚያደርጉትን አጡ፡፡ እንግዶቹን ወደ በዓታቸው ካስገቡ በኋላም እግዚአብሔርን "ውኃ ካልሰጠኸኝ ቅዱሳን አገልጋዮችህን ምን አጠጣቸዋለሁ?" እያሉ በጸሎት ይጠይቁት ጀመሩ፡፡ በስሙ ለሚታመኑ ድንቅ ሥራውን መግለጥ ልማዱ የኾነው እግዚአብሔር ጸሎታቸውን ሰምቶ ዝናብ አዘነበላቸውና የውኃ ጉድጓዶችን ሞላላቸው፡፡

እንግዶቹንም እንደ ሥርዓቱ እግራቸውን አጥበው፣ ምግብና ውኃ ሰጥተው አስተናገዷቸው፡፡ አረጋውያኑም በዝናቡ መጣል እየተገረሙ አባ ሙሴን "ብዙ ጊዜ ትወጣ፣ ትገባ የነበረው ለምንድን ነው?" ብለው ጠየቋቸው፡፡ እርሳቸውም "እግዚአብሔርን ውኃ እንዲሰጠኝ እየተማጸንኩት ነበር፡፡ በቸርነቱም ዝናምን ልኮልን ውኃን አገኘን" አሏቸው፡፡ በዚህ ጊዜ በቅዱሳኑ አድሮ ድንቅ ድንቅ ተአምራቱን የሚገልጠውን እግዚአብሔርን አመሰገኑት፤ በአባ ሙሴ ቅድስናም ተደነቁ፡፡

(ሰኔ 24 የቅዱስ ሙሴ ጸሊም ኢትዮጵያዊው የእረፍቱ መታሰቢያ ነው ➛ የቅዱስ ሙሴ ጸሊም በረከቱ አይለየን!!!)
#ይፋዊ

የትላንት የሬሜዲያ ፈተናዎች ተሰርዘዋል።

በሬሜዲያ ፈተና ሂደት ወቅት በተፈጠሩ ችግሮች ምክንያት የትምህርት ሚኒስቴር ውሳኔዎች አሳልፏል።

የ2014 ዓ.ም 12ኛ ክፍል ረሜዲያል ተጠቃሚ ተማሪዎች ፈተና ትናንት ሰኔ 26/2015 ዓ.ም በዩኒቨርስቲዎች መሰጠት መጀመሩ ይታወቃል።

ይሁን እንጂ በፈተና ሂደት በተፈጠሩ ችግሮች ምክንያት የትምህርት ሚኒስቴር የሚከተሉትን ውሳኔዎች አሳልፏል።

1) ሰኔ 26/2015 የተሰጡት የሬሜዲያል ፕሮግራም ፈተናዎች ተሰርዘው ተማሪዎች በቀሩት የትምህርት ዓይነቶች ብቻ እንዲመዘኑ።

2) ቀደም ብሎ በሁሉም ሬሜዲያል ፕሮግራም ተጠቃሚ ተማሪዎች ባላቸው ተቋማት ፈተናውን በአንድ ጊዜ ለመስጠት የታቀደው ተሻሽሎ በተለይም ከ150 በላይ የሆኑና ከ200 በላይ ካምፓስ ያላቸውን የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፈተና ቀርቶ ወደ ፊት በሚወሰን አግባብ ፈተናው በመስከረም ወር 2016 ዓ.ም እንዲሰጥ።

3) በመንግስት ተቋማት የሬሜዲያል ፕሮግራም ተጠቃሚ የሆኑትን ተማሪዎች በተያዘው ፕሮግራም መሰረት ይሰጣል።

(ትምህርት ሚኒስቴር)

NB. ትምህርት ሚኒስቴር ፤ ዛሬ ይፋ ባደረገው መረጃ ትላንት ፈተናው መሰጠት ከተጀመረ በኃላ ተፈጥረዋል ያላቸውን ችግሮችን በዝርዝር አላሳወቀም።

More : @tikvahuniversity

@tikvahethiopia
=>+"+ እንኩዋን ለስደተኛው ሊቀ ዻዻሳት "አባ ቴዎዶስዮስ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ +"+

+*" አባ ቴዎዶስዮስ "*+

=>ጻድቁ ሊቀ ዻዻሳት ተወልዶ ያደገው በምድረ ግብጽ በ6ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው:: ከልጅነቱ መጻሕፍትን ተምሮ በመንኖ ጥሪት የሚኖር ደግ ሰው ነበር:: ያ ዘመን መለካውያንና ልዮናውያን (ክርስቶስን 2 ባሕርይ የሚሉ) የሰለጠኑበት ዘመን ነበር:: በአንጻሩ ደግሞ ተዋሕዶን የሚያምኑ ሊቃውንትና ምዕመናን ቁጥራቸው የተመናመነ ነበር::

+ችግሩ ግን ይህ ብቻ አልነበረም:: በጊዜው ተዋሕዶን አምኖ መገኘት እስከ ሞት የሚደርስ ዋጋንም ያስከፍል ነበር:: ለዚሕም ነው ሮማውያን ሃይማኖትን በግድ ለማስለወጥ ከነገሥታቱ ጋር የተቆራኙት:: #ቅዱስ_ዲዮስቆሮስ ጋግራ ደሴት ውስጥ ከተገደለ በሁዋላ በግብፅ የተሾሙ ሊቃነ ዻዻሳት አብዛኞቹ መከራና ስደትን ቀምሰዋል:: ትልቁን ቦታ ግን #አባ_ቴዎዶስዮስ ይወስዳል::

+አባ ቴዎዶስዮስ ለእስክንድርያ (ግብፅ) 33ኛ ፓትርያርክ ነው:: እረኝነት (ዽዽስና) እንዳሁኑ ዘመን ሠርግና ምላሽ አይደለምና ገና እንደ ተሾመ የቀረበለት ጥያቄ አንድ ነበር:: "ተዋሕዶን ትተህ መለካዊ ትሆናለህ ወይስ የሚከተልብህን ፍርድ ትቀበላለህ?" አሉት:: ይህንን ያሉት ከንጉሡ ዮስጢያኖስ የመጡ መልእክተኞች ነበሩ:: መልሱ ፈጣን ሆነባቸው:: "እኔንም ሆነ ሕዝቤን ከቀናችው እምነታችን በምንም ልትለዩን አትችሉም" አላቸው::

+በዚህ ምክንያት በቀጥታ ግዞት (ስደት) ተፈረደበት:: ወደ በርሃ ሲያግዙት ካህናት : መምሕራንንና ምዕመናንን አደራ ብሏቸው ነው የሔደው:: መናፍቃኑ እሱን ካሰደዱ በሁዋላ ሕዝቡን ለመቀየር ብዙ ደክመዋል:: ግን ሊሳካላቸው አልቻለም:: ምክንያቱም አደርነትን የማይረሱ ደጋግ መምሕራን ነበሩና ነው::

+በዚያ ላይ አባ ቴዎዶስዮስ #ጦማር (መልእክት) በየጊዜው ይጽፍላቸው ነበር:: እጅግ ብዙ ከሆኑት መልእክቶቹ የተወሰኑት ዛሬም ድረስ #ሃይማኖተ_አበው መጽሐፍ ውስጥ ይገኛሉ::

+በዚሕ አስቸጋሪ ዘመን መልካም ነገሮችም ነበሩ:: ቀዳሚው #ማሕቶተ_ተዋሕዶ #ቅዱስ_ያዕቆብ_ዘእልበረዳይ ሲሆን 2ኛው ደግሞ የንጉሡ ሚስት የተባረከችው #ታኦድራ ናት::

+አባ ቴዎዶስዮስ በግዞትና በስደት ሳለ ንግሥቲቱ ትራዳው : ምዕመናንንም ትንከባከብ ነበር:: ቅዱስ ያዕቆብ ከሊቀ ዻዻሱ ዘንድ ክህነትን ተቀብሎ ከሶርያ እስከ ምድረ ግብጽ ስለ #ተዋሕዶ ሕልውና ተጋድሏል:: ምናልባትም ከሐዋርያው #ቅዱስ_ዻውሎስ በሁዋላ በፈሊጥ ክርስትናን በማስፋፋት ቀዳሚ አባት ነው:: (በነገራችን ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ማዕተብ ማሰርን ያስተማረ አባትም ነው)

+2ቱ (አባ ቴዎዶስዮስና ቅዱስ ያዕቆብ) ስለ ቀናች ሃይማኖት ብዙ ስለ ደከሙ የዘመኑ ምዕመናን በስማቸው "#ያዕቆባውያን እና #ቴዎዶስዮሳውያን" ተብለው ተጠርተዋል:: አባ ቴዎዶስዮስ ግን ሲታሠር ሲፈታ : ሲሰደድ ሲመለስ ብዙ ተሰቃየ::

+ሕዝቡን ግን በመልካም እረኝነት ጠብቆ : ከተኩላ አፍ ታደገ:: በዚህች ቀንም ዐርፎ ተቀብሯል:: በፓትርያርክነት ያገለገለባቸው ዘመናት 32 ዓመታት ሲሆኑ ከእነዚህ ዓመታት 28ቱ ያለቁት በስደትና በመከራ ነው::

=>እግዚአብሔር የአባቶቻችን ስደት አስቦ ከነፍስ ስደት ይሰውረን:: ከበረከታቸውም ያድለን::

=>ሰኔ 28 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.አባ ቴዎዶስዮስ ሊቀ ዻዻሳት
2.ቅዱስ ያዕቆብ ዘእልበረዳይ
3.ቅዱስ ባስልዮስ
4.ቅዱስ ባሊዲስ

=>ወርኀዊ በዓላት
1.አማኑኤል ቸር አምላካችን
2.ቅዱሳን አበው (አብርሃም: ይስሐቅና ያዕቆብ)
3.ቅዱስ እንድራኒቆስና ሚስቱ ቅድስት አትናስያ
4.ቅድስት ዓመተ ክክርስቶስ
5.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሮማዊ (ሰማዕት)

=>+"+ ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብጹዓን ናቸው:: መንግስተ ሰማያት የእነርሱ ናትና:: ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዷችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብጹዓን ናችሁ:: ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ:: ሐሴትም አድርጉ:: ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳደዋቸዋልና:: +"+ (ማቴ. 5:10)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>