ፈለገ ጥበብ ሚዲያ felegetbeb media
987 subscribers
8.72K photos
102 videos
110 files
1.31K links
ይህ ቻናል የደብረ ዘይት ደብረ መዊዕ ቅዱስ ሚካኤል ወ ደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል ፈለገ ጥበብ ሰንበት ት/ቤት የመረጃ ሚዲያ እና ህዝብ ግንኙነት ክፍል ሲሆን ይህ ቻናል ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የሆኑ አስተምህሮቶች በየእለቱ የሚለቀቅበት ቻናል ነው ቻናላችን ስለተቀላቀሉ በእግዚአብሔር ፅኑ ፍቅር እናመሰግናለን ።

#የፈለገ_ጥበብ_ሰንበት_ትምህርት_ቤት_የመረጃ_ሚዲያ_እና_ህዝብ_ግንኙነት_ክፍል
#FTM
Download Telegram
ደስ የሚል ጊዜ ነበር ያሳለፍነው በቅርብ እንደሚደገም ተስፋ እናደርጋለን ክህንን ክፍል መደገፍ መርዳት የምትፈልጉ 

Gmail: felegetbeb12@gmail.com

ፃፍልን መልዕክታችሁን አስቀምጡልን
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

❖ መስከረም ፳፫ (23) ❖

✞✞✞ እንኩዋን ለቅዱሳን #ጻድቃን_ወሰማዕት
#አውናብዮስና_እንድርያስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል
በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

+"+ #ቅዱሳን_አበው_አውናብዮስ_ወእንድርያስ +"+

=>4ኛው መቶ ክ/ዘ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ዘመነ
ከዋክብት ይባላል:: ምናልባትም በዓለም ላይ ላለፌት
1,500 ዓመታት ያንን ዘመን መልሶ ማየት አልተቻለም::

*ያ ዘመን ብዙ #ሰማዕታት ነበሩበት::
*ያ ዘመን ብዙ #ሊቃውንት ነበሩበት::
*ያ ዘመን ብዙ #ጻድቃን ነበሩበት::
*ያ ዘመን ብዙ #ደናግል ነበሩበት::
*ያ ዘመን ብዙ #መነኮሳት ነበሩበት::
*ያ ዘመን ብዙ #ባህታውያን (ግኁሳን) ነበሩበት::

+ዘመኑ #ዘመነ_ብርሃን ነው:: እልፍ አእላፍ ቅዱሳን
በዚህ ዘመን አብርተዋልና:: ጠላት ሰይጣንን ከቦታው
አሳድደው አስጨንቀውታል:: በዚህ ዘመነ ብርሃን ከወደ
ምሥራቅ ካበሩ ከዋክብት መካከል ደግሞ በዚህ ዕለት
አባቶቻችን ቅዱሳን አውናብዮስና እንድርያስን
እናዘክራለን::

+ቅዱሳኑ ባለ ብዙ ሃብት ነበሩ:: ከሰማዕታት: ከጻድቃን:
ከደናግል: ከሊቃውንቱም አሉበት:: ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-

¤በተጠቀሰው ዘመን በቅዱስ #ጊዮርጊስ ሃገር በልዳ
ከከበሩ ወገኖች ተወልደዋል::

+የቅዱሳኑ ወላጆች ክርስቲያኖች: በዚያውም ላይ ባለ
ሥልጣኖችና ሃብታሞች ነበር:: ልጆቻቸውን
(አውናብዮስንና እንድርያስን) ሥጋዊውንም:
መንፈሳዊውንም ትምሕርት አስተምረዋቸዋል:: ወጣት
በሆኑ ጊዜ ወላጆቻቸው የዚህን ዓለም ነገር
ሲያስቡላቸው: እነሱ ግን የተሻለውን እድል ያስቡ ነበር::

+ዘወትር ገድላተ ቅዱሳንን ያነቡ: ዜና አበውን ይሰሙ
ነበርና ይመንኑ ዘንድ ልቡናቸው አወካቸው:: በአንዲት
ሌሊት ግን በመንፈስ ቅዱስ አጋዘዥነት ወስነው:
ከሃገራቸው #ልዳ ወጥተው ወደ ገዳም ሔዱ::

+ክብር ለቅዱሳኑ #አባ_ሮማኖስና #አባ_በርሶማ ይሁንና
በወቅቱ በሶርያ ምድር ገዳማዊ ሕይወት ተስፋፍቶ: ብዙ
አድባራት በበርሃ ውስጥ ነበሩ:: 2ቱ ቅዱሳንም በአንዱ
ገዳም ውስጥ ገብተው አገለገሉ::

+ተጋድሏቸውን እያበረቱ እስከ ምንኩስና ደረጃም ደረሱ::
ተጋድሏቸው በጾም: በጸሎትና በትእግስት ብቻ
አይደለም:: በትሕትና በፍቅር በደግነትና በመታዘዝም
ጭምር ነበር እንጂ::

+የምንኩስናና የገዳማዊ ሕይወት ጠላት 'ፍቅረ ዓለምና
ፍትወት እንስሳዊት' ናቸው:: አንድ ሰው ከዚህ ዓለም
ቁሳቁስ ሳይርቅ መናኝ መሆን አይችልም:: ቅዱሳኑ ግን
በመንኖ ጥሪት ይህችን ዓለም ከነኮተቷ ናቁዋት:
አቃለሏት::

+የሥጋ ፈቃዳቸውን ያጠፉ ዘንድ ሰውነታቸውን በጾምና
በጸሎት: ዕረፍትም በማሳጣት ቀጧት:: #እግዚአብሔር
ደግሞ ስለዚህ ፈንታ ጸጋውን አበዛላቸው:: ቅዱሳኑ
በሶርያ ገዳማት ለዘመናት ከተጋደሉ በሁዋላ ወደ ግብጽ
ለመውረድ ወሰኑ:: ምክንያታቸው ደግሞ:-

1ኛ.ከውዳሴ ከንቱ ለመራቅ
2ኛ.ከቅዱሳን አበው ለመባረክ እና
3ኛ.ለተሻለ ተጋድሎ ለመብቃት ነበር:: እየጸለዩ
እያመሰገኑም ግብጽ: ቀጥሎም ገዳመ አስቄጥስ ደረሱ::

+ታላቁ #ርዕሰ_መነኮሳት_አባ_መቃርስን ፊት ለፊት
ቢያገኙት ደስ አላቸው:: ሐሴትንም አደረጉ::
እግዚአብሕርን በማደሪያዎቹ ማግኘት ይቻላልና:: የታላቁ
ቅዱስ ደቀ መዝሙር ሆነው: በድንግልና ተጠብቀው:
በተጋድሎ በርትተው በቦታው ለ3 ዓመታት ቆዩ::

+እግዚአብሔር ደግሞ ለሌላ አገልግሎት ፈልጐአቸው
ነበርና በዚያ ሰሞን በከተማ የነበሩ ሊቃውንት ወደ ገዳም
መጡ:: ገዳማውያንንም ዻዻስ ስላረፈብን "የምንሾመው
መልካም እረኛን ስጡን" አሏቸው::

+ገዳማውያኑ ሱባኤ ገብተው ቢጠይቁ መንፈስ ቅዱስ
ቅዱስ አውናብዮስን መረጠ:: አበውም ቅዱሱን ዽዽስና
ሲሾሙት ወንድሙን እንድርያስን ረዳት አደረጉት:: 2ቱ ቅዱሳን ከበርሃ ወደ
ከተማ መውጣታቸውን ተከትሎ ተጋድሏቸውን ለማበርታት
ወሰኑ::

+ምክንያቱም ለአንድ ገዳማዊ ከተማ ውስጥ ከመኖር
በላይ ፈተና የለምና:: ቅዱሳኑ ቀን ቀን ድውያንን
ሲጠይቁ: ሙታንን ሲቀብሩ: ሕዝቡን ሲያስተምሩ:
ሥጋውን ደሙን ሲያቀብሉ ውለው ሌሊት ይጋደላሉ::

+ለፈቃደ ሥጋቸው ሳያደሉ እንዲህ ባለ ቅድስና ኖረው
ደግሞ ሌላ ፈተና መጣ:: የከተማው ሃገረ ገዢ አረማዊ
በመሆኑ "ለጣዖት ስገዱ: ክርስቶስን ካዱ" ይል ጀመር::
ቅዱሳኑ ሕዝቡን በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባርም
ሊያስተምሩ ወደዋልና መኮንኑን "ተው! ተሳስተሃል"
አሉት::

+በዚህ ምክንያትም ብዙ ስቃይ ገጠማቸው::
በመጨረሻም በዚህች ዕለት ሰማዕት ሆነዋል:: ጌታም
ስለ ድንግልናዊ ሕይወታቸው: ስለ ወንጌል
አገልግሎታቸውና ስለ ሰማዕትነታቸው 3 አክሊላትን
አቀዳጅቷቸዋል::

=>አምላከ አበው ቸርነቱን ይላክልን:: የቅዱሳኑን
በረከትም ያሳድርብን::

=>መስከረም 23 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን
በዓላት=
1.ቅዱሳን ጻድቃን አውናብዮስ ወእንድርያስ (ሰማዕታት)
2.ቅዱስ ጐርጐርዮስ መንክራዊ
3.ቅድስት ቴክላ ድንግል
4.ቅዱስ ኤዎስጣቴዎስ ሰማዕት

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት
2.ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት
3.ነቢየ ጽድቅ ቅዱስ ሰሎሞን (ንጉሠ እሥራኤል)
4.አባ ጢሞቴዎስ ገዳማዊ
5.ቅዱስ ዳንኤል ነቢይ
6.አባ ሳሙኤል
7.አባ ስምዖን
8.አባ ገብርኤል

=>+"+ በጐንም ለማድረግ ብትቀኑ የሚያስጨንቃችሁ
ማን ነው? ነገር ግን ስለ #ጽድቅ እንኩዋ መከራን
ብትቀበሉ #ብጹዓን ናችሁ:: ማስፈራራታቸውንም አትፍሩ:
አትናወጡም:: ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስን
በልባችሁ ቀድሱት:: +"+ (1ዼጥ.3:13)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
✞✞✞ እንኩዋን #ለቅዱስ_ጐርጐርዮስ_መነኮስ_ለቅድስት_ክርስቶስ_ሠምራ_እና_ለቅዱስ_አድሊጦስ_ሐዋርያ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

✞✞✞ #ቅዱስ_ጐርጐርዮስ_መነኮስ ✞✞✞

=>በዚህ ስም ተጠርተው: ለምዕመናን አብርተው ያለፉ አባቶቻችን ብዙ ናቸው:: ለምሳሌም:-
*ጐርጐርዮስ ዘኑሲስ
*ጐርጐርዮስ ነባቤ መለኮት
*ጐርጐርዮስ ዘሮሜ
*ጐርጐርዮስ መንክራዊ
*ጐርጐርዮስ ዘአርማንያ
*ጐርጐርዮስ ረዓዬ ኅቡዓትን መጥቀስ እንችላለን::

+ከእነዚህ ዐበይት ጐርጐርዮሶች አንዱ ገዳማዊው ቅዱስ ዛሬ የሚከበረው ነው:: ቅዱስ ጐርጐርዮስ የተወለደው በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን በላይኛው ግብጽ አካባቢ ነው:: ወላጆቹ እጅግ ባለ ጠጐች በመሆናቸው የሚፈልገውን ሁሉ አሟልተው አሳድገውታል::

+በተለይ ደግሞ ሥጋዊ (የዮናናውያንን ጥበብ) እንዲማር አድርገው ወደ #ቤተ_ክርስቲያን ሰደውታል:: በዚያም ትምሕርተ ቤተ ክርስቲያንን ከሥርዓቱ ጋር አጥንቶ እጅግ አንባቢ ስለ ነበረ #አናጉንስጢስ (አንባቢ) ሆኖ ተሾመ::

+አንባቢ በሆነባቸው ዘመናትም ወጣ ገባ ሳይል ያገለግል ነበርና ጣዕመ #መንፈስ_ቅዱስ አደረበት:: ስለዚህም አንደበቱ ጥዑም (ለዛ ያለው) ነበር:: ትንሽ ቆይቶም አበው 'ይገባሃል' ብለው ዲቁናን ሾሙት:: አሁንም ታጥቆ ያለ ዕረፍት ማገልገሉን ቀጠለ::

+ዘመኑ ነጫጭ ርግቦች (የተባረኩ መነኮሳት) የበዙበት ነበርና ቅዱስ ጐርጐርዮስ አዘውትሮ ወደ ገዳም እየሔደ ይጐበኛቸው: በእጆቻቸውም ይባረክ ነበር:: በተለይ #ሊቀ_ምኔት ታላቁ ቅዱስ ዻኩሚስ (#አባ_ባኹም) በቅርቡ ነበርና ሁሌ እየሔደ ይጨዋወተው ነበር::

+ትንሽ ቆይቶ ግን ቅዱሱ የምናኔ ፍላጐቱ እየጨመረ ሔደ:: አንድ ቀን ከገዳም ውሎ ሲመለስ ወላጆቹ ጥያቄ ጠየቁት::
"ልናጋባህ እንፈልጋለንና ምን ትላለህ?" አሉት:: እርሱም ጭራሹኑ እንደማይፈልግ መለሰላቸው:: ሊያሳዝኑት አልፈለጉምና ድጋሚ አልጠየቁትም::

+ትንሽ ቆይተውም ተከታትለው ዐረፉ:: ቅዱስ ጐርጐርዮስ ወላጆቹን ቀብሮ: ሃብት ንብረቱን ሸጦ ጉዞ ጀመረ:: ወደ #አባ_ዻኩሚስ ደርሶም ያን ሁሉ ገንዘብ በታላቁ ቅዱስ ፊት አፈሰሰው:: "ምን ላድርገው ልጄ?" ቢለው "አባቴ! ፈጣሪህ ያዘዘውን" አለው::

+አባ ዻኩሚስም መነኮሳት በመብዛታቸው ቤት አልነበረምና ብዙ ቤቶችን አነጸበት:: የቅዱሱ ገንዘብ ገዳም ከታነጸበት በሁዋላ ምናኔን አንድ ብሎ ጀመረ::

+ቅዱሱ ባጭር ታጥቆ: በጾምና ጸሎት: ውሃ በመቅዳት: በመጥረግ: ምግብ በማዘጋጀት: እግዚአብሔርንም አበውንም አስደሰተ:: ቅዱሱ ምንም ቢናገሩት አይመልስም:: ማንንም ቀና ብሎ አያይም::

+"እሺ" ከማለት በቀር ትርፍ ቃል አልነበረውም:: በጸሎት እንባው: በስግደት ደግሞ ላቡ ይንቆረቆር ነበር:: ፍቅሩ: ትዕግስቱ: ትሕትናውና ታዛዥነቱ እጅግ ብዙ ዓለማውያንን ማረከ:: ስለ እርሱ የሰሙ ኃጥአን ሔደው ምንም ሳይናገራቸው በማየት ብቻ ይማሩ ነበር:: ፊቱ ብሩህ: ደግና ቅን በመሆኑ እርሱን ማየቱ በቂ ነበር::

+ለ13 ዓመታት በገዳመ ዻኩሚስ ከተጋደለ በሁዋላ ወደ ገዳመ #ቅዱስ_መቃርስ ከ2ኛው አባ መቃርስ ጋር ተጉዋዘ:: በዚያም በዓት ወስኖ ከሰው ጋር ሳይገናኝ 7 ዓመታትን አሳለፈ:: በጸጋ ላይ ጸጋ: በበረከት ላይ በረከት ሆኖለት በ22ኛ ዓመቱ አባቶችን ሰበሰባቸው::

+መንገድ ሊሔድ መሆኑን ነግሯቸው "በጸሎት አስቡኝ" አላቸው:: በማግስቱ በዚህ ቀን ሲመጡ ግን በፍቅር ዐርፎ አገኙት:: መነኮሳትም በክብር ገንዘው: ከበረከቱ ተሳትፈው: በታላቅ ዝማሬ ቀብረውታል::

+"+ #ቅድስት_ክርስቶስ_ሠምራ +"+
=>ኢትዮዽያዊቷ #ቅድስት_እናት_ክርስቶስ_ሠምራ ቅንነቷ: ደግነቷና ቅድስናዋ እጅግ የበዛ ነው:: አንድ ቀን ግን ገና በትዳር ውስጥ እያለች: ከአገልጋዮቿ አንዷን ትጠራትና ታዛታለች:: ያቺ አገልጋይ ግን የታዘዘችውን ጀሮ ዳባ ልበስ ብላ ሳትታዘዛት ትቀራለች::

+ደጋግማ ብትነግራትም ልትሰማት አልቻለችም:: ያን ጊዜ ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ልትገስጻት ብላ ጠጠር ብትወረውርባት ያች አገልጋይ ወድቃ ሞተችባት:: ቅድስቲቱ እጅግ ደንግጣ አለቀሰች:: የምታደርገውንም አጣች::

+ወዲያው ግን ፈጠን ብላ: ወገቧን ታጥቃ ትጸልይ ጀመረች:: "ጌታየ ሆይ! ከሞት አስነሳልኝና ዓለምን ትቼ በቀሪ ዘመኔ አንተን አገልለግልሃለሁ" ብላ ፈጣሪን በብዙ እንባ ተማጸነችው:: ያን ጊዜም አገልጋዩዋ ከሞት ተነሳችላት::

+ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ጊዜን አላጠፋችም:: ልጆቿን በቤት ትታ: ሃብትን ብረቷን ንቃ: አንድ ልጇን አዝላ: ቤቷን እንደ ተከፈተ ትታው ወደ ገዳም ወጣች:: በዚህ ዕለትም (መስከረም 24 ቀን) ወደ #ደብረ_ሊባኖስ ገዳም ገባች::

+"+ #ቅዱስ_አድሊጦስ_ሐዋርያ +"+

=>ቅዱሱ ሐዋርያ ተወልዶ ያደገው በግሪክ #አቴና (ATHENS) ውስጥ ሲሆን በነገድ እሥራኤላዊ ነው:: በአደገባት አቴና ከተማ ሥርዓተ ኦሪትን ከወገኖቹ: የግሪክን ፍልስፍና ደግሞ ከአርዮስፋጐስ ተምሯል:: #መድኃኔ_ዓለም ዘመነ ስብከቱ ሲጀምር ግን አድሊጦስ ወደ #ኢየሩሳሌም ሔዶ አደመጠው: ተማረከበትም::

+ወዲያውም "ጌታ ሆይ! ልከተልህ?" ሲል ጠየቀው:: ልብን የሚመረምር ጌታም ፈቅዶለት ከ72ቱ አርድእት ደመረው:: ከዚያም ከጌታችን ዘንድ ተምሮ: መንፈስ ቅዱስንም ተቀብሎ: ለወንጌል አገልግሎት ተሠማርቶ በርካታ አሕዛብን አሳምኗል:: በመጨረሻም ተወልዶ ባደገባት አቴና በዚህች ቀን ገድለውታል::
=>አምላከ ቅዱሳን በትእግስት: በፍቅርና በትሕትና ይሸልመን:: ከበረከታቸውም ያድለን::

=>መስከረም 24 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ጐርጐርዮስ ገዳማዊ
2.ቅድስ ክርስቶስ ሠምራ (ደብረ ሊባኖስ የገባችበት)
3.ቅዱስ አድሊጦስ ሐዋርያ (ከ72ቱ አርድእት)
4.አቡነ ሰላማ

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት (መምሕረ ትሩፋት)
2.ቅዱስ ቶማስ ዘመርዐስ
3.አቡነ ዘዮሐንስ ጻድቅ ዘክብራን
4.ቅዱስ አጋቢጦስ (ጻድቅ ኤዺስቆዾስ)
5.ቅዱስ አብላርዮስ ታላቁ
6."24ቱ" ካኅናተ ሰማይ (ሱራፌል)
7.ቅዱስ አባ ሙሴ ጸሊም (ኢትዮዽያዊ)

=>+"+ #ፍቅር ያስታግሳል:: ፍቅር ያስተዛዝናል:: ፍቅር አያቀናናም::ፍቅር አያስመካም:: ፍቅር አያስታብይም:: ብቻዬን ይድላኝ አያሰኝም:: አያበሳጭም:: ክፉ ነገርን አያሳስብም:: ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል እንጂ ስለ ዓመፃ ደስ አይለውም:: ሁሉን ይታገሣል:: ሁሉን ያምናል:: ሁሉን ተስፋ ያደርጋል:: በሁሉ ይጸናል:: +"+ (1ቆሮ. 13:4)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
ነገ 12 ሰአት ላይ በyoutube ቻናላችን በፈለገ ጥበብ ሚዲያ እንገናኝ ድንቅ የአባቶቻችንን ወረብ ይዘንላችሁ መተናል እስከዛው ለቅምሻ ያክል ከስር ያለውን ቪዲዬ ይዘን መተናል መልካም ምሽት አደራ ለጓደኞቻችሁ ማጋራት እንዳይረሳ👍👍👍

ደህሞ ደግሞ ስለ ማዕተም እና ማማተብ ማወቅ ከፈለጋችሁ ከስር ዲስክሪብሽን ላይ አስቀምጠንላችዋል🫱https://youtu.be/RmnbDlH2zWg
††† እንኳን ከዘመነ ክረምት ወደ ዘመነ መጸው አሸጋግሮ ለቅዱስ ዮናስ ነቢይ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ስንዱ #እመቤት #ቤተ_ክርስቲያን (ሃገራችን) ሁሉ ነገሯ በሥርዓት ነውና ዓመቱን በዘመናት ከፍላ ትጠቀማለች:: እሊሕም ዘመናት #መጸው (ጽጌ): #ሐጋይ (በጋ): #ጸደይ (በልግ) ና ክረምት ናቸው:: ዘመናቱ ወቅቶችን ከመለየትና ማሳወቅ ባሻገር የእኛ ሕይወትም ምሳሌዎች ናቸውና ልብ ልንላቸው ይገባል::

#ዘመነ_መጸው / #ወርኀ_ጽጌ/ #ጥቢ እየተባለም ይጠራል:: በዚህ ወቅት ምድር በአበባ የምታጌጥበት: ክረምት የተለፋበት አዝመራ የሚደርስበት በመሆኑ ደስ ያሰኛል:: በጊዜውም:-
1.የእመቤታችን የቅድስት #ድንግል_ማርያም ስደቷ ይታሠባል:: እርሷ ስለ እኛ:-
*የሕይወት እንጀራን ተሸክማ መራቧን::
*የሕይወት መጠጥን ይዛ መጠማቷን::
*የሕይወት ልብስን አዝላ መራቆቷን::
*ሙቀተ መንፈስ ቅዱስን የሚያድለውን ተሸክማ ብርድ መመታቷን እናስባለን::
*ዘመኑ የበረከት ነው::

2.በሌላ በኩል ጊዜው ወርኀ ትፍሥሕት (የደስታ ወቅት) ነው:: በክረምት የደከመ ዋጋውን አግኝቶ: በልቶ: ጠጥቶ ደስ ይለዋልና:: ያልሠራው ግን ከማዘን በቀር ሌላ እድል የለውም:: ይኼውም ምሳሌ ነው::

ዘመነ ክረምት የዚህ ዓለም ምሳሌ: ዘመነ መጸው ደግሞ የመንግስተ ሰማያት:: በዚህ ዓለም ምግባር ትሩፋትን የሠራ በወዲያኛው ዓለም ተድላን ሲያደርግ ሰነፎች ኃጥአን ግን እድል ፈንታቸው: ጽዋ ተርታቸው ከግብዞች ጋር የመሆኑ ምሳሌ ነው::

በወርኀ ትፍስሕት እንደ ሊቃውንቱ እንዲህ ብለን ልንጸልይ ይገባል::
"ድኅረ ኀለፈ ክረምት ወገብአ ዝናም: ዘአስተርአይከ እግዚኦ ጽጌያተ ገዳም:
አፈወ ሃይማኖት ነአልድ ወፍሬ ምግባር ጥዑም:
አትግሃነ ለስብሐቲከ ከመ ትጋሆሙ አዳም:
ለጽብስት ንሕብ ወነአስ ቃሕም::"

††† የዘመናት ባለቤት ዘመነ መጸውን #ወርኀ_ትፍስሕት ያድርግልን::

††† ቅዱስ ዮናስ ነቢይ †††

††† ዮናስ ማለት 'ርግብ: የዋህ' ማለት ሲሆን ከ12ቱ #ደቂቀ_ነቢያት አንዱ ነው:: በሰራፕታ ተወልዶ ያደገው ነቢዩ በልጅነቱ ታሞ ሙቶ ነበር:: ታላቁ ነቢይ #ኤልያስ ግን 7 ጊዜ ጸሎት አድርጐ ከሞት አስነስቶታል:: (1ነገ. 17:17) እናቱ የሰራፕታዋ መበለትም ደግ ሴት ነበረች::

ቅዱስ ዮናስ በእድሜው ከፍ ሲል የቅዱስ ኤልያስ ደቀ መዝሙር ሆነ:: የነ ኤልሳዕና አብድዩም ባልንጀራ ነበረ:: ነቢየ እግዚአብሔር ኤልያስ ካረገ በሁዋላ: ቅ.ል.ክርስቶስ በ800 ዓመት አካባቢ የነነዌ ሰዎች ኃጢአት ከመሥፈርቱ በማለፉ የእግዚአብሔር ቃል ወደ አማቴ ልጅ ወደ ዮናስ መጣ::

"ሒድና ለነነዌ ሰዎች ንስሃን ስበክላቸው" አለው:: ከነቢያት ወገን ከሙሴና ከዳዊት ቀጥሎ የዮናስን ያህል የዋህ (ገራገር) የለምና እንቢ አለ (ሰምቶ ዝም አለ):: #እግዚአብሔር እየደጋገመ ሲናገረው ግን "እንዲህ የሚዘበዝበኝ ከፊቱ ብቀመጥ አይደል!" ብሎ ወደ #ተርሴስ ኮበለለ::

ወገኖቼ አንድ ነገርን ልብ እንበል:: እንኩዋን ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዮናስ እኛ ክፉዎችም ከጌታ ፊት መሸሸት እንደማይቻል ጠንቅቀን እናውቃለን:: ታዲያ ለምን ሸሸ ቢሉ:- ጥበበ እግዚአብሔር በውስጡ ስለ ነበረበት ነው::

ምክንያቱም ዮናስ በአሣ አንበሪ ሆድ 3 ቀን እና ሌሊት ኖሮ: ሙስና (ጥፋት) ሳያገኘው መውጣቱ ለጌታ ትንሳኤ ጥላ (ምሳሌ) ነው:: ለዚህም ምስክሩ ራሱ ጌታችን ነው::
"ወበከመ ነበረ #ዮናስ ውስተ ከርሠ አንበሪ ሠሉሰ ዕለተ ወሠሉሰ ለያልየ: ከማሁ ይነብር ወልደ እጉዋለ እመ ሕያው ውስተ ልበ ምድር ሠሉሰ ዕለተ: ወሠሉሰ ለያልየ" እንዲል:: (ማቴ. 12:39)

ቅዱስ ዮናስ በገንዘቡ ዋጅቶ ወደ መርከብ በገባ ጊዜ ታላቅ ማዕበል ሆነ:: የእምነት ሰው ነውና እንዲያ እየተናወጡ እርሱ በእርጋታ ተኝቷል:: እነርሱ ግን ቀስቅሰው ቢጠይቁት (እጣ ወድቆበታልና) "የእኔ ጥፋት ስለ ሆነ ወደ ማዕበሉ ጣሉኝ" አላቸው::

እያዘኑ ቢጥሉት ታላቅ ጸጥታ ሆነ:: እነዚያ አሕዛብም እግዚአብሔርን በመስዋዕትና በስዕለት አከበሩ:: ዮናስ ግን በማዕበልና በአሣ አንበሪ ሆድ ውስጥ ለ3 ቀናት ጸለየ:: አሣ አንበሪው በ3ኛው ቀን ወደ ነነዌ ተፋው::

ቅዱሱም "እስከ ሠሉስ ዕለት ትትገፈታእ #ነነዌ ዐባይ ሃገር" እያለ ንስሃን ሰበከ:: የነነዌ ሰዎች ኃጢአታቸውን አምነው ቢጸጸቱ ከሰማይ ወርዶ ከደመና ደርሶ የነበረው የእሳት ማዕበል ተመልሶላቸዋል::

የነቢዩ ትንቢት ግን አልቀረምና ታላቋ ነነዌ ከ300 ዓመታት በሁዋላ ጠፍታለች:: ቅዱስ ዮናስ ግን በቀሪ ዘመኑ ፈጣሪውን እያገለገለ ኑሯል:: ጠቅላላ እድሜውም 170 ዓመት ነው::

††† አምላከ ቅዱስ ዮናስ እድሜ ለንስሃ: ዘመን ለፍስሃ አይንሳን:: ከበረከቱም ይክፈለን::

††† መስከረም 25 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ጸአተ ክረምት (የክረምት መውጫ)
2.ቅዱስ ዮናስ ነቢይ
3.ቅዱስ እንጦንዮስ
4.ቅድስት በርባራ
5.ሐዋርያት ዼጥሮስ ወዻውሎስ
6.ቅዱስ ዕፀ መስቀል

††† ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ መርቆሬዎስ ሰማዕት
2.ቅድስት ቴክላ ሐዋርያዊት
3.ቅዱስ አበከረዙን ሰማዕት
4.ቅዱስ ዱማድዮስ ሶርያዊ
5.አቡነ አቢብ (አባ ቡላ)
6.ቅዱስ አባ አቡፋና ጻድቅ
7.ታላቁ አባ ቢጻርዮን ገዳማዊ

††† "ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል:: ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም:: ዮናስ በአሣ አንበሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ነበረ: እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል:: የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነስተው ይፈርዱበታል:: በዮናስ ስብከት ንስሃ ገብተዋልና:: እነሆም ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ::" †††
(ማቴ. 12:39)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
📌📌📌📌📌📌📌📌📌📌