ፈለገ ጥበብ ሚዲያ felegetbeb media
986 subscribers
8.71K photos
102 videos
110 files
1.31K links
ይህ ቻናል የደብረ ዘይት ደብረ መዊዕ ቅዱስ ሚካኤል ወ ደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል ፈለገ ጥበብ ሰንበት ት/ቤት የመረጃ ሚዲያ እና ህዝብ ግንኙነት ክፍል ሲሆን ይህ ቻናል ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የሆኑ አስተምህሮቶች በየእለቱ የሚለቀቅበት ቻናል ነው ቻናላችን ስለተቀላቀሉ በእግዚአብሔር ፅኑ ፍቅር እናመሰግናለን ።

#የፈለገ_ጥበብ_ሰንበት_ትምህርት_ቤት_የመረጃ_ሚዲያ_እና_ህዝብ_ግንኙነት_ክፍል
#FTM
Download Telegram
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

❖ ግንቦት 6 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

+"+ አባ መቃርስ ካልዕ +"+

+ይህ ቅዱስ "መቃርዮስ: መቃርስ: መቃሬም" ይባላል::
ትርጉሙ በ3ቱም መንገድ አይለወጥም:: ምክንያቱም
ሥርወ ቃሉ
በዮናኒ ልሳን "ብጹዕ: ንዑድ: ክቡር" ማለት ነውና::

+ከስሙ ቀጥሎ "ካልዕ-2ኛው": አንዳንዴ ደግሞ
"እስክንድርያዊ" እየተባለ ይጠራል:: "ካልዕ-2ኛው"
የሚባለው ከቀዳሚው
(ታላቁ መቃርስ) ለመለየት ሲሆን "እስክንድርያ" ደግሞ
ተወልዶ ያደገባት ሃገር ናት::

+አባ መቃርስ በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን የነበረ ገዳማዊ:
ጻድቅና ትሩፈ-ምግባር ነው:: በዓለም ለ40 ዓመት ሲኖር
እንደ ሕጉ
ፈጣሪውን ደስ ያሰኘ ሰው ነው:: ጻድቃን እንደ ከዋክብት
በበዙበት በዚያ ዘመን የታላቁ መቃርስን ዜና ሰምቷልና
ይህቺን
ክፉ ዓለም ከነግሳንግሷ ንቋት በርሃ ገብቷል::

+እንደሚገባ ሥርዓተ ገዳምን ጠብቆ: ለአበው ታዞ:
በጾም: በጸሎት: በትሕትናና በስግደት ተጠምዶ ቢያገኘው
ፈጣሪ አከበረው::
በዚያ ጊዜም ለታላቁ ገዳመ አስቄጥስ መናንያን አበ
ምኔት ሊሆን መረጡት::

+እርሱም እረኝነትን ያውቃልና በጐቹን (መነኮሳትን)
ከተኩላ (ሰይጣናት) ይጠብቅ ዘንድ ብዙ ተጋ:: ከብቃቱ
የተነሳም
ሳያስታጉል: ሳይበላ: ሳይጠጣና ሳይቀመጥ እስከ 40 ቀን
ይጸልይ ነበር:: ሲጸልይ ደግሞ በልቡ እየተቃጠለ በፍቅረ
ክርስቶስ ነበርና አጋንንት ይርዱለት ነበር::

+እርሱ ጸሎት ሲጀምርም በገዳሙ ዙሪያ ያሉ አጋንንት
እየጮሁ ይሸሹ ነበር:: ከተጋድሎው ጽናትና ከትሕትናው
ብዛት የተነሳ
ያዩት ትዕቢተኞች ሁሉ ይገሠጹ ነበር:: በዘመኑም ብዙ
ተአምራትን ሠርቷል::

+አንድ ቀን በበዓቱ ሳለ ጅብ መጥታ ተማጸነችው::
አብሯት ወደ ዋሻዋ ቢሔድ ልጆቿ በሙሉ ዓይነ ሥውራን
ሆነው አገኛቸው::
እርሱም ወደ መሬት ምራቁን እትፍ ብሎ በጭቃ ለውሶ
ቢቀባቸው የሁሉም ዐይናቸው በርቷል::

+ስለ ውለታውም ጅቢቱ የበግ ቆዳ እየጐተተች አምጥታ
ሰጥታዋለች:: (ከሰው ልጅ በቀር እንስሳት ውለታን
አይረሱምና) ቅዱስ
መቃርስም ለወትሮው ባዶው መሬት (አፈር) ላይ ይተኛ
የነበረው ከዚያ ቀን በኋላ በአጐዛው ላይ የሚተኛ ሁኗል::

+በሃገሩ እስክንድርያም ለ2 ዓመታት ዝናብ በመጥፋቱ
ሕዝቡ ተጨንቆ ነበርና "ናልን" ሲሉ መልዕክት ላኩበት::
እርሱ መጥቶ
ሲጸልይም መብረቅ የቀላቀለ ዝናብ ጣለ:: ዝናቡም ያለ
ማቆም ለ2 ቀናት በመዝነቡ ሕዝቡ ፈርተው "አባታችን ስለ
ኃጢአታችን
እንዳንጠፋ ለምንልን?" አሉት:: እርሱም በጸሎቱ
(በፈጣሪው ኃይል) እንደ ወደዱት ዝናቡን አቁሞላቸዋል::

+የአባ መቃርስን ዜና ሕይወትና ተአምራት ተናግሬ
አልፈጽመውም:: ግን አንዲት ብቻ ላክል:: ሁሌ ሳስበው
ስለሚገርመኝም
ነው::

+ብዙዎቻችን የጌታችን ሥጋና ደም አንቀበልም:: ለምን
ያከበርነውና የፈራነው አስመስለን ኃጢአትን ለመጥገብ
ቦታን (
አጋጣሚን) ስለምንፈልግ:: በተቃራኒው ደግሞ
አንዳንዶቻችን መለኮት የተዋሐደውን የጌታ ሥጋና ደም
እንደ ተርታ ነገር (ያለ
ጥንቃቄ) ስንቀበል ይታያል:: 2ቱም ግን ስሕተት ነው::

+ፈርተን (ፍርሃቱ ጤነኛ ባይሆንም) ስለ ራቅን በፍርድ ቀን
ማምለጥ አንችልም:: "ሥጋየን ያልበላ: ደሜንም ያልጠጣ
የዘለዓለም ሕይወት የለውም" ይለናልና:: (ዮሐ. 6:52)

+በድፍረት ለምንቀበልም ሥጋው እሳት ሁኖ እንዳይበላን:
ደሙም ባሕር ሆኖ እንዳያሰጥመን ልናከብረው ይገባናል::
"ሳይገባው
ከጌታ ሥጋና ደም የተቀበለ የጌታ ሥጋ ዕዳ አለበት"
ይለናልና:: (1ቆሮ. 11:27)

<< ታዲያ የሚሻለው ለሁላችንም ንስሃ ገብቶ: በፍርሃት
ሆኖ መቅረቡ ነው:: >>

+ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና አባ መቃርስ ወደ በርሃ
እንደ ገባ ሥጋ ወደሙን ተቀብሎ ነበር:: ቅዱሱ ይህንን
እያሰበ
ለ60 ዓመታት ምራቁን ሳይተፋ ኑሯል:: ለዚያ አይደል
አበው "ብታከብሩት ያከብራቹሃል" ያሉት::

+ሊቃውንቱም ይህንን ሲያደንቁ:-
"ኢታስተማስልዎ ለቁርባን ከመ ሕብስት ዕራቆ::
አኮኑ ሥጋ መለኮት ዘይትላጸቆ::
መቃርዮስ አብ ዕበየ ቁርባን ለአጠይቆ::
ድኅረ ተወክፈ በአሚን እንበለ ያብዕ ናፍቆ::
መጠነ ዓመታት ስሳ ኢተፍአ ምራቆ::" ብለዋል::

+ቅዱስ መቃርስም በ100 ዓመቱ በ5ኛው ክ/ዘመን
መጀመሪያ አካባቢ በዚህች ቀን ዐርፏል::

❖ጌታችን ከክብሩ: ከበረከቱ አይለየን::

=>ግንቦት 6 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ አባ መቃርስ ገዳማዊ
2.እናታችን ቅድስት ሰሎሜ ኢትዮዽያዊት
3.አባ ይስሐቅ ጻድቅ
4.ቅድስት ዲላጊና 4 ሴት ልጆቿ (ሰማዕታት)
5.ቅዱስ ዳናስዮስ ሰማዕት
6.ቅዱስ በንደላዖስ ሰማዕት (የታላቁ ኤስድሮስ አባት)
7.አባ አሞን ጻድቅ (ዽዽስናን አልፈልግም ብሎ የሸሸ አባት)

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅድስት ደብረ ቁስቁዋም
2.አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን
3.አባታችን ኖኅና እናታችን ሐይከል
4.ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ
5.ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ
6.ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ
7.ቅድስት ሰሎሜ
8.አባ አርከ ሥሉስ
9.አባ ጽጌ ድንግል
10.ቅድስት አርሴማ ድንግል

=>+"+ ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው:: እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሳዋለሁ:: ሥጋዬ እውነተኛ መብል: ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና:: ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል:: እኔም በርሱ እኖራለሁ:: +"+ (ዮሐ. 6:53-56)

   <<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
https://t.me/felegetibebmedia
ስለቅዱስ ያሬድ ምን ያህል ያውቃሉ?

ልዩ እና የማይቀርበት ታላቅ መንፈሳዊ ጉባኤ በደብረዘይት ደብረ መዊዕ ቅዱስ ሚካኤል ወደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል አብያተክርስቲያናት ከግንቦት 9-11/2016 ዓ.ም ከምሽቱ 11:00 ሰዓት ጀምሮ።


🛑ሁላችንም ከላይ ያለውን poster በየሶሻል ሚዲያችን ላይ በማጋራት ከመርሀግብሩ እንዲሳተፍ ያድርጉ።

https://t.me/felegetibebmedia
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

❖ እንኳን አደረሳችሁ ❖

❖ ግንቦት 7 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ

=>በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከሐዋርያት ቀጥሎ የቅዱስ
አትናቴዎስን ያሕል ስለ ሃይማኖት የተዋጋ ቅዱስ ፈልጐ
ማግኘት አይቻልም::

❖ቅዱስ አትናቴዎስ ማን ነው?

+ቅዱስ አትናቴዎስ በቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት
በዘመነ ሰማዕታት መጠናቀቂያ በ300 አካባቢ(296)
እስክንድርያ
ግብፅ ውስጥ ነው የተወለደው:: ወላጆቹ አረማውያን
በመሆናቸው ክርስትናን አልተማረም ነበር::

+ሕጻን እያለ ለጭዋታ ከቤቱ ሲወጣ የክርስቲያን ልጆች
ሃይማኖታዊ ጨዋታ ሲጫወቱ ተመለከተ:: ሊቀላቀላቸው
ቢፈልግም
ክርስቲያን ባለመሆኑ ከለከሉት:: አትናቴዎስም ክርስቲያን
ልሁንና አጫውቱኝ ብሏቸው እሺ ስላሉት ሕጻናቱ ዕጣ
ተጣጣሉ::

+ላንዱ ቄስ: ላንዱም ዲያቆን መሆን ሲደርሳቸው
ለአትናቴዎስ ፓትርያርክ መሆን ስለ ደረሰው ሌሎቹ ሕጻናት
ይሰግዱለት ጀመር::
በአጋጣሚ ሕጻናቱ ይሕንን ሁሉ ሲያደርጉ የወቅቱ
ፓትርያርክ ቅዱስ እለ እስክንድሮስ በመገረም ያያቸው
ነበርና ለሕጻኑ
አትናቴዎስ ትንቢት ተናገረለት::

+ከዚያም የአትናቴዎስ አባቱ ሲሞት ሊቀ ዻዻሳቱ ከእናቱ
ወስዶ አጥምቆ: የሚገባውን መንፈሳዊ ትምሕርት ሁሉ
በልቡናው ላይ
ቀረጸበት:: ከዚሕ በኋላ ዲቁናን ሹሞ አስተምር አለው::
ምንም ሕጻን ቢሆንም ከሊቅነቱ: ከአመላለሱና ከአንደበቱ
ጣፋጭነት
የተነሳ የሰማው ሁሉ ይደነቅ ነበር:: ጸጋ እግዚአብሔር
በእርሱ ላይ አድራለችና::

+ቅዱስ አትናቴዎስ ሊቀ ዲቁና በተሾመ ወራት አርዮስ
ቤተ ክርስቲያንን በመረበሹ ኒቅያ ላይ 318ቱ ሊቃውንት
ሲሰበሰቡ
ጸሐፊ አድርገው ሾሙት:: በጊዜውም በዕድሜ የስንት
ጊዜ ትልቁ የሚሆነውን አርዮስን ተከራክሮ ምላሽ
አሳጣው::

ቅዱስ
አትናቴዎስ ከሊቃውንቱ ጋር ሆኖ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ
ወልደ አምላክ: እግዚአብሔር መሆኑን በአደባባይ
መሠከረ:: ጸሎተ
ሃይማኖትንም ያረቀቀው እርሱ ነው::

+ከዚሕ በኋላ የእስክንድርያ (የግብፅ) 20ኛ ፓትርያርክ
ሆኖ ተሾመ:: ቤተ ክርስቲያንን በመልካም እረኝነት ለ48
ዓመታት
ሲመግብ ብዙ መከራዎችን ተቀበለ:: ለ5 ጊዜ ከመንበሩ
አፈናቅለው ወደ በርሃ ሲያግዙት በስደት ከ15 ዓመታት
በላይ
አሳልፏል::

+በተሰደደባቸው ቦታዎች መከራን እየተቀበለ ያላመኑትን
አሳምኗል:: በጎቹ እንዳይባዝኑበት ደግሞ በጦማር
(በደብዳቤ)
ይጠብቃቸው ነበር:: ዛሬ በሃይማኖተ አበው የምናገኘው
ቃለ ሃይማኖት በዚሕ ዘመን የተጻፈ ነው::

+በወቅቱ የነበረው ንጉሥ (ትንሹ ቆስጠንጢኖስ) የአባቱን
(ታላቁ ቆስጠንጢኖስን) ዕረፍት ተከትሎ ነገሠ::

+ወዲያውም አርዮሳዊ መናፍቅ ሆነ:: ሃይማኖታቸው የቀና
አባቶችንም ያሳድድ ገባ:: ከአበው ቅዱሳን መካከል ግን
የዚህ
መከራ ቀዳሚው ገፈት ቀማሽ ታላቁ ሊቅ ቅዱስ
አንትናቴዎስ ነበር::

+በተለይ አንድ ጊዜ ንጉሡ ቅዱሱን ወደ በርሃ አግዞ:
መናፍቅ ዻዻስ በግብጽ ሹሞ: ብዙ ክርስቲያኖችን በግፍ
ሲያስገድል:
ቅዱሱን ለ6 ዓመታት አሰቃየው:: የወገኖቹ (የልጆቹን)
ስቃይ የሰማው ቅዱስ አትናቴዎስ ግን በድፍረት ወደ ቤተ
መንግስት
ገብቶ ተናገረው::

+2 አማራጭን አቅርቦ "ወይ ግደለኝና እንደ አባቶቼ
ሰማዕት ልሁን: ካልሆነ ግን ወደ መንጐቼ (ምዕመናን)
መልሰኝ" አለው::
መናፍቁ ንጉሥም ቢገድለው ብጥብጥ እንደሚነሳ
ስለሚያውቅ በስልት ሊያጠፋው ወሰነ::

+ቀዛፊ: መቅዘፊያ: ምግብና ውሃ በሌላት ጀልባ ውስጥ
ከቶም ሜዲትራኒያን ባሕር ውስጥ ጣለው:: ድንገት ግን
ከሰማይ
ጌታችን መላእክቱን አስከትሎ ወረደ::

+ሚካኤልና ገብርኤል ባሕሩን እየቀዘፍ: ሌሎች መላእክት
እየመገቡት በዚህች ቀን እስክንድርያ (ግብጽ) አድርሰውት
ተሠውረዋል:: ሕዝቡም በታላቅ ሐሴት እየዘመሩ
አባታቸውን ተቀብለውታል::

+ሐዋርያዊው ቅዱስ ስለ ኦርቶዶክስ ተዋግቶ: ብዙ
ስቃይንም ተቀብሎ በ373 ዓ/ም አካባቢ አርፏል:: ቤተ
ክስርቲያን
☞"ሊቀ
ሊቃውንት:
☞ርዕሰ ሊቃውንት:
☞የቤተ ክርስቲያን
(የምዕመናን) ሐኪም (Doctor of the Church):
☞ሐዋርያዊ" ብላ
ታከብረዋለች::

=>አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሊቁ በረከት አይለየን::
በምልጃውም ሃይማኖታችንን ይጠብቅልን::

=>ግንቦት 7 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ
2.የባሕታውያን አለቃ ታላቁ አባ ሲኖዳ (ጽንሰቱ)
3.ቅዱስ ዮሐንስ ጻድቅ (ሃብቱን: ንብረቱን: ልብሱን
ሳይቀር መጽውቶ ራቁቱን የተገኘ ደግ ሰው ነው)
4.አባ ሐርስዮስ ገዳማዊ

=>ወርሐዊ በዓላት
1.ሥሉስ ቅዱስ (አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ)
2.አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
3.አባ ሲኖዳ (የባሕታውያን አለቃ)
4.አባ ዳንኤል ዘገዳመ ሲሐት
5.አባ ባውላ ገዳማዊ
6.ቅዱስ አግናጥዮስ (ለአንበሳ የተሰጠ)

=>+"+ ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብጹዐን ናቸው:: መንግስተ
ሰማያት የእነርሱ ናትና:: ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ
በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ
ብጹዓን ናችሁ:: ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ
ይበላችሁ:: ሐሴትም አድርጉ:: ከእናንተ በፊት የነበሩ
ነቢያትን እንዲሁ አሳደዋቸዋልና:: +"+ (ማቴ. 5:10)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
https://t.me/felegetibebmedia
ከእለታት አንድ ቀን አንድ አባት ወደ አባታችን አባ መቃርዮስ በኣት ሄደና "አባቴ ሆይ ድኅነትን አገኝ ዘንድ ምን ላድርግ?" ሲል ጥያቄ አቀረበላቸው። አባታችንም እንዲህ በማለት አሉት።
"ወደ መቃብር ሂድና ሙታንን ሰድበሃቸው ና" አሉት። ይህ አባትም የተባለውን አድርጎ ተመለሰ። አባታችንም "ምን አሉህ?" ሲሉ ጠየቁት። ሰውየዉም "ምንም አልመለሱልኝም" ሲል መለሰ። አባ መቃርዮስም "አሁን ደግሞ ሂድና ሙታንን አመስግናቸው" አሉት። ሄዶም አመሰገናቸው። "አሁንስ ምን አሉህ" ሲል በድጋሚ ጠየቁት። ሰውዬም "ምንም አልመለሱልኝም" ሲል መለሰ። አባታችን አባ መቃርዮስም: "ስትሰድባቸው ፤ስታመሰግናቸው እና  ስታወድሳቸው ምንም አልመለሱም፤ አንተም ለነፍስህ ድህነትን ከፈለግህ እንደሞተ ሰው ሆነህ ኑር። ሰዎች ክፉ ቢያደርጉብህም፣ ቢያመሰግኑህም ምንም አይሰማህ" አሉት።
††† እንኳን ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጥንተ በዓለ ዕርገት እና ለጻድቁ አባ ዳንኤል ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ዕርገተ እግዚእ †††

††† ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዓለ ዕርገትን 2 ጊዜ ታከብራለች:: አንዱ "ጥንተ በዓል" : ሁለተኛው ደግሞ "የቀመር በዓል" ይሠኛል:: ጥንተ በዓል ማለት ጌታችን በትክክል ያረገበትን ቀን ያመለክታል::

የክብር ባለቤት መድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በኪነ ጥበቡ (በሕማሙ : በሞቱ) ዓለምን አድኖ: 40 ቀን ለሐዋርያቱ መጽሐፈ ኪዳንን: ትምሕርተ ኅቡዓትን አስተምሯቸዋል::

በ40ኛው ቀን 120ውን ቤተሰብ ይዟቸው ወደ ቢታንያ ወጣ:: በዚያም እስከ ሊቀ ዽዽስና ድረስ ሾሟቸው : ከኢየሩሳሌም እንዳይወጡም አዟቸው የመንፈስ ቅዱስን ተስፋ ጠብቁ ብሏቸዋል:: እየባረካቸው በተዋሐደው ሥጋ ወደ ሰማያዊ ዙፋኑ አርጓል::

ሰማያት: ምድር: ደመናት: ነፋሳት: መባርቅትና መላእክት: ፍጥረት በሙሉ አመስግኗል:: አይሁድ መናፍቃን ዕርገቱን ምትሐት ነው እንዳይሉ: ጌታችን ትንሳኤውን አማናዊ እንደሆነ ለማስረዳት በ40ኛው ቀን ዐረገ::

አንድም ራስ ባለበት ሌሎች የሰውነት ክፍሎች ሊኖሩ ይገባልና ጌታችን ዕርገቱን በገሃድ አደረገው:: "ዐርገ እግዚእ ከመ ያለቡ ዕርገተ ጻድቃን ንጹሐን" እንዲል::

††† ዐርገ እግዚአብሔር በይባቤ::
ወእግዚእነ በቃለ ቀርን::
ዘምሩ ለአምላክነ ዘምሩ:: †††
(መዝ. 46:6)

††† ታላቁ አባ ዳንኤል †††

††† ይህ ቅዱስ አባት ስም አጠራሩ ክቡር ነው:: በሁሉ ነገሩ የተቀደሰ የገዳማውያን መብራትም ነው:: ከተረፈ ንጹሕ ሕይወቱ ጣዕመ መንግስተ ሰማያትን አይቷልና:: አባ ዳንኤል በትውልድ ግብጻዊ ሲሆን ዓለምን ንቆ (መንኖ) ገዳም የገባው ገና በወጣትነቱ ነው::

ጊዜውም ዘመነ ጻድቃን (በ5ኛው መቶ ክ/ዘመን) ነበር:: በገዳመ አስቄጥስ እና በደብረ ሲሐት ይታወቃል:: ታላቋ መካነ ቅዱሳን ገዳመ ሲሐት ዛሬም ድረስ በስሙ የምትጠራ ሲሆን ለዚህም ምክንያቱ እጅግ ለብዙ ዘመናት በውስጧ ተጋድሎ ፍሬ ስላፈራባት : ደቀ መዛሙርትን በቅድስና ስለ ወለደባት ነው::

ስለዚህም ዛሬም ድረስ "አባ ዳንኤል ዘደብረ ሲሐት" ተብሎ ሲጠራ ይኖራል:: ሌላኛው ስሙ ደግሞ "ዘገዳመ አስቄጥስ" ይሰኛል:: ገዳመ አስቄጥስ የታላቁ ቅዱስ መቃርስ ርስት ሲሆን በዓለም በስፋትም : ብዙ ቅዱሳንን በማፍራትም አንደኛ የሆነ ገዳም ነው::

በዚህ ገዳም ላይ አበ ምኔት ሆኖ የሚሾሙ አበው ሁሌም የብቃት መዓርግ ላይ የደረሱ ሲሆኑ ክብራቸው ከፓትርያርክ በላይ ነው:: አባ ዳንኤልም ከብዙ የቅድስና ዓመታት በኋላ በአስቄጥስ ገዳም አበ ምኔት ሆኖ ተሹሞ እልፍ አእላፍ መነኮሳትን በጽድቅ መንገድ መርቷል::

ቅዱሱ ከትጋቱ የተነሳ ለምግብና ለእንቅልፍ ጊዜ አልነበረውም:: ቀን ቀን መነኮሳቱን ሲናዝዝ : ድውያንን ሲፈውስ : ሥርዓተ ገዳምን ሲቆጣጠር ይውላል:: ልክ ሲመሽ ጭው ወዳለውና ስውራን ወደ ሚገኙበት በርሃ ይወጣል::

+በዚያም ሙሉውን ሌሊት የተሰወሩ አባቶችን ሲፈልግ ያድር ነበር:: በዚህም ምክንያት የብዙ ስውራንን ገድል የጻፈ ሲሆን ባረፉ ጊዜም ገንዞ በመቅበር በረከታቸውን ተሳትፏል:: ታላቅ ሙያንም ፈጽሟል::

እርሱ ገንዞ ቀብሮ : ዜናቸውን ከጻፈላቸው ሥውራን ቅዱሳንም እንደ አብነት እሥራኤላዊቷን ቅድስት ዓመተ ክርስቶስን (ለ38 ዓመት ራቁቷን በሥውር የኖረች) እና ቅድስት በጥሪቃ ንግሥትን (መንግስቷን ትታ በሥውር የኖረች ናት) መጥቀስ እንችላለን::

ከዚህ ባለፈም አባ ዳንኤል በሰው ዘንድ የተናቁትንም ማክበርን ያውቅበታል:: ለምሳሌ በሴቶች ገዳም እብድ ናት ተብላ በበር የተጣለችውን ቅድስት አናሲማን : በእስክንድርያ ከተማ ሊቀ ዻዻሳቱ ሳይቀር "እብድ ነው" ብለው የናቁትን ቅዱስ ምሕርካን: እብድ ሳይሆኑ ራሳቸውን የሠወሩ ቅዱሳን መሆናቸውን ገልጧል::

አባ ዳንኤል ሐዋርያዊም ነበር:: በጊዜው ጦማረ ልዮን የሚባል የኑፋቄ ደብዳቤ ይላክ ነበርና ለዚህ ኬልቄዶናዊ ኑፋቄ በትጋት ምላሽ ይሰጥ ነበር:: አንድ ቀንም በንጉሥ ትዕዛዝ ኑፋቄው በእርሱ ገዳም ሊነበብ ሲል ቅዱሱ ከወታደሩ ቀምቶ ስለ ቀደደው ለሞት እስኪደርስ ደብድበውታል::

ጻድቁ አባ ዳንኤል አንዴ አውሎጊስ የሚባልድሃ ድንጋይ ጠርቦ እንግዳ ሲቀበል ተመልክቶ "ጌታ ሆይ! ይህንን ደግ ሰው ለምን ድሃ አደረከው?" ሲል በፈጣሪ ሥራ ገባ::

ጌታም እንደ ወትሮው በገሃድ ተገልጦ "በነፍስህ ትዋሰዋለህ?" አለው:: "አዎ ጌታየ" ስላለው ጌታችን ለአውሎጊስ ሃብትን ሰጠው:: ግን ወዲያው የጦር አለቃና ጨካኝ ሰው ሆነ::

ጻድቁ ወሬውን ሰምቶ ሊጠይቅ ቢሔድ የአውሎጊስ ወታደሮች ደበደቡት:: ጌታችንም አባ ዳንኤልን ወደ ፍርድ ዙፋኑ አቅርቦ "ወዳጄን መልስልኝ" አለው:: እመ ብርሃን ግን ቀርባ የልጇን እግር ሳመች::

"ልጄ ሆይ ማር!" አለችው:: ጌታም "እሺ" ብሎ ጻድቁን ወደ በአቱ: አውሎጊስን ወደ ቀደመ ግብሩ መለሳቸው:: የአባ ዳንኤል ድንቁ ብዙ ነው::

ሌላው ቢቀር ሽፍታ አባ ዳንኤልን መስሎ ወደ ደናግል ገዳም ሊዘርፍ : በማታለል ገባ:: ደናግሉም ጻድቁ መስሏቸው እግሩን አጥበው ዐይነ ስውሯን ቢቀቧት ዐይኗ በርቷል:: ሽፍታውም ደንግጦ ንስሃ ገብቷል:: አባ ዳንኤል ግን ተጋድሎውን ፈጽሞ በዚህች ቀን ዐርፏል::

††† በተረፈው ግን ከቅድስና ሕይወቱ ባሻገር:-
1.በገዳመ አስቄጥስ (ግብጽ) አበ ምኔት ሆኖ ተሹሞ ባሳየው ትጋት::
2.በሃይማኖት ጠበቃነቱ በደረሰበት ድብደባና ስደት::
3.ብዙ የበርሃ ቅዱሳንን በየበአታቸው እየዞረ በመቅበሩ::
4.የብዙ ስውራን ቅዱሳንን ዜና ሕይወት በመሰብሰቡ::
5.በየጊዜው በእግዚአብሔር ኃይል ይፈጽማቸው በነበሩ ተአምራት:: እና
6.ለድንግል እመቤታችን ማርያም በነበረው ልዩ ፍቅር ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታከብረዋለች::

††† ቸር አምላክ ክርስቶስ ከዕርገቱና ከጻድቁ በረከት አይለየን::

††† ግንቦት 8 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱሳን የጌታ ቤተሰብ (120ው)
2.ቅዱስ አባ ዳንኤል ጻድቅ
3.ቅዱስ ዮሐንስ ሰማዕት
4.ቅዱስ መክሲሞስ መስተጋድል
5.አቡነ ዮሐኒ ዘደብረ ዳሞ (አቡነ ተክለ ሃይማኖትንና አቡነ ኢየሱስ ሞዐን ለምንኩስና ያበቁ)

††† ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ሙሴ ሊቀ ነቢያት
2.ኪሩቤል (አርባዕቱ እንስሳ)
3.አባ ብሶይ (ቢሾይ)
4.አቡነ ኪሮስ
5.አባ ሳሙኤል ዘደብረ ቀልሞን
6.ቅዱስ ማትያስ ሐዋርያ (ከ12ቱ ሐዋርያት)

††† "እስከ ቢታንያም አወጣቸው:: እጆቹንም አንስቶ ባረካቸው:: ሲባርካቸውም ከእነርሱ ተለየ:: ወደ ሰማይም ዐረገ:: እነርሱም ሰገዱለትና በብዙ ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ:: ዘወትርም እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እየባረኩ በመቅደስ ኖሩ::" †††
(ሉቃ. 24:50-53)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
https://t.me/felegetibebmedia
«ወደ እግዚአብሔር የምንጸልየው፥ መረጃ ወይም መመሪያ ልንሰጠው ሳይሆን፥ ወደ እርሱ እንድንቀርብና ከእርሱ ጋር ኅብረት ያለን እንድንሆን ነው።»
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ

ሰናይ አዳር
#ፈለገ_ጥበብ_ሚዲያ
††† እንኳን ለእናታችን ቅድስት እሌኒ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† እሌኒ ንግሥት †††

††† ቅድስት እሌኒ የታላቁ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ እናቱና እግዚአብሔር ለበጐ አገልግሎት የጠራት ቡርክት ሴት (ንግሥት) ናት::
ጥንተ ነገሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-
የቅድስቲቱ ሃገረ ሙላዷ ሮሃ (ሶርያ) አካባቢ ነው:: ነገዷ ከእሥራኤል ዝርዋን እንደሆነም ይነገራል:: ጣልያኖች "Helena" : በእንግሊዝኛው "Helen" ይሏታል:: እኛ ደግሞ "እሌኒ" እንላታለን:: ትርጓሜው "ጥሩ ምንጭ" : አንድም "ውብና ደግ ሴት" ማለት ነው::

ቅድስት እሌኒ በመልካም ክርስትና አድጋ እንደ ቤተ ክርስቲያን መተርጉማን ተርቢኖስ የሚባል ነጋዴ አግብታ ነበር:: ወቅቱም ዘመነ ሰማዕታት ነበር:: በማይሆን ነገር ጠርጥሮ ባሕር ላይ ጥሏት ንጉሥ ቁንስጣ አግኝቷታል:: እርሱም የበራንጥያ (የኋላዋ ቁስጥንጥንያ) ንጉሥ ነበር::

ቅድስት እሌኒ ከቁንስጣ የተባረከ ልጅን ወለደች:: ቆስጠንጢኖስ አለችው:: በልቡናው ፍቅርን : ርሕራሄን : መልካምነትን እየዘራች አሳደገችው:: ቅዱሱ አባቱ በሞተ ጊዜ ተተክቶ ነገሠ::

ቅድስት እሌኒንም ንግሥት አደረጋት:: ያንን የአርባ ዓመት ግፍ በአዋጅ አስቀርቶ ለክርስቲያኖች ነፃነትን : ክብርን በይፋ ሰጠ:: አንድ : ሁለት ብለን የማንቆጥረውን ውለታ ለምዕመናን ዋለ:: ከነዚህ መልካም ምግባራቱ ጀርባ ታዲያ ቅድስት እናቱ ነበረች::

ቅድስት እሌኒ ጾምን : ጸሎትን ከማዘውተሯ ባሻገር አጽመ ሰማዕታትን ትሰበስብ : አብያተ ክርስቲያንን ታሳንጽ : ለነዳያንም ትራራ ነበር:: በኢየሩሳሌምና አካባቢው ብቻ ከሰማንያ በላይ አብያተ መቃድስ አሳንጻለች:: እነዚህንም በወርቅና በእንቁ ለብጣቸዋለች::

በዘመኗ መጨረሻም የጌታችንን ቅዱስ ዕፀ መስቀል ከተቀበረበት አውጥታ ለዓለም በረከትን አስገኝታለች::

እናታችን ቅድስት እሌኒ እንዲህ በቅድስና ተመላልሳ በሰማንያ ዓመቷ በ330ዎቹ አካባቢ ዐርፋለች:: ቤተ ክርስቲያናችንም ስለ ቅድስናዋና ውለታዋ በዓል ሠርታ : ታቦት ቀርፃ ስታከብራት ትኖራለች::

††† ከቅድስት እናታችን ምልጃና በረከት አምላካችን ያድለን::

††† ግንቦት 9 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅድስት እሌኒ ንግሥት
2.ቅዱስ ስልዋኖስ

††† ወርኀዊ በዓላት
1.አባ በርሱማ ሶርያዊ (ለሶርያ መነኮሳት ሁሉ አባት)
2.አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ (ኢትዮጵያዊ)
3.ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ቅዱሳን ሊቃውንት (ርቱዐነ ሃይማኖት ዘኒቅያ)
4.የብሔረ ብፁዐን ጻድቃን
5.አባ መልከ ጼዴቅ ዘሚዳ (ኢትዮጵያዊ)
6.ቅዱስ ዞሲማስ ጻድቅ (ዓለመ ብፁዐንን ያየ አባት)

††† "ነገር ግን ለበጐ ነገር ጥበበኞች : ለክፉትም የዋሆች እንድትሆኑ እወዳለሁ:: የሰላምም አምላክ ሰይጣንን ከእግራችሁ በታች ፈጥኖ ይቀጠቅጠዋል:: የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን::" †††
(ሮሜ. ፲፮፥፲፱)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
https://t.me/felegetibebmedia