Federal Ethics And Anti- Corruption Commission
9.89K subscribers
10.4K photos
246 videos
32 files
3.06K links
Download Telegram
በድሬዳዋ ከተማ በሕገ ወጥ ተከማችቶ የተገኘ ከ12 ሺህ ሊትር በላይ ቤንዚን ከሰባት ተጠርጣሪዎች ጋር ተያዘ

*******

(የፌ.ሥ.ፀ.ሙ.ኮ ጥር 8/2017 ዓ.ም አዲስ አበባ) በድሬደዋ ከተማ አስተዳደር በሕገ ወጥ መንገድ በቤት ውስጥ የተከማቸ ከ12 ሺህ ሊትር በላይ ቤንዚን ከሰባት ተጠርጣሪዎች ጋር መያዙን የአስተዳደሩ የንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው ሕገ ወጥ የነዳጅ ግብይት በሚፈፅሙ ማደያዎች ላይ ጥብቅና አስተማሪ እርምጃ የመውሰዱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል።

የድሬደዋ ንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ የነዳጅ ዋጋ ማሻሻያውን ተከትሎ በከተማው እየተካሄደ የሚገኘውን የነዳጅ አቅርቦትና ግብይት የተመለከተ መግለጫ ለመገናኛ ብዙሃን ሰጥቷል።

በቢሮው የንግድ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሚኖ ጠሃ እንደተናገሩት፤ በከተማዋ የሚገኙ ማደያዎች በተሻሻለው የነዳጅ ዋጋ መሠረት ነዳጅን በፍትሃዊነት ለተጠቃሚው እንዲያቀርቡ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ ይገኛል።

ነገር ግን አንዳንድ ማደያዎች መንግስት በከፍተኛ ድጎማ የሚያመጣውን ነዳጅ በሕገ ወጥ መንገድ እያሰራጩ መሆኑ ተደርሶበታል ብለዋል።

ችግሩን ለመከላከል እና ነዳጅን በፍትሃዊነት ለታለመለት አላማ ለማዋል የፀጥታና የፍትህ አካላት የተካተቱበት ግብረሃይል ተቋቁሞ የተቀናጀ ክትትል እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

በዚሁ መሰረተ በተደረገ ክትትል እና ህብረተሰቡ በሰጠው ጥቆማ በህገ ወጥ መንገድ በቤት ውስጥ ተከማችቶ የተገኘ ከ12 ሺህ 700 ሊትር ቤንዚን መያዙን ተናግረዋል።

ቤንዚኑን በመኖሪያ ቤታቸው የደበቁ እና በህገ ወጥ ተግባራት ላይ ተሰማርተዋል የተባሉ ሰባት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በህግ እየታየ መሆኑንም ተናግረዋል።

ነዳጅን በበርሜል በህገ ወጥ መንገድ ሲሸጡ የተደረሰባቸው ሁለት የነዳጅ ማደያዎች ሀላፊዎች በህግ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ ማድረጉን ገልጸዋል።

በእነዚህ አካላት ላይ አስተማሪ እርምጃ የሚወሰድባቸው መሆኑን ጠቅሰው ሌሎቹም ማደያዎች ከመሰል ህገ ወጥ ተግባር ራሳቸውን እንዲጠብቁ አሳስበዋል።

በህገ ወጥ ተግባራት ላይ በተሰማሩ ማደያዎች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ከሙስና የፀዳች እና የበለፀገች ኢትዮጵያን ዕውን እናድርግ!

#NCRS ሞባይል መተግበሪያ

#ለAndroid ስልክ ተጠቃሚዎች
https://play.google.com/store/apps/details

#ለApple or iPhone ስልክ ተጠቃሚዎች
https://apps.apple.com/us/app/ncrs/id6593662319
የ36 የመንግስት ሠራተኞች ወርሃዊ ደሞዝ በራሱ የባንክ አካዉንት እንዲገባለት ያደረገዉ የፋይናንስ ሠራተኛ በእስራት ተቀጣ

*******

(የፌ.ሥ.ፀ.ሙ.ኮ ጥር 8/2017 ዓ.ም አዲስ አበባ) በምስራቅ ሀረርጌ ዞን ግራዋ ወረዳ ዉስጥ በሀሰተኛ ሰነድ የ36 የመንግስት ሠራተኞች የወር ደሞዝ በራሱ የባንክ አካዉንት እንዲገባ ያደረገዉ የፋይናንስ ሠራተኛ በእስራት መቀጣቱን የምስራቅ ሀረርጌ ዞን አቃቤ ህግ ፅህፈት ቤት ገልጿል።

የፅህፈት ቤቱ መግለጫ እንደሚያሳየዉ ተከሳሽ አሊዬ ኡመር የግራዋ ወረዳ የፋይናንስ ፅህፈት ቤት የመንግስት ሠራተኞች የክፍያ አስተዳደር ባለሙያ ነዉ።

ተከሳሹ ያልተገባ ጥቅምን ለማግኘት ሲል የ36 የመንግስት ሠራተኞችን የአንድ ወር ደሞዝ 5 መቶ 29 ሺህ 639 ብር በራሱ አካዉንት ማስገባቱ በተደረገዉ የኦዲት ምርመራ ሊረጋገጥ ችሏል ተብሏል።

ተከሳሹ የካቲት 30/2016 ዓ.ም ለሠራተኞቹ የተዘጋጀዉን የደሞዝ ፔሮል መክፈያ ቅፅን ካፀደቀ በኃላ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ግራዋ ቅርንጫፍ በመሄድ የወንጀል ድርጊቱን መፈፀሙ ተረጋግጧል።

ከሀምሌ 1/2014 ዓ.ም ጀምሮ እስከ የካቲት 30/2016 ዓ.ም ድረስ በተደረገዉ የኦዲት ግኝት የተነሳ ወንጀሉ ሊጋለጥ እንደቻለ ተገልጿል።

የምስራቅ ሀረርጌ ዞን አቃቤ ህግ ፅህፈት ቤት የሙስና ወንጀሎችን ለመከላከል የወጣዉን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀፅ 23 በመጥቀስ ክስ መስርቷል።

ክሱን ሲከታተል የቆየዉ የምስራቅ ሀረርጌ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተከሳሹን ጥፋተኛ በማለት በ4 አመት ከ6 ወር እስራትና በ7 ሺህ ብር መቀጮ እንዲቀጣ የወሰነበት መሆኑን የምስራቅ ሀረርጌ ዞን አቃቤ ህግ ፅህፈት ቤት ገልጿል፡፡

ከሙስና የፀዳች እና የበለፀገች ኢትዮጵያን ዕውን እናድርግ!

#NCRS ሞባይል መተግበሪያ

#ለAndroid ስልክ ተጠቃሚዎች
https://play.google.com/store/apps/details

#ለApple or iPhone ስልክ ተጠቃሚዎች
https://apps.apple.com/us/app/ncrs/id6593662319
ጉቦ ሲቀበሉ እጅ ከፍንጅ የተያዙ 4 ባለሙያዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋሉ

*******

(የፌ.ሥ.ፀ.ሙ.ኮ ጥር 8/2017 ዓ.ም አዲስ አበባ) በዛሬው ዕለት በፖሊስ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት 3 ባለሙያዎች የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ አነስተኛ ግብር ከፋዮች የደረሰኝ ቁጥጥር ባለሙያዎች ናቸው።

የቅርንጫፍ ፅ/ቤቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሙሉ ኃይለሚካሄል እንደገለፁት በቁጥጥር ስር የዋሉት 3 የደረሰኝ ቁጥጥር ባለሙያዎች በወረዳ 7 አውቶቡስ ተራ አካባቢ ከቶፕ ውሃ ሽያጭ ባለሙያ በደረሰኝ ቁጥጥር 5 ሺህ ብር ጉቦ መቀበላቸው በአካባቢው ድርጊቱን ሲታዘቡ የነበሩ ሰዎች ባደረሰው ጥቆማ ነው።

ፖሊስ ከግለሰቦቹ በደረሰው ጥቆማ መሰረትም ከቁጥጥር ባለሙያዎቹ አስተባባሪ ቦርሳ በፍተሻ የተቀበሉት 5 ሺህ ብር በማግኘቱ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ አድርጓል ብለዋል ።

በአሁኑ ወቅትም ተጠርጣሪዎቹ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ መሆኑ ለማወቅ ተችሏል።

በተመሳሳይ የመርካቶ ቁጥር 1 መካከለኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ፅ/ቤት የታክስ ኦዲተር የሆነ ግለሰብ የ150 ሺህ ብር ጎቦ በመቀበሉ በቁጥጥር ስር ውሏል።

ተጠርጣሪው ግለሰብ በቁጥጥር ስር ሊውል የቻለው የፌዴራል ወንጀል ምርመራ በደረሰው ጥቆማ መሰረት በተደረገ ክትትል ሲሆን፣ ግብር ከፋዩ ለመንግስት መክፈል ያለበትን ግብር ለመቀነስ በመስማማት ከጠየቀው 150 ሺህ ብር 100 ሺህ ብሩ በቼክ መቀበሉም ተረጋግጧል።

ይሁንና ቀሪው 50 ሺህ ብር በጥሬ ገንዘብ ሲቀበል እጅ ከፍንጅ ተይዞ በአሁኑ ወቅት ጉዳዩ በህግ እየታየ መሆኑን ከአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ከሙስና የፀዳች እና የበለፀገች ኢትዮጵያን ዕውን እናድርግ!

#NCRS ሞባይል መተግበሪያ

#ለAndroid ስልክ ተጠቃሚዎች
https://play.google.com/store/apps/details

#ለApple or iPhone ስልክ ተጠቃሚዎች
https://apps.apple.com/us/app/ncrs/id6593662319
በክልሉ ከ372 ሚሊዮን ብር በላይ የተመዘበረ የህዝብ ሀብት ማስመለስ ተችሏል - ኮሚሽኑ

*******

(የፌ.ሥ.ፀ.ሙ.ኮ ጥር 9/2017 ዓ.ም አዲስ አበባ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 372 ሚሊዮን ብር በላይ የተመዘበረ የመንግስት እና የህዝብ ሀብት ማስመለስ መቻሉን የክልሉ የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ሶፎንያስ ደስታ እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት 36 የሙስና ጥቆማዎች ለተቋሙ ደርሰዋል።

በደረሰው ጥቆማ መሰረት 6 ሚሊዮን 908 ሺህ 789 ብር እዲሁም 8 የመንግስት ቤቶች፣ 1 ሀሰተኛ የይዞታ ማረጋገጫ እና ሌሎች የመንግስትና የህዝብ ሀብት በቅድመ መከላከል ስራ ማዳን መቻሉን ጠቁመዋል።

ኮሚሽኑ በ6 ወራት ባከናወነው የብልሹ አሰራር እና የፀረ-ሙስና ትግል ከ17 ሺህ ካሬ በላይ የከተማ መሬት፣ 30 ሄክታር የገጠር እርሻ ይዞታ እና ሌሎች የመንግስትና የህዝብ ሀብት ወደ መንግስት ካዝና እንዲመለሱ ማድረጉን አመልክተዋል።

በአጠቃላይ በግማሽ ዓመቱ 372 ሚሊዮን 945 ሺህ 11 ብር የተመዘበረ የመንግስትና የህዝብ ሀብት ማስመለስ ተችሏል ነው ያሉት ኮሚሽነሩ።

በተያያዘም በግማሽ ዓመቱ የ10 ሺህ አመራሮችና የመንግስት ሰራተኞች ሀብት ለመመዝገብ ታቅዶ የ11 ሺህ 03 አመራሮችና የመንግስት ሰራተኞች ሀብት መመዝገብ መቻሉንም ጠቁመዋል።

የፀረ-ሙስና ትግሉ የሁሉንም ዜጎች ርብርብ የሚጠይቅ ነው ያሉት ኮሚሽነር ሶፎንያስ፥ ሁሉም የክልሉ ነዋሪዎች አጠራጣሪ ነገር ሲገጥማቸው የተቋሙን ጥቆማ የመቀበያ አማራጮች በመጠቀም ግዴታቸውን እንዲወጡ ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ከሙስና የፀዳች እና የበለፀገች ኢትዮጵያን እውን እናድርግ!

#NCRS ሞባይል መተግበሪያ

#ለAndroid ስልክ ተጠቃሚዎች
https://play.google.com/store/apps/details

#ለApple or iPhone ስልክ ተጠቃሚዎች
https://apps.apple.com/us/app/ncrs/id6593662319
ኮሚሽኑ ከብልፅግና ፓርቲ የኢንስፔክሽን እና ሥነምግባር ኮሚሽን ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረመ

*******

(የፌ.ሥ.ፀ.ሙ.ኮ ጥር 9/2017 ዓ.ም ቢሸፍቱ) የፌደራል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን በመልካም ሥነምግባር የታነፀ አመራርና አባላት ለማፍራት የሚያስችለውን ስምምነት ከብልፅግና ፓርቲ የኢንስፔክሽን እና ሥነምግባር ኮሚሽን ጋር ተፈራርሟል።

የፌደራል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሳሙኤል ኡርቃቶ (ፒኤችዲ) ኮሚሽኑ በትውልድ ሥነምግባር ግንባታና ሙስና መከላከል ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

የብልፅግና ፓርቲ ካለዉ ሰፊ የአደረጃጀት መዋቅርና አባላት ብዛት እንዲሁም መንግስትን የመምራት ሚና አንፃር ስምምነቱ ትልቅ ቦታ እንዳለዉ ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ በቀጣይ የብልፅግና ፓርቲ አመራርና አባላትን ሙስና እና ብልሹ አሠራር ያለውን የችግር ስፋት ተረድተው እራሳቸውን በመልካም ሥነምግባር እንዲያንፁ የሚያደርጉ የሥነምግባር ግንባታ ስልጠናዎችን ይሰጣል ብለዋል።

የሁለቱ ኮሚሽኖች ስምምነት በሥነምግባር ግንባታና ሙስና መከላከል ሥራ ላይ እስከታችኛው መዋቅራቸው ድረስ በቅንጅት ለመስራት እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

ስምምነቱ በቀጣይ በሙስና እና ብልሹ አሰራር የሚጠረጠሩ የፓርቲው አመራርና አባላት ሲያጋጥሙ አስተዳደራዊና ህጋዊ ውሳኔ ለመውሰድ ይረዳል ብለዋል፡፡

ኮሚሽነሩ አክለውም ሌሎች የፓለቲካ ፓርቲዎችም ይህንኑ አርአያነት ያለዉ ተግባር ቢከተሉ ሀገርን ከሙስና እና ብልሹ አሰራር ለመታደግ በሚደረገው ትግል ዉስጥ አወንታዊ ሚና እንዲኖራቸው ያግዛል ብለዋል።

የብልፅግና ፓርቲ የኢንስፔክሽን እና ሥነምግባር ኮሚሽን ሰብሳቢ ክብርት ወ/ሮ ሰላማዊ ዳዊት በበኩላቸው ስምምነቱ ፖርቲው በፀረ-ሙስና ትግል ላይ ያለዉን አርአያነትና አቋም የሚያሳይና በመጀመሪያው የጉባኤ ዉሳኔ መሰረትም ሌብነትና ብልሹ አሰራርን ተቋማዊ በሆነ መንገድ ለመታገል እንደሆነ አስረድተዋል።

ወ/ሮ ሰላማዊት አክለውም ሁለቱ ተቋማት በጥናትና ስልጠና እንዲሁም በመረጃ ልዉዉጥ ላይ አብረው እንደሚሰሩ ገልፀው፥ የስምምነቱ ተፈፃሚነትም በፓርቲው አመራሮች፣ አባላትና በፓርቲው ሌሎች አካላት ላይ በመሆኑም በፍፁም ከመንግስታዊ ስራ ጋር እንደማይደባለቅ አስረድተዋል።

የብልፅግና ፖርቲ የኢንስፔክሽንና ሥነምግባር ኮሚሽን ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ሀብታሙ ሲሳይ የስምምነቱን ሰነድ ሲያቀርቡ እንዳሉት የብልፅግና ፓርቲ ሙስና እና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል ትኩረት አድርጎ እየሰራ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

የፓርቲው አባላት ወደ ፓርቲው ሲቀላቀሉ በመልካም ሥነምግባር የታነፁና ከብልሹ አሰራር ነፃ መሆን እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

አቶ ሀብታሙ አክለውም ከብልፅግና ፓርቲ 13 የዲሲፕሊን ጥሰቶች መካከል ሙስና አንዱ መሆኑን ገልፀው፥ ስለሆነም በቀጣይ በፀረ-ሙስና ትግሉ ላይ በቅንጅት መስራት ይኖርብናል ብለዋል።

በፊርማ ስነስርዓቱ ላይ የፌዴራል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ዋና እና ምክትል ኮሚሽነሮች እንዲሁም የብልፅግና ፓርቲ የኢንስፔክሽን እና ሥነ-ምግባር ኮሚሽን አመራሮችና አባላት ተገኝተዋል።

ከሙስና የፀዳች እና የበለፀገች ኢትዮጵያን ዕውን እናድርግ!

#NCRS ሞባይል መተግበሪያ

#ለAndroid ስልክ ተጠቃሚዎች
https://play.google.com/store/apps/details

#ለApple or iPhone ስልክ ተጠቃሚዎች
https://apps.apple.com/us/app/ncrs/id6593662319