Federal Ethics And Anti- Corruption Commission
9.91K subscribers
10.4K photos
244 videos
32 files
3.04K links
Download Telegram
በእፅ ዝውውር የተያዘን የውጭ ዜጋ አስመልጠዋል የተባሉ የፖሊስ አባላት በእስራትና በገንዘብ ተቀጡ

****************

(ፌ.ሥ.ፀ.ሙ.ኮ ጥር 28/2016 ዓ.ም አዲስ አበባ ) በኮኬይን ዕፅ ዝውውር የተያዘ የውጭ ሀገር ዜጋን አስመልጠዋል የተባሉ የፖሊስ አባላት በጽኑ እስራትና በገንዘብ እንዲቀጡ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ወሰነ።

ተከሳሾች በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በቁጥጥር ሥራ ላይ ተመድበው ሲሰሩ የነበሩት ዋና ኢንስፔክተር አዲሱ ባሌማና ዋና ኢንስፔክተር ጌታነህ ሞገስ እንዲሁም የብራዚል ዜግነት ያለው ክርስቲያን ዲ ኦሊቬራ ማርቲኒስ ናቸው።

የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ተከሳሾቹ ላይ ጥር 26 ቀን 2015 ዓ.ም አቅርቦት የነበረው ክስ የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 (1) ሀ እና አንቀጽ 33 እንዲሁም የሙስና አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9 (1) ሀ እና (2) መተላለፍ የሚል ነበር።

ዐቃቤ ሕግ በክስ ዝርዝሩ እንዳመላከተው ታህሳስ 20 ቀን 2015 ዓ.ም ከምሽቱ 1 ሰዓት ከ35 ላይ የብራዚል ዜግነት ያለውን ክርስቲያን ዲ ኦሊቬራ ማርቲኒስ የሚባል 4ኛ ተከሳሽ ከብራዚል ሳኦፓሎ ተነስቶ ትራንዚት በማድረግ ወደ ጆሃንስበርግ ለመሄድ አዲስ አበባ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ "ሴንትራል ጌም'' ተብሎ በሚጠራው የፍተሻ ጣቢያ ላይ በተደረገበት ፍተሻ እንዳይዘዋወርና ጥቅም ላይ እንዳይውል የተከተከለ 27 ነጥብ 65 ኪሎ ግራም ኮኬይን ዕፅ በሻንጣው ውስጥ ይዞ ተገኝቷል።

በወቅቱ 1ኛ ተከሳሽ ከሌሎች የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት ሠራተኞች ጋር በመሆን ቆሞ የተያዘውን ዕፅ ካስቆጠረ በኋላ ከ2ኛ ተከሳሽ ጋር በመሆን 4ኛ ተከሳሽ የሆነውን የውጭ ዜጋ ከእነ ዕፁ ለፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አደንዛዥ ዕፅ መከላከል ጠቅላይ መምሪያ የፀረ ፈንጅና አደንዛዥ ዕፅ ቁጥጥር መምሪያ ለማስረከብ በሚል ዕፁንና ግለሰቡን አሳድረው በነጋታው ታኅሳሥ 21 ቀን 2015 ዓ.ም ከጠዋቱ 2 ሠዓት ከ10 ላይ 1ኛ ተከሳሽ በሚያሽከረክረው ተሽከርካሪ ግለሰቡን ከእነ ዕፁ ጭነው ወደ ቦሌ ሚሊኒየም አዳራሽ አካባቢ መውሰዳቸውን ዐቃቤ ህግ በክስ ዝርዝሩ ላይ አስፍሯል።

ከዚህም በኋላ ቦሌ ሚሊኒየም አዳራሽ አካባቢ 3ኛ ተከሳሽ ጋር በመገናኘት ዕፁንና ግለሰቡን 3ኛ ተከሳሽም በሚያሽከረክረው ኮድ 3_B 33259 አ.አ በሆነ “ቪትዝ” መኪና ውስጥ በማስገባት ግለሰቡ እንዲሸሽ ተደርጓል ሲል ዐቃቤ ሕግ በዋና ወንጀል አድራጊነት ሥልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ አቅርቦባቸው ነበር።

ዐቃቤ ሕግ በአራት ተከሳሾች ላይ ክስ አቅርቦ የነበረ ሲሆን÷ ከተከሳሾቹ መካከል በክስ መዝገቡ በ3ኛ ተከሳሽነት ተካቶ የነበረው ዳንዔል ተሥፋ የማነ የተባለ (ሹፌር) ተከሳሽን በሚመለከት በፖሊስ ተፈልጎ ባለመገኘቱና በጋዜጣ ጥሪ ተደርጎለት ሳይቀርብ በመቅረቱ በቁጥጥር ስር እስኪውል ድረስ ክሱ እንዲቋረጥ የተደረገ ሲሆን÷ 4ኛ ተከሳሽን በሚመለከት ግን በሌለበት ጉዳዩ መታየት ቀጥሎ ነበር።

ሌሎቹ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አባል የሆኑት 1ኛና 2ኛ ተከሳሾች ግን በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ በተሰጠ ብይን መሰረት በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን ሲከታተሉ ቆይተዋል።

በዚህ መልኩ ሁለቱ ተከሳሾች በቀረበባቸው የክስ ዝርዝር ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አልፈጸምንም በማለት የሰጡትን የዕምነት ክህደት ቃል ተከትሎ ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ሕግ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን ተመልክቷል።

ፍርድ ቤቱ በተከሳሾቹ ላይ ዐቃቤ ሕግ ያቀረባቸውን ከሰባት በላይ የሰው ምስክሮችን ቃል እና የሰነድ ማስረጃን መርምሮ ተከሳሾቹ እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል።

ጉዳዩ በሌለበት የታየው የብራዚል ዜግነት ያለው ክርስቲያን ዲ ኦሊቬራ ማርቲኒስ የተባለ ተከሳሽን በሚመለከት ፍርድ ቤቱ የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፎበት ነበር።

1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች የዐቃቤ ህግ ማስረጃን አለማስተባበላቸውን ፍርድ ቤቱ ገልጾ፥ በሙስና አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9 ንዑስ ቁጥር 2 ስር የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፎባቸው ነበር።

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየት መርምሮ 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸውን፣ ያበረከቱትን የበጎ አድራጎት አስተዋጾን ጨምሮ እያንዳንዳቸው ያቀረቡትን አጠቃላይ ሰባት የቅጣት ማቅለያ አስተያየትን መያዙ በዛሬው የችሎት ቀጠሮ ገልጿል።

በዚህም በዕርከን 20 መሰረት 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾችን በ5 ዓመት ጽኑ እስራትና በ5 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ወስኗል።

በሌለበት ጉዳዩ የታየውን 4ኛ ተከሳሽን በሚመለከት ደግሞ የቀደመ የወንጀል ሪከርድ አለመቅረቡን ተከትሎ አንድ ማቅለያ በመያዝ በ8 ዓመት ጽኑ እስራትና በ20 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ወስኗል።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን 4ኛ ተከሳሽን በተገኘበት አፈላልጎ ለማረሚያ ቤት እንዲያስረክብ ትዕዛዝ መስጠቱን ኤፍቢሲ ዘግቧል።

ከሙስና የፀዳች እና የበለፀገች ኢትዮጵያን ዕውን እናድርግ!

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የጥቆማ መተግበሪያ፡- https://epfs.gov.et
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/feaccOfficial/
ቴሌግራም፦ https://t.me/feacc
የጥቆማ ኢሜል፡- CorruptionReportEthiopia@feacc.gov.et
ዩትዩብ፡- https://youtube.com/@federalethicsanti-corrupti149
ትዊተር፦ https://twitter.com/EthiopiaFeacc በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
መልካም ሥነምግባር ያለውና ሙስናን የሚፀየፍ ማህበረሰብ ለመፍጠር የሃይማኖት አባቶች በማስተማርም ሆነ በግል ህይወታቸው አርአያ መሆን እንዳለባቸው ተገለፀ

****************

(የፌ.ሥ.ፀ.ሙ.ኮ ጥር 28/2016 ዓ.ም አዲስ አበባ ) የአዲስ አበባ የሥነምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ከሃይማኖት አባቶችና መምህራን ጋር በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ በሚስተዋሉ ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው ላይ የምክክር መድረክ አካሂዷል።

በምክክር መድረኩ ላይ የአዲስ አበባ የሥነምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀማል ረዲ እንደገለፁት ሀገራችን ኢትዮጵያ የአማኞች ሀገር በመሆኗ የሃይማኖት ተቋማት፣ አባቶችና መምህራን የሚያስተምሩት አስተምህሮ ታማኝነትን፣ ርህራሄን፣ ትዕግስትን፣ አብሮነትን፣ ደግነትን እና ይቅርታን የተላበሰ መሆን አለበት ብለዋል።

የሙስና እና ብልሹ አሰራር ችግሮች መነሻቸው የአስተሳሰብ ጉደለት ነው ያሉት ኮሚሽነሩ፥ የሃይማኖት አባቶች እሴቶች ለማስረፅ ጠንካራ ስራ መስራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

የኮሚሽኑ ም/ኮሚሽነር አሰፋ ቶላ በበኩላቸው የሃይማኖት ተቋማት ማህበራዊ ትስስርን፣ አብሮነትንና በጎነትን የሚያጠናክሩ እሴቶችን የሚሰብኩ መሆን እንዳለባቸው ገልፀው፥ ማህበረሰቡ ጠንካራ የሥነምግባር እሴቶች እንዲላበስና ፈታኝ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ጭምር ሥነምግባራዊና ከጥላቻ የራቁ ንግግሮችን እንዲያደርጉ እና መልካም ውሳኔዎችን እንዲወስኑ የሚያስችሉ መሆን አለባቸው ብለዋል።

በሥነምግባራቸው ተምሳሌት የሆኑ የሃይማኖት አባቶችና መምህራን በመልካም ባህሪ የታነፀ ትውልድ ለመፍጠር ያላቸው ሚና የላቀ መሆኑን አመላክተዋል።

በውይይቱ ላይ የተሳተፉ የሃይማኖት አባቶችና መምህራን በሥነምግባር የታነፀና ሙስናን የሚፀየፍ ትውልድ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ሚናቸውን እንደሚወጡ ገልፀዋል። አክለውም መንግስት ለሌብነትና ብልሹ አሰራር በር የሚከፍቱ አሰራሮችን ተከታትሎ በማረም እና ተጠያቂነትን በማጠናከር የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

"የሃይማኖት ተቋማት መልካም ባህሪ ያለውና ሙስና የሚፀየፍ ትውልድ ከመገንባት አንፃር ያላቸው ሚና" የሚል የመወያያ ሰነድ በኮሚሽኑ የስልጠና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ጀንበሩ ኢርኮ ቀርቦ ውይይት መካሄዱን ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ከሙስና የፀዳች እና የበለፀገች ኢትዮጵያን ዕውን እናድርግ!

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የጥቆማ መተግበሪያ፡- https://epfs.gov.et
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/feaccOfficial/
ቴሌግራም፦ https://t.me/feacc
የጥቆማ ኢሜል፡- CorruptionReportEthiopia@feacc.gov.et
ዩትዩብ፡- https://youtube.com/@federalethicsanti-corrupti149
ትዊተር፦ https://twitter.com/EthiopiaFeacc በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡