Federal Ethics And Anti- Corruption Commission
9.9K subscribers
10.4K photos
244 videos
32 files
3.04K links
Download Telegram
በሸገር ከተማ “የሥነ-ምህዳር አወቃቀር እንቀይራለን” በሚል ከግለሰቦች ገንዘብ የተቀበሉ ተከሳሾች እስከ 20 ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጡ

************************

(የፌ.ሥ.ፀ.ሙ.ኮ ጥር 27/2016 ዓ.ም አዲስ አበባ) በሸገር ከተማ “የሥነ-ምህዳር አወቃቀር እንቀይራለን’’ በማለት በማጭበርበር ገንዘብ ከግለሰቦች የተቀበሉ ተከሳሾች እስከ 20 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ተቀጡ።

የቅጣት ውሳኔውን ያስተላለፈው የኦሮሚያ ክልል የሸገር ከተማ ከፍተኛ ፍ/ቤት ወንጀል ችሎት ነው።

ተከሳሾቹም፥ 1ኛ ደረጄ ካሳዬ ኢፋ፣ 2ኛ አቡና አያና ገመቹ፣ 3ኛ ሹሚ መስቀል ገዳ፣ 4ኛአለማየሁ ገዛኸኝ ደምስ፣ 5ኛ ጉታ ጫካ ሁንዴ እና 6ኛ ደበላ ረጋሳ ፉፋ ናቸው።

የኦሮሚያ ፍትሕ ቢሮ የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቢ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1 ሀ እና ለ እንዲሁም የሙስና ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር881/2007 አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 2 ስር የተመላከተውን ድንጋጌ ተላልፈዋል በማለት በሰኔ ወር 2015 ዓ.ም ተደራራቢ ክስ አቅርቦባቸዋል።

በቀረበው ክስ ላይ እንደተመላከተው ተከሳሾቹ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለራሳቸው ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ በ2014 ዓ.ም በተለያዩ ጊዜያት በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ በተለያዩ ቦታዎች የአካባቢውን ሥነ-ምህዳር አወቃቀር ለመቀየር ከባለስልጣናት እንደታዘዙ በማስመሰል ማህበር በማደራጀት ‘‘መሬት ሸንሽነን እናከፋፍላለን’’ የሚሉ ሀሰተኛ የማግባቢያ ቃላት መጠቀማቸው በክሱ ዝርዝር ላይ ተጠቅሷል።

እንደአጠቃላይ በማህበር ላደራጇቸው የተለያዩ ግለሰቦች ለእያንዳንዳቸው ‘‘200 ካሬ ሜትር ይዞታ ሸንሽነን እንሰጣለን’’ በማለት ከ4 ሚሊየን ብር በላይ ገንዘብ ከግለሰቦች በመቀበል የመንግስት ይዞታ የሆነውን 3 ሺህ ካሬ ሜትር ይዞታ ሸንሽነው ሲያከፋፍሉ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የጠቀሰው ዐቃቤ ሕግ የተከሳሾቹን የወንጀል ድርጊት ተሳትፎ ደረጃ በመጥቀስ ዝርዝር ክስ አቅርቦባቸዋል።

ተከሳሾቹ የቀረበባቸው ክስ በችሎት እንዲደርሳቸው ከተደረገ በኃላ የሰጡትን የዕምነት ክህደት ቃል ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ የሰውና የተለያዩ የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቧል።

ፍርድ ቤቱም በክስ ዝርዝሩ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት መፈጸሙን ማረጋገጡን በመግለጽ ተከሳሾቹ በተከሰሱበት ድንጋጌ እንዲከላከሉ ብይን የሰጠ ቢሆንም ተከሳሾቹ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን ማስተባበል ባለመቻላቸው የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፎባቸዋል።

ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ሕግ የቅጣት ማክበጃ አስተያየትንና የተከሳሾቹን የቅጣት ማቅለያ አስተያየት በመያዝ 1ኛ ተከሳሽን በ18 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል።

2ኛ ተከሳሽን በሚመለከት በ16 ዓመት ከ6 ወራት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ የወሰነው ፍርድ ቤቱ ፤ ከ3ኛ እስከ 6ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾችን ደግሞ እያንዳንዳቸውን በ20 ዓመት ጽኑ እስራትና በ20 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ መወሰኑን ፋና ዘግቧል።

ከሙስና የፀዳች እና የበለፀገች ኢትዮጵያን ዕውን እናድርግ!

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የጥቆማ መተግበሪያ፡- https://epfs.gov.et
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/feaccOfficial/
ቴሌግራም፦ https://t.me/feacc
የጥቆማ ኢሜል፡- CorruptionReportEthiopia@feacc.gov.et
ዩትዩብ፡- https://youtube.com/@federalethicsanti-corrupti149
ትዊተር፦ https://twitter.com/EthiopiaFeacc በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ለሚኒስቴር መ/ቤቱና ለተጠሪ ተቋማት አመራሮች ሥነምግባራዊ አመራርን የተመለከተ ስልጠና እየተሰጠ ነው

********

(የፌ.ሥ.ፀ.ሙ.ኮ ጥር 27/2016 ዓ.ም አዲስ አበባ) ሥነምግባራዊ አመራርን የተመለከተ ስልጠና ቡድን መሪ እና ከዚያ በላይ ለሆኑ ለከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር እና ለተጠሪ ተቋማት አመራሮች እየተሰጠ ነው፡፡

የፌዴራል የሥነ-ምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሥነምግባር መከታተያ ስራ አስፈጻሚ ጋር በመተባበር ለመስሪያ ቤቱ እና ለተጠሪ ተቋማት በየደረጃው ለሚገኙ አመራሮች ሥነምግባራዊ አመራርን ለመፍጠር የሚያስችል የአቅም ግንባታ ስልጠና በአለም ገና ከተማ በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በምህንድስና የስልጠና ማዕከል እየተሰጠ ይገኛል፡፡

የስልጠናው ዓላማ በዘርፉ ለሚሰሩ ተግባራት ሥነምግባራዊ አመራርን በማጎልበት ከሙስና እና ከብልሹ አሰራር የጸዳ አመራርን እንዲከተሉ የሚያስችል የአቅም ግንባታ ስልጠና ነው፡፡

የስልጠናውን መድረክ በንግግር ያስጀመሩት የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ወንድሙ ሴታ(ኢንጂነር) እንደገለፁት የሥነምግባራዊ አመራር ጽንሰ ሀሳብን በመረዳት እና በተቋማችን ለማስተግበር ዘርፉ ሰፊ ሀብትና አገልገሎት የሚሰጥበት በመሆኑ የተመደበለትን ሀብት ለታለመለት ዓላማ ለማዋል ያለንን ግንዛቤ ለማዳበር ይረዳል ብለዋል፡፡

አያይዘውም በኮንስትራክሽን እና በመሠረተ ልማት ዘርፍ በጣም ብዙ አገልግሎቶች የሚሰጡበት በመሆኑ የህዝባችንን ጥያቄ ለመመለስ፣ የተጣሉብንን ሀላፊነቶች በአግባቡ ለመወጣት፣ በተቋማችን የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት እና የመንግስትን ሀብት ለተገቢው አገልግሎት ለማዋል ስልጠናውን በአግባቡ በመከታተል በተግባር ላይ ማዋል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በፌዴራል የሥነምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ስልጠና ክፍል ዴስክ ሀላፊ የሆኑት አቶ አንተነህ ኃይሌ በሥነምግባራዊ አመራር ጽንሰ ሀሳብ፣ አስፈላጊነት፣ ክህሎቶች እና መርሆዎች ላይ ገለጻ ሲያደርጉ እንደተናገሩት በተቋማቶች ሙስናን እና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል አመራሮች ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝ ገልፀው፥ የከተማና መሠረተ ልማት ዘርፍ ለሀገር እድገትና ልማት ቁልፍ የሆነና ከፍተኛ የሀገር ሀብት የሚፍስበት እንደመሆኑ መጠን ሥነምግባራዊ አመራር ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡

ስራን በእውቀትና በብልሃት መስራት የሚችል፣ ሰራተኛውን ግንባር ቀደም ተሳታፊ የሚያደርግ፣ የሰራተኛውን ችግር የሚያውቅና መፍትሔ የሚሰጥ፣ ውሳኔን በወቅቱ መስጠት የሚችልና ሙስና የሚፈጠርባቸው ቦታዎች ላይ አጥብቆ የሚመራ መሪ ያስፈልጋል ሲሉ ለተሳታፊ አመራሮች መግለፃቸውን ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ከሙስና የፀዳች እና የበለፀገች ኢትዮጵያን ዕውን እናድርግ!

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የጥቆማ መተግበሪያ፡- https://epfs.gov.et
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/feaccOfficial/
ቴሌግራም፦ https://t.me/feacc
የጥቆማ ኢሜል፡- CorruptionReportEthiopia@feacc.gov.et
ዩትዩብ፡- https://youtube.com/@federalethicsanti-corrupti149
ትዊተር፦ https://twitter.com/EthiopiaFeacc በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡