Federal Ethics And Anti- Corruption Commission
9.88K subscribers
10.4K photos
245 videos
32 files
3.05K links
Download Telegram
ሥነምግባርን ያልተላበሰ አመራር የተቋሙን ተልዕኮ ሊያሳካ አይችልም - ም/ኮሚሽነር አቶ ፍቃዱ ሰቦቃ

****************

(ፌ.ሥ.ፀ.ሙ.ኮ መጋቢት 18/2017 ዓ.ም አዲስ አበባ) የፌዴራል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ሥነምግባራዊ አመራርነት ለተቋማዊ ተልዕኮ ስኬት በሚል መሪ ሀሳብ ለኢትዮጵያ ኤሌትሪክ አገልግሎት አመራሮች ስልጠና እየሰጠ ይገኛል።

የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የፌደራል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን የሥነምግባር ግንባታ ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ክቡር አቶ ፍቃዱ ሰቦቃ ሥነምግባርን ያልተላበሰ አመራር የተቋሙን ተልዕኮ ሊያሳካ አይችልም ብለዋል።

ኢትዮጵያ ኤሌትሪክ አገልግሎት ኤሌክትሪክን ለሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጭ የሚያከፋፍል ከዜጎች የዕለት ተዕለት ኑሮ ጋር ከፍተኛ ቁርኝት ያለው ትልቅ ተቋም ቢሆንም በዚሁ ልክ የዜጎችን ብሶት እና እሮሮ የሚበዛበት ተቋም መሆኑን ገልፀዋል።

ተቋሙ ላይ የሚስተዋሉ ከቆጣሪ ንባብ ጋር፣ መብራት አውቆ በማጥፋት ተገልጋዩን በማስገደድ ገንዘብ አምጡ ከማለት እና የኤሌትሪክ መቆራረጥ በሚፈጠርበት ወቅት ለጥገና የሚፈፀሙ የሙስና ወንጀሎች ህብረተሰቡ የሚማረርባቸው ብልሹ አሰራሮች የግዙፉን ተቋም ስም የሚያጠለሹ በአንዳንድ ሥነምግባር የጎደላቸው ሠራተኞች እና አመራሮች የሚፈፀም በመሆኑ አመራሩ በቁርጠኝነት ሊታገል ይገባዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢ/ር ጌቱ ገረመው በበኩላቸው ሙስና በመንግስትና በህዝብ ሃብትና ንብረት ላይ ስርቆት መፈጸም፣ ዝርፊያ ማካሄድ፣ ማጭበርበር፣ ህግና ሥርዓትን ተከትሎ ከመሥራት ይልቅ በዝምድና፣ በትውውቅ፣ በፖለቲካ ወገንተኝነት፣ በጐሰኝነት፣ በኃይማኖት ትስስር ላይ ተመርኩዞ በመሥራት አድሎ መፈፀም፣ ፍትህን ማጓደል፣ ስልጣንና ኃላፊነትን በህገወጥ መንገድ የግል ጥቅም ማግኛ የማድረግ እኩይ ተግባር ነው ብለዋል፡፡

ይህን አስነዋሪ ድርጊት በዘላቂነት መፍታት እና ከሙስና የጸዳ አገልገሎት መስጠት የሚቻለው ለህግ፣ ለሥርዓት እና አሠራር ተገዢ በመሆን፣ ሥራን በግልፅነትና በተጠያቂነት በመፈጸም፣ የሥነምግባር እና የሞራል ዕሴቶችን በማክበር፣ ራስን ከሙስና እና ብልሹ አሰራር በማራቅ፣ ሌብነትን በመዋጋት፣ አገልጋይና ለሌሎች አርዓያ መሆንን በተግባር ማረጋገጥ እንደሚገባ ገልፀዋል።

ኢ/ር ጌቱ ገረመው አክለውም ተቋማችን ሙስናንና ብልሹ አሰራርን ለማክሰም ከመቼውም ጊዜ በላይ ቁርጠኛ መሆኑን ለማረጋገጥ በቅርቡ አበልጽጎ ተግባራዊ ያደረገው የሞባይል መተግበሪያ አንዱ ማረጋገጫ መሆኑን ገልፀው፤ በየደረጃው የሚገኙ የተቋማችን አመራሮችና ፈጻሚዎች ሙስና እና ብልሹ አሰራርን በፅናት በመታገል የተጀመረውን ተቋማዊ የለውጥ ሥራ በውጤታማነት ማስቀጠል እንደሚገባ አሳስበዋል።

ስልጠናው በዶ/ር ይልቃል ሙሉአለም እና በዶ/ር እንድሪስ የባ እየተሰጠ ሲሆን፣ ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት የሚቀጥል ይሆናል።

ከሙስና የፀዳች እና የበለፀገች ኢትዮጵያን ዕውን እናድርግ!

#NCRS ሞባይል መተግበሪያ

#ለAndroid ስልክ ተጠቃሚዎች
https://play.google.com/store/apps/details

#ለApple or iPhone ስልክ ተጠቃሚዎች
https://apps.apple.com/us/app/ncrs/id6593662319
ጉዳይን ያለአግባብ ማጓተት የሚያስከትለው የሙስና ወንጀል የህግ ተጠያቂነትን ምን ያህል ያውቃሉ?

*******************

ጉዳይን ያለ አግባብ ማጓተት በተገልጋዩ ህብረተሰብ እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መካከል ባለ ግንኙነት የሚፈጸም ተገቢነት የሌለው ተግባር ነው፡፡ ተገልጋዩ የህብረተሰብ አባል በህግ ክርክሮች እና በአስተዳደር አከላት የሚሰጡ አስተዳደራዊ ውሳኔዎችን ለማግኘት ወደ ተለያዩ መንግስታዊ አና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ፊት ይቀርባል፡፡ በዚሁ ሁኔታ አገልግሎት ፈልጎ የቀረበው ተገልጋይ እንደ ጉዳዩ ባህሪ በህግ እና አሰራር በተቀመጠ ምክንያታዊ ጊዜ ውስጥ ለጉዳዩ እልባት አግኝቶ መሸኘት አለበት፡፡

ይህ የማይሆን ከሆነ ተገልጋዮችን ተገቢ ላልሆነ እንግልት በመዳረግ ጊዜያቸውን፣ ገንዘባቸውን እና ጉልበታቸውን እንዲያባክኑ በማድረግ ለከፋ ምሬት እና ተስፋ መቁረጥ በመዳረግ በመንግስት እና በህዝብ መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያሻክር ይሆናል፡፡ በዚህ አጭር ጽሁፍም ጉዳይን አለአግባብ ማጓተት ምንነትና የሚያስከትለውን የህግ ተጠያቂነት በአጭሩ የምንዳስስ ይሆናል፡፡

1. ጉዳይን ያለአግባብ ማጓተት ምንነት

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ህገመንግስት አንቀጽ 12 ላይ የመንግስት ስራ በግልጽነት እና ተጠያቂነት በሰፈነበት ሁኔታ መከናወን እንዳለበት ያመለክታል፡፡ ይህ መርህ በህግ እና አስተዳደራዊ ውሳኔዎች አሰጣጥ ላይ ተፈጻሚነት አለው። የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የተቋቋሙበትን አላማ ለማሳካት የሚያስችሏቸው የአገልግሎት መስጫ ስታንዳርድን የሚያመለክቱ የተለያዩ መመሪያዎች እና የአሰራር ስርዓት አላቸው፡። ከነዚህ መካከልም ጉዳዮችን ተቀብለው ውሳኔ የሚሰጡበትን የጊዜ ገደብ የሚያመላክቱ ድንጋጌዎች በአዋጅ በደንብ እና መመሪያዎች የተደነገጉ ናቸው፡፡

ከዚህ ባለፈም በዜጎች ቻርተር፣ በመሰረታዊ የአሰራር ለውጥ(ቢፒአር) እና ሌሎች የለውጥ መሳሪያዎች እንደየ ጉዳዮቹ ባህሪ እና የውስብስብነት ደረጃ የመንግስት መስሪያ ቤቶች አንድን ጉዳይ ተቀብለው መርምረው እልባት የሚሰጡበትን የጊዜ ገደብ ያመላክታሉ፡፡ እነዚህን በህግ የተዘረጉትን የአሰራር ደረጃ ባለመጠበቅ ጉዳይን ያለ በቂ ምክንያት ሳይወስኑ ወይም ሳይፈጽሙ ማቆየት ጉዳይን ያለአግባብ የማጓተት ተግባር ነው፡፡ በፍትህ አስተዳደር ዘርፍ ያለውን በምናይበት ጊዜ በመርህ ደረጃ የዘገየ ፍትህ እንደተነፈገ የሚቆጠር ነው፡፡ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 20 (1) መሰረት ማንኛውም የተከሰሰ ሰው ክስ ከቀረበበት በኋላ ተገቢ በሆነ አጭር ጊዜ ውስጥ የመሰማት መብት እንዳለው ተደንግጎ ይገኛል፡፡

በዚህም ጉዳያቸው ታይቶ የመጨረሻ ፍርድ ያልተሰጣቸውን ተከሳሾች በተገቢው ጊዜ ፍርድ መስጠት የሚገባ ሲሆን፣ ውሳኔ እስከሚያገኙ በእስር የሚቆዩበትን ጊዜ በጉዳዩ ላይ የመጨረሻ ፍርድ እንደተሰጠ ተደርጎ ሊታይ አይገባውም፡፡ በዚሁ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ 3 መሰረት ማንኛውም በወንጀል ፍርድ ሂደት ውስጥ ያለ ሰው ከጥፋተኝነት ፍርድ በፊት በተከሰሰበት ወንጀል እንደ ጥፋተኛ ሊቆጠር እና ሊታይ አይገባውም፡፡ በወንጀል ጉዳይ የተፋጠነ ፍትህ የማግኘት መብት የተከሰሱ ሰዎች መብት ብቻ ሳይሆን ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎችም መብት ነው፡፡

በዚህም በህገመንግስቱ አንቀጽ 19(3) መሰረት በወንጀል ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎች በአርባ ስምንት ሰአት ውስጥ ፍርድ ቤት ቀርበው ለመታሰር ያበቃቸውን በቂ ምክንያት የማወቅ መብት አላቸው፡፡ ለመታሰራቸው በቂ ምክንያት የሌለ ከሆነ ፍ/ቤቱ የኣካል ነጻነታቸውን ጠብቆ በነጻነት ሊለቃቸው እንደሚገባ ነገር ግን ልዩ በሆነ ሁኔታ ፍትህ እንዳይጓደል ምርመራ ለማካሄድ አስፈላጊ የሆነውን ተጨማሪ የእስር ማቆያ ጊዜ በጥብቅ መስፈርት ሊፈቅድ ይችላል፡፡

ከዚህም የምንረዳው በወንጀል ተጠርጥረው የተያዙም ሆነ የተከሰሱ ሰዎች በህገመንግስቱ በተጠበቀላቸው መብት መሰረት ጉዳያቸው ሳይጓተት ምክንያታዊ በሆነ ጊዜ ውስጥ ውሳኔ የማግኘት መብት አላቸው፡፡ በፍትሐብሄር ፍትህ አስተዳደርም ፍርድ ቤቶቻችን የሚቀርቡላቸውን ጉዳዮች እንደ ጉዳዩ ውስብስበነት በተወሰነ ጊዜ ውስጥ አይቶ አከራክሮ ለመወሰን የሚያስችላቸው የፍትሃብሄር ሥነስርዓት ህግ እና የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 008/2013 ጉዳይን በተወሰነለት የጊዜ ገደብ ውስጥ ያለማጓተት መወሰን እንደሚገባ አመላካች የአሰራር ስርዓቶች ናቸው፡፡

ጉዳይን ያለአግባብ ማጓተት በወንጀል እና በፍትሐብሄር ጉዳይ ብቻ የሚታይ ሳይሆን በማናቸውም አስተዳደራዊ ጉዳዮችም ጭምር ተቀባይነት የሌለው የአሰራር ብልሹነት ነው፡፡ የፌደራል አስተዳደር ሥነስርዓት አዋጅ ቁጥር 1183/2012 አንቀጽ 33 ላይ “በተገቢው ጊዜ መወሰን” በሚል ርእስ እንደተደነገገው የአስተዳደር ውሳኔ የሚሰጠዉ ሰዉ የአስተዳደር ውሳኔዉን ሳይዘገይ በተገቢዉ ጊዜ መስጠት እና በጉዳዩ ዙሪያ ያሉ ጥቅሞች በውሳኔው መዘግየት ምክንያት ለጉዳት እንዳይጋለጡ ማድረግ አለበት በማለት በመደንገግ በግልጽ ጉዳይን ያለ አግባብ ማጓተት ህገወጥ እንደሆነ የደነገገ ሲሆን፣ ከውጤት አንጻርም የአስተዳደር ውሳኔው በተገቢው ጊዜ ሳይሰጥ መቅረት የአስተዳደር ውሳኔ ጥያቄውን ውድቅ በማድረግ እንደተሰጠ ውሳኔ ይቆጠራል በማለት አስቀምጦ ይገኛል፡፡

በአገራችን የህግ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነው ይሄው የአስተዳደር ሥነስርዓት አዋጅ የአስተዳደር አካላት የተገልጋዮችን መብት በማክበር ጉዳያቸውን ሳያጓትቱ በተገቢው ፍጥነት መወሰን እንዳለባቸው ያመለክታል፡፡ በዚሁ አግባብ አለመወሰንም ጥያቄውን ውድቅ እንደማድረግ ይወሰዳል፡፡ ይህ ማለትም ተገልጋዩ ወደሚከተለው አቤቱታ ሰሚ የበላይ የመንግስት አካል ቅሬታውን ማቅረብ እና ምላሽ ማግኘት ይችላል ማለት ነው፡፡

2. ጉዳይን ያለአግባብ ማጓተት የሚያስከትለው የህግ ተጠያቂነት

ጉዳይን ያለአግባብ ማጓተት ወንጀል ተጋላጭ የሆኑት የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ብቻ ሳይሆኑ ህዝባዊ የሆኑ የግሉ ዘርፍ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትንም የሚያካትት ነው፡፡ ከዚሁ አኳያ በተገልጋዮች ላይ የሚፈጸም ምክንያታዊ ያልሆነ የጉዳይ ማጓታት ተግባር ከአስተዳደራዊ እና የፍሐብሄር ተጠያቂነት ብቻ ሳይሆን በወንጀልም የሚያስጠይቅ ተግባር ነው፡፡ በሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 18 መሰረት ማንኛውም የመንግስት ወይም የህዝባዊ ድርጅት ሠራተኛ በኃላፊነቱ በስራው ምክንያት በቀረበለት ጉዳይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ጥቅም ለማግኘት ሲል በጉዳዩ ላይ ጥቅም ያለውን ማንኛውንም ሰው ለመጥቀም ወይም ለመጉዳት በማሰብ ከህግ፣ ከመመሪያ ወይም ከተለመደው አሰራር ውጪ ያለበቂ ምክንያት ጉዳዩን ያልወሰነ፣ ያዘገየ ወይም ባለጉዳይን ያጉላላ ሰው እንደ ጉዳዩ ሁኔታ በመቀጮ ወይም በቀላል እስራት ወይም ከአምስት አመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት እና አምስት ሺህ ብር በማይበልጥ መቀጮ እንደሚቀጣ ደንግጎ ይገኛል፡፡
እዚህ ላይ ልብ ልንለው የሚገባው በአዋጁ እንደተደነገገው ጉዳይን ማጓተት ወንጀል የሙስና ወንጀል የሆነበትን መሰረታዊ ምክንያት ነው፡፡ በዚሁም መሰረት የሙስና ወንጀሎች በመሰረታዊነት የሚፈጸሙት የገንዘብ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለአንዱ ወገን በተለያዩ ምክንያቶች በማዳላት ሌላውን ወገን ለመጥቀም በማሰብ ነው። የዚህ ወንጀል ፈጻሚዎች ጉዳይን አለአግባብ የማጓተት ተግባር የሚፈጽሙት ባለጉዳዩ በመመላለስ ምክንያት ከሚደርስበት እንግልት ለማምለጥ ሲል ገንዘብ እንዲከፍላቸው ተጽእኖ ለማሳደር አለያም ባለጉዳዩ ተማሮ ጉዳዩን መከታተሉን እንዲተወው በማድረግ የባለጉዳዩን መብት ለመረጡት ሌላኛው ሰው በማስተላለፍ በዚህም የሚከፈላቸውን ተገቢ ያልሆነ የገንዘብ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ሌላው ልብ ልንለው የሚገባው አጥፊው ጉዳይን ያለአግባብ ማጓተት ፈጽሟል ለማለት የተላለፈው ግልጽ የሆነ በህግ፣ በመመሪያ እና በአሠራር ደንብ የተቀመጠ ምክንያታዊ የውሳኔ መስጫ ጊዜን በመተላለፍ ውሳኔውን በሰዓቱ ሳይሰጥ የቀረ መሆኑን በማስረዳት ነው፡፡ በዚህም እንደየሙያና አገልግሎት መስኩ ውሳኔ ሊሰጥበት የሚገባው ጉዳይ የሚፈልገውን ምክንያታዊ ጊዜ ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል፡፡

በአጠቃላይ የመንግስት መስሪያ ቤቶችም ሆኑ የልማት ድርጅቶች እንዲሁም የህዝባዊ ድርጅቶች ተገልጋዮቻቸውን ሲያስተናግዱ አገልግሎት ወይም ውሳኔ የሚሰጥበት ጉዳይ ያለውን ልዩ ባህሪ ግምት ውስጥ በማስገባት በህግ እና በአሠራር ስርዓት እንዲሁም የተለመዱ አካባቢያዊ ሁኔታዎችን በማገናዘብ ለተገልጋዮቻቸው በተገቢው ጊዜ ውሳኔ የመስጠት ግዴታ አለባቸው፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ያለ በቂ ምክንት ህግ እና አሰራርን በመጣስ ተገልጋዮችን ለማንገላታት እና ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት እንዲሁም አግልግሎት ጠያቂው ላይ ጉዳት ለማድረስ በማሰብ ጉዳይን ያለበቂ ምክንያት ማጓተት በህግ የሚያስጠይቅ እና የሚያስቀጣ የወንጀል ተግባር መሆኑን መረዳት ይገባል፡፡

ተገልጋዩ ማህበሰረብ በመንግስትም ይሁን ህዝባዊ ተቋማት አገልግሎት ለማግኘት ሲሄድ በህግ እና አሠራር ስርዓት የተቀመጡ የአሰራር ደረጃዎችን ተረድቶ በዛ ውስጥ ውሳኔ እንዲያገኝ መጠየቅ እና ይህ በማይሆንበት ጊዜ ጉዳዩን ያለ በቂ ምክንያት የሚያጓትቱ የመንግስት እና ህዝባዊ ድርጅት ሠራተኞች እና ኃላፊዎች ላይ የህግ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በመተባበር መስራት ያስፈልጋል፡፡

ከሙስና የፀዳች እና የበለፀገች ኢትዮጵያን ዕውን እናድርግ!

#NCRS ሞባይል መተግበሪያ

#ለAndroid ስልክ ተጠቃሚዎች
https://play.google.com/store/apps/details

#ለApple or iPhone ስልክ ተጠቃሚዎች
https://apps.apple.com/us/app/ncrs/id6593662319
ኮሚሽኑ ከተለያዩ ባላድርሻ አካላት ጋር አብሮ ለመስራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረመ

****************

(ፌ.ሥ.ፀ.ሙ.ኮ መጋቢት 18/2017 ዓ.ም አዲስ አበባ) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ከኃይማኖት ተቋማት፣ ከሚዲያ ተቋማትና ከሲቪክ ማህበራት ጋር አብሮ ለመስራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራርሟል።

ኮሚሽኑ በሥነምግባር የታነጹ ዜጎችን በመገንባት የተጀመረውን ሁሉን አቀፍ የብልጽግና ጉዞ ለማረጋገጥ እንዲቻል በክልሉ ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችል የምክክር መድረክ በሀላባ ከተማ አካሂዷል።

በመድረኩ የተገኙት የኮሚሽኑ የትምህርትና ስልጠና አውታሮች ማስተባባሪያ ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ታየች ሞላ እንደተናገሩት መልካም ሥነምግባር ያላቸውን ትውልድ ከማፍራት ረገድ በትምህርት ቤቶች እና ከተለያዩ አደረጃጀቶች ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በሀገራችን ሌብነትን የሚፀየፍ ትውልድን ማፍራት ያስፈልጋል ያሉት ምክትል ኮሚሽነሯ፣ ለዚህም ከሲቪክ ማህበራትና ሚዲያ ተቋማት ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ተቋማቱ የሙስናን አስከፊነት ለትውልድ ከማስተማር አኳያ ትልቅ ኃላፊነት መወጣት ይገባቸዋል ብለዋል።

በትውልድ ሥነምግባርና አመለካከት ላይ መስራት ሀገርን መገንባት ነው ያሉት ምክትል ኮሚሽነሯ፣ በወጣቶች ስብዕና ግንባታ ላይ ብዙ መስራት የሚጠበቅ በመሆኑ ግንዛቤ መፍጠር ዙሪያ ወጥ በሆነ መንገድ በጋራ ውጤት ለማምጣት መትጋት እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።

የምክክሩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ሙስና ሀገርን ወደ ኃላ የሚያስቀር፣ የልማትና ዕድገት ፀር በመሆኑ የማይሰርቅ ትውልድን ለማፍራት ከቤተሰብ እስከ ተቋማት ድረስ ያሉ አካላት ትልቁን ድርሻ ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

ህዝብን በንፁህ ህሊና የሚያገለግል ትውልድ መፈጠር ለሀገር ግንባታ ያለው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ ትምህርት ቤቶች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የሚዲያ ተቋማትና ሌሎች ባለድርሸ አካላት በቅንጅት መስራት እንደሚጠበቅም ገልፀዋል።

በምክክር መድረኩ የኃይማኖት ተቋማት፣ የሲቪክ ማህበራት፣ የሚዲያ ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት መሳተፋቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ዘግቧል።

ከሙስና የፀዳች እና የበለፀገች ኢትዮጵያን ዕውን እናድርግ!

#NCRS ሞባይል መተግበሪያ

#ለAndroid ስልክ ተጠቃሚዎች
https://play.google.com/store/apps/details

#ለApple or iPhone ስልክ ተጠቃሚዎች
https://apps.apple.com/us/app/ncrs/id6593662319