Federal Ethics And Anti- Corruption Commission
9.89K subscribers
10.4K photos
245 videos
32 files
3.05K links
Download Telegram
የትውልድን ሥነምግባር ማነፅ፣ የአገረ-መንግስት ግንባታ መሠረት ነው!

***************

በአገራችን የትውልድ ሥነምግባር በኃላፊነት እና በተጠያቂነት ከመገንባት አንጻር ወላጆች፣የቤተሰብ አባላት፣ ህብረተሰቡና የትምህርት ተቋማት እንዲሁም የኃይማኖት ተቋማትና ሚዲያ የሚኖራቸው ሚና የማይተካ ነው፡፡ ወላጆች እና የቤተሰብ አባላት፣ ትውልድን በሥነምግባር እና በሞራል እሴቶች በማነጽ፣ የአገራችን የፀረ-ሙስና ትግል ውጤታማ እንዲሆን ከፍተኛ ሚና መጫወት ይገባቸዋል። በተለይም የሥነምግባር ዝቅጠት ያጋጠመው የቤተሰብ አባል ሲያጋጥመው ተገቢው ክትትል እና ድጋፍ ካልተደረገ በቀር፣ አንድ የቤተሰብ አባል በሙስና እና ብልሹ አሰራር ችግሮች የመዘፈቅ አጋጣሚዎች ይሰፋሉ።

በተለይም፣ ቤተሰብ ውስጥ ምንጩ ያልታወቀ ሀብት የሚያንቀሳቅስ አባል ሲገኝ፣ በዝምታ የሚታለፍ ወይም በማሞካሸት መቀበል፣ የቤተሰብ አባላትን የሚያፈርስ የመሆን ዕድል ይኖረዋል። በመሆኑም በአገራችን ወላጅና ቤተሰብ-ተኮር የትውልድ ሥነምግባር ግንባታ እና ሙስና መከላከል ትኩረት ተሰጥቶ መሠራት ያለበት በመሆኑ፣ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በተለይም የማህበራዊ ዘርፍ ተቋማት በተልዕኳቸው በተገቢው በማካተት መተግበር ይገባል።

ቤተሰብ ትውልድን በመልካም ሥነምግባር ለመገንባት ትልቅ ኃላፊነት ካላቸው ማህበራዊ ተቋማት መካከል አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ ልጆች ወደ ማህበረሰቡ የሚቀላቀሉት ከቤተሰብ የገነቡትን እሴት ይዘው ነው፡፡ ዛሬ በአደባባይ የሚያሸልሙም ሆነ የሚያስወግዙ ተግባሮች የአስተዳደግ ድምር ውጤቶች ናቸው፡፡ የዛሬዎቹ ህፃናት የነገዎቹ ሀገር ተረካቢዎች በሥነምግባራቸው እንዲመሰገኑ ወይም እንዲወገዙ የቤተሰብ ድርሻ ትልቁን ቦታ ይይዛል፡፡ ወቅቱ የመረጃ ዘመን እንደመሆኑ ልዩ ልዩ መረጃዎች በተለያዩ መንገዶች ሊገኙ ይችላሉ፡፡

መልካም ሥነምግባር የማግኛ ዋነኛ መንገድ ግን ቤተሰብ ነው፡፡ ስለዚህ ቤተሰብ በመልካም ሥነምግባር ለልጆች የቅርብ አርዓያ በመሆን፣ ልጆች ጥሩውን ከመጥፎው እንዲለዩ በመምከርና በማስተማር፣ በጥሩ እሴቶች ጎልብተው እንዲያድጉ በመርዳት በመልካም ሥነምግባር የተገነባ ትውልድ የመቅረጽ ኃላፊነትን መወጣት ይኖርበታል፡፡ ያን ጊዜ ለራሱና ለሀገሩ ታማኝ የሆነ ትውልድ ማፍራት ይቻላል፡፡

ሌላው ለትውልድ ሥነምግባር ግንባታ መሠረት ህብረተሰቡ ነው፡፡ በየትኛውም የሥራ መስክ የተሰማሩ ሰዎች ምንጫቸው ማህበረሰቡ ነው፡፡ በሥነምግባሩ ጠንካራ የሆነ ማህበረሰብ በሥነምግባር ጉድለት የሚከሰቱ ወንጀሎች ተጠቂ ወይም ሰለባ አይሆንም፡፡ ስለዚህ ህብረተሰቡ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ መልካም ሥነምግባር እሴቶችን እያጎለበተ፣ በስግብግብነትና በሙስና የሚገኝ ብልጽግናን እያወገዘ በመልካም ሥነምግባር የተገነባ ትውልድ የመቅረፁን ኃላፊነት መወጣት አለበት፡፡

በተጨማሪም ለትውልድ ሥነምግባር ግንባታ መሠረት የትምህርት ተቋማት ናቸው፡፡ ከቤተሰብና ከህብረተሰቡ ቀጥሎ ትውልዱን በመልካም ሥነምግባር ለመገንባት ትልቅ ኃላፊነት ያለባቸው የትምህርት ተቋማት ናቸው፡፡ መምህራን ከሚሰጡት የትምህርት እውቀት ባሻገር በሥነምግባራቸው አርዓያ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ከተፃፈው ሥርዓተ ትምህርት ባሻገር መምህራን የሚያደርጉት ተግባርና እያንዳንዱ እንቅስቃሴ ሌላው በተማሪዎች የሚነበብ ድብቁ ሥርዓተ ትምህርት ነው፡፡

ስለዚህ ተማሪዎች የሚያነቡት ሁለቱንም ስርዓተ ትምህርቶች ነውና መምህራን በመልካም ሥነምግባር ጭምር አርዓያ ሊሆኑላቸው ይገባል፡፡ ዛሬ ለተማሪዎቹ አርዓያ መሆን ያልቻለ መምህር ነገ በተለያዩ ተቋማት ከሚሰሩ ተማሪዎቹ መልካም ሥነምግባርን ወይም ከብልሹ አሰራር የፀዳ አገልግሎትን መጠበቅ የለበትም፡፡ ከመምህሩ ሌላ በትምህርት ተቋማት ውስጥ በየደረጃው ያሉ የአስተዳደር ሠራተኞች በሚሰጡት መልካም አገልግሎት ለተማሪዎቻቸው አርዓያ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ይህንን በማድረግም በመልካም ሥነምግባር የተገነባ ትውልድን የመገንባት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡

እንዲሁም ለትውልድ ሥነምግባር ግንባታ መሠረት የኃይማኖት ተቋማት ናቸው፡፡ የትውልድን ሥነምግባር በመቅረጽ ረገድ የኃይማኖት ተቋማት ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ምዕመናን ወደሚያመልኩበት ተቋም የሚመጡት በፈቃዳቸው ነው፡፡ በእምነታቸው ውስጥ ያሉ እሴቶችንም ወደውና ፈቅደው ይጠብቋቸዋል፡፡ ይህ ትውልድን በመልካም ሥነምግባር ለመቅረጽ ትልቅ አጋጣሚ ነው፡፡ በመሆኑም እያንዳንዱ የእምነት ተቋም ምዕመኑን ስለመልካም ሥነምግባር በማስተማር፣ በእየተሰማራበት ቦታም የመልካም ሥነምግባር ፍሬዎችን እንዲያሳይ በማበረታታትና በመምከር በመልካም ሥነምግባር የተገነባ ዜጋን የመፍጠር ኃላፊነት አለባቸው፡፡

ለትውልድ ሥነምግባር ግንባታ መሠረት የአንበሳውን ሚና ከሚጫወቱት መካከል የሚዲያ ተቋማት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ሚዲዎች የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማስጨበጥ ድርሻቸው የጎላ መሆኑና ወጣቱ ትውልድም በስፋት እየተጠቀመበት የሚገኝ ነው፡፡ በተለይም ማህበራዊ ሚዲያው ወጣቱ ትውልድ ላይ ትልቅ ተፅዕኖ እየፈጠረ ያለ የሚዲያ አንዱ አካል ነው፡፡ በመሆኑም ትውልድን በመልካም ሥነምግባር በመገንባት መልካም እሴቶችን የሚጠብቁ፣ በሀገሪቱ የልማት እንቅስቃሴ የበኩላቸውን ድርሻ የሚያበረክቱበትና በእድገቱም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ትውልድን በመልካም ሥነምግባር እንዲታነፁ በማድረግ የሚዲያ ተቋማት ድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡

ከነዚህ በተጨማሪ ለትውልድ ሥነምግባር ግንባታ መሠረት የመንግስትና የግል ተቋማት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የመንግስትም ሆኑ የግል ተቋማት ሠራተኞቻቸውን በመልካም ሥነምግባር የመገንባት ኃላፊነት አለባቸው፡፡ እቅዳቸውን ለማሳካት የተመደበላቸውን በጀትና ንብረት በአግባቡ ለመጠቀም በመልካም ሥነምግባር የተገነባ ሠራተኛ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ስለዚህ የሥነምግባር ጉዳይን አጀንዳቸው አድርገው ከየእለት ተግባራቸው ጋር ሊያስተሳስሩት ይገባል፡፡ እሴቶቻችን ናቸው ብለው ያወጧቸው ቁምነገሮችም ከፅሁፍ አልፈው በእያንዳንዱ ሠራተኛ የዕለት ተዕለት የሥራ ውሎ ላይ ማንፀባረቅ አለባቸው፡፡

መልካም ሥነምግባር በቅጥር፣ በሠራተኛ ምልመላ፣ በእድገትና ዝውውር ላይ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራ ይገባል፡፡ የሥራ ኃላፊዎችም ሠራተኞቻቸው መልካም ሥነምግባርን የሚያጎለብቱበት ስልጠናዎችን ከማመቻቸት ባሻገር ራሳቸው የመልካም ሥነምግባር አርዓያ ሆነው መገኘት ይጠበቅባቸዋል፡፡

በአጠቃላይ በትውልድ ሥነምግባር እና ሞራል እሴት ግንባታ ተገቢውን ሚና ከመወጣት አንፃር ሁሉም አካላት ትኩረት ማድረግ አስፈላጊ ነው። በሥነምግባር የታነፀ ትውልድ፣ ሙስና እና ብልሹ አሠራርን ከመጠየፍ ባሻገር ይታገላል፣ ለአገር-መንግስት ግንባታም የላቀ ሚና መጫወት ይችላል።

ከሙስና የፀዳች እና የበለፀገች ኢትዮጵያን ዕውን እናድርግ!

#NCRS ሞባይል መተግበሪያ

#ለAndroid ስልክ ተጠቃሚዎች
https://play.google.com/store/apps/details

#ለApple or iPhone ስልክ ተጠቃሚዎች
https://apps.apple.com/us/app/ncrs/id6593662319
ስልጠናው በሥነምግባር የታነፀ አገልግሎት ለመስጠት እንዳነሳሳቸው የትራፊክ ፖሊስ አመራርና አባላት ተናገሩ

*******

(የፌ.ሥ.ፀ.ሙ.ኮ መጋቢት 15/2017 ዓ.ም አዲስ አበባ) ስልጠናው በሥነምግባር የታነፀ አገልግሎት ለመስጠት እንዳነሳሳቸው የአዲስ አበባ የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን በሰጠው ስልጠና የተሳተፉ የትራፊክ ፖሊስ አመራርና አባላት መናገራቸው ተገልጿል።

ኮሚሽኑ ለሁሉም ክፍለ ከተማ የትራፊክ ፖሊስ ዲቭዥን አመራርና አባላት በሙያ ሥነምግባር እና ሙስና መከላከል ዙሪያ ለ13 ዙር ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ተጠናቋል።

የትራፊክ ፖሊሲ አመራርና አባላት ሙያዊ ብቃትን ያረጋገጠና በህዝብ ዘንድ ታማኝ የሆነ አገልግሎት መስጠት እንደሚገባ ስልጠናውን የሰጡት በኮሚሽኑ የሥነምግባርና ፀረ-ሙስና ስልጠና ዳ/ዳይሬክተር አቶ ጀንበሩ ኢርኮ ገልጸዋል።

የሥነምግባር ጉድለት ታማኝነትን ይሸረሽራል፣ ማህበራዊ ተቀባይነትን ያሳጣል፣ ጤናማ የሥራ ግንኙነትን ይቀንሳል እንዲሁም የጥቅም ግጭት ይፈጥራል ብለዋል።

ስልጠናው በሁሉም ክፍለ ከተማ ለሚገኙ የትራፊክ ፖሊስ አመራርና አባላት በዙር ሲሰጥ የነበረው ስልጠና በስኬት መጠናቀቁን አቶ ጀንበሩ ጠቅሰዋል።

በስልጠናው የተሳተፉት የለሚ ኩራ ክ/ከተማ ትራፊክ ፖሊስ ዲቭዥን ዋና ኢንስፔክተር ጌቱ ግርማ ስልጠናው በሥነምግባር የታነፀ አገልግሎት ለመስጠት እንዳነሳሳቸው ተናግረዋል።

በስልጠናው ያገኙትን እውቀት ወደ ተግባር በመቀየር ህብረተሰባችንን በመልካም ሥነምግባር ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን መግለፃቸውን ከኮሚሽኑ የማህበራዊ ትስስር ገፅ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

ስልጠናው ከፍተኛ እውቀትና ልምድ ባለው አሰልጣኝ የተሰጠ በመሆኑ በመልካም ሥነምግባር ማገልገል የሚያስገኘውን ጠቀሜታ በመረዳት ለተሻለ ሥራ ያነሳሳ መሆኑን በስልጠናው የተሳተፉት ኢንስፔክተር እሌኒ ሙሴ ተናግረዋል።

የወሰድነው ስልጠና በግል ህይወታችንና በሥራችን ለውጥ የሚያመጣ መሆኑን ተረድተን ህዝብና ሀገርን ሙያዊ ሥነምግባርን በተላበሰ መልኩ ለማገልገል እንደተነሳሱ በስልጠናው የተሳተፉት ዋና ሳጅን ትዕግስት ታየው ገልፀዋል።

ከሙስና የፀዳች እና የበለፀገች ኢትዮጵያን ዕውን እናድርግ!

#NCRS ሞባይል መተግበሪያ

#ለAndroid ስልክ ተጠቃሚዎች
https://play.google.com/store/apps/details

#ለApple or iPhone ስልክ ተጠቃሚዎች
https://apps.apple.com/us/app/ncrs/id6593662319
የንብረት ማስመለስ አዋጁ አስፈላጊነት እና ይዞ የመጣው አዲስ ነገር (ክፍል ሶስት)

********************

1. የንብረት ማስመለስ ሥራ ኃላፊነትን በተመለከተ የተሰጠ ስልጣን ወይም ኃላፊነት፡- የንብረት ማስመለስ ሥራ የብዙ ተቋማት ቅንጅትን/ትብብርን የሚፈልግ ሥራ ሆኖ በተማከለ ሁኔታ በአንድ የህግ ማስከበር ተቋም/ዐቃቤ ህግ የሚመራ ስራ ነው፡፡ የፌደራል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽንም ለንብረት ማስመለስ አዋጁ አጋዥና መነሻ የሚሆን የሀብት ማወቅና ምዝገባ እንዲሁም የማጣራት ሥራ እየሰራ ይገኛል፡፡ ይህም ለንብረት ማስመለስ አዋጁ ጉልህ አስተዋጽኦ አለው፡፡

2. ዐቃቤ ህግ ራሱ በሚመረምርበት ጉዳይ ላይ ዕግድ ትዕዛዝ በራሱ ማውጣቱ ከማረጋገጥ፣ ሚዛናዊነት እንዲሁም ከገለልተኛነት አንፃር የማይጋጭ ስለመሆኑ፤ በተመሳሳይ እንደማንኛውም የመንግስት ሥራ ስራው ለብልሹ አሰራር ሊጋለጥ ይችላል፡፡ ነገር ግን ዋናው ቁምነገር ዜጎች ላልተገባ የመብት ጥሰት እንዳይዳረጉ ምን መንገድ አለ የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ በመሠረቱ በዚህ አዋጅ ዐቃቤ ህግ ተቋም አንድም አስተዳደራዊ በሆነ መልኩ ውርስ ሊፈፅም የሚችልበት ምንም መብት አልሰጠም፡፡ የትኛውም ክርክርም ሆነ ውርስ ትዕዛዝ መስጠት የሚችለው ፍርድ ቤት ነው፡፡ በፍርድ ቤት ደግሞ አንዱ ፍርድ ቤት ላይ የተፈፀመን የትኛውንም አይነት ስህተት የማስተካከያ የይግባኝ ስርዓት መኖሩ የታወቀ ነው፡፡

ስለዚህ ከምርመራ የይግባኝ ደረጃውን አልፎ እንስከሚሰጥ የመጨረሻ ውሳኔ ድረስ ሊደርሱ የሚችሉ የሥነምግባር ግድፈቶችን የሚጣሩበት እና ሊስተካከሉ የሚችልበትን ሥርዓት አለው፡፡ ከዚህ ወጪ ፍትህ ሚኒስቴር ግልፀኝነት የሚፈጥር እና ይህ ስርዓት የሚመራበትን ውስጣዊ የአሠራር ስርዓቶችን በህግ የሚዘረጋ ይሆናል፡፡ ይህም ጠንካራ የሥነምግባር ክትትል እና አቤቱታ መቀበያ ስርዓትንም ያካትታል፡፡

3. ዐቃቤ ህግ ራሱ በሚመረምርበት ጉዳይ ላይ ዕግድ ትዕዛዝ በራሱ ማውጣቱ ከማረጋገጥ፣ ሚዛናዊነት እንዲሁም ከገለልተኛነት አንፃር የማይጋጭ ስለመሆኑ፤ ይህ ጉዳይ በዐቃቤ ህግ ለ72 ሰዓት አስተዳደራዊ ዕግድ የሚሰጥበትን ጉዳይ በተመለከተ ሲሆን፣ ይህም በተመሳሳይ በዚህ ህግ አዲስ የመጣ አይደለም፡፡ በህግ ስርዓታችን ውስጥ ቀድሞም የነበረ ነው፡፡ በፊት ዐቃቤ ህግ ኃላፊ 48 ሰዓት የማገድ ስልጣኑን በዚህ ህግ ወደ 72 ሰዓት ከፍ እንዲል አድርጓል፡፡ በመሰረቱ ይህ የዕግድ ሁኔታ መርህ ሳይሆን ልዩ ሁኔታ ነው፡፡ ስለዚህ በጠባቡ ነው ስራ ላይ የሚውለው፡፡

አንደኛ ይህን ዕግድ ዐቃቤ ህግ ሳይሆን የተቋሙ/የዘርፉ የበላይ ኃላፊ ብቻ ነው ሊሰጥ የሚችለው፡፡ ስለዚህ በዘፈቀደ ለሁሉም ባለሙያ የተሰጠ ስልጣን አለመሆኑን ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ይህ ዕግድ ግዜያዊ እንጂ ገደብ አልባ እና እስከመጨረሻው ጸንቶ የሚቆይ አይደለም፡፡ ዐቃቤ ህግ ይህን ዕግድ ካሰጠ በኋላ መደበኛ ዕግድ ለፍርድ ቤት አቅረቦ ማስቀየር አለበት፡፡ ይህ ካልሆነ ግን በአዋጁ የተቀመጡትን የጊዜ ገደቦች ውስጥ ዕግዱ ቀሪ የሚሆንበትን አግባብ ተመላክቷል፡፡ ወደ 72 ሰዓት ከፍ ያለው ከዚህ በፊት የነበረው የ48 ሰዓት ዕግድ በተግባር ውጤታማነቱ ላይ ተግዳሮት ስለገጠመው ነው፡፡

4. የመያዝና የዕግድ ትዕዛዝ የማያርፍባቸው የንብረት አይነቶች፤ የእለት መተዳደሪያ ወይም ሙያዊ ሥራ ለመስራት የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች፣ የቤት ውስጥ መገልገያ የሆኑ ዕቃዎች፣ ለእለት ኑሮ የሚሆን እና የስድስት ወር ወይም ፍርድ ቤቱ በልዩ ሁኔታ ለሚወስነው ጊዜ የሚቆይ ስንቅ (ለምግብነት የሚውል) ንብረቶች በመርህ ደረጃ ሊያዙ ወይም ሊታገዱ አይችሉም፡፡ ሆኖም ቁሳቁሶቹ ውድ ከሆኑ ማዕድናት ወይም ከፍተኛ ዋጋ ካለው የእደ ጥበብ ሥራዎች የተሰሩ ከሆነ ወይም ንብረቱ የወንጀል ፍሬ መሆኑ በግልጽ ከታወቀ በምንም ዓይነት ሁኔታ ተጠርጣሪው ወይም ተከሳሹ ከወንጀል ፍሬው የመጠቀም መብት ስለማይኖረው የዕግድ ወይም የመያዝ ትዕዛዝ ያርፍበታል፡፡

5. የተወረሰ ንብረት በተመለከተ (እጣ ፈንታ)፤ በወንጀል የተገኘ ሀብትን ከማስመለስ አንጻር በአለምዓቀፍ ደረጃ የተቀመጡ ስምምነቶች እና የአፈጻጸም ግምገማ ሰነዶች እንዳስቀመጡት አንድ ሀገር በጣም ተጋላጭ የሆነባቸውን የተደራጁና ኢኮኖሚያዊ ወንጀሎች የሚለይበትን ጥናት ማከናወን እንዳለበት እና በዚህ መንገድ የተለዩ ወንጀሎችን በመለየት፣ በመመርመር፣ በመክሰስ፣ ተገቢውንና አስተማሪ ቅጣት በመጣል እንዲሁም የተመዘበረውን ሀብት በማስመለስ ተገቢውን የህግ ማስከበር ስራ መስራት እንዳለበት ሲያስገነዝቡ፣ ከዚህ አሠራር ጀርባ ያለው ምክንያት ደግሞ ውስን የሆነውን ሀብት ለህግ የበላይነት እና የፍትህ ስራ ለማዋል ቅድሚያ የሚሰጠው በጣም ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ለሚያደርሰው ወንጀል አይነት ነው በሚል ነው፡፡

ስለሆነም ሁሉንም ወንጀል መርምሮ ክስ ለማቅረብ እና ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ በቂ ሀብት እንደማይኖር የታወቀ በመሆኑ ምክንያት አንዳንድ ሀገራት በወንጀል የተገኘ ነው በሚል መርምረውና ክስ አቅርበው በፍርድ ቤት እንዲወረስ ውሳኔ የሚያሰጡበትን ንብረት መልሰው ለወንጀል ፍትህ አስተዳደር ተግባር ያውላሉ፡፡ በዚህ አግባብ ይህ የንብረት ማስመለስ አዋጅ ተመሳሳይ አቋም በመያዝ ከፋይናንስ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር የተወሰነውን የተወረሰ ሀብት ለወንጀል ፍትህ አስተዳደር ለማዋል የሚቻልበትን ሁኔታ አስቀምጧል፡፡

ከሙስና የፀዳች እና የበለፀገች ኢትዮጵያን ዕውን እናድርግ!

#NCRS ሞባይል መተግበሪያ

#ለAndroid ስልክ ተጠቃሚዎች
https://play.google.com/store/apps/details

#ለApple or iPhone ስልክ ተጠቃሚዎች
https://apps.apple.com/us/app/ncrs/id6593662319
ኮሚሽነር ሳሙኤል ኡርቃቶ (ፒኤችዲ) በሥነምግባር ግንባታ እና ሙስና መከላከል ዙሪያ ከአዘርባጃን አምባሳደር ሩስላን ናስቦቭ ጋር ተወያዩ

***************

(የፌ.ሥ.ፀ.ሙ.ኮ መጋቢት 16/2017 ዓ.ም አዲስ አበባ) የፌደራል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሳሙኤል ኡርቃቶ (ፒኤችዲ) በሥነምግባር ግንባታ እና ሙስና መከላከል ዙሪያ ከአዘርባጃን አምባሳደር ሩስላን ናስቦቭ ጋር ውይይት አካሂደዋል፡፡

በውይይቱ የአዘርባጃን የመልካም ሥነምግባር እና የሙስና መከላከል ባህል ግንባታ ዙሪያ የተገኙ ውጤቶች እንደመልካም ተሞክሮ የሚወሰዱ መሆኑ ተመላክቷል።

በቀጣይም በአገራችን የተጀመረውን የሥነምግባር ግንባታ፣ የሙስና ቅድመ-መከላከል እና የሙስና ወንጀል ሕግ የማስከበር ሥራዎችን ለማሻሻል የሚያስችል የልምድ ልውውጥ የሚደረግ መሆኑ ተገልጿል።

ይህን ትብብር ለማጠናከር በቀጣይ በኢትዮጵያ እና አዛርባጃን የፀረ-ሙስና ተቋማት መካከል የትብብር ስምምነት ለመፈራረም ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

ከሙስና የፀዳች እና የበለፀገች ኢትዮጵያን ዕውን እናድርግ!

#NCRS ሞባይል መተግበሪያ

#ለAndroid ስልክ ተጠቃሚዎች
https://play.google.com/store/apps/details

#ለApple or iPhone ስልክ ተጠቃሚዎች
https://apps.apple.com/us/app/ncrs/id6593662319
የሙስና ወንጀል ህግ የማስከበር ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራርን ማዘመን አስፈላጊ ነው - ም/ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

*******************

(የፌ.ሥ.ፀ.ሙ.ኮ መጋቢት 16/2017 ዓ.ም አዲስ አበባ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የሙስና ወንጀል ሕግ የማስከበር ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራርን ማዘመን አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

የሙስና ወንጀል ሕግ የማስከበር ሥራዎች የባለድርሻ ተቋማት የምክክር መድረክ ዛሬ ተካሂዷል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ የትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ በውይይታችን የባለድርሻ አካላቱ ቅንጅታዊ አሰራርና የስራ አፈጻጸም ምን እንደሚመስል ምክክር አድርገናል ብለዋል።

ተቋማቱ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ቅንጅታዊ አሰራርን በማዘመን፣ በፀረ-ሙስና ትግል ሀገራዊ የጋራ ተልዕኮን ማዕከል በማድረግ የሚያከናውኗቸውን ተግባራት አጠናክረው እንዲቀጥሉ አቅጣጫ መቀመጡንም አመላክተዋል።

ከሙስና የፀዳች እና የበለፀገች ኢትዮጵያን ዕውን እናድርግ!

#NCRS ሞባይል መተግበሪያ

#ለAndroid ስልክ ተጠቃሚዎች
https://play.google.com/store/apps/details

#ለApple or iPhone ስልክ ተጠቃሚዎች
https://apps.apple.com/us/app/ncrs/id6593662319