Event Addis Media
9.07K subscribers
5.23K photos
5 videos
3 files
3.94K links
Connect with Addis Ababa's artistic community! Find out about art exhibitions, music events, workshops, and cultural experiences. Contact: @Tmanaye
Download Telegram
አርቲስት ነፃነት ወርቅነህ በተሻለ ጤንነት ላይ እንደሚገኝ አስታወቀ

ተዋናይ፣ ደራሲ፣ ዳይሬክተር እና የቴሌቪዥን ፕሮግራም አቅራቢው ነፃነት ወርቅነህ ለህክምና ወደ ሀገረ ህንድ መሄዱን የሚገልጽ ማስታወሻ በግል የፌስቡክ ገፁ ማጋራቱ ይታወሳል።

ይህን ተከትሎ በርካታ ወዳጆቹ ፣ የሙያ አጋሮቹ እና አድናቂዎች ለአርቲስቱ መልካም ምኞታቸውን ሲገልፁ ነበር።

ገሚሶቹ ደግሞ አርቲስቱ ላይ ያጋጠመው የጤና እክል የከፋ ይሆናል የሚል ስጋታቸውን ጭምር ሲገልፁ እንደነበር ይታወሳል።

ያም ሆኖ ግን አርቲስቱ ጉዳዩን አስመልክቶ በማህበራዊ ትስስር ገፁ ባጋራው መልዕክቱ በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል።

በተጨማሪም መልካም ምኞታቸውን ለተመኙለት ምስጋናውን በማቅረብ በጥቂት ቀናት ውስጥ የህክምና ክትትሉን አገባዶ ወደ ሀገር ቤት እንደሚመለስ ተናግሯል።

ለተጨማሪው :https://t.me/EventAddis1
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሞያዎች ማኀበር

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማኅበር ሐምሌ 6 2016 ዓ.ም ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ በሦስት ዋና ዋና አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል።

በጉባኤውም ያለፈው ሁለት ዓመት የሥራ ክንውን እና የቀጣይ ዓመት ዕቅድ ቀርቦ ሰፊ ግምገማ ተደርጎበታል።

ላለፉት ሁለት ዓመታት ማኅበሩን በፕሬዝዳንትነት ያገለገለው ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ ባለበት የሥራ መደራረብ ምክንያት ማኅበሩን ተተኪዎች እንዲመሩት በመጠየቁ በጠቅላላ ጉባኤው በክብር ተሸኝቷል።

በማኅበሩ መተዳደሪያ ደንብ መሰረት በሥራ ላይ ያሉት የሥራ አስፈጻሚ አባላት የቆይታ ጊዜያቸው ስለተጠናቀቀ የተጓደሉትን ጨምሮ እንደ አዲስ የዘጠኝ የሥራ አስፈጻሚ አባላት ምርጫ ተካሂዷል። በዚህም መሰረት ሶስት ነባር ሥራ አስፈጻሚዎችና ስምንት አዳዲስ አባላት በእጩነት ቀርበው ምርጫ ተደርጓል። በጉባኤው ለምርጫ ከቀረቡ እጩዎች መካከል ዘጠኝ ሥራ አስፈጻሚዎች በጠቅላላ ጉባዔው በድምፅ ምርጫ ተመርጠዋል።

በጠቅላላ ጉባዔው ሥራ አስፈጻሚ ሆነው የተመጡት እታገኘሁ መኮነን፣ ትብለፅ ተስፋዬ፣ ሲሳይ ሳህሉ፣ሳሙኤል አባተ፣ ዳግማዊት ግርማ፣ዳዊት ታደሰ፣መርሻ ጥሩነህ፣ማናዬ እውነቱ፣ዳዊት አስታጥቄ ናቸው።

ከተመረጡት ዘጠኝ ሥራ አስፈጻሚዎች መካከል በተደገው የፕሬዝዳንት የምርጫ ውድድር ጋዜጠኛ እታገኘሁ መኮነን አብላጫ ድምጽ በማግኘት የማህበሩ ፕሬዝዳንት ሆና ተመርጣለች፡፡

አዲሱ ሥራ አስፈጻሚ የማኅበሩን ጠንካራጰ ጎኖች በማስቀጠልና ከአባላት ጋር በመተባበር ለጋዜጠኞች መብት መከበር እና ለኢትዮጵያ ሚዲያ አጠቃላይ ዕድገትና ነፃነት እንደሚሰራ ቃል ገብቷል።

ለተጨማሪው :https://t.me/EventAddis1
9ኛው የኢትዮጵያ የልብ ሕክምና ባለሞያዎች ዓመታዊ ጉባኤ ተካሄደ።

9ኛው የኢትዮጵያ የልብ ሕክምና ባለሞያዎች ዓመታዊ ጉባኤ ከሐምሌ 6 እስከ 7 ቀን በኃይሌ ግራንድ ሆቴል አዲስ አበባ ተካሄደ።

ለተከታታይ ሁለት ቀናት በተካሄደው በዚህ ጉባኤ የልብ ሕክምና አገልግሎትን በሀገሪቱ ለማስፋት የተሰሩ ልዩ ልዩ ሥራዎች ለማኅበሩ አባላት እና ጥሪ ለተደረገላቸው እንግዶች ገለጻ ተደርጓል። ከዚህም ባሻገር በመስኩ የተሰማሩ የሀገር ውስጥ እና የውጪ ሃገር ተቋማት ምርቶቻቸውን እና አገልግሎቶቻቸውን ለተሳታፊዎች ለ ዕይታ አቅርበዋል። በልብ ሕክምና ዘርፍ የተሰሩ ልዩ ልዩ ጥናቶች ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል።

የማኅበሩ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ከፈለኝ ደጀኔ የልብ ሕክምና ባለሞያተኞች ማኅበር ባለፉት ጊዜያት ማኅበሩ እና የልብ ሕክምና አገልግሎቶች እንዲጠናከሩ በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ጠቅሰው፤ የልብ ሕክምና አገልግሎት ተደራሽነት እና ጥራት እየጨመረ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ማኅበሩ የልብ ሕክምና አገልግሎት እንዲጠናከር ከልብ ሕሙማን ማኅብር እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እንደሚሰራም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የልብ ሕክምና ባለሞያተኞች ማኅበር በመስኩ የተሰማሩ ከ300 በላይ አባላት በመላው ሀገራችን ክፍል ያሉት ሲሆን ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ የልብ ሕክምና አገልግሎት አስጣጥን ለማሻሻል በርካታ ሥራዎችን እየሰራ ይገኛል።

ለተጨማሪው :https://t.me/EventAddis1
ዕውቁ ደራሲ እና ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ የተዘከረበት መርሃ ግብር ተካሄደ

አብሮ አደግ በፍቅር የመረዳጃ ማሕበር ያዘጋጀው የዕውቁ ደራሲ እና ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ የተዘከረበት መርሃ ግብር  በተግባረ ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ መሰብሰቢያ አዳራሽ ተካሂዷል። በዚህ መርሃ ግብር የገነነ ስራዎች እና ሕይወት በዝርዝር መዘከሩ ተነግሯል።

መርሃ ግብሩን በንግግር የከፈቱት የማሕበሩ ሰብሳቢ አቶ ቤዛው ሹምዬ ማሕበሩ ባለፉት አስር ዓመታት ስላደረጋቸው ዕንቅስቃሴ አትተዋል። አክለውም "ያለፉትን በመዘከር፣ የሰሩትን በማክበር ተተኪዎችን እንፍጠር!" በሚል መሪ ቃል ስለተዘጋጀው ይህ መርሃ ግብር በዝርዝር አብራርተዋል።

የገነነ መኩሪያ የሕይወት ታሪክ በንባብ የቀረበ ሲሆን፣ በሕይወት ዘመኑ ያበረከታቸው የተለያዩ ስራዎች በመታሰቢያ መርሃ ግብሩ ላይ ተዘክረዋል። ከገነነ መኩሪያ "ኢሕአፓ እና ስፖርት" መጽሐፍ የተቀነጨበ ስራ ለዕድምተኞች በትረካ ቀርቧል።

በተጨማሪም፣ ለቀድሞ የእግርኳስ ተጨዋቾች ተካ ገለታ፣ ግርማ አበበ፣ እና ጌቱ መልካ፤ ለቀድሞ ቦክሰኛ ደረጀ ደሱ እና ለድምጻውያኑ ጎሳዬ ተስፋዬ እና አብዱ ኪያር፣ ለሁለገቡ የኪነ ጥበብ ሰው ዳዊት አፈወርቅ፣ ለተዋናይ ተሰማ ገለቱ፣ ለኬሮግራፈር ዳንኤል ደሳለኝ፣ ለጋዜጠኛ እንግዱ ወልዴ እና ለሕግ ባለሞያዋ ሰናይት ፍስሐ (ፕ/ር) ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ምክትል ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ እና የገነነ መኩሪያ ባለቤት ወይዘሮ አስቴር አየለ ጨምሮ ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በመርሃ ግብሩ ላይ ታድመዋል።

አብሮ አደግ በፍቅር የመረዳጃ ማሕበር የተመሰረተበትን አስረኛ ዓመት በዚሁ መርሃ ግብር ላይ ተከብሯል።

መረጃው የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ነው።

https://t.me/EventAddis1
"የሚስቶቼ ባሎች"ተውኔት ነገ ይሰናበታል

በደራሲ አበባየሁ ታደሰ ተደርሶ በተስፋዬ ገ/ማርያም እና ይገረም ደጀኔ የተዘጋጀው " የሚስቶቼ ባሎች " ተውኔት ነገ ረቡዕ ሐምሌ 10 2016 ዓ.ም ከምሽቱ 12:00 ጀምሮ  ከዓለም ሲኒማ መድረክ በክብር እንደሚሰናበት ኤቨንት አዲስ ድረገፅ ከአዘጋጆቹ ሰምቷል።

በሐምሌት መልቲሚዲያ የቀረበው"የሚስቶቼ ባሎች " ተውኔት ላይ ይገረም ደጀኔ፣ ሸዊት ከበደ ፣የምስራች ግርማ ፣ ብሩክ ምናሴና ሔኖክ ብርሃኑ በተዋናይነት ተሳትፈዋል።

ቴአትሩ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር፣ በአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ እንዲሁም በሀገርፍቅር ቴአትር አዳራሽ ለእይታ ቀርቦ የነበረ ሲሆን ከዓመታት በኃላ ባሳለፍነው ዓመት ሰኔ 21 2015 ዓ.ም ነበር ወደ መድረክ የተመለሰው።

https://t.me/EventAddis1

https://t.me/EventAddis1
"ተንኳሾቹ" መጽሐፍ ለንባብ በቃ

ነዋሪነቱን በደቡብ ኮሪያ ያደረገው ጋዜጠኛ ዳዊት ንጉሡ ረታ (ዳ ን ረ ) ለራሱ ሁለተኛ የሆነው መፅሃፉን " ተንኳሾቹ " በሚል ርዕስ ለህትመት አብቅቷል።

" ተንኳሾቹ " መፅሃፍ 310 ገፆች ያሉትና ሃያ አንጋፋና ወጣት አዋቂዎችንና ታዋቂዎችን በእንግድነት ጋብዞ ለአንባቢያን ኮርኳሪ ሃሳቦቻቸውን እንዲያካፍሉ ያስቻለበት መፅሃፉ እንደሆነ ዳዊት ንጉሡ ለዝግጅት ክፍላችን ተናግሯል።

ከዚህ ቀደም "በ97 እና ሌሎች ታሪኮች" በሚል የመጀመሪያ መፅሃፉን ያቀረበልን ዳዊት ሁለተኛ መፅሃፉ ተንኳሾቹን በአገር ውስጥ በብር አራት መቶ ሃምሳ ብቻ ለአንባቢያን እንዳቀረበ ገልፆልናል።

መጽሃፉ የመጀመሪያ ዙር ውስን ቁጥር  ህትመቱ በደቡብ ኮሪያ የተከናወነ ሲሆን ለአገር ቤት አንባቢያን ደግሞ በአገር ውስጥ ለማሳተም ከአሳታሚዎችና አከፋፋዮች ጋር ውይይት በማድረግ ሂደት ላይ እንዳለም ጨምሮ ተናግሯል።

https://t.me/EventAddis1
"የማያረጅ ውበት" የሥዕል አውደርዕይ ተከፈተ

የሠዓሊ እንዳልካቸው ተፈራ የሥዕል ስራዎች የቀረቡበት "የማያረጅ ውበት" የሥዕል አውደርዕይ ትላንት ረቡዕ ሐምሌ 10 2016 ዓ.ም ጀምሮ ካዛንቺስ በሚገኘው ፈንድቃ የባህል ማዕከል ውስጥ ለእይታ በቅቷል።

ይህ የሥዕል አወድርዕይ እስከ ሐምሌ 24  2016 ዓ.ም እንደሚቆይ ኤቨንት አዲስ ድረገፅ ሰምቷል።

ለተጨማሪው :https://t.me/EventAddis1
በእረፍት ቀንዎ ቴአትር ይመለከቱ !

አንጋፋው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር  እና የቦሌው ዓለም ሲኒማ አርብ፣ ቅዳሜ እና እሁድ እነዚህን ተውኔቶች ለታዳሚያን ያቀርባሉ።

📍 የፍቅር ካቴና

ድርሰትና ዝግጅት: አለልኝ መኳንት ፅጌ
ቀን: አርብ
ሰዓት: 12:00
ቦታ: ዓለም ሲኒማ

📍 "እሳት ወይ አበባ"

ድርሰት: ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን እንደጻፈው
ዳንስና ዳንስ ቅንብር: ሽፈራው ታሪኩ ቢረጋ
ቀን: አርብ
ሰዓት:11:30
ቦታ: ብሔራዊ ቴአትር

📍 ባሎች እና ሚስቶች

ድርሰት: ውዱ አለን
አዘጋጅ: ሳሙኤል ተስፋዬ
ቀን: ቅዳሜ
ሰዓት: 8:00
ቦታ: ብሔራዊ ቴአትር

📍 ባቡሩ

ድርሰት: አርኖልድ ሪድሊ
አዘጋጅ:ራሔል ተሾመ መሐመድ
ቀን: ቅዳሜ
ሰዓት:11:30
ቦታ: ብሔራዊ ቴአትር

📍 ሸምጋይ

ድርሰት:ታደለ አያሌው
አዘጋጅ: ሳሙኤል ተስፋዬ
ቀን: እሁድ
ሰዓት: 8:00
ቦታ: ብሔራዊ ቴአትር

📍 እምዩ ብረቷ

ድርሰት: ቤልቶልት ብሬሽት
አዘጋጅ: ማንያዘዋል እንዳሻው
ቀን: እሁድ
ሰዓት:11:30
ቦታ: ብሔራዊ ቴአትር

የእናንተው ኤቨንት አዲስ ድረገፅ መልካም የእረፍት ቀን ይሁንላችሁ ይላል !

ለተጨማሪው: https://t.me/EventAddis1
የሙዚቃ አቀናባሪው ያምሉ ሞላና ወጣቷ ድምጻዊት መና ወረደ በጋራ የሰሩት ግሚስ አልበም ተለቀቀ

"አዲስ ቀለም" የተሰኘ ርዕስ የተሰጠውና የሙዚቃ አቀናባሪው ያምሉ ሞላ እና ወጣቷ ድምጻዊት መና ወረደ የተጣምሩበት ግሚስ(EP) የሙዚቃ አልበም በስፖቲፋይ የሙዚቃ መተግበሪያ በኩል ለአድማጮች ተለቋል።

"አዲስ ቀለም" ግሚስ አልበም በውስጡ ምንድነው ፣ ኤሌክትሪክ፣ ማዕዘን፣ተው ተው፣አንድ ሰሞን የተሰኙ አምስት ሙዚቃዎችን የያዘ እንደሆነ ኤቨንት አዲስ ድረገፅ ተመልክቷል።

የግሚስ አልበሙ ግጥም ፣ ዜማ፣ እንዲሁም ከሙዚቃው ቅንብር እስከ ማስተሪንጉ ድረስ በያምሉ ሞላ ተሰርቷል።

በተጨማሪም በከበሮ አገረሰላም ሻፊ ፣ በመሰንቆ ሀዲንቆ፣በክራራ ፋሲካ ኃይሉ ተሳትፈዋል።

በአልበሙ ከተካተቱ ሙዚቃዎች ውስጥ "ተው ተው" የተሰኘው ሙዚቃ የበርካታ የአገራችን ሴቶች ሕይወት (የቤተሰብ ኃላፊነትን) የሚዳሰስ ሙዚቃ እንደሆነ ኤቨንት አዲስ ድረገፅ ከሙዚቀኛ ያምሉ ሞላ ሰምቷል።

ዛሬ ማለዳ በስፖቲፋይ የሙዚቃ መተግበሪያ የተለቀቀው አልበሙ አመሸሻ ላይ በዩቲዩብ በኩልም ይለቀቃል ተብሏል።

ለተጨማሪው: https://t.me/EventAddis1
📍 የሥነጽሑፍ ውይይት

በአዳም ረታ መጻሕፍት ላይ ውይይት

በኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት (ወመዘክር) የሚዘጋጅው " የወር ወንበር" መሰናዶ ላይ በዚህ ወር በደራሲ አዳም ረታ መጻሕፍት ላይ ያተኮር "አዳም ከአለፍ አገደም" የአዳም ረታ ሥራዎች ጥቂት ምልከታ" በሚል ርዕስ ዛሬ ቅዳሜ ሐምሌ 13 2016 ዓ.ም ከቀኑ 10:00 እስከ 12:00 በወመዘክር አዳራሽ ሥነጽሑፋዊ ውይይት ይካሄዳል።

በዚህ ሥነጽሐፋዊ ውይይት ላይ አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡ መነሻ ሀሳብ ያቀርባሉ ተብሏል።

በዝግጅቱ ላይ የሚገኙ ከሆነ ይህንን ቅፅ  https://bit.ly/3S45QS2 ይሙሉ ተብለዋል።

ለተጨማሪው: https://t.me/EventAddis1
📍የሥነጽሑፍ ውይይት

በ"ግርባብ ያ ደግ ሰው" መጽሐፍ ላይ ውይይት

በደራሲ ፍቃዱ አየልኝ "ግርባብ ያ ደግ ሰው" መጽሐፍ ላይ ዛሬ ቅዳሜ ሐምሌ 13 2016 ዓ.ም ከቀኑ 10:00 እስከ 12:00 አራት ኪሎ በሚገኙ ዋልያ መጻሕፍት ውስጥ ውይይት ይካሄዳል።

በዕለቱም በመጽሐፉ ላይ ሥነጽሑፍ ዳሰሳ እና ውይይት ይደረጋል ተብሏል።

አወያይ: ዮናስ ታረቀኝ

ዳሰሳ አቅራቢዎች: ምግባር ሲራጅና ዮሴፍ ይድነቃቸው

ለተጨማሪው: https://t.me/EventAddis1
"ኦሎምፒክ "ኮንሰርት ለሁለተኛ ጊዜ ተራዝሟል

አንጋፋ እና ወጣት ድምጻዊያን የሙዚቃ ስራዎቻቸውን ያቀርቡበታል በሚል ሲተዋወቅ የቆየው እና ዛሬ ሐምሌ 13 2016 ዓ.ም ከቀኑ 7:00 ጀምሮ ይካሄዳል የተባለው "ኦሎምፒክ 2024" የተሰኘ ኮንሰርት ለሁለተኛ ጊዜ ተራዝሟል።

ይህ ኮንሰርት ሐምሌ 6  2016 ዓ.ም ይካሄዳል ከተባለ በኃላ ወደዛሬ ሐምሌ 13  2016 ዓ.ም  እንደተራዘመ ይታወሳል።

ምናልባትም ኮንሰርቱ ሙሉበሙሉ ሊሰርዝ የሚችልበት እድል ሊኖር እንደሚችል ኤቨንት አዲስ ድረገፅ ከውስጥ ምንጮች ሰምቷል።

ይህ የሙዚቃ ኮንሰርት ሌብል ዋን ኢንተርቴይመንት እና ላላ ፕሮዳክሽን  በመተባበር ያዘጋጁት ነው።

የኮንሰርቱም ዋንኛ ዓላማ  የፓሪስ ኦሎምፒክ ተሳታፊ አትሌቶችን ለመደገፍ የተዘጋጀ ተብሏል።

ለተጨማሪው: https://t.me/EventAddis1
የኢትዮጵያ ቤተመጻሕፍት ክፍል በስፔን ማድሪድ

በስፔን ማድሪድ ብሔራዊ ቤተ-መጻሕፍት የኢትዮጵያ ቤተመጻሕፍት ክፍል እንደተከፈተ ተነግሯል።

የአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት ዋና ዳይሬክተር ውብአየሁ ማሞ እንደገለጹት በሀገሪቱ ብሄራዊ ቤተ-መጻሕፍት ቅጥር ግቢ የተደራጀው የኢትዮጵያ ቤተ-መጻሕፍት ክፍል የኢትዮጵያን ታሪክ ባህልና ቋንቋ ለዓለም ለማስተዋወቅ እንዲረዳ መደራጀቱን ገልፀዋል።

መጻሕፍቶቹ በስፔን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በሚገባ እንዲጠቀሙባቸው አመች በሆነ የዲጂታል መተግበሪያዎች ሳይቀር መገኘት እንደሚችሉ ዋና ዳይሬክተሩ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ለተጨማሪው: https://t.me/EventAddis1
ቤሪ ከረጅም ጊዜ በኃላ ወደ ሙዚቃ ተመልሳለች

ድምጻዊት ብስራት ኃ/ማርያም (ቤሪ) ከረጅም ጊዜ በኃላ በሙዚቃ ዝግጅት ወደ ሙዚቃው ተመልሳለች።

ዛሬ ሐምሌ 13 2016 ዓ.ም በቃና ዌርሐውስ በተዘጋጀው የሙዚቃ መሰናዶ ላይ በ"ልዩ ዝግጅት" የሙዚቃ ዝግጅቷን እንደምታቀርብ ኤቨንት አዲስ ድረገፅ ከድምጻዊት ብስራት ኃ/ማርያም ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

ድምጻዊት ብስራት ኃ/ማርያም(ቤሪ) ከዓመታት በፊት  "ከምን ነፃ ልውጣ" የተሰኘ አልበም ለአድማጮች አድርሳለች።

"ከምን ነፃ ልውጣ "አልበም ከአንድ ዜማ ውጪ የሙሉ አልበሙ ግጥም፣ዜማ እና ሙዚቃ ቅንብሩን የሰራው ኤልያስ መልካ ነው።

ይህ በፕላቲኒየም ሪከርድስ አከፋፋይነት በ2008 አ.ም ለአድማጭ የደረሰው የቤሪ "ከምን ነፃ ልውጣ" አልበም በሙዚቃዊ ሀሳብ መርቀቅ፣በዜማ ከፍ ማለት፣በሙዚቃ ቅንብር ሌላ እርምጃ የታየበት ተጠቃሽ አልበም ነው ።

ግጥም እና ዜማው በኤልያስ መልካ የተደረሰው እና የአልበሙ መጠሪያ የሆነው "ከምን ነፃ ልውጣ" ሙዚቃ ሀሳቡ በእጅጉ የገዘፈ ቁምነገርን ከማዝናናት ጋር የተላበሰ ስራ ነው ።

ለተጨማሪው: https://t.me/EventAddis1
"ቴኳንዶ ለሁሉም" የተሰኘ መጽሐፍ  ተመረቀ

በግሎባል ማስተር አረፋይኔ ወልደ ሚካኤል አማካኝነት የተጻፈው "ቴኳንዶ ለሁሉም" በሚል ርዕስ የተዘጋጀው መጽሐፍ በትናንትናው ዕለት በካፒታል ሆቴል የጸሐፊው የሙያ አጋሮች፣ ቤተሰቦች  እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ተመርቋል።

"ቴኳንዶ ለሁሉም" መጽሐፍ በወርልድ ቴኳንዶ ስፖርት ላይ ያሉ ዋና ዋና መርሆች ማለትም ከቴኳንዶ ዓለማቀፍ እስከ አገር አቀፍ ታሪክ ጀምሮ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች፣ ራስን የመከላከል ጥበቦች ፣ከመጀመሪያ ደረጃ ጀምሮ እስከ ጥቁር ቀበቶ (አንደኛ ዲግሪ) ድረስ ያሉ ፑምሴ (አርት) ሁሉም መሰረታዊ እንቅስቃሴዎችን እና የቴኳንዶ ስነ-ምግባርና ፍልስፍና አጠቃሎ የያዘ እንዲሁም የሰልጠና ማኑአል ፣ የመወዳደሪያ ህጎችና ፣ የቀበቶ ደረጃ አሰጣጥን እንደ ማስተማሪያም ሊያገለግል በሚችል መልኩ በግሎባል ማስተር አረፋይኔ ወልደ ሚካኤል አማካኝነት  የተዘጋጀ መጽሐፍ ነው፡፡

መጽሐፉ ከአማርኛ ቋንቋ ባሻገር በእንግሊዘኛ ቋንቋ ተተርጉሞ በቅርቡ ለአንባቢያን የሚደርስ መሆኑን ግሎባል ማስተር አረፋይኔ ወልደ ሚካኤል በምረቃው መርሐግብር ላይ ለተገኙ መገናኛ ብዙሃን ተቋማት ገልጿል ሲል የዘገባው ፋስት መረጃ ነው።

ለተጨማሪው: https://t.me/EventAddis1
ኢሳት ቴሌቪዥን እና "የሞርስ" የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅ ጋዜጠኛ እዮብ ደመቀ ተለያዩ 

የኢሳት ጋዜጠኛና በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ የሆነው ሳምንታዊው "ሞርስ" የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅ የነበረው አንጋፋው ጋዜጠኛ ከሚሠራበት የቴሌቭዥን ጣቢያ ጋር መለያየቱን ኤቨንት አዲስ ድረገፅ ሰምቷል።

ጋዜጠኛ ኢዮብ ደመቀ በሚያዘጋጀውና የራሱ ፈጠራ የሆነውን "ሞርስ" ፕሮግራም ላይ የሚፈጸመው ስውር በደል አድጎ ከኤዲቶርያል ፖሊሲው ውጭ ዕውቀቱ በሌላቸው ግለሰቦች የሳንሱር መቀስ እያረፈበት በመሆኑ ሥራውን ለመልቀቅ ምክንያት እንደሆነው ኤቨንት አዲስ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

በተጨማሪም ጋዜጠኛውን"በአስገዳጅ ሁኔታ ከሥራ ገበታው ተገፍቶ እንዲወጣ ከወጣ በኋላ ፕሮግራሙን ለመንጠቅና በሌላ ሰው ለማሠራት ተዘጋጅተናል በማለት የሞራልና የአካል ጉዳት ለማድረስ እየተዛተበት መሆኑን ተከትሎ እንዲህ ከሚያደርጉ ግለሰቦች ጋር መቀጠል የህሊና ባርነት ስለሆነ ከጣቢያው ጋር የነበረኝን ግንኙነት አቋርጫለሁ" ብሏል።

"ሞርስ" የተሰኘው የቴሌቪዥን ፕሮግራም የጋዜጠኛው  የፈጠራ ውጤት በመሆኑ በዩቲዩብ፣ በቴሌግራም፣በፌስቡክ ፣ በኢኒስታግራም "ሞርስ ኮሙኒኬሽን" በማለት ስራውን እንደሚጀምር ከጋዜጠኛው  ሰምተናል።

ድረገፅችን በዚህ ጉዳይ ከኢሳት ቴሌቪዥን በኩል መረጃ ለማግኘት ሙከራ ቢያደርግም አልተሳካለትም።

ለተጨማሪው: https://t.me/EventAddis1