Gazette Plus / ጋዜጣ ፕላስ/
25.1K subscribers
41K photos
338 videos
7 files
5.81K links
Ethiopian Press Agency, established in 1940 , is a public printing media enterprise operating in Ethiopia.
Download Telegram
በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በተደረገ የቤት ውሰጥ ብርበራ ህገወጥ መሣሪያ ከተጠርጣሪዎች ጋር ይዞ ምርመራ እያጣራ እንደሚገኝ ፖሊስ አሰታወቀ
*******************
(ኢ.ፕ.ድ)

በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በተለያየ ጊዜ በተደረገ የቤት ውሰጥ ብርበራ ህገ-ወጥ የሆኑ 5ሽጉጦች ፣ 102 የሽጉጥ ጥይቶች እና 8 የክላሽ ጥይቶች ከ7ተጠርጣሪዎች ጋር ይዞ ምርመራ እያጣራ እንደሚገኝ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አሰታወቀ።

በተለያየ ቦታ እና ጊዜ ፖሊስ ከህብረተሰቡ በደረሰው ጥቆማ መሰረት ከፍርድቤት የመበርበሪያ ትዕዛዝ በማውጣት ባደረገው ብርበራ ህገ-ወጥ ሽጉጦችን እና ጥይቶችን ሊይዝ መቻሉን አስታውቋል።

የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ፖሊሰ መምሪያ የወንጀል ምርመራ ማስተባበሪያ ሀላፊ ም/ኢንስፔክተር ተዘራ ከፍያለው ከአዲስ ፖሊስ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳብራሩት፤ ከክፍለከተማው ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ከከተማው ዳር የሚገኝ እና የኬላ ፍተሻ በመኖሩ ቀደም ሲል በርካታ የጦር መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ የህብረተሰቡ ጥቆማ መሰረት ባደረገው ብርበራ ህገ ወጥ የሆኑ 5ሽጉጦች፣102 የሽጉጥ ጥይቶች፣8የክላሽ ጥይቶች እና የሽጉጥ ካርታዎችን ከነ ተጠርጣሪዎች በመያዝ ምርመራ እየተጣራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

በህጋዊ ሽፋን ህገወጥ ጦር መሳሪያ ይዘው የሚቀሳቀሱ ግለሰቦች እንዳሉ ያስታወሱት መርማሪው ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ለሀገር ሰላም እጦት ከመሆኑም ባሻገር ለኢኮኖሚ ውድመት ትልቅ መንስኤ በመሆኑ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመከላከል ህብረተሰቡ እያደረገ ያለውን እገዛ አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ሲሉ ሓላፊው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የትራምፕን ንግግር መቃወሚያ ዓለምአቀፍ የበይነመረብ ፊርማ የማሰባሰቢያ ንቅናቄ ተጀመረ
*********************************
(ኢፕድ)
አዲስ አበባ፡- በታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክርቤት ጽሕፈት ቤት እና በሌሎች አጋር አካላት አማካኝነት የዶናልድ ትራምፕ ንግግርን ለመቃወም ‹‹ፊርማችን ለህዳሴያችን›› በሚል የበይነ መረብ ዓለም አቀፍ የፊርማ ማሰባሰብ ንቅናቄ ተጀመረ።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሔ ፊርማ የማሰባሰቡ ንቅናቄ ይፋ በተደረገበት ወቅት እንደተናገሩት፤ የፊርማ ማሰባሰብ ሥራ ከባድና ለአገር ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ከመሆኑም በላይ ኢትዮጵያውያን እንዴት በጋራ መቆም እንደሚችሉ ማሳያ ነው። የተከፈተውን በር ተከትሎ መግባቱና ውጤቱን ማሳየቱ የእኛ ድርሻ ነውና እጃችንን ወደ ፊርማችን እናድርግ ብለዋል።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብርሀም በበኩላቸው እንዳሉት፤ ግድቡ ለድርድር የሚቀርብና ፕሬዚዳንቱ እንደተናገሩት ለቦምብና ለጥይትም የሚታሰብ አይደለም።

በሰላማዊ መንገድ ጨርሰን በዓለምአቀፉ ሕግ መሠረት እኛም ጎረቤቶቻችንም ተካፍለን እንድንጠቀምበት እየሰራን እንገኛለን።ስለሆነም የበይነ መረብ የፊርማ ማሰባሰብ ተግባር ከምንም በላይ የሚያስፈልግ በመሆኑ በድል እንዲጠናቀቅ ሁላችንም የበኩላችንን እንወጣ ሲሉ ጥሪ አድርገዋል።

ኢትዮጵያውያን ጸብን ሳይሆን ወዳጅነትን አንግበን የምንንቀሳቀስ ሕዝብ ነን።ሆኖም ግን ከጥንት ጀምሮ ለነካን ምላሹን እናውቅበታለን።አሁንም በዴሞክራሲያዊ መንገድ ድምጻችን ለህዳሴያችን በሚል የተለያዩ እንቅስቃሴዎች አድርገን ውጤታማ እንደሆንነው ሁሉ አሁንም ፊርማችን ለህዳሴያችንም በሚለው ሪከርድ ሰባሪ መሆን ይጠበቅብናል።ለዚህም ሁሉም ኢትዮጵያዊ በይነ መረቡ በመግባት ፊርማውን እንዲያኖር ሲሉ አቶ ኃይሉ አሳስበዋል።

ከአስተባባሪዎቹ መካከል አቶ ፍሬው በቀለ እንዳሉት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ምላሽ ለማግኘት 100 ሺህ የፊርማ ስብስብ መደረግ እንዳለበት ተናግረዋል።እርሳቸው እንዳሉት፤ ይህ ዓለምአቀፍ ንቅናቄ በመቶ ሺህ ብቻ የሚገደብ መሆን የለበትም።እንዲያውም ታሪክ ሊሰራበት የሚገባውና ሪከርድ የምንሰብርበት ሊሆን ይገባል ብለዋል።

ፊርማው በኢትዮጵያውያን ብቻ ቢፈረም እንኳን በሚሊዮን ይቆጠራል።በዓለምአቀፍ ሲሆን ደግሞ ብዙ የኢትዮጵያ ወዳጆችና ሰላም ወዳዶች በመኖራቸው ይህንን ይቀላቀላሉ።

ስለሆነም በተለይ ሚዲያው ይህንን በማሳወቅ በኩል የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።ፊርማው ተሰባስቦ ለአሜሪካ ምክርቤት ብቻ ሳይሆን ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ለአፍሪካ ህብረት፣ ለአውሮፓ ህብረት፣ ድርድሩን ለሚመሩት አካላት እንዲሁም ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ለሚባሉት ሁሉ ገቢ ይደረጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጭ ማህበር ፕሬዚዳንትና የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት አባል ኢንጅነር አመሀ ስሜ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ እስከዛሬ በሆኑት ሁሉ ኢትዮጵያን በአንድነት ከተነሱ ምንም የሚገታቸው ነገር እንደሌለ ማሳያ ነው።አሁን ደግሞ በአገር ሉአላዊነት ላይ ጣታቸውን የቀሰሩት ትራምፕ ያልተረዱት ነገር ካለ እንዲረዱትና ከተረዱም በኋላ የእኛ አጋር ሆነው አብረውን እንዲቆሙ ለማድረግ ይህን እንቅስቃሴ ማድረጉ እጅጉን ይጠቅማል።ዋጋው ጥቂት ቢመስልም በትሪሊዬን የሚገመት ዲፕሎማሲያዊ ምላሽን ያስገኛልና ፊርማችንን ለህዳሴያችን እንስጥ ሲሉ አሳስበዋል።

የፕሬዚዳንቱ ንግግር ሕዝቡን አንድ አድርጎታል። ይህንን በተለያዩ መንገዶች መደገፍ ያስፈልጋል ያሉት ኢንጅነሩ፤ በተለይ በውጭ ዲፕሎማሲው የተሻለ ሥራ መስራትና የፊርማ ማሰባሰቡን በታሪክ ማጠናቀቅ እንደሚገባ አስረድተዋል።በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ መነጋገር፤ መደማመጥና መሸናነፍ መቻል ላይ ማተኮር ይገባል።

ይህ ሲሆን አንድነት መጥቶ ኃይል ይሆናል፤ ይህንን አጥብቆ መያዝና በአባይ ጉዳይ አምባሳደር መሆን መቻልይገባል ሲሉ ተናግረዋል።የፕሬዚዳንቱን ንግግር ለመቃወም change.org እና petition gard white house በማለት ድረ-ገጽ ላይ ገብቶ መፈረም እንደሚቻል ተገልጿል። በተመሳሳይ ከሰኞ ጀምሮ ሁሉም ሰው የፌስቡክ ፕሮፋይሉን በህዳሴው እንዲቀይርም ጥሪ ቀርቧል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 22/2013
የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀመንበር ጄነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን ለሁለት ቀናት የሥራ ጉብኝት አዲስ ፈበባ ገብተዋል።
ብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ኢትዮ ቴሌኮምን በዓመት ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ሊያሳጣ በሚችል ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ
*****************
(ኢ.ፕ.ድ)
ብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ኢትዮ ቴሌኮምን በዓመት ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ሊያሳጣ በሚችል ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ።

የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ከኢንፎርሜሽን  መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ ከተማ የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል በሚፈፀምባቸው ቦታዎች ላይ ጥብቅ የመረጃና የክትትል ሥራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል።

በዚህም ትናንት በአዲስ አበባ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 እና ልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 በተካሄደ ኦፕሬሽን በህገ ወጥ መልኩ ዓለም አቀፍ የስልክ ጥሪዎችን በመጥለፍ በራሳቸው መስመሮች ለደንበኞች በማቅረብ ሕገወጥ ድርጊት ሲፈፅሙ የነበሩ ሦስት ተጠርጣሪዎች በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አማካኝነት በህግ በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ማድረጉን አገልግሎት መስሪያ ቤቱ አስታውቋል።

ተጠርጣሪዎቹ ከኢትዮ ቴሌኮም አውቅና ውጪ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የስልክ ጥሪዎችን በማስተላለፍ የራሳቸውን ገቢ ሲሰበስቡ መቆየታቸውን የገለፀው ብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፤ ሕገ ወጥ ድርጊቱ ባይከሽፍ ኖሮ፤ ኢትዮ ቴሌኮምን በዓመት ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ሊያሳጣው እንደሚችልም ጠቁሟል።

በወንጀል ድርጊቱ የተጠረጠሩት ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ሲውሉ፤ ሲገለገሉባቸው የነበሩ 10 ጌትዌይ (ሲምቦክስ)፣ 17 ቲፕሊንክ፣ 59 ሲዲኤምኤ፣ 3 ራውተር፣ 2 ሺህ ሲምካርድ፣ 3 ላፕቶፕ፣ የባንክ  ደብተሮች፣ ሲፒኦዎችና ሌሎች ሕገ ወጥ  መሳሪያዎች በኢግዚቢትነት  መያዛቸውን  ብሄራዊ  መረጃና ደህንነት አገልግሎት አስታውቋል።
 
ሕገ ወጦችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል በነበረው ሂደት ህብረተሰቡ ላሳየው የላቀ ተሳትፎ አገልግሎት መስሪያ ቤቱ ምስጋና አቅርቧል።

በቀጣይም ህብረተሰቡ ሕገ ወጦችን በማጋለጥ ረገድ የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል አገልግሎት መስሪያ ቤቱ ጥሪ አቅርቧል።
"የኢትዮጵያ እና የሱዳን ሕዝቦች በባህልና ታሪክ የተሳሰረ ጠንካራ ግንኙነት አላቸው"
ጠቅላይ ሚኒስትር  አቢይ አህመድ 
**************
(ኢ.ፕ.ድ)
የኢትዮጵያ እና የሱዳን ሕዝቦች በባህል እና በታሪክ የተሳሰረ ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጄነራል አልቡርሀን ጋር የአዳማ ከተማን የጎበኙ ሲሆን፤ በዚሁ ወቅት  አባ ገዳዎች ለጄነራል አልቡርሃን ፈረስ እና ጋሻ  ሸልመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስር ዶ/ ር አብይ አህመድ በማህበራዊ ገጻቸው፤ "አባገዳዎች የሁለቱ ሕዝቦች ትስስር ይጠብቅ ዘንድ መርቀውናል። ለጄነራል አልቡርሃን ፈረስ እና ጋሻ በመሸለም አክብሮታችንን ገልጸንለታል" ሲሉም አስታውቀዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ  ባለቤታቸው የማይታወቁ ቦታዎች፣ ህንጻዎች እና ቤቶች መገኘታቸውን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ
**************
(ኢ.ፕ.ድ)

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማው ያሉ ህገ-ወጥ ተግባራትን ለመከላከልና  ወደ ህጋዊ መስመር ለማምጣት ባደረገው ማጣራት ባለቤታቸው የማይታወቁ ቦታዎች፣ ህንጻዎች እና ቤቶች መገኘታቸውን አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ፅህፈት ቤት ዛሬ ማምሻውን ባወጣው የጥሪ ማስታወቂያ፤ የከተማ አስተዳደሩ በከተማው ያሉ ህገ-ወጥ ተግባራትን ለመከላከልና  ወደ ህጋዊ መስመር ለማምጣት የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ መሆኑ ገልጿል።

ከነዚህ ተግባራትም ውስጥ አንደኛው እና ዋነኛው ህገ-ወጥ የመሬት ወረራና ህገ-ወጥ  ግንባታ ሲሆን ይህንኑ በከተማው የሚታየውን ህገ-ወጥ ድርጊት ለማጣራት  እና መረጃ ለማሰባሰብ   በየደረጃው ግብረሃይል በማደራጀት እና ህዝቡን በማሳተፍ ከአንድ ወር በላይ  የማጣራት ስራ ሲሰራ መቆየቱ የሚጠቀስ ነው ብሏል፡፡

ግበረ ሀይሉ ባደረገው ማጣራትም የደረሰባቸው ዋና ዋና  ግኝቶቹን የገለጸ ሲሆን፤ በህገ-ወጥ መንገድ የታጠሩ እና ባለቤትነታቸውን ማረጋገጥ ያልተቻለ ቦታዎችን፣ በህገ-ወጥ መንገድ መገንባት የተጀመሩ ግንባታዎች መኖራቸውን እና ባለቤቶቻቸው ያልታወቁ ቤቶች እና ህንፃዎች መገኘታቸውን  አስታውቋል።

የከተማ አስተዳደሩ በግኝቶቹ ላይ ውሳኔ ወስኖ እርምጃ ከመውሠዱ በፊት የኔ ነው ባይ ካለ አንድ እድል ለመስጠት እንደሚፈልግ ጠቅሶ፤ ህጋዊ ማስረጃ አለኝ የሚል አካልም ሆነ ግለሰብ ከነገ (ጥቅምት 23/02/2013) ጀምሮ ለ3 ተከታታይ ቀናት መረጃም ሆነ ማስረጃ በመያዝ ለዚሁ ጉዳይ በየክፍለ ከተማው በተዋቀረ ግብረሃይል ጋር በመቅረብ እንዲያስረዳ የከተማ አስተዳድሩ አሳስቧል።
በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሶስትዮሽ ድርድር ዛሬ ተካሂዷል። የዛሬውን ውሎ በተመለከተ የውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር መግለጫ አውጥቷል።

የመግለጫው ሙሉ ቃል ከላይ ተያይዟል
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ የሰላማዊ ሰዎችን ሕይወት ባጠፋው ኦነግ ሸኔ ላይ እርምጃ እንደሚወስድ አስታወቀ
****************************
(ኢ ፕ ድ)
በምዕራብ ወለጋ ሰላማዊ ዜጎች ጭካኔ በተሞላበት መንገድ በአንድ ስፍራ ህይወታቸው እንዲያልፍ ባደረገው የኦነግ ሸኔ ቡድን ላይ እርምጃ እንደሚወስድ የኦሮሚያ ክልል መንግስት አስታወቀ።
የክልሉ መንግስት ባወጣው መግለጫ፥ መንግስት የህዝቡን ፍላጎትና ጥያቄ በማገናዘብ የልማት ስራዎችን፣ የሰላም እና የስርዓት ግንባታ ላይ እየሰራ ባለበት በአሁኑ ወቅት፤ ከለውጡ በተቃራኒ የቆሙ ሀይሎች በህዝቡ ላይ አሰቃቂ አደጋ እያደረሱ መሆኑን አስታውቋል።
የጥፋት ሀይሎቹ መንግስት የፖለቲካ እና የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት እየሰራ ባለበት ወቅት በተቃራኒው በመቆም ጭቃኔ የተሞላበት ተግባር በህዝቡ ላይ እየፈፀሙ ነው ብሏል።
የኦነግ ሸኔ ሽፍታ ከህውሃት ጋር በመሻረክ በኦሮሚያ ክልል እና በሀገሪቱ ሰላም እና መረጋጋት እንዳይኖር ሲሰሩ መቆየታቸውን ያስታወሰው መግለጫው፤ በተለያዩ ወቅቶች የግጭት አጀንዳዎችን በማዘጋጀት በሚዲያ በማሰራጨት እንዲሁም በህገ ወጥ መንገድ በገቡ የጦር መሳሪያዎች በፀጥታ ሀይሎች፣ በመንግስት መዋቅር እና በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ የግድያ እርምጃ በመውሰድ ችግሮችን ሲፈጥሩ ቆይተዋል ብሏል መግለጫው።
ጭካኔ በተሞላበት መንገድ በተፈፀሙ በእነዚህ ተግባራትም በህብረተሰቡ ላይ የስነ ልቦና ጫና እንዲፈጠር፣ በስጋት እንዲሞላ እና ከዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ራሱን ቆጥቡ በረሃብ እና በጥማት እንዲጎዳ እያደረጉ ነውም ብሏል።
በተለይም በምዕራብ ኦሮሚያ አቅጣጫ በሚገኙ ዞኖች ህፃናት፣ ሴቶች፣ አዛውንቶች እና ወጣቶችን ጨምሮ ጭካኔ በተሞላበት መንገድ እንዲገደሉ፣ በእሳት እንዲቃጠሉ፣ የአካል ጉዳት እንዲደርስባቸው እንዲሁም የስነ ልቦና ጉዳት እንዲደርስባቸው ማድረጉ ይታወቃልም ብሏል፡፡
ከሁሉም በላይ በጫካ ውስጥ መሽጎ ከቦታ ቦታ የሚዘዋወረው ኦነግ ሸኔ ሰዎችን ጠልፎ በመውሰድ ጉዳት ሲያደርስ መቆየቱ ያወሳው መግለጫው፤ በተለያዩ ጊዜያትም የፀጥታ እና የአስተዳደር አካላት በተመሳሳይ መንገድ ጫካ ውስጥ በአሰቃቂ ሁኔታ ህይወታቸው እንዲያልፍ ሲያደርግ ቆይቷልም ነው ያለው።
የኦነግ ሸኔ ሽፍታ እስካሁን በፈፀማቸው የሽብር ተግባራት በርካታ ቤተሰቦች ተበትነዋል፣ ህፃናትን ያለ አባትና እናት አስቀርቷል ያለው መግለጫው፥ የህዝቡና የግለሰቦች ሀብትም እንዲጠፋ ማድረጉን አስታውሷል።
የኦሮሚያ ክልል መንግስት የህዝቡን ሰላም ለማረጋገጥ ያለውን ተልዕኮ እና ሀላፊነት ለመወጣት ህዝቡን ባሳተፈ መልኩ የህግ የበላይነትን የማስከበር ስራ በስፋት እያከናወነ መሆኑንም ጠቅሷል፡፡
የህወሓት ተላላኪ የሆነው ይህ የኦነግ ሸኔ ቡድን ህዝቡ እና መንግስት በጋራ በመሆን የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እየወሰዱት ባለው እርምጃ ለመጥፋት መቃረቡንም መግለጫው አመላክቷል።
እየተወሰደ ባለው እርምጃ የመቃብር አፋፍ ላይ የደረሰው ይህ ቡድን ተስፋ በመቁረጡ በአንድ ስፍራ በሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ጥቃት እያደረሰ መሆኑም ተገልጿል።
በትናትናው እለትም በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ጋዋ ቀናቲ ቀበሌ ጨለማን ተገን በማድረግ በፈፀመው የሽብር ጥቃት ሰላማዊ ዜጎችን ጭካኔ በተሞላበት መንገድ በአንድ ስፍራ ህይወታቸው እንዲያልፍ ማድረጉንም ነው የገለጸው።
የኦሮሚያ ክልል መንግስት ከህዝቡ እንዲሁም የፀጥታ እና አስተዳደር አካላት ጋር በመሆን እነዚህ ሽፍታዎች የገቡበት ቦታ በመግባት አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድም ገልጿል።
በተፈፀመው ጥቃት ለተሰው ወገኖች የተሰማውን ሀዘን የገለፀው የክልሉ መንግስት ለቤተሰቦቻቸው መጽናናትን ተመኝቷል።
በቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የፌደራል ፖሊስ ገለጸ
************************************
(ኢ.ፕ.ድ)

በአዲስ አበባ ከተማ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማና በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ፣ በቴሌኮም ማጭበርበር የተጠረጠሩ በርካታ ግለሰቦች ከነመሳሪያዎቻቸው በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ አስታወቀ፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ህጋዊ ፈቃድ ሳይኖራቸው የቴሌኮም መሳሪያዎችን ወደ ሀገር በማስገባትና ከውጭ ሀገር ወደ ኢትዮጵያ የሚደረጉ የስልክ ጥሪዎች ኢትዮ ቴሌኮም በዘረጋው ኔትወርክ ሳይሆን ራሳቸው በዘረጉት መስመሮች ለደንበኞች ሲያቀርቡ መቆየታቸውን በፋይናንስ ተቋማት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ምርመራ ዲቪዥን ኃላፊ ኢንስፔክተር ሳሙኤል ሰለሞን ገልፀዋል።

ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ መሰረት የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ ከኢንሳ፣ ከኢትዮ ቴሌኮም፣ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንና ከሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ባደረገው ክትትል ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ኢንስፔክተር ሳሙኤል ተናግረዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ለዚህ ህገ-ወጥ ተግባር ሲጠቀሙባቸው የነበሩ 6 ጌትወይ፣ ከ570 በላይ ሲም ካርዶች፣ ቲፕሊንኮችና ሌሎች ህገ-ወጥ የቴሌኮሙኒኬሽን መሳሪያዎች መያዛቸውም ተገልጿል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በሁለቱ ክፍለ ከተሞች ከቴሌኮም እውቅና ውጭ ማሽኖቹን በመጠቀምና የራሳቸውን ኔትወርክ በመፍጠር የውጭ ሀገር ጥሪዎችን በማስተላለፍ በቴሌኮም ላይ ኪሳራ ሲያደርሱ መቆየታቸንውን ኢንስፔክተር ሳሙኤል ሰለሞን በመግለፅ ህብረተሰቡ ለፖሊስ ባደረሰው ጥቆማ መሰረት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጠቁመዋል፡፡

የወንጀል ምርመራ ቢሮው ከፍርድ ቤት የብርበራ ትዕዛዝ በማውጣት ማሽኖቹን ከነ አክሰሰሪዎቹ በመያዝ በኢትዮ ቴሌኮም መሰረተ ልማት ላይ ተጠርጣሪዎቹ ያደረሱትን ኪሳራ ለማጣራት መሳሪያዎቹን ለብሔራዊ መረጃና ደህንነት ልኮ የምርመራ ውጤቱን እየተጠባበቀ ይገኛልም ብለዋል፡፡

ህብረተሰቡ ቤቱን ከማከራየቱ በፊት ስለ ተከራዮች ማንነት በቂ መረጃ በመያዝ በትክክል ማጣራት እንዳለበትና እንደዚህ አይነት ህግ-ወጥ ተግባራት ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችን ሲመለከት በአካባቢው ለሚገኙ የፀጥታ አካላት ጥቆማ በመስጠት የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግም ኢንስፔክተር ሳሙኤል ሰለሞን ጥሪ አቅርበዋል፡፡
"በኢትዮጵያውያን ላይ እየተፈጸመ ባለው ማንነትን መሠረት ባደረገው ጥቃት እጅግ ማዘኔን እገልጣለሁ"
- ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር)
*********************
(ኢ ፕ ድ)
የኢትዮጵያ ጠላቶች፤ "ወይ እኛ እንገዛለን፤ ወይ ሀገር አትኖርም" ብለው ተነሥተዋል። ለዚህም የጥፋት ዐቅማቸውን ሁሉ እየተጠቀሙ ነው። አንደኛው ዒላማቸውም የሕዝባችንን ቅስም መስበር ነው።
ለዚህ እየተጠቀሙበት ያለው ስልት ግራ ቀኝ የሜያውቁ ሰዎችን እየሰበሰቡ በማሠልጠንና በማስታጠቅ በየአካባቢው ማንነትን መሠረት ያደረገ አረመኔያዊ ጥቃት ማድረስ ነው። ይህ ተግባር ሕዝቡ እንዲደናገጥ፣ እንዲፈራና በስሜት ያልተገባ ርምጃ እንዲወስድ የታለመ ነው።
መንግሥት በተለያዩ ቦታዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ ያላቸውን ጥፋቶች በቅድሚያ መረጃ ሰብስቦ ርምጃ በመውሰድ ሲያከሽፍ ቆይቷል። ነገር ግን ያለፈው ሥርዓት ያወረሰንን ቀዳዳዎች ሁሉ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ደፍኖ መጨረስ አልተቻለም።
የጥፋት ኃይሎች ከውጭ ላኪዎቻቸውና በመንግሥት መዋቅር ውስጥ በሚገኙ ባልጠሩ አድር ባዮች ትብብር በሕዝባችን ላይ አሳዛኝ ጥቃት እያደረሱ ነው። ሁኔታው እንደ መሪም እንደ ዜጋም ልብ ይሰብራል።
ይህ ግን ከመንገዳችን ወደኋላ፣ ከግባችን ወደ ሌላ አያደርገንም። ተስፋ ቆርጠን እንድናቆም፣ ተሸንፈን እንድናፈገፍግ አያደርገንም። ከምንጊዜውም በላይ ኃይላችንን አሰባስበን እንድንነሣ ያደርገናል እንጂ።
መንግሥት ሁሉንም ዓይነት አማራጮች ተጠቅሞ የችግሩን ሰንኮፍ ይነቅለዋል። የጸጥታ አካላት ጥቃቱ ወደተፈጸመበት አካባቢ ተሠማርተዋል። ርምጃም እየወሰዱ ነው። በቀጣይም የሕዝባችንን ደኅንነት ለማስጠበቅ መንግሥት የመንግሥትነቱን ሥራ በቁርጥና በጽናት ይሠራል።
ሕዝቡ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የጸጥታ አካላት።፣ ምሁራንና ሌሎችም፧ መንግሥት ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ የሚወስደውን ርምጃ በመደገፍ የሚጠበቅባቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ አቀርባለሁ።
የኢፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ በንፁኃን ዜጎች ላይ የተፈፀመውን አሰቃቂ ጭፍጨፋ በማስመልከት መልዕክት አስተላልፈዋል።
***************
(ኢ.ፕ.ድ)

የተከበራችሁ የሃገራችን ህዝቦች!

በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ በንፁኃን ዜጎች ላይ የተፈፀመው አሰቃቂ ጭፍጨፋ የተሰማኝን ሃዘን እየገለፅኩ፤ ለሟች ቤተሰቦች መፅናናትን እመኛለሁ፡፡

በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ቀደም ሲል ብሄርን፣ ሃይማኖትን እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት የማድረስ ዓላማ ያላቸው ጥቃቶችና ጭፍጨፋዎች ተካሂደዋል፡፡ በተመሳሳይ በምዕራብ ወለጋ ዞን በንፁኃን ዜጎች ላይ አሰቃቂ ጭፍጨፋ ተፈፅሟል፡፡

በተለይ የአማራን ማህበረሰብ ትኩረት ያደረገና በንፁኃን ዜጎች ላይ የሚካሄደው ጭፍጨፋ ፍፁም አረመኔያዊና በፍጥነት መቆም ያለበት እኩይ ድርጊት ነው፡፡ ድርጊቱ አስቀድሞ መዋቅራዊ በሆነ መልኩ ሲዘራ የቆየ በመሆኑ፤ ችግሩን የሚመጥን መፍትሄ በዘላቂነት ለማበጀት አስፈላጊው ሁሉ ይደረጋል፡፡

ከዚህ አኳያ የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ እንዲሁም ከሁሉም አቅጣጫ የሚቃጡ ጥቃቶችን ለመመከት የመንግስትና ህዝብ ቅንጅታዊ ርብርብ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
የምክር ቤቱ አባላት በምዕራብ ወለጋ ዞን ከተፈጸመው ግድያ ጀርባ አሉ የተባሉት እንደ ህወሓት ያሉ ድርጅቶች በአሸባሪነት ሊፈረጁ ይገባል ሲሉ ጠየቁ

👉 ጉዳዩን በተመለከተ የሚመለከተው የመንግስት አካል ማብራሪያ እንዲሰጥበት እንደሚደረግ አፈጉበኤው አስታውቀዋል
******************
(ኢ ፕ ድ)

የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባላት በምዕራብ ወለጋ ዞን በንጹሀን ዜጎች ላይ ማንነትን መሰረት አድርጎ በተፈጸመው ግድያ ላይ እጃቸው አለበት የተባሉት እንደ ህወሓት እና ሸኔ ያሉ ድርጅቶች በአሸባሪነት ሊፈረጁ ይገባል ሲሉ ጠየቁ።

ዛሬ ለመደበኛ ስብሰባ የተጠራው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከመደበኛ አጀንዳዎች አስቀድሞ በንጹሀን ዜጎች ግድያ ላይ መወያያት አለብን በሚል በጥቃቱ ዙሪያ ሰፊ ውይይት አድርጓል።

በዚሁ ውይይት ላይ የምክር ቤቱ አባላት እንደተናገሩት፤ በምዕራብ ወለጋ ዞን በንጹሀን ዜጎች ላይ ማንነትን መሰረት አድርጎ በተፈጸመው ግድያ ላይ እጃቸው አለበት የተባሉት እንደ ህወሓት እና ኦነግ ሸኔ ያሉ ድርጅቶች በአሸባሪነት ሊፈረጁ ይገባል ብለዋል።

የትናንት በስቲያውን ጨምሮ ባለፉት ሁለት አመታት ማንነት ላይ የተመሰረቱ ግድያዎችን የፈጸሙ፣ የመለመሉ ድጋፍ ያደረጉ እንደ ህወሓት ያሉ አካላትን በተመለከተ መረጃና ማስረጃ አደራጅቶ በሽብርተኝነት ሊፈረጁ ይገባል ያሉት አባላቱ፤ የሚመለከተው የመንግስት አካል ይሄንን መረጃ አደራጅቶ ለምክር ቤቱ እንዲያቀርብም ነው የጠየቁት።

አባላቱ በዚሁ ውይይታቸውም በግድያው ዙሪያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የሰላም ሚኒስቴር እና የመከላከያ የስራ ሃላፊዎች በጉዳዩ ላይ ምክር ቤት ቀርበው ማብራሪያ ሊሰጡ ይገባል ሲሉ አንስተዋል።

አፈጉበኤው በምላሻቸው የምክር ቤቱ አባላት በግድያው ዙሪያ ስሜታቸውን በዚህ አግባብ መግለጻቸው ትክክል መሆኑን በመጥቀስ፤ ጉዳዩን በተመለከተ የሚመለከተው የመንግስት አካል ማብራሪያ እንዲሰጥበት እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

በጌትነት ተስፋማርያም
“ለሀገርና ለህዝብ ጥቅም ሲባል ልናሰምረው እና ልናከብረው የሚገባን ቀይ መስመር ተጥሷል”
- የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ሳህለ-ወርቅ ዘውዴ
*********************
(ኢ ፕ ድ)
የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ሳህለ-ወርቅ ዘውዴ በምዕራብ ወለጋ ዞን በንጹሀን ዜጎች ላይ የተፈጸመውን ግድያ በማስመልከት ያስተላለፉት መልዕክት።
የሰማሁት አሰቃቂ ግድያ ልቤን በእጅጉ ሰብሮታል:: ንጹሀን ዜጎች በሌሎች እብደት ውድ ሕይወታቸውን የሚከፍሉበት ንብረታቸው የሚወድምበት መሄጃ አጥተው የሚንከራተቱበት ምንም ምክንያት የለም:: የዛሬ ዓመት በ 30/10/2019 የጻፍኩትን ትዊት ልድገመው::
ዘርና ሀይማኖት ለፖለቲካ ጥቅም እንዲውሉ ሲደረግ፤ ንጹሀን ዜጎቻችን በአሰቃቂ ሁኔታ ሲገደሉ፣ ሲፈናቀሉና ሲንከራተቱ ስናይ ስሜትን ለመግለጽ ቃላት ያጥራል: ለቅሶ፣ድንጋጤና ሥጋት የብዙዎችን በር አንኳኩቷል ሃዘናቸው ሃዘኔ/ሃዘናችን ነው::
ለሀገርና ለህዝብ ጥቅም ሲባል ልናሰምረው እና ልናከብረው የሚገባን ቀይ መስመር ተጥሷል፡ አገራችንን ካንዣበበባት ክፉ አዳጋ ለማዳን ሁላችንም ሚና አለን፡የሚመለከታቸው ሁሉ የበኩላቸውን መወጣት አለባቸው፡ቀይ መስመር መጣስ የለበትም እንበል::
የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ
ሕወሓት በትግራይ በሚገኘው የመከላከያ ካምፕ ላይ ጥቃት ማድረሱና በዳልሻሕ በኩልም ጦርነት መክፈቱ ተገለጸ
********************
(ኢ ፕ ድ)
ሕወሓት በትግራይ በሚገኘው የመከላከያ ካምፕ ላይ ጥቃት ማድረሱ እና በዳልሻሕ በኩልም ጦርነት መክፈቱ ተገለጸ።
የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ እንዳስታወቁት ህወሓት የሰሜን ዕዝንም ለመዝረፍ ሙከራ አድርጓል።
እንድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ ይህ ሠራዊት ከሃያ ዓመታት በላይ የትግራይን ሕዝብ ሲጠብቅ የቆየ ሠራዊት ነው። በቦታው የሚገኘውም የትግራይን ሕዝብ ከጥቃት ለመከላከል ነው። ሕወሐት ግን እንደ ባዕድና እንደ ወራሪ ሀገር ሠራዊት ቆጥሮ፤ የመከላከያ ሠራዊቱን ለመምታትና ለመዝረፍ ተነሥቷል።
ህወሓት በዳልሻሕ በኩልም ጦርነት ከፍቷል።
መንግሥት የትግራይ ሕዝብ እንዳይጎዳ በማሰብ፣ ጦርነት እንዳይፈጠር የትእግሥቱ ጫፍ ድረስ ታግሷል ያሉት ዶ/ር አብይ፤ ጦርነት የሚቀረው ግን በአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ አይደለም ነው ያለት።
"የመከላከያ ሠራዊታችን በኮማንድ ፖስት እየተመራ ሀገሩን የማዳን ተልዕኮውን እንዲወጣ ትእዛዝ ተሰጥቶታል። ቀዩ መሥመር የመጨረሻው ነጥብ ታልፏል። ሀገርና ሕዝብ ለማዳን ሲባል ኃይል የመጨረሻው አማራጭ ሆኗል" ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ነገሮችን በሰከነ መንፈስ እንዲከታተል፣ በየአካባቢው ሊከሠቱ የሚችሉ ትንኮሳዎች በንቃት እንዲቃኝና ከመከላከያ ሠራዊታችን ጎን እንዲቆም ጥሪ አቀርባለሁ ብለዋል።
ሕወሐት በትግራይ በሚገኘው የመከላከያ ካምፕ ላይ ጥቃት አድርሷል። ሰሜን ዕዝንም ለመዝረፍ ሙከራ አድርጓል። ይህ ሠራዊት ከሃያ ዓመታት በላይ የትግራይን ሕዝብ ሲጠብቅ የቆየ ሠራዊት ነው። በቦታው የሚገኘውም የትግራይን ሕዝብ ከጥቃት ለመከላከል ነው። ሕወሐት ግን እንደ ባዕድና እንደ ወራሪ ሀገር ሠራዊት ቆጥሮ። የመከላከያ ሠራዊቱን ለመምታትና ለመዝረፍ ተነሥቷል። በዳልሻሕ በኩልም ጦርነት ከፍቷል።
በአዲስ አበባ በተለምዶ አዋሬ ገበያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የተነሳው የእሳት አደጋ በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገለጸ
**********************
(ኢ ፕ ድ)
ከሌሊቱ 10 ሰአት አካባቢ የተነሳው የእሳት አደጋ በአዲስ አበባ ከተማ የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የእሳት አደጋ መከላከል ባለሙያዎች ፣ፖሊሶች እና የአካባቢው ወጣቶች በቁጥጥር ስር መዋሉን የየካ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አስፋው ተክሌ ተናግረዋል፡፡
የእሳት አደጋውን መንስኤ እና ያደረሰውን ጉዳት በፖሊስ እየተጣራ መሆንን ዋና ስራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡
ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና ከየካ ክፍለ ከተማ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በቦታው ተገኝተው የጉዳቱን መጠን በመመልከት ጉዳት የደረሰባቸውን ነዋሪዎች በማጽናናት ላይ ናቸው።
በእሳት አደጋው የደረሰውን ጉዳት በማጣራት በቀጣይ ሰዓታት የሚገለጽ ይሆናል ተብሏል፡፡
👉 በየጊዜው የሸረሪት ድር ስናፀዳ አንኖርም፤
👉 ትህነግ አልመዳ በሚባለው የጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ውስጥ የኤርትር
የመከላከያ ሰራዊት አልባሳትን በማምረት የኤርትራ ሰራዊት ወረረህ ለማለት
ዝግጅት ያደረገ ነው፤
👉 በአማራ ክልል በሶሮቃና ቅርቃር አካባቢ ትህነግ የጦርነት ሙከራ አድረጓል፤
ነገር ግን በአማራ ክልል ልዩ ኃይል ሙሉ በሙሉ ተመክቶ ተመልሷል፤
👉 ትህነግን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመደምሰስ ለሚደረገው ርምጀ ህዝቡ፣
ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ ከመንግስት ጎን ቆመው ሊያግዙና አካባቢያቸውን
ሊጠብቁ ይገባል፤
አቶ ተመሥገን ጥሩነህ
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር
ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አቢይ አሕመድ በሰጡት መግለጫ ያነሷቸው ዋናዋና ነጥቦች
👉 ውድ የሀገሬ ህዝብ ሆይ! ዛሬ ከሃዲ ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያን
ወግተዋታል፤
👉 ኢትዮጵያ ያጎረሰ እጇ ያጠባ ጡቷ ተነክሷል፤
👉 ላለፉት 20 ዓመታት የቀበሮ ምሽግ ውስጥ በመሆን ሀገሬን ወገኔን
ህዝቤን ብሎ በብዙ ሺዎች መስዋዕትነት ከፍሎ ቆስሎ ደምቶ ሀገሩንና
ህዝቡን የታደገው የመከላከያ ሰራዊት ላይ ዛሬ ምሽት ከመቀሌ ጀምሮ
በበርካታ ስፍራዎች በካሃዲው ኃይሎች እና ባደራጁት ኃይል ጥቃት
ተፈፅሞበታል።
👉 ይህ ጥቃት በሀገራችን እስካሁን ከደረሱት ጥቃቶች እጅግ አሰፋሪ
የሚያደርገው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ሰላም ለማስከበር በተለያዩ
ሀገራት በተሰማራበት ሀገር በውጭ ኃይል እንኳ አጋጥሞት
በማያውቀው ሁኔታ በገዛ ወገኑ ከጀርባው ጥቃት ተፈፀሞበታል።
👉 በዳንሻ በኩል በአማራ ክልል ላይ የፈፀሙት ጥቃት በአማራ ክልል
በነበረው ኃይል ተመክቷል
👉 የትግራይ ሕዝብ ወገናችን ነው ለጥቂት እኩዮች ሲባል ምንም እንኳ
የእኩዮች መሸሸጊያ ዋሻ ቢሆንም ሕዝባችን ላይ ጥቃት አንሰነዝርም
ብሎ በትዕግስት በቆየው ሰራዊት ላይ ጥቃት ተፈፅሞበታል
👉 በመላ ሀገራችን ቀድመው ባሰለጠኑት ባሰማሩት ባዘጋጁት ኃይል
በተለያየ ቦታ በተለያየ ከተማ በንፁሃን ዜጎች ላይ ጥቃት ሊፈፅሙ
ስለሚችል መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ከሚሊሻው ከፖሊስ ሰራዊት
እንዲሁም በአካባቢያቸው ከሚገኝ የመከለከያ ሰራዊት ጋር
በመተባበር ቀያችሁን ሰፈራችሁን እንድትጠብቁ አሳስባለሁ
👉 የመከላከያ ሰራዊት ከጠቅላይ ሰፍር በሚሰጥ ትዕዛዝ መለዮውን
ሀገሩንና ህዝቡን እንዲከላከል ለሚከፍለው መስዋዕትነት ዛሬም
እንደተለመደው በታሪኩ ውስጥ የሚታሰብ መሆኑን እገልፃለሁ።
👉 ይህ እኩይ ኃይል መጥፊያው በመድረሱ በሰላም በንግግር
በውይይት ሊፈቱ የሚችሉ ነገሮችን ባለፉት ጥቂት ቀናት ካለምንም
ሀፍረት በሚዲያ በመውጣት ከየትኛውም የውጭ ኃይል ጋር
በመተባበር ኢትዮጵያን እወጋለሁ ብሎ ሲያውጅ የነበረው ኃይል
ይህን ለማመን የሚያስቸግር ንግግር በተግባር ማዋሉን በዚህ ምሽት
አረጋግጧል።
👉 የትግራይ ህዝብ ወገኔ ዘመዴ ሕዝቤ ብሎ ላለፉት 20 ዓመታት
በቀበሮ ምሽግ ውስጥ በመሆኑ በብዙሺዎች የሚቆጠር መስዋዕትነት
የከፈለውን አንተን ለመጠበቅ አስፈላጊውን ሁሉ ያደረገው
የመከላከያ ሰራዊት የደረሰበት ጥቃት ጥቃትህ መሆኑን በመገንዘብ
ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጎን በመቆም ሀገርህን ከነዚህ ከሃዲ ኃይሎች
እንድትከላከልና በንቃት እንድትጠብቅ አሳስባለሁ።
👉 ይህ ጉዳይ ለኢትዮጵያ አሳዘኝ አሳፈሪም ተግባር ቢሆንም ዛሬም
እንደተለመደው በተደመረ በተባበረ ክንድ ይህንን ከሃዲ ጡት ነካሽ
ኃይል ለማሳፈርና ለመደምሰስ እስፈላጊውን ሁሉ የምናደርግ
መሆኑን እገልፃለሁ።
👉 ይህ አሳፋሪ ተግባር በማይደገምበት ሁኔታ የሚቀለበስበትን ተግባር
መላው የኢትዮጵያ ህዝብና የሀገር መከላከያ ሰራዊት በመተባበር
የሚፈፅሙት ይሆናል።
👉 ለመላው የሀገራችን ህዝቦች አስፈላጊውን መረጃ በየጊዜው
በሚመለከታቸው የመንግስት አከላት የሚሰጥ መሆኑን
እገልፃለሁ።
የኢፌድሪ ሚኒስትሮች ምክር ቤት በትግራይ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጀ
***********************
(ኢ ፕ ድ)
የኢፌድሪ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ጥቅምት 25/2013 ባደረገው 21ኛ አስቸኳይ ልዩ ስብሰባ መንግሥት የሀገርን ሰላምና ሕልውና፣ የሕዝብንና የዜጎችን ደህንነት የማረጋገጥ እና ሀገሪቷን ወደ ሁከትና ብጥብጥ የሚወስዱ ማናቸውንም ድርጊቶችን የመከላከል ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነት ያለበት መሆኑን በመገንዘብ፤
እንዲሁም በትግራይ ብሔራዊ ክልል ውስጥ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን እንዲሁም የሕዝብን ሰላምና ፀጥታ አደጋ ላይ የሚጥሉ በተለይም የሀገርን ሉዐላዊነት የሚገዳደሩ፣ የፌደራል መንግሥት በሕገ መንግሥቱ የተሰጠውን ሥልጣንና ኃላፊነት በክልሉ እንዳይወጣ እና ሀገሪቷን የጦር አውድማ የሚያደርጉ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔዎችን ጭምር በመጣስ በርካታ ሕገ ወጥ ተግባራት እየተፈፀሙ በመሆኑ፤
ይህን ሁኔታ በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የማይቻልበት ደረጃ ላይ መደረሱን በመረዳት፤ በሕገ መንግሥቱ በተደነገገው መሠረት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመጠበቅ ልዩ እርምጃዎችን መውሰድ የሚያስችል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመደንገግ እና ተግባራዊ በማድረግ ሁኔታውን በመቆጣጠር በሀገሪቱ ሰላምና ሕልውና ላይ የተጋረጠውን አደጋ መከላከል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 93/1/ሀ መሰረት የሚከተለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለስድስት ወራት ተፈጻሚ የሚሆን ሲሆን፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚያስፈፅም በኢፌድሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ሰብሳቢነት የሚመራና አግባብነት ካላቸው አካላት የተወጣጡ አባላት ያሉት ግብረኃይል በዚህ አዋጅ ተቋቁሟል።
ግብረኃይሉ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲሆን ‘‘የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ግብረሀይል’’ ተብሎ ይጠራል።
አዋጁ በመላው የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መስተዳድር ተፈፃሚ የሚደረግ ሲሆን፣ እንደያስፈላጊነቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተፈፃሚ ወይም ቀሪ የሚሆንባቸውን ተጨማሪ አካባቢዎችን ግብረኃይሉ በሚያወጣው በመመሪያ ይወስናል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አስመልክቶ ዝርዝር መርጃዎች በየጊዜው ለህብረተሰቡ የሚሰጡ ይሆናል።
"መከላከያ ሠራዊት የሀገር አንድነት እና ሰላምን ለማስከበር የሚወስዳቸውን እርምጃዎች በመደገፍ የኢዜማ አባላት እና አመራር ከጎኑ እንደሚሰለፉ ፓርቲው አስታወቀ
************************************
(ኢ ፕ ድ)
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ሕወሓት በትግራይ ክልል በሚገኘው የኢፌዴሪ መከላለከያ ሠራዊት ላይ የከፈተውን ጥቃት በፅኑ እንደሚያወግዘው ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።
በተለያየ ጊዜ ሕወሃት ሲያስተላልፋቸው የነበሩ የሥርዓት አልበኝነት ጥሪዎች እና በክልሉ ሕግን ተላልፎ ሲፈጽም የነበራቸው ድርጊቶች አልበቃ ብለው የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ምልክት የሆነው መከላከያ ሠራዊታችን ላይ የፈፀመው ጥቃት በፍፁም በዝምታ የሚታለፍ እንዳልሆነ እናምናለን ብሏል፤ ኢዜማ በመግለጫው።
የነበረው ችግር በንግግር መፈታት ከሚችልበት ምዕራፍ አልፎ አሁን የደረሰበት ደረጃ መድረሱ በጣም አሳዝኖናል ሲልም ነው ያስታወቀው።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የሀገር አንድነት እና ሰላምን ለማስከበር የሚወስዳቸውን እርምጃዎች በመደገፍ የኢዜማ አባላት እና አመራር ከጎኑ እንደምንሰለፍ እናሳውቃለን ያለው ኢዜማ፤ በሚወሰዱ እርምጃዎች ሰላማዊ ዜጎችን ምንም ዓይነት ጉዳት እንዳይደርስባቸው አስፈላጊው ጥንቃቄ መደረግ እንደሚገባው ለማስታወስ እንወዳለን ሲልም አሳስቧል።
የትግራይ ሕዝብ የሚወሰደው እርምጃ ለሀገር አንድነት እና ሰላም ማስከበር ብቻ እንደሆነ በመረዳት ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን እንዲቆም ኢዜማ ጠይቋል።
"መላው የኢትዮጵያ ሕዝብም ይህንኑ በመረዳት አብሮነታችንን አደጋ ላይ የሚጥሉ እና ለሰላም እና ደህንነት እንቅፋት የሚሆኑ ማንኛውንም እንቅስቃሴዎች ከማድረግ ተቆጥበን አካባቢያችንን በንቃት እየጠበቅን ለሰላም እና ደህንነት መከበር ከፀጥታ አስከባሪዎች ጋር ትብብር እንድናደርግ የአደራ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን" ሲልም ኢዜማ ገልጿል።