Gazette Plus / ጋዜጣ ፕላስ/
25.1K subscribers
41K photos
338 videos
7 files
5.81K links
Ethiopian Press Agency, established in 1940 , is a public printing media enterprise operating in Ethiopia.
Download Telegram
የመምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች የሙያ ፈቃድ አሰጣጥና ዕድሳት በቴክኖሎጂ የተደገፋ እንደሚሆን ተገለፀ።
----------------------------
የትምህርት ሚኒስቴር ከሁሉም ክልሎች ከተወጣጡ የመምህራንና ትምህርት ቤት አመራሮች የሙያ ፈቃድ ባለሙያዎች ጋር እየተወያየ ነው።
በውይይቱም የ 2012 ዓ.ም እቅድ አፈፃፀም እና የ 2013ዓ.ም እቅድ ይቀርባል።።
በትምህርት ሚኒስቴር የመምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች ሙያ ፈቃድ አሰጣጥና ዕድሳት ዳይሬክተር ወ/ሮ ካሳነሽ አለሙ የትምህርት ዘርፉን ጥራት የሚለካበት አንዱ መንገድ የሙያ ፈቃድ አሰጣጥና እድሳት በመሆኑ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ትኩረት ሰጥቶ እየተሰራበት መሆኑን ገልፀዋል።
በውይይት መድረኩ የተመዛኞችን የምዘና ውጤትና ትንተናን ጨምሮ ከምዝገባ እስከ ሰርቲፊክሽን ድረስ ያለውን ሂደት የሚያሳይ በቴክኖሎጅ የተደገፈ ዳታ ቤዝ ትውውቅ ይደረጋል፡፡
በመድረኩም የሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳድሮች የመምህራንና ትምህርት ቤት አመራሮች የሙያ ፈቃድ የ2012 በጀት ዓመት ሪፖርት ይቀርባል።
በቀጣይም የመምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች ምዘና የጥናት ሰነድ ላይና ከመምህራን ትምህርት ኮሌጅ ተመርቀው በሚወጡ መምህራን የሙያ ብቃትና ሌሎች የትኩረት አቅጣጫዎች ዘሪያ ውይይት የሚደረግ ይሆናል።
የኢትዮጵያ ከንቲባዎች ፎረም ተመሠረተ
***********
(ኢ.ፕ.ድ)

የኢትዮጵያ ከተሞች የከንቲባዎች ፎረም ዛሬ ተመስርቷል።
በፎረሙ ምሥረታ ላይ የከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ሚኒስትሯ ኢ/ር አይሻ መሐመድ እንደገለፁት ፎረሙ የከተማ ከንቲባዎች እና አመራሮች የነዋሪዎቻቸውን ችግሮች ለመፍታት በጋራ እንዲመክሩ እድል ይፈጥራል ብለዋል።

ከንቲባዎች በሚመሯቸው ከተሞች በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በመኖሪያ ቤት ግንባታ እና በመሠረተ ልማት አቅርቦት ባለሀብቱን እና ኅብረተሰቡን በማሳተፍ እና ባለቤት በማድረግ ከተሞች ላይ ውጤት ለማምጣት በማሰብ የተመሠረተ ነው ተብሏል ።
በተጨማሪም ፎረሙ ከተሞችን ውብ፣ ጽዱ እና አረንጓዴ በማድረግ ለነዋሪዎች ማመቻቸት ላይ የሚሠራ ሲሆን ድህነት ቅነሳ እና ዘላቂ ልማት ማረጋገጥ ላይም አተኩሮ እንደሚሠራ ተገልጿል። ከዚህም ባለፈ ፎረሙ በከንቲባዎች መካከል የእርስ በእርስ ትብብር እና የተሞክሮ ልውውጥ እንዲኖር ያስችላል ተብሏል።
የከተማ ከንቲባዎች በበኩላቸው ፎረሙ በከተሞች ለሚታዩ ችግሮች የተናጠል ሳይሆን የጋራ መፍትሔ ለማምጣትና የልምድ ልውውጦችን ለማድረግ ያስችላል ብለዋል።

ፎረሙ የከተማ ከንቲባዎች ተገናኝተው በወቅታዊ የከተሞች የትኩረት አጀንዳ ላይ ጽሁፍ ቀርቦ የሚወያዩበት፣ የተሻለ አሰራር ካላቸው ከንቲባዎች ልምድ የሚለዋወጡበት፣ ያጋጠማቸው ፈተና ካለም መፍትሔ በጋራ የሚያፈላልጉበት እና የተሻለ አፈጻጸም ላከናወኑ ከንቲባዎች ዕውቅና የሚሰጥበት ነው ተብሏል፡፡

በተጨማሪም ሀገር በቀል የሆነ እውቀት እንዲጎለብት ማበረታታትና ከተሞች ከከተሞች ጋር የሚኖራቸውን ትብብርና ትስስር ማመቻቸት የፎረሙ አንዱ አላማ መሆኑን በምስረታ ላይ ተገልጿል ።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያ ከንቲባዎች ፎረም “የተሻለ ከተማ ለተሻለ ህይወት” በሚል መሪ ቃል የከተሞች ፎረም የመመስረቻ ስነ ስርዓት ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ፣የከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ሚንስትር ኢ/ር አይሻ መሀመድ እና የክልል ከተሞች ከንቲባዎች ተሳትፈዋል ።
በኢትዮጵያ የከተሜነት ሂደት ረጅም ዘመን ከማስቆጠሩ አንፃር ዕድገቱን የሚመጥኑ ስራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳሰቡ
*************
(ኢ.ፕ.ድ)

በኢትዮጵያ የከተሜነት ሂደት ረጅም ዘመን ከማስቆጠሩ አንፃር ዕድገቱን የሚመጥኑ ስራዎች በፍጥነት ማጠናከር እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን አሳሰቡ።

የከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር አዘጋጅነት "ክልላዊ ስፓሻል ልማት ፕላን ለተመጣጣኝ ሀገራዊ እድገት እና ብልፅግና" በሚል መሪ ቃል ሃገር-አቀፍ መድረክ በሸራተን አዲስ ሆቴል ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በሃገሪቱ የከተሜነት ሂደት ረጅም ዘመን ከማስቆጠሩ አንፃር ዕድገቱን የሚመጥኑ ስራዎች በፍጥነት ማጠናከር ይገባል ~ ብለዋል።

የክልላዊ ስፓሻል የልማት ፕላን ዝግጅት እና የከተማ ሙከራ ማዕከል ምስረታ ከሃገራዊ ለውጥ ጉዞ ጋር አጣጥሞ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ከህዝብ ብዛት ፈጣን ዕድገት ጋር ተያይዞ ከተሞች ሊሸከሙ የሚችሉበትን ኢኮኖሚያዊ አቅም አስቀድመው በመገንባት ሚናቸውን እንዲወጡ አስገንዝበዋል።

በቀጣይ ተግባራዊ በሚደረገው ዕቅድ መሰረት በተለያየ ደረጃ በከተሞች እና አጎራባች የገጠር ቀበሌዎች የሚስተዋሉ ህገ-ወጥነት እና የከተሞች ዘፈቀዳዊ መስፋፋት በዘላቂነት ለመፍታት ርብርብ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

በተጨማሪ የክልላዊ ስፓሻል ልማት እና ክላሰተር ፕላን ማዘጋጀትና የከተማ መሬት አሰተዳደር ስርዓቱን ማዘመን በዕቅዱ ልዩ ትኩረት እንደተሰጠው የምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት መረጃ ግልጿል።

የከተሜነት እድገት ስርዓት ተመጋጋቢ፣ የተመጣጠነ እና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ በውጤታማነት ለመምራት በየደረጃው የሚገኙ አመራር አካላት በትኩረት እንዲረባረቡ ጥሪ አቅርበዋል።

በመጨረሻም የክልላዊ ስፓሻል የልማት ፕላን ዝግጅት እና የከተማ ላብራቶሪ ምስረታ ለዚህ ደረጃ እንዲበቃ አስተዋጽኦ ያበረከቱ አካላትን አመስግነዋል።
በሕገ መንግሥቱ የተሰጠውን ኃላፊነት በተሻለ መልኩ ለመወጣት ማሻሻያዎችን ሊያደርግ መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስታወቀ
*******************
(ኢ.ፕ.ድ)

በሕገ መንግሥቱ የተሰጠውን ኃላፊነት በተሻለ መልኩ ለመወጣት የሚያስችለውን አቅም ለመፍጠር ሪፎርም ለማድረግ በሂደት ላይ መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስታወቀ።

ምክር ቤቱ ተቋማዊ ማሻሻያ ለማድረግ ይቻል ዘንድ በአዲስ አበበ ዩኒቨርሲቲ አጥኚ ቡድን በተዘጋጀው መነሻ ሪፖርት ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።

ምክር ቤቱ በሕግ በተሰጠው ሥልጣንና ተግባራት መሠረት በሕዝቦች መካከል በፍትሕ እና በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ዴሞክራሲያዊ ሕብረ ብሔራዊነት አንድነት ስር እንዲሰድድ እና እንዲዳብር በማድረግ ጠንካራ ሀገረ መንግሥት በመገንባት፣ ተቋማትን በመገንባት እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ ባህል ግንባታ ሂደት ከፍተኛ ድርሻ ያለው ምክር ቤት መሆኑን በመድረኩ ላይ ለተሳታፊዎች ተብራርቷል።

ምክር ቤቱ የአሁን ቁመና ከላይ የተዘረዘሩትን ሚናዎች ለመወጣት በሚያስችለው ቁመና ላይ የማይገኝ በመሆኑ ተቋማዊ ሪፎርም ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አቶ አደም ፋራህ ገልጸዋል።

በመሆኑም በሕገ መንግሥቱ የተሰጠውን ኃላፊነት በተሻለ መልኩ ለመፈጸም ሪፎርም ይደረጋል ብለዋል አፈ ጉባዔው።

ምክር ቤቱ የሚያካሄደው ሪፎርም አራት መሠረታዊ የትኩረት አቅጣጫዎች ማለትም ሕብረ ብሔራዊ አገራዊ አንድነት እና ዘላቂ ሰላም መገንባት፣ ውጤታማ የፊሲካል ሽግግር፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ማረጋገጥ፣ የሕገ መንግሥት የበላይነትን እና ሕገ መንግሥታዊነትን ማረጋገጥ እንዲሁም ተቋማዊ የማስፈጻም አቅም ግንባታ ይገኙበታል ሲሉ አፈ ጉባዔው አክለው ገለጻዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አጥኚ ቡድን የሚካሄደው ጥናትም በአራቱ መሠረታዊ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ አተኩሮ ምክር ቤቱን ያጠነክረዋል ተብሎ ይጠበቃልም ነው ያሉት።

ከጥናቶቹ አንዱ ‘ልዩ ዓላማ ያላቸው የበጀት ድጎማ ጥራት እና ስርጭት ዳሰሳ’ የሕገ መንግሥት የበላይነትን እና ሕገ መንግሥታዊነትን ማረጋገጥ ላይ ያተኩራል።

ጥናቱ የበጀት ድጎማ ስልት ክልሎችን ፍትሓዊ በሆነ መልኩ ለመጥቀም በቀጣይ በምን መልኩ እንደሚከናወን አጠቃላይ አቅጣጫን የሚያመለክት ይሆናል ተብሏል።

ጥናቱ ‘በክልሎች መካከል የሚደረገውን የመሠረተ ልማት ዝርጋታን’ እንደሚዳስስ ነው የተገለፀው።

መሠረተ ልማት ለኢኮኖሚ ዘርፍ ውጤታማነት አቻ የማይገኝለት ዘርፍ መሆኑን ዩኒቨርሲቲው ባቀረበው መነሻ ጥናት ተጠቆሟል።

በክልሎች መካከል የሚደረገው የመሠረተ ልማት ስርጭት ፍትሐዊነትን ማዕከል በማድረግ የማኅበረሰብ እና የፖለቲካ ብልጽግና እውን የሚያደርግ ሀገረ-መንግሥት ግንባታን የሚያግዝ በሚሆንበት መልኩ እንዲሆን አቅጣጫ ያስቀምጣል ነው የተባለው።

ሕብረ ብሔራዊነት እና ዘላቂ ሰላም ላይ አተኩሮ ስለሚካሄደው ጥናት እና የተቋሙን የማስፈጸም አቅም አስመልክቶ ስለሚካሄደው ጥናትም መነሻ ሪፖርት ቀርቧል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና በበኩላቸው ጥናቱ ምክር ቤቱ በሚፈልገው መልኩ እንደሚካሄድ እና ዩኒቨርሲቲው ጥናቱን በሁለት ወራት ውስጥ አጠናቅቆ ለማስረከብ እንደሚሠራም መግለጻቸውን ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የጦር መሳሪያ አዋጁ የሚቀማ ሳይሆን የያዙትን ህጋዊ ለማድረግ እንደሚረዳ ተገለጸ
*************************
(ኢፕድ)
አዲስ አበባ: ኢትዮጵያ ያጸደቀችው የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅ በግለሰቦች እጅ የተያዙትን መሳሪያ ለመቀማት የወጣ ሳይሆን ህጋዊ ለማድረግ የሚረዳ መሆኑን የሰላም ሚኒስትር ሚኒስቴር አማካሪ አቶ ሚናስ ፍሰሃ ተናገሩ።

የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር አማካሪ ሚናስ ፍሰሃ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅ ህብረሰተቡ ቀድሞ የያዘውን የጦር መሳሪያ የሚቀማ ሳይሆን ቀድሞ የያዙትም ህጋዊ ለማድረግ የሚረዳ ነው። ማስመዝገቡም ጥቅሙ ከፍተኛ ነው።

አዋጁ ከጸደቀ 10 ወራት ያስቆጠሩን ያስታወሱት አቶ ሚናስ ፣ ቀደም ብለው የታጠቁ የህብረተሰብ ክፍሎች የታጠቁት የጦር መሳሪያ በቀሪው ዓመት ከሁለት ወር የሽግግር ጊዜ በአካባቢያቸው በሚገኙ ተቆጣጣሪ ተቋም ተገኝቶ በሚያወጣው የጊዜ ሰሌዳ ህጋዊ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል።

እንደ አቶ ሚናስ ገለጻ፤ በጊዜው የጦር መሳሪያውን የሚያስመዘግብ ሰው ከዚህ ቀደም መሳሪያው በህገወጥ መንገድ የተገኘ ቢሆንም እንኳ እንደየወንጀሉ ሁኔታ ምህረት ይደረግለታል። ሆኖም በጊዜ ገደቡ ውስጥ ፍቃድ ያልወጣበት የጦር መሳሪያ በተቆጣጣሪው የሚወረስ ሲሆን፤ የጦር መሳሪያ ፍቃዱ ለግለሰብ በሁለት ዓመት ለድርጅት ደግሞ በ5 ዓመት መታደስ እንዳለበት ስለተደነገገ ቀድሞ ፍቃድ ማውጣት ይገባል።

ለመሳሪያቸው ፍቃድ ለማግኘት የሚፈልጉ ሰዎች የአደንዛዥ እጽ ወይም የመጠጥ ሱስ የሌለባቸው እና የአእምሮ ጤናቸው የተስተካከለ እንዲሁም በአካባቢያቸው የመልካም ስነ ምግባር መገለጫ ማረጋገጫ ማቅረብ ይኖርባቸዋል ያሉት አቶ ሚናስ፣ ለአብነት በመንደራቸው ከብዙ ሰዎች ጋር የሚጣሉ እና አምባጓሮ ውስጥ በተደጋጋሚ የሚሳተፉ ከሆነ ለደህንነታቸው ሲባል የጦር መሳሪያ እንዲይዙ ህጉ እንደማይፈቅድ አስታውቀዋል ።

እንደ አቶ ሚናስ ከሆነ፤ አዋጁ በተለምዶ የጦር መሳሪያ የሚጠቀሙ አርብቶ አደር እና አርሶአደሮችን አኗኗር ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው። በባህል እና በደንባቸው መሰረት ሲወለድም ጭምር መሳሪያ የሚሰጥበት አካባቢ ቢኖርም ረጅም ጊዜያት ወንጀል ሳይፈጽሙ የሚኖሩ ማህበረሰቦችም አሉ።

ባህሉንምባገናዘበ መልኩ ለአካለ መጠን የደረሰ እና መሳሪያ ለመያዝ ብቁ የሆነ ሰው እንዲይዝ ህጋዊ እውቅና የሚሰጥ በመሆኑ አዋጁ መሳሪያዎቻችንን ይነጥቀናል የሚል እሳቤ ያላቸው ሰዎች በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው መስራት ያስፈልጋል።

ፍቃድ በሚሰጣቸው የጦር መሳሪያዎች ላይ መለያ ምልክት እንደሚደረግ የተናገሩት አቶ ሚናስ፤ ወንጀል ሲፈጸም ለይቶ ለምርመራ ለማቅረብ እና ወንጀለኛን ለመያዝ የሚረዳ አሰራር ተግባራዊ እንደሚደረግም ገልጸዋል። “አርኤስቲኤስ” የሚባል የህገወጥ ጦር መሳሪያን እና ፍቃድ ያላቸውን ለይቶ መመዝገብ እና ለትንተና ለማቅረብ የሚረዳ ቴክኖሎጂ በሀገር ውስጥ መገጠሙን ተናግረዋል።

ቴክኖሊጂው ልክ እንደመኪና ሻንሲ እና ሞተር ቁጥር የእያንዳንዱን መሳሪያ ቁጥር እና ይዘት ከሙሉ መስረጃው ጋር ይመዘገብበታል። በመሳሪያው ዙሪያ ለሚመለከታቸው ተቋማት ባለሙያዎች ስልጠና መሰጡትን አስረድተዋል። ቴክኖሎጂው ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሲደረግ የሰዎችን ሰላም ደህንነት ውስጥ የከተተውን ህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርንም ለመከላከል እንደሚረዳ ገልጸዋል።

ወጥ የሆነ ቅንጅት ባለመኖሩ በኢትዮጵያ የሚገኝ የጦር መሳሪያ ብዛት እንደማይታወቅ የገለጹት አቶ ሚናስ፤ በተለይ የድንበር አካባቢዎች የህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ይውሉ እንደነበር ገልጸዋል። አዋጁ ተፈጻሚ ከሆነ በኋላ ግን በቀጣይ ጊዜያት ማን ጋር ምን አይነት መሳሪያ እንዳለ እና ሀገር ውስጥ ምን ያክል መሳሪያዎች እንዳለ በማወቅ ለህገወጥነት እና ወንጀሎችን በብቃት ለመከላከል የሚያስችል አቅም እንደሚፈጠር አስረድተዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅን በ2012 ዓ.ም ታህሳስ ወር መጨረሻ ላይ ማጽደቁ ይታወሳል ። በአዋጁ መሰረት አነስተኛ ወይም ቀላል መሳሪያን ለአንድ ሰው አንድ ብቻ እንዲይዝ የሚፈቅድ ነው። ከፍቃድ ውጪ የጦር መሳሪያ፣ የጉዳት ማድረሻ እቃ፣ የጦር ሜዳ መነጽር፣ በጦር መሳሪያ ላይ ሊገጠም የሚችል ማንኛውም አይነት መነጽር ወደ ሀገር ማስገባት፣ ከሀገር ማውጣት፣ መያዝ፣ ማስቀመጥ፣ ማከማቸት፣ መገልገል፣ ማሳየት፣ መደለል፣ መሸጥ፣ መግዛት፣ ማስተላለፍ፣ ማዘዋወር፣ ማጓጓዝ፣ ማምረት፣ ማሰልጠንና ማስወገድ ክልክል ሆኗል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 21/2013
ጌትነት ተስፋማርያም
የኦሮማራ መድረክ ወደ ብሄራዊ መድረክነት አደገ
****************************
(ኢፕድ)
አዳማ ፦ ከአንድ አመት በፊት የተጀመረው የኦሮ-ማራ መድረክ ወደ ብሄራዊ መድረክነት ማደጉ ተገለጸ ። መድረኩ ብሄራዊ መግባባት ለመፍጠርና የውይይትን ባህል ለማዳበር ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተጠቆመ።

በአዳማ ከተማ ትናንት መድረኩ ሲከፈት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት አንጋፋው ፖለቲከኛ አቶ ሊንጮ ለታ፣ ከዚህ ቀደም በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተነሳውን ውዝግብ ተከትሎ ችግሩን ለማርገብ መድረኩ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አነሳሽነት የዛሬ ዓመት አካባቢ መጀመሩት አስታውሰዋል።

መድረኩ ወደ ብሄራዊ መድረክነት መሸጋገሩን አስታውቀው፣ መድረኩ ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ትልቅ ተግዳሮት የሆነውን ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ችግር ለዘለቄታው ለመፍታት የሚያስችል እንደሚሆን አመልክተዋል ።

የችግሩ መሰረታዊ ምንጭ የዲሞክራሲ ባህላችን አለማደግ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ሌንጮ ፣ ለአንድ ዓመት ያህል የአማራና የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች በአገራዊና በክልላዊ ጉዳዮች ሲወያዩ መቆየታቸው አስታውቀዋል። በዚህም በተለያዩ ጉዳይ ላይ መግባባት ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል ። ይህም በሰከነ መንፈስ የመነጋገር እና የዲሞክራሲን ባህልእየተለማመድን ለመሆናችን ማሳያ ነው ብለዋል።

አገር አቀፍና ሁሉንም ቡድኖች ያሳተፈው የውይይት መድረኩ ለፖለቲካ ችግሮችን ዘላቂ መፍትሄ ያስገኛል ተብሎ እንደሚታመን ገልጸው፣ በተለይ ምን አይነት ኢትዮጵያ ናት የምታግባባን እና ልታስማማን የምትችለው በሚለው ጉዳይ ላይ ስምምነት ይደረሳል ተብሎ እንደሚጠበቅም አመልክተዋል።

የመድረኩ አወያይ ዶክተር ዲማ ነጋዎ በበኩላቸው፤ የኦሮሞና የአማራ የፖለቲካ ድርጅቶች ከዚህ ቀደም በ10 ጉዳዮች ላይ ስምምነቶች መደረሳቸውን አመልክተው፣ በሁለቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ምሁራንና ሽማግሌዎች ተወስኖ የቆየው የወይይት መድረክ ወደ አገራዊ መድረክነት እንዲሸጋገር መደረጉን አስታውቀዋል። ይህም በአገራችንን ያለውን የፖለቲካ የውይይት ባህል ለማዳበርና ብሄራዊ መግባባት ለመፍጠር ይረዳል ብለዋል።

የመድረኩ ሌላኛው አወያይ ዶክተር ገበያው ጥሩነህ በበኩላቸው፣ የአሮሞና የአማራ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጀመሩት ውይይት ፍሬ አፍርቶ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ደርሰዋል ። የዚህ ፍሬ አንዱ ማሳያም በሁለቱ ወገኖች ተወስኖ የነበረው ውይይት ወደ አገራዊ ውይይት ማደግ መቻሉ እንደሆነም ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት በመካሄድ ላይ ያለው አገራዊ የፖለቲካ ሽግግርና የለውጥ ሂደት መልካም አጋጣሚዎች በመጠቀም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በአገራዊ የፖለቲካ ፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የምክክር መድረኮች በመካሄድ ላይ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

በአማራና በኦሮሞ ብሄሮች ምሁራንና ተጋባዥ እንግዶች፣ ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ የሁለቱ ህዝቦች ሁሉን አቀፍ ግንኙነቶች የበለጠ ለማጠናከር የሚያስችሉ ውይይቶችና ጉባኤዎችን ከታህሳስ 2012 ዓ.ም ጀምሮ በተደጋጋሚ ማካሄዳቸውን ጠቁመዋል።

በተለይም የፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎች በክልላዊና አገራዊ ነባራዊና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ምክክር ሲያደርጉ ቆይተው፣ በበርካታ ፖለቲካዊ አቋሞች ላይ የጋራ መግባባት በመድረስ መስከረም 23 ቀን 2013 ዓ.ም ታሪካዊ ስምምነት መፈራረማቸውን አመልክተዋል ።

በአዳማ ከተማ በተካሄደው አገራዊ መድረክም በአገሪቱ ከሚገኙ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ ምሁራን፤ ታዋቂ ሰዎች፣ የሲቪል ማህበራት፣ ወጣቶች፣ ሴቶችና የብሄር ብሄረሰቦች ተወካዮች ተሳትፈዋል። ይኸው አገራዊ የምክክር መድረክም በቀጣይ ባህር ዳር ከተማ እንደሚካሄድ ዕቅድ መያዙም በወቅቱ ተገልጿል።

በመድረኩ ተሳታፊ የሆኑት የአማራ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ፕሬዚዳንት ሼህ ሰይድ ማህመድ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የሀይማኖት አባቶች የአገርን ችግር ለመፍታት ያለመ ውይይት ማድረጋቸው ጥሩ ጅምር መሆኑን ገልጸው፤ ይህ ወደ ህዝቡ ወርዶ ፍሬ እንዲያፈራ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

ውይይቱ የሰላም መታጣት ባለባቸውና ግጭቶች በሚከሰቱባቸው አካባቢዎች ተወያይቶና ችግሩን ለይቶ መፍትሄ ለመስጠት መንገድ ይጠርጋል የሚል እምነት እንዳላቸው አመልክተው፣ በተለይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከራሳቸውን ፍላጎት ይልቅ ለህዝብ ጥቅም አስበው ህዝብ እንዳይጋጭ የማድረግ አላፊነት እንዳለባቸው አመልክተዋል። ውይይቱ ለዚህ ስንቅ እንደሚሆናቸው ጠቁመዋል።

የሀይማኖት አባቶች ግጭት እንዳይከሰት፤ ከተከሰተም በእርቅ እንዲፈታና በህዝቦች መካካል ወንድማማችንትን፣ መተባበርና አንድነትን በማስረጽ ረገድ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው አመልክተዋል።

“ በእነዚህ እሴቶች ዙሪያ በቤተ ክርስቲያናት፣ በመስኪዶች ትምህርቶች ቢሰጡም ሰው የአምላኩን ቃል ሰምቶ ቢተገብር ኖሮ ሰዎች አይፈናቀሉም፣ የሰው ህይወት አይጠፋም ግጭቶችም አይኖርም። ይህም ሆኖ በአገሪቱ በስነ ምግባር የታነጸ መልካም ዜጋና አንድነትን በሚሸረሽሩ ጉዳዮች የማይሳተፍ አማኝ ለማፍራት የማስተማር ስራቸውን አጠና ከረው ሊቀጥሉ ይገባል”ብለዋል ።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 21/2013
ጌትነት ምህረቴ
“ትራምፕ የሰነዘሩት ንግግር ለአፍሪካውያን ያላቸውን የተዛባ አመለካከት የሚያሳይ ነው” ፕሮፌሰር አደም ካሚል
***************************
(ኢፕድ)
አዲስ አበባ:- የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በህዳሴ ግድብ ላይ የሰነዘሩት ንግግር ለአፍሪካውያን ያላቸውን የተዛባ አመለካከት የሚያሳይ ነው ሲሉ የታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር አደም ካሚል ተናገሩ።

የታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር አደም ካሚል ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኢትዮጵያ እና በግብጽ መካከል ጦርነት ሊቀሰቅስ የሚችል ንግግር ከሰሞኑ ማድረጋቸው ከተመረጡ ጀምሮ ለአፍሪካ ሀገራት የነበራቸውን የተዛባ አመለካከት
የሚያሳይ ከመሆኑ በተጨማሪ ፕሬዚዳንቱ በንግድ ላይ ትርፋማ የሚያደርጋቸውን ጉዳይ እንጂ ፖለቲካው ላይ እምብዛም በሳል አለመሆናቸውን ያሳየ ነው።

እንደ ፕሮፌሰር አደም ገለጻ፤ ፕሬዚዳንቱ በሁለት ሀገራት መካከል በጦርነት መሃል ለሚፈጠረው ቀውስ ሳይሆን በዚሁ ቀውስ መካከል ለሚኖረው የመሳሪያ ውድድር ትኩረት እንዳላቸው በንግግራቸው አሳይተዋል። በምስራቅ አፍሪካ አካባቢ አዲስ የጦር መሳሪያ ገበያ ቀጣና ለማቋቋም ያሰቡ የሚያስመስል ጠብ ጫሪ ንግግር ማንሳታቸው በብዙዎች ዘንድ ለዲፕሎማሲ እና ፖለቲካዊአካሄድ ቁብ እንደማይሰጡ አመላካች ሆኗል።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ በአብዛኛውን ጊዜ ከንግግራቸው መታዘብ እንደተቻለው ለአፍሪካ ያላቸው አመለካከት የተዛባ ነው ያሉት ፕሮፌሰር አደም፤ ከዚህ ቀደም የዘር ሃረጋቸው ከአፍሪካ በሚመዘዝ አሜሪካውያን ላይ አጸያፊ ንግግሮችን ሰንዝረው የነበረ መሆኑን አስታውሰዋል። ይህ ተግባራቸው እየተባባሰ ሄዶ አሁን ላይ ሀገራትን ወደጦርነት የሚጋብዝ ንግግር በህዳሴ ግድብ ላይ መሰንዘራቸው ደግሞ ፕሬዚዳንቱ በኢትዮጵያ እና በግብጽ በሚካሄድ ጦርነት ተጠቃሚ ሊያደርጋቸውን የሚችለውን ምክንያት እየፈለጉ መሆኑን እንደሚያመላክት ገልጸዋል።

ብዙውን ጊዜ አሜሪካ እና ሌሎች ኃያል ሀገራት ኢኮኖሚያቸውን ለማነሰራራት እና ገቢያቸውን ለማሳዳግ በሁለት ቡድኖች አሊያም ሀገራት ግጭት መካከል ገብተው የጦር መሳሪያ በገፍ እንደሚያቀርቡ ይታወቃል። በቅርቡ እንኳን ቱርክና ግሪክ ውዝግብ ውስጥ ሲገቡ ወደጦርነት ማምራታቸው አይቀርም በሚል በአውሮፓ የሚገኙ ኩባንያዎች በአንድ ጊዜ 80 አውሮፕላኖችን ለመሸጥ ዝግጅት ሲያደርጉ እንደነበር ታውቋል።

ይህ የሚያሳየው የአንዱ ጦርነት ለሌላው የገቢ ምንጭ መሆኑን ነውና ጉዳዩን ተገንዝቦ በጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ስራ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና፣ ግብጽ ጉዳያቸውን መፍታት ይጠበቅባቸዋል።

እንደ ፕሮፌሰር አደም ከሆነ፤ ግብጾችም በበኩላቸው የግድቡን ስራ ለማስተጓጎል ብዙ ስራ ከጣሩ በኋላ ነው አማራጭ ሲጠፋ ወደአፍሪካ ህብረት አደራዳሪዎች የተመለሱት። በኢትዮጵያ ላይ አንዳች አደጋ ቢሰነዘር ደግሞ በቀጣናው ብሎም በአፍሪካ አህጉር የሚከሰተው ችግር ከባድ መሆኑን ግብጾችም ይገነዘቡታል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት ማዕከል መሆኗ እና በአህጉሪቷ ያላት ተቀባይነቷ ከፍተኛ በመሆኑ ግብጾችም የትራምፕን ንግግር ተከትለው ወደግጭት ቢያመሩ ውጤቱ ይሰምርላቸዋል ተብሎ አይጠበቅም። ኢትዮጵያን በጦነት መድፈር ማለት አፍሪካን መድፈር በመሆኑ አፈሪካውያንም ጉዳዩን አይቀበሉትም።

ሃበሾች እስካልነኳችሁ ድረስ እንዳትነኳቸው የሚለውን የነብዩ መሃመድን ትዕዛዝ መኖሩን ያስታወሱት ፕሮፌሰር አደም፤ ይህን ጥሰው ጥቃት ቢፈጽሙ የነብዩን ትዕዛዝ እንደመዳፈር የሚቆጠር በመሆኑ ግብጾች ከዕምነታቸውም አንጻር ሁኔታውን ግምት ውስጥ ማስገባታቸው እንደማይቀር ያላቸውን እምነት አስቀምጠዋል።

ግብጾች ኢትዮጵያ በሙስሊሙ ዓለም ያላትን ታሪካዊ ክብር ተጋፍተው እና የትራምፕን ንግግር ተከትለው ወደጦርነት ቢገቡ እንኳን የሚደርስባቸው ውርደት እና ኪሳራ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል። የዓረቡ ዓለምም የትራምፕ ጦርነት ቀስቃሽ ንግግር ቢኖር እንኳን ኢትዮጵያ ላይ አንድም ጥቃት እንዲፈጸም ለግብጽ ፍቃድ የሚሰጡበት ሁኔታ እንደሌለ ሀሳባቸውን ሰንዝረዋል።

ፕሮፌሰር አደም እንደገለጹት፤ ጦርነት ቢባል እንኳን ግብጾች ከእስራኤል ጋር በተደጋጋሚ ጊዜ የተሸነፉ መሆኑ ሲታወስ የጦር ሃይል ብዛት ሳይሆን ዋነኛው ነገር የአሸናፊነት ስሜቱ ነው። ኢትዮጵያውያንም ተለያይቶ ሀገርን ማዳን አይቻልምና ለውጭ ሃይል ክፍተት የማይሰጥ አንድነታቸውን አጠናክረው መቀጠል አለባቸው።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 21/2013
ጌትነት ተስፋማርያም
በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በተደረገ የቤት ውሰጥ ብርበራ ህገወጥ መሣሪያ ከተጠርጣሪዎች ጋር ይዞ ምርመራ እያጣራ እንደሚገኝ ፖሊስ አሰታወቀ
*******************
(ኢ.ፕ.ድ)

በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በተለያየ ጊዜ በተደረገ የቤት ውሰጥ ብርበራ ህገ-ወጥ የሆኑ 5ሽጉጦች ፣ 102 የሽጉጥ ጥይቶች እና 8 የክላሽ ጥይቶች ከ7ተጠርጣሪዎች ጋር ይዞ ምርመራ እያጣራ እንደሚገኝ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አሰታወቀ።

በተለያየ ቦታ እና ጊዜ ፖሊስ ከህብረተሰቡ በደረሰው ጥቆማ መሰረት ከፍርድቤት የመበርበሪያ ትዕዛዝ በማውጣት ባደረገው ብርበራ ህገ-ወጥ ሽጉጦችን እና ጥይቶችን ሊይዝ መቻሉን አስታውቋል።

የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ፖሊሰ መምሪያ የወንጀል ምርመራ ማስተባበሪያ ሀላፊ ም/ኢንስፔክተር ተዘራ ከፍያለው ከአዲስ ፖሊስ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳብራሩት፤ ከክፍለከተማው ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ከከተማው ዳር የሚገኝ እና የኬላ ፍተሻ በመኖሩ ቀደም ሲል በርካታ የጦር መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ የህብረተሰቡ ጥቆማ መሰረት ባደረገው ብርበራ ህገ ወጥ የሆኑ 5ሽጉጦች፣102 የሽጉጥ ጥይቶች፣8የክላሽ ጥይቶች እና የሽጉጥ ካርታዎችን ከነ ተጠርጣሪዎች በመያዝ ምርመራ እየተጣራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

በህጋዊ ሽፋን ህገወጥ ጦር መሳሪያ ይዘው የሚቀሳቀሱ ግለሰቦች እንዳሉ ያስታወሱት መርማሪው ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ለሀገር ሰላም እጦት ከመሆኑም ባሻገር ለኢኮኖሚ ውድመት ትልቅ መንስኤ በመሆኑ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመከላከል ህብረተሰቡ እያደረገ ያለውን እገዛ አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ሲሉ ሓላፊው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የትራምፕን ንግግር መቃወሚያ ዓለምአቀፍ የበይነመረብ ፊርማ የማሰባሰቢያ ንቅናቄ ተጀመረ
*********************************
(ኢፕድ)
አዲስ አበባ፡- በታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክርቤት ጽሕፈት ቤት እና በሌሎች አጋር አካላት አማካኝነት የዶናልድ ትራምፕ ንግግርን ለመቃወም ‹‹ፊርማችን ለህዳሴያችን›› በሚል የበይነ መረብ ዓለም አቀፍ የፊርማ ማሰባሰብ ንቅናቄ ተጀመረ።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሔ ፊርማ የማሰባሰቡ ንቅናቄ ይፋ በተደረገበት ወቅት እንደተናገሩት፤ የፊርማ ማሰባሰብ ሥራ ከባድና ለአገር ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ከመሆኑም በላይ ኢትዮጵያውያን እንዴት በጋራ መቆም እንደሚችሉ ማሳያ ነው። የተከፈተውን በር ተከትሎ መግባቱና ውጤቱን ማሳየቱ የእኛ ድርሻ ነውና እጃችንን ወደ ፊርማችን እናድርግ ብለዋል።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብርሀም በበኩላቸው እንዳሉት፤ ግድቡ ለድርድር የሚቀርብና ፕሬዚዳንቱ እንደተናገሩት ለቦምብና ለጥይትም የሚታሰብ አይደለም።

በሰላማዊ መንገድ ጨርሰን በዓለምአቀፉ ሕግ መሠረት እኛም ጎረቤቶቻችንም ተካፍለን እንድንጠቀምበት እየሰራን እንገኛለን።ስለሆነም የበይነ መረብ የፊርማ ማሰባሰብ ተግባር ከምንም በላይ የሚያስፈልግ በመሆኑ በድል እንዲጠናቀቅ ሁላችንም የበኩላችንን እንወጣ ሲሉ ጥሪ አድርገዋል።

ኢትዮጵያውያን ጸብን ሳይሆን ወዳጅነትን አንግበን የምንንቀሳቀስ ሕዝብ ነን።ሆኖም ግን ከጥንት ጀምሮ ለነካን ምላሹን እናውቅበታለን።አሁንም በዴሞክራሲያዊ መንገድ ድምጻችን ለህዳሴያችን በሚል የተለያዩ እንቅስቃሴዎች አድርገን ውጤታማ እንደሆንነው ሁሉ አሁንም ፊርማችን ለህዳሴያችንም በሚለው ሪከርድ ሰባሪ መሆን ይጠበቅብናል።ለዚህም ሁሉም ኢትዮጵያዊ በይነ መረቡ በመግባት ፊርማውን እንዲያኖር ሲሉ አቶ ኃይሉ አሳስበዋል።

ከአስተባባሪዎቹ መካከል አቶ ፍሬው በቀለ እንዳሉት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ምላሽ ለማግኘት 100 ሺህ የፊርማ ስብስብ መደረግ እንዳለበት ተናግረዋል።እርሳቸው እንዳሉት፤ ይህ ዓለምአቀፍ ንቅናቄ በመቶ ሺህ ብቻ የሚገደብ መሆን የለበትም።እንዲያውም ታሪክ ሊሰራበት የሚገባውና ሪከርድ የምንሰብርበት ሊሆን ይገባል ብለዋል።

ፊርማው በኢትዮጵያውያን ብቻ ቢፈረም እንኳን በሚሊዮን ይቆጠራል።በዓለምአቀፍ ሲሆን ደግሞ ብዙ የኢትዮጵያ ወዳጆችና ሰላም ወዳዶች በመኖራቸው ይህንን ይቀላቀላሉ።

ስለሆነም በተለይ ሚዲያው ይህንን በማሳወቅ በኩል የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።ፊርማው ተሰባስቦ ለአሜሪካ ምክርቤት ብቻ ሳይሆን ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ለአፍሪካ ህብረት፣ ለአውሮፓ ህብረት፣ ድርድሩን ለሚመሩት አካላት እንዲሁም ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ለሚባሉት ሁሉ ገቢ ይደረጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጭ ማህበር ፕሬዚዳንትና የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት አባል ኢንጅነር አመሀ ስሜ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ እስከዛሬ በሆኑት ሁሉ ኢትዮጵያን በአንድነት ከተነሱ ምንም የሚገታቸው ነገር እንደሌለ ማሳያ ነው።አሁን ደግሞ በአገር ሉአላዊነት ላይ ጣታቸውን የቀሰሩት ትራምፕ ያልተረዱት ነገር ካለ እንዲረዱትና ከተረዱም በኋላ የእኛ አጋር ሆነው አብረውን እንዲቆሙ ለማድረግ ይህን እንቅስቃሴ ማድረጉ እጅጉን ይጠቅማል።ዋጋው ጥቂት ቢመስልም በትሪሊዬን የሚገመት ዲፕሎማሲያዊ ምላሽን ያስገኛልና ፊርማችንን ለህዳሴያችን እንስጥ ሲሉ አሳስበዋል።

የፕሬዚዳንቱ ንግግር ሕዝቡን አንድ አድርጎታል። ይህንን በተለያዩ መንገዶች መደገፍ ያስፈልጋል ያሉት ኢንጅነሩ፤ በተለይ በውጭ ዲፕሎማሲው የተሻለ ሥራ መስራትና የፊርማ ማሰባሰቡን በታሪክ ማጠናቀቅ እንደሚገባ አስረድተዋል።በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ መነጋገር፤ መደማመጥና መሸናነፍ መቻል ላይ ማተኮር ይገባል።

ይህ ሲሆን አንድነት መጥቶ ኃይል ይሆናል፤ ይህንን አጥብቆ መያዝና በአባይ ጉዳይ አምባሳደር መሆን መቻልይገባል ሲሉ ተናግረዋል።የፕሬዚዳንቱን ንግግር ለመቃወም change.org እና petition gard white house በማለት ድረ-ገጽ ላይ ገብቶ መፈረም እንደሚቻል ተገልጿል። በተመሳሳይ ከሰኞ ጀምሮ ሁሉም ሰው የፌስቡክ ፕሮፋይሉን በህዳሴው እንዲቀይርም ጥሪ ቀርቧል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 22/2013
የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀመንበር ጄነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን ለሁለት ቀናት የሥራ ጉብኝት አዲስ ፈበባ ገብተዋል።
ብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ኢትዮ ቴሌኮምን በዓመት ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ሊያሳጣ በሚችል ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ
*****************
(ኢ.ፕ.ድ)
ብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ኢትዮ ቴሌኮምን በዓመት ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ሊያሳጣ በሚችል ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ።

የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ከኢንፎርሜሽን  መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ ከተማ የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል በሚፈፀምባቸው ቦታዎች ላይ ጥብቅ የመረጃና የክትትል ሥራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል።

በዚህም ትናንት በአዲስ አበባ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 እና ልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 በተካሄደ ኦፕሬሽን በህገ ወጥ መልኩ ዓለም አቀፍ የስልክ ጥሪዎችን በመጥለፍ በራሳቸው መስመሮች ለደንበኞች በማቅረብ ሕገወጥ ድርጊት ሲፈፅሙ የነበሩ ሦስት ተጠርጣሪዎች በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አማካኝነት በህግ በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ማድረጉን አገልግሎት መስሪያ ቤቱ አስታውቋል።

ተጠርጣሪዎቹ ከኢትዮ ቴሌኮም አውቅና ውጪ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የስልክ ጥሪዎችን በማስተላለፍ የራሳቸውን ገቢ ሲሰበስቡ መቆየታቸውን የገለፀው ብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፤ ሕገ ወጥ ድርጊቱ ባይከሽፍ ኖሮ፤ ኢትዮ ቴሌኮምን በዓመት ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ሊያሳጣው እንደሚችልም ጠቁሟል።

በወንጀል ድርጊቱ የተጠረጠሩት ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ሲውሉ፤ ሲገለገሉባቸው የነበሩ 10 ጌትዌይ (ሲምቦክስ)፣ 17 ቲፕሊንክ፣ 59 ሲዲኤምኤ፣ 3 ራውተር፣ 2 ሺህ ሲምካርድ፣ 3 ላፕቶፕ፣ የባንክ  ደብተሮች፣ ሲፒኦዎችና ሌሎች ሕገ ወጥ  መሳሪያዎች በኢግዚቢትነት  መያዛቸውን  ብሄራዊ  መረጃና ደህንነት አገልግሎት አስታውቋል።
 
ሕገ ወጦችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል በነበረው ሂደት ህብረተሰቡ ላሳየው የላቀ ተሳትፎ አገልግሎት መስሪያ ቤቱ ምስጋና አቅርቧል።

በቀጣይም ህብረተሰቡ ሕገ ወጦችን በማጋለጥ ረገድ የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል አገልግሎት መስሪያ ቤቱ ጥሪ አቅርቧል።
"የኢትዮጵያ እና የሱዳን ሕዝቦች በባህልና ታሪክ የተሳሰረ ጠንካራ ግንኙነት አላቸው"
ጠቅላይ ሚኒስትር  አቢይ አህመድ 
**************
(ኢ.ፕ.ድ)
የኢትዮጵያ እና የሱዳን ሕዝቦች በባህል እና በታሪክ የተሳሰረ ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጄነራል አልቡርሀን ጋር የአዳማ ከተማን የጎበኙ ሲሆን፤ በዚሁ ወቅት  አባ ገዳዎች ለጄነራል አልቡርሃን ፈረስ እና ጋሻ  ሸልመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስር ዶ/ ር አብይ አህመድ በማህበራዊ ገጻቸው፤ "አባገዳዎች የሁለቱ ሕዝቦች ትስስር ይጠብቅ ዘንድ መርቀውናል። ለጄነራል አልቡርሃን ፈረስ እና ጋሻ በመሸለም አክብሮታችንን ገልጸንለታል" ሲሉም አስታውቀዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ  ባለቤታቸው የማይታወቁ ቦታዎች፣ ህንጻዎች እና ቤቶች መገኘታቸውን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ
**************
(ኢ.ፕ.ድ)

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማው ያሉ ህገ-ወጥ ተግባራትን ለመከላከልና  ወደ ህጋዊ መስመር ለማምጣት ባደረገው ማጣራት ባለቤታቸው የማይታወቁ ቦታዎች፣ ህንጻዎች እና ቤቶች መገኘታቸውን አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ፅህፈት ቤት ዛሬ ማምሻውን ባወጣው የጥሪ ማስታወቂያ፤ የከተማ አስተዳደሩ በከተማው ያሉ ህገ-ወጥ ተግባራትን ለመከላከልና  ወደ ህጋዊ መስመር ለማምጣት የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ መሆኑ ገልጿል።

ከነዚህ ተግባራትም ውስጥ አንደኛው እና ዋነኛው ህገ-ወጥ የመሬት ወረራና ህገ-ወጥ  ግንባታ ሲሆን ይህንኑ በከተማው የሚታየውን ህገ-ወጥ ድርጊት ለማጣራት  እና መረጃ ለማሰባሰብ   በየደረጃው ግብረሃይል በማደራጀት እና ህዝቡን በማሳተፍ ከአንድ ወር በላይ  የማጣራት ስራ ሲሰራ መቆየቱ የሚጠቀስ ነው ብሏል፡፡

ግበረ ሀይሉ ባደረገው ማጣራትም የደረሰባቸው ዋና ዋና  ግኝቶቹን የገለጸ ሲሆን፤ በህገ-ወጥ መንገድ የታጠሩ እና ባለቤትነታቸውን ማረጋገጥ ያልተቻለ ቦታዎችን፣ በህገ-ወጥ መንገድ መገንባት የተጀመሩ ግንባታዎች መኖራቸውን እና ባለቤቶቻቸው ያልታወቁ ቤቶች እና ህንፃዎች መገኘታቸውን  አስታውቋል።

የከተማ አስተዳደሩ በግኝቶቹ ላይ ውሳኔ ወስኖ እርምጃ ከመውሠዱ በፊት የኔ ነው ባይ ካለ አንድ እድል ለመስጠት እንደሚፈልግ ጠቅሶ፤ ህጋዊ ማስረጃ አለኝ የሚል አካልም ሆነ ግለሰብ ከነገ (ጥቅምት 23/02/2013) ጀምሮ ለ3 ተከታታይ ቀናት መረጃም ሆነ ማስረጃ በመያዝ ለዚሁ ጉዳይ በየክፍለ ከተማው በተዋቀረ ግብረሃይል ጋር በመቅረብ እንዲያስረዳ የከተማ አስተዳድሩ አሳስቧል።
በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሶስትዮሽ ድርድር ዛሬ ተካሂዷል። የዛሬውን ውሎ በተመለከተ የውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር መግለጫ አውጥቷል።

የመግለጫው ሙሉ ቃል ከላይ ተያይዟል
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ የሰላማዊ ሰዎችን ሕይወት ባጠፋው ኦነግ ሸኔ ላይ እርምጃ እንደሚወስድ አስታወቀ
****************************
(ኢ ፕ ድ)
በምዕራብ ወለጋ ሰላማዊ ዜጎች ጭካኔ በተሞላበት መንገድ በአንድ ስፍራ ህይወታቸው እንዲያልፍ ባደረገው የኦነግ ሸኔ ቡድን ላይ እርምጃ እንደሚወስድ የኦሮሚያ ክልል መንግስት አስታወቀ።
የክልሉ መንግስት ባወጣው መግለጫ፥ መንግስት የህዝቡን ፍላጎትና ጥያቄ በማገናዘብ የልማት ስራዎችን፣ የሰላም እና የስርዓት ግንባታ ላይ እየሰራ ባለበት በአሁኑ ወቅት፤ ከለውጡ በተቃራኒ የቆሙ ሀይሎች በህዝቡ ላይ አሰቃቂ አደጋ እያደረሱ መሆኑን አስታውቋል።
የጥፋት ሀይሎቹ መንግስት የፖለቲካ እና የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት እየሰራ ባለበት ወቅት በተቃራኒው በመቆም ጭቃኔ የተሞላበት ተግባር በህዝቡ ላይ እየፈፀሙ ነው ብሏል።
የኦነግ ሸኔ ሽፍታ ከህውሃት ጋር በመሻረክ በኦሮሚያ ክልል እና በሀገሪቱ ሰላም እና መረጋጋት እንዳይኖር ሲሰሩ መቆየታቸውን ያስታወሰው መግለጫው፤ በተለያዩ ወቅቶች የግጭት አጀንዳዎችን በማዘጋጀት በሚዲያ በማሰራጨት እንዲሁም በህገ ወጥ መንገድ በገቡ የጦር መሳሪያዎች በፀጥታ ሀይሎች፣ በመንግስት መዋቅር እና በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ የግድያ እርምጃ በመውሰድ ችግሮችን ሲፈጥሩ ቆይተዋል ብሏል መግለጫው።
ጭካኔ በተሞላበት መንገድ በተፈፀሙ በእነዚህ ተግባራትም በህብረተሰቡ ላይ የስነ ልቦና ጫና እንዲፈጠር፣ በስጋት እንዲሞላ እና ከዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ራሱን ቆጥቡ በረሃብ እና በጥማት እንዲጎዳ እያደረጉ ነውም ብሏል።
በተለይም በምዕራብ ኦሮሚያ አቅጣጫ በሚገኙ ዞኖች ህፃናት፣ ሴቶች፣ አዛውንቶች እና ወጣቶችን ጨምሮ ጭካኔ በተሞላበት መንገድ እንዲገደሉ፣ በእሳት እንዲቃጠሉ፣ የአካል ጉዳት እንዲደርስባቸው እንዲሁም የስነ ልቦና ጉዳት እንዲደርስባቸው ማድረጉ ይታወቃልም ብሏል፡፡
ከሁሉም በላይ በጫካ ውስጥ መሽጎ ከቦታ ቦታ የሚዘዋወረው ኦነግ ሸኔ ሰዎችን ጠልፎ በመውሰድ ጉዳት ሲያደርስ መቆየቱ ያወሳው መግለጫው፤ በተለያዩ ጊዜያትም የፀጥታ እና የአስተዳደር አካላት በተመሳሳይ መንገድ ጫካ ውስጥ በአሰቃቂ ሁኔታ ህይወታቸው እንዲያልፍ ሲያደርግ ቆይቷልም ነው ያለው።
የኦነግ ሸኔ ሽፍታ እስካሁን በፈፀማቸው የሽብር ተግባራት በርካታ ቤተሰቦች ተበትነዋል፣ ህፃናትን ያለ አባትና እናት አስቀርቷል ያለው መግለጫው፥ የህዝቡና የግለሰቦች ሀብትም እንዲጠፋ ማድረጉን አስታውሷል።
የኦሮሚያ ክልል መንግስት የህዝቡን ሰላም ለማረጋገጥ ያለውን ተልዕኮ እና ሀላፊነት ለመወጣት ህዝቡን ባሳተፈ መልኩ የህግ የበላይነትን የማስከበር ስራ በስፋት እያከናወነ መሆኑንም ጠቅሷል፡፡
የህወሓት ተላላኪ የሆነው ይህ የኦነግ ሸኔ ቡድን ህዝቡ እና መንግስት በጋራ በመሆን የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እየወሰዱት ባለው እርምጃ ለመጥፋት መቃረቡንም መግለጫው አመላክቷል።
እየተወሰደ ባለው እርምጃ የመቃብር አፋፍ ላይ የደረሰው ይህ ቡድን ተስፋ በመቁረጡ በአንድ ስፍራ በሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ጥቃት እያደረሰ መሆኑም ተገልጿል።
በትናትናው እለትም በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ጋዋ ቀናቲ ቀበሌ ጨለማን ተገን በማድረግ በፈፀመው የሽብር ጥቃት ሰላማዊ ዜጎችን ጭካኔ በተሞላበት መንገድ በአንድ ስፍራ ህይወታቸው እንዲያልፍ ማድረጉንም ነው የገለጸው።
የኦሮሚያ ክልል መንግስት ከህዝቡ እንዲሁም የፀጥታ እና አስተዳደር አካላት ጋር በመሆን እነዚህ ሽፍታዎች የገቡበት ቦታ በመግባት አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድም ገልጿል።
በተፈፀመው ጥቃት ለተሰው ወገኖች የተሰማውን ሀዘን የገለፀው የክልሉ መንግስት ለቤተሰቦቻቸው መጽናናትን ተመኝቷል።
በቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የፌደራል ፖሊስ ገለጸ
************************************
(ኢ.ፕ.ድ)

በአዲስ አበባ ከተማ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማና በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ፣ በቴሌኮም ማጭበርበር የተጠረጠሩ በርካታ ግለሰቦች ከነመሳሪያዎቻቸው በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ አስታወቀ፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ህጋዊ ፈቃድ ሳይኖራቸው የቴሌኮም መሳሪያዎችን ወደ ሀገር በማስገባትና ከውጭ ሀገር ወደ ኢትዮጵያ የሚደረጉ የስልክ ጥሪዎች ኢትዮ ቴሌኮም በዘረጋው ኔትወርክ ሳይሆን ራሳቸው በዘረጉት መስመሮች ለደንበኞች ሲያቀርቡ መቆየታቸውን በፋይናንስ ተቋማት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ምርመራ ዲቪዥን ኃላፊ ኢንስፔክተር ሳሙኤል ሰለሞን ገልፀዋል።

ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ መሰረት የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ ከኢንሳ፣ ከኢትዮ ቴሌኮም፣ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንና ከሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ባደረገው ክትትል ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ኢንስፔክተር ሳሙኤል ተናግረዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ለዚህ ህገ-ወጥ ተግባር ሲጠቀሙባቸው የነበሩ 6 ጌትወይ፣ ከ570 በላይ ሲም ካርዶች፣ ቲፕሊንኮችና ሌሎች ህገ-ወጥ የቴሌኮሙኒኬሽን መሳሪያዎች መያዛቸውም ተገልጿል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በሁለቱ ክፍለ ከተሞች ከቴሌኮም እውቅና ውጭ ማሽኖቹን በመጠቀምና የራሳቸውን ኔትወርክ በመፍጠር የውጭ ሀገር ጥሪዎችን በማስተላለፍ በቴሌኮም ላይ ኪሳራ ሲያደርሱ መቆየታቸንውን ኢንስፔክተር ሳሙኤል ሰለሞን በመግለፅ ህብረተሰቡ ለፖሊስ ባደረሰው ጥቆማ መሰረት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጠቁመዋል፡፡

የወንጀል ምርመራ ቢሮው ከፍርድ ቤት የብርበራ ትዕዛዝ በማውጣት ማሽኖቹን ከነ አክሰሰሪዎቹ በመያዝ በኢትዮ ቴሌኮም መሰረተ ልማት ላይ ተጠርጣሪዎቹ ያደረሱትን ኪሳራ ለማጣራት መሳሪያዎቹን ለብሔራዊ መረጃና ደህንነት ልኮ የምርመራ ውጤቱን እየተጠባበቀ ይገኛልም ብለዋል፡፡

ህብረተሰቡ ቤቱን ከማከራየቱ በፊት ስለ ተከራዮች ማንነት በቂ መረጃ በመያዝ በትክክል ማጣራት እንዳለበትና እንደዚህ አይነት ህግ-ወጥ ተግባራት ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችን ሲመለከት በአካባቢው ለሚገኙ የፀጥታ አካላት ጥቆማ በመስጠት የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግም ኢንስፔክተር ሳሙኤል ሰለሞን ጥሪ አቅርበዋል፡፡
"በኢትዮጵያውያን ላይ እየተፈጸመ ባለው ማንነትን መሠረት ባደረገው ጥቃት እጅግ ማዘኔን እገልጣለሁ"
- ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር)
*********************
(ኢ ፕ ድ)
የኢትዮጵያ ጠላቶች፤ "ወይ እኛ እንገዛለን፤ ወይ ሀገር አትኖርም" ብለው ተነሥተዋል። ለዚህም የጥፋት ዐቅማቸውን ሁሉ እየተጠቀሙ ነው። አንደኛው ዒላማቸውም የሕዝባችንን ቅስም መስበር ነው።
ለዚህ እየተጠቀሙበት ያለው ስልት ግራ ቀኝ የሜያውቁ ሰዎችን እየሰበሰቡ በማሠልጠንና በማስታጠቅ በየአካባቢው ማንነትን መሠረት ያደረገ አረመኔያዊ ጥቃት ማድረስ ነው። ይህ ተግባር ሕዝቡ እንዲደናገጥ፣ እንዲፈራና በስሜት ያልተገባ ርምጃ እንዲወስድ የታለመ ነው።
መንግሥት በተለያዩ ቦታዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ ያላቸውን ጥፋቶች በቅድሚያ መረጃ ሰብስቦ ርምጃ በመውሰድ ሲያከሽፍ ቆይቷል። ነገር ግን ያለፈው ሥርዓት ያወረሰንን ቀዳዳዎች ሁሉ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ደፍኖ መጨረስ አልተቻለም።
የጥፋት ኃይሎች ከውጭ ላኪዎቻቸውና በመንግሥት መዋቅር ውስጥ በሚገኙ ባልጠሩ አድር ባዮች ትብብር በሕዝባችን ላይ አሳዛኝ ጥቃት እያደረሱ ነው። ሁኔታው እንደ መሪም እንደ ዜጋም ልብ ይሰብራል።
ይህ ግን ከመንገዳችን ወደኋላ፣ ከግባችን ወደ ሌላ አያደርገንም። ተስፋ ቆርጠን እንድናቆም፣ ተሸንፈን እንድናፈገፍግ አያደርገንም። ከምንጊዜውም በላይ ኃይላችንን አሰባስበን እንድንነሣ ያደርገናል እንጂ።
መንግሥት ሁሉንም ዓይነት አማራጮች ተጠቅሞ የችግሩን ሰንኮፍ ይነቅለዋል። የጸጥታ አካላት ጥቃቱ ወደተፈጸመበት አካባቢ ተሠማርተዋል። ርምጃም እየወሰዱ ነው። በቀጣይም የሕዝባችንን ደኅንነት ለማስጠበቅ መንግሥት የመንግሥትነቱን ሥራ በቁርጥና በጽናት ይሠራል።
ሕዝቡ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የጸጥታ አካላት።፣ ምሁራንና ሌሎችም፧ መንግሥት ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ የሚወስደውን ርምጃ በመደገፍ የሚጠበቅባቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ አቀርባለሁ።
የኢፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ በንፁኃን ዜጎች ላይ የተፈፀመውን አሰቃቂ ጭፍጨፋ በማስመልከት መልዕክት አስተላልፈዋል።
***************
(ኢ.ፕ.ድ)

የተከበራችሁ የሃገራችን ህዝቦች!

በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ በንፁኃን ዜጎች ላይ የተፈፀመው አሰቃቂ ጭፍጨፋ የተሰማኝን ሃዘን እየገለፅኩ፤ ለሟች ቤተሰቦች መፅናናትን እመኛለሁ፡፡

በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ቀደም ሲል ብሄርን፣ ሃይማኖትን እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት የማድረስ ዓላማ ያላቸው ጥቃቶችና ጭፍጨፋዎች ተካሂደዋል፡፡ በተመሳሳይ በምዕራብ ወለጋ ዞን በንፁኃን ዜጎች ላይ አሰቃቂ ጭፍጨፋ ተፈፅሟል፡፡

በተለይ የአማራን ማህበረሰብ ትኩረት ያደረገና በንፁኃን ዜጎች ላይ የሚካሄደው ጭፍጨፋ ፍፁም አረመኔያዊና በፍጥነት መቆም ያለበት እኩይ ድርጊት ነው፡፡ ድርጊቱ አስቀድሞ መዋቅራዊ በሆነ መልኩ ሲዘራ የቆየ በመሆኑ፤ ችግሩን የሚመጥን መፍትሄ በዘላቂነት ለማበጀት አስፈላጊው ሁሉ ይደረጋል፡፡

ከዚህ አኳያ የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ እንዲሁም ከሁሉም አቅጣጫ የሚቃጡ ጥቃቶችን ለመመከት የመንግስትና ህዝብ ቅንጅታዊ ርብርብ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
የምክር ቤቱ አባላት በምዕራብ ወለጋ ዞን ከተፈጸመው ግድያ ጀርባ አሉ የተባሉት እንደ ህወሓት ያሉ ድርጅቶች በአሸባሪነት ሊፈረጁ ይገባል ሲሉ ጠየቁ

👉 ጉዳዩን በተመለከተ የሚመለከተው የመንግስት አካል ማብራሪያ እንዲሰጥበት እንደሚደረግ አፈጉበኤው አስታውቀዋል
******************
(ኢ ፕ ድ)

የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባላት በምዕራብ ወለጋ ዞን በንጹሀን ዜጎች ላይ ማንነትን መሰረት አድርጎ በተፈጸመው ግድያ ላይ እጃቸው አለበት የተባሉት እንደ ህወሓት እና ሸኔ ያሉ ድርጅቶች በአሸባሪነት ሊፈረጁ ይገባል ሲሉ ጠየቁ።

ዛሬ ለመደበኛ ስብሰባ የተጠራው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከመደበኛ አጀንዳዎች አስቀድሞ በንጹሀን ዜጎች ግድያ ላይ መወያያት አለብን በሚል በጥቃቱ ዙሪያ ሰፊ ውይይት አድርጓል።

በዚሁ ውይይት ላይ የምክር ቤቱ አባላት እንደተናገሩት፤ በምዕራብ ወለጋ ዞን በንጹሀን ዜጎች ላይ ማንነትን መሰረት አድርጎ በተፈጸመው ግድያ ላይ እጃቸው አለበት የተባሉት እንደ ህወሓት እና ኦነግ ሸኔ ያሉ ድርጅቶች በአሸባሪነት ሊፈረጁ ይገባል ብለዋል።

የትናንት በስቲያውን ጨምሮ ባለፉት ሁለት አመታት ማንነት ላይ የተመሰረቱ ግድያዎችን የፈጸሙ፣ የመለመሉ ድጋፍ ያደረጉ እንደ ህወሓት ያሉ አካላትን በተመለከተ መረጃና ማስረጃ አደራጅቶ በሽብርተኝነት ሊፈረጁ ይገባል ያሉት አባላቱ፤ የሚመለከተው የመንግስት አካል ይሄንን መረጃ አደራጅቶ ለምክር ቤቱ እንዲያቀርብም ነው የጠየቁት።

አባላቱ በዚሁ ውይይታቸውም በግድያው ዙሪያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የሰላም ሚኒስቴር እና የመከላከያ የስራ ሃላፊዎች በጉዳዩ ላይ ምክር ቤት ቀርበው ማብራሪያ ሊሰጡ ይገባል ሲሉ አንስተዋል።

አፈጉበኤው በምላሻቸው የምክር ቤቱ አባላት በግድያው ዙሪያ ስሜታቸውን በዚህ አግባብ መግለጻቸው ትክክል መሆኑን በመጥቀስ፤ ጉዳዩን በተመለከተ የሚመለከተው የመንግስት አካል ማብራሪያ እንዲሰጥበት እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

በጌትነት ተስፋማርያም
“ለሀገርና ለህዝብ ጥቅም ሲባል ልናሰምረው እና ልናከብረው የሚገባን ቀይ መስመር ተጥሷል”
- የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ሳህለ-ወርቅ ዘውዴ
*********************
(ኢ ፕ ድ)
የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ሳህለ-ወርቅ ዘውዴ በምዕራብ ወለጋ ዞን በንጹሀን ዜጎች ላይ የተፈጸመውን ግድያ በማስመልከት ያስተላለፉት መልዕክት።
የሰማሁት አሰቃቂ ግድያ ልቤን በእጅጉ ሰብሮታል:: ንጹሀን ዜጎች በሌሎች እብደት ውድ ሕይወታቸውን የሚከፍሉበት ንብረታቸው የሚወድምበት መሄጃ አጥተው የሚንከራተቱበት ምንም ምክንያት የለም:: የዛሬ ዓመት በ 30/10/2019 የጻፍኩትን ትዊት ልድገመው::
ዘርና ሀይማኖት ለፖለቲካ ጥቅም እንዲውሉ ሲደረግ፤ ንጹሀን ዜጎቻችን በአሰቃቂ ሁኔታ ሲገደሉ፣ ሲፈናቀሉና ሲንከራተቱ ስናይ ስሜትን ለመግለጽ ቃላት ያጥራል: ለቅሶ፣ድንጋጤና ሥጋት የብዙዎችን በር አንኳኩቷል ሃዘናቸው ሃዘኔ/ሃዘናችን ነው::
ለሀገርና ለህዝብ ጥቅም ሲባል ልናሰምረው እና ልናከብረው የሚገባን ቀይ መስመር ተጥሷል፡ አገራችንን ካንዣበበባት ክፉ አዳጋ ለማዳን ሁላችንም ሚና አለን፡የሚመለከታቸው ሁሉ የበኩላቸውን መወጣት አለባቸው፡ቀይ መስመር መጣስ የለበትም እንበል::
የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ