ERA ኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር
13.8K subscribers
3.69K photos
43 videos
45 files
539 links
Official ERA Telegram Channal
በዚህ የቴሌግራም ቻናል
የመንገድ ዜናዎችን
የስራና የመንገድ ጨረታ ማስታወቂያዎችን
የመንገድ ፎቶዎች እና አጫጭር ቪዲዮችን ያገኛሉ።
Download Telegram
የጎንጂ-ቆለላ አስፋልት መንገድ ፕሮጀክት 98.82 በመቶ አፈጻጸም ላይ ደረሰ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 25 ቀን 2018 ዓ.ም (ኢመአ)፤ በጎንጂ ቆለላ ወረዳ የሚገነባው የቆሬ - አዲስ ዓለም የአስፋልት መንገድ ፕሮጀክት በአሁኑ ወቅት የ10.59 ኪሎ ሜትር ግንባታን በማጠናቀቅ 98.82 በመቶ አጠቃላይ አፈጻጸም ላይ ደርሷል። ከባህር ዳር ወደ ሞጣ በሚወስደው መንገድ ላይ ከምትገኘው ቆሬ ቀበሌ ተነስቶ ምስራቅ አቅጣጫ በመጓዝ ሂዳሴ መንደርን አቋርጦ አዲስ ዓለም ከተማ የሚገባው ይህ ፕሮጀክት፣ በአጠቃላይ 10.74 ኪሎ ሜትር ርዝመት አለው። ቀድሞ የነበረውን የጠጠር መንገድ ወደ አስፋልት ደረጃ የሚያሳድገው ይህ ግንባታ፣ የመንገዱ ስፋት በገጠር 10 ሜትር፣ በቀበሌ 12 ሜትር እንዲሁም በወረዳ 21.5 ሜትር ሆኖ እየተገነባ ይገኛል።
 
ግንባታው ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ሲሆን በአካባቢው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ አዲስ ተስፋ ይዞ ይመጣል። በተለይም አርሶ አደሩ በአካባቢው በስፋት የሚያመርታቸውን እንደ ጤፍ፣ ሰሊጥ፣ በርበሬና ማሽላ ያሉ የግብርና ምርቶችን ያለምንም እንግልት በወቅቱ ወደ ገበያ ለማቅረብና የቱሪዝም መዳረሻዎችን በቀላሉ ለማገናኘት ጉልህ ሚና ይኖረዋል። ከዚህም በላይ ነዋሪዎች ቀድሞ ለመጓጓዝ ይወስድባቸው የነበረውን የጉዞ ጊዜ በአንድ ሰዓት ያህል በማሳጠር የዕለት ተዕለት ህይወታቸውን ያቀልላቸዋል።
 
ይህ ታላቅ ተስፋ የተሰነቀበት ፕሮጀክት ግንባታው እስከአሁን ድረስ ያጋጠሙና በሥራው ፍጥነት ላይ ጫና ያሳደሩ እንደ የጸጥታ፣ እና የወሰን ማስከበር ችግሮች እንዲሁም የነዳጅ እጥረት ተግዳሮቶችን ቀርፎ አሁን ያለበት ደረጃ ደርሷል። ሥራው እንዳይቋረጥ ከተለያዩ የመንግስት አካላት ጋር በቅንጅት በመሥራት፣ ለግንባታው የሚሆን ነዳጅ በቅድሚያ እንዲያገኝ በማድረግና ከፍተኛ ክትትል በማድረግ የተከለሰው የፕሮጀክቱ ማጠናቀቂያ ቀን በጥቅምት ወር 2019 ዓ.ም እንዲሆን ተደርጓል።
 
የበጀት ፍሰቱን በተመለከተ ቫትን ጨምሮ ከ333 ሚሊዮን ብር በላይ የተመደበለት ሲሆን፣ የስራ ተቋራጭነቱን ኅብር ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ሲያከናውነው የሃይዌይ ኢንጂነርስ ኤንድ ኮንሰልታንትስ ኃ/ተ/ግ/ማ ደግሞ የአማካሪነት ሚናውን እየተወጣ ይገኛል። ተቋራጩ አፈጻጸሙን እንዲያሻሽልና ቀሪ ሥራዎችን በተያዘው የበጀት ዓመት እንዲያጠናቅቅም በየደረጃው ከፍተኛ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገለት ነው።
 
በአሁኑ ወቅት የጠረጋ፣ የአፈር ቆረጣና ሙላት፣ የሰብ ቤዝ፣ የቤዝ ኮርስ ንጣፍ እንዲሁም ሙሉ የ10.74 ኪሎ ሜትር የአስፋልት ንጣፍ ሥራዎች 100 በመቶ ሙሉ በሙሉ ተጠናቀዋል። በተጨማሪም የፍሳሽ ማስወገጃ (ድሬኔጅ) ሥራው 98.58 በመቶ ላይ የደረሰ ሲሆን፤ እንደ እግረኛ መንገድና የመንገድ ምልክቶች ያሉ ቀሪ ሥራዎችንም 50 በመቶ በማድረስ ፕሮጀክቱን ሙሉ በሙሉ ወደ ማጠናቀቂያው ምዕራፍ ለማሸጋገር የመጨረሻ ደረጃ ሥራዎች በከፍተኛ ፍጥነት እየተከናወኑ ይገኛሉ።

በተጨማሪ
› አጭር መልዕክት 8561
› ፖስታ ሳጥን ቁጥር 1770
› ድህረገጽ www.era.gov.et
› ፊስቡክ https://www.facebook.com/www.era.gov.et
› ቴሌግራም https://t.me/ethioroads
› ትዊተር https://twitter.com/EthiopiaRoadsAd
› ኢንስታግራም https://www.instagram.com/ethioroads
› ኢሜል communication@era.gov.et
› ዩቲዮብ www.youtube.com/@ethioroads
3👍2
በ2018 በጀት ዓመት የ580 ኪሎ ሜትር አዳዲስ መንገዶች ግንባታ መከናወኑ ተገለጠ
 
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 26 ቀን 2018 ዓ.ም (ኢመአ)፦ በ2018 በጀት ዓመት የ580 ኪሎ ሜትር አዳዲስ መንገዶች ግንባታ እና 12 ሺህ 882 ኪሎ ሜትር የሚሸፍኑ የተለያዩ የመንገድ ጥገና ሥራዎች መከናወናቸው ተገለጸ። ተቋሙ የ2018 በጀት ዓመት አጠቃላይ አፈጻጸም እና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድን አስመልክቶ በዓለምገና ኢንጅነሪንግ እና ማኔጅመንት ማሠልጠኛ ማዕከል ከአመራሮችና ከሠራተኞች ጋር አጠቃላይ ዓመታዊ የውይይት መድረክ አካሂዷል።
 
በተቋሙ ፕላንግና ፕሮግራም ዳይሬክቶሬት በቀረበው ሪፖርት መሠረት፤ በበጀት ዓመቱ የ238 ኪሎ ሜትር የነባር መንገዶች ደረጃ ማሻሻል እንዲሁም የ16 ኪሎ ሜትር የነባር መንገዶች ማጠናከር ሥራዎች በስኬት ተከናውነዋል። ተቋሙ በበጀት ዓመቱ የምህንድስና ግዢ፣ የዲዛይን ፕሮጀክቶች እንዲሁም የተቋማዊ አቅም ግንባታ ተግባራትን ማከናወኑ ተገልጿል።
 
በተጨማሪም በበጀት ዓመቱ 24 የመንገድ ፕሮጀክቶች ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት የሆኑ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል የኢተያ - አርሲ ሮቤ፣ የእስቴ - ስማዳ፣ የድሬዳዋ ባይፓስና ሽንሌ፣ የጅግጅጋ ከተማ ማለፊያ (ባይፓስ) መንገድ እንዲሁም የሳውላ - ቃቆ መንገድ ፕሮጀክቶች በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው። ተቋሙ በተያዘው አዲስ በጀት ዓመት ከ1 ሺህ 67 ኪሎ ሜትር በላይ አዳዲስ መንገዶችን ለመገንባት እና ከ16 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍኑ የተለያዩ መንገዶችን ለመጠገን አቅዶ ወደ ተግባር መግባቱ ተመላክቷል።
 
የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር መሐመድ አብዱራህማን (ኢንጅነር) በወቅቱ ባስተላለፉት መልእክት፤ የ2018 በጀት ዓመት ተቋሙ የተመሠረተበትን 75ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ በዓል በደማቅ ሥነ-ሥርዓት ያከበረበት ልዩ የታሪክ ምዕራፍ መሆኑን አስታውሰዋል። ተቋሙ ባለፉት 75 ዓመታት ሰፊ የመንገድ መሠረተ-ልማት አውታሮችን በመዘርጋት ኢትዮጵያን እርስ በርስ ማስተሳሰር የቻለና ለአገሪቱ ሁለንተናዊ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የማይተካ የበኩሉን አስተዋጽኦ ያበረከተ መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
 
ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም፣ በ2019 በጀት ዓመት በመንገድ ዘርፉ የተጣሉትን አገራዊ ግቦች በውጤታማነት ለማሳካት የተጀመረው ተቋማዊ ሪፎርም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር የአሠራር ሽግግሮችንና የዲጂታላይዜሽን በአግባቡ ከመተግበር ጎን ለጎን የሥራ ባህልንና የበጀት አጠቃቀምን በተጠያቂነትና በግልጽነት መንፈስ መምራት እንደሚገባ በጥብቅ አሳስበዋል፡፡

በተጨማሪ
› አጭር መልዕክት 8561
› ፖስታ ሳጥን ቁጥር 1770
› ድህረገጽ www.era.gov.et
› ፊስቡክ https://www.facebook.com/www.era.gov.et
› ቴሌግራም https://t.me/ethioroads
› ትዊተር https://twitter.com/EthiopiaRoadsAd
› ኢንስታግራም https://www.instagram.com/ethioroads
› ኢሜል communication@era.gov.et
› ዩቲዮብ www.youtube.com/@ethioroads
12👍2
የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ከክልልና የከተማ መስተዳድር ኤጀንሲዎች ጋር ዓመታዊ የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እያካሄደ ነው

ቢሾፍቱ ፣ ነሐሴ 29 ቀን 2018 ዓ.ም. (ኢመአ)— የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በመንገድ ፈንድ የጥገና በጀት ድጋፍ ከሚደረግላቸው የሁሉም ክልሎች እና የዋና ከተማ መስተዳድሮች የመንገድ ኤጀንሲዎች የሥራ ኃላፊዎች ጋር የሚያካሂደው ዓመታዊ የዕቅድ አፈጻጸም የውይይት መድረክ በቢሾፍቱ ከተማ እየተተካሄደ ነው።

የውይይት መድረኩን በንግግር የከፈቱት የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር መሀመድ አብዱራህማን እንደገለጹት፤ የመድረኩ ዋና ዓላማ የሥራ አፈጻጸሞችን በበጎ ጎን ማየት ብቻ ሳይሆን በሥራ ሂደት ውስጥ ያጋጠሙ የአሠራር ክፍተቶችን በግልጽ በመወያየት ቀጣይ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ ነው። በመድረኩ ያለፈው የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም በዝርዝር የሚገመገም ሲሆን፣ አዳዲስ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ውይይት ይደረግበታል።

ዋና ዳይሬክተሩ የመንገድ ግንባታና ልማት በአገሪቱ ከፍተኛ ትኩረት ከተሰጣቸው የመሠረተ ልማት ዘርፎች ቀዳሚው እና የልማት ጉዞውን ለማፋጠን የሚያገለግል ቁልፍ ምሰሶ መሆኑን ገልጸዋል። በመንግሥት ልዩ ትኩረት ምክንያት ዛሬ ላይ ደረጃቸውን የጠበቁ የመንገድ መዋቅሮች በከፍተኛ ሁኔታ መስፋፋታቸውንና አሁንም በስፋት እየተገነቡ መሆናቸውን አብራርተዋል። መንገድ የተራራቁ ሕዝቦችን በማገናኘት፣ ለአርሶ አደሮች ምርት ገበያ፣ ለትምህርትና ለጤና ተደራሽነት፣ ለኢንቨስትመንት እንዲሁም ለቱሪዝም ዕድገት ትልቅ ሚና እንደሚጫወትም አክለዋል።

ይሁን እንጂ የተገነቡ መንገዶች በዲዛይናቸው መሠረት የረጅም ዘመን አገልግሎት እንዲሰጡ ወቅታዊ ጥገና ሊደረግላቸው እንደሚገባ ኢንጂነር መሀመድ አሳስበዋል። መሠረተ ልማቱ ለብልሽት ከተጋለጠ ለተሽከርካሪ መለዋወጫ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ በማናር በሀገር ሀብት ላይ ከፍተኛ ጫና ስለሚፈጥር፣ ቀጣይነት ያለው የጥገና ሥራና ቋሚ የፋይናንስ ድጋፍ ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ይህን የፋይናንስ ፍላጎት በዘላቂነት ለመመለስ መንገድ ፈንድ ከ28 ዓመታት በፊት ራሱን ችሎ መቋቋሙን ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ተቋሙ ከነዳጅ፣ ከቅባትና ዘይት ታሪፎች፣ የሀገሪቱን ድንበር አቋርጠው ከሚገቡ ተሽከርካሪዎች ክፍያ፣ ከፈቃድ ማደሻና ከክብደት ወሰን በላይ ጭነት ቅጣት ገቢዎችን በመሰብሰብ ዓላማውን በስኬት እያሳካ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ከ2014 በጀት ዓመት ጀምሮ መንገድ ፈንድ በአዋጅ በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ሥር መደራጀቱ ደግሞ ለሥራ ቅልጥፍና ትልቅ ዕድል መፍጠሩ ተብራርቷል።

በ2019 በጀት ዓመት ከመንገድ ፈንድ የገቢ ምንጮች የሚሰበሰበውን ገቢ በመገመት ለፌደራል፣ ለክልል እና ለከተማ መንገድ ኤጀንሲዎች ለመደበኛና ለወቅታዊ ጥገና፣ ለከባድ (መልሶ) ጥገና፣ ለመንገድ ደኅንነት እንዲሁም የኤጀንሲዎችን አቅም ለመገንባት የሚያስፈልጉ መሣሪያዎች ግዢ የሚውል በጀት መደልደሉም በዚሁ መድረክ ተገልጿል።


በተጨማሪ
› አጭር መልዕክት 8561
› ፖስታ ሳጥን ቁጥር 1770
› ድህረገጽ www.era.gov.et
› ፊስቡክ https://www.facebook.com/www.era.gov.et
› ቴሌግራም https://t.me/ethioroads
› ትዊተር https://twitter.com/EthiopiaRoadsAd
› ኢንስታግራም https://www.instagram.com/ethioroads
› ኢሜል communication@era.gov.et
› ዩቲዮብ www.youtube.com/@ethioroads
8👍2