Ethiopia Election
41 subscribers
34 photos
2 videos
26 links
የኢትዮጵያ ኢንሳይደር የምርጫ ዘገባዎች - #ምርጫ2018 | Ethiopia Insider's dedicated platform for election coverage
Download Telegram
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ከመጪው ምርጫ ጋር በተያያዘ በዋትስአፕ መተግበሪያ ላይ እየተፈጸሙ ያሉ የተቀናጁ የጠለፋ ጥቃቶች አሉ በማለት የጥንቃቄ መልዕክት አስተላለፈ

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በተለይም 7ተኛውን ሀገራዊ የምርጫ ሂደትን ተገን በማድረግ፣ ዋትስአፕ ተጠቃሚዎችን ኢላማ ያደረጉ ጠላፊዎች ሰፊ የሳይበር ጥቃት እየፈጸሙ እንደሚገኙ አስተዳደሩ በሚደርሱት መረጃዎችና የሳይበር ደህንነት ትንተናዎች ማረጋገጥ መቻሉን ገልጿል፡፡

ይህ ጥቃት በተለይ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችን፣ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ተማሪዎችን፣ በርቀት ሆነዉ በዲጂታል አማራጮች የሚማሩ ግለሰቦችን እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን ዒላማ ያደረገ በመሆኑ፣ መላው የዋትሳፕ ተጠቃሚ ማህበረሰብ የጥቃት ስልቶችና የመከላከያ መንገዶች በማወቅ እንዲጠነቀቅ ጥሪ አቅርቧል፡፡

የባለ 6-አሃዝ ኮድ ለዋትስአፕ ተጠቃሚዎች በመላክ የምርጫ ደጋፊ በመምሰል፣ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ደጋፊ በሚመስል መልኩ የፓርቲዎችን አርማ (Logo) በመጠቀም፣ የምርጫ መረጃ አቅራቢ በመምሰል፣

▶️ ‎"ለፓርቲያችን ድጋፍዎን እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን ይግለጹ" ፣

▶️‎"የምርጫ ቅስቀሳ ቡድናችንን ይቀላቀሉ" ፣

▶️‎ "የምርጫ ጣቢያዎትን ለማወቅ"፣

▶️ ‎"የዕጩዎችን ዝርዝር ለማየት" ወይም

▶️‎ "የምርጫ ውጤቶችን በቅድሚያ ለማግኘት" የሚሉ አሳሳች ማስፈንጠሪያዎችን (Links) በመጠቀም የተጠቃሚዎችን የዋትስአፕ አካውንት በቁጥጥራቸው ስር እያዋሉ እንደሚገኙም አስተዳደሩ ገልጿል።

#ምርጫ2018 #EthiopiaElection
😁1
የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) በመጪው ሀገራዊ ምርጫ ራሱን እንደ "ዕጩ መንግሥት" አድርጎ እንደሚቆጥር የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ነቢሃ መሐመድ ገለጹ። ፓርቲው ለፌደራልና ለክልል ምክር ቤቶች ወደ 1,500 የሚጠጉ ዕጩዎችን ማስመዝገቡንና ዝርዝር የምርጫ ስትራቴጂ ማዘጋጀቱንም አስታውቀዋል። የምርጫ ስትራቴጂው ፓርቲው በምርጫው ውጤታማ ለመሆን የሚከተለውን አጠቃላይ ፍኖተ ካርታ እንደያዘም ገልጸዋል።


ነእፓ ለዘብተኛ ሊበራሊዝም ርዕዮተ ዓለምን የሚከተል ሲሆን፣ ከሌሎች ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ጥምረት ለመፍጠር ጥናት እያካሄደ መሆኑን የፓርቲው ሊቀመንበር ዶ/ር አብዱልቃድር አደም በቅርቡ አስታውቀዋል።

🔴ዝርዝር ዘገባውን ለማንበብ ➡️ https://ethioelections.com/ነእፓ-ራሱን-ዕጩ-መንግሥት-አድርጎ-እን/
#ምርጫ2018 #EthiopiaElection
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፊታችን ቅዳሜ የካቲት 28፣ 2018 ዓ.ም የሚጀመረውን የመራጮች ምዝገባን ለማካሄድ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታወቀ።

ቦርዱ ትላንት የካቲት 25 ቀን 2018 ዓ.ም. በምርጫ ሂደት የዜጎችን ተሣትፎን ለማበረታታት “ምርጫችን ነው -ሀገር ያለኛ” የተሰኘ አዲስ የምርጫ ኅብረ ዝማሬን በይፋ ባስመረቀበት ሥነ ስርዓት ወቅት የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ መራጮች ባሉበት ቦታ ሆነው "ምርጫዬ" በተሰኘውን የሞባይል መተግበሪያ መመዝገብ እንደሚችሉ አስታውቀዋል።

በተጨማሪም በምርጫ ጣቢያ በመገኘት በዲጂታል እንዲሁም ከዚህ በፊት በተለመደው መልኩ መመዝገብ እንደሚችሉም ገልጸዋል። ቦርዱ ከዚህ በፊት ይፋ ባደረገው የመራጮች ምዝገባ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ምዝገባው እስከ መጋቢት 28 ቀን 2018 የሚቀጥል ይሆናል።

#ምርጫ2018 #EthiopiaElection
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ7ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ የመራጮች ምዝገባን ከየካቲት 28 ቀን ጀምሮ እንደሚካሄድ ቢያስታውቅም፣ በሀገሪቱ በተለይም በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል፣ እንዲሁም በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎች ያለው የጸጥታ ችግር የምርጫው ሂደት ላይ ጥላ አጥልቷል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደሚጠቁሙት በአንዳንድ አካባቢዎች ያለው የጸጥታ ሁኔታ አካታች እና ፍትሃዊ ምርጫን ለማካሄድ እንቅፋት ሆኗል። ቦርዱ ከክልል መስተዳደሮችና ጸጥታ ኃይሎች ባገኘው መረጃ መሰረት በምርጫ ክልሎች ያለውን የጸጥታ ሁኔታን በአረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ በመመደብ ምርጫው ሊካሄድ የሚቻልባቸውን እና የማይቻልባቸውን ለይቷል። ሆኖም መረጃውም ሆነ ምደባው እስከ ምርጫው ቀን ድረስ ተቀያያሪ ሊሆን ስለሚችል ሙሉ ለሙሉ ይፋ ከማድረግ ተቆጥቧል።
🔴ዝርዝር ትንታኔውን ለማንበብ ➡️ https://ethioelections.com/7ኛው-ጠቅላላ-ሀገራዊ-ምርጫ-ላይ-ጥላ-ያጠላው/

#ምርጫ2018 #EthiopiaElection
👍2
የ7ተኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ነገ የካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም ይጀምራል። ምዝገባው በአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ መስተዳደሮች እንዲሁም በሐረሪ ክልል ሙሉ በሙሉ በዲጂታል የሚከናወን ሲሆን በአፋር ክልል ደግሞ ከዚህ በፊት በተለመደው በእጅ ወይም በማኑዋል የሚከናወን ይሆናል። በተቀሩት ክልሎች የመራጮች ምዝገባው በዲጂታል እና በማኑዋል አማራጮች ይካሄዳል።

የዲጂታል ምዝገባው በሁለት አይነት አማራጭ የሚከናወን እንደሆነ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል። አንደኛው “ምርጫዬ” የተሰኘውን የሞባይል መተግበሪያ በመጠቀም መራጮች በራሳቸው ምዝገባውን የሚያከናውኑበት ነው ሲሆን ሁለተኛው አማራጭ መራጮች አቅራቢያቸው በሚገኙ ምርጫ ጣቢያዎች በመገኘት በምርጫ አስፈጻሚዎች እገዛ በታብሌት የሚያከናወን ነው።

ምርጫ ቦርድ ባወጣው የግዜ ሰሌዳ መሰረት የመራጮች ምዝገባ እስከ መጋቢት 28 ቀን 2018 ዓ.ም የሚቆይ ይሆናል።

#ምርጫ2018 #EthiopiaElection
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ7ተኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ የተመዘገቡ የዕጩዎች ቁጥር 10 ሺህ 934 እነደሆነ አሳውቋል። ቦርዱ ይህንን የዕጩዎች ቁጥር የመዘገበዉ ከ47 የፖለቲካ ፖርቲዎች እና 73 የግል ተወዳዳሪዎች መሆኑንም አሳውቋል።

ከዚህ ውስጥ 2 ሺህ 198 ዕጩዎች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወዳደሩ ሲሆኑ የተቀሩት 8 ሺህ 736 ደግሞ ለክልል ምክር ቤቶች የሚፎካከሩ ይሆናሉ። ዕጩዎቹ በፆታም የተገለፁ ሲሆን በዚህ መሠረት 2ሺህ 760 ሴቶች ሲሆኑ 8ሺህ 174 የሚሆኑት ደግሞ ወንዶች ናቸዉ።

#ምርጫ2018 #EthiopiaElection
Media is too big
VIEW IN TELEGRAM
የ7ተኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ትላንት የካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም ተጀምሯል። መራጮች “ምርጫዬ” በተሰኘው መተግበሪያ ለመመዝገብ የሚከተሉትን ሂደቶች መከተል አለባቸው፦
1. “ምርጫዬ” የተሰኘውን መተግበሪያ ከፕሌይ ስቶር ወይም አፕ ስቶር በማውረድ ተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸው ላይ መጫን
2. መተግበሪያውን በመክፈት ለ7ተኛው ጠቅላላ ምርጫ ይመዝገቡ የሚለውን መጫን
3. የመራጭ መታወቂያቸውን ለማግኘት የፋይዳ መታወቂያ መለያቸውን በመጠቀም መግባት
4. በተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸው በጸሑፍ መልዕክት የሚደርሳቸውን የፋይዳ ኮድ ወይም OTP በማስገባት የፋይዳ መረጃዎች ጥቅም ላይ እንዲውሉ መፍቀድ
5. የአካል ጉዳት ሁኔታን መምረጥ
6. የግል መረጃን (ሙለ ስም ከነአያት፣ የመኖርያ አድራሻና የመሳሰሉትን) መሙላት
7. በአካባቢው ካሉ የምርጫ ጣቢያዎች ዝርዝር በመምረጥ መመዝገብ
8. በመጨተሻም በአካባቢው በነዋሪነት ያሳለፉትን ግዜ ርዝማኔ በመሙላትና የመታውቂያ ዓይነት መርጠው በመጫን የመራጭነት መታወቂያን ማግኘት ይችላሉ።
#ምርጫ2018 #EthiopiaElection
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ራስን በራስ ለመመዝገብ በተዘጋጀውና “ምርጫዬ” በተሰኘው የመራጮች ምዝገባ መተግበሪያ የሚመዘገቡ “የተወሰኑ መራጮች ቋሚ የመራጮች ቁጥር እንዳገኙ ምዝገባው የተጠናቀቀ አድርገው በመውሰድ ለ7ተኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጭነት ካርድ” አለመውሰዳቸውን አሳወቀ።

ዛሬ የካቲት 29 ቀን 2018 ዓ.ም ቦርዱ ባወጣው መግለጫ “አብዛኛው “ምርጫዬ” መተግበሪያን በመጠቀም ራስን በራስ በመመዝገብ ሂደት ቋሚ የመራጭነት ቁጥር ያገኙ መራጮች፤ የምዝገባውን ሂደት በመቀጠል” እንዲሁም በሲስተሙ አማካኝነት “ምርጫ ጣቢያቸውን መርጠው ለ7ተኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚያገለግለውን ካርድ” እንዳገኙ ገልጿል።

ሆኖም “የተወሰኑ መራጮች ግን ቋሚ የመራጮች ቁጥር እንዳገኙ ምዝገባው የተጠናቀቀ አድርገው በመውሰድ ለ7ተኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጭነት ካርድ ከሲስተሙ ላይ አለመውሰዳቸውን ለመረዳት ተችሏል” ሲል ቦርዱ በመግለጫው አሳውቋል።

🔴ዝርዝሩን ለማንበብ ➡️ https://ethioelections.com/ምርጫ-ቦርድ-በምርጫዬ-መተግበሪያ-የሚ/

#ምርጫ2018 #EthiopiaElection
የትምህርት ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር በመመካከር፣ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ልዩ የምርጫ ጣቢያ የማቋቋም አሠራር እንዲቀር መወሰኑ ቅሬታ አስነሳ። ተማሪዎች በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በየመኖሪያ አካባቢያቸው ሄደው እንዲሳተፉ ያስተላለፈው መመሪያ፣ ለትግበራ አዳጋችና የተማሪዎችን ተሳትፎ የሚቀንስ እንደሆነ የተለያዩ አካላት ገልጸዋል።


ሚኒስቴሩ “ተማሪዎች መርጠው ለመመለስ የሚያስፈልጋቸው ቀናት ብቻ ታስቦ እንዲፈቀድላቸው” ሲል ያሰራጨው መመሪያ፣ በተለይ በማኑዋል የመራጮች ምዝገባ በሚካሄድባቸው አካባቢዎች ለሚኖሩ ተማሪዎች አመቺ እንዳልሆነ ተመልክቷል።


ተማሪዎች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ባልደረቦች እና የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ለ“ምርጫ 2018 - ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በሰጡት አስተያየት፤ ለመመዝገብና ድምፅ ለመስጠት ሁለት ጊዜ መመላለስ በፀጥታ፣ በሎጂስቲክስ እና በኢኮኖሚክ ምክንያቶች እጅግ አስቸጋሪ መሆኑን ገልጸዋል። ይህም በምርጫው የመሳተፍ ዕድላቸውን በእጅጉ እንደሚቀንስ ተናግረዋል።
🔴ዝርዝሩን ለማንበብ ➡️ https://ethioelections.com/ልዩ-የምርጫ-ጣቢያ-ዩኒቨርሲቲዎች-ውስጥ-የ/

#ምርጫ2018 #EthiopiaElection
“ምርጫ 2018 - ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን (ኢቲቪ) ከጥር 16 እስከ የካቲት 15 ቀን 2018 ዓ.ም ባለው የአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በምሽት ሁለት ሰዓት ዜናዎቹ ያቀረባቸውን የቅድመ ምርጫ ዘገባዎች የተመለከተ ዳሰሳ አካሄዷል። በዚህም መሰረት በመንግሥት በጀት የሚተዳደረው ይህ መገናኛ ብዙኃን ለሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ተመጣጣኝ እና ፍትሓዊ የዘገባ ሽፋን እንዳልሰጠ ማረጋገጥ ችሏል።

በዳሰሳው መሠረት ብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ የአየር ሰዓት ከተሰጣቸው አምስት ዘገባዎች ውስጥ ሁለቱን አግኝቷል። በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በብልፅግና ፓርቲ ስብሰባ ላይ ምርጫን በተመለከተ ያቀረቡት ንግግር ላይ ያተኮረ ዜና ብቻውን 10 ደቂቃ በመውሰድ ከፍተኛ የአየር ሰዓት ሽፋን ሲያገኝ፣ ለፓርቲው ማኒፌስቶ እና አርማ ማስተዋወቂያ የተዘጋጀው ፕሮግራም ደግሞ 4 ደቂቃ ከ10 ሰከንድ በመውሰድ አራተኛ ከፍተኛ የአየር ሰዓት ሽፋን አግኝቷል።

በአንፃሩ “የመገናኛ ብዙኃንና የጋዜጠኞች የምርጫ አዘጋገብ ሥነ-ምግባር እና አሠራር መመሪያ ቁጥር 02/2013” በአንቀጽ 16(1) ላይ የመንግሥት ሚዲያዎች “ሁሉም ተወዳዳሪ ፓርቲዎች አቋማቸውን ለመራጭ ሕዝቡ ለማቅረብ ፍትሓዊ ዕድል እንዲያገኙ” የማድረግ ግዴታ ጥሎባቸዋል። እንዲሁም በአንቀጽ 16(6) መሠረት በምርጫ ወቅት ለሚዘጋጁ የውይይት፣ የክርክር እና የቃለ-መጠይቅ ፕሮግራሞች ተገቢ የዜና ሽፋን መስጠት እንዳለባቸው ይደነግጋል።

ሙሉ የዳሰሳውን ውጤት የሚመለከተውን ዘገባ እዚህ ያንብቡ:- https://ethioelections.com/የኢትዮጵያ-ቴሌቪዥን-የቅድመ-ምርጫ-2018-አዘጋ/

#ምርጫ2018 #EthiopiaElection #EBCNews
“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ባደረገው የሚዲያ ዳሰሳ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን (ETV) ከጥር 16/2018 እስከ የካቲት 15/2018 ባሉት ቀናት ውስጥ የቀረቡ የምሽት 2፡00 ሰዓት ምርጫ ነክ ዜናዎች የተሰጣቸውን አጠቃላይ ሽፋን ተመልክቷል።


ብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ የአየር ሰዓት ከተሰጣቸው አምስት ዘገባዎች ውስጥ ሁለቱን አግኝቷል። በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በብልፅግና ፓርቲ ስብሰባ ላይ ምርጫን በተመለከተ ያቀረቡት ንግግር ላይ ያተኮረ ዜና ብቻውን 10 ደቂቃ በመውሰድ ከፍተኛ የአየር ሰዓት ሽፋን ሲያገኝ፣ ለፓርቲው ማኒፌስቶ እና አርማ ማስተዋወቂያ የተዘጋጀው ፕሮግራም ደግሞ 4 ደቂቃ ከ10 ሰከንድ በመውሰድ አራተኛ ከፍተኛ የአየር ሰዓት ሽፋን አግኝቷል። ከአምስቱ ከፍተኛ የአየር ሰዓት ከተሰጣቸው ዜናዎች ውስጥ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን የሚመለከት አንድም ዜና የለም።

በአንፃሩ ከአምስቱ ከፍተኛ የአየር ሰዓት ከተሰጣቸው የምርጫ ነክ ዜናዎች ውስጥ ባይገባም፣ ሕብር ኢትዮጵያ የምርጫ ማኒፌስቶ ማዘጋጀቱን የሚገልጸው ዜና 3 ደቂቃ ከ46 ሰከንድ የወሰደ የአየር ሰዓት ያገኘ እና የተናጠል የዜና ሽፋን ያገኘ ብቸኛው ተቃዋሚ ፓርቲ ሆኗል። 2ኛ ከፍተኛ የአየር ሰዓት የወሰደው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምርጫ ነክ ትንታኔ ቢሆንም በፓርላማ መንግሥትን በመወከል ያደረጉት ንግግር መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት ለብልፅግና ፓርቲ የተሰጠ የአየር ሰዐት ተደርጎ በዳሰሳው አልተወሰደም።

ሙሉውን የዳሰሳውን ዘገባ ለመመልከት፣ የ"ምርጫ 2018 - ኢትዮጵያ ኢንሳይደር" ደረገጽ ላይ ይመልከቱ፤ https://ethioelections.com/የኢትዮጵያ-ቴሌቪዥን-የቅድመ-ምርጫ-2018-አዘጋ/
#ምርጫ2018 #EthiopiaElection #EBCNews
“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ባደረገው የሚዲያ ዳሰሳ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን (ETV) ከጥር 16/2018 እስከ የካቲት 15/2018 ባሉት ቀናት ውስጥ የቀረቡ የምሽት 2፡00 ሰዓት ምርጫ ነክ ዜናዎች ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተጠቀሱባቸውን ድግግሞሽ ተመልክቷል።

በዚህም በዜናዎቹ ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተናጠል ወይም በቡድን በተጠቀሱበት ድግግሞሽ መሠረት ሲታዩ፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) 6 ዘገባዎች ላይ ሥሙ በተደጋጋሚ የተጠቀሰ ቀዳሚው ፓርቲ ሆኖ ተገኝቷል። ከኢዜማ በመቀጠል ብልፅግና ፓርቲ 5 ጊዜ፣ ነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) 3 ጊዜ ቢጠቀሱም፣ ሌሎቹ ሰባት ፓርቲዎች ከአንድ ጊዜ በላይ አልተጠቀሱም።

ተቃዋሚዎቹ ፓርቲዎች ምንም እንኳን ሥማቸው እና እነርሱን የሚመለከቱ ጉዳዮች በዜና ዘገባዎች ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር አንድ ላይ በጋራ ቢጠቀሱም፣ “ሕብር ኢትዮጵያ” የተባለ የፓርቲዎች ቅንጅት የምርጫ ማኒፌስቶ እያዘጋጀ መሆኑን የሚገልጽ የዜና ትንታኔ ከማግኘቱ በቀር የተናጠል ሽፋን ዘገባ ያገኘ ሌላ ተቃዋሚ ፓርቲ በዳሰሳው በተቃኙ ዘገባዎች ውስጥ አልታየም። ሆኖም፣ በዜና እወጃዎች ሰዓት መካከል በተደጋጋሚ ይለቀቁ በነበሩ ማስታወቂያዎች ብልፅግና ፓርቲ፣ ኢዜማ፣ እና ነእፓ የፓርቲዎቻቸውን ዝግጅት የሚመለከቱ ቃለ መጠይቆች እንደተደረጉላቸው መገንዘብ ይቻላል።

ሙሉውን የዳሰሳውን ዘገባ ለመመልከት፣ የ"ምርጫ 2018 - ኢትዮጵያ ኢንሳይደር" ደረገጽ ላይ ይመልከቱ፤https://ethioelections.com/የኢትዮጵያ-ቴሌቪዥን-የቅድመ-ምርጫ-2018-አዘጋ/
#ምርጫ2018 #EthiopiaElection #EBCNews
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ7ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ እስካሁን ከ9 ሚሊዮን በላይ መራጮች መመዝገባቸውን ያስታወቀ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት በ46,757 ጣቢያዎች ምዝገባው እየተከናወነ እንደሚገኝም ገልጿል። ሆኖም በ6,395 የምርጫ ጣቢያዎች በጸጥታ ስጋት፣ በቁሳቁስ ስርጭት መዘግየት እና ባልተጠበቀ የዝናብ ሁኔታ ምክንያት ምዝገባው ገና እንዳልተጀመረ የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ገልጸዋል።


ቦርዱ ከዲጂታል ምዝገባ ጋር የተያያዙ የኢንተርኔትና የመብራት መቆራረጥ ችግሮችን ለመፍታትም ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።


​በሌላ በኩል፣ የምርጫ ካርድ መውሰድን ለሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶች እንደ ቅድመ ሁኔታ የሚጠይቁ አካላት መኖራቸውን ጠቅሶ ድርጊታቸው ተገቢ አለመሆኑን ቦርዱ አሳስቧል። መምረጥ መብት እንጂ ግዴታ አለመሆኑን የገለጹት ሰብሳቢዋ፤ ዜጎች በማንም ተጽዕኖ ሳይወድቁ በነጻነትና በራሳቸው ፈቃድ ብቻ መመዝገብ እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል። በተጨማሪም የምርጫ ሂደቱን ለማደናቀፍ በሚሞክሩና አስፈጻሚዎችን ለማማለል በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ ቦርዱ አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል።

🔴ዝርዝሩን ለማንበብ ➡️ https://ethioelections.com/2026/03/17394/
#ምርጫ2018 #EthiopiaElection
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ትላንት፣ መጋቢት 4፣ 2018 በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳሳወቀው፣ ለ7ተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ከዘጠኝ ሚሊዮን በላይ መራጮች በአንድ ሳምንት ውስጥ ተመዝግበዋል። ከነዚህ ውስጥ 93.4% በማኑዋል የተመዘገቡ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ በዲጂታል ስርዓት መመዝገባቸውን አሳውቋል።


በተመሳሳይ በፀጥታና ሎጅስቲክ እክሎች ሳቢያ 12 በመቶ የሚገመቱ የምርጫ ጣቢያዎች መራጮችን መመዝገብ እንዳልቻሉ ቦርዱ ገልጿል።
#ምርጫ2018 #EthiopiaElection
“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ባደረገው የሚዲያ ዳሰሳ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን (ETV) ከጥር 16/2018 እስከ የካቲት 15/2018 ባሉት ቀናት ውስጥ የቀረቡ የምሽት 2፡00 ሰዓትየ7ተኛውን ሀገራዊ ምርጫ ነክ ዜናዎች ውስጥ ብልፅግና ፓርቲ በተደጋጋሚ የመጠቀስ እና ሰፊ የአየር ሽፋን የማግኘት ዕድል እንደተሰጠው አረጋግጧል።

ሐምሌ 3፣ 2013 ዓም፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ6ኛውን አገር ዐቀፍ ምርጫ ይፋ ባደረገበት ወቅት፣ የቀድሞዋ የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ባደረጉት ንግግር “ዛሬ እዚህ የምትቀርፁን የመንግሥት ሚዲያዎች… የመንግሥት ባለሥልጣናት ኮታቸው ላይ የተሰካው ማይክራፎን የማይወልቅ ይመስል ሌት ተቀን የእነሱን ካምፔን እና ቅስቀሳ ስታስተላልፉ ቆይታችሁ የተቃዋሚዎችን 10 እና 15 ደቂቃ ማድረጋችሁ ፍትሐዊነታችንን አጉድሎብናል” ማለታቸው ይታወሳል።


በዳሰሳው እንደተስተዋለው፣ ብልፅግና ፓርቲ በተናጠል ወይም ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር በጋራ የሚጠቀስባቸው ዘገባዎች 17 ደቂቃ የአየር ሰዓት ሽፋን ያገኙ 5 ዜናዎች ሲሆኑ፣ በአንፃሩ ሌሎች 9 የተወዳዳሪ ፓርቲዎች በተናጠል ወይም ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር የተጠቀሱባቸው ዘገባዎች 16 ደቂቃ የወሰዱ አጫጭር ዜናዎቹ ናቸው። በዚህም በድምሩ 25 ደቂቃ ከሰላሳ ሰከንድ ብቻ የአየር ሰዓት ሽፋን እንዳገኙ ዳሰሳው ያሳያል።


ሙሉውን የዳሰሳውን ዘገባ ለመመልከት፣ የ"ምርጫ 2018 - ኢትዮጵያ ኢንሳይደር" ደረገጽ ላይ ይመልከቱ፤፤https://ethioelections.com/የኢትዮጵያ-ቴሌቪዥን-የቅድመ-ምርጫ-2018-አዘጋ/
#ምርጫ2018 #EthiopiaElection #EBCNews