የሐዋሳ ሰ/ም/ቅ/ማ/ቤ የውሉደ ያሬድ ሰንበት ት/ቤት መንፈሳዊ ቻናል
97 subscribers
412 photos
8 videos
72 files
9 links
የሐዋሳ ሰ/ም/ቅ/ማ/ቤ የውሉደ ያሬድ ሰንበት ት/ቤት መንፈሳዊ ቻናል ነው በዚህም መንፈሳዊ ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን የጠበቁ ትምህርቶችን የምንማማርበት ነው ፡፡
Download Telegram
የቅበላ ሰንበት ወንጌል ዮሐ 4
አንዳንድ የድካም ንግግሮችን ስለ መዝለል!

ዮሐ 4:4 የተጻፈው ታሪክ በኑሯችን ሁሉ እንዴት መራመድ እንዳለብን ጌታችን ያቺን ሳምራዊት ሴት ካናገረበትና ካስተማረበት መንገድ በጣም ብዙ የምንማረው ነገር አለ
ጌታችን ሴቷ ከመምጣቷ በፊት ቀድሟት ሄዶ ነው ምንጩ ዳር የተገኘው እንኳን ወደ እኛ መጥተው ለሚማሩት ይቅርና ወደ ችግረኞች ሄደን ማስተማር እንዳለብን ያሳያል
የምንሄደውም በምቾት ሳይሆን የፀሐዩ ሐሩር በበረታበትና በቀትር ተጠምተንና ደክመን መሆን እንዳለበት ያሳያል ወደኪሞ እግዚእ ኢየሱስ በሐዊረ ፍኖት ይላል።

😘 ጌታ ውኃ አጠጪኝ ሲላት ለተጠማ ሰው ውኃ ከማጠጣት ይልቅ የዋለ ያደረ የሕዝብ ጥያቄ እያነሳች በጥማቱ ላይ አደከመችው እንጂ ልታጠጣው አልወደደችም አንዳንዴ ሰዎች ከምን የተነሣና በምን ምክንያት ከንግግራችንና ከሐሳባችን እንደሚርቁ መረዳትና ሕመማቸውን ማወቅ አለብን
ከሰው ምላስና ንግግር ይልቅ የቀኑ ሐሩር ይሻለኛል ብላ ወደ ወንዝ የመጣች ሴት ናት ብዙ ሆድ የባሳት ሴት ናት ምንም ብትናገር ይገባታል
እግዚአብሔር በእርሷ ብቻ የጨከነ እስኪመስላት ድረስ ከአምስት ባሎች ጋር የነበራት ነገር የተበላሸ ነው
በምድር ላይ ለሰዎች መሳለቂያ ሆና የተፈጠረች እስኪመስላት ድረስ ሰዎች የሚጠቋቆሙት በእርሷ ነው ይህ መገለሏ ሳያንስ ደግሞ እንደ ሕዝብ ደግሞ እስራኤልና ሰማርያ ተብለው መከፋፈላቸው አንዱ አንዱን ማቃለሉምና መጸየፉ ያሳስባት ኖሯል
በማምለኪያ ቦታቸው ሳይቀር ተከፋፍለው እነዚያ በኢየሩሳሌም ብቻ እነርሱም በዚህ ተራራ ብቻ የሚል አቋም መያዛቸውም እንደ አቅሟ የሃይማኖት ጥያቄ ነበራትና ጌታ በትምህርት ሲያሳድጋት ይህን ሁሉ አጀንዳ ቀስ በቀስ እያነሣች ጥያቄዋን አቅርባለች

ስለዚህ ጌታ የልቧን ቁስል የአእምሯዋን መጎዳት ሁሉ ተረድቶ ውኃ አጠጪኝ ሲላት ውኃ ከመስጠት ይልቅ በደኅና ጊዜ ትጸየፉን የለም ወይ? እንዴት ከእኔ ሳምራዊቷ ሴት ለምን ውኃ ትለምናለህ አለችው?
ለተጠማ ሰው የውኃ መቅጃ ይዞ ነገር መቅዳትኮ ያማል
ጌታ ግን ውስጣዊ ሕመሟን ስለሚያውቅ ሊያክማትና ስውር ጥማቷን ሊያበርድላት ማስተማር ያዘ
ሕመሟን ያውቃልና አልፈረደባትም ኒቆዲሞስን አንተ የአይሁድ መምህር ሆነህ ሳለህ ይህንን አታውቅምን እያለ የገሠጸው ጌታ ይህችን ሴት ግን በልኳና በሕመሟ ልክ ማከም ያዘ ሰዎች የሚሰጣቸው መድኃኒት በእነርሱ ጥንካሬና ድካም ልክ ነውና መድኃኒቱን መቋቋም የማይችሉም ስለሚኖሩ ነው።

እርሱም የሚለምንሽ ማን እንደሆነስ የእግዚአብሔርን ስጦታ ብታውቂ ብሎ ማንነቱንና ምንነቱን በምሥጢር ነገራት እንኳን መቅጃሽን ልጸየፈው ይቅርና ከሕዝብና ከአሕዛብ ተወልጄ የመጣሁ የሕይወት ስጦታ ነኝ እያላት ነው

መቅጃ የለህም ጉድጓዱ ጥልቅ ነው ብላ ሌላ ክርክር አነሣች ለጊዜው የሚጸየፏቸው አይሁድ ስለሆኑ እርሱ እስካልተጠየፋትና እስካልናቃት ድረስ ውኃ መስጠት ነበረባት
እርሱ ግን በሰለቻት መንገድ ሊያስተምራት እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ አይጠማም አላት
ይህንን ሲላት በእየ ጊዜው ፀሐይ እየቀጠቀጣት ብቻዋን ወደ ምንጩ የምትመላለስበት የሰለቸ የድግግሞሽ ሕይወቷ ታያትና እባክህ ይህንን ውኃ ስጠኝና ከመመላለስ ገላግለኝ አለችው
ይገርማል የራበው ሰው እግዚአብሔርን የሚያየው በእንጀራ ሒሳብ ነው እንደሚባለው ሁሉ የዚህች ሴት የሕይወት ውኃ ማለት አንዴ ተጠጥቶ ወደ ወንዝ አለመመላለስ ነበር ጌታም ባልሽን ጠርተሽ ነይ በማለት በንስሐ ወደ ሥርዓተ ቁርባን ስንቀርብ ባል ሚስትን ሚስትም ባሏን ይዛ ለመቅረብ መጣር እንዳለባቸው ሲያስረዳ የሕይወት ውኃን ለመጠጣት ባልሽን ጥሪ አላት
በዚህ ንግግሩም ወደ ትክክለኛ ሕይወቷ ገባ ገና እንዳገኛትና ውኃ አጠጪኝ ሲላት አምስት ባሎች እንደሸኘች ቢናገራት ኖሮ በምሬትና ተስፋ በመቁረጥ እርሱንም በሸሸችው ነበርና እያባበለ አስተማራት
ብዙ ሐኪሞች በመልካም መንገድ ያክሙ ይሆናል ጌታ ይህችን ሴት ያከመበትና ቁስሏን የጠረገበት መንገድ ግን እጅግ ይደንቃል ለካ ሳምራዊት ሴት መሆኔን ብቻ ሳይሆን ይህንን ሁሉ ጉዴንና ነውሬንም እያወቀ ነው ውኃ የለመነኝ ብላ እንድትደነቅም አድርጓታል

አምስት ባሎች ነበሩሽ ብሎ ማንነቷን ሲነግራት የእኔን ሕይወት ተወው ለጨዋታም ለአጀንዳም አይመችም ይልቁንስ ነቢይ ትመስለኛለህ ስለዚህ ሃይማኖታዊ ጥያቄ ላቅርብ ብላ ከእንስራ ጀርባ የሃይማኖት አጀንዳ መዘዘች ጌታም ይህንንም በሚገባት መንገድ አስረዳት እርሷ ግን ምሥጢሩ ስለረቀቀባት የቀረውን ደግሞ መሲሑ ሲመጣ ሁሉን ይነግረናል ብላ በነቢያት ተስፋ የምትኖር ሴት መሆኗን ተናገረች
በዚህ ጊዜ ጌታ ስብከቱን ጨረሰና የምትይው እኮ እኔ ነኝ አላት
ይደንቃል በመዋዕለ ሥጋዌው ጌታ እራሱን የገለጠው ለሁለት ሰዎች ሲሆን አንዷ ይህች እድለኛ ሴት ናት

ጌታችንም እንዲህ ተጠምቶና ደክሞ አልቀረም ይህንን ሁሉ ካየች በኋላ ከሰው ተደብቃ በቀትር የመጣች ሴት ሰው ምን ይለኛል ሳትል ወደ መንደር ገብታ ሕዝብ መሰብሰብ ጀመረች ብዙ ሰው አስከትላ መጣች
ከሰው ተደብቃ የጨለማ ሕይወት የምትመራ ሴት ለብዙ ሰዎች ብርሃን ሆና ተገኘች
እንሥራና ውኃ አጀንዳዋ ላይሆን ለመጨረሻ ጊዜ ጥላው ሄደች ለብዙ ዘመን ሰዎች የጫኑባት ነውሯና ፍርሐቷ የተወገደው በጥቂት ደቂቃዎች የጌታ ስብከት ነበር ዛሬም እኛ የተስፋ መቁረጥ እና የብሶት እንሥራ የተሸከሙ ሰዎችን በንግግራቸው ልክ ከመናገርና በድካማቸው ልክ ከምንፈርድ ይልቅ ብሶታቸውን የምንጠግንበትና የምናክምበትን ጥበብ አምላከ ቅዱሳን ያድለን።
👉Share በማድረግ አብራችሁን ስለምታገለግሉ ዋጋ አላችሁ።
በማስተዋል መነበብ የሚገባው አንድ ጽሑፍ ሊለቀቅ ነው🎯
ኃጢአቴን መናዘዝ ከበደኝ፤ እንዴት ልጀምር?

👂እውነት ነው፤ የኃጢአት ሸክም የልብን ሰላም እንደሚነሳው፣ የንስሐም ደጅ መክፈት ፈተና እንደሚሆን አይካድም። “ኃጢአቴን መናዘዝ ከበደኝ፤ እንዴት ልጀምር?” የሚለው ጥያቄ፣ የብዙዎች መንፈሳዊ ትግል ነጸብራቅ ነው። ይህ ስሜት፣ ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የሚመጣ የተለመደ እንቅፋት ነው። ነፍስህ ከፈጣሪዋ ጋር ለመታረቅ የምትሻ ቢሆንም፣ የሠራሃቸው ኃጢአቶች ግን እንደ ከባድ ማሰሪያ ይዘውህ እንደሆነ ይሰማህ ይሆናል። ንስሐ ለመግባት ስታስብ፣ የኃጢአትህ ብዛትና ክብደት ልብህን ያደክመው ይሆናል።

የንስሐ ደጅ የእግዚአብሔር ምሕረት እንጂ የእፍረት ግድግዳ አይደለም

በዚህ ስሜት ውስጥ ብቻህን አይደለህም። ብዙዎች በኃጢአት ሸክም ተጎድተው፣ ራሳቸውን ከእግዚአብሔር ፊት ለማቅረብ ሲፈሩ፣ በቤተ ክርስቲያን ደጃፍ ላይ ቆመው አዝነው ኖረዋል። ይህ ስሜት ግን ከጠላት የሚመጣ ተንኮል መሆኑን መረዳት ይገባል። ዲያብሎስ ሁልጊዜ የኃጢአትህን መጠን አጋኖ በማሳየት፣ የእግዚአብሔርን ምሕረት ደግሞ አሳንሶ በማቅረብ ተስፋ እንድትቆርጥ ይገፋፋሃል። እርሱ “እፍረት” የሚባል መጋረጃ ለብሶ፣ የእግዚአብሔርን ፍቅር እንዳታይ ይጋርድሃል።

ግን ልብ በል፤ የንስሐ ደጅ የእፍረት መድረክ ሳይሆን፣ የእግዚአብሔር አብ ሞቅ ያለ እቅፍ ነው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ኃጢአተኞችን ሊያድን እንጂ ጻድቃንን ሊጠራ እንዳልመጣ ተናግሯል። (ማቴዎስ 9:13) እርሱ ለታመሙት እንጂ ለጤነኞች ሐኪም አያስፈልግም ብሎ አላለም? ንስሐ ደግሞ ለነፍስ ቁስል ታላቅ መድኃኒት ነው። ኃጢአትህ ምንም ያህል ቢከብድ፣ ምንም ያህል ቢበዛ፣ ከእግዚአብሔር ምሕረት አይበልጥም። የቅዱስ ዳዊት መዝሙር “እንደ ምሕረትህ ብዛት በደሌን ደምስስ” (መዝሙረ ዳዊት 51:1) ሲል የጮኸው፣ የዚያን ታላቅ የእግዚአብሔር ፍቅር መናዘዣ ነው።

መጀመር ማለት የፍቅርን ጥሪ ማስተዋል ነው

ታዲያ እንዴት መጀመር ይቻላል? የመጀመሪያው እርምጃ፣ በልብህ ውስጥ ያለውን የእግዚአብሔር የፍቅር ጥሪ ማስተዋል ነው። እግዚአብሔር አንተን ለመኮነን አይደለም የሚፈልገው፤ ይልቁንም ወደ እርሱ እንድትመለስና የጠፋውን ሰላምህን እንድታገኝ ነው። ልክ የበግ ጠባቂ የጠፋች በጉን ለማግኘት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል እንደሚፈልግ ሁሉ፣ ጌታችንም የአንተን መመለስ እየናፈቀ ነው።

የመናዘር ሂደት ማለት፣ ነፍስህ በኃጢአት ከቆሸሸች በኋላ እንደገና ለመታጠብ እንደመወሰን ነው። ቤተ ክርስቲያናችን ንስሐን ሁለተኛ ጥምቀት የምትለው ለዚህ ነው። በእውነት፣ ልክ አባቶቻችን በካህናት እጅ ዕጣን ሲያጨሱ፣ የመስቀሉ ቅርጽ ያለው ጭስ ወደ ላይ እንደሚያርግ ሁሉ፣ የእኛም ንስሐ በእግዚአብሔር ፊት መዓዛ ይዞ የሚያርግ ጸሎት ነው።

የአባቶች ጥበብ እና የቅዱሳን ምስክርነት

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ “ንስሐ ከኃጢአት ውድቀት በኋላ የሚገኝ የመዳን መልሕቅ ነው” ብሏል። ይህ ምንኛ እውነት ነው! ልክ መርከብ በማዕበል ከተናወጠች በኋላ መልሕቅ ተጥሎላት እንደምትረጋጋ ሁሉ፣ በኃጢአት ባህር ውስጥ ስትናወጥ፣ ንስሐ መልሕቅህ ነው። ከቅዱሳን አባቶቻችን እንደተማርነው፣ የንስሐ በር ሁልጊዜ ክፍት ነው። ምንም ያህል ዘግይቶ ቢመጣ፣ ምንም ያህል ከባድ ኃጢአት ቢሠራ፣ የእግዚአብሔር እጅ ዘርግቶ ይጠብቃል።

በእኛ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ፣ መናዘዝ ማለት ከመንፈሳዊ አባት ጋር መነጋገር ነው። የንስሐ አባት የእግዚአብሔር ምሕረት መሳሪያ ነውና። እርሱ ምእመኑን የሚወድ፣ የሚረዳና ወደ እግዚአብሔር የሚመራ መንፈሳዊ መሪ ነው። እርሱ እንደ ዘመድ፣ እንደ ወንድም፣ እንደ አባት የሚቆጥር ነው። ብዙ ጊዜ የንስሐ አባቶች ጸልየው፣ ምከረው፣ ጾመውና ተግተው ለንስሐ ልጆቻቸው ይማልዳሉ።

የተሳሳቱ አመለካከቶችን ማስተካከል

አንዳንድ ጊዜ ሰዎች “ኃጢአቴን እንዴት ለአባት እነግረዋለሁ? ያፍርብኛል!” ብለው ያስባሉ። ይህ ግን ስህተት ነው። የንስሐ አባት የሰማውን ማንንም አይናገርም። ምስጢረ ንስሐ ቅዱስ ምሥጢር ነው። እርሱ የሰማውን ሁሉ እንደ ራሱ ኃጢአት ቆጥሮ በእግዚአብሔር ፊት የሚያቀርብ ነው። ይልቁንም፣ የንስሐ አባትን ፊት ሲያዩ፣ በውስጥ የነበረው ሸክም ወዲያው እንደሚቀል ታያለህ። ልክ በበዓላት ቀን፣ ቤተ ክርስቲያን በዕጣን መዓዛ ታውዳ፣ ደወል ሲደውል፣ ምዕመናን በመስቀል ምልክት ሲባረኩ ሰላም እንደሚያገኙ ሁሉ፣ የንስሐን ሰላም ታገኛለህ።

የመናዘዝ ከባድነት የሚመጣው ከኃጢአቱ ሳይሆን፣ ከፍርሃትና ከትዕቢት ነው። “እንዲህ ያለ ኃጢአት የሠራሁ እኔ ማን ነኝ?” የሚለው ጥያቄ ሰይጣናዊ ነው። “እግዚአብሔር ይቅር የማይለው ኃጢአት የለም” የሚለው የእግዚአብሔር ቃል ግን መለኮታዊ ነው። (1ኛ ዮሐንስ 1:9) የኃጢአትን መጠን በመናገር እግዚአብሔርን አያስደንቅም። እርሱ ሁሉን ያውቃል። ንስሐ የሚገባው ለእርሱ ነው። የሚነገረውም በራስ ለመታመን፣ ክፋትን አውቆ ንስሐ ለመግባት ነው።

የሰላም እና የተስፋ መንገድ

አሁን፣ ምንም ሳትፈራ ተነስ። ለመጀመር ትንሽ ዝግጅት ማድረግ ትችላለህ።
👉ጸልይ: የእግዚአብሔርን እርዳታ ለምን። “አቤቱ ይቅር በለኝ፤ ኃጢአቴን እንድናዘዝ ብርታት ስጠኝ” በል።
👉ጻፍ: የምታስታውሳቸውን ኃጢአቶች በወረቀት ላይ መጻፍ ከባድነትን ይቀንሳል፤ ምንም እንኳን ለመናዘዝ የግድ መጻፍ ባይጠበቅ።
👉የንስሐ አባት አግኝ: እስካሁን ከሌለህ፣ ታማኝና የምታምነው ካህን ምረጥ። ካለህ ደግሞ፣ እሱን አግኝ። ቀጠሮ ያዝ።
👉ሂድ: አንዴ ከወሰንክ፣ አትዘግይ። የቅዱሳን መላእክት ሠራዊት አብሮህ እንዳለ እመን።

አንዴ ስትጀምር፣ ያ ሸክም ከአንገትህ ላይ ሲነሳ፣ ያ ጨለማ ከልብህ ሲወገድ ይሰማሃል። በክርስቶስ ደም የጸዳህ፣ የረከሰ ልብስህን አውልቀህ ንጹሕ ልብስ እንደለበስክ ሁሉ፣ የንስሐን ሰላም ታገኛለህ። ልክ በቅዳሴ ጊዜ ቃና ዘገሊላ ሲዘመር፣ ክርስቶስ ውሃውን ወደ ወይን እንደለወጠው ሁሉ፣ እርሱም የኃጢአትን መራራነት ወደ ንስሐ ጣፋጭነት ይለውጥልሃል።

ሁላችንም ወድቀናል፤ ነገር ግን የመነሣት ኃይል አለን። በእግዚአብሔር ምሕረት፣ በቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ በቅዱሳን ጸሎትና በቤተ ክርስቲያን በረከት፣ ይህንን ከባድነት አሸንፈህ፣ የንስሐን ሰላም እንድታገኝ እጸልያለሁ። እግዚአብሔር በቸርነቱ ይርዳህ/ሽ! አሜን
Share share ይደረግ የምትችሉ ኑ! ነፍሳትን ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ ጋብዙ🙏
“ለጌታ ያስፈልጉታል”ማቴ 21፥3

ብዙ ሰው ተስፋ ያለው ሆኖ ተፈጥሮ ሳለ ተስፋ በመቁረጥ ስሜት ውስጥ ይገኛል አንዳንዴ ማንም አይፈልገኝም ለማንም አልጠቅምም እያለ ሲጨነቅ ሲያስብ ይስተዋላል ተወዳጆች ሆይ እናንተስ እንዲህ ብላችሁ ይሆን በእንዲህ አይነት የተስፋ መቁረጥ ስሜት ውስጥ ገብታችሁ ይሆን?

ሆሳዕናን ቢሰብኩ ግዜ ከእንዲህ ያለ የከንቱነት ስሜት ለማውጣት የሚረዳ አንድ ታሪክ አስታውሳለሁ ጌታ ሐዋርያቱን ሂዱና ፈታችሁ አምጡልኝ ብሎ በላካቸው ጊዜ እንዲህ ነበር ያላቸው ማንም አንዳች ቢላችሁ ለጌታ ያስፈልጉታል ባሉ። ወዳጄ አስተውል እንዲህ የተባለላት ጌታዋን ያከበረች አህያ ናት በእውነቱ

👉አንተ ከአህያዋና ከውርነጭላይቱ ታንሳለህን?
👉በአርአያው የተፈጠርክ አንተ በሃልዮ ከተፈጠረች እንስሳ ታንሳለን?
👉ዋጋ የተከፈለልህ አንተ ከአህያ ታንሳለህ?
👉 እግዚአብሔር ከሰማይ ሰማያት የወረደልህ ሥጋህንማ ተዋሕዶ ያከበረህ አንተ ከአህያ ታንሳለህን?

ብናስተውል እኛ ክብራችንን ማወቅ እስካልተሳነን ድረስ ከአህያ አናንስም “ሰው ግን ክቡር ሆኖ ሳለ አያውቅም፤ እንደሚጠፉ እንስሶች መሰለ”
(መዝ 49፥12) እንዳለ ክብር ዳዊት በአርአያው በአምሳሉ ግሩምና ድንቅ ሆነን የተፈጥርን የእጆቹ ስራዎች ነን።

ጌታ ለደቀ መዛሙርቱ አህያውን ፈታችሁ አምጡልኝ ነው ያላቸው አንተንም ይፈልግሃል የማይፈልገው ማሰርያህን ነው ማሰርያህን ፍታ ፤ካህናትም ዘንድ ቀርበህ ተፈታ፤
👉 አንተ በሱስ ታስረሃል ተፈተህ ብትቀርብ ግን ለጌታ ታስፈልገዋለህ
👉አንተ በዝሙት ታስረሃል ተፈተህ ብትመጣ ግን ለጌታ ታስፈልገዋለህ
👉አንተ በሃሜት ታስረሃል ተፈተህ ብትመጣ ግን ለጌታ ታስፈልገዋለህ

ስለዚህ ማሰርያህን ፍታ ለጌታ ታስፈልገዋለህ ና ከካህናቱ ዘንድ ተፈተህ ቅረብ ለጌታ የምታስፈልግ ነህ አንተ ከግኡዟ አህያ ትሻላለህና ጌታህ ሥራ ሊሠራብህም ይፈልግሃልና አንተ ከታሰርክበት የኃጥአት ገመድ ተፈታና ቅረብ።

አልጠቅምም ግን አትበል ልብህ ንጹሕ ይሁን እንጂ አንተም ለጌታ ታስፈልገዋለህ።

ሰናይ በዓል