ኤፌሶን~፩
650 subscribers
75 photos
1 video
23 links
Download Telegram
ጥር ፳፫ /23/


በዚች ዕለት የጳውሎስ ደቀ መዝሙሩ የሆነ ሐዋርያው ጢሞቴዎስ በሰማዕትነት ሞተ። የዚህም ቅዱስ ልደቱና እድገቱ ልስጥራን ከሚባል አገር ነው አባቱም ከዋክብትን የሚያመልክ ዮናናዊ ነው እናቱ ግን በኦሪት ሕግ ጥላ ሥር ያለች ናት።

የከበረ ሐዋርያ ጳውሎስም በልስጥራን ሀገር በሰበከ ጊዜ ይህ ጢሞቴዎስ ስብከቱንና ትምህርቱን ሰማ እግዚአብሔርም በጳውሎስ እጅ የሚያደርጋቸውን ድንቆች ተአምራቶችን አይቶ እሊህም ተአምራቶች አስተዋዮችና ጥበበኞች የሚደነግጡባቸው ናቸው ስለዚህም ወደ ሐዋርያ ጳውሎስ ሒዶ በእርሱ ትምህርት በክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ተጠምቆ የሐዋርያ ጳውሎስ ደቀ መዝሙሩ ሆነ ወደ ብዙ አገሮችም ተከትሎት በመሔድ ከእርሱ ጋር ደከመ ታላቅ መከራና ብዙ ኀዘንም ደርሶበታል ሐዋርያው ጳውሎስም በኤፌሶን ውስጥ በአንዲት አገር ላይ ኤጲስቆጶስነት ሾመው።

በዚያንም ጊዜ ወደርሷ ገብቶ ለሰዎቿ በክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ሰበከ ብዙዎችንም ወደ ቀናች ሃይማኖት መልሶ የክርስትና ጥምቀትን አጠመቃቸው ከዚህም በኋላ በዙሪያዋ ወዳሉ ብዙዎች አገሮች በርቀትም ለሚገኙ አገሮችም የከበረ ወንጌልን ሰበከላቸው።

በትምህርቱም አይሁድንና ዮናናውያንን ይገሥጻቸውና ይዘልፋቸው ነበር እነርሱም ቀንተውበት ሁሉም በጠላትነት ተነሡበት ተሰብስበውም ገደሉት ምእመናንም ሥጋውን አንሥተው ቀበሩት ጻድቅ ቈስጠንጢኖስም እስከ ነገሠ በዚያው ኖረ እርሱም ስለ ሥጋው አስቦ ወደ ቊስጥንጥንያ ከተማ በጥር ወር በሃያ ሰባት ቀን አፈለሰው በዚያችም ቀን በዓል አደረገለት።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ምንጭ፦ መጽሐፈ ስንክሳር

@efeson_2

💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫
ጥር ፳፯ /27/


በዚችም ዕለት የአዳም ልጅ ኄኖክን መላእክት ይዘው አሳረጉት።

ይኸውም በመባርቅትና በነፋሳት ላይ ተጭኖ በመብረር ወደ ሰማይ ወስደው ከረቂቃን መላእክት ጋር አኖሩት የእግዚአብሔርም ትእዛዝ ጸሐፊ ተባለ።

በደብር ቅዱስ ለነበሩ ለኃጢአት ለሚተጉ ለሴት ልጆች ይዘልፋቸው ዘንድ ቃል እንደጠራውና እንዳሳየው ተናገረ።  በእሳት ቅጽርም የተሠራ በክብር ከሁሉ የሚበልጥ በውስጡም ከፍ ያለ የእግዚአብሔርን ዙፋን አየሁ መልኩም እንደ ውርጭ ነው አጎበሩም እንደሚያበራ ፀሐይ ነው። ከዙፋኑም በታች የኪሩቤል ድምፅ ይሰማል።

በሰማይ ገጽ ስለሚመላለሱ ብርሃናት እንዲህ አለ አንዱም አንዱ በየወገናቸው በሠለጠኑበትና በተሠየሙበት ጸንተው ይኖራሉ ስለ ነፋሳትም መውጫዎች እንዲህ ብሎ ተናገረ ሦስቱ በሰማይ ገጽ ሦስቱ በምድር ገጽ ሦስቱ በቀኝ ሦስቱ በግራ ናቸው። ስለ አዳምም እንዲህ አለ እነሆ በሬ ከምድር ወጣ ፀዓዳም ሆነ ስለ ሔዋንም ደግሞ ሴት እምቦሳ ከርሱ ወጣች አለ።

ስለ ምኵራብም ያንን አሮጌ ቤት እስከሚአሳንሰው ድረስ አየሁ አለ ምሰሶዎቹንም ከውስጡ አወጣ። ስለ ቤተክርስቲያንም ጌታ አዲስ የበጎች ቤት አምጥቶ እስቲሠራ ድረስ አየሁ ከቀድሞውም ቤት የበለጠ ነው በጎችም ሁሉ በውስጧ ይሠማራሉ አለ ። ስለ ምእመናንም የእሊህም በጎች ፀጕራቸው ንጹሕ ነጭ ነው የተበተኑትም ከአራዊት ጋራ ይሠማራሉ ሁሉም በአንድነት ተሰብስበው ገራሞች ሆነዋልና።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር


@efeson_2

💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫
መድኃኔዓለም ሆይ አስቀድሞ ፈያታዊ ዘየማንን እንዳስብከው አቤቱ አዳኝ ቤዛ በሚሆን መስቀልህ አስበኝ፤ ፈጣሪዬ ክርስቶስ ሆይ አቤቱ ቸር ጠባቂ ነህና እንደ ዓይን ብሌን ጠብቀኝ፤ አቤቱ እኔን መከረኛውን ሃዘንተኛውን በምስጋናህ የወይን ጠጅ አስደስተኝ አረጋጋኝ።
    
                "መልክአ መድኃኔዓለም"



@efeson_2

💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫
🌿🍁🌿🍁🌿🍁🌿🍁🌿🍁🌿🍁🌿🍁🌿🍁

እንኳን ጌታችን በአካል ተገልጦ በደሃ ሰው ተመስሎ ከማኅበረ ዴጔ ጋር በመካከላቸውም ተገኝቶ የጽዋ ማኅበር እየጠጣ ተራው ደርሶ ተዓምር አድርጎ  አምላክነቱ ለገለጠበት ቀን ለመታሰቢያ በዓል፣  የስሟ ትርጓሜ መጻተኛ ለሆነ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በራእይ ለተገለጠላትና ከከበሩ ነገሥታት ወገን ለሆነችው ዓለምን ንቃ በመመንኰስ በምትተኛ ጊዜ ያለ ምንጣፍ በምድር ላይ እየተኛችና ጥሬ ባቄላን ብቻ እየተመገበች በታላቅ ተጋድሎ ለኖረችው ለከበረች ቅድስት አክሳኒ ለዕረፍቷ በዓል መታሰቢያ፣ ተጋዳይ ለሆነ በበረሃ ውስጥ የሞተ ሰው ራስ ቅል አግኝተው የራስ ቅሉን ላነጋገሩና ሥራውን መርምረው ለተረዱ በኋላም አማልደውት ምሕረትን ላሰጡት አባ እስጢፍኖስ ለዕረፍታቸው በዓል በሰላም አደረሰን። በተጨማ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ ከድንግል እመቤታችን ማርያም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ ከተወለደበት ከልደቱ መታሰቢያ፣ ከመስተጋድል ከከበረ ሰማዕት ከሰርያኮስ ከመታሰቢያው፣ ከሮሜ ሰዎች ውስጥ ከንጹሐት ሴቶች ከመታሰቢያቸው፣ ከፊልንማ፣ ከኢያልኒ፣ ከሰረባሞኒና ከቃውት እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።

@efeson_2

🌿🍁🌿🍁🌿🍁🌿🍁🌿🍁🌿🍁🌿🍁
🔥1
ጥር ፴ /30/


በዚችም ዕለት ተገዳይ የሆነ መነኰስ የከበረ አክርስጥሮስ አረፈ።

ይህም አባት በዮርዳኖስ ገዳም የሚኖር ነበር ከመነኰሳቱም አንዱ እየሰገደ እንዲህ ብሎ ጠየቀው "አባቴ አክርስጥሮስ ሆይ ከእኔ ጋር ፍቅርን አደርግ እጠቀምበትም ዘንድ ሥራህን ሁሉ ንገረኝ" አለው።

ሽማግሌው አክርስጥሮስም እንዲህ ብሎ መለሰለት ልጄ ሆይ ጎልማሳ ሆኜ ሳለ በመነኰስኩ ጊዜ በዚያ እጸልይ ዘንድ በሌሊት ወደ ቅዱስ ቴዎድሮስ መቅደስ እሔድ ነበር። ዐሥራ ሁሉት ደረጃዎችም አሏት በየአንዳንዱም ደረጃ መቶ መቶ ስግደቶችን እሰግዳለሁ ደወልንም በሚደውሉ ጊዜ ወደ ቤተ ክርስቲያን በመግባት ከወንድሞች ጋርየማኅበሩን የጸሎት ሥርዓት እፈጽማለሁ እንዲሁም በማድረግ ዐሥር ዓመት ኖርኩ።

ከሌሊቶችም በአንዲቱ የተለመደ ጸሎቴን ከፈጸምኩ በኋላ ልቡናዬ በተመሥጦ ተማረከ ነጫጭ ልብሶችን የለበሱ ሁለት ሰዎች መቅረዞችን ሲያበሩ እኩሌቶቹ ሲበሩ እኩሌቶቹም ሲጠፉ አየሁ። እኔም ይህ ሥራ ምንድን ነው አልኳቸው እነዚያም አባቶች ባልንጀራውን የሚወድ መቅረዙ የበራለታል አሉኝ እኔም ደግሜ መቅረዜ የቱ ነው አልኋቸው እነርሱም ሒድ ከወንድሞችህ ጋር ተፋቀር እኛ እናበራልሃለን አሉኝ በነቃሁም ጊዜ ማንንም አላገኘሁም።

ከዚህም በኋላ አባ አክርስጥሮስ ብቻውን ወደ ደብረ ሲና ሒዶ በዚያ እየተጋደለ ኀምሳ ዓመት ኖረ ወደርሱም እንዲህ የሚለው ቃል መጣ ከአባቶችህ ጋር ትኖር ዘንድ ወደ ገዳምህ ተመለስ ከዚህም በኋላ በተመለሰ ጊዜ በሰላም አረፈ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑርለዘላለሙ አሜን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

@efeson_2

💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫
1
🌿🍁🌿🍁🌿🍁🌿🍁🌿🍁🌿🍁🌿🍁

እንኳን #ጌታችንን_ሽቱ_ለቀባችው_ለማርያም_እንተ ዕፍረት ለዕለፍቷ መታሰቢያ በዓል፣ ለዓለሙ ሁሉ መምህር ለሆነ ለሮሜ አገር ሊቀ ጳጳሳት ለከበረ አባት #ለአባ_አቡሊዲስ ሥጋው ከባሕር ለወጣበት በዓልና #ለከበሩ_ቅዱሳን_አቡቂርና_ዮሐንስ ለሦስቱ ደናግላን #ለቅድሳት_ቴዎድራ_ቴዎፍና_ቴዎዶክስያና ለእናታቸው #ለቅድስት_አትናስያ ሰማዕትነት ለተቀበሉበት ለዕረፍታቸው በዓል በሰላም አደረሰን። ከእነዚህ  ቅዱሳን እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።


@efeson_2

🌿🍁🌿🍁🌿🍁🌿🍁🌿🍁🌿🍁🌿🍁
የካቲት ፲ /10/


በዚች ቀን ከዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ የዕልፍዮስ ልጅ የከበረ ሐዋርያ ያዕቆብ በሰማዕትነት ሞተ።

ይህም ሐዋርያ በብዙ ሀገሮች ውስጥ ከሰበከ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ ወደ ምኵራብም ገብቶ የክብር ባለቤት የጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ሃይማኖት በግልጥ አስተማረ።

አይሁድም ደሙ በእኛ ላይ ይሁን ብለው ከሕዝብ መካከል ነጥቀው ወሰዱት ለሮም ንጉሥ እንደራሴ ለንጉሥ ቀላውዴዎስም አቀረቡትና ይህ ሰው ስለ ቄሣር ሳይሆን ስለ ሌላ ንጉሥ ይሰብካል ብለው ወነጀሉት ንጉሡም በሰማ ጊዜ በደንጊያ እንዲወግሩት አዘዘ አይሁድም ፈጥነው ወገሩት ነፍሱንም በጌታችን እጅ ሰጠ ምእመናንም ሥጋውን ገንዘው ቀበሩት።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በሐዋርያ ያዕቆብ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ምንጭ፦ መጽሐፈ ስንክሳር

@efeson_2

💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫
የካቲት ፲፩ /11/


በዚች ቀን የሮሜ ሊቀ ጳጳሳት የከበረ አባት በላትያኖስ በሰማዕትነት ሞተ።

ይህም ቅዱስ ብልህና አዋቂ የሆነ ታላቅ ተጋድሎን የሚጋደል ነው በሮሜ ሀገርም ሊቀ ጵጵስና ተሹሞ በቅዱስ ጴጥሮስ ወንበር ላይ ዐሥራ ሁለት ዓመት በሰላም ኖረ። ሕዝቡን የቀናች ሃይማኖትን እያስተማራቸው ሳለ መኰንኑ ፊሊጶስ በንጉሥ ቀላውዴዎስ ላይ ተነሥቶ በገደለው ጊዜ በርሱ ፈንታ ነገሠ በምእመናንም ላይ ታላቅ መከራን አመጣ በዚህ በንጉሥ ዳኬዎስ እጅ ብዙዎች በሰማዕትነት ሞቱ።

በዘመኑም ሰባት ሰዎች ከእርሱ ሸሹ ሦስት መቶ ሰባ ሁለት ዓመት ተኝተው ነቁ እርሱም በኤፌሶን ከተማ መስጊድ ሠርቶ በውስጡ ጣዖታትን አኖረ ሰዎችን ሁሉ ለጣዖታት እንዲሠዉ አስገደዳቸው ለጣዖታት ያልሠዉትንም ገደላቸው።

ይህ የከበረ በላትያኖስም የጣዖታት አምልኮን እንደሚቃወም ሕዝቡም በክብር ባለቤት በክርስቶስ ሃይማኖት ይጸኑ ዘንድ እንደሚያስተምር ንጉሥ በሰማ ጊዜ ወደ ሮሜ አገርልኮ ወደ ኤፌሶን ከተማ አስመጣውና ለጣዖታት እንዲሠዋ ለመነው።

እርሱ ግን ቃሉን አልሰማም ተሣለቀበት አማልክቶቹንም ረገመ እንጂ። ንጉሡም ተቆጣ አንዲት ዓመት ያህልም ጽኑዕ ሥቃይን አሠቃየው ማሠቃየቱንም በሰለቸ ጊዜ በሰይፍ ራሱን ቆረጠው የምስክርነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑርለዘላለሙ አሜን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

@efeson_2

💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫
1
የካቲት ፲፫ /13/


በዚች ዕለት የከበረ አባት የእስክንድርያ አገር ሊቀ ጳጳሳት ጢሞቴዎስ አረፈ።

እርሱም ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ሠላሳ ሁለተኛ ነው ይህንንም አባት ስለ ቀናች ሃይማኖት ብዙ መከራና ችግር ደርሶበታል እንዲህም ሆነ በዚያን ወራት የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ሳዊሮስ ወደ ግብጽ አገር መጣ እርሱም ከዚህ አባት ጢሞቴዎስ ጋር ምእመናንን እያጽናና ከሀገር ወደ ሀገር ከገዳም ወደ ገዳም ከቦታ ወደ ቦታ የሚዘዋወር ሆነ።

በዚህም አባት ጢሞቴዎስ ዘመን ከቊስጥንጥንያ የመጡ ክፉዎች ሰዎች በግብጽ አገርተገለጡ እነርሱም የክርስቶስን ተዋሕዶ ምትሐት በሚያደርግ መከራውንና ትንሣኤውንም በሚክድ በረከሰ በአውጣኪ ትምህርት የሚያምኑ ናቸው ይህም አባት አውግዞ ከግብጽ አገር አሳደዳቸው።

ዳግመኛም በዘመኑ ምእመን ንጉሥ አንስጣስዮስ አረፈና በርሱ ፈንታ ኬልቄዶናዊ መናፍቅ ዮስጣትያኖስ ነገሠ እርሱም በአባ ጢሞቴዎስ ፈንታ ሊናርዮስን ሊቀ ጵጵስና ሾመው ሃይማኖታቸው የቀና ምእመናንን ሁሉ በኬልቄዶን ግባኤ ወደተወሰነ ሃይማኖት ሊመልሳቸው ወዶ በቍስጥንጥኒያ ጉባኤ ሰብስቦ የአንጾኪያውን ሊቀ ጳጳሳት አባ ሳዊሮስን ከኤጲስቆጶሳቶቹ ጋር አስመጣው።

በኬልቄዶን ጉባኤ በተወሰነች በተበላሸች ሃይማኖቱ ያምኑ ዘንድ አስገደዳቸው እነርሱ ግን አልተቀበሉትም ትእዛዙንም አልሰሙም ስለዚህም ሃይማኖታቸው በቀና ምእመናን ሁሉ ታላቅ መከራ አደረሰባቸው። ይህም አባት ጢሞቴዎስ በመንበረ ሢመቱ ዐሥራ ሰባት ዓመት ኑሮ በሰላም አረፈ።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

@efeson_2

💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫
1
🍁️🍁️🍁️🍁️🍁️🍁️🍁️🍁️🍁️

"ጸሎት በሕይወት ማዕበል ውስጥ መጠጊያ ወደብ ማእበል ለሚያንገላታቸው መልሕቅ የድሃው ሐብት የባለጸጋው ደህንነት የታማሚው መዳኛ ወይም ጤና ማግኛ ነው ጸሎት መጥፎ ነገሮችን ያስወግዳል መልካሙን ይጠብቃል።"

                              🍁️ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ

"ከንቱ ውዳሴ በመንገድ ሁሉ የሚከተልህ የተሸሸገና ጭንብል ያጠለቀ ሌባ ነው። አሳዳጅ በመሆኑ በጣም ደኅንነት በሚሰማህ አሳቻ ሰዓት ሳታውቀው ይዘርፈሀል፤ ይገድልህማል። "

                             🍁️ቅዱስ ጎርጎርዮስ

"ብርሃን ወደ አንድ ቤት ውስጥ ሲገባ ጨለማን እንደሚያስወግድ ሁሉ፤ እግዚአብሔርን መፍራት ወደ አንድ ሰው ልብ ሲገባም አለማወቅን (በኃጢአት የሚወድቅባትን) ያስወግዳል።"

                           🍁️አባ እንጦንስ

"ካህኑን እንደ መንፈሳዊ አባትነቱ እየው፤ ልክ በሽተኛ የተሸፈኑ ቁስሎችን ለሐኪም እንደሚያሳይና እንደሚፈውስ ምስጢሮችህን በግልጽ ንገረው”

                         🍁️ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ።


"ሰይጣን ክርስቶስ በልብህ ውስጥ ያለ መሆን አለመሆኑን ያውቃል፡፡ ይኸውም ስትቆጣ ወይም ስትጮህ ወይም የማይረቡ ከንቱ ነገሮችን ስትናገር ሲያይህ ጠላት በአንተ ዘንድ እግዚአብሔር እንደሌለ ያውቃል ያን ጊዜ በውስጥህም በውጭህም ያለውን ሳይቀር ይገዛል ፤ መዝጊያ እንደሌለው ቤት እንደ ክፉ ሌባ ይገባና ውስጥህን ይበረብረዋል፡፡"

                          🍁️ ቅዱስ ባስልዮስ


"ጥላቻን በልቡ ውስጥ የሚሸሽግ ሰው እባብን በጭኑ ላይ የሚያስቀምጥን ሰውን ይመስላል።
ጭስ ንቦችን እንደሚያባርር ሁሉ ጥላቻም በልብ ውስጥ የተቀመጠን እውቀት ያጠፋል፡፡"

                        🍁️ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ


ሰው ሆይ! ጻድቅ መሆንን ትወዳለህን? አዎን ትለኝ እንደሆነ፥ እንግዲያውስ ለራስህ ንፉግ ለሌላው ግን ቸር ሁን፡፡

                     🍁️ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ


@efeson_2

🍁️🍁️🍁️🍁️🍁️🍁️🍁️🍁️🍁️
🌿🍁🌿🍁🌿🍁🌿🍁🌿🍁🌿🍁🌿🍁🌿🍁


እንኳን #ለኢትዮጵያውያን_ጻድቅ ውኃ ከዓለት ድንጋይ ላይ እያፈለቁ አሕዛብን ሁሉ እያስተማሩ ያጠምቁ ለነበረ፤ ኅብስትም ከሰማይ እየወረደላቸው ሕዝቡን ያቆርቡ ለነበረ ለታላቁ አባት #ለአቡነ_ክፍለ_ማርያም_ዘድባጋ ከዚህ ዓለም እንደነ #ቅዱሳን_ሄኖክና_ኤልያስ ከሞት ለተሰወሩበት በዓልና #ለአባ_ገብረ_መርዓዊ_ዘአግዶ_ገዳም ለመታሰቢያ በዓላቸው እግዚአብሔር አምላክ በሰላም አደረሰን።

@efeson_2

🌿🍁🌿🍁🌿🍁🌿🍁🌿🍁🌿🍁🌿🍁🌿🍁
የካቲት ፳፩ /21/


በዚችም ዕለት የከበረ የሐዋርያው የጳውሎስ ደቀ መዝሙር የሆነ ቅዱስ አናሲሞስ በሰማዕትነት አረፈ።

ይህም ቅዱስ አስቀድሞ ፊልሞና ለሚባል ለሮሜ ሰው አገልጋይ ነበር። ሰይጣን  የአናሲሞስን ልቡ ለወጠና የጌታውን ገንዘብ ሰርቆ  ወደ ሮሜ ሔደ።

በእግዚአብሔርም ፈቃድ ወደከበረ ሐዋርያ ጳውሎስ ሔደ ትምህርቱንም ሰምቶ በክብርባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመነ ለቅዱስ ጳውሎስም ደቀ መዝሙሩ ሆነ። ነገር ግን የጌታውን ገንዘብ በመስረቁ በአናሲሞስ ልብ ጽኑ ሀዘን አደረ ለሐዋርያ ጳውሎስም የሠራውን ሁሉ ነገረው ሐዋርያ ጳውሎስም አትፍራ ልብህም አይዘን አለው የቀድሞ ጌታው በሰላም እንዲቀበለው ወደ ፊልሞናም መልእክትን ጻፈለት ይቺም ስለ አናሲሞስ የጻፋት ከመልእክቶቹ አንዲቱ ናት።

ይህ የከበረ አናሲሞስም ወደ ፊልሞና ወደ ጌታው በደረሰ ጊዜ በማመኑና በመጸጸቱ ደስ አለው ሐዋርያው እንዳዘዘውም ተቀበለው። ከዚህም በኋላ ሸኙትና ወደ ሮሜ አገር ተመለሰ በሰማዕትነት እስከ ሚሞትበት ጊዜ ሐዋርያ ጳውሎስን የሚያገለግልው ሆነ።

ከሐዋርያው ጳውሎስም የምስክርነት ሞት በኋላ የንጉሥ ጭፍራ ይህን ቅዱስ ይዞ ወደ አንዲት ደሴት ሰደደው በዚያም ያሉትን አስተምሮ አጠመቃቸው። ያ ጭፍራም ይህን በሰማ ግዜ በብዙ አሰቃይቶት በዚች ቀን ምስክርነቱንም ፈጸመ። የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ምንጭ፦ መጽሐፈ ስንክሳር

@efeson_2

💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫
🌿🍁🌿🍁🌿🍁🌿🍁🌿🍁🌿🍁🌿🍁🌿🍁


እንኳን ለከበሩ #በቅዱስ_ጳውሎስ ትምህርት ላመኑ #ለቅዱሳን_አውሳንዮስ_ፊልሞ፣ ለድንግል #ቅድስት_ሉቅያ ሰማዕትነት ለተቀበሉበት ለዕረፍታቸው በዓል፣ ለከበረ #ሐዲስ_አባ_እንጦኒ ይህም ረውሕ ለሚባለው ሰማዕትነት ለተቀበለበት ለዕረፍቱ በዓልና ከግብጽ አገር ከእስሙናይን አውራጃ ለሆነ ዐሥራ ስምንቱ ዓመት ቆሞ ሳይቀመጥ ለጸለየ #ለአባ_አቡፋ ለዕረፍት በዓል በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ ከሮሜ አገር #ከዲያቆን_ቶና ከአገረ ቊስ #ሚናስ_ከጋዛ_ይልማድዮስ በሰማዕትነት ከዐረፉ፣ #ከደማይልናልና_ከርጊኖስ ከመታሰቢያቸው እግዚአብሔር አምላክ  ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።

@efeson_2

🌿🍁🌿🍁🌿🍁🌿🍁🌿🍁🌿🍁🌿🍁🌿🍁
የካቲት ፳፮ /26/


በዚች ዕለት ዖዝያ ይባል የነበረ ዕውነተኛ ነቢይ ሆሴዕ አረፈ። ዳግመኛም ይህ ነቢይ በአራቱ የይሁዳ ነገሥታት ዘመን ትንቢት ተናገረ። እሊህም ዖዝያን፡ ኢዮአታም፡ አካዝ፡ ሕዝቅያስ ናቸው።

በትንቢቱም ድንቆች ሥራዎችን ተናገረ የእስራኤልንም ልጆች ገሠጻቸው የአመንዝራ ልጆች ብሎም ጠራቸው እግዚአብሔርም ቍጣውን ከእርሳቸው እንደማይመልስ አስረዳቸው። እንዲህም አለ የእስራኤል ልጆች ቍጥራቸው እንደማይሠፈርና እንደማይቈጠር የባሕር አሸዋ ቢሆን ከጥቂት በቀር አይተርፍም አለ። ስለ አሕዛብም በእግዚአብሔር ማመን ተናገረ እንዲህም አለ እኔ ወገኖቼ ያልሆኑትን እጠራቸዋለሁ እነርሱም ይሰሙኛል።

ዳግመኛም ስለ መድኃኒታችን መከራ መቀበልና በከበረ ደሙ ስለ መዳናችን ስለ ትንሣኤውም እንዲህ ብሎ ተናገረ። እሱ በመከራ ገርፎ ያድነናል እርሱም በመከራ አቍስሎ ይቅር ይለናል ሲያድነንም በሁለተኛው ቀን ነው በሦስተኛውም ቀን ድነን በሱ ፊት እንነሣለን እግዚአብሔርንም አውቀን እንከተለው ዘንድ ስለ ሞት ሥልጣን መሻር ስለ መቃብርም መሸነፍ እንዲህ ብሎ ትንቢት ተናገረ ሞት ይዘህ ማስቀረትህ መቃብርስ ድል መንሳትህ ወዴት ነው ትንቢትን እየተናገረ ሰባ ዓመት ያህል ኑሮ በበጎ ሽምግልና አረፈ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑርለዘላለሙ አሜን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ምንጭ፦ መጽሐፈ ስንክሳር

@efeson_2

💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫
🌿🍁🌿🍁🌿🍁🌿🍁🌿🍁🌿🍁🌿🍁🌿🍁

እንኳን #በታላቁ_በቈስጠንጢኖስ_ዘመን ለነበረ ለከበረ አባት ለአንጾኪያ አገር ሊቀ ጳጳሳት ትምህርቱ በዓለም ለመላ ቁጥሩ #ከሠለስቱ_ምዕት ለሆነ #ለታላቁ_አባት_ለአባ_አንስጣስዮስ ለዕረፍት በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰበው፦ #ከቸሩ_መድኃኔዓለም_ከስቅለቱ መታሰቢያ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።


@efeson_2

🌿🍁🌿🍁🌿🍁🌿🍁🌿🍁🌿🍁🌿🍁🌿🍁
📣📣ዜና ዕረፍት

ለበርካታ ዓመታት ከገጠር እስከ ከተማ ከሀገር ውስጥ እስከ ውጭ ሀገራት ቅዱሱን ሕያው ወንጌል በታማኝነትና በትጋት ያለዕረፍት ያገለገሉት መምህር ዘለዓለም ወንድሙ በትናንትናው ዕለት ከድካመ ሥጋ ዐረፉ።

ኦ እግዚኦ አዕርፍ ነፍሰ ገብርከ ወልደ ሰማዕት
ሀገረ ሕይወት መንግስተ ሰማያት ያውርስልን፤ በአብርሃም በይስሐቅ በያዕቆብ ዕቅፍ ያኑርልን፤
ለቤተሰቦቻቸው ለወዳጅ ዘመዶቻቸው እንዲሁም ለኦርቶዶክሳውያን በሙሉ መጽናናትን እንመኛለን።

📣የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ አገልግሎት

@efeson_2

📣📣📣📣📣📣
🌿🍁🌿🍁🌿🍁🌿🍁🌿🍁🌿🍁🌿🍁
እንኳን #ለኢትዮጵያዊቷ_ጻድቅ በአጤ (ዐፄ) #ሱሱንዮስ አንገቷን ተሰይፈ ሰማዕት ከሆነች በኋላ #ቅዱስ_ሚካኤል ገነትንና ሲኦልን አሳይቶ 14ቀን በሰማያዊት ኢየሩሳሌም ከተቀመጠች በኋላ እንደገና እንደተኛ ወይም ከእንቅልፉ እንደሚነቃ ሰው ከሞት ተነስታ ብዙ ገዳማትን (ታላቁን ገዳም ራማ ኪዳነ ምሕረትን) ላቀናች #ለታላቋ_ለጻድቅ_ወሰማዕት_ለቅድስት_ፍቅርተ_ክርስቶስ (እመ ምዑዝ) ለዕረፍቷ በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።

@efeson_2

🌿🍁🌿🍁🌿🍁🌿🍁🌿🍁🌿🍁🌿🍁
1
መጋቢት ፫ /3/


በዚች ቀን በእስክንድርያ ለተሾሙ ሊቃነ ጳጳሳት ሃምሣ ስምንተኛ የሆነው የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ብፁዕ ወቅዱስ አባ ቆዝሞስ አረፈ።

ይህም አባት እውነተኛና ንጹሕ የዋህ ርኅራኄው የበዛ የቤተ ክርስቲያንንም መጻሕፍትና ትርጓሜያቸውን የሚያውቅ ነበር።

እግዚአብሔርም በወንጌላዊው ማርቆስ መንበር ላይ ለሊቀ ጵጵስና ሹመት መረጠው የግብጽ ንጉሥ መቅትር በነገሠ በአሥራ ስምንት ዓመት ሊቀጳጳሳት ሁኖ ተሾመ። ጴጥሮስ የሚባል ጳጳስን ለኢትዮጵያ አገር ሹሞ ነበር ። አባ ጴጥሮስም ወደ ኢትዮጵያ በደረሰ ጊዜ ጥቂት ዘመን በሰላም ኖረ።

በዚያም ሳለ ሰይጣን ያደረባቸው ከሶርያ የመጡ ሁለት መነኮሳት አባ ቆዝሞስ በሾመው በአባ ጴጥሮስ ላይ ሴራ ሰርው በእርሱ ፈንታ እነርሱ ተሾሙ። ከግዜም በኋላ በእግዚአብሔር ቸርነት ሴራቸው ታወቀ የኢትዮጲያ ንጉስም አባ ጴጥሮስን ያመጡት ዘንድ አዘዘ ነገር ግን ሙቶ አገኙት ይሕንንም አባ ቆዝሞስ ሲሰማ በጣም አዘነ። በዚህም ምክንያት ለሰማንያ አራት ዓመታት ያህል ለኢትዮጵያ ሰዎች ጳጳስ ተሹሞ አልተላከላቸውም።

አባ ቆዝሞስም እጅግ ሸመገለ የሹመቱም ዘመን ደኀንነትንና ሰላምን የተመላ ነበር። በወንጌላዊ ማርቆስ ወንበርም አሥራ ሁለት ዓመት ኖረ በሰላምም አረፈ እግዚአብሔርበጸሎቱ ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ምንጭ፦ መጽሐፈ ስንክሳር

@efeson_2

💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫
መጋቢት ፬ /4/


በዚህችም ቀን የከበረና የተመሰገነ መኰንን ሐኑልዮስ ከጵንፍልያ አውራጃ ብርግያ በምትባል ከተማ በሰማዕትነት አረፈ።

ይህንንም ቅዱስ ምስጋና ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ስለ መውደዱና እርሱንም ስለ ማምለኩ ከዲዮቅልጥያኖስ ተልኮ የመጣ ብርይንኮስ የተባለ መኰንን ያዘው።

በመኰንኑም ፊት በቆመ ጊዜ ምስጋና ይግባውና የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሃይማኖት ከፍ ከፍ ባሉ ቃላት አብራርቶ ገለጠ። ብዙ ምስጋናዎችንም ለእግዚአብሔር አቀረበ የረከሱ ጣዖታትንም ረገማቸው።

መኰንኑም በዕንጨት መስቀል ላይ ይሰቅሉት ዘንድ አዘዘ ስለ ከበረ ስሙም ምስክር ይሆን ዘንድ ስለ አደለው ምስጋና ይግባውና ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን አመሰገነው። ከዚያም ምስጋና ይግባውና በእግዚአብሔር እጅ ነፍሱን ሰጠ። ጸሎቱና በረከቱ ከሁላችን ጋራ ለዘላለም ይኑር አሜን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ምንጭ፦ መጽሐፈ ስንክሳር

@efeson_2

💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫
1