Ethiopian Coffee and Tea Authority
6.03K subscribers
5.9K photos
30 videos
67 files
372 links
Ethiopian Coffee and Tea Authority
Download Telegram
አርሶ አደር ላኪዎች የገበያ ትስስር መፍጠር በሚችሉበት እና የመደራደር አቅማቸውን በሚያሳድጉበት ቴክኒክ ዙሪያ ጠቃሚ ስልጠና ተሰጠ!!
ታህሳስ 24∕2016 ዓ.ም
ሀዋሳ
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን፤ አርሶ አደር ላኪዎች አለማቀፍ የቡና ገበያውን መቆጣጠር እና የገበያ ትስስር መፍጠር በሚችሉበት እንዲሁም የመደራደር አቅማቸውን ማሳደግ በሚያስችላቸው ቴክኒክ ዙሪያ በዛሬው እለት በሀዋሳ ከተማ ጠቃሚ ስልጠና ሰጥቷል∶∶ አርሶ አደሮቹ የተውጣጡት ከኦሮሚያ፣ ሲዳማ፣ ደቡብ እንዲሁም ማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ሲሆን ቁጥራቸው ደግሞ ከመቶ የሚልቅ ነው∶∶
ስልጠናውን በቦታው ተገኝተው የከፈቱት ክቡር አቶ መስፍን ቃሬ የሲዳማ ክልል ቡናና ፍራፍሬ ልማት ዋና ዳይሬክተር እንዲሁም ክቡር አቶ ሬድዋን ከድር የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቡናና ቅ∕ቅመም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ናቸው∶∶
ክቡር አቶ መስፍን ሰልጣኞችን እና ዝግጅቱን ያስተባበሩትን አካላት እንዲሁም አሰልጣኙን እንኳን ደህና መጣችሁ “ዳኢ ዊሾ“ ካሉ በኋላ፤ ቡና ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን ከፖለቲካዊ፣ አካባቢያዊ እንዲሁም ማህበራዊ ህይወት ጋር በቀጥታ የተቆራኘ ከመሆን ባሻገር የአገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ግኝት መሰረት እና ኢትዮጵያ ካላት ህዝብ ቁጥር ሩብ ያህሉ የኑሮ መሰረት መሆኑን ባስተላለፉት መልእክት ገልጸዋል∶∶ ቀደም ባለው ጊዜ ቡና በቂ ትኩረት ስላልተሰጠው እና በበርካታ ውስብስብ ችግሮች የተጠላለፈ ቢሆንም አሁን ያለው መንግስት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ትኩረት በመስጠት የተለያዩ አዋጅ፣ ደንብ፣ መመሪያዎች እና የሪፎርም ተግባራት በመከናወናቸው አገሪቱም ሆነ አርሶ አደሩ የተሻለ ተጠቃሚ ቢሆኑም የታሰበው ደረጃ ላይ ለመድረስ የበለጠ ምርት እና ምርታማነትን መጨመር፣ ጥራትን መጠበቅ እንዲሁም የገበያ መዳረሻዎችን ማስፋት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል∶∶ ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ የመሰለ ውድድር በአገራችን መደረጉም በርካታ ሚሊየነር የቡና አርሶ አደሮችን መፍጠር እንዳስቻለና ከፍተኛ መነቃቃትንም እንደፈጠረ ተናግረዋል∶∶
ክቡር አቶ ሬድዋን በበኩላቸው አርሶ አደር ላኪዎች በተፈጠረላቸው ምቹ ሁኔታ የላኪነት ፈቃድ አውጥተው በዚህ ደረጃ መገኘታቸው አስደሳች መሆኑን ጠቅሰው አገሪቱ ባስቀመጥችው ግብ መሰረት በ2022 በአለም 2ኛዋ ቡና አምራች አገር እንድትሆን ለማድረግ የአርሶ አደሩ ሚና ወሳኝ እንደሆነ ተናግረዋል∶∶ ይህን ግብ ከዳር ለማድረስ ከፌዴራል ጀምሮ በየደረጃው ባለው የመንግስት እርከን ሰፊ ስራ እየተሰራ እንደሆነና በቡና እሴት ሰንሰለቱ የሚገኙ ተዋናዮችም የየድርሻቸውን መወጣት እንደሚገባቸው ጥሪ አቅርበዋል∶∶ ቡናችን ተፈጥሯዊ በመሆኑና የተፈጥሮ ማዳበሪያን ብቻ በመጠቀም የሚለማ በመሆኑ ሰፊ የገበያ እድል እንዳለው እና ጥራትን መጠበቅ እና ምርታማነትን ማሳደግ እስከተቻለ ድረስ እነብራዚል እና ኮሎምቢያ ተርታ ለመሰለፍ የሚያዳግት ነገር አለመኖሩን አስረድተዋል∶∶
ከሀላፊዎች መክፈቻ ስነስርአት በኋላ የአርደንት ኮፊ ማኔጂንግ ዳይሬክተር እና ባለቤት አቶ አሸናፊ አርጋው አለማቀፍ የቡና ገበያ ሁኔታ፣ ኢትዮጵያ ያላት የቡና መልማት ወርቃማ እድል፣ የገበያ ትስስርን እንዴት በቀላሉ መፍጠር ይቻላል? የኮንትራት አፈጻጸም ዘዴ እንዲሁም አርሶ አደር ላኪዎቹ የመደራደር አቅማቸውን በሚያሳድጉበት ቴክኒክ ዙሪያ ረዘም ያለ፣ እጅግ ሳቢ እና ጠቃሚ ስልጠና ሰጥተዋል∶∶
ስልጠናው እንደተጠናቀቀ አርሶ አደር ላኪዎቹ በርካታ ሙያዊ ጥያቄዎችን አቅርበው ከመድረክ በቂ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው የተደረገ ሲሆን ይህን መሰል ህይወታቸውን መቀየር የሚያስችል ስልጠና በመሰጠቱ በእጅጉ መርካታቸውን እና ለሌሎችም መሰሉ እድል ሊመቻች እንደሚገባ ጠቁመዋል∶∶ ለዚህም ባለስልጣን መ∕ቤቱን እና አቶ አሸናፊን እጅግ ከልብ በመነጨ ስሜት አመስግነዋል∶∶
አለም አረቢካ ቡናን የሚያደንቅበት ምስጢር ምን ይሆን?

ስብስብ እና ትርጉም: በሳህለማርያም

አረቢካ ቡና በሚከተሉት ዋና ዋና ምክንያቶች በዓለም ዙሪያ ከፍተኛ አድናቆት አለው።
1. ውስብስብ እና ስስ/የማይከብድ/ቀለል ያለ ጣዕም፡- አረቢካ ቡና እንደ Robusta ካሉ የቡና አይነቶች በበለጠ የበለፀገ እና ውስብስብ ባህርይ ያለው ጣዕም አለው። አበባ አበባ የሚል፣ ፍራፍሬ ፍራፍሬ የሚል፣ ቸኮሌት ቸኮሌት የሚል፣ ጤና አዳም ጤና አዳም የሚል፣ የደረቀ ለውዝ አይነት ጣዕም፣ ወይን ወይን የሚል፣ የሚንት እና የሌሎች ቅመማ ቅመሞች አይነት በውስጥ ደስታን እና ልዩ ቃናን መፍጠር ይችላል።
2. ምጥን አሲድ፡- አረቢካ ቡና አብዛኛውን ጊዜ ከፍ ያለ የአሲድነት መጠን ቢኖረውም ሚዛኑን የጠበቀ እና ደስ የሚያሰኝ ስሜት ያለው እንጂ እንደ ሮቡስታው የሚጎፈንን አይነት ጣዕም በምላስ የሚያስቀር ባለመሆኑ ተወዳጅ እና መንፈስን የሚያድስ ነው ይሉታል።
3. 3. ቀለል ያለ እና ሲጠጡት የማይከብድ፡- ፡- ከሮቡስታ ጋር ሲወዳደር አረቢካ ብዙ ጊዜ ቀለል ያለ አልኮል ስላለው ቡናን የማይወዱትን ጨምሮ ለመጠጥነት ቀላል፣ የማይከብድ እና ለብዙ ሰዎች ተስማሚ የሆነ ነው ይባልለታል።
4. ረዥም ጊዜ በአፍ ውስጥ መቆየት የሚችል ጣዕም፡- አረቢካ ቡና ብዙ ጊዜ በአፍ ውስጥ ረዥም እና አስደሳች የሆነ ቃናን ይተዋል፣ ከእያንዳንዱ ፉት በኋላ እርካታ እየጨመረ ይሄዳል፡፡
5. ዝቅተኛ ካፌይን፡- አረቢካ ከRobusta ያነሰ የካፌይን ይዘት ስላለው የልብና የደም ሥር (cardiovascular system) የተረጋጋ እንዲሆን ስለሚያደርገው ለካፌይን ልዩ ስሜታዊ ለሆኑ ሰዎች የበለጠ ተስማሚ ሊሆን ይችላል።
6. የአካባቢ እና የአየር ንብረት ሁኔታዎች፡- አረቢካ ብዙ ጊዜ የሚበቅለው እርጥበታማ እና ብዙም ለፀሀይ ብርሀን ገላጣ ባልሆነ ቦታ ላይ ሲሆን አፈሩም በተለያዩ ማዕድናት የበለፀገ ነው። በእነዚህ ሁኔታዎች ቡናዎች ተወዳጅ እና ልዩ ጣዕም እንዲኖራቸው ከማድረግ ባሻገር ለዘላቂ ግብርና እና አካባቢያዊ ስነምህዳሩን ምቹ ከማድረግ አንጻር/ To promote the development of distinctive flavors but also create a diverse ecosystem that contributes to sustainable agriculture. የሚያበረክተው አስተዋጽዖ የላቀ ነው።
7. ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ፡- አረቢካ ቡና ብዙውን ጊዜ በአለም አቀፍ ገበያው ላይ ተወዳጅ አን ተመራጭ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ብልሆች ሆነው ቡናቸውን በልዩ እንክብካቤ፣ በከፍተኛ ጥራት እና መጠን ለሚያዘጋጁ አዱኛን/ተዝቆ የማያልቅ ሀብትን መሰብሰብ የሚያስችላቸው ከመሆኑ ሌላ ለአገራቸውም የውጭ ምንዛሬ የላቀ አስተዋጽዖ ለማበርከት ያስችላቸዋል።
8. የተለያዩ አዘገጃጀት ሂደቶች/Processing፡- የአረቢካ ቡና ከተመረተ በኋላ በተለያዩ ዘዴዎች የታጠበ፣ ደረቅ፣ ሀኒ፣ አናሮቢክ፣ ካርቦኒክ ወዘተ. በሚል በተለያየ ጣዕም እና ልዩ ቃና በማዘጋጀት ለቆዪዎች እና ተጠቃሚዎች በማድረስ በፍቅር እንዲጠጣ ይደረጋል፡፡ ይህ ሁኔታ መገኛ የሆንንበት አረቢካ ቡናችንን ከሌሎች የተለየ እና ማራኪ ያደርገዋል።
የኢትዬጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን በቡና ግብይት ዙሪያ በጅማ ከተማ ስልጠና እየሰጠ ይገኛል። ስልጠናውን እየወሰዱ የሚገኙት ከጅማ፣ ቡኖ በደሌ፣ ኢሉባቦር ዞኖችና እንዲሁም ከደቡብ ምዕራብ ኢትዬጵያ የመጡ አርሷደር ላኪዎች ናቸው። ይኸው ስልጠና ከቀናት በፊት በሐዋሳ ከተማ ለአርሷደር ላኪዎች እንደተሰጠ የሚታወስ ነው።
ስፔሻሊቲ ቡና ምንድነው? ስፔሻሊቲ ቡና ብለን ከምንጠራው ስያሜ በስተጀርባ ያለው እውነታ!! ለቅምሻ ያህል….
ሳህለማርያም ገ/መድህን
ስፔሻሊቲ ብለን ስንል የተለየ፣ የተመረጠ፣ ደረጃው ከፍ ያለ ወይም ባለ ዝና የሚል እሳቤ ወደ እዝነ ልቡናችን ይመጣልናል፡፡ ይህን ቃል ወደ ቡናችን ስናመጣውም ትርጉሙ ከዚህ እምብዛም የተለየ እንዳልሆነ እንመለከታለን፡፡ ነገር ግን የንግዱ/commercial የሆነውን ቡና ሳይሆን (ስፔሻሊቲ ቡና) በመባል የሚታወቀው ከፍተኛ ጥራት ያለው ቡና ከአበቃቀል ጀምሮ እስከ መሰብሰብ፣ ማዘጋጀት፣ ማጓጓዝ፣ ማቀነባበር ብሎም እስከ መቁላት እና ቅምሻ ድረስ ያለውን ሂደት ለመግለጽ/ለማመልከት የሚያገለግል ቃል ነው።
ይህ ቡና በአሁኑ ሰዓት በአለማቀፍ ደረጃ ከሚቀርቡ ቡናዎች አንጻር ያለው ድርሻ 15 በመቶ ሲሆን በፍጥነት በማደግ ላይ የሚገኝ ገበያ ነው፡፡ ከዋጋም አንጻር አሁን ባለው የገበያ መረጃ መሰረት በፓውንድ ከ3-5 ዶላር እየተሸጠ የሚገኝ ቡና ነው፡፡
ልዩ ቡና ልዩ መሆኑ ከሚታወቅባቸው ባህርያት መካከል፤ እንደአለማቀፉ ልዩ ቡናዎች ማህበር Specialty Coffee Association (SCA) ስታንዳርድ «ምጥን በሆነ ሁኔታ በእጅጉን የተለየ ጥፍጥና/ቃና ወይም ጣዕም ያለው መሆኑ ፕሮፌሽናል የሙያው ባለቤት በሆኑት ቀማሾች መረጋገጡ ሲታመን እና ከመቶኛ የሚሰጡት ውጤትም ከሰማንያ አጋማሽ በላይ ያስመዘገቡ መሆን ሲችሉ እንደሆነ ተጠቅሷል።
ስፔሻሊቲ ቡና ከሚለው በስተጀርባ ያለው ታሪክ…
"ልዩ ቡና" የሚለው ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ እ.ኤ.አ በ1974 ኤርና ክኑትሰን በተባለ ሰው "የሻይ እና ቡና ንግድ ጆርናል" እትም ላይ ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ Knutsen ቃሉን የተጠቀመው በተወሰኑ/በታወቁ አካባቢዎች በቅለው፣ ልዩ ባህርይ እና ጣዕም ኖሯቸው ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን የቡና ዛላ/ፍሬዎችን ለመግለጽ የተጠቀመበት ነው፡፡
ግብይቱ የተጀመረውም ስታር ባክስ በሚባል ኩባንያ አማካይነት እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
በዚያ በኋላ ባሉ ቀጣዮቹ ዓመታት ደግሞ የቡና ኢንዱስትሪው በፍጥነት እያደገ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የልዩ ቡናዎች ገበያ ዕድገትም በዚያው ልክ እድገቱን አስመዝግቧል። በዚሁ መሰረት የሚከተሉት ሁኔታዎችን መሰረት በማድረግ ለልዩ ቡና ስታንዳርድ ለማውጣት እና በዚያ መሰረትም ደረጃ ለመስጠት/ለመገምገም ደረጃዎች እንዲዘጋጁ ተደርገዋል፤

ሀ. የቡናው ጥራት፡- ልዩ ቡና ጥሩ ጣዕም ያለው እና ምንም አይነት/ የተጋነነ እንከን የለሽ መሆን አለበት።
ለ. እንዴት እንደሚመረት፡- ስፔሻሊቲ ቡና ብዙ ጊዜ አካባቢ ጥበቃን እና ሰራተኞችም ፍትሃዊ የስራ ሁኔታ አላቸው ወይ? የሚለውን ጥያቄ በሚመልስ ሁኔታ ላይ ትኩረት አድርጎ በዘላቂነት/ sustainably ይመረታል።
ሐ. ዱካው መታወቅ፡- ልዩ ቡና ብዙ ጊዜ የጠራ መነሻ አለው፣ እያንዳንዱ የቡና ክፍል ከየትኛው ማሳ ተመረተ፣ ምን አይነት እንክብካቤ እና ታሪክ አለው፣ የት/እንዴት ተለቀመ፣ የት/እንዴት ተዘጋጀ፣ የት/እንዴት ተጓጓዘ ወይም የት/እንዴት ደረሰ የሚለውን ጥያቄ በግልጽ ሊመልስ ይችላል።
መ. ደረጃ አሰጣጥ፤ የስፔሻሊቲ ቡና ማህበር (SCA): በልዩ የቡና ኢንዱስትሪ ውስጥ ግንባር ቀደም የሙያ ድርጅት በመሆኑ የSCA አጠቃላይ የቡና ደረጃ አሰጣጥ ስነ ስርዓትን መሰረት አድርጎ ደረጃ አሰጣጡ ይከናወናል፡፡
ሠ. ማሸግ እና ነጥብ መስጠት፡- ቡና ደረጃውን/ስታንዳርድ በጠበቀ ሁኔታ መጠቅለያ ዘዴ/እሸጋ ተጭኖ ከ100 ነጥብ መለኪያ ሲመዘን ስፔሻሊቲ ቡና ነው ለመመባል 80 ነጥብ ከረገጠ እና ከዚያ በላይ ከሆነ እንደ ልዩ ቡና/ specialty ቡና ይቆጠራል።
አስደሳች ዜና!! የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን  ለመጀመርያ ግዜ በአፍሪካ ፋይን ኮፊ አሶስዬሽን እና በኢንተር አፍሪካ ኮፊ ኦርጋናይዜሽን የጋራ ጥምረት  የሚከበረውን የመጀመርያው "የአፍሪካ የቡና ሳምንት በኢትዮጵያ" እና  20ኛው የአፍሪካ ፋይን ኮፊ አሶስዬሽን ኮንፈረንስና ኤግዚቢሽን  ከጥር 28 እስከ የካቲት 2/2016 ዓ.ም በመዲናችን አዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ያካሄዳል፡፡
በዝግጅቱ ከ600 በላይ ታዳሚዎች ተሳታፊ ይሆናሉ። በመድረኩም ከፍተኛ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገራት የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና ተወካዮች፣ በቡና ልማትና ግብይት ዘርፍ የታወቁ ተመራማሪዎች፣ ባለሙያዎች፣ አለማቀፍ ቡና ገዢዎች እና ታዋቂ ግለሰቦች ይታደማሉ፡፡
የኢትዮጵያ ምድር ያበቀለቻቸው የተለያየ ዝርያ ያላቸው ቡናዎችም ቀርበው ታዋቂ ባለሙያዎች እና እንግዶች እንዲቀምሱት፣ እንዲያጣጥሙት ይደረጋል፡፡
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ይህንን  አለማቀፍ ሁነት ለማከናወን የቅድመ ዝጅግት ስራውን ማጠናቀቁን ስንገልጽ በታላቅ ኩራት ነው፡፡

«የአፍሪካ የቡና ሳምንት በኢትዮጵያ»
ቡናችን ወርቃችን፤ ቡናችን መለያ፣ ክብር እና አንድነታችን!!!
በቡና ማሰልጠኛ ማዕከሉ በዘመናዊ የቡና አቆላል ዙሪያ ስልጠና ተሰጠ
ጥር 15/ 2016 ዓ.ም
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ቡና ምርትና ግብይት ለማሻሻል በሚያደርገው ጥረት በተለያዩ ጊዜያት ሲያደርገው እንደቆየው ሁሉ በዛሬው ዕለትም ከዩኒዶ ጋር በመተባበር ከዚሁ ተቋም ጋር በጋራ ባቋቋመው የቡና ማስልጠኛ ማዕከል ዕሴት የተጨመረበት ቡና ጥራቱን ጠብቆ እንዴት ማዘጋጀት እንደሚቻል ስልጠና ሰጥቷል፡፡
ስልጠናውን የሰጡት በዩኒዶ በኩል ከጣሊያን የመጡና የካበተ ልምድ ያላቸው አሰልጣኘ ሲሆኑ ስልጠናውን የወሰዱት ደግሞ ከቡና ቆዬዎች ማኅበር ለመጡና ሌሎች አጋር አካላት ሲሆን ጉዳዩ የሚመለከታቸው የባለስልጣን መስሪያቤቱ ሰራተኞችም ስልጠናውን እንዲወስዱ የተደረገ ሲሆን 5 ሴቶችና 10 ወንዶች በድምሩ 15 ሰልጣኞች ስልጠናውን ወስደዋል፡፡ ይህ ለሶስት ቀናት የተሰጠው ስልጠና ዕሴት የተጨመረበት ቡና አዘጋገጃጀት ላይ ያለው የዕውቀትና የክህሎት ክፍተት ይዘጋል ተብሎ ታምኖበታል፡፡ ስልጠናው በንድፈሃሳብና በተግባር የተሰጠ ሲሆን በዋናነት በኤሌክትሪክና በጋዝ ማሽኖች እንዴት ጥራቱን ጠብቆ መቁላት ላይ ያለተኮረ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡
ከስልጠና ማዕከሉ እንደተገለጸው ስልጠናው በሶስት ዙር የተሰጠ ስልጠና አንዱ አካል ሆኖ ይህ ሶስተኛው ዙር ስልጠና እንደሆነና መሰል ስልጠና ለዚህ ቀደም በሁለት ዙር እንደተሰጠ አስተውሰዋል፡፡ ሁለቱን ስልጠናዎች አስመልክቶ የባለስልጣኑ የሕዝብ ግንኙነትና ኮምዩኒኬሽን ክፍል በዜና ማስነበቡ ይታወሳል፡፡