ብራና ሚዲያ BRANA MEDIA
355 subscribers
1.3K photos
11 videos
146 files
169 links
Download Telegram
ንባብ ለወሬ

"ንባብ ለህይወት"፣ "ንባብ ለዕውቀት"፣ "ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል"... የሚሉና ሌሎችም ስለ ንባብ የተጠቀሱ ተመሳሳይ አባባሎች አሉ። ማንበብ ግን ለወሬ እንኳ ቢሆን አስፈላጊ ነው። ይህም ከንባብ ጥቅሞች አነስተኛው ደረጃ (minimum of requirement) ነው ማለት ይቻላል። ያነበቡና ሌጣቸውን የሆኑ ሰዎች የሚያነሱት ጨዋታ እንኳ ወዙና ለዛው ለየቅል ነው። የወሬያቸው ጣዕም የእንጨትና የሙዝ ያህል ሆኖ ልዩነቱ በግልፅ ይስተዋላል። ሳሙኤል ቤከር የተባለ ጸሐፊ "ማንበብ የዕውቀት መሠረት ነው። የማያነብ የሚያስበው ያጣል የሚናገረውም ያንሳል" ሲል መናገሩ ምንኛ እውነት ነው..! የማሰላሰል አድማሳችንና ርዕሳችን እንዲሰፋ፣ ንግግራችን ጥልቅ፣ ጥብቅና ማራኪ እንዲሆን ሁነኛው መድኅን ንባብ ነው።

የንባብ ጥም መቁረጫ ምንጮች የሆኑ መጻሕፍት "ንባብ ለህይወት" በሚል ርዕስ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ከዛሬ ሐምሌ 28 እስከ ነሐሴ 2 / 2014 ዓ.ም ድረስ በሚዘልቅ የመጻሕፍት አውደ ርዕይ ይቀርባሉ።

በኤግዚብሽኑ የታሪክ፣ የፍልስፍና፣ የረዥምና አጭር ልብ ወለድ፣ የስነ-ግጥም፣ የሃይማኖት፣ የፖለቲካ፣ የታዋቂ ሰዎች ግለ ታሪክና ሌሎችም መጻሕፍት ለእይታና ለሽያጭ ቀርበዋል። በአውደ ርዕዩ በርካታ መጻሕፍት መደብሮችና ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ስለሚሳተፉበት ከገበያ የጠፉ የቀድሞ መጻሕፍትና በቅርብ ጊዜ ለሕዝብ የተዋወቁ አዳዲስ መጻሕፍትም ይገኛሉ። በ2012 ዓ.ም እና በያዝነው 2014 ዓ.ም ለሕትመት ያበቃኋቸው "ምልሰት" እንዲሁም "የሳንኮፋ ሰንኮፍ እና ሌሎች" የተሠኙ መጻሕፍቶቼ በኤግዚብሽኑ ይገኛሉ።

አንባቢያን አውደ ርዕዩን ጎብኙ... መጻሕፍትን ግዙ... አንብቡ...!
የመጽሐፉ ርዕስ፦ የነገረ መለኮት መግቢያ
የመጽሐፉ አዘጋጅ፦ መምህር ግርማ ባቱ
የመጽሐፉ የገጽ ብዛት፦ 290
የመጽሐፉ ዋጋ፦ 170 ብር
የኅትመት ዘመን፦ 2012 ዓ.ም
መጽሐፉ በአራት ምዕራፎች የተዘጋጀ ነው። የመጽሐፉን መቅድም ያዘጋጀው በመጻሕፍት መቅድም እና መግቢያ ላይ የማናጣው መምህር ብርሃኑ አድማስ ነው። መምህር ብርሃኑ በመቅድሙ ላይ "መልካም ነገር እነሆ" በሚል ርእስ በማቴዎስ ወንጌል 19፥16-17 ያለውን ኃይለ ቃል በማንሳት ስለመልካምነት ካብራራ በኋላ የመጽሐፉን መልካምነት እንዲህ ሲል ያውጃል፦ "የመምህር ግርማ መጽሐፍ፣ በምንጩ፣ በትምህርቱና በምሥጢሩ መልካምነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ በአቀራረቡ ደግሞ በዘመናችን ያለውን የጥናት ወይም የምርምር መንገድ የተጠቀመ መሆኑን መርሣት ተገቢ አይደለም።"
የመጽሐፉ መግቢያ የተዘጋጀው የመጽሐፉ ጸሐፊ በሆኑት በመምህር ግርማ ባቱ ነው። መምህር ግርማ በመግቢያቸው ነገረ መለኮት የምሥራቅ እና የምዕራብ እየተባለ የሚከፈል መሆኑን እና ከምሥራቁ ወገን እኛን ኦሪየንታሎችን ጨምሮ እነ ግሪክ፥ ሩሲያ እና የመሳሰሉት ሲገኙበት በምእራቡ ወገን የሮማ ካቶሊክና እና ልጇ ፕሮቴስታንት እንደሚገኙ ይነግሩናል። እንዲሁም የእኛን የምሥራቁን ነገረ መለኮት "ተማህልሎአዊ" የሚል ሀገራዊ ሥያሜ ይሰጡታል። ይሄም Mystical, Apophatic, Negative Theology የሚባሉት የሚተካ ነው። ተማህልሎአዊ መንፈሳዊነትን እና ምሥጢራዊነትን አስተባብሮ የያዘ መገለጫ ነው። በምናውቀው ምሥጢራዊ እውቀት እና በምንኖረው መንፈሳዊ ሕይወት መካከል ምንም የተሠመረ ድንበር የለም።
ይሄም በሊቁ Viladmir Lossky አገላለጥ ሲገለጥ "The Eastern Tradition has never made a sharp distinction between mysticism and theology; between personal experience of the divine mysteries and the dogma affirmed by the Church."
ተማህልሎአዊ ያሰኘውም እንዲህ ዓይነቱ የነገረ መለኮት ሕይወት ነው። መምህር ግርማ እንዲህ ዓይነቱን ነገረ መለኮት ከምዕራቡ ክርስትና የተሠወረ ነው በማለት በምሥራቅ እና በምዕራቡ የክርስትና ዓለም ያለውን የነገረ መለኮት አቀራረብ(Theological Approach ) ልዩነት በመጠኑ ይነግሩናል።
የኦርቶዶክሳዊው ነገረ መለኮት(Mystical Theology) ትሑት፥ ተማህልሎአዊ፥ አሉታዊ(Negative)፥ መጽሐፍ ቅዱሳዊ፥ ከጥንታውያን የቤተክርስቲያን አባቶች አስተምህሮ፥ ሕይወትና ጽሑፎቻቸው ጋር የተመሳከረ (patristic) እና ባለ ብዙ ምንጭ ነው። በማለት የምሥራቁን የነገረ መለኮት የአቀራረብና የአረዳድ ምሥጢራዊነት ይገልጹታል።
ይሄን Kallistos Ware እንዲህ ይገልጹታል "Orthodox Theology is less systematic and more Mystical in its approach"
የምዕራቡ የነገረ መለኮት አቀራረብ ደግሞ ሳይንሳዊ፥ ፍልስፍና መር፥ አዎንታዊ(cathaphatic) ማለትም ከሰው አቅም በላይ የሆኑትን መለኮታዊ ምሥጢራት ጭምር ደፍሮ የሚበይን እና በአጥኚው ግለሰብና በሚጠናው እውነት መካከል የአጥኚና የተጠኚ ግንኙነት(subject - object relationship) የፈጠረ ነው።
በማለት በሁለቱ የነገረ መለኮት አቀራረቦች መካከል ያለውን ልዩነት ይነግሩንና ከሁለቱ መካከል ኦርቶዶክሳዊ የሆነውንና መጽሐፉም የቀረበበትን ተማህልሎአዊውን ነገረ መለኮት በመግቢያችው በደንብ ያስተዋውቁናል።
የመጽሐፉ የመጀመርያው ምዕራፍ ተማህልሎአዊ ነገረ መለኮት(Mystical Theology) በሚል ርዕስ ይጀምራል። በዚህ ርዕስ ሥር ልክ እንደ ኦሪቱ የዘፍጥረት መጽሐፍ ስለሀለዎተ እግዚአብሔር (Existence of God) በመናገር ይጀምራል።
"ክርስቲያናዊ ነገረ መለኮት በሀልዎተ እግዚአብሔር ላይ ባለ ፍጹም እምነት ይጀምራል" በማለት በኦርቶዶክሳዊው በነገረ መለኮት ትምህርት ሀለዎተ እግዚአብሔር የሚሰጠውን ቦታ ይዳስሳል። እንዲሁም በሀልዎተ-እግዚአብሔር ዙሪያ ያሉት አመለካከቶች ማለትም አማኒነት(Theism) ኢ-አማኒነት(Atheism) እና ኢ-ታዋቂነት(Agnosticism) በመጠኑ ይዳስሳል። በተጨማሪ በዚህ ምዕራፍ ውስጥ "የነገረ መለኮት አረዳድ እና ብያኔ በዘመናችን"ና "ዕውቀት እና ነጽሮተ እግዚአብሔር" የሚሉ ሁለት ንዑሳን ርዕሶች ተዳሰውበታል።
በምዕራፍ ሁለት የነገረ መለኮት ምንጮች(Sources of Theology) በሚል ርዕስ እግዚአብሔር በተለያየ መልክ እና ጎዳና እራሱን ለሰው ልጆች በአቅማቸው ልክ የገለጠላቸውን መገለጦችን የነገረ መለኮት ምንጮች አድርገን የምንጠቀም መሆናችንን የሚዳስስ ምዕራፍ ነው። በዚህ ምዕራፍ የእግዚአብሔር መገለጥን (Revelation) በሁለት መከፈላቸውን እነርሱም አጠቃላይ መገለጥ(General Revelation) እና ልዩ መገለጥ(Special Revelation) እንደሚሰኙ ይገልጣል። አጠቃላይ መገለጥ(General Revelation) የሚባሉትን፦ የግዑዙ ዓለም ተፈጥሮ(physical Nature)፥ የሰው ተፈጥሮ(Human Nature) እና ታሪክ(History) እንዲሁም ልዩ መገለጥ(Special Revelation) ተዳሰዋልን። በተጨማሪም የነገረ መለኮት ምንጮች የሆኑትን ትውፊትን(Tradition) መጽሐፍ ቅዱስ(The Holy scripture) የአባቶች ትምህርት ፥ ዓለም አቀፍ ጉባኤያት ውሳኔዎች፥ ሥርዓተ አምልኮ(Liturgy), ፥ ምሥጢራት(sacraments) የሚባሉት የኦርቶዶክሳዊ ነገረ መለኮት ምንጮች በስፋት ታይተዋል።
ምዕራፍ ሦስት በመጽሐፉ ሰፊውን ሥፍራ የያዘ ምዕራፍ ነው። ኦርቶዶክሳዊ ነገረ ሰብእ በሚል ርዕስ ሰው በኦርቶዶክሳዊው ነገረ መለኮት እንዴት ይታያል የሚለውን እያነሳ በተቀራኒው ያሉትን ፍልስፍናዊ እና ሳይንሳዊ እይታዎችን በምሥራቃዊ የነገረ መለኮት መነጽርነት ይተቻቸዋል። በተጨማሪም ለኦርቶዶክሳዊው ነገረ ሰብእ(Orthodox Anthropology) መሠረት የሆነውን የእግዚአብሔር አርያና አምሳል የሚሉ አሳቦችን ሕሊና አበውን በመጠቀም ኦርቶዶክሳዊው ነገረ መለኮት የትክክለኛው ሰብአዊ ክብር ምንጭ መሆኑን ይነግረናል። እንዲሁም ነገረ ሰብእ በነገረ ክርስቶስ(Christological Anthropology), ፥ ወላዲተ አምላክና ነገረ ሰብእ(Theotokos and Anthropology)ና ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን እና ነገረ ሰብእ በሚሉ ርዕሶች አማካኝነት ከጥንተ ተፈጥሮ ጀምሮ የእግዚአብሔርን አርአያና አምሳል ይዞ ከመፈጠር፥ በእመቤታችን ምክንያትነት በምሥጢረ ሥጋዌ እንዲሁም በምሥጢረ ጥምቀት እና ቁርባን፥ በቤተክርስቲያን ውስጥ ያለ ፍጹም ማንነትን መሠረት በማድረግ ኦርቶዶክሳዊው ነገረ ሰብእ በስፋት እና በጥልቀት ተዳሷል።
የመጨረሻው ምዕራፍ ማኅበራዊ- አከባበያዊ ነገረ መለኮት(socio-Ecological Theology) በሚል ርዕስ የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ጋር ባለ ምሥጢራዊ ኅብረት እንደጠበቀ ከሰው ጋር እና ከተቀረው ፍጥረት ጋር እንዴት ያለ ጤናማ ግንኙነት ሊኖረው እንደሚገባ "ሰው ከሰው" እና ነገረ መለኮትና ሥነ ምሕዳር በሚሉ ንዑሳን ርእሶች አማካኝነት ይዳስሳል። ለዚህ ጤናማ ማኅበራዊ እና ሥነ ምኅዳራዊ ግንኙነት የቤተክርስቲያን አስተምህሮ ምን ያህል ለሀገር አስተዋጽኦ እንዳደረገና የጋራ የሆነ አገራዊ ስሜትን ከመፍጠር እና በየገዳማቱ ያሉትን የተፈጥሮ ጥበቃዋን እያነሳ የቤተክርስቲያኒቱ ባለውለታነት አሰምቶ
ይናገራል።
በአጠቃላይ በዚህ መጽሐፍ የምሥራቁ ኦርቶዶክሳዊ ነገረ መለኮት ምን መልክ እንዳለው፥ በእግዚአብሔር መገለጥ ላይ የተመሠረቱት ምንጮቹንና የምንጮቹ ነገረ መለኮታዊ አረዳድ፥ ሰው ምንድነው? የሚለውን ጥያቄ መሠረት ያደረገውና በነገረ መለኮት ሰፊ ሽፋን የሚሰጠውን ኦርቶዶክሳዊ ነገረ ሰብእን በማስረዳትና በመተንተን የሰው ልጆች ክብራቸውን አውቀው እግዚአብሔርን ወደ መምሰል(Theosis) የክርስትና ጉዞ እንዲያቀኑ የሚያደርግ ነው። እንዲሁም እግዚአብሔርን በመምሰል ሂደት ውስጥ የምናገኛቸውን ሰው እና ሌሎች ፍጥረታትን እንዴት ባለ አኳኋን መመልከት እንዳለብን ባጠቃላይ ከእግዚአብሔር እና የእርሱ ከሆኑት ፍጥረታት ጋር ምሥጢራዊ እና መንፈሳዊ ኅብረታዊ ግንኙነት እንዲኖረን የሚያግዝ የሚያስረዳ እና የሚራዳ መጽሐፍ ነው።
ለመምህራችን እግዚአብሔር ይስጥልን። ከእጅ ቁርጥማት ከደረት ውጋት ይሰውርዎት! ወርቃማ ብዕርዎት ትለምልም! ለመጽሐፍ ቀጠሮ ያብቃን!!!

መጽሐፉን ያንብቡ ያስነብቡ!!

እውነተኛ የነገረ መለኮት መግቢያ በሩ ይሄ ነው!
መጽሐፉ ርዕስ፦ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ታሪክ(ከጥንት - 6ኛ ክፍለ ዘመን) ቅጽ 1
የመጽሐፉ አዘጋጅ፦ መምህር ግርማ ባቱ
የመጽሐፉ የገጽ ብዛት፦ 448
የመጽሐፉ ዋጋ፦ 390
የኅትመት ዘመን፦ 2014 ዓ.ም
መምህር ግርማ ባቱ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በሥነ መለኮት(theology) ሰርተዋል፡፡ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናቶች ተቋም(Addis Abeba Institute of Ethiopian Studies) በባህል ጥናት(cultural studies) እና ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደግሞ በሥነ መለኮት (theology) ሰርተዋል፡፡ በሕንድ ሀገር የዶክትሬት ዲግሪያቸውን እያጠኑ(ያጠኑ?) ሲሆን፣ በቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርስቲ የሥነ መለኮት መግቢያና (Introduction to Theology) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ታሪክ እያስተማሩ ይገኛሉ፡፡ እኚህ በሁለት እጅ የማይነሱ ታላቅ መምህር በቅርቡ የቤተክርስቲያን ታሪክ መጽሐፍ አበርክተውልናል። የኢትዮጵያ የቤተክርስቲያን ታሪክ በተለያዩ ዕይታዎች ማለት አውሮፓ ተኮር ዕይታ(Eurocentrism) ፥ አፍሪካ ጠል ዕይታ(Afrophobia) እንዲሁም ግብፃዊ የታሪክ ዕይታ ብዙ ዱላ የበዛበትን ታሪክ እሳቸው መነጽሩን በማስተካከል ወደ በኢትዮጵያ ተኮር ዕይታ(Ethiocentric) በዕይታና የራስን ተልዕኮ በመያዝ የኢትዮጵያን ታሪክ ወተቱን አጥቁረው ላቀረቡልን ምዕራባውያን እና የሀገር ቤት የታሪክ ጻፊዎች "እውነቱ ይሄ ነው" እያሉ በማስረጃና በመረጃ ቁጭ ብድግ እያደረጉ ይሞግታሉ። የኢትዮጵያን የታሪክ ምንጮች የመተርጎም ሥልጣን ኢትዮጵያዊ የታሪክ ዕይታ(Ethiocentric) ያላቸው ኢትዮጵያውያን እንጂ አውሮፓውያን ወይም ጥሙቅ አውሮፓውያን አይደሉም መሆንም የለባቸውም እያሉ በምሬትና በቁጭት ይነግሩናል። እንዲሁም ኢትዮጵያ ሀገረ እግዚአብሔር ሕዝቦቿም ሕዝበ እግዚአብሔር የሆኑ ቅድስት ሀገር መሆኗን ከሕገ ልቦና ወደ ሕገ ኦሪት እንዲሁም ሕገ ወንጌል የተቀበለች በነቢያትና በሐዋርያት መሠረትነት ላይ የመሠረተች መሆኗን የሕገ ኦሪት የአምልኮ ሥርዓት ማሳያዎችን እንደ ታቦተ ጽዮን፥ ግዝረትን፥ የቀዳሚት ሰንበትን አከባበር የምግብ ሥርዓታችንን(የሚበሉና የማይበሉ)ና የሕንፃ ቤተክርስቲያን አሠራራችንን እያነሱ ያስረዱና። ማን እንደተከለው የማይታወቅ "ኢትዮጵያ ክርስትናን የተቀበለች 4ኛው ክፍለዘመን ነው" እያሉ ብዙዎች ለሚጮኹት ከንቱ ጮኾት በመጻፋቸው "4ተኛው ክፍለዘመን ላይ የተደረገው ለውጥ ክርስትና ብሔራዊ ሃይማኖት የሆነበት እንጂ የገባበት ተደርጎ ሊነገር አይገባም" እያሉ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ታሪክ ሦስት ዓበይት ክፍሎች እንዳሉት እነርሱም፦ ክርስትና የተዋወቀበት(የጃንድረባው ባኮስ) ፥ ክርስትና የተደራጀበት(የቅዱስ ፍሬምናጦስ)ና ክርስትናው የተስፋፋበት(የዘጠኙ ቅዱሳን መምጣት) በማለት አስፍተው አምልተው ምንጭ እየጠቀሱ ክርስትናው ከኢትዮጵዊው ጃንደረባ የሚጀምር መሆኑን ጮኾቱን ከንቱ ያሰኙታል ። እንዲሁም በቤተክርስቲያን መምህራን ሳይቀር ትኩረት ያልተሰጠውን እንዲሁም "በኢትዮጵያ ወንጌልን ሰበኩ ብሎ የሚመካ ሐዋርያ" የለም ተብሎ የተካደውን የቅዱስ ማቴዎስን ወደ ኢትዮጵያ መምጣት መስበኩንና ማስተማሩን በማስረጃ ያስረዳሉ ይሞግታሉ። እንዲሁም የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ወርቃማው ዘመን ውስጥ የዐፄ ካሌብን ወደ ናግራን ያደረጉትን ዘመቻና ከድል መልስ የተደረገውን በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያሰኝ ሰላማዊ የሆነ የሥልጣን ሽግግር ይዳስሳል። በመቀጠል ለዘመኑ ወርቃማነት ወርቅ ሆነው ስለተገኙት ማኅሌታዊው ቅዱስ ያሬድ ፥ ዘጠኙ ቅዱሳንና ዐፄ ገብረ መስቀል አንድ በአንድ በተናጥል እና በጋራ ለወርቃማው ዘመን ያበረከቱትን ከወርቅ የላቀ ሥራና አስተዋጽኦ ይተነትናሉ። በመጨረሻም ስለኢትዮጵያ ጥንታዊ ትምህርት እና ቅዱስ ያሬድ በዚህ ዙርያ ስላደረገው ትልቅ አስተዋጽኦ ያትታል። ኢትዮጵያ የምትድነው የራሷ በሆነው ጥንታዊ ትምህርት እና ከሌሎች የተገኘውን ዕሴት ጨምሮ የራስ በማድረግ መሆኑንና ሁሉን መጣልና ሁሉን መቀበል የማይገባ ከዚህ ይልቅ የሚበጀን ወደፊት የሚያስኬደን አስተጻምሮ(synthesis ) እንደሆነ በተዋሕዶ ማክበርን መርሕ የሚከተሉትን ዶክተር እጓለን ጠቅሰው ያስረዱበትና የተረዱበት መጽሐፍ ነው። የመምህር ግርማ ባቱን የታሪክ መጽሐፍ ያነበበ(ወይም በክፍል የተማረ) ሰው የኢትዮጵያን ታሪክ ይረዳል፥ የኢትዮጵያን ታሪክ የራስ ያደርጋል፥ በኢትዮጵያ ታሪክ ይኮራል፥ በኢትዮጵያ ታሪክ ዛሬያችንን እያየ ይቆጫል፥ ታሪክን ለመድገም ይነሣሣል። መጽሐፉ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ታሪክ ማለት የኢትዮጵያ ታሪክ መሆኑን በሚገባ ይገልጣል። ነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ ዐጤ ምኒልክና ኢትዮጵያ በሚለው መጽሐፉቸው የመጀመርያ ገጽ ላይ እውነተኛን ታሪክ ለመጽሐፍ 3 ነገሮች ያስፈልጋሉ ይላሉ።
1, ተመልካች ልቦና 2, የማያዳላ አእምሮ 3, የጠራ የቋንቋ አገባብ ብለው ይዘረዝራሉ። መምህር ግርማ እኚህን ሦስቱን ያሟሉ እውነተኛ ታሪክ ጸሐፊ መሆናቸውን በመጽሐፋቸው አስመስክረዋል። ነጋድራስ ዛሬ በሕይወት ቢኖሩ ልጃቸውን መምህር ግርማን እውነተኛ ታሪክ ጽፈሐልና እደግ ተመንደግ ብለው ግንባሩን ይስሙት ነበር። አስረስ የኔሰው ዶክተር እጓለ ተመሳሳዩን ያደርጉ ነበር።

እውነተኛውን የኢትዮጵያን ታሪክ መረዳት ለሚፈልግ ኢትዮጵያዊ ሁሉ የተደረገ የመጽሐፍ ግብዣ መጽሐፉን ያንብቡ ያስነብቡ!
የመምህር ግርማ መጽሐፍ የሌለበት የመጽሐፍ መደርደሪያ ሙሉ አይሆንም መጽሐፉን በመግዛት መደርደሪያዎትን ሙሉ ያድርጉ።

የልጅ ምርቃት፦ መምህር ግርማ ሆይ የኢትዮጵያ አምላክ ግርማ ሞገስ ይስጥልኝ። የጻፈ ያጻፈ ከሚለው በረከት ያድልልን። ብዕርዎት ትለምልም። ሞትህን ከገብርኤልና ከሚካኤል ጋር ያድርገው!

ያለ ሰው ያልተወን የአባቶቻችን የቅዱሳኑ አምላክ የተመሰገነ ይሆኑ!!!
Add...
ብራና መጽሐፉ BRANA BOOK
በዚህ ግሩፕ ላይ ቢሳተፉ የምትሏቸውን Add ያድርጉ....
MIKIYAS DANAIL:
፨የብራና መጽሐፉ BRANA BOOK፨
®ዓላማ፦
1,ያነበብናቸውን መጽሐፉ የምንጠቁምበት
2,ካነበብናቸው መጽሐፉ ውስጥ ገዢ ሀሳቦችን። የምንለዋወጥበት
3,ነባር እና አዳዲስ የታተሙ መጽሐፉ የምንጠቁምበት።
4,በአጠቃላይ ስለመጽሐፍ የምንወያይበት ነው።
*የንስሐ መንገዶች (በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ)*

አምስት የንስሃ መንገዶች አሉ ። የተለያዩ ቢሆኑም ቅሉ ሁሉም የሚያደርሱት ግን ርስት መንግስተ ሰማያት ነው ። እነርሱስ ምን ምን ናቸው ? ያልከኝ እንደሆነ እንድህ ብየ እመልስልሃለሁ፦

፩ኛ • የመጀመሪያው መንገድ "የራስን ኃጢአት ማመን፣ መጥላትና ማውገዝ ነው።

ይኽውም ልዑል ቃል ኢሳይያስ "እንድትጸድቅ መጀመሪያ ኃጢአትህን ተናገር እንዳለው" (ኢሳ 43 ፥26 )፤ ክቡር ዳዊትም "በደሌን አልሸፈንኩም፤ ለእግዚአብሔር መተላለፌን እንግራለሁ አልሁ ፤ አንተም የልቤን ኃጢአት ተውኽልኝ" ብሎ እንደተናገረ መዝ 31፥5 ስለዚህ አንተም ስለ ሰራኽው ኃጢአት እራስህን ውቀሰው። በዚህ እግዚአብሔር ይቅር እንዲልህ ታደርገዋለህና። ይህ ብቻ ሳይሆን ስለ ኃጢአቱ እራሱን የሚወቅስና ኃጢአቱን የሚኮንን ሰው በተመሳሳይ ኃጢአት በቀላሉ አይወድቅምና። ስለዚህ በጌታ የፍርድ ዙፋን የሚወቅስህ እንዳይኖር ዛሬ እውነተኛ ወቃሽ በኾነው ሕሊናህን አንቅተህ በራስህ ላይ ወቃሽና ከሳሽ አድርገህ ሹመው። ይህ አንዱና ደገኛው መንገድ ነው ።

፪• ሁለተኛው የንስሐ መንገድ ደግሞ
የወገኖቻችንን በደል ይቅር ማለትና በበደሉህ ላይ ቅሬታና ቂም አለመያዝ ነው።

እንዲህ ስናደርግ "ለሰወች ኃጢአታቸውን ይቅር ብትሉ የሰማዩ አባታችሁ እናንተንም ደግሞ ይቅር ይላችኋል" እንዲል እኛ በጌታችን ላይ ያደረግነውን በደል ይቅር እንባላለንና። ማቴ 6 ፡14

፫• ሦስተኛውን የንስሃ መንገድ መንበረ ጸባዖት የደርስ በትጋትና በጥልቅ ስሜት የሚደረግ "ከልብ የመነጨ ጸሎት ነው"

ጨካኙ ዳኛ እንዲርፈድላት ያደረገችው ያች መበለት እንዴት እንዲፈርድላት እንዳደረችገው አታያትም? ( ሉቃ 18፥3) አንተ ግን ሩኅሩኅና መሐሪ የኾነ ጌታ ነው ያለህ። እርሷ በጠላቶቿ ላይ እንዲፈርድላት ነው የጠየቀችው፤ አንተ ግን እምትጠይቀው ስለራስህ ድኅነት ነው።

፬• አራተኛ መንገድ አለ እርሱም "ምጽትዋ ነው " ይህም እጅግ በጣም ታላቅ የኾነ ኃጢአትን የሚስተርይ ኃይል አለውና።

ናቡከደነጾር ኃጢትን ንቅስ ጥቅስ አርድጎ ወደ ክኅደት ሁሉ በገባ ጊዜ እንድህ ብሎታልና፦ "ንጉስ ሆይ ! ምክሬ ደስ ያሰኝህ ኃጢአትህም ለጽድቅ በደልህን ለድኾች በመመጽወት አስቀር" (ዳ.ን 3፥27 ) ይህ ቸርነትና ሰውን መውደድስ ምንስ ይስተካከለዋል? እንዴት ያልከኝ እንደሆነ ስፍር ቁጥር የሌለውን ኃጢአት ከሰራ በኋላ ከዚያ ኹሉ በደል በኋላ እንደርሱ ለሆኑ ሰወች ርኅራኄን ቢያደርግ ከተገዳደረውና ከተጣላው አምላክ ጋር መታረቅ እንደሚችል ቃል ተገብቶለታልና ።

፭• አምስተኛው መንገድ "እንዲሁም ትሕትናና እራስን ማዋረድ ኃጢአትን ያደክማል"

ይህንንም ቀራጩ ያረጋግጥልናል አይኖቹን ወደ ሰማይ ለማንሳት እንኳንስ እስኪፈራ ድረስ በታላቅ ትሕትና ራሱን ባዶ ባደረገ ጊዜ "ጻድቅ ሆኖ ሄደ ተብሏልና ።(ሉቃ 18፥13) ስለዚህም ምንም ምግባር ቢኖርህም እንኳን በደልህን ከመናር በቀር በጎ ምግባርህን አታስበው። ያን ጊዜ እግዚአብሔር የበደል ሸምክህን ያራግፍልሃል።

ስለዚህ እነዚህን መንገደኞች ተመላለስባቸው እንጅ ሰነፍ አትኹን ።

("አምስቱ የንስሐ መንገዶች እና ሌሎች በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ" መጽሐፍ በ ገብረ እግዚአብሔር ኪደ የቀረበ)
“ማር ኤፍሬም ሶርያዊ”
የመንፈስ ቅዱስ ዕንዚራ (ܟܢܪܐ ܕܪܘܚܐ, Kenārâ d-Rûḥâ)፤የኤፍራጥስ ወንዝ፣ የኤዴሳ ዲያቆን (Deacon of Edessa)፤ የሶርያዎች ፀሓይ (the Sun of the Syrians)፤ የቤተ ክርስቲያን ምሰሶ (a Pillar of the Church) ተብሏል። ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ በግእዝ “ማር ኤፍሬም ሶርያዊ” በማለት ኢትዮጵያውያን ይጠሩታል፡፡ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም ይኽነን ሊቅ ሲያወድሰው፡-
“ሰላም ለኤፍሬም ደራሲ ዘጽሩይ ልሳኑ፤
አብያተ ክርስቲያናት ይሠረጉ በድርሳኑ”፡፡
(በድርሳኑ አብያተ ክርስቲያናት የሚሸለሙ (የሚያጌጡ) አንደበቱ የጠራ ለደራሲው ለኤፍሬም ሰላምታ ይገባል) ብሎታል፡፡

ማር ኤፍሬም ሶርያዊ ሕይወጡን እና ሥራዎቹን ያጠኑ አለማቀፍ ሊቃውንት እንደሚገልጹት ከሆነ በአጠቃላይ ከ14,000 በላይ ድርሳናትን እንደደረሰ ይታመናል፤ በግእዝ ከተተረጐሙት መጻሕፍት ውዳሴ ማርያምን ጨምሮ በጥንታዊ ብራና መጻሕፍቶቻችን ውስጥ ከ95 በላይ የቅዱስ ኤፍሬም መጻሕፍቶች ሲገኙ እጅግ በጣም ጥቂቶቹ ብቻ በሃይማኖተ አበው ላይና በግብረ ሕማማት ላይ ብቻ ለሕትመት ሲበቁ ሌሎቹ ግን በዘረፋ ብራናዎቹ ከሀገር በመውጣታቸው ምክንያት ሊገኙ አልቻሉም፡፡

የአምላክ እናትም ለርሷ ያለውን ጥልቅ ፍቅር አይታ ከልጇ አማልዳው “አኀዝ እግዚኦ መዋግደ ጸጋከ” (አቤቱ የጸጋኽን ማዕበል ግታልኝ) እስኪል ድረስ እጅግ በርካቶች መጻሕፍትን እንዲጽፍ ኾኗል፡፡ ለዚኽ ፍጹም አባትም ቅድስት ድንግል ማርያም ለሰባት ተከታታይ ቀናት በታላቅ ክብር ኾና እየተገለጸችለት ውዳሴዋን ሰተት አድርጋ አስደርሳዋለች፤ በዚኽም የአምላክ እናት “የቅዱስ ኤፍሬም እመቤት” ተብላ ትወደሳለች፡፡
=========================
ብራና ሚዲያ BRANA MEDIA
https://t.me/brana_Book
~~~~~
መ/ር ሚኪያስ ዳንኤል
*ተጻፈ ፪/፲፪/፳፻፲፬ ዓ.ም*
Mikiyas danail የፌስቡክ ፔጅ https://www.facebook.com/Mikiyas-danail-102145778357310/
+++++++++++++++++++
መልካም ንባብና ምርምር ይሁንለዎ
ማን ነው ወዳጄ! ስለ ጻድቁ ክብር ሲል የመግቢያ ትኬት የሚገዛኝ?
#ቡሄ_ሔ
የደብረ ታቦር በዓል ከዘጠኙ ዐበይት በዓላት አንዱ ቢሆንም በምዕመናን ዘንድ ቡሄ/ሔ በመባል ይታወቅል ለመሆኑ የደብረ ታቦር በዓል ለምን ቡሄ/ሔ እያልን እንጠራዋለን? ስለምንስ ችቦ እናበራለን? የሚጮኸው የጅራፍ ድምጽ ምንድነው ምሥጢሩ የሚለውን በአጭሩ እንመከታለን፡፡
=================_//_==============
ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ስለ ደብረ ታቦር በዓል አከባበር በኢትዮጵያ ሲናገሩ እንዲህ ይላሉ “ቡሄ/ሔ ዘውእቱ በዓለ ኖሎት ደቀ መዛሙርት “ ይህውም ደብረ ታቦር ወይም የቡሄ/ሔ በዓል የደቀ መዛሙርትና የእረኞች በዓል ነው እንደ ማለት ፡፡ ምክንያቱም በጥንቷ ኢትዩጵያ የደብረ ታቦርን በዓል እረኞች የቆሎ ተማሪዎች በስፋት ስለሚያከብሩት ነው፡፡
===============_//_=================
#ቡሄ፡- ማለት “የበራ የደመቀ የጐላ ብርሃን“ የብርሃን በዓል እንደ ማለት ነው ይህም በቅዱስ ወንጌል እንደተጻፈው ጌታችን በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን በገለጠ ጊዜ ፊቱ እንደ ፀሐይ በማብራቱ፥ ልብሱም አጣቢ በምድር ላይ ሊያነጣው እስከማይችል ድረስ በጣም ነጭ አንጸባራቂ በመሆኑ ነው ማቴ 17፥2 ማር9፥3 ሉቃ9፥29
=============_//_===================
#ቡሔ፡- ማለት ደግሞ “ደስታ ፍሥሐ“ማለት ይሆናል፡፡ ይህውም በትንቢት እንደተፃፈው ታቦር ወአርምንዔም በስመ ዘአከ ይትፈሥሑ መዝ88፥12 በዚህ ትንቢታዊ ቃል መሠረት በወቅቱ የጌታ ብርሃን በዙሪያቸው አብርቷል ከታቦርም እስከ አርምንዔም ተራራ ድረስ ታይቷል፡፡ ይህም መለኮታዊ ብርሃን በወረደበት ጊዜ ከብቶቻቸውን ይጠብቁ የነበሩ በታቦርና በአርሞንየም አካባቢ ያሉ መዓልቱ የሌሊቱን ቦታ ስለ ወሰደው በሁኔታው ሐሴትን አድርገዋል፡፡ሙልሙል/ኀብስቱ፡- በታቦር ተራራ ዙሪያ ለነበሩት እረኛች ወላጆቻቸው ምግባቸውን ይዘው መሄዳቸውን ያጠይቃል፡፡ አንድም የኀብስቱ ምሳሌነት ለክርስቶስ ነው “አነ ውእቱ ኅብስተ ሕይወት ዘወረደ እምሰማያት” ዮሐ 6፥32-59
=================_//=================
#ጅራፍ፡- በደብረ ታቦር ዋዜማ ከፍ ያለ ቦታ ላይ ሆነን ጅራፍ የምናጮኸው መሠታዊ ሃይማኖታዊ ምሥጢር ምሳሌነት አለው።
++++++++++++++++++++++++++++++++++++
እግዚአብሔር አብ በመልክ የሚመስለኝ በባህሪ የሚተካከለኝን ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው አንድያ ልጄ ነው፡፡ እርሱን ስሙት ተቀበሉት ብሎ ድምጹን በደመና በደብረ ታቦር ተራራ ላይ የመሰከረበትን እያሰብን ነው፡፡
++++++++++++++++++++++++++++++++++++
የጅራፍ ጩኸት ከጫፍ ጫፍ ይሰማል በመዝሙረ ዳዊት “……….. ድምጻቸው ወደ ምድር ሁሉ ቃላቸውም አስከ ዓለም ዳርቻ ወጣ፡፡” መዝ18፥4 በማለት የሐዋርያት ስብከት በዓለም ዳርቻ መድረሱን ያመለክታል፡፡ መኃ 2፥12
ሌላው የጅራፍ ጩኸት ማስደንገጡ ደግሞ ሦስቱ አዕማድ ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ ድምጸ መለከትን ሰምተው ደንግጠው መውደቃቸውን ያስታውሳል፡፡
++++++++++++++++++++++++++++++++++++
በተጨማሪም የልጆቹ ወላጆች በታቦር ተራራ ዙሪያ የነበሩትን ልጆቻቸው ለመፈለግ ችቦ እያበሩ ሲሄዱ ልጆቹም ጅራፍ በማጮኽ ያሉበትን ሥፍራ መጠቆማቸውን ያስረዳል፡፡
ችቦ፡- ተሰብስበን ችቦ የማብራታችን ምሳሌ ደግሞ ጌታችን በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን የገለፀበት ምሳሌ በመሆኑ ነው፡፡ የሐ 8፥1፣ መዝ 26፥1 “እግዚአብሔር ብርሃኔና መድሐኒቴ ነው……..”
================_//=================
#ማጠቃለያ፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የደብረ ታቦርን በዓል በየዓመቱ ነሐሴ 13 ቀን ታከብረዋለች፤ ይኸውም በዕለቱ በዓሉን የሚያዘክር በቤተክርስቲያን ምንባባት ይነበባል፡፡ ቅዳሴ ይቀደሳል፣ ምስባክ ይሰበካል፣ ቃለ እግዚአብሔር ይሰጣል፣ ወረብ ይወረባል………… ወዘተ በዚህም ዕለት የቤ/ክ አባቶችና ምእመናን በዓሉን በደማቅ ሥነ ሥርዓት ያከብሩታል፤ ምክንያቱም ከላይ በስፋት እንደ ተመለከትነው ደብረ ታቦር እሥራኤላውያን የድል ካባ የደረቡበት መሳ 4፥1—3 የትርጓሜ ትምህርት የተሰጠበት ማቴ 15፥15፣ ኑፋቄ (ጥርጥር) የተወገደበት ማቴ 16፥13—20፣ ምሥጢረ ሥላሴን የተረዳንበት፣ የክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት የተሰበከበት፣ የሐዋርያት ባለሟልነት የተገለጠበት፣ የተግባር ትምህርት የተሰጠበት፣ አሉባልታና ተራ ወሬ የከሸፈበት፣ የቅዱሳን ነቢያት ሐዋርያት ክብር የተገለጠበት፣ የተቀደሰን ቦታ አክብሮት፣የተማርንበት የታየበት፣ ብሔረ ሕያዋን መኖሩ የተመሠከረበት፣ የትንሣኤ ሙታን ዋስትና የተረጋገጠበት ነው፡፡
++++++++++++++++++++++++++++++++++++
“በዘመኑም ፍጻሜ የእግዚአብሔር ቤት ተራራ በተራሮች ራስ ላይ ጸንቶ ይቆማል…………” ኢሳ ፪፥፪
••MIKIYAS DANAIL••
https://t.me/mikiyasBRANAbook
https://www.facebook.com/mikiyas.danail
=============//================
መልካም የደብረ ታቦር በዓል
••••••••••••••
©መ/ር ሚኪያስ ዳንኤል
ነሐሴ12/2014