ብራና ሚድያ - Birana Media
641 subscribers
1.67K photos
40 videos
4 files
572 links
+ የወጣቶች መንፈሳዊ ሕይወት
+ ገዳማትና ታሪካዊ ስፍራዎች
+ የቅዱሳን አበው መንፈሳዊ ተጋድሎና ታሪክ
+ እንዲሁም በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች የውይይት መድረክ በማዘጋጀት ወደ እናንተ ውድ ተከታታዮች መንፈሳዊ ይዘቱን ጠብቆ በየእለቱ ይቀርባል።
ቻናላችንን Subscribe በማድረግ ይቀላቀሉን።
https://www.youtube.com/c/BiranaMedia
ጥያቄ ካሎት በዚህ ይጻፉልን @birana259
Download Telegram
ብራና ሚድያ - Birana Media
Photo
የዐቢይ ጾም የመጀመሪያ ሳምንት

ዘወረደ

በዚህ ሳምንት የቃል ርደት፣ የወልድ ልደት፣ የአዳም ድኅነት ቢነገርም እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ከሰማይ የወረደ ሰማያዊ፣ በክብር ያረገ በኩረ ትንሣኤ መሆኑ አይዘነጋም፡። ለዚህም ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ “እውነት እውነት እልሃለሁ፥ የምናውቀውን እንናገራለን፤ ያየነውንም እንመሰክራለን፥ ነገር ግን ምስክርነታችንንም አትቀበሉትም። በምድር ያለውን ስንነግራችሁ ካላመናችሁኝ፥ በሰማይ ያለውን ብነግራችሁ እንዴት ታምኑኛላችሁ? ከሰማይ ከወረደው የሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው ነው። ሙሴ በምድረ በዳ እባቡን እንደ ሰቀለው የሰው ልጅ እንዲሁ ይሰቀል ዘንድ አለው፡፡ያመነበት ሁሉ ለዘለዓለም ሕያው ሆኖ እንዲኖር እንጂ እንዳይጠፋ፣ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወትን እንዲያገኝ እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ቤዛ አድርጎ እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶታልና” እንዳለ እርሱ ምድራዊ ያይደለ ሰማያዊ ነው። (ዮሐ.፫፥፲፩-፲፮)  “ተጠምቀ ሰማያዊ በእደ መሬታዊ” ስለ ፍቅሩ በፈጠረው የተጠመቀ ሰማያዊ ነው።

ጾመ ድጓው የሚጀምረውም እንዲህ በማለት ነው፤ “ዘወረደ እምላዕሉ፣ አይሁድ ሰቀሉ…. እግዚአ ኩሉ ዘየሐዩ በቃሉ፤ ….በቃሉ የሚያድነውን ከላይ የወረደውን የሁሉን ጌታ አይሁድ ሰቀሉት…”

ዘወረደ የዐቢይ ጾም የመጀመሪያ ሳምንት ነው። ስያሜውም የቅዱስ ያሬድ ነው። ትርጉሙም “ከሰማያት የወረደ” ማለት ነው። ቅድመ ዓለም ከአባቱ ከአብ የተወለደ ፣ድኅረ ዓለም ከድንግል ማርያም የተወለደ ነው። ስም አጠራሩ  ያለና የነበረ፣ እግዚአብሔር፣ በፈቃዱ ዓለምን ለማዳን የመምጣቱን ምሥጢር የምንረዳበት ሳምንት ነው። ይህ የመጀመሪያው ሳምንት ‹ጾመ ሕርቃል› እየተባለም ይጠራል፡፡ ሕርቃል (ኤራቅሊዮስ) በ፮፻፲፬ ዓ.ም የነበረ የቤዛንታይን ንጉሥ ነው፡፡ለክርስቲያኖች ባደረገው ርዳታ ምክንያት አንድ ሳምንት ጾመውለት ነበር፡፡ ዛሬም ድረስ ጾመ ሕርቃል እየተባለ ይጠራል፡፡ ሙሉ ታሪኩ በፍትሐ ነገሥት ትርጓሜ አንቀጽ ፲፭ ላይ ይገኛል፡፡

በዚህ ሳምንት ቤተ ክርስቲያን ስለ ጾም ጥቅምና እንዴት መጾም እንዳለብን ታስተምረናለች፡፡ቅዱስ ያሬድ በጾመ ድጓው “አከለክሙ መዋዕል ዘኃለፈ ዘተቀነይክሙ ለግዕዘ ሥጋክሙ፤ ለሥጋቸሁ ፈቃድ የተገዛችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃችኋል፤ ከአሁን በኋላ ግን ጹሙ፣ ጸልዩ ለእግዚአብሔር ተገዙ” እያለ የጾም አዋጅ ያውጃል። ጾም ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ፣ ፈቃደ ነፍስን ለፈቃደ እግዚአብሔር የምናስገዛበት መንፈሳዊ መሣሪያ ነው፡፡

ጾሙ በሚጀመርበት ሰንበት በሚሰበከው ምስባክ እንዲህ ብሎ ያሳስበናል፤ “ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ፣ በረዓድም ደስ ይበላችሁ” ጾም ከምግብና ከመጠጥ እንዲሁም ከሌሎች ምቾቶችና ደስታዎች ከመከልከል ያለፈ ጥልቅ ትርጉም ያለው ተግባር ነው። (መዝ.፪፥፲፩-፲፪) “ንጹም ጾመ ወናፍቅር ቢጸነ ከመ ያብርህ ብርሃነ ስብሐቲሁ በላዕሌነ፤ (የእግዚአብሔር) የክብሩ ብርሃን በላያችን ላይ ያበራ ዘንድ ጾምን እንጹም፤ወንድማችንንም እንውደድ” እንዲል። (ጾመ ድጓ)

በዘወረደ እሑድ የሚነበቡት ምንባባትም ይህንን የጾምን ጸጋ የያዙ ናቸው።

“ነገር ግን ፈጣሪያችን የምትበልጠውን ጸጋ ይሰጣል፤ ስለዚህም “እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል” ይላል፡፡ እንግዲህ እግዚአብሔርን እሺ በሉት፤ ሰይጣንን ግን እንቢ በሉት፤ ከእናንተም ይሸሻል፡፡ እግዚአብሔርን ቅረቡት፤ ይቀርባችሁማል፤ እናንተ ኃጥኣን እጆቻችሁን አንጹ፤ ሁለት አሳብም ያላችሁ እናንተ ልባችሁን አጥሩ፡፡ እዘኑና አልቅሱ፤ ሳቃችሁን ወደ ልቅሶ÷ ደስታችሁንም ወደ ኀዘን መልሱ፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ፤ እርሱም ከፍ ከፍ ያደርጋችኋል፡፡” (ያዕ.፬፥፮-፲)

“በውኑ እንግዲህ በስሙ እናምን ዘንድ የከንፈሮቻችን ፍሬ የሚሆን የምስጋና መሥዋዕትን በየጊዜው ለእግዚአብሔር ልናቀርብ አይገባንምን? ነገር ግን ለድሆች መራራትን፥ ከእነርሱም ጋር መተባበርን አትርሱ፤ እንዲህ ያለው መሥዋዕት እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋልና፡፡” (ዕብ.፲፫፥፲፭-፲፮)

በጾም የተጠቀሙ ቅዱሳንን እያሰብን ለጾም እንድንተጋም ወደ እነርሱ እንድንመለከት ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች፡፡“ ልባችሁ በመብል ያይደለ በጸጋ ቢጸና ይበልጣልና፤ በዚያ ይሄዱ የነበሩ እነዚያ አልተጠቀሙምና።” (ዕብ.፲፫፥፱) ሳምንቱ በሚጀምርበት ሳምንት የሚነበበው የቅዱስ ጳውሎስ መልእክት እንዲህ ይላል፡፡ ጾመ ድጓው አባቶቻችን ያገኙትን በረከት እንደምናገኝበት ሲገልጽ “የእግዚአብሔር የክብሩ ብርሃን በላያችን ላይ ያበራ ዘንድ ጾምን እንጹም፤ ወንድሞቻችንም እንውደድ፤ ኤልያስ በጾም ወደ ሰማይ አርጓልና፤ዳንኤልም ከአናብስት አፍ ድኗልና፡፡”

ጾም ፈቃደ ነፍስን በፈቃደ ሥጋ ለማሠልጠን የአጋንንት ኃይል ለመቋቋም የሚያስችል የክርስቲያኖች ጋሻ በመሆኑ በሃይማኖት ለሚመሩ ምእመናን እጅግ አስፈላጊና ከምንም በላይ የሕይወታቸው መርሕ መሆን እንደሚገባ ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ እንዲህ በማለት   ያስተምራል፡፡ ” አሁንም ወንድሞቻችን በዚህ በሥጋችን ሳለን ፈቃደ ሥጋችንን ልንሠራ አይገባም፤ ፈቃደ ሥጋቸውን የሚሠሩ ሰዎች በወዲያኛው ዓለም ምውታን ናቸውና፡፡ የሥጋችሁን ፈቃድ በነፍሳችሁ ፈቃድ ድል ከነሣችሁት ለዘለዓለም ሕያዋን ትሆናላችሁ፡፡ የነፍሳቸውን ፈቃድ የሚሠሩ ሰዎች ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና፡፡" (ሮሜ ፰፥፲፪-፲፬)

ጾም አበው ቅዱሳን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በጊዜ ቀምረው፣ በበታ ወስነው፣ በሁኔታ ገድበው... ባስቀመጡልን ወቅት ከእህልና ከውኃ በመከልከልና ሰውነትን በማድከም ብቻ ሳይሆን ለስሕተት ከሚዳርጉ ነገሮችና ቦታዎች ተቆጥቦ በጸሎት መትጋትም እጅጉን አስፈላጊ ነው፡፡ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊትም ይህንን እውነታ በተመለከተ እንዲህ ይላል፡፡ “እኔ ግን እዘንልን፤ ለምንልን ባሉኝ ጊዜ ማቅ ምንጣፍ ለብሼ አዘንኩላቸው፤ ሰውነቴን በጾም አደከምኩዋት፤ ልመናዬም እኔም ወደመጥቀም ተመለሰችልኝ፡፡” (መዝ. ፴፬/፴፭፥፲፫)

ጾም ከሥነ ምግባራት ሕግ አንዱ በመሆኑ እንኳንስ ያልተፈቀደውን የተፈቀደውም ቢሆን የማይጠቅም ከሆነ ፈጽሞ በመተው ለእግዚአብሔር ያለንን ፍጹም ፍቅር የምናስመሰክርበት ምሥጢር ነው፡፡

ጾም ከመብልና ከመጠጥ ጋር የተያያዘም በመሆኑ መብል ጊዜያዊ ስለሆነ ማለትም በዚህ ዓለም እስካለን ብቻ የምንገለገልበት እንጂ ዘለዓለማዊ ስላይደለ ለጊዜያዊ መብልና መጠጥ ምክንያት ከሃይማኖት ሥነ ምግባር እንዳንወጣ ቅዱሳን አባቶቻችን ሐዋርያት ሲመክሩ “መብል በእግዚአብሔር ዘንድ ግዳጅ አይፈጽምልንም ወደ እግዚአብሔር አያቀርበንም፤ ብንበላም አይረባንም፤ አይጠቅመንም፤ ብንተወውም አይጎዳንም” በማለት ሲመክሩን ቅዱስ ጳውሎስም የመብልና የሆድ ጊዜያዊነት አስመልክቶ እንዲህ በማለት አስተምሯል፡፡ (፩ኛቆሮ.፰፥፰)

“ሁሉ ነገር ተፈቅዶልኛል፤ ሁሉ ግን አይጠቅመኝም፡፡ ሁሉ ተፈቅዶልኛል በእኔ ላይ ግን አንድ ነገር እንኳን አይሠለጥንብኝም፡፡ መብል ለሆድ ነው ሆድም ለመብል ነው፡፡ እግዚአብሔር ግን ሁለቱንም ያሳልፋቸዋል”፤ (፩ኛቆሮ.፮፥፲፪-፲፫) “ለሚጠፋ ምግብ አትሥሩ፤ ይልቅስ የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ የዘለዓለም ሕይወት ስለሚሆን ምግብ ሥሩ” እንደ ተባለ (ዮሐ.
ብራና ሚድያ - Birana Media
Photo
፮፥፳፯) ካለን ጊዜ ለመንፈሳዊ ሕይወታችን ጊዜ በመስጠት ቢበሉት የማያስርበውን፣ ቢጠጡት የማያስጠማውን፣ የዘለዓለም ሕይወት የምናገኝበትን ሥጋ እና ደሙን ተቀብለን መንግሥቱን እንድንወርስ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን።

ሥርዓት ቅዳሴ
ከሠራኢ ካህን፣
ቅዳሴ፡ ዘእግዚእነ
“ዘበእንቲኣነ ለሰብእ ወበእንተ መድኃኒትነ፡ ወረደ እምሰማያት። ተሰብአ፡ ወተሠገወ እመንፈስ ቅዱስ ወእማርያም እምቅድስት ድንግል፤ ስለ እኛ ስለ ሰዎች እኛን ለማዳን ከሰማይ ወረደ፤ በመንፈስ ቅዱስ ግብር  ከቅድስት ድንግል ማርያም ፍጹም ሰው ሆነ፡፡”

ወንጌል፡ ዮሐ.፫፥፲-፳፬
የዕለቱ ምንባባት:-
•  በሠራኢ ዲያቆን (ዕብ.፲፫፥፯-፲፯)
•  በንፍቅ ዲያቆን (ያዕ.፬፥፮-ፍጻሜ)
•  በንፍቅ ካህን (የሐዋ. ፳፭፥፲፫-ፍጻሜ)

ምስባክ፡ “ተቀነዩ ለእግዚአብሔር በፍርሃት ወተሐሠዩ ሎቱ በረዓድ አጽንዕዋ ለጥበብ ከመ ኢይትመዐዕ እግዚአብሔር” (መዝ.፪፥፲፩)

ወንጌል፡ ዮሐ.፫፥፲-፳፬

ስብሐት ለእግዚአብሔር ኪያነ ዘፈጠረ ከመ ናምልኮ፤ እንድናመልከው እኛን ለፈጠረ ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይሁን!
©️ማኅበረ ቅዱሳን
ቅድስት

የዐቢይ ጾም ሁለተኛ ሳምንት

የቅድስና ባለቤት የሆነው እርሱ እግዚአብሔር አምላክ ነው። እቀደስ አይል ቅዱስ፣ እባረክ አይል ቡሩክ ነው። በእርሱ የባሕርይ ቅድስና እኛን በአርአያውና በአምሳሉ ፈጥሮ ቡሩክ ሆኖ ባረከን፣ ቅዱስ ሆኖ ቀደሰን፣ሕያው ሆኖ ሕያዋን አደረገን። የጸጋ ቅድስናንም ከእርሱ አገኘን። ቅድስናው የተለየ፣ የከበረ፣ የሚመሰገን፣ የሚሰጥ/የሚያድል፣ የሚያነጻ፣ የሚባርክ እናም የሚያስተሰርይ ስለሆነ እንከን፣ ጉድለት የሌለበት ምሉዕ ነው። ለባለሟሎቹ ቢሰጠው የማይጎድል፣ ተከፍሎ የሌለበት ቅድስና ሆኖ እኛም የቅድስና በጸጋ ተካፋይ ሆነናል።

የተሰጠንን ቅድስና ገንዘብ እንድናደርግ እና እንድንጠቀምበት ደግሞ በጾም፣ በጸሎት፣ በስግደት፣ በምጽዋትና በሌሎች በጎ ምግባራት መትጋት ይገባናል። ‹‹እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ›› እንዲል፡፡ (ዘፍ.፪፥፫፣ ዘሌ.፲፱፥፪) የት መሄድ እንዳለብንም በግልጽ ልበ አምላክ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ‹‹ወደ ቅዱስ መቅደስህ እሰግዳለሁ፤ ስለ ትምህርትህና ስለ እውነትህ ስምህን አመሰግናለሁ፤ በሁሉ ላይ ቅዱስ ስምህን ከፍ ከፍ አድርገሃልና›› ይላል። (መዝ.፻፴፯÷፪) የተቀደሰን መሥዋዕት በተቀደሰ ቦታ እንፈጽማለን። መቼ ቢሉ፣ በሰንበት፣ በበዓላት በማኅበረ ዐቢይ/ክርስቲያኖች በሚሰበሰቡበት፣ ስመ እግዚአብሔር በሚጠራበት፣ ታቦት ባለበት፣ እግረ እግዚአብሔር በቆመበት ቅዱስ ስሙን ከፍ ከፍ በማድረግ ቅድስናን ገንዘብ እናደርጋለን።

ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ለዐቢይ ጾም ሁለተኛው እሑድ በአዘጋጀው ምስጋና አማካኝነት ዕለቱ ‹‹ቅድስት›› የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ ትርጉሙም ‹‹የተለየች፣ የተመረጠች፣ የከበረች›› ማለት ነው። (መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ገጽ ፯፻፹፬) ቅድስት የሚለው ቃል ዕለቱ ‹‹ቅድስት›› ተብሎ የተሰየመበት ምክንያት ስለ ዕለተ ሰንበት እንዲሁም ስለ እግዚአብሔር አምላክ ፍጹም ቅድስና የሚያወሳ በመሆኑ ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክም ፍጥረታቱ የእርሱን ስም በማመስገን ይኖሩ ዘንድ ለቅድስና ሕይወት ፈጥሯቸዋልና በሰንበት እሑድ ክርስቲያኖች የቅድስና ተግባራትን ከሌላው ቀን አብዝተው ይፈጽማሉ፡፡ ዕለት ከተግባር፣ ስም ከክብር የተባበረባት ክብርት ሰንበት ቅድስት ስለሆነች ቅዱስ ያሬድ “ቅድስት” ብሎ ጠራት። ይኸውም የምትቀድስ፣ ከብራ የምታከብረን፣ አክብረናት የምንከብርባት በመሆኗ ነው።

ለዚህም ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በጾመ ድጓ “ግነዩ ለእግዚአብሔር ወጸውዑ ስሞ ወንግርዎሙ ለአሕዛብ ምግባሮ፤ ሀቡ ስብሐተ ለስሙ፤ አክብሩ ሰንበተ ተገበሩ ጽድቀ፤ ዝግቡ ለክሙ መዝገበ ዘበሰማያት ኀበ ፃፄ ኢያማስኖ ወኢይረክቦ ሰራቂ፤ ድልዋኒክሙ ንበሩ ዘበላዕሉ ጸልዩ ኀበ ሀሎ ክርስቶስ” ትርጉም፦ “ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ ስሙንም ጥሩ፤ ሥራውንም ለአሕዛብ ንገሯቸው፤ ለስሙም ምስጋናን አቅርቡ ሰንበትን አክብሩ፤ እውነትንም አድርጉ፤ ብል የማያበላሸው ሌባም የማያገኘው በሰማያት ያለ መዝገብን ለእናንተ ሰብስቡ፤ ተዘጋጅታችሁም ተቀመጡ፤ ክርስቶስ ወዳለበት ወደ ላይ አስቡ፡፡“ ስለዚህ ሰው ሰንበትን አክብሮ ጾሞ ጸልዮ፣ ቅድስናን ጠብቆ መኖር እንዲችል እግዚአብሔር የፍቅሩ መገለጫ የሆኑ ትእዛዛቱ ይነግሩናል።

ቅዱስ ያሬድም ወቅቱን “ቅድስት” ብሎ ሲሰይም፦

፩. የአርባ ቀን ጾም መጀመሪያ በመሆኑ፦ ዕለቱ ከዐቢይ ጾም ቀናት ውስጥ አርባው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመው ጾም መጀመሪያ ስለሆነች፣

፪. ቅድስት ሰንበት ላይ በመዋሉ፣ እንግዲህ “የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ” ተብሏል፡፡ (ዘፀ.፳፥፰) የሰንበትን ቀን አስቀድሞ የቀደሰ የባረከ ራሱ እግዚአብሔር ነው፡፡ እግዚአብሔርም ሰባተኛውን ቀን ባረከው፤ ቀደሰውም፤ እግዚአብሔር ሊያደርገው ከፈጠረው ሥራ ሁሉ በእርሱ ዐርፎአልና፡፡” (ዘፍ.፪፥፫)
“ከምእመናን ወገን አንድስ እንኳን በእሑድ ቀን ለገንዘብ መትጋት፣ ገንዘቤን አምጣ ብሎ መጣላት እና ዋስ መያዝ አይገባውም። ሁሉም ምእመናን ወደ ቤተ ክርስቲያን በንጽሕና በትሕትና ሆነው። ዳኛ ግብሬን፣ አበዳሪ ብድሬን፣ ኤጲስ ቆጶስ ዐሥራት በኵራት፣ ነጋ ድራስ ቀረጥ አምጡ ይሉናል ብለው ሳይፈሩ ይምጡ።

፫. ወቅቱ ወርኃ ጾም በመሆኑ፦ ምእመናን ይህንን ወቅት በጾም፣ በጸሎት፣ በእንባ፣ በስግደት፣ በአርምሞ፣ በመልካም ሥራ ቅድስናን የምናገኝበት፣ ጊዜው ሰው ወደ እግዚአብሔር አብዝቶ የሚተጋበት ወቅት በመሆኑ፣ ለእግዚአብሔር የሚገባ ነገር ለማድረግ የነገር ሁሉ መጀመሪያ፣ ለመልካም ነገር መነሻው በቅድስና በንጹሕ ልቡና መቅረብ ስለሆነ ቅድስት ብሏታል። “እስመ ጾም እማ ለጸሎት ወእኅታ ለአርምሞ ወነቅዓ ለአንብዕ መቅድመ ኩሉ ግብር ሠናይት፤ ጾም ማለት የጸሎት እናት፣ የትሕትና እኅት፣ የእንባ ምንጭ፣የመልካም ሥራ ሁሉ መጀመሪያ ናት” እንዳለው ቅዱስ ያሬድ። ”ጾምን ቀድሱ፤ ጉባኤውንም ዐውጁ” የተባልን የተሰጠንን የጸጋ ቅድስና በእጃችን ላይ መኖሩን አመላካች ቃል ነው። (ኢዩ.፩፥፲፬)

፬. የወንጌል ትእዛዝ በመሆኑ ዕለቱን ተጠቅሞ ዓለምን አስተምሮበታል። “ዛቲ ዕለት እንተ ገብረ እግዚአብሔር ንትፈሣሕ ወንትሐሠይ ባቲ” ትርጉም፡- “ይህች ዕለት እግዚአብሔር የሠራት ቀን ናት፤ ሐሤትን እናድርግ፥ በእርስዋም ደስ ይበለን።” (መዝ.፻፲፯፥፳፬) ቅዱስ ዮሐንስም በራእዩ ሰንበት የጌታ ቀን ስለመሆኗ እንዲህ ይላል፤ “በጌታ ቀን በመንፈስ ነበርሁ፡፡” (ራእ. ፩፥፲)

ሊቃውንቱ በፍትሐ ነገሥት “ተጋብኡ ኵሎ ዕለት ኀበ ቤተ ክርስቲያን ወፈድፋደሰ በዕለተ ሰንበት ወበበዓላት ወበዕለተ ትንሣኤ ዘውእቱ ዕለተ እሑድ” ትርጉም፦ “ሁልጊዜ በቤተ ክርስቲያን ተሰብሰቡ፤ ይልቁንም በዕለተ እሑድ፣ በዕለተ ቀዳሚት፣ በጌታ በዓላት ወደ ቤተ ክርስቲያን ተሰብሰቡ” በማለት አዘውናል፡፡ (ፍትሐ ነገሥት፣ ገጽ ፪፶፬)

በትጋት ጾመን፣ ጸልየን ርስቱን እንድንወርስ የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ምልጃ፤ የቅዱሳን በረከት ይጠብቀን።

የዕለቱ መዝሙር (ከጾመ ድጓ)፦ግነዩ ለእግዚአብሔር

ምንባባት፡ (፩ኛ.ተሰ.፬÷፩-፲፫)፣ (፩ኛጴጥ.፩÷፲፫-ፍጻ.፣ሐዋ.፲÷፲፯-፴
ምስባክ “እግዚአብሔርሰ ሰማያተ ገብረ:: አሚን ወሠናይት ቅድሜሁ፣ ቅድሳት ወዕበየ ስብሐት ውስተ መቅደሱ፤ እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ፈጠረ፡፡ እምነትና በጎነት በፊቱ፣ ቅድስናና የክብር ገናናነት በመቅደሱ ውስጥ ናቸው፡፡” (መዝ.፺፭÷፭)
ወንጌል (ማቴ.፮÷፲፮-፳፭)
ቅዳሴ: ዘኤጲፋንዮስ

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
«ወኢትምጻእ ቅድመ እግዚአብሔር አምላክከ ዕራቀከ»
በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ራቁትህን አትምጣ
【ዘዳ ፲፮፥፲፮】

በዚህ መጻሕፍት ይተባበሩበታል
✧ "ወኢታስተርኢ ቅድሜየ ዕራቀከ ☞ በፊቴም አንድ ሰው ባዶ እጁን አይታይ" 【ዘጸ ፴፬፥፳】
✧ "ወኢትትረአይ በቅድሜየ ዕራቀከ ☞ በፊቴም ባዶ እጃችሁን አትታዩ። 【ዘጸ ፳፫ ፥፲፭ / ፳፬፥፲፩】
✧ ሲራክም "ኢትባእ ቅድመ እግዚአብሔር ዕራቀከ ☞ ወደ እግዚአብሔር ማደሪያ ባዶህን አትግባ" 【ሲራ ፴፪፥፮】

በቅድሜየ ወይም በፊቴ ማለቱ ለእግዚአብሔርስ ሁሉ ቅድሙ ወይም ፊቱ ነው፤ በሁሉ ያለና ከፊቱ የሚሸሸግ የሌለ ሆኖ ሳለ መገለጫ መክበሪያውን ሲያይ ፊቴ ይላል።
☞ በዘመነ ብሉይ በደብተራ ኦሪትና በቤተ መቅደስ በረድኤት ያድር ነበርና
☞ ዛሬም በዘመነ ሐዲስ በሥጋውና ደሙ በቤተክርስቲያን ይገለጽባታልና ከሁሉ አብልጦ ማደርያ ቤቱን ቅድሜየ አላት።

ይህን ራሱ ሙሴ ሲገልጠው «ቅድመ እግዚአብሔር ፥ ውስተ መካን ዘኀርየ እግዚአብሔር አምላክከ ☞ በእግዚአብሔር ፊት ፥ እርሱ አምላክህ በመረጠው ስፍራ» ሲል አስረድቷል፤

ለሰው አካሉን ገልጦና ሰውነቱን አራቁቶ ለመታየት የታወቀ (በቂ) ምክንያት ያስፈልጋል፤ ሠለስቱ ምዕት ለመታከም «የሚተኮስ» «የሚታገም» አካል ቢኖር አልያም ከጸበል ሊነከሩና ሊታጠቡ እንጂ በሌላውስ መንገድ በማንም ፊት እርቃን መታየት ክልክል ነው ብለዋል።

"ወዓዲ ተዐቀብ ከመ ኢትትዐረቅ እምልብስከ ቅድመ መኑሂ ዘእንበለ ዳዕሙ ሶበ ይረክበከ ምክንያት ለተዐርቆ። ☞ ዳግመኛም በማንም ፊት ከልብስህ ራቁትህን እንዳትሆን ተጠበቅ፤ የምትራቆትበት ምክንያት ቢያገኝህ ነው እንጂ" 【ሃይ አበው ፳፥፲፪】

ራቁትነት በውጭ ያለ (አፍኣዊ) ገላን መክደኛ ነውርን መሸፈኛ ከሆነው ጨርቅ ከመራቆት በላይ በሦስት መንገድ ውሳጣዊ እርቃንን የሚያስረዱ ሦስት መንገዶችን እናስቀምጥ

፩ኛ] ራቁት የሚለው #በኃጢዓት_መመላለስ በበደል መጽናትን ነው። ያንን በንሰሐ ሳያጠሩ በእግዚአብሔር ፊት መቆም የሚገባ አይደለምና።

በኃጢዓት ከመውደቃቸው አስቀድሞ የማይተፋፈሩ የነበሩ አዳምና ሴቲቱ ከሕግ ሲወጡ ራቁትነትን አወቁ፤

“የሁለቱም ዓይኖች ተከፈቱ፥ እነርሱም ዕራቁታቸውን እንደ ሆኑ አወቁ፤ የበለስንም ቅጠሎች ሰፍተው ለእነርሱ ለራሳቸው ግልድም አደረጉ።” 【ዘፍ ፫፥፯】

ቅዱስ ዳዊት ይህን ድርጊት «እንሰሳትን መምሰል» ብሎታል
【መዝ ፵፰፥፲፪/፳】

አባ ጊዮርጊስም በመጽሐፈ ምሥጢር እርቃን ከመቅረት በላይ እንሰሳትን መምሰል ወዴት አለ? ብሏል
“ምንት ውእቱ ተመስሎ እንስሳ ዘእንበለ ተከሥቶ ዕርቃኑ ማእከለ ዕፀዊሃ ለገነት ሶበ ነፍጸ አጽፈ ብርሃን ዘላዕሌሁ ኀደጎ አጽፈ ብርሃን ⇨ በገነት ዛፎች መካከል ዕርቃኑን ሆኖ ከመተየት በስተቀር እንስሳን መምሰል ምንድ ነው? የብርሃን ልብስ ከበላዩ ላይ በተገፈፈ ጊዜ የብርሃን መጐናጸፊየው ተለየው”

ክዶ ከአምላኩ ተለይቶ የነበረው ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታው በፊቱ በቆመ ሠዓት ለጊዜ እርቃኑን በልብስ ደብቆ ከባህር ጠልቆ መታየቱ ነውን በንሰሐ አርቆ ሥጋን በቅጣት አስጨንቆ ድኅነት እንደሚገኝ ማሳያ ነው።
“ኢየሱስ ይወደው የነበረውም ደቀ መዝሙር ጴጥሮስን፦ ጌታ እኮ ነው አለው። ስለዚህ ስምዖን ጴጥሮስ ጌታ መሆኑን በሰማ ጊዜ ዕራቁቱን ነበረና ልብሱን ታጥቆ ወደ ባሕር ራሱን ጣለ።” 【ዮሐ ፳፩፥፯】

እንደ ወርቅ የተፈተነ ቃሉን በመያዝ ፣ እንደ ነጭ ልብስ የከበረውን ጸጋ ልጅነት ለማጽናት… ከፊቱ ቀርቦ በንሰሐ መመላለስ ይገባል
“ባለ ጠጋ እንድትሆን በእሳት የነጠረውን ወርቅ፥ ተጐናጽፈህም የራቁትነትህ ኃፍረት እንዳይገለጥ ነጭ ልብስን፥ እንድታይም ዓይኖችህን የምትኳለውን ኵል ከእኔ ትገዛ ዘንድ እመክርሃለሁ።” 【ራእ ፫፥፲፰】

፪ኛ) ራቁት ማለት ራስን መግለጥ #ተርእዮን_መሻት እግዚአብሔርን መርሳት አምላከ ቅዱሳንን ማስረሳት ማለት ነው። ራስን ለመስበክና ስለራስ ለማውራት እግዚአብሔር ፊት መቆም ተገቢ አይደለም።
በሰማይ ያሉ አገልጋዮቹ ከመንበሩ ፊት የቆሙ መላእክቱ ፊት እግራቸውን መሸፈናቸው ለዚህ መማርያ ይሆነናል
“ሱራፌልም ከእርሱ በላይ ቆመው ነበር፥ ለእያንዳንዱም ስድስት ክንፍ ነበረው፤ በሁለት ክንፍ ፊቱን ይሸፍን ነበር፥ በሁለቱም ክንፍ እግሮቹን ይሸፍን ነበር፥ በሁለቱም ክንፍ ይበር ነበር።” 【ኢሳ ፮፥፪】

ራሱን ሲሰብክ ለዋለው
"ኢየሱስን ልናይ እንወዳለን ብለው ለመኑት” (ዮሐ 12፥2) የሚል መልእክት ልከው
ኋላ ተመልሶ ራሱን ሰውሮ ክብረ ክርስቶስን ቢሰብክላቸው
“ጌታን ባዩ ጊዜ ደስ አላቸው።” (ዮሐ20፥20) ብለው አመስግነውታል።

፫ኛ) ራቁት ማለት ባዶ እጅ #ምንም_ሳይዙ_መምጣት ማለት ነው፤ መባዕ፣ ስእለት ፣ ምጽዋት ፣ ዐሥራት፣ በኩራት፣ ቀዳምያት እና መስዋእት ሳይይዙ ወደመቅደሱ መምጣት የሚገባ አይደለምና።

“ስጡ ይሰጣችሁማል፤ በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ተመልሶ ይሰፈርላችኋልና፥ የተጨቈነና የተነቀነቀ የተትረፈረፈም መልካም መስፈሪያ በእቅፋችሁ ይሰጣችኋል።” 【ሉቃ ፮፥፴፰】

©️ ዲ/ን ቴዎድሮስ በለጠ መንግስቱ ( ዶ/ር )
መነኰሳዪት ቅድስት ሣራ

  ቅድስት ሣራ ከላይኛው ግብጽ ናት ወላጆቿም የክብር ባለቤት ክርስቶስን የሚያመልኩ ክርስቲያን ናቸው። እጅግም ባለጸጎች ነበሩ። ነገር ግን ከእርስዋ በቀር ልጆች የሏቸውም በመልካም አስተዳደግም አሳደጓት ለክርስቲያን የሚገባ ትምህርትን ሁሉ አስተማሩዋት ደግሞም ጽሕፈትን አስተማሯት ሁሉጊዜም የቤተ ክርስቲያንን መጻሕፍት ታነባለች ይልቁንም የመነኰሳትን ዜና ታነብ ነበር። መጻሕፍትንም አዘወትራ ስለምታነብ የምንኵስና ልብስ ለመልበስ ፈለገች በላይኛው ግብጽ ከሚገኙ ገዳማትም ወደ አንዱ ገዳም ሄዳ ገባች ብዙ ዘመናትም ደናግልን እያገለገለች ኖረች።

ከዚህም በኋላ የምንኵስና ልብስን ለበሰች ሰይጣንን ድል እስከ አደረገችው ድረስ። ሰይጣን የሚያመጣውን ሥጋዊ ፍትወት እየታገለች ዐሥራ ሦስት ዓመት ኖረች። ንጽሕናን ከመውደዷ ጽናት በተሸነፈ ጊዜ በትዕቢት ሊጥላት ወዶ በቤት መዛነቢያ ልትጸልይ ቁማ ሳለች ተገልጦ "ሣራ ሆይ ሰይጣንን ድል አደረግሽዋልና ደስ ይበልሽ" አላት እርሷም መልሳ "እኔ ደካማ ሴት ነኝ ከክብር ባለቤት ከጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ድል አድርጌ ላበረው አልችልም" አለችው።

ይህችም ቅድስት አብረዋት ላሉ ደናግል ጥቅም ያላቸውን ብዙ ትምህርቶችን ታስተምራቸው ነበር። እንዲህም ትላቸዋለች "ከቀን ብዛት ጠላት እንዳያስተኝ እኔ እንደምሞት አስቀድሜ ሳላስብ እግሬን ከአንዱ መወጣጫ ደረጃ ወደ ሁለተኛዋ  አውጥቼ አላኖራትም"። ዳግመኛም "ለሰው ርኅራኄ ማድረግ በተሻለው ነበር ይህንንም በሚያደርግ ጊዜ የኋላ ኋላ በእግዚአብሔር ፈቃድ ውስጥ ይኖራል" በዜና አረጋውያን መነኰሳት መጽሐፍ ውስጥ የተጻፉ ሌሎች ብዙ ቃሎችንም ተናግራለች።

ታላቅ ተጋድሎም እየተጋደለች በዓቷም በባሕር ዳርቻ ሁኖ ሰባት ዓመት ኖረች አንዲት ቀን እንኳን ከሰው አንዱም አላያትም እርሷ ግን ሁሉን ታይ ነበር። ሸምግላ እስከ ሰማንያ ዓመት በደረሰች ጊዜ ከዚህ ዓለም የሕይወት ማሠሪያ ተፈትታ የዘላለም ተድላ ደስታ ወደሚገኝበት መጋቢት15 ቀን ሔደች። የቅድስት ሣራ ጸሎቷ በረከቷ ከእኛ ጋራ ለዘላለሙ ይኑር አሜን።
ብራና ሚድያ - Birana Media
Photo
ምኵራብ፡- የዐቢይ ጾም ሦስተኛ ሳምንት
 
“ቦአ ኢየሱስ ምኵራበ አይሁድ ወመሐረ ቃለ ሃይማኖት፤ ወይቤሎሙ ምጽዋተ አበድር እመሥዋዕት፤ አነ ውእቱ እግዚኣ ለሰንበት ወአቡሃ ለምሕረት፤ እግዚኣ ውእቱ ለሰንበት ወልደ እጓለ እመሕያው፤ ጌታችን ኢየሱስ ወደ አይሁድ ምኵራብ ገባ፤ የሃይማኖት ቃልን አስተማረ፤ ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን እወዳለሁ፤ የሰንበት ጌታዋ የምሕረት አባቷም እኔ ነኝ፤ የሰው ልጅም የሰንበት ጌታዋ ነው።” (ጾመ ድጓ)
 
በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሦስተኛውን የዐቢይ ጾም ሳምንት “ምኵራብ” ይባላል። ቀጥተኛ ፍቺው “ኮረብታ፣ ተራራ የሚያህል ታላቅ ሕንጻ፣ ሰቀላ መሰል አዳራሽ” ሲሆን፣ የአይሁድ መካነ ጸሎት ወይም ቤተ መቅደስ በመሆን ያገለግል ነበር። በብሉይ ኪዳን አይሁድ ቤተ መቅደስ ነበራቸው፡፡
 
ናቡከደነጾር ኢየሩሳሌምን በወረረ ጊዜ ግን ቤተ መቅደሱን አፈረሰ፤ ሕዝቡን ወደ ባቢሎን አፈለሰ፤(፪ኛነገ.፳፬-፳፭፣ኤር.፬፥፯:፣፴፱፥፩-፲፣፶፪፥፩-፴) ከዚህ ጊዜ ጀምሮ አይሁድ በሚኖሩባቸው ሥፍራዎች ሁሉ ለጸሎት ቤት ይሠሩ ነበር፡፡ በዚያን ዘመን ቢያንስ ዐሥር አባ ወራዎች/የቤተ ሰብ ኃላፊዎች/ በቦታው ከተገኙ እነዚህን ምኵራቦችን ለመሥራት ይፈቀድላቸው ነበር፡፡ (Talmud Mishnah, Responsa literature, Jewish Encyclopedia, Academic Scholarly Works.)  ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኢየሩሳሌም እየተዘዋወረ በሚያስተምርበት ጊዜ ግን ብዙ ምኵራቦች ነበሩ፡፡ በሐዲስ ኪዳንም ለሐዋርያት በብዛት የስብከት ዓውደ ምሕረቶች ሆነው አገልግለዋል።

 
ምኵራበ አይሁድ በውስጡ የብራና የሕግ እና የነቢያት መጻሐፍት ይገኛሉ፡፡ ምእመኑ እንዲሰማቸው ከፍ ባለ መድረክ ላይ በመሆን መምህራንና ካህናት ቆመው መጻሕፍትን ያነባሉ፤ ቃለ እግዚአብሔርንም  ያስተምሩ ነበር። የምኵራብ ሹማምንት አለቆች ጥፋተኛ ሰው ሊቀጡ ሥልጣን ነበራቸው፡፡ አገልጋይ ወይም የሚራዱ ወጣቶችም ልጆችን በማስተማር፣ በማቅረብ በተጨማሪ የአለቆችን ትእዛዝ በመፈጸም ያገለግላሉ፡፡
 
በሰንበት ሕዝብ ሁሉ በምኵራብ ተሰብስቦ ከሕግና ከነቢያት ንባብ፣ ስብከትና ቡራኬ በመቀበል አምልኮታቸውን ይፈጽሙ ነበር፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምኵራብ ተገኝቶ ሕዝቡን አስተምሯል፡፡ ቅዱስ ሉቃስ በወንጌሉ ”ወዳደገበትም ወደ ናዝሬት መጣ፤ እንደ ልማዱም በሰንበት ቀን  ምኵራብ ገባ ሊያነብም ተነሣ” እንዳለ ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ፣ መማር፣ መመርመር፣መተርጎም፣ጉባኤ መሥራት አዘውትረው የሚፈጽሙት ተግባር እንደነበር ያስረዳል።(ሉቃ.፬፡፥፲፮)
 
ነገር ግን በምኵራብ ሰዎች ለተለያየ ዓላማ ይሰበሰቡ ነበር፡፡
 
፩. አማናዊ እረኛ ነው ብለው፦ ወልድ ዋሕድ ብለው ሲጠብቁት የነበረው ተስፋ “ደረሰልን፤ ወረደ፤ ተወለደ፤ የዓለም መድኃኒት እርሱ ነው” ብለው አዳኝነቱን አምነው ይከተሉታል። “ነዋ በግዑ ለእግዚብሔር ዘያአትት ወያሴስል ኃጢአተ ዓለም፤ የዓለሙን ኃጢአት የሚያስተሰርይ የእግዚብሔር በግ መሆኑን አውቀው የሚከተሉት አሉ። ”በጎቹም ድምፁን ያውቃሉና ይከተሉታል” እንዲል። (ዮሐ.፲፥፬)
 
፪. የቃሉን ትምህርት የእጁን ተአምራት ሽተው፦ ከደዌ ለመፈወስ ይሰበሰባሉ፤ ልብሱን ዳሰው፣ ወድቀው ሰግደው፣ ጥላውን ተጋርደው፣ በእጁ ተዳሰው የሚፈወሱ ነበሩ። (ማር. ፭፥፳፪ እስከ ፍጻሜ)። ጌታችን በዕለተ ሰንበት ሕዝብ በተሰበሰበበት በምኵራብ እንደሚያስተምር ያስረዳናል፤ ”ሰንበትም በሆነ ጊዜ በምኵራብ ያስተምር ጀመር፤…ወደ ምኩራባቸውም ገብቶ ዝም ይሉ ዘንድ ገሠፃቸው፤ እነርሱም ትምህርቱን፣ የቃሉን ግርማ፣ የአነጋገሩን ጣዕምና፣ የአንደበቱን ቅልጥፍና አደነቁ፡፡”  (ማር.፮፥፩) “ወደ ገዛ አገሩም መጥቶ እስኪገረሙ ድረስ በሚገባቸው ያስተምራቸው ነበር።” (ማቴ.፲፫፥፶፬)
 
፫. ምግበ-ሥጋ ፈልገው ደም ግባቱን አይተው:- ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከምኵራብ ጉባኤ ትምህርት በኋላ ጥቂቱን አበርክቶ እልፉን ይመግብ ስለነበር ጉባኤውን ይታደማሉ። ክርስቲያኖች እግዚአብሔርን የምናመልከው ምግበ ሥጋ ስለሰጠን አይደለም። እርሱንማ ለሕዝብም ለአሕዛብም ሳይሰስት የሚመግብ መጋቤ ዓለማት ነው። ክርስቲያን በመብል አይገመትም። “እንግዲህ በመብልም ቢሆን÷ በመጠጥም ቢሆን÷ በልዩ ልዩ በዓላትም ቢሆን÷ በመባቻም ቢሆን÷ በሰንበትም ቢሆን የሚነቅፋችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ፡፡” እንዲል፡፡ (ቆላ. ፪፥፲፮ እስከ ፍጻሜ)
 
፬. ለክስ የሚቀርቡ አሉ፦ ከቃሉ ግድፈት ከትምህርቱ ስሕተት የሚፈልጉ ሰቃለያን አይሁድ፣ ሊቃነ ካህናት አምላክነቱን የሚጠራጠሩ አይሁድ የሸንጎውን ጌታ ለሸንጎ ፍርድ ሊያቀርቡት ከግር በግር ይከተሉት ነበር። “ወጸቢሖ ተጋብኡ ሊቃነ ካህናት ወጸሐፍት ወሊቃናተ ሕዝብ ወወሰድዎ ውስተ ዐውዶሙ። ወይቤልዎ እመ አንተሁ ክርስቶስ ንግረነ ገሃደ ወይቤሎሙ እመኒ አይዳእኩክሙ ኢተአምኑኒ፡፡ በነጋም ጊዜ፥ የካህናት አለቆች፥ ጻፎችና የሕዝቡ ሽማግሌዎች ተሰብስበው ወደ ሸንጎአቸው ወሰዱት፡፡ “አንተ ክርስቶስ እንደ ሆንህ በግልጥ ንገረን” አሉት፡፡እርሱም እንዲህ አላቸው፥ “ብነግራችሁም አታምኑኝም” እንዲል፡፡ (ሉቃ. ፳፪፥፷፮፣ ማቴ.፳፮፥፶፱)
 
ዛሬም በአማናዊቷ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሥጋዊ ነገር ብቻ ገዝፎባቸው ቤተ መቅደሱን ለንግድ፣ ንዋያተ ቅድሳትን ለትርፍ ብቻ አሳልፈው የሚሸጡ፣ የሚለውጡ፣ ለክስ የሚፋጠኑ ከምኵራብ ያልወጡ የበጎችን እረኛ አሳልፈው የሚሰጡ አዋልደ ይሁዳ እንዳሉ ግልጽ ነው። “ወረከበ በምኵራብ እለ ይሠይጡ አልህምተ ወአባግዐ ወአርጋበ …፤ በመቅደስም በሬዎችን፣ ላሞችን፣ በጎችን፣ ርግቦችን፣ የሚሸጡትን አገኘ …፤ “ኢትግበሩ ቤተ አቡየ ቤተ ምስያጥ ቤትየሰ ቤተ ጸሎት ይሰመይ፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቦታ አታድርጉት፤ እናንተ ግን የሌቦች ዋሻ አደረጋችሁት፤ ቤቴስ የጸሎት ቤት ይባላል” እያለም የሃይማኖትን ቃል አስተማራቸው፡፡ (ዮሐ.፪፥፲፮፣ማቴ.፳፩፥፲፫)
 
በምኵራብ ይሸጡ፣ ይለውጡ የነበሩትን የገሠፀበት፣ ቤተ መቅደስን የከብት መንጃ የወርቅ መነገጃ ያደረጉ ሰዎችን ከእነ ሸቀጣቸው ከቤተ መቅደስ ያስወጣበት፣ ቤተ መቅደስ የእግዚአብሔር ማደሪያ፣ የመሥዋዕቱ መክበሪያ፣ የጸሎት ሥፍራ ምስካበ ቅዱሳን መሆኗን ያስተማረበት ዕለት ነው። ቃሉ በዚያን ዘመን ተነግሮ ብቻ ያለፈ አይደለም፤ ለእኛ የተነገረን መሆኑን አውቀን የባለቤቱ ጅራፍ ሳይገርፈን ልንመለስ ይገባል። “የገመድም ጅራፍ አበጅቶ ሁሉን በጎችንም በሬዎችንም ከመቅደስ አወጣቸው፥ የለዋጮችንም ገንዘብ አፈሰሰ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ፡፡” (ዮሐ.፪፥፲፬)
 
ከሚመጣው ጅራፍ ለመዳን እምነት ከተግባር ይዞ መገኘት ያስፈልጋል።” ወንድሞቻችን ሆይ÷ እምነት አለኝ፤ ምግባር ግን የለኝም የሚል ሰው ቢኖር÷ ምን ይጠቅመዋል? በውኑ እምነቱ ልታድነው ትችላለችን? ከወንድሞቻችን÷ ወይም ከእኅቶቻችን÷ የታረዙ ወይም የዕለት ምግብ ያጡ ቢኖሩ÷ ከእናንተም አንዱ …እንደዚሁም ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው።” እንዳለ። (ያዕ.፪፥፲፬ እስከ ፍጻሜ)
ብራና ሚድያ - Birana Media
Photo
 
የዕለቱ መዝሙር (ከጾመ ድጓ)፦ ቦአ ኢየሱስ ምኩራበ አይሁድ ወመሐረ ቃለ ሃይማኖት፤ጌታችን ኢየሱስ ወደ አይሁድ ምኩራብ ገባ፤ የሃይማኖት ቃልን አስተማረ፤
 
መልእክታት፦(ቆላ.፪፥፲፮ እስከ ፍጻሜ) (ያዕ.፪፥፲፬ እስከ ፍጻሜ)
ወንጌል፦ (ዮሐ.፪፥፲፪-እስከ ፍጻሜ)
(የሐዋ.፲፥፩-፰)
 
ምስባክ፦ “እስመ ቅንዐተ ቤትከ በልዐኒ፡፡ ትዕይርቶሙ ለእለ ይትዔየሩከ ወድቀ ላዕሌየ፡፡ወቀጻዕክዋ በጾም ለነፍስየ፡፡” ትርጉም “የቤትህ ቅንዓት በልቶኛልና፥ የሚሰድቡህም ስድብ በለዬ ወድቆአልና፡፡ ሰውነቴን በጾም አደከምኋት፡፡  (መዝ.፷፰፥፱)     
 
በምሕረቱ ይታደገን፤ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፤ አሜን!!!
ብራና ሚድያ - Birana Media
Photo
መፃጒዕ

አራተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ‹መፃጒዕ› ይባላል፡፡ ስያሜው በዮሐንስ ወንጌል ፭፥፩ ላይ ከሚገኘው ኃይለ ቃል ያለ ነው፡፡ መፃጒዕ ደዌ የጸናበት በሽተኛ፣ ሕመምተኛ ማለት ነው፡፡ መፃጒዕ ለ፴፰ ዓመት በአልጋው ላይ ሆኖ ምሕረትን ሲጠባበቅ የኖረ ሰው ነው። ስፍራዋም “ቤተ ሳይዳ” ትባላለች።ቤተ ሣህል (የምሕረት ቤት) ማለት ነው፤ መጠመቂያዋም በሰሎሞን ቤተ መቅደስ አጠገብ የምትገኝ ናት፡፡ (ዘሌ.፱፥፪) “ቤተ ሳይዳ” ዘይሁዳና “ቤተ ሳይዳ” ዘገሊላ የሚባሉ እንዳሉ በግልጽ በቅዱሳት መጻሕፍት ተገልጿል። “ወቦ ውስተ ኢየሩሳሌም ምጥማቃት ዘጵሩጳጥቄ ቅልንብትራ ዘውእቱ ቀላየ አባግዕ ብሂል ወይቤልዋ ስማ በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ ወባቲ ኃምስቱ ሕዋራት” …በኢየሩሳሌምም በበጎች በር አጠገብ በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ የምትባል አንዲት መጠመቂያ ነበረች፤ አምስትም መመላለሻ ነበረባት” ብሎ ሲገልጽ ነው። (ዮሐ.፭፥፪)


ቤተ ሳይዳ ዘኢየሩሳሌም ባለ አምስት በር፣ እርከን (መመላለሻ)፣ አምስት ዓይነት ድውያን ፈውስን ለማግኘት ጥምቀቱን ሲጠባበቁ የሚኖሩባት ናት። ውኃው የቤተ አይሁድ ምሳሌ፣ አምስት መመላለሻ የሕግጋተ ኦሪት እና የአምስቱ መጻሕፍተ ሙሴ ምሳሌ በእነዚያ ተጠብቀው ለመኖራቸው ምሳሌ ነው። ቀድሞ የገባባት አንዱ እንዲድን፣ እነርሱም አንድነት ቤተ እስራኤል ተሰኝተው ለመኖራቸው ምሳሌ ነው። አንድም አምስቱ እርከን (መመላለሻ) የአምስቱ አዕማደ ምሥጢር በዚያ ሊያምኑ ያሉ ተስፈኞችና ያመኑባትም ልጅነትን ያገኙባታልና። አምስቱ ዓይነት ድውያንም የአምስቱ ጾታ ምእመናን ከእነ ፈተናቸው ምሳሌ ነው፡፡ እነርሱም አእሩግ በፍቅረ ነዋይ፣ ወራዙት በዝሙት፣ አንስት በትውዝፍት (በምንዝር ጌጥ)፣ ካህናት በትዕቢት አእምሯችን ረቂቅ መዓረጋችን ምጡቅ እያሉ፣ መነኮሳት በስስት ምግብን በፈለጉት ጊዜ ባያገኙት ይልቁንም በአት እየፈቱ በከንቱ የመፈተናቸው ምሳሌ ሆኖ ይነገራል።

መልአከ እግዚአብሔር ወርዶ ውኃውን ሲያናውጥ ቀድሞ የገባ የሚነጻባት፣ ነገር ግን በዕለቱ ከአንድ ሕመምተኛ በቀር ለሌላው ፈውስ የማይደገምባት ቦታ ናት። ሐተታው የመጠመቂያ ውኀው የማየ ጥምቀት ምሳሌ ሲሆን ውኃውን ያናውጥ (ይባርክ) የነበረው መልአክ የቀሳውስት (ካህናት) “ለቀድሶተ ማየ ጥምቀት” የመውረዳቸው ምሳሌ ነው፤ ፈውሱም የሚከናወነው በዕለተ ቀዳሚት ሲሆን የሚፈወሰው አንድ ሰው ብቻ ነበር፡፡ የሚድነው አንድ ታማሚ ብቻ መሆኑ የአባቶቻቸው ምሕረት አለመቅረቱን ሲያሳይ፣ አለመደገሙ ደግሞ ፍጹም ድኅነት እንዳልነበረ ያሳያል፡፡

ለሠላሳ ስምንት ዓመታት ያህል በደዌ ዳኛ፣ በአልጋ ቁራኛ ተይዞ የኖረ መፃጉዕን በአልጋው ተኝቶ ሳለ ደዌው እንደጠናበት ፈውስ እንደዘገየበት አይቶ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቀርቦ ያንን በሽተኛ “ትፈቅድኑ ትሕየው? … ባድንህ ፈቃድህ ነውን?” አለው። ማእምረ ኅቡዓት ክርስቶስ፣” አዎን፥ እንዲለው እያወቀ”፤ ቅዱስ ጳውሎስ በዕብራውያን መልእክቱ “የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል፤ እኛን በሚቆጣጠር በእርሱ ዓይኖቹ ፊት ሁሉ ነገር የተራቆተና የተገለጠ ነው እንጂ፥ በእርሱ ፊት የተሰወረ ፍጥረት የለም” ብሎ የመሰከረለት ጌታችን ፈውስን በመጠባበቅ ከመዳን ውጪ ሌላ ዓላማ ያልነበረውን ይህን ሰው አይቶ ፈቃዱን እያወቀ ግን ፍቀድልኝና ላድንህ አለው። (ዕብ.፬፥፲፪) “ሰው በከንቱ ወራቱ ቍጥርና እንደ ጥላ በሚያሳልፈው ዘመኑ በሕይወቱ ሳለ ለሰው የሚሻለውን የሚያውቅ ማነው?“ እንዲል፤ (መክ.፮፥፲፪) የሚያስፈልገንን ሳንነግረው የሚያውቅ የሚሰጠንም ከእርሱ ከፈጣሪው ውጪ በእውነት ማን አለ?

መፃጉዕ በኋላ የሚክድ ነውና “ሳልፈቅድለት ነው ያዳነኝና አልጋ ያሸከመኝ” እንዳይል፣ በዕለተ ዓርብ የሚከስበትን ሲያሳጣውና ለኋላ ጥፋቱ የገዛ ኅሊናው እንዲቀጣው ፈቃዱን ጠየቀው። “ሰው የሌለኝ ሆኖ እንጂ ያንንማ ማን ይጠላል” በሚል ጉጉቱን ከወዳጅ አልባነቱ ጋር ድኅነትን ፈቅዶ ገለጠ። እስከ ውኃው መናወጥ ሳያቆየው “ተንሥእ ንሣእ ዓራተከ ወሑር …፤ ተነሥና አልጋህን አንሥተህ ሂድ” አለው፤ ወዲያው አፈፍ ብሎ በፍጥነት ያን ሁሉ ዘመን የተሸከመች አልጋ ተሸክሟት ሄደ።

ጌታችን መፃጉዕን ‹‹ተነሥተህ አልጋህን ተሸክመህ ሂድ›› ያለው፦

• አንደኛው ቅዱስ ኤስድሮስ እንዳለው አልጋው ጠንካራ የብረት አልጋ ነበረና ጽንዓ ተአምራቱን ለማሳየት ነው፡፡

• ሁለተኛው ‹‹ታዲያ ቢያድነኝ በከንቱ መች ሆነና የገዛ አልጋዬን ትቼለት የመጣሁ ለመዳኔ ዋጋ የከፈልኩበት አይደለምን?›› እንዳይል  “አልጋህን ተሸክመህ ሂድ” ብሎታል።

ያለ ተረፈ ደዌ አንሥቶት “ያለህን ይዘህ ሂድ፤ እኔ ከአንተ አንዳች አልሻም” ባሰኘ ቃል ሸኝቶታል። ታዲያ ይህ ምስኪን መፃጒዕ “ሰው የለኝም” ብሎ የደረሰለትን ረሳ፤ ማን እንደሆነ እንኳን አላወቀውም። ወንጌላዊውም “ዘሐይወ ኢያእመረ ዘአሕየዎ …፤የዳነው ያዳነውን አላወቀውም” ይለዋል። ( ዮሐ.፭፥፲፫) ይህን ሁሉ ያደረገው አምላክ ተዘነጋ። ዛሬም ከደዌው፣ ከማጣቱ፣ ከችግሩ፣ ከሥጋ ኑሮ ጉድለቱ እንደ መፃጒዕ አምላኩን ያልረሳ ማነው? ተአምራቱን አይቶ፣ ቃሉን ሰምቶ አምላኩን ያስታወሰስ ማነው? ቃሉን ያይና ይሰማ ዘንድ በእግዚአብሔር ምክር የቆመ ማን ነውና? ቃሉንስ ያደመጠስ ማን ነው?” (ኤር. ፳፫፥፲፰)። እኛም ብንሆን ከአዳም በደል ነጻ ያደረገንን አምላክ ውለታ ዘንግተን የምናፌዝ ሁላችንንም ወደ ልባችን እንድንመለስ ነቢዩ እንዲህ ሲል ይመክረናል “እስራት እንዳይጸናባችሁ አታፊዙ፡፡” (ኢሳ.፳፰፥፳፪ )

መፃጉዕ ያዳነው ማን እንደሆነ ሲጠየቅ እንኳን አላወቀም። ወንጌላዊውም “የዳነው ያዳነውን አላወቀውም” ብሎ ገልጾታል። (ዮሐ.፭፥፲፫) በምኩራብ አግኝቶት ያዳነውን እንዳወቀውም ሄዶ ለአይሁድ “ያዳነኝ እርሱ ጌታ ኢየሱስ ነው” ብሎ ነገራቸው፡፡ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በቤተ መቅደስ ሳለ ያን ያዳነውን ሰው አገኘውና “ዑቅ ኢትአብስ ዳግመ እንከ ከመ ዘየአኪ ኢይርከብከ፤ ከዚህ የከፋ “ስለ ደዌ ሥጋ ፈንታ ደዌ ነፍስ” እንዳያገኝህ ሁለተኛ እንዳትበድል” (ቁ.፲፬) ያለውን ዘንግቶ ደዌ ዘኃጢአትን ጠርቶ ተወዳጃት፤ በዕለተ ዓርብ የጌታውን ጉንጮች የጸፉች እጁም ደርቃ ሰላ ቀርታለች።

ዛሬም ቢሆን እንደ መፃጉዕ ሰዎች በኃጢአት ብዛት ልባቸው የደረቀና ያበጠ፣ ሰውነታቸው የሰለለ፣ ዓይነ ሕሊናቸው የታወረ፣ እግረ ልቡናቸው የተሰበረ ብዙዎች ሕሙማን በጠበል ቦታ፣ በገዳማት እና በአድባራት አሁንም አሉ፡፡ ፈውስን ይሻሉ፤ ድኅነትን ይፈልጋሉ፡፡ እንደ መፃጕዕ ቦታቸውን ሳይለቁ እግዚአብሔርን በተስፋ ቢጠብቁት አንድ ቀን ይፈወሳሉ።

ስለዚህ ይህ ሳምንት ጌታችን ድውያንን ስለመፈወሱ የሚነገርበትና እኛም ባለን ዓቅም በነፍስ በሥጋ የተቸገሩትን ሁሉ መርዳትና ማገዝ እንዳለብን የምንማርበት ሳምንት ነው፡፡ ሕሙማንን መጠየቅ፣ የታሰሩትን መጎብኘትና ማስፈታት፣ የተራቡትን ማብላት፣ የተጠሙትን ማጠጣት፣ የታረዙትን ማልበስ፣ ያዘኑትን ማረጋጋት ከጌታችን የተማርናቸው ክርስቲያናዊ ምግባራት   ናቸው፡፡
ብራና ሚድያ - Birana Media
Photo
በዚህ ዕለት የእግዚአብሔር አምላካችን ፈዋሽነትና አዳኝነት እንዲሁም ታዳጊነትና የወደቁትን የማይረሳ እውነተኛ መድኃኒት መሆኑ የሚዘከርበትና ምስጋና የሚቀርብበት ነው። ቅዱስ ዳዊትም "እግዚአብሔር ይረድኦ ውስተ ዐራተ ሕማሙ፣ ወይመይጥ ሎቱ ኩሎ ምስካቤሁ እምደዌሁ፣ አንሰ እቤ እግዚኦ ተሣሃለኒ፤ እግዚአብሔር በደዌው አልጋ ሳለ ይረዳዋል፤ መኝታውንም ሁሉ በበሽታው ጊዜ ያነጥፍለታል፣ እኔም አቤቱ ማረኝ እልሃለሁ” በማለት የእግዚአብሔርን አዳኝነት በዝማሬው አረጋግጧል።

ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “ችግረኛውን ከቀማኛው እጅ፣ ረዳት የሌለውንም ምስኪን ያድነዋልና” ሲል ሲቀኝ፣ (መዝ.፸፪፥፲፪)  ጻድቁ ኢዮብም እንዲሁ “ረዳት (ኃይል) የሌለውን ምንኛ ረዳኸው”  በማለት የእግዚአብሔርን አዳኝነት መስክሯል፡፡ (ኢዮ.፳፮፥፪) ስለዚህ ገንዘብ፣ ሥልጣን፣ ወገን፣ ረዳት የለኝም በማለት ተስፋ የቆረጥን ሰዎች እግዚአብሔር ከሰውም፣ ከሥልጣንም፣ ከገንዘብም በላይ ነውና እርሱን ተስፋ አድርገን ሁል  ጊዜ በስሙ መጽናናት እና የሚያስጨንቀንን ሁሉ በእርሱ ላይ መጣል እንደሚገባን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት “አቤቱ የሚፈልጉህ ሁሉ በአንተ ደስ ይበላቸው፤ሐሤትም ያድርጉ፡፡ ሁል ጊዜ ማዳንህን የሚወዱ ዘወትር እግዚአብሔር ታላቅ ይሁን ይበሉ” እንዳለው ሁል ጊዜም በአምላካችን እግዚአብሔር ደስተኞች

እንሁን። (መዝ.፵፥፲፮)

በኃጢአት ከሚመጣ ደዌ ተጠብቀን በአባታዊ ምሕረቱ የሚጠብቀንን ቸሩ አምላካችንን እያመሰገንን በቤቱ እንድንጸና መፃጒዕን “ተነሣ” እንዳለው እኛንም ከወደቅንበት ኃጢአት በንስሓ እንዲያነሣንና ዳግም ከመበደልም እንዲጠብቀን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁን። የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በረከት አይለየን፤ አሜን!

በመልእክታቱ የሚነበቡት 
(ገላ.፭፥፩ እና ያዕ.፭፥፲፬) ስለ ድውያን መፈወስ የሚያወሱ ናቸው፡፡
ከሐዋርያት ሥራ የሚነበውም እንዲሁ (ሐዋ.፫፥፩)

የዕለቱ ምስባክ፦ “እግዚአብሔር ይረድኦ ውስተ ዐራተ ሕማሙ፤ ወይመይጥ ሎቱ ኵሉ ምስካቢሁ እምደዌሁ፤ አንሰ እቤ  እግዚኦ ተሣለኒ፤ በደዌው አልጋ ላይ ሳለ ይረዳዋል፤ መኝታውንም ሁሉ ከበሽታው የተነሣ ይለውጥለታል፡፡ እኔስ “አቤቱ ይቅር በለኝ፤ አንተን በድያለሁና ለነፍሴ አስተስርይላት” አልሁ፡፡” ይላል (መዝ.፵፥፫)
Media is too big
VIEW IN TELEGRAM
#አስደሳች ዜና

ተከታታይ መንፈሳዊ ትምህርት መማር ለሚፈልጉ በሙሉ

መንፈሳዊ ትምህርት ለመማር አስበው አልመቻች ብሎት ይሆን? ምናልባትም የተማሩትን ማስታወስ ፈልገውስ ቢሆን?

እንግዲያውስ ተዋሕዶ ሚዲያ ማዕከል በተመችዎት ጊዜና ሰዓት ያለ ምንም ክፍያ እንዲማሩ መሠረታዊ የቤተክርስቲያን ተከታታይ ትምህርቶችን /ኮርሶችን/ ይዞ ቀርቧል

-ትምህርተ ሃይማኖት
-ነገረማርያም
-ነገረ ድኅነት
-ሥርዓተ ቤተክርስቲያን
-የቤተክርስቲያን ታሪክና ሌሎች የቤተክርስቲያን መሠረታዊ ተከታታይ ትምህርቶችን በተዋሕዶ ሚዲያ ማዕከል ዩቲዩብ ቻናል በቅርብ ቀን ይጠብቁን
በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደረጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ስዩም እና የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ መምህር ዋሲሁን በላይ ዛሬ ሚያዚያ 24/2016 ዓ.ም ከመኖሪያ ቤታቸው በጸጥታ አካላት መወሰዳቸው ታውቋል።

የሁለቱ አገልጋዮች መኖሪያ ቤት መፈተሹም ተገልጿል።

በአሁኑ ሰዓት ሜክሲኮ ፌዴራል ፓሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ የሚገኙ ሲሆን የተያዙበት ምክንያት አልታወቀም።

ዝርዝር እንደደረሰን እናቀርባለን።
ዓርብ ስቅለት (የድኅነት ቀን)

እንኳን አደረሰን!

ዓርብ ስቅለት የዕዳ ደብዳቤያችን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ለመጨረሻ ጊዜ የተደመሰሰበት፤ ከአጋንንት አገዛዝ ነጻ የወጣንበት ዕለት ስለኾነ ‹የድኅነት ቀን› ይባላል፡፡ ጌታችን ከተያዘባት ሰዓት አንሥቶ አይሁድ ከቀያፋ ወደ ሐና፣ ከሐና ወደ ቀያፋ ሲያመላልሱት አደሩ፡፡ ሲነጋ ከቀያፋ ወደ ጲላጦስ አደባባይ አስረው ወሰዱት (ማቴ. ፳፯፥፩-፶፯)፡፡ አይሁድ ይህን አጥፍቶአል የሚሉት ነጥብ ሳይኖራቸው ነውና ጌታችንን ለፍርድ ያቀረቡት ጲላጦሰ እነርሱ ወደ ተሰባሰቡበት ቦታ ወጥቶ ‹‹ይህን ሰው ወደ እኔ ያመጣችሁበት በደል ምንድን ነው?›› ሲል በጠየቃቸው ጊዜ በቂ ምላሽ አላቀረቡም፡፡

‹‹ክፉ የሠራ ባይኾንስ ወደ አንተ ባላመጣነውም ነበር›› በሚል የሸፍጥ ቃል ሲያጕረመርሙ ጲላጦስ መልሶ ‹‹እኔ ምንም ጥፋት አላገኘሁበትም፤ እናንተወስዳችሁ እንደ ሕጋችሁ ፍረዱበት፤›› አላቸው፡፡ አይሁድም ኦሪት ‹‹ኢትቅትል ብእሴ ጻድቀ ወኀጥአ ኢታኅዩ፤ ጻድቅን ሰው አትግደል፤ ኀጥኡንም ከፍርድአታድን፤›› ትላለችና ‹‹እኛስ ማንንም ልንገድል አልተፈቀደልንም፤›› ብለዋል (ዮሐ. ፲፰፥፳፰-፴፩)፡፡ ይኸውም መንፈስ ቅዱስ ‹‹በሕጋችን ጻድቀ ባሕርይክርስቶስን መግደል አይገባንም ሙሉ በሙሉ ጥፋተኞች ነን፤›› ሲያሰኛቸው ነው፡፡ በኋላም እርሱ ሞቶ ዓለም ይድን ዘንድ ወደ ምድር መጥቷልና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያለ ጥፋቱ ሞት ተፈረደበት፡፡ ስለዚህም ገርፈው ሰቀሉት፡፡

ጌታችን ሲሰቅልም የሚከተሉት ሰባት ተአምራት ተፈጽመዋል፤

፩. ፀሐይ ጨለመ፤

፪. ጨረቃ ደም ኾነ፤

፫. ከዋክብት ረገፉ፤

፬. የቤተ መቅደስ መጋረጃ ተቀደደ፤

፭. አለቶች ተፈረካከሱ፤

፮. መቃብራት ተከፈቱ፤

፯. ሙታን ተነሡ (ማቴ. ፳፯፥፶፩-፶፬)፡፡

ጌታችን በመስቀል ላይ ሳለ የሚከተሉትን ሰባት ዐበይት ቃላት አሰምቶ ተናግሯል፤

፩. ‹‹ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ (አምላኪየ አምላኪየ ለምን ተውኸኝ?)››፤

፪. ‹‹እውነት እውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትኖራለህ››፤

፫. ‹‹አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁትምና ይቅር በላቸው››፤

፬. እመቤታችንን ‹‹ሴትዮ ሆይ፣ እነሆ ልጅሽ››፤ ደቀ መዝሙሩንም ‹‹እናትህ እነኋት›› በማለት የቃል ኪዳን እናትነትና ልጅነት ማከናወኑ፤

፭. ‹‹አባት ሆይ በአንተ እጅ ነፍሴን አደራ እሰጣለሁ››

፮. ‹‹ተጠማሁ››፤

፯. ‹‹ዅሉ ተፈጸመ›› (ማቴ. ፳፯፥፵፭-፵፮፤ ሉቃ. ፳፫፥፵፫-፵፮፤ ዮሐ. ፲፱፥፲-፴)፡፡

ከስድስት ሰዓት እስከ ዘጠኝ ሰዓት ጨለማ ኾኖ ከቈየ በኋላ ከዘጠኝ እስከ ማታ እንደ ተለመደው ብርሃን ኾኖአል፡፡ ‹‹ወፍና ሠርክ ይበርህ ብርሃነ ፀሐይ›› እንዲል (ዘካ. ፲፬፥፯)፡፡ በዚህ ዕለት ሰባት መስተፃርራን (ጠበኞች) ታረቁ፤ ተስማሙ፡፡ እነዚህም፡- ሰውና እግዚአብሔር፣ ሰውና መላእክት፣ ሕዝብና አሕዛብ፣ ነፍስና ሥጋ ናቸው (ኤፌ. ፪፥፲፤ ቈላ. ፩፥፳)፡፡ ጌታችን ጠዋት በሦስት ሰዓት ተገረፈ፤ በስድስት ሰዓት ተሰቀለ (ማቴ. ፳፯፥፩-፴፯፤ ሉቃ. ፳፫፥፩-፵፬፤ ዮሐ. ፲፱፥፩)፡፡

በዘጠኝ ሰዓት ጌታችን በውኃው ተጠምቀን፣ ደሙን ተቀብለን የእግዚአብሔር ልጆች እንኾን ዘንድ ከቀኝ ጎድኑ ጥሩ ውኃ፣ ትኩስ ደም አፈሰሰልን (ዮሐ. ፲፱፥፴፬)፡፡ በዐሥራ አንድ ሰዓት ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ከመስቀል አውርደው ሽቶ እየረበረቡ በድርብ በፍታ ገንዘው ቀበሩት (ሉቃ. ፳፫፥፶-፶፬፤ ዮሐ. ፲፱፥፴፰-፵፪)፡፡ ቅድስት ነፍሱ ወደ ሲኦል ወርዳ ነፍሳትን ነጻ አወጣች (፩ኛ ጴጥ. ፫፥፲፱)፡፡ በዚህ ጊዜ በርሃነ መለኮቱ በሲኦል ተገለጠ፡፡ ስለዚህም ‹‹ንሴብሖ ለእግዚአብሔር›› እየተባለ ይዘመራል፡፡ ከሆሣዕና አንሥቶ ተከልክሎ የነበረው ኑዛዜ ይናዘዛል፤ ጸሎተ ፍትሐት ይደረጋል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡
✥••┈┈┈••✞••┈┈┈••✥
ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን = በዓቢይ ሃይል ወሥልጣን
አሰሮ ለሰይጣን = አግአዞ ለአዳም
ሰላም = እምእዘየሰ
ኮነ = ፍሰሃ ወሰላም
+++
ክርስቶስ በታላቅ ሃይሉና ሥልጣኑ ከሙታን መካከል ተለይቶ ተነሳ፤
ሰይጠንን አሰረው፤ አዳምን ነፃ አወጣው፤
ከእንግዲህ ወዲህ ፍሰሃ፣ ሰላም፣ ደስታ ሆነ።
እንኳን ለጌታችንና መድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ትንሣኤ በሰላምና በጤና አደረሰን: አደረሳችሁ። የሰላም የፍቅር የጤና በዓል ያድርግልን : አሜን።