ብራና ሚድያ - Birana Media
692 subscribers
1.65K photos
40 videos
4 files
570 links
+ የወጣቶች መንፈሳዊ ሕይወት
+ ገዳማትና ታሪካዊ ስፍራዎች
+ የቅዱሳን አበው መንፈሳዊ ተጋድሎና ታሪክ
+ እንዲሁም በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች የውይይት መድረክ በማዘጋጀት ወደ እናንተ ውድ ተከታታዮች መንፈሳዊ ይዘቱን ጠብቆ በየእለቱ ይቀርባል።
ቻናላችንን Subscribe በማድረግ ይቀላቀሉን።
https://www.youtube.com/c/BiranaMedia
ጥያቄ ካሎት በዚህ ይጻፉልን @birana259
Download Telegram
ብራና ሚድያ - Birana Media
Photo
ምኵራብ፡- የዐቢይ ጾም ሦስተኛ ሳምንት
 
“ቦአ ኢየሱስ ምኵራበ አይሁድ ወመሐረ ቃለ ሃይማኖት፤ ወይቤሎሙ ምጽዋተ አበድር እመሥዋዕት፤ አነ ውእቱ እግዚኣ ለሰንበት ወአቡሃ ለምሕረት፤ እግዚኣ ውእቱ ለሰንበት ወልደ እጓለ እመሕያው፤ ጌታችን ኢየሱስ ወደ አይሁድ ምኵራብ ገባ፤ የሃይማኖት ቃልን አስተማረ፤ ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን እወዳለሁ፤ የሰንበት ጌታዋ የምሕረት አባቷም እኔ ነኝ፤ የሰው ልጅም የሰንበት ጌታዋ ነው።” (ጾመ ድጓ)
 
በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሦስተኛውን የዐቢይ ጾም ሳምንት “ምኵራብ” ይባላል። ቀጥተኛ ፍቺው “ኮረብታ፣ ተራራ የሚያህል ታላቅ ሕንጻ፣ ሰቀላ መሰል አዳራሽ” ሲሆን፣ የአይሁድ መካነ ጸሎት ወይም ቤተ መቅደስ በመሆን ያገለግል ነበር። በብሉይ ኪዳን አይሁድ ቤተ መቅደስ ነበራቸው፡፡
 
ናቡከደነጾር ኢየሩሳሌምን በወረረ ጊዜ ግን ቤተ መቅደሱን አፈረሰ፤ ሕዝቡን ወደ ባቢሎን አፈለሰ፤(፪ኛነገ.፳፬-፳፭፣ኤር.፬፥፯:፣፴፱፥፩-፲፣፶፪፥፩-፴) ከዚህ ጊዜ ጀምሮ አይሁድ በሚኖሩባቸው ሥፍራዎች ሁሉ ለጸሎት ቤት ይሠሩ ነበር፡፡ በዚያን ዘመን ቢያንስ ዐሥር አባ ወራዎች/የቤተ ሰብ ኃላፊዎች/ በቦታው ከተገኙ እነዚህን ምኵራቦችን ለመሥራት ይፈቀድላቸው ነበር፡፡ (Talmud Mishnah, Responsa literature, Jewish Encyclopedia, Academic Scholarly Works.)  ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኢየሩሳሌም እየተዘዋወረ በሚያስተምርበት ጊዜ ግን ብዙ ምኵራቦች ነበሩ፡፡ በሐዲስ ኪዳንም ለሐዋርያት በብዛት የስብከት ዓውደ ምሕረቶች ሆነው አገልግለዋል።

 
ምኵራበ አይሁድ በውስጡ የብራና የሕግ እና የነቢያት መጻሐፍት ይገኛሉ፡፡ ምእመኑ እንዲሰማቸው ከፍ ባለ መድረክ ላይ በመሆን መምህራንና ካህናት ቆመው መጻሕፍትን ያነባሉ፤ ቃለ እግዚአብሔርንም  ያስተምሩ ነበር። የምኵራብ ሹማምንት አለቆች ጥፋተኛ ሰው ሊቀጡ ሥልጣን ነበራቸው፡፡ አገልጋይ ወይም የሚራዱ ወጣቶችም ልጆችን በማስተማር፣ በማቅረብ በተጨማሪ የአለቆችን ትእዛዝ በመፈጸም ያገለግላሉ፡፡
 
በሰንበት ሕዝብ ሁሉ በምኵራብ ተሰብስቦ ከሕግና ከነቢያት ንባብ፣ ስብከትና ቡራኬ በመቀበል አምልኮታቸውን ይፈጽሙ ነበር፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምኵራብ ተገኝቶ ሕዝቡን አስተምሯል፡፡ ቅዱስ ሉቃስ በወንጌሉ ”ወዳደገበትም ወደ ናዝሬት መጣ፤ እንደ ልማዱም በሰንበት ቀን  ምኵራብ ገባ ሊያነብም ተነሣ” እንዳለ ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ፣ መማር፣ መመርመር፣መተርጎም፣ጉባኤ መሥራት አዘውትረው የሚፈጽሙት ተግባር እንደነበር ያስረዳል።(ሉቃ.፬፡፥፲፮)
 
ነገር ግን በምኵራብ ሰዎች ለተለያየ ዓላማ ይሰበሰቡ ነበር፡፡
 
፩. አማናዊ እረኛ ነው ብለው፦ ወልድ ዋሕድ ብለው ሲጠብቁት የነበረው ተስፋ “ደረሰልን፤ ወረደ፤ ተወለደ፤ የዓለም መድኃኒት እርሱ ነው” ብለው አዳኝነቱን አምነው ይከተሉታል። “ነዋ በግዑ ለእግዚብሔር ዘያአትት ወያሴስል ኃጢአተ ዓለም፤ የዓለሙን ኃጢአት የሚያስተሰርይ የእግዚብሔር በግ መሆኑን አውቀው የሚከተሉት አሉ። ”በጎቹም ድምፁን ያውቃሉና ይከተሉታል” እንዲል። (ዮሐ.፲፥፬)
 
፪. የቃሉን ትምህርት የእጁን ተአምራት ሽተው፦ ከደዌ ለመፈወስ ይሰበሰባሉ፤ ልብሱን ዳሰው፣ ወድቀው ሰግደው፣ ጥላውን ተጋርደው፣ በእጁ ተዳሰው የሚፈወሱ ነበሩ። (ማር. ፭፥፳፪ እስከ ፍጻሜ)። ጌታችን በዕለተ ሰንበት ሕዝብ በተሰበሰበበት በምኵራብ እንደሚያስተምር ያስረዳናል፤ ”ሰንበትም በሆነ ጊዜ በምኵራብ ያስተምር ጀመር፤…ወደ ምኩራባቸውም ገብቶ ዝም ይሉ ዘንድ ገሠፃቸው፤ እነርሱም ትምህርቱን፣ የቃሉን ግርማ፣ የአነጋገሩን ጣዕምና፣ የአንደበቱን ቅልጥፍና አደነቁ፡፡”  (ማር.፮፥፩) “ወደ ገዛ አገሩም መጥቶ እስኪገረሙ ድረስ በሚገባቸው ያስተምራቸው ነበር።” (ማቴ.፲፫፥፶፬)
 
፫. ምግበ-ሥጋ ፈልገው ደም ግባቱን አይተው:- ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከምኵራብ ጉባኤ ትምህርት በኋላ ጥቂቱን አበርክቶ እልፉን ይመግብ ስለነበር ጉባኤውን ይታደማሉ። ክርስቲያኖች እግዚአብሔርን የምናመልከው ምግበ ሥጋ ስለሰጠን አይደለም። እርሱንማ ለሕዝብም ለአሕዛብም ሳይሰስት የሚመግብ መጋቤ ዓለማት ነው። ክርስቲያን በመብል አይገመትም። “እንግዲህ በመብልም ቢሆን÷ በመጠጥም ቢሆን÷ በልዩ ልዩ በዓላትም ቢሆን÷ በመባቻም ቢሆን÷ በሰንበትም ቢሆን የሚነቅፋችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ፡፡” እንዲል፡፡ (ቆላ. ፪፥፲፮ እስከ ፍጻሜ)
 
፬. ለክስ የሚቀርቡ አሉ፦ ከቃሉ ግድፈት ከትምህርቱ ስሕተት የሚፈልጉ ሰቃለያን አይሁድ፣ ሊቃነ ካህናት አምላክነቱን የሚጠራጠሩ አይሁድ የሸንጎውን ጌታ ለሸንጎ ፍርድ ሊያቀርቡት ከግር በግር ይከተሉት ነበር። “ወጸቢሖ ተጋብኡ ሊቃነ ካህናት ወጸሐፍት ወሊቃናተ ሕዝብ ወወሰድዎ ውስተ ዐውዶሙ። ወይቤልዎ እመ አንተሁ ክርስቶስ ንግረነ ገሃደ ወይቤሎሙ እመኒ አይዳእኩክሙ ኢተአምኑኒ፡፡ በነጋም ጊዜ፥ የካህናት አለቆች፥ ጻፎችና የሕዝቡ ሽማግሌዎች ተሰብስበው ወደ ሸንጎአቸው ወሰዱት፡፡ “አንተ ክርስቶስ እንደ ሆንህ በግልጥ ንገረን” አሉት፡፡እርሱም እንዲህ አላቸው፥ “ብነግራችሁም አታምኑኝም” እንዲል፡፡ (ሉቃ. ፳፪፥፷፮፣ ማቴ.፳፮፥፶፱)
 
ዛሬም በአማናዊቷ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሥጋዊ ነገር ብቻ ገዝፎባቸው ቤተ መቅደሱን ለንግድ፣ ንዋያተ ቅድሳትን ለትርፍ ብቻ አሳልፈው የሚሸጡ፣ የሚለውጡ፣ ለክስ የሚፋጠኑ ከምኵራብ ያልወጡ የበጎችን እረኛ አሳልፈው የሚሰጡ አዋልደ ይሁዳ እንዳሉ ግልጽ ነው። “ወረከበ በምኵራብ እለ ይሠይጡ አልህምተ ወአባግዐ ወአርጋበ …፤ በመቅደስም በሬዎችን፣ ላሞችን፣ በጎችን፣ ርግቦችን፣ የሚሸጡትን አገኘ …፤ “ኢትግበሩ ቤተ አቡየ ቤተ ምስያጥ ቤትየሰ ቤተ ጸሎት ይሰመይ፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቦታ አታድርጉት፤ እናንተ ግን የሌቦች ዋሻ አደረጋችሁት፤ ቤቴስ የጸሎት ቤት ይባላል” እያለም የሃይማኖትን ቃል አስተማራቸው፡፡ (ዮሐ.፪፥፲፮፣ማቴ.፳፩፥፲፫)
 
በምኵራብ ይሸጡ፣ ይለውጡ የነበሩትን የገሠፀበት፣ ቤተ መቅደስን የከብት መንጃ የወርቅ መነገጃ ያደረጉ ሰዎችን ከእነ ሸቀጣቸው ከቤተ መቅደስ ያስወጣበት፣ ቤተ መቅደስ የእግዚአብሔር ማደሪያ፣ የመሥዋዕቱ መክበሪያ፣ የጸሎት ሥፍራ ምስካበ ቅዱሳን መሆኗን ያስተማረበት ዕለት ነው። ቃሉ በዚያን ዘመን ተነግሮ ብቻ ያለፈ አይደለም፤ ለእኛ የተነገረን መሆኑን አውቀን የባለቤቱ ጅራፍ ሳይገርፈን ልንመለስ ይገባል። “የገመድም ጅራፍ አበጅቶ ሁሉን በጎችንም በሬዎችንም ከመቅደስ አወጣቸው፥ የለዋጮችንም ገንዘብ አፈሰሰ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ፡፡” (ዮሐ.፪፥፲፬)
 
ከሚመጣው ጅራፍ ለመዳን እምነት ከተግባር ይዞ መገኘት ያስፈልጋል።” ወንድሞቻችን ሆይ÷ እምነት አለኝ፤ ምግባር ግን የለኝም የሚል ሰው ቢኖር÷ ምን ይጠቅመዋል? በውኑ እምነቱ ልታድነው ትችላለችን? ከወንድሞቻችን÷ ወይም ከእኅቶቻችን÷ የታረዙ ወይም የዕለት ምግብ ያጡ ቢኖሩ÷ ከእናንተም አንዱ …እንደዚሁም ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው።” እንዳለ። (ያዕ.፪፥፲፬ እስከ ፍጻሜ)
ብራና ሚድያ - Birana Media
Photo
 
የዕለቱ መዝሙር (ከጾመ ድጓ)፦ ቦአ ኢየሱስ ምኩራበ አይሁድ ወመሐረ ቃለ ሃይማኖት፤ጌታችን ኢየሱስ ወደ አይሁድ ምኩራብ ገባ፤ የሃይማኖት ቃልን አስተማረ፤
 
መልእክታት፦(ቆላ.፪፥፲፮ እስከ ፍጻሜ) (ያዕ.፪፥፲፬ እስከ ፍጻሜ)
ወንጌል፦ (ዮሐ.፪፥፲፪-እስከ ፍጻሜ)
(የሐዋ.፲፥፩-፰)
 
ምስባክ፦ “እስመ ቅንዐተ ቤትከ በልዐኒ፡፡ ትዕይርቶሙ ለእለ ይትዔየሩከ ወድቀ ላዕሌየ፡፡ወቀጻዕክዋ በጾም ለነፍስየ፡፡” ትርጉም “የቤትህ ቅንዓት በልቶኛልና፥ የሚሰድቡህም ስድብ በለዬ ወድቆአልና፡፡ ሰውነቴን በጾም አደከምኋት፡፡  (መዝ.፷፰፥፱)     
 
በምሕረቱ ይታደገን፤ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፤ አሜን!!!
ብራና ሚድያ - Birana Media
Photo
መፃጒዕ

አራተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ‹መፃጒዕ› ይባላል፡፡ ስያሜው በዮሐንስ ወንጌል ፭፥፩ ላይ ከሚገኘው ኃይለ ቃል ያለ ነው፡፡ መፃጒዕ ደዌ የጸናበት በሽተኛ፣ ሕመምተኛ ማለት ነው፡፡ መፃጒዕ ለ፴፰ ዓመት በአልጋው ላይ ሆኖ ምሕረትን ሲጠባበቅ የኖረ ሰው ነው። ስፍራዋም “ቤተ ሳይዳ” ትባላለች።ቤተ ሣህል (የምሕረት ቤት) ማለት ነው፤ መጠመቂያዋም በሰሎሞን ቤተ መቅደስ አጠገብ የምትገኝ ናት፡፡ (ዘሌ.፱፥፪) “ቤተ ሳይዳ” ዘይሁዳና “ቤተ ሳይዳ” ዘገሊላ የሚባሉ እንዳሉ በግልጽ በቅዱሳት መጻሕፍት ተገልጿል። “ወቦ ውስተ ኢየሩሳሌም ምጥማቃት ዘጵሩጳጥቄ ቅልንብትራ ዘውእቱ ቀላየ አባግዕ ብሂል ወይቤልዋ ስማ በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ ወባቲ ኃምስቱ ሕዋራት” …በኢየሩሳሌምም በበጎች በር አጠገብ በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ የምትባል አንዲት መጠመቂያ ነበረች፤ አምስትም መመላለሻ ነበረባት” ብሎ ሲገልጽ ነው። (ዮሐ.፭፥፪)


ቤተ ሳይዳ ዘኢየሩሳሌም ባለ አምስት በር፣ እርከን (መመላለሻ)፣ አምስት ዓይነት ድውያን ፈውስን ለማግኘት ጥምቀቱን ሲጠባበቁ የሚኖሩባት ናት። ውኃው የቤተ አይሁድ ምሳሌ፣ አምስት መመላለሻ የሕግጋተ ኦሪት እና የአምስቱ መጻሕፍተ ሙሴ ምሳሌ በእነዚያ ተጠብቀው ለመኖራቸው ምሳሌ ነው። ቀድሞ የገባባት አንዱ እንዲድን፣ እነርሱም አንድነት ቤተ እስራኤል ተሰኝተው ለመኖራቸው ምሳሌ ነው። አንድም አምስቱ እርከን (መመላለሻ) የአምስቱ አዕማደ ምሥጢር በዚያ ሊያምኑ ያሉ ተስፈኞችና ያመኑባትም ልጅነትን ያገኙባታልና። አምስቱ ዓይነት ድውያንም የአምስቱ ጾታ ምእመናን ከእነ ፈተናቸው ምሳሌ ነው፡፡ እነርሱም አእሩግ በፍቅረ ነዋይ፣ ወራዙት በዝሙት፣ አንስት በትውዝፍት (በምንዝር ጌጥ)፣ ካህናት በትዕቢት አእምሯችን ረቂቅ መዓረጋችን ምጡቅ እያሉ፣ መነኮሳት በስስት ምግብን በፈለጉት ጊዜ ባያገኙት ይልቁንም በአት እየፈቱ በከንቱ የመፈተናቸው ምሳሌ ሆኖ ይነገራል።

መልአከ እግዚአብሔር ወርዶ ውኃውን ሲያናውጥ ቀድሞ የገባ የሚነጻባት፣ ነገር ግን በዕለቱ ከአንድ ሕመምተኛ በቀር ለሌላው ፈውስ የማይደገምባት ቦታ ናት። ሐተታው የመጠመቂያ ውኀው የማየ ጥምቀት ምሳሌ ሲሆን ውኃውን ያናውጥ (ይባርክ) የነበረው መልአክ የቀሳውስት (ካህናት) “ለቀድሶተ ማየ ጥምቀት” የመውረዳቸው ምሳሌ ነው፤ ፈውሱም የሚከናወነው በዕለተ ቀዳሚት ሲሆን የሚፈወሰው አንድ ሰው ብቻ ነበር፡፡ የሚድነው አንድ ታማሚ ብቻ መሆኑ የአባቶቻቸው ምሕረት አለመቅረቱን ሲያሳይ፣ አለመደገሙ ደግሞ ፍጹም ድኅነት እንዳልነበረ ያሳያል፡፡

ለሠላሳ ስምንት ዓመታት ያህል በደዌ ዳኛ፣ በአልጋ ቁራኛ ተይዞ የኖረ መፃጉዕን በአልጋው ተኝቶ ሳለ ደዌው እንደጠናበት ፈውስ እንደዘገየበት አይቶ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቀርቦ ያንን በሽተኛ “ትፈቅድኑ ትሕየው? … ባድንህ ፈቃድህ ነውን?” አለው። ማእምረ ኅቡዓት ክርስቶስ፣” አዎን፥ እንዲለው እያወቀ”፤ ቅዱስ ጳውሎስ በዕብራውያን መልእክቱ “የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል፤ እኛን በሚቆጣጠር በእርሱ ዓይኖቹ ፊት ሁሉ ነገር የተራቆተና የተገለጠ ነው እንጂ፥ በእርሱ ፊት የተሰወረ ፍጥረት የለም” ብሎ የመሰከረለት ጌታችን ፈውስን በመጠባበቅ ከመዳን ውጪ ሌላ ዓላማ ያልነበረውን ይህን ሰው አይቶ ፈቃዱን እያወቀ ግን ፍቀድልኝና ላድንህ አለው። (ዕብ.፬፥፲፪) “ሰው በከንቱ ወራቱ ቍጥርና እንደ ጥላ በሚያሳልፈው ዘመኑ በሕይወቱ ሳለ ለሰው የሚሻለውን የሚያውቅ ማነው?“ እንዲል፤ (መክ.፮፥፲፪) የሚያስፈልገንን ሳንነግረው የሚያውቅ የሚሰጠንም ከእርሱ ከፈጣሪው ውጪ በእውነት ማን አለ?

መፃጉዕ በኋላ የሚክድ ነውና “ሳልፈቅድለት ነው ያዳነኝና አልጋ ያሸከመኝ” እንዳይል፣ በዕለተ ዓርብ የሚከስበትን ሲያሳጣውና ለኋላ ጥፋቱ የገዛ ኅሊናው እንዲቀጣው ፈቃዱን ጠየቀው። “ሰው የሌለኝ ሆኖ እንጂ ያንንማ ማን ይጠላል” በሚል ጉጉቱን ከወዳጅ አልባነቱ ጋር ድኅነትን ፈቅዶ ገለጠ። እስከ ውኃው መናወጥ ሳያቆየው “ተንሥእ ንሣእ ዓራተከ ወሑር …፤ ተነሥና አልጋህን አንሥተህ ሂድ” አለው፤ ወዲያው አፈፍ ብሎ በፍጥነት ያን ሁሉ ዘመን የተሸከመች አልጋ ተሸክሟት ሄደ።

ጌታችን መፃጉዕን ‹‹ተነሥተህ አልጋህን ተሸክመህ ሂድ›› ያለው፦

• አንደኛው ቅዱስ ኤስድሮስ እንዳለው አልጋው ጠንካራ የብረት አልጋ ነበረና ጽንዓ ተአምራቱን ለማሳየት ነው፡፡

• ሁለተኛው ‹‹ታዲያ ቢያድነኝ በከንቱ መች ሆነና የገዛ አልጋዬን ትቼለት የመጣሁ ለመዳኔ ዋጋ የከፈልኩበት አይደለምን?›› እንዳይል  “አልጋህን ተሸክመህ ሂድ” ብሎታል።

ያለ ተረፈ ደዌ አንሥቶት “ያለህን ይዘህ ሂድ፤ እኔ ከአንተ አንዳች አልሻም” ባሰኘ ቃል ሸኝቶታል። ታዲያ ይህ ምስኪን መፃጒዕ “ሰው የለኝም” ብሎ የደረሰለትን ረሳ፤ ማን እንደሆነ እንኳን አላወቀውም። ወንጌላዊውም “ዘሐይወ ኢያእመረ ዘአሕየዎ …፤የዳነው ያዳነውን አላወቀውም” ይለዋል። ( ዮሐ.፭፥፲፫) ይህን ሁሉ ያደረገው አምላክ ተዘነጋ። ዛሬም ከደዌው፣ ከማጣቱ፣ ከችግሩ፣ ከሥጋ ኑሮ ጉድለቱ እንደ መፃጒዕ አምላኩን ያልረሳ ማነው? ተአምራቱን አይቶ፣ ቃሉን ሰምቶ አምላኩን ያስታወሰስ ማነው? ቃሉን ያይና ይሰማ ዘንድ በእግዚአብሔር ምክር የቆመ ማን ነውና? ቃሉንስ ያደመጠስ ማን ነው?” (ኤር. ፳፫፥፲፰)። እኛም ብንሆን ከአዳም በደል ነጻ ያደረገንን አምላክ ውለታ ዘንግተን የምናፌዝ ሁላችንንም ወደ ልባችን እንድንመለስ ነቢዩ እንዲህ ሲል ይመክረናል “እስራት እንዳይጸናባችሁ አታፊዙ፡፡” (ኢሳ.፳፰፥፳፪ )

መፃጉዕ ያዳነው ማን እንደሆነ ሲጠየቅ እንኳን አላወቀም። ወንጌላዊውም “የዳነው ያዳነውን አላወቀውም” ብሎ ገልጾታል። (ዮሐ.፭፥፲፫) በምኩራብ አግኝቶት ያዳነውን እንዳወቀውም ሄዶ ለአይሁድ “ያዳነኝ እርሱ ጌታ ኢየሱስ ነው” ብሎ ነገራቸው፡፡ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በቤተ መቅደስ ሳለ ያን ያዳነውን ሰው አገኘውና “ዑቅ ኢትአብስ ዳግመ እንከ ከመ ዘየአኪ ኢይርከብከ፤ ከዚህ የከፋ “ስለ ደዌ ሥጋ ፈንታ ደዌ ነፍስ” እንዳያገኝህ ሁለተኛ እንዳትበድል” (ቁ.፲፬) ያለውን ዘንግቶ ደዌ ዘኃጢአትን ጠርቶ ተወዳጃት፤ በዕለተ ዓርብ የጌታውን ጉንጮች የጸፉች እጁም ደርቃ ሰላ ቀርታለች።

ዛሬም ቢሆን እንደ መፃጉዕ ሰዎች በኃጢአት ብዛት ልባቸው የደረቀና ያበጠ፣ ሰውነታቸው የሰለለ፣ ዓይነ ሕሊናቸው የታወረ፣ እግረ ልቡናቸው የተሰበረ ብዙዎች ሕሙማን በጠበል ቦታ፣ በገዳማት እና በአድባራት አሁንም አሉ፡፡ ፈውስን ይሻሉ፤ ድኅነትን ይፈልጋሉ፡፡ እንደ መፃጕዕ ቦታቸውን ሳይለቁ እግዚአብሔርን በተስፋ ቢጠብቁት አንድ ቀን ይፈወሳሉ።

ስለዚህ ይህ ሳምንት ጌታችን ድውያንን ስለመፈወሱ የሚነገርበትና እኛም ባለን ዓቅም በነፍስ በሥጋ የተቸገሩትን ሁሉ መርዳትና ማገዝ እንዳለብን የምንማርበት ሳምንት ነው፡፡ ሕሙማንን መጠየቅ፣ የታሰሩትን መጎብኘትና ማስፈታት፣ የተራቡትን ማብላት፣ የተጠሙትን ማጠጣት፣ የታረዙትን ማልበስ፣ ያዘኑትን ማረጋጋት ከጌታችን የተማርናቸው ክርስቲያናዊ ምግባራት   ናቸው፡፡
ብራና ሚድያ - Birana Media
Photo
በዚህ ዕለት የእግዚአብሔር አምላካችን ፈዋሽነትና አዳኝነት እንዲሁም ታዳጊነትና የወደቁትን የማይረሳ እውነተኛ መድኃኒት መሆኑ የሚዘከርበትና ምስጋና የሚቀርብበት ነው። ቅዱስ ዳዊትም "እግዚአብሔር ይረድኦ ውስተ ዐራተ ሕማሙ፣ ወይመይጥ ሎቱ ኩሎ ምስካቤሁ እምደዌሁ፣ አንሰ እቤ እግዚኦ ተሣሃለኒ፤ እግዚአብሔር በደዌው አልጋ ሳለ ይረዳዋል፤ መኝታውንም ሁሉ በበሽታው ጊዜ ያነጥፍለታል፣ እኔም አቤቱ ማረኝ እልሃለሁ” በማለት የእግዚአብሔርን አዳኝነት በዝማሬው አረጋግጧል።

ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “ችግረኛውን ከቀማኛው እጅ፣ ረዳት የሌለውንም ምስኪን ያድነዋልና” ሲል ሲቀኝ፣ (መዝ.፸፪፥፲፪)  ጻድቁ ኢዮብም እንዲሁ “ረዳት (ኃይል) የሌለውን ምንኛ ረዳኸው”  በማለት የእግዚአብሔርን አዳኝነት መስክሯል፡፡ (ኢዮ.፳፮፥፪) ስለዚህ ገንዘብ፣ ሥልጣን፣ ወገን፣ ረዳት የለኝም በማለት ተስፋ የቆረጥን ሰዎች እግዚአብሔር ከሰውም፣ ከሥልጣንም፣ ከገንዘብም በላይ ነውና እርሱን ተስፋ አድርገን ሁል  ጊዜ በስሙ መጽናናት እና የሚያስጨንቀንን ሁሉ በእርሱ ላይ መጣል እንደሚገባን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት “አቤቱ የሚፈልጉህ ሁሉ በአንተ ደስ ይበላቸው፤ሐሤትም ያድርጉ፡፡ ሁል ጊዜ ማዳንህን የሚወዱ ዘወትር እግዚአብሔር ታላቅ ይሁን ይበሉ” እንዳለው ሁል ጊዜም በአምላካችን እግዚአብሔር ደስተኞች

እንሁን። (መዝ.፵፥፲፮)

በኃጢአት ከሚመጣ ደዌ ተጠብቀን በአባታዊ ምሕረቱ የሚጠብቀንን ቸሩ አምላካችንን እያመሰገንን በቤቱ እንድንጸና መፃጒዕን “ተነሣ” እንዳለው እኛንም ከወደቅንበት ኃጢአት በንስሓ እንዲያነሣንና ዳግም ከመበደልም እንዲጠብቀን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁን። የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በረከት አይለየን፤ አሜን!

በመልእክታቱ የሚነበቡት 
(ገላ.፭፥፩ እና ያዕ.፭፥፲፬) ስለ ድውያን መፈወስ የሚያወሱ ናቸው፡፡
ከሐዋርያት ሥራ የሚነበውም እንዲሁ (ሐዋ.፫፥፩)

የዕለቱ ምስባክ፦ “እግዚአብሔር ይረድኦ ውስተ ዐራተ ሕማሙ፤ ወይመይጥ ሎቱ ኵሉ ምስካቢሁ እምደዌሁ፤ አንሰ እቤ  እግዚኦ ተሣለኒ፤ በደዌው አልጋ ላይ ሳለ ይረዳዋል፤ መኝታውንም ሁሉ ከበሽታው የተነሣ ይለውጥለታል፡፡ እኔስ “አቤቱ ይቅር በለኝ፤ አንተን በድያለሁና ለነፍሴ አስተስርይላት” አልሁ፡፡” ይላል (መዝ.፵፥፫)
Media is too big
VIEW IN TELEGRAM
#አስደሳች ዜና

ተከታታይ መንፈሳዊ ትምህርት መማር ለሚፈልጉ በሙሉ

መንፈሳዊ ትምህርት ለመማር አስበው አልመቻች ብሎት ይሆን? ምናልባትም የተማሩትን ማስታወስ ፈልገውስ ቢሆን?

እንግዲያውስ ተዋሕዶ ሚዲያ ማዕከል በተመችዎት ጊዜና ሰዓት ያለ ምንም ክፍያ እንዲማሩ መሠረታዊ የቤተክርስቲያን ተከታታይ ትምህርቶችን /ኮርሶችን/ ይዞ ቀርቧል

-ትምህርተ ሃይማኖት
-ነገረማርያም
-ነገረ ድኅነት
-ሥርዓተ ቤተክርስቲያን
-የቤተክርስቲያን ታሪክና ሌሎች የቤተክርስቲያን መሠረታዊ ተከታታይ ትምህርቶችን በተዋሕዶ ሚዲያ ማዕከል ዩቲዩብ ቻናል በቅርብ ቀን ይጠብቁን
በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደረጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ስዩም እና የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ መምህር ዋሲሁን በላይ ዛሬ ሚያዚያ 24/2016 ዓ.ም ከመኖሪያ ቤታቸው በጸጥታ አካላት መወሰዳቸው ታውቋል።

የሁለቱ አገልጋዮች መኖሪያ ቤት መፈተሹም ተገልጿል።

በአሁኑ ሰዓት ሜክሲኮ ፌዴራል ፓሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ የሚገኙ ሲሆን የተያዙበት ምክንያት አልታወቀም።

ዝርዝር እንደደረሰን እናቀርባለን።
ዓርብ ስቅለት (የድኅነት ቀን)

እንኳን አደረሰን!

ዓርብ ስቅለት የዕዳ ደብዳቤያችን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ለመጨረሻ ጊዜ የተደመሰሰበት፤ ከአጋንንት አገዛዝ ነጻ የወጣንበት ዕለት ስለኾነ ‹የድኅነት ቀን› ይባላል፡፡ ጌታችን ከተያዘባት ሰዓት አንሥቶ አይሁድ ከቀያፋ ወደ ሐና፣ ከሐና ወደ ቀያፋ ሲያመላልሱት አደሩ፡፡ ሲነጋ ከቀያፋ ወደ ጲላጦስ አደባባይ አስረው ወሰዱት (ማቴ. ፳፯፥፩-፶፯)፡፡ አይሁድ ይህን አጥፍቶአል የሚሉት ነጥብ ሳይኖራቸው ነውና ጌታችንን ለፍርድ ያቀረቡት ጲላጦሰ እነርሱ ወደ ተሰባሰቡበት ቦታ ወጥቶ ‹‹ይህን ሰው ወደ እኔ ያመጣችሁበት በደል ምንድን ነው?›› ሲል በጠየቃቸው ጊዜ በቂ ምላሽ አላቀረቡም፡፡

‹‹ክፉ የሠራ ባይኾንስ ወደ አንተ ባላመጣነውም ነበር›› በሚል የሸፍጥ ቃል ሲያጕረመርሙ ጲላጦስ መልሶ ‹‹እኔ ምንም ጥፋት አላገኘሁበትም፤ እናንተወስዳችሁ እንደ ሕጋችሁ ፍረዱበት፤›› አላቸው፡፡ አይሁድም ኦሪት ‹‹ኢትቅትል ብእሴ ጻድቀ ወኀጥአ ኢታኅዩ፤ ጻድቅን ሰው አትግደል፤ ኀጥኡንም ከፍርድአታድን፤›› ትላለችና ‹‹እኛስ ማንንም ልንገድል አልተፈቀደልንም፤›› ብለዋል (ዮሐ. ፲፰፥፳፰-፴፩)፡፡ ይኸውም መንፈስ ቅዱስ ‹‹በሕጋችን ጻድቀ ባሕርይክርስቶስን መግደል አይገባንም ሙሉ በሙሉ ጥፋተኞች ነን፤›› ሲያሰኛቸው ነው፡፡ በኋላም እርሱ ሞቶ ዓለም ይድን ዘንድ ወደ ምድር መጥቷልና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያለ ጥፋቱ ሞት ተፈረደበት፡፡ ስለዚህም ገርፈው ሰቀሉት፡፡

ጌታችን ሲሰቅልም የሚከተሉት ሰባት ተአምራት ተፈጽመዋል፤

፩. ፀሐይ ጨለመ፤

፪. ጨረቃ ደም ኾነ፤

፫. ከዋክብት ረገፉ፤

፬. የቤተ መቅደስ መጋረጃ ተቀደደ፤

፭. አለቶች ተፈረካከሱ፤

፮. መቃብራት ተከፈቱ፤

፯. ሙታን ተነሡ (ማቴ. ፳፯፥፶፩-፶፬)፡፡

ጌታችን በመስቀል ላይ ሳለ የሚከተሉትን ሰባት ዐበይት ቃላት አሰምቶ ተናግሯል፤

፩. ‹‹ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ (አምላኪየ አምላኪየ ለምን ተውኸኝ?)››፤

፪. ‹‹እውነት እውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትኖራለህ››፤

፫. ‹‹አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁትምና ይቅር በላቸው››፤

፬. እመቤታችንን ‹‹ሴትዮ ሆይ፣ እነሆ ልጅሽ››፤ ደቀ መዝሙሩንም ‹‹እናትህ እነኋት›› በማለት የቃል ኪዳን እናትነትና ልጅነት ማከናወኑ፤

፭. ‹‹አባት ሆይ በአንተ እጅ ነፍሴን አደራ እሰጣለሁ››

፮. ‹‹ተጠማሁ››፤

፯. ‹‹ዅሉ ተፈጸመ›› (ማቴ. ፳፯፥፵፭-፵፮፤ ሉቃ. ፳፫፥፵፫-፵፮፤ ዮሐ. ፲፱፥፲-፴)፡፡

ከስድስት ሰዓት እስከ ዘጠኝ ሰዓት ጨለማ ኾኖ ከቈየ በኋላ ከዘጠኝ እስከ ማታ እንደ ተለመደው ብርሃን ኾኖአል፡፡ ‹‹ወፍና ሠርክ ይበርህ ብርሃነ ፀሐይ›› እንዲል (ዘካ. ፲፬፥፯)፡፡ በዚህ ዕለት ሰባት መስተፃርራን (ጠበኞች) ታረቁ፤ ተስማሙ፡፡ እነዚህም፡- ሰውና እግዚአብሔር፣ ሰውና መላእክት፣ ሕዝብና አሕዛብ፣ ነፍስና ሥጋ ናቸው (ኤፌ. ፪፥፲፤ ቈላ. ፩፥፳)፡፡ ጌታችን ጠዋት በሦስት ሰዓት ተገረፈ፤ በስድስት ሰዓት ተሰቀለ (ማቴ. ፳፯፥፩-፴፯፤ ሉቃ. ፳፫፥፩-፵፬፤ ዮሐ. ፲፱፥፩)፡፡

በዘጠኝ ሰዓት ጌታችን በውኃው ተጠምቀን፣ ደሙን ተቀብለን የእግዚአብሔር ልጆች እንኾን ዘንድ ከቀኝ ጎድኑ ጥሩ ውኃ፣ ትኩስ ደም አፈሰሰልን (ዮሐ. ፲፱፥፴፬)፡፡ በዐሥራ አንድ ሰዓት ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ከመስቀል አውርደው ሽቶ እየረበረቡ በድርብ በፍታ ገንዘው ቀበሩት (ሉቃ. ፳፫፥፶-፶፬፤ ዮሐ. ፲፱፥፴፰-፵፪)፡፡ ቅድስት ነፍሱ ወደ ሲኦል ወርዳ ነፍሳትን ነጻ አወጣች (፩ኛ ጴጥ. ፫፥፲፱)፡፡ በዚህ ጊዜ በርሃነ መለኮቱ በሲኦል ተገለጠ፡፡ ስለዚህም ‹‹ንሴብሖ ለእግዚአብሔር›› እየተባለ ይዘመራል፡፡ ከሆሣዕና አንሥቶ ተከልክሎ የነበረው ኑዛዜ ይናዘዛል፤ ጸሎተ ፍትሐት ይደረጋል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡
✥••┈┈┈••✞••┈┈┈••✥
ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን = በዓቢይ ሃይል ወሥልጣን
አሰሮ ለሰይጣን = አግአዞ ለአዳም
ሰላም = እምእዘየሰ
ኮነ = ፍሰሃ ወሰላም
+++
ክርስቶስ በታላቅ ሃይሉና ሥልጣኑ ከሙታን መካከል ተለይቶ ተነሳ፤
ሰይጠንን አሰረው፤ አዳምን ነፃ አወጣው፤
ከእንግዲህ ወዲህ ፍሰሃ፣ ሰላም፣ ደስታ ሆነ።
እንኳን ለጌታችንና መድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ትንሣኤ በሰላምና በጤና አደረሰን: አደረሳችሁ። የሰላም የፍቅር የጤና በዓል ያድርግልን : አሜን።
ከዕለተ ትንሣኤ እስከ ዳግም ትንሣኤ

ከዕለተ ትንሣኤ እስከ ዳግም ትንሣኤ ባሉት ዕለታት በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የሚፈጸመው መንፈሳዊና ሐዋርያዊ አገልግሎት ልክ እንደ መጀመሪያው የትንሣኤ ሥርዓት ኾኖ ይከናወናል፡፡ ከትንሣኤ እሑድ ጀምሮ እስከ ሳምንቱ እሑድ ድረስ የሚገኙት ዕለታትም ‹ሰሙነ ፋሲካ› ወይም ‹ትንሣኤ› እየተባሉ ይጠራሉ፤ የየራሳቸው ምሥጢራዊ ስያሜም አላቸው፡፡ ስያሜአቸውንም በአጭሩ እንደሚከተለው እንመለከታለን፤

ሰኞ

የትንሣኤው ማግሥት ዕለተ ሰኞ ‹ፀአተ ሲኦል› ወይም ‹ማዕዶት› ትባላለች፡፡ ይህቺውም ጌታችን በትንሣኤው ነፍሳትን ከሲኦል አውጥቶ ወደ ገነት አሻግሮ ለማስገባቱ መታሰቢያ ናት (ዮሐ. ፲፱፥፲፰፤ ሮሜ. ፭፥፲-፲፯)፡፡

ማክሰኞ

ይህቺ ዕለት፣ ለሐዋርያው ቶማስ መታሰቢያ ትኾን ዘንድ ‹ቶማስ› ተብላ ትጠራለች፡፡ የትንሣኤው ዕለት እሑድ ማታ ጌታችን በዝግ ቤት ገብቶ ለሐዋርያት ሲገለጽ ቶማስ ከእነርሱ ጋር አልነበረም፡፡ በመጣ ጊዜ ሌሎቹ ሐዋርያት ትንሣኤውን ቢነግሩት ‹‹ሳላይ አላምንም›› ብሎ ነበር፡፡ በሳምንቱ እርሱ በተገኘበት ጌታችን በድጋሜ ለሐዋርያት ተገለጸ፡፡ ስለዚህም ይህቺ ዕለት በሐዋርያው ቶማስ ስም ተሰይማለች (ዮሐ. ፳፥፳፬-፴)፡፡

ረቡዕ

ጌታችን ከሞተና ከተቀበረ ከአራት ቀናት በኋላ ከመቃብር ጠርቶ ላስነሣው ለአልዓዛር መታሰቢያ ናት፡፡ በክርስቶስ ሥልጣን የአልዓዛርን ከሞት መነሣት አይተው ብዙ ሕዝብ በጌታችን ስለ አመኑ ዕለቲቱ (ረቡዕ) ‹አልዓዛር› ተብላ ትታሰባለች (ዮሐ. ፲፩፥፴፰-፵፮)፡፡

ኀሙስ

ይህቺ ዕለት ‹‹ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ (አምስት ሺሕ ከአምስት መቶ ዓመት ሲፈጸም) ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ፤›› ተብሎ ቃል የተገባለት የአዳም ተስፋው ተፈጽሞ ከነልጅ ልጆቹ ወደ ቀደመ ክብሩ ለመግባቱ መታሰቢያ ኾና ‹የአዳም ኀሙስ› ወይም ‹አዳም› ተብላ ትከበራለች (ሉቃ. ፳፬፥፳፭-፵፱)፡፡

ዐርብ

የትንሣኤ እሑድ ስድስተኛዋ ዐርብ ደግሞ በክርስቶስ ደም ለተመሠረተችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መታሰቢያ ትኾን ዘንድ ‹ቤተ ክርስቲያን› ተብላ ትጠራለች (ማቴ. ፳፮፥፳፮-፳፱፤ ሐዋ. ፳፥፳፰)፡፡

ቀዳሚት ሰንበት

በሰሙነ ፋሲካው ያለችው ቀዳሚት ሕዝቡ ከአንዳንዱ በቀር ገበያ እንኳን ስለማይገበያይባት ‹የቁራ ገበያ፣ የገበያ ጥፊያ› ተብላ ትጠራለች፡፡ በቤተ ክርስቲያን ደግሞ ጌታችን በዘመነ ሥጋዌው በገንዘባቸውና ጕልበታቸው ላገለገሉት፤ በስቅለቱ ጊዜ እስከ ቀራንዮ ድረስ ለተከተሉት፤ በትንሣኤው ዕለት በሌሊት ወደ መቃብሩ ሽቱና አበባ ይዘው ለገሰገሱት፤ በትንሣኤውም ጌታችንን ከዅሉ ቀድሞ ለማየት ለበቁት ሴቶች መታሰቢያ ትኾን ዘንድ ‹ቅዱሳት አንስት› ተብላ ትጠራለች (ማቴ. ፳፭፥፩-፲፩፤ ሉቃ. ፳፫፥፳፯-፴፫፤ ፳፬፥፩-፲)፡፡

እሑድ ሰንበት

በዋናው ትንሣኤ ሳምንት የምትመጣዋ ዕለተ እሑድ ‹ዳግም ትንሣኤ› ተብላ ትዘከራለች፡፡ ከላይ እንደ ተጠቀሰው ጌታችን በትንሣኤው ዕለት ማታ በዝግ በር ገብቶ፣ በቅዱሳን ሐዋርያት መካከል ተገኝቶ ‹‹ሰላም ለዅላችሁ ይኹን!›› በማለት ትንሣኤውን ሲገልጽላቸው ሐዋርያው ቶማስ አልተገኘም ነበር፡፡ በኋላ ከሔደበት ሲመጣ ጌታችን እንደ ተነሣ እና እንደ ተገለጸላቸው ሐዋርያት በደስታ ሲነግሩት ‹‹በኋላ እናንተ ‹አየን› ብላችሁ ልትመሰክሩ፤ ልታስተምሩ፤ እኔ ግን ‹ሰምቼአለሁ› ብዬ ልመሰክር፤ ላስተምር? አይኾንም፡፡ እኔም ካላየሁ አላምንም›› አለ፡፡

ስለዚህም የሰውን ዅሉ፤ ይልቁንም የመረጣቸው የወዳጆቹን የልብ ዐሳብ የሚያውቀው፣ ቸርነቱ ወሰን የሌለው የባሕርይ አምላክ መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ልክ እንደ መጀመሪያው ትንሣኤ ዕለት አበው ሐዋርያት በተዘጋ ቤት በአንድነት ተሰባስበው እንዳሉ በሩን ሳይከፍት ገብቶ ‹‹ሰላም ለዅላችሁ ይኹን!›› በማለት በመካከላቸው ቆመ፡፡ ቶማስንም ‹‹ያመንህ እንጂ ተጠራጣሪ አትኹን፤ እነሆ የተቸነከሩ እጆቼንና እግሮቼን፣ የተወጋ ጐኔንም ናና እይ፤›› ብሎ አሳየው፡፡

እርሱም ምልክቱን በማየቱ፣ በመዳሰሱ ትንሣኤውንና አምላክነቱን እንደ ፍላጎቱ በመረዳቱ ‹‹ጌታዬ፣ አምላኬ ብሎ መስክሮ›› የክርስቶስን ትንሣኤ አመነ፡፡ የሳምንቷ ዕለተ ሰንበት፣ የትንሣኤው ምሥጢር ለሁለተኛ ጊዜ ለሐዋርያት የተገለጠበት ዕለት በመኾኑ የትንሣኤው ሳምንት እሑድ ‹ዳግም ትንሣኤ› ተብሎ ይጠራል፤ ይከበራል (ዮሐ. ፳፥፳፬-፴)፡፡

ብርሃነ ትንሣኤውን የገለጸልን አምላካችን ለብርሃነ ዕርገቱም በሰላም ያድርሰን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡
"#የትናንት ሊቃውንት አባቶቻችን ጦም እያደሩ  የጠበቋትን ቤተ ክርስቲያን እኛ እየበላን አሳልፈን መስጠት አይገባም"  ብፁዕ አቡነ አብርሃም

ከ200 በላይ የአብነት መምህራን የተሳተፉበት የምክክር ጉባኤ በመንበረ ፓትርያርክ ጽርሐ ተዋሕዶ እየተካሔደ ይገኛል።

አዲስ አበባ (ግንቦት ፲፭/፳፻፲፮ ዓ/ም / ብራና ሚድያ )

በመንበረ ፓትርያርክ ትምህርትና ማሰልጠኛ መምሪያ ከሊቃውንት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው  ሀገር አቀፍ የምክክርና የውይይት ጉባኤ ማካሔዱን ጀምሯል።

በመርሐ ግብሩ ላይ ብፁዕ አቡነ አብርሃም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የባሕር ዳር ሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ የበላይ ሊቀ ጳጳስ፣የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያ ሐላፊዎች  ከየ አህጉረ ስብከቱ የመጡ ከ200 በላይ ሊቃውንት ቤተ ክርስቲያንና የጉባኤ መምህራን  ተገኝተዋል።

ጉባኤው በጸሎተ ወንጌል የተጀመረ ሲሆን በማስከተልም የደብረ ምሕረት ሰአሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያምና ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ካቴድራል ሊቃውንት
"ያሬድ ካህኑ ለእግዚአብሔር
ትርድአነ ነዐ በህየ መካኑ ያሬድ ነዐ ትርድአነ" የሚለውን ወረብ አቅርበዋል።

የመምሪያው ሐላፊ  መልአከ መዊዕ ሳሙኤል እሸቱ ሊቃውንቱ ከየጉባኤ ቤቱ የመጡትን ሊቃውንት አስተዋውቀዋል።
በዚህም የድጓ፣ የዝማሬ መዋስዕት ፣ የቅኔ ፣የአቋቋም ፣ የሐዲሳትና የብሉያት  መጻሕፍት ትርጓሜ መምህራን መሆናቸው ተገልጿል።

መልአከ መዊዕ ሳሙኤል እሸቱ ለጉባኤ መሳካት የበኩሉን ድርሻ የተወጡትን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የትምህርትና ስልጠና ዋና ክፍልንና ሌሎችን አመስግነዋል።

አክለውም ጉባኤ  ሁልጊዜ በየዓመቱ ከግንቦቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ርክበ ካህናት ከመጀመሩ በፊት ጉባኤ እንዲዘጋጅና እውቅና እንዲሰጠው ጥያቄ አቅርበዋል።

የእንኳን ደህና መጣችሁ አባታዊ መልእክት ያስተላለፉት ብፁዕ አቡነ አብርሃም  ብዙ ኪሎ ሜትሮችን አልፈው ወቅታዊ የሀገሪቱ ሁኔታ ተቋቁመው   የተገኙትን ሊቃውንት እንኳን ደህና መጣችሁ ያሉ ሲሆን የምክክር ጉባኤውን  ያሰናደውን የትምህርት ማሰልጠኛ መምሪያ  አመስግነዋል።

ብፁዕነታቸው  አክለውም ለዘመናት የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባቶች ቤተ ክርስቲያናችንን በበላይነት በሚመሩበት ጊዜ  "አማኙን ከሀገሩ" "እምነቱን ከታሪኩ" ጠብቀው ያቆዩ ሊቃውንት መሆናቸውን በማስታወስ አሁንም የበኩላችሁን የሊቅነት ድርሻችሁን በመወጣት ቤተ ክርስቲያናችንን ልታስከብሩ ይገባል ብለዋል።

በዚህ ዘመን በሕይወት የሚያገለግሉትን ሊቃውንት በኑሯቸውም ልናስባቸውና የት አሉ ልንል ይገባልም ብለዋል።

"የትናንት ሊቃውንት አባቶቻችን ጦም እያደሩ  የጠበቋትን ቤተ ክርስቲያን እኛ እየበላን አሳልፈን መስጠት አይገባም" ሲሉ ገልጸዋል።

ስለሆነም ሊቅነትን ከቤተ ክርስቲያን ተልእኮ ውጤት ጋር በማጣመር ዘመኑን የዋጀና ትውልዱን የሚያተርፍ  አገልግሎት እንድታገለግሉ ወደፊት መምጣት ይገባችኋል ብለዋል።
 
ጉባኤው ለሁለት ቀናት የሚቆይ እንደሆነ ከወጣው መርሐ ግብር ለማወቅ ተችሏል።
#Ethiopia 
#Birana_Media
#BM_Addia_Ababa

ብራና ሚዲያ
የኦርቶዶክሳዊያን ድምፅ

የዩቲዩብ ቻናላችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ
https://www.youtube.com/c/BiranaMedia

የቴሌ ግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ ፤ ፈጣን መረጃዎችን ያግኙ
https://t.me/birana3

በፌስቡክ ገጻችን ትምህርቶች እና ወቅታዊ መረጃዎችን ያግኙ
https://www.facebook.com/birana22

አጫጭር ትምህርታዊ እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት የቲክ ቶክ አማራጫችንን ይመልከቱ
https://www.tiktok.com/@birana16

የኢንስታግራም ገጻችንን
www.Instagram.com/birana96
መጋቤ ኅሩያን የማነብርሃን ጌታኹን
(የኔታ የማነብርሃን)

©️አለምነህ ዓይናለም

እውነትም ስም የሚስማማላቸው ኅሩይ ምርጥ መምህረ ቅዳሴ መምህረ ምግባር ወትሩፋት ናቸው። የማናይ ናቸው። የእኛን ድንቁርና ገፍፈው የሚጥሉ ብሩሃ አእምሮ የተሰጣቸው አሰላሳይ ዘመኑን የዋጁ የቤተ ክርስቲያናችን መምህር የኔታ የማነብርሃን።

ለአርብዓ ዓመት ያለመታከት በታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ገዳም የካህናት ማሠልጠኛ ተቋም መደበኛ እና ኢመደበኛ ደቀ መዛሙርት የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን በተለይም ይህን ዘፈን ዘፈን የሚለውን ‘መዝሙር‘ ሰው እንዲለይ ከዜማ ሊቅነታቸው አንፃር እየተመለከቱ ሰንበት ትምህርት ቤቶችን በማንቃት (በነገራችን ላይ የተሐድሶ ሤራን ቀድመው በመረዳት ቀዳሚ ጉባኤ በጽ/ጽዮን እና ጎላ ሚካኤል ሰ/ት/ቤት አዳራሽ እንደተጀመረ ነው የማውቀው 1997/98።) በማንቃት እና መድኃኒቱንም ጭምር በማዘጋጀት እጅግ ከፍተኛ ሚና የተወጡ የኔታችን ናቸው። የሊቀ ጉባኤ ጌታኹን ደምፀ Getahun Demtse Ayele ሚናቸው እጅግ ከፍተኛ ነው።

የግእዝ ሥርዓተ ንባብ በማስተማር በመጽሐፍ አሳትመው በማሰራጨት በድምፅ ወምስል ተሰጥኦዎችን ሰዓታትን ወዘተ ከቴክኖሎጂ ጋር የተፋለሙ ሰው በርህቀት እንዲማር ትጉ አባት።

የዜማ ምልክቶች በጽሑፍ ወደ ኮምፒዩተር ለማስገባት ሲያደርጉ የነበረው ጥረት: ሰው በተሰጠው ጸጋ ማገልገል ይኖርበታል እንጂ ምንም ዓይነት ሰበብ ማቅረብ እንደሌለበት የሚመክሩት ቋሚ መጽኛችን የኔታ የማነብርሃን :ኅሩይ: ናቸው።

የኔታ የማነብርሃን እና ኮሜርስ ግቢ ጉባኤ የማይነጣጠሉ ናቸው። ዝማሜ በማጥናት መመረቅ: ከቅኔ ማኅሌት ያለውን ያሬዳዊ ውብ ዜማን በሰርግ መርሐ ግብር ላይ ለምእመናን ከታደሙበት ኹሉ በዝማሜ ወረብ ማጀብ እንዲቻል ማድረግ የየኔታ ውጤት ነው።

በማኅበረ ቅዱሳን የመዝሙር ሕግን ሥርዓትን በማውጣት ዝማሬው ዝማሜው የየኔታ አሻራ ቀዳሚ ሳይሆን ይቀራል?

የሁላችን አባት የኔታ የማነብርሃን እንኳን ደስ ያለዎ። ረጅም ዕድሜ ከሙሉ ጤንነት ያድልዎ። ጸጋ በዲበ ጸጋ ያብዛልዎ።

ዘንድሮ የአብነት መምህራን ጉባኤ ላይ ከቅዱስ ፓትርያርካችን ለአርብዓ (40) ዓመታት ላገለገሉበት የቅዳሴ መምህርነት የዕውቅና ሰርተፊኬት በመሰጠትዎ እጅግ ደስስስ ብሎናል የኔታ።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ዛሬ ግንቦት ፳፩ ቀን ፳፱፲ወ፮ ዓ/ም ባደረገው የጠዋቱ የግንቦት ርክበ ካህናት የቅዱስ  ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ስብሰባ ሰባት አበው ሊቃነ ጳጳሳትን በመወያያ አጀንዳ አርቃቂነት ሰየመ።
በዚሁም መሰረት በመወያያ አጀንዳ አርቃቂነት የተሰየሙት ሰባት አበው ሊቃነ ጳጳሳት  ሕገ ቤተ ክርስቲያን በሚያዘው መሰረት ከቋሚ ሲኖዶስ ለምልአተ ጉባኤ እንዲቀርቡ የተመሩ እና ተጨማሪ የሚባሉ አጀንዳዎችን በመቅረጽ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የማስጸደቅ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል።
በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በጀንዳ አርቃቂ ኮሚቴነት የተመረጡት አበው ሊቃነ ጳጳሳት የሚከተሉት ናቸው።

1.ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ
2.ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ
3.ብፁዕ አቡነ ማርቆስ
4. ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ
5. ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል
6. ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ
7. ብፁዕ አቡነ ገብርኤል