ቤተ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
35.6K subscribers
908 photos
16 videos
16 files
721 links
በዚህ ቻናል የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ትምህርቶች እና የአበው ቀደምት የተናገሯቸው መንፈሳዊ ንግግሮች እንዲሁም ልዩ ልዩ ሐይማኖታዊ ትምህርቶችና መልዕክቶች ይተላለፉበታል፡፡
Download Telegram
የሰሙነ ህማማት ሰኞ፡-

መርገመ በለስ የተፈጸመበት ዕለት ነው፡

ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሆሣዕና ዕለት ቢታንያ አድሮ በማግሥቱም ከቢታኒያ ሲመጡ ተራበ፡፡ (ማር.11፤11-12) ቅጠል ያላት በለስ ከሩቅ አይቶ ወደ በለሲቱ ቀረበ፤ ነገር ግን ከቅጠል በቀር አንዳች ፍሬ አላገኘባትም፡፡ ከአሁን ጀምሮ ማንም ከአንቺ ፍሬ አይብላ ብሎ ረገማት። በለስ የተባለች ቤተ-እስራኤል ናት፤ ፍሬ የተባለች ሃይማኖትና ምግባር ናት፤ ከእስራኤል ፍቅርን፤ ሃይማኖትን፤ ምግባርን ፈለገ አላገኘም፤ እስራኤል (ሕዝበ እግዚአብሔር) መባልን እንጂ፤ ደግ ሰው አይገኝብሽ ብሎ ረገማት፤ በመርገሙ ምክንያት እርሱ ከለያቸው በስተቀር ደግ ሰው ጠፋባት፡፡

በለስ ኦሪት ናት፤ ኦሪትን በዚህ ዓለም ሰፍና ቢያገኛት ኦሪትና ነቢያትን ልሽር አልመጣሁም ልፈጽም እንጂ በማለት ፈጸማት፤ ሕገ ኦሪትን ከመፈጸም በቀር በእርሷ ድኅነት አላደረገባትምና፤ ፍሬ በአንቺ አይሁን አላት፤ ደኅነት በአንቺ አይደረግብሽ ብሏታልና እንደመድረቅ ፈጥና አለፈች፡፡

በለስ ኃጢአት ናት፤ የበለስ ቅጠል ሰፊ እንደሆነች ሁሉ ኃጢአት በዚህ ዓለም ሰፍታ ሰፍና አገኛት፡፡ በለስ ሲበሉት ይጣፍጣል፤ ቆይቶ ግን ይመራል፤ ኃጢአትም ሲሰሩት ደስ ደስ ያሰኛል፤ ኋላ ግን ያሳዝናል፤ ወደ እርሷም ሄዶ ማለትም ከኃጥአን ጋር ዋለ፤ ኃጥእ ከመባል በቀር በአንደበቱ ሐሰት፤ በሰውነቱ ክፋት እንዳልተገኘበት ለማመልከት ፍሬ አላገኘባትም አለ፤ በአንቺ ፍሬ አይገኝ የሚለውም፤ በኃጢአት ፍዳ ተይዞ የሚቀር አይኑር ለማለት ነው፤ ስትረገም ፈጥና መድረቋም፣ በአዳም ምክንያት ያገኘችን ዕዳ በደል በእርሱ ካሣነት እንደጠፋችልን ለመግለጽ ነው፡፡

አንጽሆተ ቤተመቅደስ የተፈጸመበት ዕለት ነው፦

ጌታችን በለስን ከረገማት በኋላ ወደ ቤተመቅደስ ሄደ፤ ቤተመቅደስ፣ቤተጸሎት፣ ቤተመሥዋዕት መሆኑ ቀርቶ ቤተ ምስያጥ (የንግድ ቤት) ሆኖ ቢያገኘው ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች፤ እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት ብሎ የሚሸጡበትን ሁሉ ገለበጠባቸው፤ ገርፎም አስወጣቸው፤ ይህም የሚያሳየው ማደሪያው ቤቱ የነበርን የአዳም ልጆች ኃጢአት ሰፍኖብን ስንኖር ቢያገኘን ኃጢአታችንን ሁሉ እንዳራቀልን የሚገልጽ ነው፡፡

በዚህ በሰሙነ ሕማማት ካህናትና ምእመናን በቤተክርስቲያን ተገኝተው ወዛቸው ጠብ እስኪል ድረስ በነግህ፤ በሠለስተ፣ በስድስቱ ሰዓት፤ በተሰዓቱ ሰዓትና በሠርክ መላልሰው ሲሰግዱና ሲጸልዩ ይሰነብታሉ፤ በተለይም ካህናት በማንኛውም አገልግሎት ጥቁር ልብስ ይለብሳሉ፤ ምክንያቱም የደረሰብን መከራ ኀዘኑን እና 5ሺ ከ5መቶ ዘመን የሰው ልጅ በጨለማ ይኖር እንደነበረ ለማዘከር ነው፡፡

🍀🌸 🌸🍀
💐 @beteafework 💐
🌺🍂 @beteafework 🍂🌺
💐 @beteafework 💐
🍂🏜💒🏜🍂
በግብረ ሕማማት ውስጥ የሚገኙ እንግዳ ቃላት እና ትርጉማቸው ፡-

በግብረ ሕማማት ውስጥ ወደ ግእዝም ሆነ በኋላ ወደ አማርኛ ሳይተረጎሙ የተቀመጡ የዕብራይስጥ፣ የቅብጥ እና የግሪክ ቃላት ይገኛሉ፡፡ የእነዚህ ቃላት ትርጉም የሚከተለው ነው፡፡

#ኪርያላይሶን
ቃሉ የግሪክ ሲሆን አጠራሩ «ኪርዬ ኤሌይሶን»ነው፡፡ «ኪርያ» ማለት «እግዝእትነ» ማለት ሲሆን «ኪርዬ» ማለት ደግሞ «እግዚኦ» ማለት ነው፡፡ ሲጠራም «ኪርዬ ኤሌይሶን» መባል አለበት፡፡ ትርጉሙ «አቤቱ ማረን»ማለት ነው፡፡ «ኪርያላይሶን» የምንለው በተለምዶ ነው፡፡ ይኼውም ኪርዬ ከሚለው «ዬ» ኤላይሶን ከሚለው ደግሞ«ኤ» በመሳሳባቸው በአማርኛ «ያ»ን ፈጥረው ነው፡፡

#ናይናን
የቅብጥ ቃል ሲሆን ትርጉሙ «መሐረነ፣ ማረን» ማለት ነው፡፡

#እብኖዲ
የቅብጥ ቃል ሲሆን ትርጉሙ «አምላክ» ማለት ነው፡፡ «እብኖዲ ናይናን» ሲልም «አምላክ ሆይ ማረን» ማለቱ ነው

#ታኦስ
የግሪክ ቃል ሲሆን ትርጉሙ «ጌታ፣ አምላክ» ማለት ነው፡፡ «ታኦስ ናይናን» ማለትም «ጌታ ሆይ ማረን» ማለት ነው፡፡

#ማስያስ
የዕብራይስጥ ቃል ሲሆነ ትርጉሙ «መሲሕ» ማለት ነው፡፡ «ማስያስ ናይናን» ሲልም «መሲሕ ሆይ ማረን» ማለት ነው

#ትስቡጣ
«ዴስፓታ» ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ ሲሆን ትርጉሙም ደግ ገዥ ማለት ነው

#አምነስቲቲ_ሙኪርያቱ_አንቲ_ፋሲልያሱ
የቅብጥ ቃል ሲሆን ትርጉሙም «ተዘከረነ እግዚኦ በውስተ መንግሥትከ- አቤቱ በመንግሥትህ አስበኝ» ማለት ነው፡፡

#አምንስቲቲ_ሙዓግያ_አንቲ_ፋሲልያሱ
የቅብጥ ቃል ሲሆን «ተዘከረነ ኦ ቅዱስ በውስተ መንግሥትከ -ቅዱስ ሆይ በመንግሥትህ አስበን» ማለት ነው፡፡

#አምንስቲቲ_ሙዳሱጣ_አንቲ_ፋሲልያሱ
የቅብጥ ቃል ሲሆን ትርጉሙም «ተዘከረነ እግዚአ ኩሉ በውስተ መንግሥትከ- የሁሉ የበላይ የሆንክ ወይ በመንግሥትህ አስበን» ማለት ነው፡፡
Forwarded from ገብረ እግዚአብሔር ኪደ (ገብረእግዚአብሔር ኪደ)
ዐቢይ ጦም ሊጠናቀቅ ሲል የተሰጠ ምዕዳን

እነሆ የተቀደሰውን ወርኃ ጦም ወደ ማጠናቀቅ ተቃርበናል፤ የጦሙን ጉዞ ወደ ማገባደድ ደርሰናል፤ እግዚአብሔር ረድቶንም ወደ ወደቡ ልንደርስ ተጠግተናል፡፡

ነገር ግን እንዲህ በመኾኑ ልል ዘሊላን ልንኾን አይገባንም፤ ይህን ምክንያት አድርገን ከከዚህ በፊቱ ላይ ትጋታችንንና ንቃታችንን እጅጉን እንጨምር እንጂ፡፡

የመርከብ አለቆች ብዙ ባሕረኞችንና ዕቃ ጭነው ረጅም የባሕር ላይ ጉዞ ካደረጉ በኋላ ወደ ወደቡ ሊደርሱ ሲሉ መርከባቸው ከዓለት ጋር እንዳትጋጭና ድካማቸውን ኹሉ ከንቱ ላለማድረግ ከፍ ያለ ጥንቃቄ ያደርጋሉ፡፡ ሯጮችም እንደዚሁ ወደ መጨረሻው መስመር ሊቃረቡ ሲሉ ኃይላቸውን ኹሉ አሟጥጠው ተጠቅመው ሽልማቱን ለመውሰድ ይጥራሉ፡፡ ትግለኞችም ምንም እንኳን ስፍር ቊጥር የሌለው ቡጢ ቢደርስባቸውም፣ ምንም እንኳን ብዙ ጊዜ ተመትተው ቢወድቁም ሽል ማቱን ይወስዱ ዘንድ የመጨረሻውን ዙር ትግል እጅግ ከፍ ባለ ጉልበ ት ይታገላሉ፡፡

ስለዚህ የመርከብ አለቆች፣ ሯጮችና ትግለኞች ድል ወደ ማድረግ ሲቃረቡ እጅግ ከፍ ያለ ትጋትና ጥንቃቄ ኃይልም እንደሚጠቀሙ፥ እኛም ወደ ታላቁ ሳምንት ደርሰናልና እግዚአብሔር ስለረዳን እያመሰገንን ጸሎታችንን፣ ተአምኖ ኃጢአታችንን፣ በጎ ምግባራችንን፣ ምጽዋ ታችንን፣ ከሌሎች ሰዎች ጋር ያለን መስተጋብራችንን፣ ራስን የመግዛት ጠባያችንን፣ እንደዚሁም ይህን የመሰለው ሌላው ምግባራችንን ከፍ ባለ ትጋትና ጥንቃቄ ልንፈጽም ይገባናል፡፡ እነዚህን በጎ በጎ ነገሮችን ወደ ጌታ ቀን (ወደ በዓለ ትንሣኤ) የምንደርስ ከኾነ ከጌታችን ዘንድ ባለሟልነትን እናገኛለን፤ ከማዕዱ ዘንድ መሳተፍ ይቻለናል፡፡

© አምስቱ የንስሐ መንገዶች፣ ገጽ 148
የሰሙነ ህማማት ማክሰኞ

#የጥያቄ_ቀን_ይባላል፡-

ሰኞ ባደረገው አንጽሖተ ቤተመቅደስ ምክንያት፣ ሹመትን ወይም ሥልጣንን ለሰው ልጅ የሰጠ ጌታችን፣ ስለ ሥልጣኑ በጸሐፍት ፈሪሳውያን ተጠይቋልና፤ የጥያቄ ቀን ይባላል፡፡

ጥያቄውም ከምድራውያን ነገሥታት፣ ከሌዋውያን ካህናት ያይደለህ ትምህርት ማስተማር፣ ተዓምራት ማድረግ፣ ገበያ መፍታትን፣ በማን ሥልጣን ታደርጋለህ? ይህንንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ? የሚል ነበር፡፡ /ማቴ. 21፥23-27፣ ማር. 11፥ 7-35፣ ሉቃ.21፥23-27፣ ማር.11፥27-33፣ ሉቃ. 20፥1-8/፤ እርሱም ሲመልስ፤ «እኔም አንድ ነገር እጠይቃችኋለሁ፣ እናንተም ብትነግሩኝ በማን ሥልጣን እነዚህን እዳደርግ እነግራችኋለሁ፡፡ የዮሐንስ ጥምቀት ከወዴት ነበረ፣ ከሰማይ ነውን? ወይስ ከሰዉ? በእግዚአብሔር ፈቃድ፣ ወይስ በሰው ፈቃድ?» አላቸው፡፡ እነርሱም ከሰማይ ብንል ለምን አልተቀበላችሁትም ይለናል፤ ከሰው ብንል ሕዝቡ ሁሉ ዮሐንስን እንደ አባት ያከብሩታል፣ እንደ መምህርነቱ ይፈሩታልና ሕዝቡን እንፈራለን፤ ተባብለው ከወዴት እንደሆነ አናውቅም ብለው መለሱለት፡፡ እርሱም እኔም በማን ሥልጣን እነዚህን እንደማደርግ አልነግራችሁም አላቸው» ይህንንም መጠየቃቸው እርሱ የሚያደርጋቸውን ሁሉ በራሱ ሥልጣን እንዲያደርግ አጥተዉት አልነበረም፣ ልቡናቸው በክፋትና በጥርጥር ስለተሞላ እንጂ፡፡

#የትምህርት_ቀንም_ይባላል፡-

በማቴ. 21፥28፣ ምዕ. 25፥46፣ ማር.12፥2፣ ምዕ.13፥37፣ ሉቃ. 20፥9፣ ምዕ. 21፥38 የሚገኙት ትምህርቶች ሁሉም የማክሰኞ ትምህርት ይባላሉ፡፡ በዚህ ዕለት በቤተ መቅደስ ረጅም ትምህርት ስላስተማረ፣ የትምህርት ቀንም ይባላል፡፡ ክርስቲያን የሆነ ሁሉ ከሥጋዊ ነገር ርቆ በዚህ ሰሞን የሃይማኖት ትምህርት ሲማር ሲጠይቅ መሰንበቱ መጽሐፋዊ ሥርዓት ነው፡፡


🍀🌸 🌸🍀
💐 @beteafework 💐
🌺🍂 @beteafework 🍂🌺
💐 @beteafework 💐
🍂🏜💒🏜🍂
"እግዚአብሔር የሚወዳችሁ እናንተም የምትወዱት ልጆቼ ሆይ! ወርሐ ጾሙ ሲያልቅ ባዶ እጃችንን እንዳንገኝ በኹሉም ረገድ እንበርታ ብዬ እማልዳችኋለሁ፡፡ በጾም እየደከሙ ሳለ የጾምን ዋጋ ሳያገኙ መቅረት አለና፡፡ "ይህስ እንደምን ነው?" ያላችሁኝ እንደኾነም፦"ከምግበ ሥጋ እየጾምን ሳለ የኃጢአትን መብል ስንመገብ፣ሥጋን ከመብላት ተከልክለን ሳለ የድኻውን ቤት ስንበረብር፣ ወይንን ከመጠጣት ታቅበን ሳለ በክፉ መሻቶች ስንሰክር፣ ቀን ሙሉ ምግብ ሳንበላ ውለን ሳለ ዓይናችን ግን ክፉ ነገሮችን ሲመለከት ነዋ" ብዬ እመልስላችኋለሁ፡፡"

ቅዱስ ዮሃንስ አፈወርቅ
"የሰሙነ ህማማት ረቡዕ"

ምክረ አይሁድ ይባላል፦
ምክንያቱም የአይሁድ ሊቃነ ካህናትና ጸሐፍት ጌታን እንዴት መያዝ እንደሚገባቸው ምክር ያጠናቀቁበት ቀን ነውና፡፡ በዚህ ምክራቸው ላይ በጣም ትልቅ ጭንቀት ነበር፡፡ ምክንያቱም ወቅቱ የፋሲካ በዓላቸውን የሚያከብሩበት ቀን የተቃረበ በመሆኑ ብዙው ሕዝብም በጌታችን ትምህርት የተማረኩ ተአምራቱንም የሚያደንቁ ስለ ነበር ሁከት እንዳይፈጠር ነው፡፡ በዚህ ጭንቀት ሳሉ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ የአስቆሮቱ ይሁዳ በመካከላቸው በመገኘት የምክራቸው ተባባሪ ሆኖ ጭንቀታቸውን አስወግዶላቸዋል፡፡/ማቴ. 26÷1-14፣ ማር. 14÷1-2፣ ሉቃ. 22÷1-6/ የሐዲስ ኪዳን ካህናትና ምእመናን በዚሁ ዕለት በቤተ ክርስቲያን ተሰብስበው መላ ሰውነታቸውን ለእግዚአብሔር አስገዝተው የሞት ፍርዱን በማሰብና በማልቀስ ሐዋርያት ከጌታችን መያዝ በኋላ በኀዘን በፍርሐት እንደነበሩ እያሰቡ መጻሕፍትን በማንበብ በጾም በጸሎትና በስግደት ተወስነው ይቆዩና ከአሥራ ሁለት ሰዓት በኋላ ወደ ቤታቸው ይሄዳሉ፡፡

የመልካም መዓዛ ቀንም ይባላል፦
ምክንያቱም ጌታችን በዚህ ዕለት በቤተ ስምዖን ዘለምጽ ተቀምጦ ሳለ መላ ሕይወቷን ለዝሙት አስገዝታ ትኖር የነበረችው ማርያም እንተ እፍረት /ባለሽቱዋ ማርያም/ «ከእንግዲህ ወዲህ በኃጢአት ተበላሽቶ ይኖር የነበረውን ሕይወቴን እንደዚህ መልካም ሽቱ የሚያጣፍጥ ኃጢአትን ይቅር የሚል አምላክ መጣ» ስትል ዋጋው እጅግ በጣም ውድ የሆነ ከሦስት መቶ ዲናር በላይ የሚያወጣ በአልባስጥሮስ ብልቃጥ የተሞላ ሽቱ ይዛ በመሔድ በጠጉሩ /በራሱ/ ላይ በማርከፍከፍ ስለቀባችው ረቡዕ የመዓዛ ቀን ይባላል፡፡

የእንባ ቀንም ይባላል፦
ማርያም እንተ እፍረት በጌታችን እግር ላይ ተደፍታ መላ ኃጢአቷን ይቅር እንዲላት በእንባዋ እግሩን አጥባዋለችና በጠጉሯም በእንባዋ ያጠበችውን እግሩን አብሳዋለችና፡፡/ማቴ. 26÷6-13፣ ማር. 14÷9፣ ዮሐ. 12÷8/ ኃጢአትን በማሰብ ማልቀስና ራስን የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር ማቅረብን ከምታስተምረን ማርያም እንተ እፍረት እንባን ለንስሐ ሕይወት ልንጠቀምበት ይገባል፡፡

እንበለ ደዌ ወህማም እንበለ ጻማ ወድካም ያብጽሐነ ያብጽሕክሙ ለብርሃነ ትንሳኤሁ እግዚአብሔር በፍስሐ ወበሰላም።


🍀🌸 🌸🍀
💐 @beteafework 💐
🌺🍂 @beteafework 🍂🌺
💐 @beteafework 💐
🍂🏜💒🏜🍂
ሰሙነ ህማማት ዘሐሙስ (ጸሎተ ሐሙስ)

በቤተ ክርስቲያን የተለያዩ ስያሜዎች ያሏቸው በርካታ ድርጊቶች የተፈጸሙበት ዕለት ነውና ጸሎተ ሐሙስ ይባላል፡፡ የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋን የተዋሐደ አምላክ፣ መሆኑን ለመግለጥና ለአርአያነት ጠላቶቹ መጥተው እስኪይዙት ድረስ ሲጸልይ ያደረበት ነውና ጸሎተ ሐሙስ ተባለ፡፡ ማቴ. 26፣ 36-46 ዮሐ.17

#ሕፅበተ_ሐሙስ_ይባላል
ጌታችን በዚህ ዕለት የደቀመዛሙርቱን እግር በፍጹም ትሕትና ዝቅ ብሎ አጥቧል፡፡ ይህም የሚያሳየው የዓለምን ሁሉ ኃጢአት ለማጠብ የመጣ መሆኑን ነው፡፡ ይህን ለማስታወስ ዛሬም ካህናት በተለይም ሊቃነ ጳጳሳት፣ የደብር አስተዳዳሪዎች፤ «በመካከላችን ተገኝተህ የእኛንና የሕዝብህን ኃጢአት እጠብ እኛም የአንተን አርአያ አንዘነጋም የሌላውን እግር እናጥባለን፤» ሲሉ በቤተ ክርስቲያን የተገኙትን ምእመናንን እግር በወይንና በወይራ ቅጠል ያጥባሉ፡፡

#የምስጢር_ቀን_ይባላል
ከሰባቱ ምስጢራት አንዱ በዚህ ዕለት ተመሥርቷልና፡፡ ይኸውም «ይህ ስለ እናንተ በመስቀል ላይ የሚቆረሰው ሥጋዬ ነው፡፡ እንካችሁ ብሉ» ጽዋውንም አንስቶ አመሰገነ «ይህ ስለ እናንተ ነገ በመስቀል የሚፈስ ደሜ ነው ከእርሱም ጠጡ» በማለት፤ እኛ ከእርሱ ጋር፣ እርሱ ከእኛ ጋር አንድ የምንሆንበትን ምስጢር ከጠላት ዲያብሎስ ሰውሮ፣ ለደቀ መዛሙርቱ የገለጠበት ቀን በመሆኑ የተሰጠ ሥያሜ ነው፡፡ በዚህ ዕለት ክርስቲያን የሆነ ሁሉ በንስሐ ታጥቦ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ለመቀበል ይዘጋጃል፡፡

#የሐዲስ_ኪዳን_ሐሙስ_ይባላል
ምክንያቱም መሥዋዕተ ኦሪት ማለትም በእንስሳት ደም የሚቀርበው መሥዋዕት ማብቃቱን ገልጦ፣ ለድኅነተ ዓለም ራሱን የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበበት ዕለት በመሆኑ ነው፡፡ «ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው በደሜ የሚሆን ሐዲስ ኪዳን ነው፡፡ ከእርሱ ጠጡ» በማለቱ ይታወቃል /ሉቃ. 22፣20/ ኪዳን ማለት በሁለት ወገን መካከል የሚደረግ ውል፣ ስምምነት፣ መሐላ ማለት ነው፡፡ በዚህ መሠረት ጌታችን ለአዳምና ለልጆቹ ሁሉ ዘለዓለማዊውን ቃል ኪዳን በራሱ ደም የፈጸመበት ዕለት ስለሆነ የሐዲስ ኪዳስ ሐሙስ ተባለ፡፡

#የነጻነት_ሐሙስ_ይባላል
ለኃጢአትና ለዲያብሎስ ባሪያ ሆኖ መኖር ማብቃቱ፣ የሰው ልጅ ያጣውን ክብር መልሶ ማግኘቱ የተረጋገጠበት ቀን ስለሆነ ነው፡፡ ጌታችን ስለ ሰው ልጅ ነጻነት ሲናገር «ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም ባርያ ጌታዉ የሚያደርገውን አያውቅምና ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ» በማለት /ዮሐ. 15፣15/፤ ከባርነት የወጣንበት ልጆች የተባልንበትን ቀን የምናስብበት በመሆኑ ሊቃውንቱ የነጻነት ሐሙስ አሉት፡፡ እያንዳንዱ ክርስቲያንም ከኃጢአት ባርነት ርቆ፣ ከእግዚአብሔር ጋር የሚያወዳጀውን መልካም ሥራ በመሥራት ሕይወቱን መምራት ይኖርባታል፡፡ ባሮች አልላችሁም ተብለናልና፡፡
ጉልባን
ጉልባን ከባቄላ ክክ፣ ከስንዴ ወይንም ከተፈተገ ገብስ ጋር አንድ ላይ ተቀቅሎ የሚዘጋጅና የጸሎተ ሐሙስ ዕለት የሚባላ ንፍሮ ነው፡፡ የጉልባን ትውፊት እስራኤላውያን ከግብፅ ተሰደው በሚወጡበት ጊዜ በችኮላ ስለነበር፤ አቡክተው ጋግረው መብላት ያለመቻላቸውን ሁኔታ ያመለክታል፡፡ ያን ጊዜ ያልቦካውን ሊጥ እየጋገሩ ቂጣ መብላት፤ ንፍሮም ቀቅለው ስንቅ መያዝ ተግባራቸው ነበርና ይህን ለማሰብ በሰሙነ ሕማማት ቂጣና ጉልባን በማዘጋጀት በዓሉ ይታሰባል፡፡

በጸሎተ ሐሙስ ይህንን መሠረት በማድረግ የሚዘጋጀው ጉልባን አንዲህም ቂጣ ጨው በዛ ተደርጎ ይጨመርበታል፡፡ ጨው ውኃ የሚያስጠማ በመሆኑ የጌታን መጠማት ያስታውሳል፡፡ ይህ ትውፊታዊ ሥርዓት ከእስራኤላውያን የመጣ ሲሆን በኢትዮጵያም አብዛኛዎቹ የትውፊት ክንዋኔዎች የብሉይ ኪዳን መነሻ ስላላቸው ሥርዓቱ ዛሬም ይከበራል፡፡

(ስምዐ ጽድቅ ልዩ እትም ዘሰሙነ ሕማማት መጋቢት 2002)
የሰሙነ ሕማማት ዕለተ ዓርብ

ዕለተ ዓርብ በቤተክርስቲያን ልዩ ቀን ነው፡፡ የማይታመመው ታሞ የዋለበት፣ የወደቁ ከተረሱበት ከትቢያ የሚያነሳ እሱ ሲወድቅ ሲነሳ የዋለበት፣ ሕመምተኞችን የሚፈውስ እሱ ሲያቃስት የዋለበት፣ ከሲኦል የዲያብሎስ ግብር ነፃ የሚያወጣ ሲገረፍ የዋለበት፣ ወልደ እግዚአብሔር ለወዳጆቹ ድኅነት በመስዋዕትነት ሙሽራ የሆነበት የደስታ ቀን፤ አሳዳጅ አሳሪያችን ዲያብሎስ ከነወጥመዱ ድል የተነሳበት ቀን ነው። ከዚህም የተነሳ በቤተክርስቲያን የተለያየ ምስጢራዊ ስያሜዎች ተሰጥቶታል፡፡

#የስቅለት_ዓርብ ይባላል
የዓለም ሁሉ መድኀኒት የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዳምና ለልጆቹ ሁሉ ቤዛ ሆኖ በመልዕልተ መስቀል ላይ ተሰቅሎ ለዓለ ድኅነት መስዋዕት ሆኖ የዋለበት ዕለት በመሆኑ የስቅለት ዓርብ ተብሏል። (ማቴ 27፡35)

#መልካሙ_ዓርብ ይባላል
ይህም የሚያስገነዝበን ከስቅለተ ክርስቶስ በፊት ማንም ሰው ሲያጠፋ በመስቀል ተሰቅሎ እንዲሞት ይደረግ ነበር፡፡ በተለይ በሮማውያንና በፈሪሳውያን ሕግ መስቀል የወንጀለኞች መቅጫ ነበረ። በዚህ ዕለት ግን ታሪክን የሚቀይር ነገርን የሚገለብጠው አምላክ የወንጀለኞች መቅጫ ምልክት የነበረውን መስቀል በደሙ ቀድሶ የምህረት ምልክት፣ የሕይወት አርአያ፣ የዲያብሎስ ድል መንሻ ፣ የቤተክርስቲያን ጌጥ፣ የገዳማት ዘውድ ስላደረገውና በዕለተ ዓርብ በሞቱ ሕይወትን ስላገኘን መልካሙ ዓርብ ተብሏል፡፡

በዚህ ዕለትም ጌታ ሁሉ ተፈጸመ ብሎ ቅድስት ነፍሱን ከቅድስት ስጋው በራሱ ፈቃድ ከለየ በኋላ አምላክነቱን ለመግለፅ ተአምራት አሳይቷል፦
1. ፀሐይ ጨልማለች
2. ጨረቃ ደም ሆናለች
3. ከዋክብት ረግፈዋል
4. የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ተቀዷል
5. ምድር ተናወጣለች (ተንቀጥቅጣለች)
6. መቃብሮች ተከፍተዋል
7. ሙታን ተነስተዋል

በዓመት አንድ ጊዜ የምናገኘው ይህ ዕለት ቀራንዮን የምናስብበት ነገረ መስቀሉን የምናስተውልበት እንጂ ስለምድራዊ ኑሮአችን ስንባክን የምንውልበትና በዋዛ ፈዛዛ ልናሳልፈው አይገባም፡፡
ይህን ያህል ትሕትና እንደምን ያለ ትሕትና ነው። ይህን ያህል ትዕግሥት እንደ ምን ያለ ትዕግስት ነው። ይህን ያህል ዝምታ እንደምን ያለ ዝምታ ነው። ይህን ያህል ቸርነት እንደምን ያለ ቸርነት ነው። ይህን ያህል ሰውን ማፍቀር እንደምን ያለ ፍቅር ነው። ፍቅር ያምላክን ልጅ ከዙፋኑ ሳበው እስከ ሞትም አደረሰው። በደል የሌለበትን እንደ በደለኛ ሰቀሉት ሕይወትን የሠራውን ከበደለኞች ጋር ቆጠሩት። አዳምን የፈጠሩ እጆች በመስቀል ቀኖት ተሸነከሩ ወዮ በገነት የተመላለሱ እግሮች በመስቀል ቀኖት ተቸነከሩ ወዮ። በአዳም ፊት የሕይወት መንፈስን እፍ ያለ አፍ ከሐሞት ጋር የተቀላቀለ የኮመጠጠ መጻጻን ጠጣ ወዮ።

የወልድን መከራውን የሚናገር ምን አፍ ነው ምን ከንፈር ነው ምን አንደበት ነው። የፍቅር የጌታ ሕማማት በተነገረ ጊዜ ልብ ይለያል ኅሊናም ይመታል ነፍስም ትንቀጠቀጣለች ሥጋም ይደክማል። የማይሞተው ሞተ ሞትን ይሽረው ዘንድ ሞተ ሙታንን ያድናቸው ዘንድ ሞተ።

(የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ቅዳሴ)
ቀዳም ሥዑር (የተሻረች ቅዳሜ)

#ቀዳም_ሥዑር ይባላል፡-
በዚች ዕለች ከድሮው በተለየ መልኩ የጌታችንን መከራ በማሰብ በጾም ታስባ ስለምትውል የተሻረችው ቅዳሜ ትባላለች፡፡ የማትጾመዋ ቅዳሜ ስለምትጾም ስዑር /የተሻረች/ ተብላለች በዓል መሻርን አይመለከትም በቀዳም ሥዑር ሌሊት ሥርዓቱ የሚጀመረው በመኀልየ ሰሎሞን ምንባብ ነው፡፡ ማኀሌቱም እዝሉ እየተቃኘ እየተመጠነ፣ እየተዘመመ እየተመረገደ እየተጸፋ ያድራል፡፡ ጥዋት አቡን መዋሥዕት ውዳሴ ማርያም ዜማ ተደርሶ ወለመልአከ ሕይወትሰ ሰቀልዎ በሚለው ሰላም ይጠናቀቃል፡፡በዚህ ዕለት ልብሰ ተክህኖ የለበሱ ካህናትና ዲያቆናት ቄጤማ ተሸክመው ቃጭል ሲያቃጨሉ መታየታቸው ዕለተ ትንሣኤውን ለሚናፍቅ ምእመን ትልቅ ብስራት ነው፡፡

#ለምለም_ቅዳሜ ይባላል፡-
ካህናቱ ለምእመናን ለምለም ቀጤማ የሚያድሉበት ዕለት ስለሆነ በዚህ ተሰይሟል፡፡ ቀጤማውንም ምእመናን እስከ ትንሣኤ ሌሊት በራሳቸው ላይ ያስሩታል፡፡ በቀዳም ስዑር ቀሳውስቱና ዲያቆናቱ ቃጭል /ቃለዓዋዲ/ እየመቱ ገብረ ሰላመ በመስቀሉ ትንሣኤሁ አግሃደ የሚለውን ያሬዳዊ ዜማ በመዘመር፤ ጌታ በመስቀሉ ሰላምን እንደሰጠን እና ትንሣኤውንም እንደገለጠልን በማብሰር፤ ቄጤማውን ለምእመናን ይሰጣሉ፡፡ ምእመናኑም በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚውል ገጸ በረከት ያቀርባሉ፡፡ ቄጤማውንም በራሳቸው ያስራሉ፡፡ ይህም አይሁድ ጌታችንን እያሰቃዩ ሊሰቅሉት ባሉ ጊዜ የእሾህ አክሊል ጭንቅላቱ ላይ ያሠሩበትን ድርጊት የሚያስታውስ ነው፡፡

(የቀጤማው አመጣጥና ምስጢርም ከአባታችን ከኖኅ ታሪክ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ምድር በማየ አይኅ /በጥፋት ውኃ/ በጠፋችበት ወቅት የኖኅ ታማኝ መልእክተኛ ርግብ የውኃውን መጉደል ያበሰረችው ቀጤማ ይዛ በመግባት ነው፡፡ ዛሬም ለሐዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች የኃጢአት ውኃ ጐደለ፣ የኃጢአት ውኃ ጠፋ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ነጻነት ተሰበከ ታወጀ በማለት ካህናት ቄጠማ ይዘው ምእመናንን ያበሥሩበታል፡፡)

#ቅዱስ_ቅዳሜ ይባላል፡-
ቅዱስ ቅዳሜ መባሉ ቅዱስ የሆነ እግዚአብሔር በጥንተ ተፈጥሮ ፍጥረታትን አከናውኖ ከፈጠረ በኋላ በዚህ ቀን ከሥራው ሁሉ ያረፈበት ነው፡፡ በዘመነ ሐዲስ ደግሞ የማዳን ሥራውን ሁሉ ፈጽሞ በሥጋው በመቃብር ሲያርፍ፣ በነፍሱ ሲዖልን በርብሮ ባዶዋን አስቀርቷታል፡፡ በዚያ ለነበሩት ነፍሳትም የዘለዓለም ዕረፍትን ያወረሰበት ዕለት ስለሆነ ከሌሎቹ ዕለታት የተለየ ዕለት ለማለት ቅዱስ ቅዳሜ ተብሏል፡፡

(ስምዐ ተዋሕዶ የስምዐ ጽድቅ ልዩ እትም ዘሰሙነ ሕማማት ሚያዝያ 2004 ዓም)
እግዚአብሔርን የሚያምንና የሚወድ ቢኖር፥ እርሱ በዚህ አንፀባራቂና የደስታ በዓል ደስ ይበለው፡፡ ብልህ አገልጋይ ቢኖር፥ እርሱ ወደ ጌታው ሐሴት ገብቶ ዕልል ይበል፡፡

በጾም የደከመ ቢኖር፥ አሁን ደመወዙን ይቀበል፡፡ በመጀመሪያው ሰዓት ወደ አምላኩ የቀረበ ቢኖር፥ ዛሬ ሽልማቱን ይውሰድ፡፡
በሦስተኛው ሰዓት የመጣ ቢኖር፥ እርሱ በዓሉን በምስጋና ያክብር፡፡ በስድስተኛው ሰዓት የደረሰ ቢኖር፥ አይጎድልበትምና አይጠራጠር፡፡ እስከ ዘጠነኛ ሰዓት የዘገየ ቢኖር፥ ሳይጠራጠር ይቅረብ፡፡ እስከ ዐሥራ አንደኛዋ ሰዓት የዘገየ ቢኖር፥ ስለ መዘግየቱ አይደንግጥ፡፡ ጌታ ቸር ነውና፤ በመጨረሻ የመጣውንም እንደ መጀመሪያው አድርጐ ይቀበሏልና፡፡ በዐሥራ አንደኛው ሰዓት ለመጣው ከመጀመሪያው ሰዓት አንሥቶ ሲደክም ከነበረው ጋራ እኩል ይሰጧልና፡፡
መጨረሻ ለመጣው ጌታ ምሕረቱን ይለግሰዋል፤ መጀመሪያ ለመጣውም ያስብለታል፡፡ ለአንደኛው ይሰጠዋል፤ ለሌላኛውም ጸጋውን ያድለዋል፡፡ ለአንደኛው መልካም ምግባሩን ይቀበልለታል፡፡ ለሌላኛውም መልካም ፍቃዱን ይቀበልለታል፡፡ ለአንዱ ምግባሩን ያከብርለታል፤ ለሌላኛውም በቅን ልቡና የሚያደርገውን ጥረት ያደንቅለታል፡፡ ስለዚህ ኹላችሁም ወደ ጌታችሁ ደስታ ግቡ፡፡

ፊተኞች ኋለኞችም ሆይ! እኩል ደመወዛችሁን ተቀበሉ፡፡ ባለጸጐች ድኾችም ሆይ! በአንድነት ዘምሩ፡፡ እናንተ ብርቱዎች ደካሞችም ሆይ! በዓሉን አክብሩት፡፡ እናንተ የጾማችሁ መጾም ያልቻላችሁም ሆይ! ዛሬ ላይ ደስ ይበላችሁ፡፡
መሠዊያው ሙሉ ነውና ኹሉም በማዕዱ ደስ ይበለው፡፡ ፍሪዳው የሰባ ነውና አንድ ሰው ስንኳ እንደ ተራበ እንዳይሔድ፡፡ ኹላችንም የእምነት በዓሉን እንካፈል፤ ከቸርነቱና ከፍቅሩ ሀብትም እንቋደስ፡፡

ማንም ስለ ድኽነቱ አይዘን፥ ኵላዊቷ መንግሥት ተገልጣለችና፡፡ ማንም በኃጢአቱ አያንባ፥ ከመቃብሩ የይቅርታ ብርሃን ተንቦግቧልና፡፡ ማንም ሞትን አይፍራ፥ የመድኃኒታችን ሞት ከዚህ ነጻ አውጥቶናልና፡፡ ለእርስዋ በመታዘዝም ጌታ አጥፍቷታልና፡፡
በሞቱ ሞትን ገደለው፡፡ ወደ ሲዖል በመውረድ ሲዖልን በዘበዘው፡፡

ኢሳይያስም አሰምቶ እንደ ተናገረ ሲዖል ከጌታችን ጋር ፊት ለፊት ተገናኘች፤ መረራትም! ከንቱ አድርጓታልና መረራት! ሸንግሏታልና መረራት! ሽሯታልና መረራት!
ነፍሳትን ይዛ እንዳታስቀር አስሯታልና መረራት!
[መቃብር የዕሩቅ ብእሲ] ሥጋ አገኘሁ ብላ ዋጠችው፤ ስትውጠው ግን እግዚአብሔር ኾኖ አገኘችው - መረራትም!

ሞት ሆይ! መውጊያህ ወዴት አለ? ሲዖል፥ መቃብርም ሆይ! ድል መንሣትህ ይዞም ማስቀረትህ ወዴት አለ?
ክርስቶስ ተነሣ፤ ሞት ሆይ፥ አንተም ጠፋህ!
ክርስቶስ ተነሣ፣ አጋንንትም አዘኑ!
ክርስቶስ ተነሣ፤ መላእክትም ሐሴት አደረጉ!
ክርስቶስ ተነሣ፤ የሰው ሕይወትም ነጻ ወጣች!
ክርስቶስ ተነሣ፤ መቃብርም ባዶ ኾነች!
ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ተነሥቶ ለአንቀላፉት ኹሉ በኵር ኾኖላቸዋልና፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
ከትንሳኤ እሁድ በኋላ ያሉ ዕለታት ስያሜ፡-

#ሰኞ- ማዕዶት ይባላል፡-
ማዕዶት ማለት መሻገር፣ ማለፍ ማለት ነው፡፡ በዚህ ዕለት በፋሲካችን በክርስቶስ ትንሣኤ ከድቅድቅ ጨለማ ወደ ሚደነቅ ብርሃን፣ ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከሲኦል ወደ ገነት፣ ከሃሳር ወደ ክብር መሻገራችንን እናስባለን፡፡

#ማክሰኞ- ቶማስ ይባላል፡-
በዚህ ዕለት ቶማስ ጌታን አይቶ ማመኑ፤ ጌታዬና አምላኬ ብሎ መመስከሩ ይዘከራል፡፡ ዮሐ. 20፡27-29

#ረቡዕ- አልአዛር ይባላል፡-
በዚህ ዕለት ትንሣኤና ሕይወት የሆነው ጌታ ኢየሱስ አልአዛርን ከሞት እንዳስነሳው እናስባለን፡፡ ክርስቶስ የሞትን ስልጣን የሻረ የሕይወት ራስ፤ የመቃብርን ሥርዓት ያጠፋ ትንሣኤ፡ በድልም ያረገ ንጉሥ መሆኑን እንመሰክራለን፡፡

#ሐሙስ- አዳም ሐሙስ ይባላል፡-
በዚህ ዕለት ለአዳም የተሰጠው ተስፋ እና የተገባለት ኪዳን እንደተፈጸመ አዳምና ልጆቹ ነጻ እንደወጣን እናስባለን፡፡

#አርብ- ቅድስት ቤተክርስቲያን ይባላል፡-
በዚህ ዕለት ቤተክርስቲያን በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ስለመመስረቷ ይሰበካል፡፡ ክርስቶስ ስለ እርሷ ራሱን አሳልፎ ሰጥቶ ቤዛ ሆኖ በደሙ አንጽቶ በትንሣኤው ድል ሰጥቶ እንዳከበራት ይነገራል፡፡ ቤተክርስቲያን ስንል ሕንፃውን ሳይሆን አማኞችን ነው፤ ክርስቶስ ለሕንፃ አልሞተምና፡፡

#ቅዳሜ- ቅዱሳት አንስት ይባላል፡-
በዚህ ዕለት ቅዱሳት አንስት የክርስቶስን አካል ሽቶ ለመቀባት ጨለማ አቋርጠው ወደ መቃብር መምጣታቸውና ትንሣኤውንም ቀድመው ማየታቸው ይሰበካል፡፡

#እሁድ- ዳግም ትንሳኤ ይባላል፡-
በዚህ ዕለት ክርስቶስ ለሦስተኛ ጊዜ ለደቀመዛሙርቱ ተገልጦ ሰላምን መስበኩ እና ሥልጣንን መስጠቱ ይሰበካል፡፡
አይናችን ነሽ ማርያም አንቺን አይንኩብን
የተዋህዶ ልጆች እንወድሻለን
ግቢ ከቤታቸን በረከታችን ነሽ
በሀሴት ቆመናል ደስታን ስለወለድሽ
ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ
(ሚያዝያ 23 እረፍቱ ለቅዱስ ጊዮርጊስ)

ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ በጥር 20 ቀን በ277 ዓ.ም ተወለደ። ሀገሩ ፍልስጤም ሲሆን ልዩ ስሟ ልዳ ይባላል። ጊዮርጊስ ማለት ኮከብ፣ ብሩህ፣ ሐረገወይን፣ ፀሐይ ማለት ነው። አባቱ ዞሮንቶስ የተባለ የልዳ መኳንንት እናቱ ቴዎብስታ ትባላለች። ማርታና እስያ የሚባሉ እህቶች ነበሩት። 10 ዓመት ሲሞላው አባቱ ስለሞተ ሌላ ደግ ክርስቲያናዊ መስፍን ከቤቱ ወስዶ አሳደገው። በጦር ኃይልም አሠለጠነው። ሃያ አመት ሲሞላው መስፍኑ የ15 ዓመት ቆንጆ ልጅ ነበረችውና እርሷን አግብቶ ሀብቴን ወርሶ ይኑር ብሎ ድግስ ሲያስደግስ ጌታ ቅዱስ ጊዮርጊስን ለዚህ አላጨውምና የመስፍኑን ነፍስ ወሰደ። እርሱም ኀዘኑን ጨርሶ ወደ ቤሩት ሄደ።

በቤሩት ደራጎንን ያመልኩና ሴት ልጃቸውን ይገብሩለት ነበርና በኃይለ መስቀል ድል ነስቶት ህዝቡን ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር አስገብቷቸዋል። ወደፋርስ ቢመለስ ዱድያኖስ ሰባ ነገሥታት ሰብስቦ ሰባ ጣዖታት አቁሞ ሲሰግድ ሲያሰግድ ቢያገኛቸው ለሃይማኖቱ ቀናዒ ነውና ከቤተመንግስቱ ገብቶ “እኔ ክርስቲያን ነኝ በኢየሱስ ክርስቶስ አምናለሁ” አለው። እርሱም ማንነቱን ከተረዳ በኋላ “አንተማ የኛ ነህ በ10 አህጉር ላይ እሾምሃለሁ የኔን አምላክ አጵሎንን አምልክ” አለው። ቅዱስ ጊዮርጊስም “ሹመት ሽልማትህ ለአንተ ይሁን እኔ አምላኬ ኢየሱስ ክርስቶስን አልክድም” አለ። በዚህ ጊዜ እጅግ ተናዶ መከራን አጸናበት እርሱ ግን “ይህን ከሀዲ እስካሳፍረው ድረስ ነፍሴን አትውሰድ”በማለት እግዚአብሔርን የለመነና እንደጸሎቱ የተደረገለት። በእምነቱም ጽናት የሰው ልጅ ሊሸከም የማይችለውን መከራ የተቀበለ ቅዱስ አባት ነው።
ከእነዚህም መከራዎች ውስጥ፡-

1. በእንጨት አስቀቅሎ ሥጋውን በመቃን አስፈተተው፣ ረጃጅም ችንካሮች ያሉበት የብረት ጫማ አጫምቶት ሂድ አለው። ቅዱስ ሚካኤልን ልኮለት ፈውሶታል። በሰባ (70) ችንካር አስቸንክሮ በእሳት አስተኩሶ አናቱን በመዶሻ አስቀጥቅጦ በሆዱ ላይ የደንጊያ ምሰሶ አሳስሮ እንዲያንከባልሉት አደረገ። ሥጋውን በመጋዝ አስተልትሎ ጨው ነስንሶበት ሥጋው ተቆራርጦ ወደቀ። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመንፈቀ ሌሊት በእጁ ዳስሶ “ገና 6 ዓመት ለስሜ ትጋደላለህ፣ 3 ጊዜ ትሞታለህ፣ በ4ኛው ታርፋለህ።” አለው።

2. ዱድያኖስ ደንግጦ “የሚያሸንፍልኝ ቢኖር ወርቅ እሰጠዋለሁ” ቢል አትናስዮስ የተባለ መሰርይ ከንጉሱ ላምን በጆሮዋ ሲያንሾካሹክባት ለሁለት ተሰንጥቃ ገድሏት ፈቃድን ተቀበለ። ሆድ በጥብጦ አንጀት ቆራርጦ የሚገድል መርዝ ቀምሞ አስማተ ሰይጣን ደግሞ ሰጠው። ቅዱስ ጊዮርጊስ ግን ስመ እግዚአብሔርን ጠርቶ ቢጠጣው እንደ ጨረቃ ደምቆ እንደ አበባ አሸብርቆ ተገኝቷል። ጠንቋዩም ማረኝ ብሎት ከእግሩ ወደቀ። መመለሱን አይቶ የቆመባትን መሬት በእግሩ ረግጦ ውሃን አፍልቆ ወደ ጌታችን ቢያመለክት ሐዋርያው ቶማስ በመንፈስ መጥቶ አጥምቆት ጥር 23 ቀን አንገቱን ለሰይፍ ሰጥቶ በሰማዕትነት አርፏል። እሱን ግን በመንኮራኩር አስፈጭቶ ከትልቅ ጉድጓድ ጥሎት ደንጊያ ዘግቶበት አትሞበት ሄዷል። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተፈጨውን ሥጋ በእጁ ዳስሶ መንፈሱን መልሶ አንስቶታል፤ ተመልሶም “አምላኬ ከሞት አዳነኝ” ብሏቸዋል።

3. በብረት አልጋ አስቸንክሮ ከበታቹ እሳት አንድዶበታል። እሳቱም ደሙ ሲንጠባጠብ ጠፍቷል። ዱድያኖስ “ኢየሱስ አምላክ መሆኑን አሳየኝ” ቢለው የለመለሙትን ዕፅ አድርቆ፣ የደረቁትን አለምልሞ፣ ከሞቱ 430 ዓመት የሆናቸውን ሙታንን አስነስሰቶ አሳይቶታል። ነገር ግን ልቡ ክፉ ነውና በረሀብና በጽም ይሙት ብሎ ምንም ከሌላት መበለት ቤት አሳስሮታል። እርሷም የሚቀመስ ስትፈልግ ቤቷን በእህል አትረፍርፎ የታሰረበት ግንድ አፍርቶ ልጇ ጆሮው የማይሰማ ነበርና ፈውሶላት መበለቲቷን ከነልጆቿ አጥምቆ ቅዱስ ሚካኤል ከእስራቱ ፈትቶት ተመልሷል። ዳግም በመንኩራኩር ፈጭታችሁ ደብረ ይድራስ ወስዳችሁ ዝሩት ብሎ አስፈጭቶ ሥጋውን ቢዘሩት ሥጋው ያረፈበት ሳር፣ ቅጠሉ፣ ደንጊያው፣ እንጨቱ ሁሉ “ጊዮርጊስ ቅዱሱ ለእግዚአብሔር፣ ጊዮርጊስ ሰማዕቱ ለእግዚአብሔር፣” እያሉ አመስግነዋል። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ለሦስተኛ ጊዜ ከሞት አስነስቶታል። ሔዶም “አምላኬ ከሞት አዳነኝ” አላቸው። ጭፍሮቹ ደንግጸው ከእግሩ ስር ወደቁ። ከመሬት ውሃ አመንጭቶ ቅዱስ ዮሐንስ አጥምቋቸዋል።

4. “ንጉሡ ልሹምህ ለአጵሎን ስገድ” ብሎ ቢለምነው እሺ ብሎ ገብቶ ሲጸልይ የንጉሱ ሚስት እለእስክንድርያ “ምን እያልክ ነው?” ብትለው አስተምሯት አሳምኗታል። ሲነጋ ንጉሱ በአዋጅ ህዝብን አሰብስቦ “ጊዮርጊስ ለጣዖቴ ሊሰግድ ነው’ ብሎ በተሰበሰበ ህዝብ መካከል አንድን ብላቴና (የመበለቷን ልጅ) “የክርስቶስ ኢየሱስ አገልጋይ ጊዮርጊስ ይጠራሃል” በል ብሎ ወደጣዖቱ ቢልከው ጣዖቱ ላይ ያደረው ሰይጣን እየጮኸ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያለበት ቦታ መጣ፤ አምላክ አለመሆኑን አናዞት መሬት ተከፍታ እንድትውጠው አደረገ። ብዙ ሰዎች ይህንን ተዓምር አይተው አመኑ። ንጉሱን ሚስቱ እንዲመለስ ብትነግረው በአደባባይ አሰቅሎ አሰይፏት ሞታለች ደሟን ጥምቀት አድርጎላት ሰማዕት ሆናለች። በመጨረሻም በሰይፍ እንዲመተር አስደረገ። ቅዱስ ጊዮርጊስም ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቃልኪዳን ተገብቶለት በ27 ዓመቱ በሚያዝያ 23 ሰማዕት ሆኗል። አንገቱ ሲቆረጥም ውሃ፣ ደም እና ወተት ወጥቷል።

ከሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ረድኤት በረከት ይክፈለን!!!

(ገድለ ቅዱስ ጊዮርጊስ)
“ማግባት ለሚሹ” የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ምክር

ከምንም በፊት የጋብቻ ዓላማን ማወቅ አለባችሁ፡፡ በሕይወታችን ለምን ጋብቻ እንደሚያስፈልገን መረዳት አለባችሁ፡፡ ከዚህ ውጪ ሌላ ነገርን አትጠይቁ፡፡ እናስ የጋብቻ ዓላማው ምንድነው? ለምንድነው እግዚአብሔር ጋብቻን የሰጠን? ብጹዕ ጳውሎስን እናድምጠው፤ እንዲህ ያለውን፦ "ስለ ዝሙት ጠንቅ ለእያንዳንዱ ለራሱ ሚስት ትኑሮው፤ ለእያንዳንዲቱ ደግሞ ለራሷ ባል ይኑራት" (1ኛ ቆሮ.7፥2)። "ከድህነት ይወጣ (ትወጣ) ዘንድ" ነው የሚለውን? ወይስ "ሀብት ለማግኘት ሲባል" ነው የሚለውን? አይደለም፡፡ ታዲያ ምንድነው የሚለው? ከዝሙት እንጠበቅ ዘንድ፤ ራሳችንን መቆጣጠር እንችል ዘንድ፤ ንጽህናን ገንዘብ እናደርግ ዘንድ፤ በትዳር አጋራችን ደስ ተሰኝተን እግዚአብሔርን እናመሰግን ዘንድ፡፡ አያችሁ ይኼ ነው የጋብቻ ስጦታው ይኼ ነው የጋብቻ ፍሬው፤ ይኼ ነው የጋብቻ ጥቅሙ፡፡

ስለዚህ ልጆቼ! እማልዳችኋለሁ ትልቁን ጥቅም ዘንግታችሁት ዓይናችሁን በትንሹ ላይ አታሳርፉ፡፡ የትዳር አጋርን ስትመርጡ የሀብት ጉዳይ የእናንተ ትልቅ አጀንዳ ሊኾን አይገባም፡፡ ስለ ሀብት ብሎ የትዳር አጋርን መምረጥ ድንቁርና ነው፤ ሀብት ነገ ሊጠፋ ይችላልና፡፡ ስለዚህ ለትዳር የምትመርጡት ሰው ከምንም በላይ መንፈሳዊ ሀብቱን ተመልከቱ፡፡ በዚህም ዓለም በወዲያኛውም ዓለም ይበልጥ የሚጠቅማችሁ ይኼ ነውና፡፡

አባቶች ሆይ! አብርሃምን ምሰሉት፡፡ አብርሃም ለልጁ ለይስሐቅ ሚስትን ሲፈልግለት፦ ሀብትን አላየም፤ የንጉሣውያን ቤተሰብን አልተመለከተም፤ አፍአዊ ውበትን መመዘኛ አላደረገም፤ ወይም ይህን የመሰለ ሌላ መስፈርትን አልደረደረም፡፡ የነፍስ ንጽህናን እንጂ፡፡

እናቶች ሆይ! ሴት ልጆቻችሁን እንደ ርብቃ አሳድግዋቸው፡፡

እናንተ ማግባትን የምትሹ ወጣቶች ሆይ! ይስሐቅን ምሰሉት፦ ዘፈንን፣ ዳንኪራን፣ ሳቅና ስላቅን፣ የከበሮንና የዋሽንት ጫጫታን፣ ሌላውንም የዲያብሎስ ትርኢት በሰርጋችሁ ቀን አታስቡ፡፡ ከዚህ ይልቅ በምታደርጉት ኹሉም ላይ እግዚአብሔር እንዲቀድማችሁ ለምኑት፡፡ ይህን ያደረጋችሁ እንደኾነ ትዳራችሁ ፍቺ፣ ዝሙት፣ ቅናት፣ ጭቅጭቅ፣ ንትርክ የሌለበት ኾኖ ይፀናላችኋል፡፡ ይህን ያደረጋችሁ እንደኾነ፥ ሌላው በረከትም ተትረፍርፎ ይመጣላችኋል፡፡ የአውሎ ነፋስ ዓይነት በዙሪያችሁ ቢነፍስም፥ አትነዋወፁም፡፡

እናንተ ልጃገረዶች ሆይ! ርብቃን ምሰሏት፡፡ የትዳር አጋራችሁን ፍጹም ለማፍቀር የተዘጋጃችሁ ኹኑ፡፡ ይህን ያደረጋችሁ እንደኾነ ቤታችሁ ፍጹም ሰላማዊ ባሎቻችሁ የምትልዋቸውን የሚያደርጉና በፍቅራችሁ የሚንበረከኩ ይኾናሉ፡፡ ትዳር እንዲህ ኾኖ ሲጀመር፥ እግዚአብሔርንና ወላጆቹን ደስ የሚያሰኝ ልጅ ይገኝበታል፡፡

የቤት ዕቃዎችን መግዛት ስንፈልግ፥ በጣም እንጠነቀቃለን፡፡ የሻጮቹን ማንነት አይተን፣ የዕቃዉንም ጥንካሬ አገላብጠን ተመልክተን ነው የምንሸምተው፡፡ ሚስት ስናገባም ከዚህ የበለጠ ልንጠነቀቅ ይገባናል፡፡ የገዛነው ዕቃ ችግር ቢኖርበት ለሸጠልን ሰው መመለስ እንችላለን፡፡ ሚስት ስናገባ ግን ወደ ቤተሰቦቿ መመለስ አንችልም፤ እስከ ዕድሜአችን ፍጻሜ ድረስ ከእኛ ጋር ነው የምትኾነው፡፡ ክፉ ናት ብለን ብንመልሳት፥ በሕገ እግዚአብሔር መሠረት አመንዝራ እንኾናለን፡፡ ስለዚህ፥ ሚስት ስትመርጡ የሀገራችሁን ሕገ መንግሥትን ብቻ አታንብቡ፤ ከኹሉም በፊት ሕገ ቤተ ክርስቲያንን አንብቡ እንጂ፡፡

(የተደገመ)
#እናንተ_ማግባትን_የምትሹ_ወጣቶች_ሆይ፦ ይስሐቅን ምሰሉት፦ ዘፈንን፣ ዳንኪራን፣ ሳቅና ስላቅን፣ የከበሮንና የዋሽንት ጫጫታን፣ ሌላውንም የዲያብሎስ ትርኢት በሰርጋችሁ ቀን አታስቡ፡፡ ከዚህ ይልቅ በምታደርጉት ኹሉም ላይ እግዚአብሔር እንዲቀድማችሁ ለምኑት፡፡ ይህን ያደረጋችሁ እንደኾነ ትዳራችሁ ፍቺ፣ ዝሙት፣ ቅናት፣ ጭቅጭቅ፣ ንትርክ የሌለበት ኾኖ ይፀናላችኋል፡፡ ይህን ያደረጋችሁ እንደኾነ፥ ሌላው በረከትም ተትረፍርፎ ይመጣላችኋል፡፡ የአውሎ ነፋስ ዓይነት በዙሪያችሁ ቢነፍስም፥ አትነዋወፁም፡፡

#እናንተ_ልጃገረዶች_ሆይ፦ርብቃን ምሰሏት፡፡ የትዳር አጋራችሁን ፍጹም ለማፍቀር የተዘጋጃችሁ ኹኑ፡፡ ይህን ያደረጋችሁ እንደኾነ ቤታችሁ ፍጹም ሰላማዊ ባሎቻችሁ የምትልዋቸውን የሚያደርጉና በፍቅራችሁ የሚንበረከኩ ይኾናሉ፡፡ ትዳር እንዲህ ኾኖ ሲጀመር፥ እግዚአብሔርንና ወላጆቹን ደስ የሚያሰኝ ልጅ ይገኝበታል፡፡

የቤት ዕቃዎችን መግዛት ስንፈልግ፥ በጣም እንጠነቀቃለን፡፡ የሻጮቹን ማንነት አይተን፣ የዕቃዉንም ጥንካሬ አገላብጠን ተመልክተን ነው የምንሸምተው፡፡ ሚስት ስናገባም ከዚህ የበለጠ ልንጠነቀቅ ይገባናል፡፡ የገዛነው ዕቃ ችግር ቢኖርበት ለሸጠልን ሰው መመለስ እንችላለን፡፡ ሚስት ስናገባ ግን ወደ ቤተሰቦቿ መመለስ አንችልም፤ እስከ ዕድሜአችን ፍጻሜ ድረስ ከእኛ ጋር ነው የምትኾነው፡፡ ክፉ ናት ብለን ብንመልሳት፥ በሕገ እግዚአብሔር መሠረት አመንዝራ እንኾናለን፡፡ ስለዚህ፥ ሚስት ስትመርጡ የሀገራችሁን ሕገ መንግሥትን ብቻ አታንብቡ፤ ከኹሉም በፊት ሕገ ቤተ ክርስቲያንን አንብቡ እንጂ።

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ

@beteafework @beteafework
@beteafework @beteafework
@beteafework @beteafework
ባሎች ለሚስቶቻቸው ሊያሳዩአቸው የሚገባ ፍቅር በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ

ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ እንደምትገዛ ሚስትህ ለአንተ ትገዛልህ ዘንድ ትሻለህን? ክርስቶስ ለቤተ ክርስቲያን እንዳደረገላት አንተም እንዲሁ ለሚስትህ አድርግላት፡፡ ሕይወትህን ስለ ርሷ አሳልፈህ መስጠት ካለብህ ስለርሷ ሕይወትህን አሳልፈህ ስጥ፤ መከራም መቀበል ካለብህ መከራን ለመቀበል አትሰቀቅ፡፡

አንተ ይህን ብትፈጽመው ስንኳ ክርስቶስ ለቤተ ክርስቲያን ካደረገላት ጋር ሲነጻጸር የሚወዳደር አይደለም፡፡ ምክንያቱም አንተ ይህን ያደረግኸው ከአንተ ጋር ፈጽማ ለተዛመደችህ ለአንዲት ሴት ነው፡፡ “እርሱ ግን ከእርሱ ለተመለሰችውና ለጠላቸው ራሱን አሳልፎ ሰጠ፡፡” ርሱ ከርሱ የተመለሰችውንና የጠላችውን እንዲሁም ያቃለለችውን ገንዘቡ ሲያደርጋት በማስፈራራት፣ በማስገደድ ወይም ይህን በመሳሰሉ ነገሮች አልነበረም፤ ነገር ግን ኀዘን ባልተቀላቀለበት ፍጹም በሆነ ፍቅር በመሆን ነበር፡፡ አንተም ለሚስትህ እንዲሁ አድርግላት አዎን! ምናልባት ሚስትህ አንተን ልታመናጭቅህ፣ ልትንቅህ፣ ልታፌዝብህም ትችላለች፤ ቢሆንም ግን አንተ ለርሷ ካለህ አርቆ አሳቢነት ንጹሕ ፍቅርና ኀዘኔታ የተነሣ ልትታገሣት ይገባሃል፡፡

ከሰው ሁሉ ጋር ተስማምቶ ለመኖርም ከእነዚህ የተሻሉ ነገሮች ፈጽሞ አናገኝም፡፡ በተለይም ለባልና ለሚስት፡፡ አንድ ሰው አገልጋይ ባሪያውን በማስፈራራት ለመግዛት ቢሞክር ለጥቂት ጊዜአት ሊገዛለት ይችላል፡፡ ሆኖም ይህ ባሪያ እንዲህ ዓይነት አገዛዝ ስለማይመቸው ከእርሱ ፈጥኖ ይሸሻል፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው የሕይወቱን አጋር፣ የልጆቹን እናት፣ የደስታው ሁሉ ምንጭ የሆነችውን ሚስቱን በፍቅርና በፍጹም አክብሮት እንጂ ልክ እንደ ባሪያ በፍርሃት ሰንሰለት በማሰር ወይም በማስጨነቅ ርሷን ሊገዛት መሞከር አይገባውም፤ ሚስት በባልዋ ምክንያት የምትሸበር ከሆነ አንድነታቸው ምን ዓይነት አንድነት ነው? ከባሪያ ጋር እንደ መኖር ከሚስት ጋር መቀመጥ ለባል የሚፈጥርለት ምን ዓይነት ደስታ ነው? አዎን ይልቁኑ አንተ ስለ ርሷ ስትል ብዙ መከራዎችን መቀበል ሲገባህ በተቃራኒው በቁጣ ርሷን በማስጨነቅና በማሸበር ታስፈራራታለህን? ክርስቶስ እንዲህ አላደረገም፡፡

“በውኃ መታጠብና ከቃሉ ጋር አንጽቶ አንዲቀድሳት ስለ ርሷ (ስለ ቤተ ክርስቲያን) ራሱን አሳልፎ ሰጠ ፡፡ ከቃሉ እንደምንረዳው ቤተ ክርስቲያን (እኛ) አስቀድማ ንጽሕት አልነበረችም፤ ጉድፍ ነበረባት፤ መልከ ጥፉም ነበረች፡፡ ስለዚህም ለእርሱ የተገባች አልነበረችም፡፡ አንተ እንደ ቤተ ክርስቲያን የሆነችውን ሴት ሚስትህ ትሆን ዘንድ አትመርጥም፡፡ ቤተ ክርስቲያን ከክርስቶስ የተለየችውን ያህል ከአንተ ፈጽማ የማትስማማውን ሴት ሚስትህ ትሆን ዘንድ ወደ አንተ አታቀርባትም፡፡ እርሱ ግን እጅግ መልከ ጥፉ ብትሆንም አልጠላትም፣ አልተጸየፋትም፣ ስለ መልከ ጥፉነቷ የተጻፈውን መስማት ትፈልጋለህን? ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ርሷ ምን እንደሚል ስማ “ቀድሞ ጨለማ ነበራችሁ” (ኤፌ.፭፡፰) አላት፤ የገጽታዋን መጥቆር ትመለከታለህን? ከጨለማስ የበረታ ጥቁረት ምን አለ? የአመሏን መክፋት ደግሞ ስማ “በክፋትና በምቀኝነት” ይልና “የምንኖር” ይላል፤ ስለ ነውሮቿ ደግሞ “የማንታዘዝና የምንስት ለልዩ ልዩ ተድላ እንደ ባሪያዎች የምንገዛ” ይላታል (ቲቶ.፫፡፫)፡፡

ነገር ግን ለርሷ ስለተደረገላት በጎነት ምን ማለት ይቻለኛል? ርሷ ስንፍናን የተሞላችና ክፉ አንደበት የነበራት እንዲሁም በነውሮቿ ሁሉ ያደፈች ብትሆንም እነዚህ ሁሉ ጠባዮቿ ከርሷ አላራቀውም፡፡ ነገር ግን ልክ የደስ ደስ እንዳላት ልጃገረድ በአፍቀሪም ዘንድ ለምትወደድ ውብ ሴት እንደሚደረገው ርሱ ስለ ርሷ ራሱን አሳልፎ የሰጠ አይደለምን? ይህንንም በማድነቅ ቅዱስ ጳውሎስ “ስለጽድቅ የሚሞት በጭንቅ ይገኛልና ስለ ቸር ሰው ግን ሊሞት ስንኳ የሚደፍር ምናልባት ይገኛል” ይልና “ነገር ግን ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቷልና”(ሮሜ.፭፡፯-፰) ብሎአል፡፡ በዚህ መልክ ርሷ ለርሱ ትሆን ዘንድ አቀረባት፤ በመንፈሳዊ ውበትም አስጌጣት፤ ንጽሕት አደረጋት፤ ስለ ርሷም ራሱን አሳልፎ ለመስጠት ስንኳ የጨከነ ሆነ፡፡

(የትዳር አንድምታ እንደ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ አስተምህሮ ገጽ 17-19 - በመምህር ሽመልስ መርጊያ)