Amhara Education Bureau
18.9K subscribers
4.16K photos
8 videos
236 files
429 links
Quality Education
Download Telegram
ከድህነት ቅርቃር ለመውጣት ትምህርት ላይ መስራት ይገባል ተባለ!!
።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።
የአብክመ ትምህርት ቢሮ ከጎንደር ቀጠና የትምህርት አመራሮችና የትምህርት ባለድርሻ አካላት ጋር የ2016ዓ.ም የትምህርት ስራዎች አፈፃፀም የምክክር መድረክ እያካሄደ ነው። ታህሳስ 20/2016-ጎንደር
የአብክመ ትምህርት ቢሮ ከጎንደር ቀጠና የትምህርት አመራሮችና የትምህርት ባለድርሻ አካላት ጋር የ2016ዓ.ም የትምህርት ስራዎች አፈፃፀም የምክክር መድረክ እያካሄደ ሲሆን በምክክር መድረኩ መክፈቻ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የትምህርት ቢሮ ም/ሃላፊ ወ/ሮ እየሩስ መንግስቱ ትምህርት ራስን፣ አካባቢን ፣አገርንና አለምን እንዲሁም በአለም ውስጥ ያሉ ተፈጥሯዊና ሠው ሠራሽ ነገሮችን የምንመለከትበትን የእይታ አድማስ ያሰፋል ብለዋል። ትምህርት ከማህበራዊ አገልግሎቱ በተጨማሪ ለኢኮኖሚ እድገትና ብልፅግና ቁልፍ መሳሪያ ነው ያሉት ምክትል ሃላፊዋ ዛሬ በሳይንሰና ቴክኖሎጅ የበለፀጉት ሀገራት የእድገት ሚስጥራቸው ጥራት ያለው ትምህርት ለዜጎቻቸው መስጠታቸው መሆኑን አስረድተዋል። በዚህም ምክንያት ከድህነትና ሃላቀርነት መላቀቅ ችለዋል ያሉት ወ/ሮ እየሩስ ከድህነት ቅርቃር ለመውጣት ትምህርት ላይ መስራት ይገባል ሲሉ አፅንኦት ሰጥተዋል። የትምህርት ስራችን ወደ ኋላ እንዲጓተት ማደናቀፍና አለመስራት ከድህነትና ኋላ ቀርነት ጋር ለመኖር እንደመወሰን ይቆጠራል። በመሆኑም ለመደበኛው ትምህርት፣ የጎልማሶች ትምህርት፣ የቅድመ አንደኛ ደረጃ፣ ለትምህርት ቤቶች ደረጃ በሚረዱ ጉዳዮች ፣ የተፋጠነ ትምህርትና ሌሎች ፕሮግራሞችንም ትኩረት አድርጎ መፈፀም እንደሚገባ ሃላፊዋ አሳስበዋል።
የምክክር መድረኩ እስከ ታህሳስ 21/2016 የሚቀጥል ሲሆን በምክክር መድረኩ የዞን ትምህርት አመራሮችና ባለሙያዎች፣ የወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ሃላፊዎችና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ይገኛል።
ብዝኃነትን መኖር በሚል መሪ ሐሳብ የአብሮነት ቀን ለስድስት ቀናት መከበር ጀምሯል።
..................................................

ታህሳስ 20/2016 ዓ.ም (ትምህርት ሚኒስቴር) እ.አ.አ. በ1995 የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት ፦ ዩኔስኮ ኅዳር 6 ቀንን ዓለም አቀፍ የአብሮነት (Tolerance) ቀን እንዲኾን ዐውጇል፡፡

የቀኑ መታወጅ ዓላማ በኅብረተሰቡ ውስጥ የአብሮነትን ጥቅም ግንዛቤ ለመፍጠርና መቻቻል ያለዉን ፋይዳ ማስገንዘብ ነው፡፡

በኢትዮጵያም ብዝኃነትን የሚያከብር፣ አብሮነትን ገንዘብ ያደረገ፣ ኃላፊነት የሚሰማዉ ትውልድ ለማፍራት የተጀመረዉን ጥረት ለማገዝ፣ ማኅበራዊ ዕሴቶቻችንን ለማሳደግና ለለውጥ ዝግጁ ዜጋና ኅብረተሰብ ለመፍጠር ተቻችሎ መኖር አንዱ ለአንዱ አስፈላጊዉ አንደኾነ ማመንን ለማስረጽና ግንዛቤ ለማሳደግ ቀኑ ይከበራል፡፡

ዘንድሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ26ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ለ14ኛ ጊዜ የሚከበረዉ ዓለም አቀፉ የአብሮነት ቀን "ብዝኃነትን መኖር!" በሚል መሪ ሐሳብ ከታኅሣሥ 20-25 ቀን 2016 ዓ.ም እየተከበረ ይገኛል።

የአብሮነት ሳምንቱ በልዩ ልዩ ኹነቶች እንደሚከበር ከመርሐ ግብሩ መረዳት ተችሏል።

የበዓሉን አከባበር ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ከተለያዩ የፌዴራል ተቋማትና ከሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር በመኾን ያስተባብራል።

MOE
የመደበኛ ተማሪወች መግቢያ ጥሪ ማስታወቂያ፤

ለደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የ2016 ዓ.ም. ነባር መደበኛ ተማሪወች፤

ምዝገባ ጥር 2 እና ጥር 3 ቀን 2016 ዓ.ም.
፨፨፨

To All Senior Regular Students at Debre Tabor University;

Registration Dates is on JANUARY 11-12/2024
ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ፣ ለክልላችን መምህራን፣ ተማሪዎች፣ የትምህርት አመራሮች፣ የትምህርት ባለሙያዎች፣ የትምህርት ማህበረሰብ፤
እንኳን ለጌታችን መድሃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም፣ በፍቅር፣ በደስታ አደረሳችሁ እያልኩ፤

የአብክመ ትምህርት ቢሮ በክልሉ ትምህርትና ሥልጠናን በስፋት፣ በጥራትና በፍትሀዊነት በማዳረስ፣ የሕብረተሰቡን አመራር ተሣትፎ ባረጋገጠ አደረጃጀት ተነሳሽነቱ የጐለበተ፣ በመብቱ የሚጠቀም፣ ግዴታውን የሚወጣ፣ ምርታማነቱ የዳበረ፣ ለአጠቃላይ ልማት መምጣት ምክንያት የሚሆን ሰብአዊ ሀብት ማፍራት ተልዕኮ ይዞ በትጋትና ቁርጠኝነት እየሰራ ያለ ተቋም ነው፡፡
ተቋሙ ይዞት የተነሳውን ተልዕኮ በማሳካትም ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህፃናት የትምህርት እድል እንዲያገኙ፣ ጥራት ያለው ትምህርትን በማቅረብ፣ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል ትምህርት ለትውልድ ንቅናቄን በማስቀጠል፣ የትምህርት ግብዓቶችን በማቅረብ በተለይም በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት የታተሙ መፅሐፍት ስርጭት ስራዎችን በመስራት፣ የተማሪዎችን ውጤታማነት ማሳደግ ላይ ትኩረት አድርገን እየሰራን እንገኛለን።
አሁን ላይ በክልላችን የተፈጠረውን ሰላም በመጠቀም የትምህርት ስራዎችን ከወትሮው በተለየ መንፈስና ብርታት መፈፀም የሁላችንም ሃላፊነት ነው። ትምህርት ማህበራዊ ዘርፍ እንደመሆኑ ለስኬቱ ሁላችንም ተደጋግፈን መስራት ይገባል። መምህራን ለተማሪዎች መማርና ውጤታማነት ተኪ የላቸውም። የትምህርት አመራሩ የትምህርት ስራዎችን በመምራትና ማህበረሰቡን በማስተባበር ትምህርት ቤቶች ትውልድ መገንቢያ ተቋማት እንዲሆኑ የመሪነት ሚናቸውን መወጣት አለባቸው። በመሆኑም በዓሉን ስናከብር የአብሮነት እሴቶቻችንን በማጎልበት፣ በፍቅር፣ አቅም ለሌላቸው ዜጎች ካለን በማካፈልና በመደጋገፍ እንድናሳልፍ በእኔ እና በትምህርት ማህበረሰቡ ስም ጥሪየን አስተላልፋለሁ!
ሙሉነሽ ደሴ(ዶ/ር)
በም/ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ሃላፊ

መልካም በዓል!!
በኮምቦልቻ ከተማ ከ90 ሚሊየን ብር በላይ ወጭ የተደረገባቸው የትምህርት ተቋማት ተመረቁ(ጥር 19/2016_ኮምቦልቻ)
በምረቃ ፕሮግራሙ ላይ የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተሞች ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተማ እና መሰረተ ልማት  ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) ጨምሮ የክልልና የዞን የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን በምረቃ ፕሮግራሙ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ትምህርት ለሀገር እድገትና ሁለንናዊ ልማት መሠረት ነው። የትምህርት መሠረትነቱ የሚረጋገጠው ሀገርን በሁለንተናዊ ሁኔታ ለማሳደግ የሚረዳው የሰው ሀይል የሚለማው በትምህርት ተቋማት በመሆኑ ነው ብለዋል። የትምህርት ተቋማት ጤንነቱ የተጠበቀ፣ በምክንያት የሚያምን፣ ችግሮች ሲገጥሙ በንግግርና ውይይት የሚያምን ዜጋ በመፍጠር ረገድ ሚናቸው ትልቅ ነው ብለዋል። ዜጎች በመከባበር፣ በመነጋገር፣ በፍቅርና አንድነት እንዲኖሩ ይህንንም እሴት አበልፅገውና ባህላቸው አድርገው እንዲኖሩ ለማስቻል ትምህርት ቤቶች ትኩረት አድርገው ሊሰሩ ይገባል።
ስለሆነም የትምህርት ፋይዳው ዘርፈ ብዙ በመሆኑ ዛሬ ደረጃቸውን በጠበቁ ትምህርት ቤቶች  የሚማሩ ተማሪዎች ነገ ሀገራችንን ተረክበው የሚመሩ፣ በቴክኖሎጂ የመጠቀችና የላቀች ፣ሰላማዊ፣ ጠመንጃና ተኩስ የማይሰማባት ሀገር እንድትሆን የሚተጉ ህፃናትና ወጣቶች የሚወጡበት ተቋም ነው። መምህራን ለተማሪዎች ከሚያስተላልፉት እውቀት በተጨማሪ ስነምግባርና አብሮ የመኖር ባህል፣ መተሳሰብ፣ተማሪዎች ወገን ዘለል ትስስር፣አለማቀፋዊ እውቀት፣በቴክኖሎጅ የዳበሩ አድርጎ እንዲወጡ ማድረግ አለባቸው ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የትምህርት ተቋማት ከተገነቡ በሗላ የተሻለ ጥራት ያለው ትምህርት ለመስጠት እንዲቻል የትምህርት ግብዓት መፅሐፍትን ጨምሮ እንዲሟሉ ማድረግ እንደሚገባ አስረድተዋል። ሁሉንም የትምህርት ግብዓቶች በመንግስት አቅም ማሟላት ስለማይቻል የአካባቢው ማህበረሰብ፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ባለሀብቶች ከመንግስት ጋር በቅንጅት መስራት አለባቸው ያሉ ሲሆን ትምህርት ቤቶች ስለሰላም ትውልዱን ማስተማር፣ በትምህርት ቤቶች ውስጥም ሰላም እንዲሰፍን መስራት እንደሚገባ ገልፀዋል።
በከተማ አስተዳደሩ 6 ትምህርት ቤቶች ግንባታቸው ተጠናቆ የተመረቁ ሲሆን 3ቱ በትምህርት ሚኒስቴር የበጀት ድጋፍ፣ 2ቱ በክልሉ መልሶ መቋቋም ፈንድ ፅ/ቤት እንዲሁም አንድ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በክልሉ ትምህርት ቢሮ የበጀት ድጋፍ የተገነባ ነው።
ዘገባው የትምህርት ቢሮ ህዝብ ግንኙነት ነው
የመጀመሪያዉ “ትምህርት ቤት” ማን ነው?
ጥር 20 ቀን 2016 ዓ.ም

ሀገር ወዳድ፣ ሰው አክባሪ፣ የመልካም ስብዕና ባለቤት…የሆነ ዜጋ ለመፍጠር የመጀመሪያው “ትምህርት ቤት” ቤተሰብ እንደሆነ በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የፎክለር መምህር እና የሀዲስ ዓለማየሁ ባህል ጥናት ልማት ተቋም ዳይሬክተር መስፍን ፈቃዴ (ዶ/ር) ለበኲር ጋዜጣ ዘጋቢ በስልክ ተናግረዋል:: እንደ እርሳቸው ማብራሪያ ቤተሰብ በአንድ ቤት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ስብስብ ነው:: በዚህ ተቋም ሕጻናት ደህንነት ተሰምቷቸው፣ ከፍርሀት ነፃ ሆነው እና የማወቅ ጉጉታቸውን በብቃት የሚጠበቅበት፣ የአዕምሮ ብስለት እና ማህበራዊ ክህሎታቸውን የሚያዳብሩበት የመጀመሪያው ትምህርት ቤት ነው::
አንድ ቤተሰብ በአብዛኛው በእናት እና በአባት እንዲሁም በልጆች ይመሠረታል:: ሆኖም ግን ሌሎች የቅርብ ዘመዶች አክስት፣ አጎት፣ አያት… ሊጨምር እንደሚችል መስፍን ፈቃዴ (ዶ/ር) አስረድተዋል። አክለውም ቤተሰብ ወላጆች ተለያይተው እናት ወይም አባት ለብቻ በአንድ ወላጅ እና በሌሎች ሊገነባ ይችላል:: አልፎ አልፎ ቤተሰብ ሁለቱም ወላጆች በሕይወት ከሌሉ በልጆች ብቻ አሊያም በሕጻናት ማሳደጊያ ተቋማት ውስጥ ሊመሰረት እንደሚችልም አስገንዝበዋል::
እንደ መስፍን ፈቃዴ (ዶ/ር) ማብራሪያ የቤተሰብ አባላት እርስ በርስ መልካም ግንኙነት፣ ግልፅነት፣ መተሳሰብ፣ መተባበር…ሲኖር ደስተኛ ያደርጋል። ወላጆች ለልጆቻቸው ፍቅር በመለገስ፣ በማበረታታት፣ ዘወትር ጤናቸውን በመጠበቅም መልካም ግንኙነት ሊረጋገጥ ይችላል።
መልካም ቤተሰብ ለማፍራት ወላጅ ልጆቹን ለማዳመጥም ሆነ ታሪክ ለመንገር በቂ ጊዜ ያለው፣ ልጆቹ ጥፋት ሲፈፅሙ ለማረም አካላዊ ጉዳት የሌለው ተገቢ ቅጣት እና ግሳጼ የሚያደርግ፣ ልጆችን በለጋ እድሜያቸው በጠንካራ አመራር እና ክትትል እንዲሁም በፍቅር የማይፈለግ ባህሪያት እንዲወገዱ የቤተሰብ መሪዎች ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርጉ እንደሆነ መስፍን ፈቃዴ (ዶ/ር) አስገንዝበዋል።
ልጆች ሲያድጉ ከመልካም ቤተሰብ የሚቀስሙት ልምድ ነገ ከነገ ወዲያ ቤተሰባቸውን ተክተው በጥሩ ማህበራዊ ሕይወት እና ሕግጋት ተመስርቶ እንዲመሩ ያስችላቸዋል። በዚህ ሂደት የሚመጡ ልጆች በራሳቸው የሚተማመኑ፣ ጠንካራ፣ ችግርን በራሳቸው የሚፈቱ እና ከጥገኝነት የራቁ እንደሚሆኑ ምሁሩ አብራርተዋል። ለመልካም ግንኙነት መፈጠር ቤተሰብ አብሮ የሚያሳልፍበት በቂ ጊዜ ሊኖረው እና ያለምንም ማዳላት ልጆችን መምራት እንደሚገባም መስፍን ፈቃዴ (ዶ/ር) መክረዋል።
ወላጆች (አሳዳጊዎች) ልጆች በራስ መተማመንን እንዲያዳብሩ እንዲሁም ስለቤተሰብ፣ ስለ ሀገር እና ስለ ዓለም እንዲገነዘቡ ዐይን ለዐይን እየተያዩ፣ እየደባበሱ እና እነሱ በሚረዱበት ሁኔታ ማውራት ጠንካራ ዜጋ መፍጠር እንደሆነ ምሁር ተናግረዋል።
ከሦስት ዓመት በታች ካሉ ልጆች ውጪ እንደየ አቅማቸው ቤት ውስጥ መታዘዝን በመልመድ እገዛ እያደረጉ ማሳየት፤ ከቤተሰቦቻቸው መደረግ ያለበትን እና የሌለበትን እያወቁ ካደጉ በተራቸው ቤተሰብ ሲመሰርቱ በሚኖራቸው መስተጋብር የራሳቸውን ሚና ሳይቸገሩ መወጣት እንደሚችሉም ምሁሩ አስረድተዋል።
መስፍን ፈቃዴ ( ዶ/ር )እንደሚሉት ቤተሰብ ሕጻናት የመጭው ዓለም ወሳኝ አካል መሆናቸውን እያንዳንዱ አሳዳጊ መገንዘብ መቻል አለበት። ቤተሰብ ልጆች ዓለምንም ሆነ አካባቢያቸውን የሚገነዘቡበት ወቅት በመሆኑ ጭቅጭቅ ቢኖር እንኳን ከእነርሱ ፊት መሆን የለበትም:: ምክንያቱ ደግሞ ጭቅጭቅ እና ድብድብ የልጆችን ሥነ ልቦና ስለሚጎዳ ወላጅ ለሚያደርገው ነገር እና ለሚያሳየው ባህሪ መጠንቀቅ መቻል አለበት፤ ለምሳሌ ሲጋራ የሚያጨስ አባት ልጆቹ ፊት ካጨሰ ድርጊቱ አባት ስላደረገው ትክክለኛ እንደሆነ እያሳመነ ነው።
እንደ ምሁሩ ገለጻ በዓለም በመጥፎ ድርጊታቸው የሚታወቁ ሰዎች ወደ ኋላ አስተዳደጋቸው ሲመረመር በቤተሰባቸው ውስጥ መጥፎ ጠባሳ ያለባቸው ስለመሆናቸው ተረጋግጧል:: ይሄ የሚያመለክተው መጥፎ አስተዳደግ ለራስም፣ ለሀገርም፣ ለዓለምም የማይጠቅም መሆኑን ነው:: ስለሆነም ወላጆች ከልጆች ጋር በአግባቡ ተነጋግረው መተማመንን መፍጠር የነገ መገለጫ ይሆናቸዋልና።
ቤተሰብ ትልቁ ኃላፊነት ልጆችን ሲያሳድግ ፍቅር መስጠት፤ ልጆች “ሁሉም ነገር ይገባኛል! ሲሉ ከነሱ እድሜ፣ ደረጃ እና ሥነ ልቦና ጋር እንዲሁም ከቤተሰቤ ሁኔታ አንፃር እንዲገነዘቡ ማድረግ እንዳለባቸው መስፍን ፈቃዴ ( ዶ/ር ) አስገንዝበዋል::
ቀድሞ እና አሁን ስላለው የልጅ አስተዳደግ ምሁሩ ሲያብራሩ፤ ቀድሞ የነበረው የልጅ አስተዳደግ በአመዛኙ በቤት ውስጥ ከልክ ያለፈ አዛዥ እና ታዛዥነትን እንዲያውቁ፣ ሰው ፊት እንዳይቀርቡ የሚያስገድድ በመሆኑ በራሳቸው የማይተማመኑ ያደርጋል:: በሌላ በኩል ደግሞ መጥፎ ድርጊት ሲፈፀም የታየ ልጅ ጎረቤትም ቢሆን ስለሚቆጣ ማህበረሰቡን የማክበር ሁኔታ ነበር። በአሁኑ ወቅት ግን የምን አገባኝ መንፈስ ስላለ በአብዛኛው ልጆች ማንንም አይፈሩም፤ አያከብሩም።
እናም መልካም ቤተሰብ፣ በሥነ ምግባር የታነጸ ዜጋ ለማፍራት የቤተሰብ ግንባታ ግንኙነት የሚጀምረው ልጆች ከጨቅላ እድሜያቸው ጀምሮ በመሆኑ የቤተሰብ መሪዎች ከልጆች ጋር ፊት ለፊት በመነጋገር፣ ከቤት ውጭ አብሮ በመንቀሳቀስ፣ ቤተሰብን፣ ወላጅን፣ አካባቢን እና ሀገርን መውደድ እንዳለባቸው ማስተማር ይጠበቅባቸዋል::
አሁን የሚታየው “ልጆቼን ማንም አይነካቸውም!” የሚለው አስተሳሰብ በስፋት ይስተዋላል:: ለአብነት ልጆች የአመጋገብ ሥርዓት እንዳያውቁ በስልክ ምግብ እንዲመገቡ የማድረግ ችግር አለ። ስለዚህ ለእያንዳንዱ ተግባር ሥርዓት እና ደንብ ሊኖር እንደሚገባ ቤተሰብ ማስተማር እንዳለበት ምሁሩ አስገንዝበዋል:: ይህን ተከትሎም ልጆችን በጣም ልቅ አድርጎ ማሳደግ ወደ ፊት በራሳቸው እንዳይተማመኑ፣ ሠርተው ገንዘብ የማያመጡ፣ የወላጆችን ልፋት የማይገነዘቡ ስለሚሆኑ ማስተካከል ያስፈልጋል። ጤናማ ቤተሰብ እና ጠንካራ ሀገር ለመገንባት ልጆችን በእድሜ፣ በኑሮ ደረጃ እና ከሀገር ባህል እና ወግ ጋር አቆራኝቶ ማሳደግ እንደሚገባ ምሁሩ አስገንዝበዋል::

(ማራኪ ሰውነት)
በኲር ጥር 20 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም
በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘወትር ሰኞ የምትታተመውን የበኲር ጋዜጣን ሙሉ ፒዲኤፍ
በhttp:// www.ameco.et/Bekur
በቴሌግራም - https://t.me/bekur123 ላይ ማግኘት ይችላሉ።
ተማሪዎችን ውጤታማ ሊያደርጉ የሚችሉ የአጠናን ዘዴዎች!!

1. የጥናት መርሃ ግብር ማዘጋጀት፡- የጥናት ጊዜን ቀድሞ ማቀድና እና በየቀኑ የሚዳሰሱ ጉዳዮችን ወይም ርዕሶችን ያካተተ መርሃ ግብር ማዘጋጀት። ይህም ተማሪው ለፈተና ዝግጁ ሆኖ እንዲቆይና እና ለእያንዳንዱ ርዕሰ ጉዳይ በቂ ጊዜ እንዲኖረው ይረዳል።

2. ከፋፍሎ ማጥናት፡- የሚጠናውን ይዘት ወደ ትናንሽ፣ ማስተዳደር በሚቻልባቸው ክፍሎች ማዘጋጀት። ይህ በአንድ ጊዜ በአንድ ፅንሰ-ሀሳብ ላይ ለማተኮር፣ በደንብ ለመረዳት እና ወደሚቀጥለው ይዘት ለሻገር ቀላል ያደርገዋል።

3. ንቁ የመማር ልምምድ ማዳበር :- መፅሐፋትን/ደብተራችንን በተለመደው ዘይቤ ከማንበብ ይልቅ ጥናታችንን ስንጨርስ ምን ያህል እንደተረዳን ትምህርቱን በራስ ቃላት ማጠቃለል፣ ለሌላ ሰው ማስተማር ወይም ያነበቡትን ለመፈተሽ ፍላሽ ካርዶችን በመፍጠር በዚያ ላይ መለማመድ፣

4. ኒሞኒክ ቁሳቁሶችን ፡- ማኒሞኒክስ ውስብስብ መረጃዎችን ለማስታወስ የሚረዱ የማስታወሻ መሳሪያዎች ናቸው። እውነታዎችን ወይም ጽንሰ-ሐሳቦችን ለማስታወስ ቀላል የሚያደርጉ አህጽሮተ ቃላትን፣ ግጥሞችን ወይም ምስላዊ ማህበራትን ሊያካትቱ ይችላሉ።

5. እረፍት መውሰድ:- ያለ እረፍት ለረጅም ጊዜ ማጥናት/ማንበብ ድካም ያመጣል። ትኩረታችንን ይቀንሳል። ለማረፍ፣ ለመዝናናት እና አእምሮን ለማደስ በየሰዓቱ አጭር እረፍቶችን መውሰድ አስፈላጊ ነው።

6. ያለፉ የፈተና ጥያቄዎች ወይም የናሙና ጥያቄዎችን መለማመድ:- ወይም ያለፉ የፈተና ጥያቄዎች ወይም የናሙና ጥያቄዎችን በመስራት ያነበቡትን ምን ያህል እንዳወቁ ራስን ለመፈተሽ ይረዳል።

7. ከአቻ የጥናት ቡድኖች ጋር በጋራ መስራት:-በጥናት ቡድኖች ውስጥ ከክፍል ጓደኞች ጋር መተባበር ጠቃሚ ሊሆን ይችላል, ይህም እርስ በርስ ለመወያየት እና ጽንሰ-ሀሳቦችን ለማስረዳት ያስችላል። ከጓደኞች ጋር ጥያቄዎችን መስራት፣መማማር ስለ ትምህርቱ ያለንን ግንዛቤ ያሳድጋል።

8. በቂ እንቅልፍ እና ተመጣጣኝ ምግብ መውሰድ:- በቂ እንቅልፍ ለትውስታ ማጠናከሪያ እና የእውቀት (ኮግኒቲቭ) ተግባር ወሳኝ ነው። በቂ እረፍት ማግኘትና የተመጣጠነ ምግቦችን መመገብ እና አእምሮዎን እና ሰውነትን በጥሩ ሁኔታ መጠበቅ እንዲሁም አዘውትረው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ለጥናት አስፈላጊ ነው።

9. አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ግልፅ ያልሀሆኑ ጉዳዮችን መጠየቅ:- በምናነብበት ወቅት ግልፅ ያልሆኑ ነገሮች ከገጠሙን ከመምህራን፣ ከክፍል ጓደኞች ወይም ከኦንላይን መርጃዎች እርዳታ ለመጠየቅ ወደኋላ አትበል። ተጨማሪ ማብራሪያዎችን እና ድጋፍን ሊሰጡ የሚችሉ በርካታ ትምህርታዊ ድረገጾች፣ መድረኮች እና አጋዥ ስልጠናዎች አሁን ላይ በስፋት ይገኛሉ።

10. አዎንታዊ መሆን እና ጭንቀትን መቆጣጠር፡- አዎንታዊ አስተሳሰብን መጠበቅ እና ጭንቀትን መቆጣጠር በፈተና ዝግጅት ወቅት አስፈላጊ ነው። እንደ ጥልቅ መተንፈስ ወይም ማሰላሰል ያሉ የመዝናኛ ዘዴዎችን መለማመድ እና ለመነሳሳት የጥናት ግቦችን በማሳካት እራስን መሸለም በትምህርት ውጤታማ ለመሆን ከሚረዱ በርካታ የአጠናን ዘዴዎች ውስጥ ጥቂቶች ከላይ የዘረዘርናቸው ናቸው።

👉 ያስታውሱ፣ ሁሉም ሰው የተለያየ የመማሪያና የማጥኛ ዘይቤ አለው፣ ስለዚህ በእነዚህ ቴክኒኮች መሞከር እና ለእርስዎ የሚስማማውን ማግኘት አስፈላጊ ነው።