"ኤልሮኢ ዘተዋህዶ"
1.2K subscribers
26 photos
3 videos
5 files
21 links
ኤልሮኢ
"በእውኑ የሚያየኝን ጌታ አየሁት"
በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ
አምላክ አሜን።
ይህ መንፈሳዊ ቻናል
የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ አስተምህሮና ስርዓትን የጠበቁ:- +ዝማሬ
+ ምክሮች
+ ስነፅሁፎች
+ አጫጭር ትርክቶች እንዲሁም
+ ምስባክና
+ ወንጌል ይለቀቁበታል።

ለበለጠ መረጃ @AleroeBot
ግሩፑን ለማግኘት @alero
Download Telegram
ኤልሮኢ:
​​ ተዋህዶ_አትፈርስም

ድርጅት አይደለም በሰዉ የታነፀ፣
ፖለቲካም አይደል ዘርን ያጣቀሰ፣
ሚስጥሩ ፍቅር ነዉ ቃላት የማይበቃዉ፣
እኛን ስለመዉደድ በፍቅር ተስቦ መስቀል ላይ የወጣዉ።
በደም ታንፀናል በማይጠፋ ቀለም፣
ለእኛ ብሎ እርሱ ጌታ ቢሰቀልም፣
መሠረቱ ኢየሱስ ግድግዳዉ ቅዱሳን፣
ግንቦቹ እኛ ነን የእርሱ ምዕመናን።
ልንወድቅ አንችልም በእርሱ ፍቅር ፀንተን፣
እግዚአብሔርን ይዘን ማን ይሆን የሚከሰን?
መሃመዳዊያን ወይም ጅሆቫ ዊትነስ፣
ፕሮቴስታንትም ሁን ወይ ደግሞ ካቶሊክ
አለቱን ላታፈርስ የሰዉ ደም አታፍስስ፣
ምንጩንም ላታደርቅ ከመቅደሱ እራቅ።
ካህኑ ቢታረድ መቅደሱ ቢቃጠል፣
እንበዛለን እንጂ የለም የሚጎድል።
ስንሞት እንበዛለን መከራዉ ሲበዛ በፍቅር እንፀናለን፣
በእሳት ስንቃጠል እንለመልማለን።
ከማይደክም አባት ተፈጥረናልና፣
አርዮስ አትልፋ እንላለን ቀና።
ሰልፉ የእኛ ነዉ ድልም የእኛ ብቻ፣
እንደ አሸዋ የበዛን እስከዓለም ዳርቻ።
ካህኑን ግደሉ መቅደሱን አቃጥሉ፣
ቅጥሩንም አፍርሱ ልጆቹን በትኑ፣
እናንተ ስትጠፉ በገሀነም እሳት፣
ሰማዕታት በአባታቸዉ እቤት
ይሰበሰባሉ መንግስተ ሰማያት።
ይህ ነዉ ክርስትና የማይጠፋ ቀለም፣
በፍፁም ማይጨልም ሁሌ ሚሰጥ ብርሃን።
እናማ አርዮስ ቁርጥህን እወቀ፣
ድል ላታደርግ እንደዉ ራስህን አታስጨንቀዉ፣
ሃሰት እዉነትን መቼ ነዉ አሸንፎ የሚያቀዉ?
ባንድነት ተነሱ የእምነትን ሰይፍ ያዙ፣
በፍቅር ማርኩና የዲያቢሎስን ሴራ በእምነታችሁ ናዱ።
በእምነት እንሞላ በፅናት እንቁም በተስፋ እንዉጣ፣
ጠላት አፍሮ እንዲቀር መድረሻም እንዲያጣ።
የጦር ዕቃችሁን ልበሱ እንደ ካባ፣
ዘመቻዉን አፅኑት ቅድስቲቷ ምድር አርዮስ እንዳይገባ።
የጦር ሠልፍ አንሻም ቀስት አንወረዉርም፣
ደም እያፈሰስን እርሱ የፈጠረዉን እኛ አንገድልም።
ቀስትና ጦር ይዘን አንወጣም ዘመቻ፣
ጠጠርም አንለቅምም አሳዳጁን መምቻ።
መምቻው ክርስቶስ ነው የእሳት መዶሻ፣
ምሽጋችን ቅድስት የኃጥአን መሸሻ።

@aleroe
ኤልሮኢ:
በትዕግሥቱ ብዛት

በትእግሥቱ ብዛት ባይገለጥ ኃይሉ
ስቀለው ስቀለው አይሁድ ተባባሉ/2/
የኃያላን አምላክ አልፋና ኦሜጋ
እንድኛ ታመመ በለበሰው ሥጋ
ኅብስት አበርክቶ የሚመግብ ጌታ
ታሰሮ ተገረፈ እንደክፉ ሽፍታ
እጅና እሮቹ ታሰረው ብታይ
ድንግል አለቀሰች እለች ዋይ ዋይ
የሚንቀጠቀጡለት መላእእክት በፈቱ
እንደምን በችንካር ተወጋ ደረቱ
የንጹሐን አምላክ ወንጀለኛ ተብሎ
ዋለ ቀረንዮ እርቃኑን ተሰቅሎ
በደል ሳይኖርበት ተሰቀለልን
ሞታችንን ሞቶ ሕይወትን ሰጠን

@aleroe
ኤልሮኢ:
‹‹አዝለህ ውሰደኝ››

‹‹አባታችን አባ ኪሮስም በበዓቱ ሳለ ከዕለታት አንድ ቀን ጌታን እጅግ የጎበጠ ፈጽሞ ያረጀ መነኩሴ መስሎ በእጁ ምርኩዝ ይዞ ቀስ ቀስ እያለ ሄዶ ከጥላ ሥር ሲያርፍ ከሩቅ አየው፡፡ አባ ኪሮስም ከሩቅ አይቶ ወደ ‹ይህ መነኩሴ ፈጽሞ ደክሟል› ብሎ አደነቀ፣ ሊጠይቀውም ወደ እርሱ ሄደ፡፡ ያም ሽማግሌ ‹እግዚአብሔርን የምትወድ ከሆንክ ከአንተ ጋር ወደ በዓትህ ውሰደኝ› አለው፡፡ አባ ኪሮስም ‹ከወዴት መጣህ?› አለው፡፡ ሽማግሌውም ‹ኤረር ከሚባል ቦታ ነው የመጣሁት› አለው፡፡ መልሶም ‹ኤረር የሚሉት ቦታ የት ነው ያለው?› አለው፡፡ ያም ሽማግሌ ‹በምሥራቅና በምዕራብ፣ በደቡብና በሰሜን አይደለም› አለው፡፡ አባ ኪሮስም ‹አባ ምን ትላለህ? በምሥራቅና በምዕራብ፣ በደቡብና በሰሜን ካልሆነ በየት ሀገር ነው?› አለው፡፡ ሽማግሌውም ‹ዛሬስ አታውቀውም፣ ኋላ ግን ታውቀዋለህ› አለው፡፡ አባታችን አባ ኪሮስም ‹ሃይማኖትህ ከሃይማኖታችን ጋር አንድ ይሆናልን?› አለው፡፡ ሽማግሌውም ‹አዎ አንድ ነው› አለው፡፡ አባ ኪሮስም ‹ምስጋናህ በሰማይና በምድር የመላ አንድ አምላክ የሚሆን አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በል› አለው፡፡ ያም ሽማግሌ አባታችን አባ ኪሮስ እንዳለው አለ፡፡ ያንጊዜም አባታችን አባ ከሮስ ‹እውነተኛ ክርስቲያን ነህና ወደ በዓቴም እንሂድ› አለው፡፡ ሽማግሌውም ‹አንተ ብርቱ ነህ፣ እኔ ግን ደካማ ሽማግሌ ነኝ፡፡ እግዚአብሔርን የምትወድ ከሆንክ አዝለህ ውሰደኝ› አለው፡፡ አባታችን አባ ኪሮስም ‹እሺ እሸከምሃለሁ› ብሎ ወገቡን በአፅፉ ታጥቆ አዝሎ ጥቂት ጥቂት እያለ ሔዶ ደከመ፡፡ ያ ሽማግሌም አባ ኪሮስን ‹ደከምክን?› አለው፡፡ አባታችንም ‹ጸሎትህ ይረዳኛል› አለው፡፡ ያንጊዜም የሽማግሌው መልኩ ተለወጠ፣ ነጎድጓድ ብልጭልጭታም ሆነ፡፡ አባ ኪሮስም ክብሩን ማየት ተሳነው፣ ዐይኑም ተጋረደና ወደ መሬት ወደቀ፡፡ ጌታችንም አባ ኪሮስን ‹ፈጽሜ ላከብርህ ነው እንጂ ላጠፋህ አልመጣሁምና ተነሥ› አለው፡፡››


@aleroe
ኤልሮኢ:
አንሱ_አላነሳም
========÷=======
አንዲት ሴት ወይዘሮ በባቡር ጉዞ ላይ ሳሉ አጠገባቸው ባለው ወንበር ላይ የተቀመጠ ሻንጣ ስለነበር አንድ ሠራተኛ መጥቶ ይህ ወንበር ለሰው መቀመጫ እንጂ ለዕቃ ማኖሪያ አልተፈቀደምና እባክዎ ያንሱ ሲላቸው ‹‹አላነሳም›› አሉት፡፡ ‹‹ቢያነሱ ይሻላል እምቢ ካሉ ላለቃዬ እነግራለሁ›› ቢላቸውም
‹‹ሂድ ንገር›› አሉት፡፡ ሂዶ ሲነግረው አለቅየው መጥቶ "ያንሱ እንጂ ለምን አላነሳም ይላሉ?" ብሎ ቢናገራቸው ‹‹አላነሳም›› በሚለው ሐሳባቸው ጸንተው የማይበገሩ ሆኑበት፡፡ በመጨረሻም ዋናው ኃላፊ ተነግሮት ይመጣና ‹‹ይህን ሻንጣ ያንሱ›› ሲላቸው ‹‹አላነሳም›› አሉት፡፡ ዋና ኃላፊውም ‹‹ለምን?›› ሲላቸው ‹‹ገና አሁን አዋቂ ሰው መጣ፡፡ እኔ የቸገረኝ እኮ እስካሁን ድረስ ‹‹ለምን›› ብሎ የጠየቀኝ ባለመኖሩ ነበር፡፡ አንተ ‹‹ #ለምን ?›› ስላልከኝ አመሰግንናለሁ፡፡ በመሠረቱ ግን ሻንጣው የእኔ #አይደለም
ሲሉት በመደነቅ ይቅርታ ጠየቃቸው፡፡
አብዛኞቻችን በሰዎች ላይ በደፈናው እንፈርዳለን፡፡ ምእመኑ ሰንበት ተማሪው ላይ፣ ሰንበት ተማሪው ካህናቱ ላይ ሁሉም በአዙሪት ይፈርዳል ቤተክርስቲያናችን ያጣችው የሚፈርድ ሳይሆን እውነትን እየፈልገ ከጎኗ የሚቆም ሰው ነው። እናም ሁሌም በደፈናው ከመፍረዳችን በፊት "ለምን?" ብሎ መጠየቅም እውቀት ነው፡፡

@aleroe
ኤልሮኢ:
ጥበበኛዋ ትል

አንዲት ትል ከአንድ ረጅም ዛፍ ስር ሆና ወደ ላይ ስትመለከት ዛፉ በማፍራት ላይ ያለውን ፍሬዎች በመመልከቷ ከፍሬው ለመመገብ ወደ ዛፉ ላይ የመውጣትን ጉዞ ጀመረች፡፡
በእሷ ፍጥነት (ዝግመት) ዛፉን ወጥታ ያሰበችበት ለመድረስ ረዘም ያለ ጊዜ እንደሚፈጅ ከተሞክሮ ብታውቀውም በጣም እየጸለየች ወደላይ በወጣች ቁጥር በበለጠ ሁኔታ እየታያት የመጣውን የአካባቢ ገጽታ እያየች በደስታ ዳገቱን ተያያዘችው፡፡
ብዙም ሳትርቅ ከዛፉ ላይ ወደታች የምትወርድ አንዲት ምንነቷ በውል ያልታወቀ እንስሳ ቆም ብላ፣ “ወደየት ነው እንደዚህ በደስታ እየተፍለቀለቅሽ የምትሄጂው አለቻት”፡፡
ትል፣ “ዛፉ ጫፍ ላይ ያለውን ፍሬ ልበላ” አለች፡፡
እንስሳዋም፣ “እኔ ከዚያ ነው የመጣሁት፣ ፍሬዎቹ ገና አልበሰሉምና አትልፊ፡፡ ሲቀጥል ደግሞ አጉል ደስተኛነት አያጥቃሽ ጉዞው ቀላል እንዳይመስልሽ፣ ስለዚህ ብትመለሺ ይሻልሻል” አለቻት፡፡
ትሏም፣ ቆም ብላ እዚያ ለመድረስ የሚፈጅባትን ጊዜ ካሰላች በኋላ፣ “ችግር የለውም፣ እዚያ እስከምደርስ ድረስ ፍሬዎቹ ይበስላሉ” በማለት ጉዞዋን ቀጠለች፡፡
ያሰብከው ከፍታ ለመድረስና የለፋህበትን መንፈሳዊ ፍሬ ለማግኘት . . .
1. ዓላማህን ከጊዜ ጋር አጣጥመህ እቅድ አውጣ
ከሁሉ በፊት ለመድረስ የምትፈልግበትን የዓላማ ከፍታ ወስን፡፡ ከዚያም፣ እዚያ ዓላማህ ጋር ለመድረስ የሚፈጅብህን የጊዜ ሁኔታ አስላና ሁለ-ገብ እቅድ አውጣ፡፡ ሁለ-ገብ እቅድ ማለት፣ እንደ አንተ ሁኔታ ገንዘብን፣ ትምህርትን፣ እድሜን . . . ያካተተ ሊሆን ይችላል፡፡
2. የሰዎችን ሃሳብ አመዛዝን
ሁል ጊዜ ከፍ ያለ እቅድ ስታወጣና መንቀሳቀስ ስትጀምር ተቃራኒውን የሚነግሩህ ሰዎች እንደሚያጋጥሙህ አትርሳ፡፡ አንዳንዶች ለአንተ አስበው በቅንነት፣ ሌሎቹ ደግሞ በአንተ ላይ አስበው በምቀኝነት፡፡ በጭፍንነት ከሰማሃቸው ውጤቱ ያው ስለሆነ ሁለቱንም ቢሆን በጥንቃቄ ማስተናገድ አስፈላጊ ነው፡፡ በዋናነት ደግሞ ዲያቢሎስ በየሄድክበት ሁሉ የእንቅፋት ችግኙን ይተክልብሃል ይህንንም በጸሎት ኃይል ተቃወም ።
3. በጉዞው ተደሰት
ወደ ዓላማህ በአንተ አቅምና ፍጥነት ስትጓዝ ፍጻሜው ላይ የመድረስን ደስታ እስከምታገኝ ተስፋ አትቁረጥ፡፡፡ የመድረስ ደስታ ዓላማህ ላይ እስከምትደርስ ድረስ ያስጠብቅሃል፡፡ የጉዞው ደስታ ደግሞ አሁኑኑ በመደሰት ለጉዞው ጉልበትን ይሰጥሃል፡፡
ያሰብከው ደረጃ መድረስህና ፍሬህን መብላትህ አይቀርምና፣ በፍጹም እንዳትቆም!!!

(ቅዱስ ያሬድንና ያቺን ትል አስብ)

@aleroe
ኤልሮኢ:
ለመላቀቅ መልቀቅ!

የስድስት አመት ልጅ ነው፡፡ የሚኖረው ከአባትና ከእናቱ ጋር እንዲሁም ከሁለት ታላላቅ ወንድሞቹ ጋር ነው፡፡ ይህ ልጅ
ከወንድሞቹ ይልቅ ፈጣንና አንዳንዴም ከመስመር ወጣ ያለ ቅልጥፍና ያለው ልጅ ነው፡፡ አንድን ነገር ካየና ከወደደው ያንን ነገር በእጁ የሚያስገባበትን መንገድ በዚህም ሆነ በዚያ ፈልጎ ነገሩን በእጁ ያስገባል፡፡ አንድን ነገር እጁ ለማስገባት ማልቀስ ካለበት ማልቀስን፣ መጣላት ካለበት መጣላትን፣ መስረቅ ካለበት መስረቅን ከመጠቀም የሚመልሰው የለም፡፡ መኝታ ቤቱ ያለው የመጫወቻ ብዛት ይህ ነው አይባልም፡፡ ከየት ለቃቅሞ እንዳመጣው የማይታወቅ ብዙ ነገር ነው ያለው፡፡ አባቱ ይህንን
ባህሪውን ያውቃል፣ ሆኖም በተለያየ መልኩ ሊያስተምረው ከመሞከር ውጪ ምንም ሊያደርገው አልቻለም፡፡
አንድ ቀን ይህ ልጅ የማይረሳውን ትምህርት አገኘ፡፡ ከትምህርት
ቤት ተመልሶ ትንሽ ምግብ ከቀማመሰ በኋላ በረንዳው ላይ ይጫወታል፡፡ የጎረቤታቸውን በረንዳና የእነርሱን በረንዳ
የሚለየው አንድ ከብረት የተሰራ በሰው ቁመት ልክ የሆነ አጥር
ነው፡፡ ይህ ልጅ ቀና ብሎ ሲያይ የጎረቤታቸው ልጅ ሲጫወትባት
የነበረች ትንሽ ሳንቲም የምታክል መጫወቻ ያያል፡፡ በተለያዩ
ቀለማት ስለምታብረቀርቅ ልቡን ሳበችው፡፡ ዘወር ብሎ ዙሪያውን ሲመለከት ማንም ሰው የለም፡፡ ቀና ብሎ ወደ ጎረቤቱ ግቢ ሲያጤን ያ በጣም የሚፈራው ውሻም በአካባቢው የለም፡፡ በቀስታ እጁን በብረት አጥሩ መካከል አሾልኮ ያችን ያጓጓችውን መጫወቻ በእጁ ከጨበጠ በኋላ በቀስታ አጁን ውጣ ቢለው እንዴት ይውጣ! ሁለት ሶስቴ ከሞከረ በኋላ እምቢ ስላለው መደንገጥ ጀመረ፡፡ ከአሁን ከአሁን ውሻው ይመጣብኛል ብሎ ፈራ፡፡ ብዙ ከታገለ በኋላ አልቦታል፤ ከፍርሃትም የተነሳ እንደ ማልቀስ ቃጥቶታል፡፡
በዚህ ሁኔታ ላይ እያለ ነበር አባት የደረሰው፡፡ ዘወር ብሎ አባቱ
መምጣቱን እንዳየ መለስ ሲል ያ ክፉ የጎረቤትም ውሻ ብቅ
አለ፡፡ ልጁ በፍርሃት ማልቀስ ጀመረ፡፡ አባት፣ “ምን ሆነህ ነው?”
ልጅ፣ “እጄ አልወጣ ብሎኝ”፡፡ አባት፣ “እጅህ በሁለቱ የብረት
አጥሮች መካከል እንዴት ገባና ነው አልወጣ ያለህ?” ልጅ፣
“መዳፌን ዘርግቼ ነው ያስገባሁት፡፡” አባት፣ “ታዲያ ለምን
መዳፍህን ዘርግተህ ልክ እንዳስገባኸው አታስወጣውም?”፡፡
ልጅ፣ “መዳፌን ከዘረጋሁት የያዝኩት ነገር ስለሚያመልጠኝ
መልቀቅ አልፈልግም፡፡”
አባት፣ “ካለህበት ሁኔታ መላቀቅ ከፈለግህ የያዝከውን ነገር
መልቀቅ የግድ ነው፡፡ አለዚያ እንደተያዝክ በዚያው መቅረትህ
ነው” ብሎት ጥሎት ሄደ፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር የውሻው ድምጽ
የተሰማው፡፡ ውሻው እየዘለለ ሲመጣ ያየው ይህ ልጅ ምንም
ምርጫ ስለሌለው የጨበጠውን ነገር በመልቀቅ ከተያዘበት ነገር
ተላቀቀ፡፡ የተያዝክበትና የተጨነክበት ነገር እንዲለቅህ ምናልባት መልቀቅ
ያለብህ ነገር ይኖር ይሆን? በሕይወትህ አልሄድና አልተው ያለህ ችግርህ ምናልባት አንተው መልቀቅና መተው ከሚገባህ ነገር ጋር ይገናኝ ይሆን?
ብዙዎቻችን ጨብጠን ያለቀቅናቸው ብዙ ባዕድ ልማዶች አሉን! እነሱን ሳንተው ከፈጣሪ ዘንድ ልንደርስ አይቻለንም። እናም ክርስቲያኖች መልቀቅ ያለብንን ለቀን መያዝ ያለብን ላይ እናተኩር።


@aleroe
ኤልሮኢ:
ታህሳስ 28/04/12ዓ.ም
ዕለተ በዐለ ልደቱ ለእግዚእነ

በዕለቱ ቅዳሴ ሰዓት የሚነበቡ መልዕክታት፣ወንጌልና ምስባክ፡፡

ዲ/ን ገላ 4 ÷1_12
ን/ዲ 1 ዮሐ 4÷9_ፍ.ም
ን/ካ ግብ፡ሐዋ 13÷16_22

#ምስባክ፦መዝ 79÷1
የሐዩ ወይሁብዎ እምወርቀ ዓረብ።
ወዘልፈ ይፄልዩ በእንቲአሁ።
ወኲሎ አሚረ ይድኅርዎ።

#ትርጉም፦ 
እርሱ ይኖራል ከዓረብም ወርቅ ይሰጡታል።ሁልጊዜም ወደ እርሱ ይፀልያሉ።ዘወትር ይባርኩታል።

#ወንጌል፦ ሉቃ 2 ፥1 - 21
#ቅዳሴ፦ ጎርጎርዮስ ካልእ

@aleroe
ኤልሮኢ:
እሰይ እሰይ
===========
እሰይ እሰይ ተወለደ
እሰይ እሰይ ተጠመቀ
ከሰማየ ሰማያት ወረደ
ከድንግል ማርያም ተወለደ/4/
አዝ--------------//
እሱ ባይወለድ እሰይ እሰይ
ቸሩ አምላካችን እሰይ እሰይ
እርሱ ባይጠመቅ እሰይ እሰይ
መደኃኒታችን እሰይ እሰይ
መች ትገኝ ነበር እሰይ እሰይ
ገነት ርስታችን እሰይ እሰይ
አዝ--------------//
ብርሃን ወጣላቸው እሰይ እሰይ
በእውነት ወገኖቹ እሰይ እሰይ
በጨለማው ጉዞ እሰይ እሰይ
እንዳይሰላቹ እሰይ እሰይ
አዝ--------------//
እንደ ጠል ወረደ እሰይ እሰይ
ከሰማይ ወደኛ እሰይ እሰይ
ወገኖቹን ሊያድን እሰይ እሰይ
ከክፉ ቁራኛ እሰይ እሰይ
አዝ--------------//
እግዚአብሔር አብ ላከ እሰይ እሰይ
እንድያ ልጁን እሰይ እሰይ
እርሱ ወዷልና እሰይ እሰይ
እንዲሁ አለሙን እሰይ እሰይ

@aleroe
ኤልሮኢ:
ዝምተኛው መነኩሴ (#ራስአገዝ)

ከዝምተኛው መነኩሴ አባ ዮስጦስ ፀሎት አንዱ "ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ቅዱሳን በተጓዙበት ጎዳና ምራኝ" ነበር፡፡ የዚህ ጸሎት ትርጉም ቅዱስ አድርገኝ ማለት እንደነበር በህይወታቸው ፍፃሜ በሚገባ ተረድተናል፡፡ ቅዱስ እንደሆኑ ማሰብ እንጂ ቅዱስ ለመሆን ማሰብ ወይም በቅድስና መንገድ ለመጓዝ መሻትና መጸለይ መልካም ነው፤ ምክንያቱም ከፈጣሪያችን ትእዛዛትና ፈቃድ አንዱን ለመፈጸም መመኘት ነውና እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋል፡፡ እግዚአብሔር በቃሉ "እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ" እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስም "እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ" በማለት የቅድስናን ህይወት እንድንኖር እንደመከረን ስናስተውል ቅዱስ የመሆን ትእዛዝ እንዳለብን እንረዳለን፡፡ ስለቅድስና ሲነሳ እኛ ቅዱሳን ልንሆን ይገባል ማለቱ በራሱ ወደር የማይገኝለት ድፍረት ሆኖ ሳይሰማን አይቀርም፡፡ነገር ግን መሻቱ ሳይሆን የቅድስና ቁምነገር ነኝ አለማለቱ እና በጭራሽም ነኝ ብሎ አለማሰቡ ላይ ነው፡፡ ሰው ቅዱስ የሚሆነውም ከእግዚአብሔር ፈቃድ ባሻገር በምርጫውና በፍላጎቱ ነውና ይህን የሚያስረዳን ነው።

ዲያቢሎስ ስለመረጠ ከቅድስና ጎድሏል፥ ቅዱሳን መላእክት ደሞ በምርጫቸው ቅዱሳን ሆነዋል ፡፡ሰውም እንዲሁ ነው፡፡ ስለዚህ ለቅድስና መጠራታችንን እና መታዘዛችን እንዲፈጸምልን መጸለይ መሻት መጣር ያስፈልገናል፡፡የጌታችን አማናዊ ቃሉ "ለምኑ፥ ይሰጣችሁማል፤ ፈልጉ፥ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያን አንኳኩ፥ ይከፈትላችሁማል።"ይለናልና።(ማቴ 7:7)
ስለዚህ ቅዱስ የመሆን ፍላጎት ቅዱስ ነውና በማሰባችን ወይም በመመኘታችን ድፍረት መስሎን መጨነቅ አይደገፍም፡፡ ነገር ግን በትህትና መለመንና ሁሉም ነገር በእግዚአብሔር ቸርነት እንደሚፈጸም ማመን ነው፡፡ ያለ እግዚአብሔር ቸርነት (ሰጪነት) በጥረታችን የምናገኘው ምንም ነገር የለም፡፡ "እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ። ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፥ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል።" (ዮሐ 15:5) እንዳለ ያለእርሱ ቅዱስ መሆን ቀርቶ ቅድስናን ማሰብም እንኳን አይቻልም፤ ከእርሱጋ ግን ሁሉ ይቻላል፡፡ ወደቅድስና ከሚመሩን በርካታ ነገሮች እጅግ ጥቂቶቹ በመቀጠል ቀርበዋል፡፡

✞የእግዚአብሔርን ቸርነት እና ፍቅር ማሰላሰል

✞ህዋሳትን ኃጢአት ከመስራት መጠበቅ

✞ ለሰሩት በደል በቶሎ መፀፀት

✞ከሰው ክብርን አለመፈለግ

✞ምስጋናን አለመሻት

✞ ጥላቻንና ትችትን በፍቅር መቀበል

✞ መጸሐፍቅዱስን አዘውትሮ ማንበብ

✞ ያለማቋረጥ መጸለይ

✞በምስጢራት መካፈል

✞ትእዛዛቱን ለመፈጸም መጣጣር

✞በምክረ ንስሀ መጓዝ

✞ራስን እንደተለየ ነገር አለመቁጠር

✞ራስን መገምገም መመልከት

✞ቃለእግዚአብሔርን ማዳመጥና

✞የምንሰማዉን ቃል መፈጸም

✞ከልብ የሆነ ጾምን መጾምና መጸለይ

✞በጎ አድራጎትን መፈጸም

ማንኛውም የምንሰራው ሥራ እግዚአብሔርን ደስ እንዲያሰኝ ብሎ እንጂ አንዳች ጥቅም አገኝበታለሁ በማለት አይደለም፡፡ መሪ ምክንያቱ ፍቅር እንጂ ጥቅም መሆን የለበትም፡፡ ለቅድስና መጋደል እንጂ ቅዱስ እንደሆኑ ማሰብ መጀመር የውድቀት መጀመሪያው ሳይሆን መጨረሻ መሆኑን ማስመር ይገባል፡፡ እነኚህ በየጥቂቱ ልናድግባቸው የምንችላቸው መንፈሳዊ ተጋድሎ የሚጠይቁ ልምምዶች ናቸው ፡፡

ይቆየን!

@aleroe
ኤልሮኢ:
ምን ይል ይሆን

ዛፍ ቆራጩ የዛፉን ቅርንጫፍ መልምሎ ሲያበቃ ዛፉ እንደቆመ ራሱን ከዛፉ ጋር አስሮ ከግንዱ ጋር ሊታገል ወደ ላይ ተስቦ ከጫፍ ደርሷል። አሳቡ ቅርንጫፉ ተመልምሎ ያለቀለትን ብቻውን የቆመውን ዛፍ ከላይ ጀምሮ እየቆረጠ ወደ ታች ለመውረድ ነው።
መጥረብያውን ወደ ላይ ሲያነሳ ግን ንፋሱ ወደ ኋላ እያስጎነበሰውና በፍጥነት እያቃና ያንገላታዋል። ይሄኔ በሁለት እጁ ግንዱን አፈፍ ያደርግና ዥዋዥዌ ይጫወታል።
ንፋሱ እንኳንስ ስራ ሊያሰራው ቀርቶ ለህይወቱም አስጊ ሆነ። ይሄኔ ሁሉንም ርግፍ አርጎ ዐይኖቹን ወደ ሰማይ በማቅናት "ፈጣሪዬ ሆይ ከዚህ በሰላም ካወረድከኝ በኪሴ ያለውም 50 ብር አምጥቼ አስገባለሁ" ሲል ይሳላል
ወድያው ይህን ተናግሮ ሲጨርስ ነፋሱ ይቆምና በሰላም ይወርዳል። ነገር ግን እግሩ መሬት ሲነካ ፍርሃቱ ሁሉ በኖ ስለጠፋ 50 ብሩን ለማስገባት ሳስቶ ምክንያት ይፈልግ ጀመር
"አዎ በርግጥ ከዚህ ዛፍ ላይ ካወረድከኝ ብዬ ተስያለሁ ነገር ግን የወረድኩት እኔ ራሴ ነኝ። ተሸክሞ ያወረደኝ ሳይኖር ለምንድነው 50ብሬን የማወጣው"  ብሎ እራሱን በማሳመን ወደ ቤቱ ጉዞ ቀጠለ።
ዳሩ ግን ትንሽ እየተራመደ ትከሻው ቀለለውና ቢዳብሰው መጥረብያው የለም። መጥረብያው ከዛፉ ጫፍ እንደተሰካ ነው። አሁንስ ምን ይል ይሆን።
የሰው ልጅ ፍጡር ነው ሁሌ ከፈጣሪ እጅ አይወጣም እንድያው ይመስለናል እንጂ ያለ እግዚአብሔር መኖር አንችልም። ያለእኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉም ይለናል ዮሐ 15፣5

@aleroe
ኤልሮኢ:
+++ ምን ብዬ ልጸልይ? +++

በግሪክ ሀገር ሁለት ሴት ልጆቹን ያሉት አንድ አባት ነበር። በአንድ ዓመት ብቻ የሚበላለጡትን እነዚህን ሕጻናት እንደ አባትም እንደ እናትም ሆኖ ተንከባክቦ ማሳደግ የዚህ ሰው ዋነኛ ሥራው ነበር።
ስለዚህ ወጥቶ በገባ ቁጥር ልጆቹን የሚያስደስት ነገር እየገዛ ፣ የሚጠይቁትን እያሟላ በድሎት ያኖራቸው ነበር። የራሱን ሕይወት ወደ ጎን ትቶ ለልጆቹ መኖሩ ያለ ዋጋ አልቀረም። ሁለቱም ልጆቹ በጤንነት አድገው ዕድሜያቸው ለጋብቻ ደረሰ።
አባት የለፋባቸው ልጆቹን ከመዳሩ በፊት ብዙ መሰብ ነበረበት። አስተዋይ ነበርና ብዙ ሽማግሌ ቢላክበትም ልጆቹን ለመሥጠት የወሰነው ግን በጥንቃቄ ነበር። ስለዚህ ልጆቹ ሁለቱም በአንድ ጊዜ እንዳይቸገሩ በማሰብ የተለያየና የማይነጥፍ መተዳደሪያ ላላቸው ወንዶች ባል እንዲሆኑ ለማድረግ ወሰነ።
እንዲህ ሲልም ያወጣና ያወርድ ጀመር :
"ሰዎች ሁልጊዜም ምግብ ያስፈልጋቸዋል ስለዚህ ገበሬ መቼም ቢሆን እህል ገዢ አያጣም። እንዲሁም ሰዎች ውኃ ለመቅዳት ምግብ ለመሥራት ሸክላ ስለሚፈልጉ ሸክላ ሠሪም ገበያ አያጣም።
ስለዚህ ልጆቼን የምሠጠው ለሸክላ ሠሪና ለገበሬ ነው" አለ። እንዳለውም አንዲቷ ልጁ የገበሬ ሚስት ሌላኛዋ ደግሞ የሸክላ ሠሪ ሚስት እንዲሆኑ ሠጣቸው።
ከብዙ ጊዜ በኋላ በአንድ ሰንበት ይህ ሽማግሌ ዛሬስ ልጆቼን ልጠይቅ ብሎ ተነሣ። በመጀመሪያ ወደ ገበሬው ሚስት ሔዶ ሲጫወት አረፈደ።
ተሰናብቶ ሊወጣ ሲል ልጁ እንዲህ አለችው :
"አባዬ እስካሁን ኑሮአችን ሰላም ነበር። አሁን ግን ችግር ላይ ነን። ላለፉት ሁለት ወራት ዝናም ጨርሶ አልዘነበም። በዚሁ ከቀጠለ የዘራነው አይበቅልም ፣ ተክሎቻችንም ይደርቃሉ።
አባዬ አደራ! በሚመጣው ወር ከባድ ዝናም እንዲጥል ወደ ፈጣሪ ጸልይልን!"
አባት አደራውን ተቀብሎ ተሰናብቶ ወደ ሁለተኛዋ ልጁ ቤት ለመሔድ ጉዞውን ጀመረ።
ከሰዓት በኋላ ወደ ሁለተኛዋ ልጁ ቤት ሲደርስ ከሸክላ ሠሪው ባሏ ጋር በአክብሮት ተቀብለው አስተናገዱት። ከጠዋቱ የበለጠ ደስተኛ ሆኖም አሳለፈ። መሰናበቻው ላይ ግን ልጁ ተነሥታ እንዲህ አለችው:
"አባዬ ለአንተ ለጸሎተኛው አባቴና ለጠንካራው ባለቤቴ ምስጋና ይሁንና ኑሮአችን እስካሁን ጥሩ ነው። እንደምታውቀው ላለፉት ሁለት ወራት ዝናም አልዘነመም። በዚህም ደስተኞች ነን። አሁን የምለምንህ አንድ ነገር ብቻ ነው።
በሜዳ ላይ ተደርድሮ እንደምታየው እጅግ ብዙ ሸክላዎች እየሠራን ነው። በሚመጣው ወር ዝናም ካልዘነመና ደረቅ ከሆነ የሠራናቸው ዕቃዎች ሁሉ ደርቀው ለገበያ ይደርሱልናል። ስለዚህ በሚመጣው ወር ዝናም እንዳይጥል ወደ ፈጣሪህ ጸልይልን"
አባት ተሰናብቶ ሲወጣ ወደ ሰማይ ቀና ብሎ
"ፈጣሪዬ ሆይ አንዲቱ እንዳይዘንም ጸልይ አለችኝ ፣ ሌላዋ እንዲዘንም ጸልይ አለችኝ ፣ ምን ብዬ ልጸልይ?" አለ።
ይህ አረጋዊ የእኛን ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ ቢያስቀድስ ኖሮ ግን እንዲህ አይጨነቅም ነበር። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ ላይ ዲያቆኑ የሚያነበው ምእመናን በግንባራቸው ተደፍተው የሚሰሙት "በእንተ ቅድሳት" የሚባል ጸሎት ላይ የዚህን ሽማግሌ ልብ የሚያረጋጋ ስለ ዝናም የሚጸለይ አንቀጽ አለ። እንዲህ ይላል:
"በሚሻበት ቦታ እግዚአብሔር ዝናሙን ያዘንም ዘንድ ስለ ዝናም እንማልዳለን"
"በሚሻበት" የሚለው ቃል ላይ "ሻ" ጠብቃ ትነበባለች። "በሚፈለግበት ቦታ እግዚአብሔር ዝናሙን ያዘንም ዘንድ" (ኀበ ዘይትፈቀድ መካን) ማለት ነው። ቀሳውስቱም ስለ ዝናማት በሚጸልዩት መስተብቁዕ ላይ "ወደ ሚሻበት ቦታ ዝናሙን ይልክ ዘንድ" (ከመ ዝናሞ ይፈኑ ውስተ ኀበ ይትፈቀድ መካን) "ወደሚሻበት ቦታ ዝናሞችህን ላክ"(ዝናማቲከ ፈኑ ውስተ ኀበ ይትፈቀድ መካን) ይላሉ።
ዝናም እንደ ገበሬው ቤት የሚፈለግበት ቦታ እንዳለ ሁሉ እንደ ሸክላ ሠሪው ቤት ደግሞ የማይፈለግበት ቦታ አለና ቤተ ክርስቲያን ከፈጣሪዋ ዝናም ከመለመን አልፋ የሚያዘንምበትን ቦታም እየጠቆመች ትጸልያለች።

"ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ "

@aleroe
ኤልሮኢ:
ይህን ያውቁ ሮሯል!!!

በተለምዶ ‹‹ አርባ አራቱ ታቦት›› እያልን የምንጠራቸው አብያተ ክርስቲያናት ያሉት በጐንደር ከተማ ሲሆን ስማቸውም የሚከተለው ነው፡፡

1. ፊት ሚካኤል
2. ፊት አቦ
3. አደባባይ ኢየሱስ
4. ግምጃ ቤት ማርያም
5. እልፍኝ ጊዮርጊስ
6. መድኃኔዓለም
7. ቅዱስ ገብርኤል
8. ጠዳ እግዚአብሔር አብ
9. አባ እንጦንዮስ
10. ደብረ ብርሃን ሥላሴ
11. አደባባይ ተክለሃይማኖት
12. ሠለስቱ ምእት
13. ልደታ ለማርያም
14. አጣጣሚ ሚካኤል
15. አቡነ ኤውስጣቴዎስ
16. ቅዱስ ሩፋኤል
17. ደፈጫ ኪዳነ ምሕረት
18. ቁስቋም ደብረ ፀሐይ
19. መጥምቁ ዮሐንስ
20. በኣታ ለማርያም
21. ቅዱስ ቂርቆስ
22. ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ
23. አባ ጃሌ ተ/ሃይማኖት
24. ፈንጠር ልደታ
25. ደብረ ምጥማቅ ማርያም
26. አባ ዐቢየ እግዚእ
27. ቅዱስ ፋሲለደስ
28. ሐዋርያት
29. ቀሃ ኢየሱስ
30. አርባዕቱ እንስሳት
31. ጎንደሮች ጊዮርጊስ
32. ጎንደሮች ማርያም
33. አበራ ጊዮርጊስ
34. ብላጅግ ቅዱስ ሚካሌል
35. አባ ሳሙኤል
36. አይራ ሚካኤል
37. ጓራ ዮሐንስ
38. ወረንግቦ ጊዮርጊስ
39. አሮጌ ልደታ
40. አዘዞ ተ/ሃይማኖት
41. ምንዝሮ ተ/ሀይማኖት
42. ሰራራ ማርያም
43. ዳሞት ጊዮርጊስ
44. ጫጭቁና ማርያም

በቃል ያለ ይረሳል በ………………………

@aleroe
ኤልሮኢ:
ቤተ ክርስቲያን መሄድ ጥቅም የለውምን ?

የግብጻዊው መነኩሴ ምክር

…………ብዙ ጊዜ በእግረ ስጋው ወደ ቤ/ክ ይመላለስ የነበረ አንድ አማኝ ወደ አንድ አባት ሄዶ ብዙ ጊዜ ቤተ ክርስቲያን መመላለሱ ስሜት አልባ እና ትርጉም የሌለው ነገር እንደሆነበት እየተማረረ እንዲህ አላቸው “ለ 30 አመታት ያህል ቤተ ክርስቲያን ተመላልሻለሁ፣ በእነዚህ አመታት ብዙ ጉባኤያትን ተካፍያለሁ፣ ቅዳሴ አስቀድሻለሁ፣ ንስሀ ገብቻለሁ. . . . . . ግን ትርጉም ያለው ነገር የለኝም፣ ካሳለፍኳቸው አገልግሎቶች ውስጥ ትዝ የሚሉኝ ብዙም የሉም፣ እንደ ትዝታ የሚታወሰኝም የለኝም፣ እንደ ብክነት አየዋለሁ . . . .ካህናቱና ሰባክያኑም ያለ ምንም ትርፍ ጊዜያቸውን እያባከኑ ያለ ይመስለኛል. . . . .”
ካህኑ በጥንቃቄ አዳመጡት፡፡ የብዙ አማኝ ችግርም እንደሆነ አስረዱት፣ ሰይጣን ሆነ ብሎ የቀየሰው ወጥመድ እንደሆነ አስታወሱትና ያለፈውን የህይወት ተሞክሯቸውን እያነሱለት እሱ እንደ ብክነት መስሎት የተመለከተው ነገር ጥቅሙ እንደነበር ነግረውት የእሱ ችግር ሰይጣን ቤተ ክርስቲያን ባሳለፋቸው 30 አመታት የተጠቀመውን እንዳይመለከት አይኑን ዘግቶት ጉድለቱን ብቻ እያሳየው ተስፋ እያስቆረጠው እንደሆነ ነግረውት የራሳቸውን ተሞክሮ በዘይቤ እንዲህ አሉት ፡-
“ትዳር የያዝኩት የዛሬ 30 አመት ነው፣ ካገባሁ 30 አመት ሞልቶኛል፡፡ በእነዚህ 30 አመታት ውስጥ ባለቤቴ ከ 32,000 በላይ የምግብ አይነት ሰርታ መግባኛለች፡፡ ሆኖም ግን አንድም ቀን እነዚህን የምግብ ዝርዝሮች ለአንድ ጊዜም ቢሆን አስታውሻቸው አላውቅም፣ የማውቀው ነገር ቢኖር ግን ይህንን ነው፡- እነዚህ ምግቦች ተንከባክበውኛል፣ በሽታ እንዳያጠቃኝ ተከላክለውልኛል፣ ስራዬን በአግባቡ እንድሰራ ጥንካሬ ሰጥተውኛል፣ የነቃ አእምሮ እንዲኖረኝ አንቅተውኛል፡፡ ባለቤቴ ዛሬ በዚህ ጤንነት እንድቆም ያደረገኝን ምግብ ባትመግበኝ ኖሮ በህይወት ባልኖርኩና በሞትኩ ነበር ፣ አይነታቸው ትዝ ስላላለኝ ጥቅም የላቸውም ልል ይገባኛልን? ለዛሬ መኖሬ ምክንያት ባለፈው 30 አመታት የተመገብኳቸው ግን አሁን ትዝ የማይሉኝ ምግቦች ናቸው፣ ምግብ ሁሌም አዲስ ነው፣ የምንመገበውም እንደ አዲስ ነውና፡፡ ባልሞት እንኳን ንቁ ሆኜ ሰው የሚጠቀምበትን አገልግሎት ባላገለገልኩ እንደ አንተ አይነት ያሉትን ባልመከርኩ ነበር” ልክ እንዲሁ ላለፉት ብዙ ጊዜያት ወደ ቤተ ክርስቲያን ሄጄ ባይሆን ኖሮ በመንፈሴ ሞቼ በኖርኩ ነበር፡፡ ዛሬ ቤተ ክርስቲያንን ተጠግቼ ህይወቴን እንድመለከት ባልሆንኩ ነበር፤ ሌላው ቢቀር እንኳን “ያሳለፍኩት አመታት ብክነት ይሆኑ እንዴ” ያስባለኝ ቤተ ክርስቲያን መመላለሴ ነው፡፡ የሰማኋቸው፣ ያነበብኳቸው የቃል ምግቦቹ በዝተው ዛሬ እንድቆም አድርገውኛል፡፡ ጥቅሜን ማየት ተስኖኝ እንጂ ለካ ዛሬ በመንፈሴ ጤናማ ሆኜ የቆምኩት ባለፉት 30 አመታት የተመገብኳቸው አገልግሎቶች ናቸው? የዛሬ 20 እና 25 ዓመታት የተማርናቸውን ትምህርቶች ላናስታውሳቸው እንችል ይሆናል፡፡ ዛሬ መልካም አእምሮ እንዲኖረን ያደረጉት፣ ኃጥያት ስንሰራ የሚገስፅ አእምሮ እንዲኖረን ያደረጉት እዚህ በመመላለሳችን ያገኘናቸው ሀብቶች ናቸው። ለምንም ወደታች ስትወርድ እግዚአብሔር ለአንድ ነገር ወደ ላይ ያወጣሃል፡፡ የወረድክ ቢመስልህም አትመን ጌታ ወደ ላይ ለጥቅም ያወጣሃልና፡፡ በቤቱ ያለ ትርፍ እየተመላለስክ ያለህ አይምሰልህ ሽልማት ላይ ደርሰሃልና፡፡ እምነት የማይታየውን ያያል፣ የማይታመነውን ያምናል፣ የማይቻለውን ይቀበላል፡፡ ሴጣን ከቤ/ክ እንድንቀር፣ ፀሎት እርግፍ አድርገን እንድንተው ሲፈልግ ነው ያንን ማድረጋችን ምንም ጥቅም እንደሌለው ደጋግሞ ያሳስበናል። በቤቱ መመላለሳችን ግን ጥቅም አለው በረከት አለው። ማንም የአንድ ባለፀጋ ቤት ተጋብዞ ሄዶ ሳይበላ ሳይጠጣ ሚመጣ የለም፣ እኛም ከሁሉ የሚበልጠው ባለፀጋው የመድህን ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ቤት(ቤተክርስቲያን) ኑ ብሎ ጠርቶን ሄደን ባዶአችንን ፍፅም አንመለስም። ለእኛ አሁን ጥቅሙ ባይታየንም የመንፈስ ቅዱስ በረከት ግን እያደረብን ይሄዳል።

በቤቱ ፀንተን ለዘለዓለም እንድንኖር ይርዳን።
አሜን!

@aleroe
This media is not supported in your browser
VIEW IN TELEGRAM
ኤልሮኢ :
ኃዲጎ ተሰአ
ኀዲጎ ተሰአ ወተሰአተ ነገደ /2/
ማእከለ ባሕር /4/ ቆመ ማእከለ ባሕር/2/
ኤልሮኢ:
ልሳነ_ግዕዝ ሞክሼ_ፊደላት

ሞክሼ ፊደላት የሚባሉት አንድ አይነት ድምጽ ያላቸው ነገር ግን በቅርጽ እና በስራቸው የተለያዩ ፊደላት የሆኑ ናቸው።
በድሮ ጊዜ ግን አባቶቻችን ሀን ከ ሐ ፣ ጸን ከ ፀ... ፊደሎችን በድምጽ አወጣጥ ይለዮአቸው ነበር።

እኝህ ፊደላት በቁጥር ፱(9) ሰሆኑ
ሀ ፣ ሐ ፣ ኀ ፣ ሠ ፣ ሰ ፣ አ ፣ ዐ ፣ ጸ ፣ ፀ ናቸው።

ሀ ➺ ሃሌታው "ሀ" ይባላል።
◦ሃሌ ሉያ ብለን ስንጽፍ የምንጠቀመው ይህን ፊደል ስለሆነ ሃሌታው "ሀ" ተብሏል።

ሐ ➺ ሐመሩ "ሐ" ይባላል።
◦ሐመር ብለን ስንጽፍ የምንጠቀመው በዚህ ፊደል ስለሆነ ነው።

ኀ ➺ ብዙኀኑ "ኀ" ይባላል
◦ብዙህ ብለን ስንጽፍ የምንጠቀመው ይህን ስለሆነ ነው።

አ ➺ አልፋው "አ" ይባላል።
◦አልፋ ኦሜጋ ብለን ስንጽፍ የምንጠቀምበት ስለሆነ ነው።

ዐ ➺ ዓይኑ "ዐ" ይባላል።
◦ዓይኑ ብለን ስንጽፍ የምንጠቀምበት ስለሆነ ነው።

ሠ ➺ ንጉሡ "ሠ" ይባላል።
◦ንጉሥ ብለን ስንጽፍ የምንጠቀመው ይሄን ፊደል ስለ ሆነ ነው።

ሰ ➺ እሳቱ "ሰ" ይባላል።
◦እሳት ብለን ስንጽፍ የምንጠቀመው ይህን ስለሆነ ነው።

ጸ ➺ ጸሎቱ "ጸ" ይባላል።
◦ጸሎት ብለን ስንጽፍ የምንጠቀመው ይሄን ፊደል ስለሆነ ነው።

ፀ ➺ ፀሐዩ "ፀ" ይባላል።
◦ፀሐይ ብለን ስንጽፍ የምንጠቀመው ይህን ፊደል ነው።
እነዚህ ሞክሼ ፊደላት አንዱ በአንዱ ቦታ መግባት የለበትም ምክንያቱም የትርጉም ለውጥ ያመጣሉ።
ለምሳሌ ፦
➺ ሠረቀ = ወጣ
ሰረቀ = ሰረቀ
➺ አመት = አገልጋይ
ዓመት = ዘመን
➺ ሰዐለ = ስዕል ሳለ
ሰአለ = ለመነ
➺ መሀረ = አስተማረ
መሐረ = ይቅር አለ
➺ ኀለየ = አመሰገነ
ሐለየ = አሰበ
➺ ፈጸመ = ጨረሰ
ፈፀመ = ነጨ
➺ ማኅሌት = ማመስገን
ማሕሌት = ማሰብ

@aleroe
ኤልሮኢ:
#ፍቅር_ማለት

ያን_ሁሉ መስዋእት ያን ሁሉ ግርፋት
ልጅን_ከአባት ጋር አባትን ከልጅ ጋር
           አስታርቆ ለማየት ፤
እኔ ያ ሰው ነኝ የከበረ ዋጋ የተከፈለበት
እኔ ያ. ሰው ነኝ በደሙ_ታጥቤ
 ነፃ የሆንኩበት ፤
ታድያ ለዚህ ከንቱ አለም ላልወደደው
         በትንሽነቱ ሰው ሁሉ ለናቀው ፤
እንዴትስ ተገብቶት ጌታ ሊሞትለት
እንዴትስ ተደርጎ ክብሩን ሊተውለት ፤

ይህ_ፍጡር ማን ቢሆን ነው ከቶ
የሰማዩን_ንጉስ ግዛቱን አስትቶ
በሀጥያቷ ክርፋት ወደ ገማች ምድር
ጠርቶና ጎትቶ ፤
ሞትን_ያቀመሰው የትኛው ፍቅር ነው
የቱ ቅድስና የቱ ማንነቴ የቱ ንፅህና ፤
ንፁህ_የሆነውን ፅድቅ የለበሰውን
ስጋ ያለበሰው ሀጥያት ያደረገው
የቱ እኔነቴ እሱነቱን ትቶ እንዲያ
ሚያዋርደው ? ፤

ያንን_ፍቅርማ ቃላት ተቆፍረው
ያንን_መውደድማ ፊደላት ተጣምረው ፤
ከቶ አይገልፁትም ፍፁም አይደርሱትም
ብርሀን አያደምቀው ጨለማ አይጋርደው
የቀናት መገስገስ የአመታት መንጎድ
        ዘመን የማይሽረው ፤
ፍ ቅ ር ማለት ያ ያ ነው
ፍቅር_ውልደቱ ነው ፍቅር መከራው ነው
ፍቅር_መሞቱ_ነው ፍቅር ትንሳኤው ነው ፤
በዘመን ጅማሬ በዘመን ፍፃሜም
የፍቅር  ስንኙ   የፍቅር ሀረጉ
         ኢ  የ  ሱ  ስ ብቻ ነው !
__________________
@aleroe
ኤልሮኢ:

# ትሕትና + ትእግስት + ተስፋ + ፅናት + ፍቅር + እምነት + አምልኮት + ምግባር=>ስኬት!!

~አንዲት ስጋ የምትጠብስ ሴት ስጋውን መጥበሻው ላይ ትጥደውና ስጋውን ታገላብጠዋለች ።ከዛ መብሰል አለመብሰሉን ለማረጋገጥ በሹካ ወጋ ወጋ አድርጋ ታየዋለች። ከበሰለ ታወርድና ለመዓድ ገበታ ላይ ታቀርበዋለች።ልብ በሉ....
~ፈጣሪም እኛን ይለዉጥናል እውቀት ይሰጡናል ያበስሉናል ብሎ ባሰባቸው በተለያዩ ነገሮች ላይ ይጥደንና ጤና ማጣት፣ስራ ማጣት፣ወዳጅ ማጣት፣ የህይወት አጋር ማጣት፣ገንዘብ ማጣት፣ፍትሕ ማጣት፣ተስፋ ማጣት፣ነገሮችን አለመሳካት፣ሰርቶ መና፣መከዳት፣መናቅ፣ወ ... በተባሉ ሹካዎች ወጋ ወጋ አድርጎ መብሰል አለመብሰላችንን ያረጋግጣል።
~ችግር ውስጥ ሆነን ካመሰገንን በስለናል ካማረርን ግን ይቀረናልና፤አንዳንዴ በተለያዩ ችግር ውስጥ ጥዶ ያገላብጠናል።
~አንድ ካሜራ ማን እኛን ፎቶ ከማንሳቱ በፊት ፈገግ በል ቀና በል ትንሽ ወደ ቀኝ ምናምን እያለ አስቀድሞ ያስተካክለናል ከዛ ያነሳናል። ፈጣሪም እኛን በተለያዩ ችግሮች ውስጥ እያስገባ ነው ህይወታችንን ሚያስተካክለው ምክንያትም የደፈረሰ ህይወታችን መጥራት ስላለበትና ጥርት ለማድረግ።
~መከራ ፈጣሪ እኛን ወደሱ የሚጎትትበት ገመድ ነው። ዳይመንድን ውድ ካደረጉት ነገሮች መካከል አንዱ አቆራረጡ ነው።ዳይመንድን የምናውቀውን ቅርፁን ያስያዘውና ከተለያየ አቅጣጫ እንዲያንፀባርቅ ያደረገው አቆራረጡ ነው ይላሉ። እኛንም ዛሬ እየቆረጡንና እያስጨነቁን ያሉ ሳንቋቋማቸው ቀርተን እያማረርንባቸው ያለን ችግሮቻችንን ነገ እኛን ዉድና የሚያበራ ማንነት ባለቤት የሚያደርጉን ናቸው ።
~ማዕበል ሲነሳና ባህሩን ሲያማስለው ሁሉም እንስሶች ይሸሻሉ።ንስር አሞራው ግን በመሀሉ ገብቶ ዓሳ ይዞ ይወጣል።
~ ወዳጄ ሆይ እንደ ንስር አሞራው በችግር ውስጥ ብትሆንም እራስህን አንፅ። ሸክላ የምትሰራ ሴት እንኳን ሸክላዋን ሰርታ ስትጨርስ እንዲጠነክርላት በእሳት ነው ምትጠብሰው።ዛሬ የሚጠብሱህ ችግሮችና የህይወት መሰናክሎች ከፀናህ ማንነትህን ነው የሚያጠነክሩልህ።
~ ስለዚህ ስለሆነው ስለሚሆነው እየሆነ ስላለው ፣ ስለተደረግልህ ስላልተደረገልህ ፣ ስለ ሰጠህ ስለ ነፈገህ ነገር ሁሉ እሱን አመስግነው።
~ # እንዲ_በለው ፦
"ደስታንም ሆነ መከራን ብትሰጠኝ አመሰግንሀለሁ፤ ከኔ ይልቅ አንተ ነህና ለእኔ ምትቀርበው።ስለዚህም ጌታ ሆይ በመንገዴና በህይወቴ ሁሉ ፈቃድህ እንጂ ፈቃዴ አይሁን።"
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን።

@aleroe
ኤልሮኢ:

#ነበርኩ_መች_ያድናል


ሀጢያትን ስትሰራ አምላክን እረስተህ
ቅዱሱን ሰውነት በሀጢያት አርክሰህ
ትእዛዝን ሳትፈጽም መልካምን ሳትሰራ
ዘይት ሳታዘጋጅ መብራትህ ሳይበራ
በተጠራህ ጊዜ መላከሞት ሲመጣ
ለማያልፈው አለም ሲወጣልህ እጣ
ለሚዛን ስትቀርብ አገልጋይ ነበርኩኝ እያልክ መናገሩ
መዝሙር ዘምሬያለው ሄጃለው ከበሩ
ብሎ መከራከር ያኔ መች ይጠቅማል
ይዞ መገኘት ነው ነበርኩ መች ያድናል!!!!
____________________

@aleroe
ኤልሮኢ:

ለራስህ ነው

አንተ ሰው! ቊጥር የሌላቸው ክፋቶች ቢኖሩብህም እንኳ በጎ ምግባር በልጅህ ይኖር ዘንድ በማድረግ አካክሰው፡፡ ለክርስቶስ የሚኾን ተሽቀዳዳሚ (ሯጭ) አሳድግ! ወዳጄ ሆይ! እንደዚህ ብዬ ስነግርህ አትፍራ፤ አትሸበርም፡፡ ልጅህ እንዳያገባ አድርገው አላልኩህም፡፡ ወደ ገዳም ወስደህ እንድታመነኩሰው ወይም የብሕትውና ሕይወትን እንዲመራ አድርገው አላልኩህም፡፡ እያልኩህ ያለሁት ይህን አይደለም፡፡ ልጅህ ቢመነኩስ እወድ ነበር፡፡ ብዙዎች ወደዚህ ሕይወት እንዲገቡ የዘወትር ጸሎቴ ነውና፡፡ ነገር ግን የምንኵስና ሕይወት [ሳይጠሩ ከገቡበት] ከባድ ሸክም ስለ ኾነ ሰዎች መነኰሳት ካልኾኑ ብዬ ግድ አልልም፡፡ ለአንተም እንደዚህ በግድ አመንኩሰው አልልህም፡፡ እያልኩህ ያለሁት ለክርስቶስ የሚኾን ተሸቀዳዳሚ አሳድግ ነው፡፡ በዚህ ዓለም አግብቶ፣ ልጆችንም ወልዶ የሚኖር ቢኾንም እንኳን ገና ከሕፃንነቱ አንሥቶ ሰውን የሚያከብር እንዲኾን አድርገህ አሳድገው ነው፡፡
ገና ጨቅላ እያለ በጎ በጎ ትእዛዛት በሕሊናው ጓዳ በልቡናው ሰሌዳ ላይ ከተቀረጸ፥ በሰም እንደ ታተመ ጸንቶ ይኖራል እንጂ ሲያድግ እነዚህን ትእዛዛት ሊያጠፋበትና ሊፍቅበት የሚችል ማንም አይኖርምና፡፡ ልጅህ አሁን ያለበት ዕድሜ ደግሞ በሚያየውና በሚነገረው በሌላም ነገር ኹሉ የሚንቀጠቀጥበት፣ የሚፈራበትና የሚደነግጥበት ዕድሜ ነው፡፡ ስለዚህ ልክ እንዳልደረቀ ሰም እንደምትፈልገው አድርገህ ቅረጸው፡፡ እንደዚህ አድርገህ ስታበቃ፥ መልካም ልጅ ቢኖርህ የመጀመሪያው ተጠቃሚ የምትኾነው አንተው ራስህ ነህ፡፡ እግዚአብሔር የሚጠቀመው ከአንተ በኋላ ነው፡፡ ስለዚህ የምትደክመው ለሌላ አካል ሳይኾን ለራስህ ነው፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ኦርቶዶክሳዊ ቤተሰብ

@aleroe
ጥር 24/05/2012

የቅዳሴ ምንባባት

፪ ቆሮ ም ፩ ቁ ፲፫-ፍ.ም
፩ ዮሐ ም ፪ ቁ ፳፪-ፍ.ም
ግብ.ሐዋ ም ፲፫ ቁ ፳-፳፰

ምስባክ

እግዚአብሔር እግዚእ አስተርእየ ለነ
ግበሩ በዐለበት ትፍሥሕት በኀበ እለ ያስተሐምምዎ
እስከ አቅርንቲሁ ለምሥዋዕ


🙏 ትርጉም

እግዚአብሔር አምላክ ነው ለእኛም በራልን
እሰከ መሠዊያው ቀንዶች ደረሱ
በዓሉ መሥዋዕት በገመድ እስሩት

መዝ ፻፲፮-፳፮

ወንጌል
ሉቃ 2÷42 ፍ.ም

ቅዳሴ
ዘሐዋርያት አው ዘዲዮስቆሮስ


@aleroe