የታሪክ-ድርሳን
2.84K subscribers
766 photos
1 video
72 files
40 links
ዛሬ ነፃ ሰዎች ነን፡፡
በባርነት ጭነት ቅስማችን ያልተሰበረ፤
በጭቆና ቀንበር ልባችን ያልተሸበረ፤
ጎንበስ ማለት የሚያንገሸግሸን፤
ቀና ብለን ኖረን ቀና እንዳልን ማለፍ የሚናፍቀን፤
የነጮችን ጥቃት ለመቋቋም ቆዳችን የሚሳሳብን፤
አልደፈር ባይ የጥቁር አፈር ትንታጎች ነን፡፡

ባለ ታሪክ ኢትዮጵያዊ ነን

ይህን የአያቶቻችንን ስጦታ ታሪክ
ላልሰማ አሰሙ!



📜📜📜የታሪክ-ድርሳን📜📜📜
Download Telegram
ከጤና ባለሞያዎች(ዶክተር ቤዛ)(ዶክተር ሲሳይ ለማ) እና ከተመራማሪዎች የተገኘና ኮሮና ቫይረስ ማለት ምን ማለት እንደሆነ፣ እንዴት ከሰው ወደ ሰው እንደሚተላለፍ እንዴት በዕለት ተዕለት የህይወት እርምጃ ውስጥ የቫይረሱን ስርጭት ማስቆም እንደሚቻል የተሰጠ መረጃ አጠናቅረን አቀረብን ተግባራዊ በማድረግ ሐላፊነታችንን እንወጣ ላልሰማም ያሰሙ ዘንድ እንጠይቃለን!

< ኮሮና ቫይረስ የአፍንጫ እርጥበት እና አክታ የሚያስከትል ሳል ያለው አይደለም፡፡ በተቃራኒው አፍንጫ የማያረጥብ እና ደረቅ ሳል የሚያስከትል በመሆኑ በቀላሉ ልንረዳው የምንችለው ነው፡፡

< ቫይረሱ ከ26-27 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ያለውን ሙቀት መቋቋም የማይችል በመሆኑ ይሞታል፡፡ ስለዚህ እንደ ሻይ፣ ሾርባ ፣ ትኩስ ውሃ ...ወዘተ ያለትን ትኩስ ነገሮች በየቀኑ ደጋግሞ መጠጣት ቫይረሱን ይገድበዋል፡፡ ትኩስ ነገሮችን መጠጣት ደግሞ ከባድ አይደለም፡፡
< በጣም የቀዘቀዘ ውሃ አትጠጡ፣ የበረዶ ኩቦችን ወይም አመዳይ/ Snow አትመገቡ! < የምትችሉ ሁሉ የጸሐይ ሙቀት ተቀበሉ፡፡

1. ኮሮና ቫይረስ ከ400-500 ናኖሜትር ዳያሜትር ርዝመት ያለው ትልቅ ቫይረስ በመሆኑ ለመከላከል የሚያስፈልገው ጭምብል ወይም ማስክ በተለየ መንገድ የተሰራ መሆን የለበትም። ማንኛውንም አይነት ጭምብል መጠቀም ይቻላል፡፡

< በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች በሚገኙባቸው ተቋማት የሚያክሙ የጤና ባለሙያዎች ግን የተለዩ የመከላከያ መንገዶችን መጠቀም አለባቸው፡፡

< አንድ በቫይረሱ የተጠቃ ሰው ከፊት ለፊታችሁ ከ3 ሜትር ርቀት ላይ ቢያስነጥስ ቫይረሶቹ ወደ ምድር የሚወድቁ በመሆናቸው በቫይረሱ ተጠቂ አትሆኑም፡፡

2. ቫይረሱ ብረትነት ባላቸው ገጾች/አካሎች ላይ ካረፈ በኋላ ለ12 ሠዓታት በህይወት ሊኖር ይችላል፡፡ ስለዚህ ከብረት የተሰሩ እንደ እጀታዎች፣ በሮች፣ የቤት ዕቃዎችን፣ የአውቶቡስ የባቡር ወይም የትራም መደገፊያ እጀታዎችን ወይም ምሰሶዎችን ከነካችሁ በኋላ እጃችሁን በደምብ በሳሙና መታጠብ ይገባል፡፡

3. ቫይረሱ በልብስ እና በጨርቆች ውስጥ ተሰግስጎ ከ6-12 ሰዓታት ሊኖር ይችላል፡፡ ስለዚህ መታጠብ የሚችሉትን ልብሶች በሙሉ ዘወትር በምንጠቀምባቸው ሳሙናዎች ብናጥባቸው ቫይረሱን ይገድለዋል፡፡ በየእለቱ መታጠብ የማይችሉ ልብሶችን ጸሐይ ላይ ብታሰጡዓቸው ቫይረሱን የጸሐይ ሙቀት ይገድለዋል፡፡

በቫይረሱ የመጠቃት ምልክቶች #ምን ምንድን ናቸው?

1. ቫይረሱ መጀመሪያ መቀመጫውን ጎሮሮ ላይ በማድረግ የጉሮሮ ብግነት እና የጎሮሮ ድርቀት ስሜት ያስከትላል፡፡ ይህ የህመም ስሜት ከ3-4 ቀን በሰው ላይ ሊቆይ ይችላል::

2. ቫይረሱ በመተንፈሻ ቱቦ ውስጥ ያለውን እርጥበት በመጠቀም ወደ ትራኪያ ከወረደ በኋሊ መቀመጫውን ሳምባ ውስጥ ያደርጋል፡፡

ሳምባን በማጥቃት ኒሞንያ/ የሳምባ ብግነት ያስከላል፡፡ ይህ ምልክት የሚታይባችሁ ሁሉ በፍጥነት ወደ ህክምና ሂዱ!!

በቫይረሱ ላለመያዝ ምን ማድረግ ይገባል?

1. የቫይረሱ ስርጭት በአብዛኛው ቀጥታ ከንክኪ ጋር የተያያዘ ሲሆን ቫይረሱ ያረፈባቸውን ቁሳቁሶች እና ልብሶች ወዘተ... መጠቀም ዋነኛ መተላለፊያው መንገዱ ነው፡፡ ይህም ማናቸውንም ነገር ከነኩ በኋላበተደጋጋሚ እጅን በደምብ መታጠብ ዋነኛ መከላከያ መሆኑን ያስገነዝበናል፡፡

< ቫይረሱ በሰው እጅ ላይ በሕይወት መቆየት የሚችለው 10 ደቂቃ ያህል ነው፡፡ ይሁን እንጂ በአስር ደቂቃዎች ውስጥ ብዙ ነገር ሊከናወን ይችላል፡- አይንን ማሸት፣ አፍንጫን መንካት፣ ጣቶችን ወደ አፍ መውሰድ ወይም [እንደ ጥፍር የመመጥመጥ ክፉ ልማድ] ቫይረሱን በቀላሉ ወደ ጉሮሮ እንዲሄድ ሊያደርገው ይችላል፡፡

< ስለዚህ ለራሳችሁና ለባልንጀራችሁ (ለሌላው ሰው) ደህንነት ስትሉ በጣም በተደጋጋሚ እጆቻችሁን ታጠቡ፡፡

2. አፍ እና ጉሮሮን ጸረ-ተሕዋስ መድሀኒቶችን በመጠቀም መጉመጥመጥ ቫይረሱን ሊያስወግድ ወይም ወደ ጉሮሮ የሚሄዱትን መጠን ሊቀንስ ይችላል፡፡ አፍን መጉመጥመጥ ወደ ጉሮሮ ወደ ትራኪያ አልፎም ወደ ሳምባ ቫይረሱ የሚያደርገውን ጉዞ ሊያግደው ወይም ሊቀንሰው ይችላል፡፡

3. የኮምፒውተራችሁን ኪ-ቦርድ እና ማውዝ በጸረ- ተህዋስ በሚገባ አጽዱ።

#ኮሮናቫይረስ ከትንፋሻችን ጋር በሚወጡ ብናኞች ውስጥ
ከአንድ ሜትር እስከ ሁለት ሜትር ይጓዛል። [ቫይረሱ] ብዙ መሄድ
አይችልም ክብደት አለው።

ማህበራዊ መጠጋጋትን እጂግ እንቀንስ ችላ አንበል!!

በአካባቢው ባሉ ዕቃዎች ላይ ያርፋል። ንክኪ ሲኖር እጃችን ላይ ሊያርፍ ይችላል።

በስኳር፣ ልብ እና ደም ግፊት #ሕሙማን እና ዕድሜያቸው የገፋ ሰዎች ላይ ይበረታል። የበሽታ መከላከል አቅማቸው ከጤናማዎች አንፃር የተዳከመ፤ ትንባሆ የሚያጤሱ እና አልኮል የሚጠጡ ሰዎችም ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል።

ጤና ይስጥልኝ !
የባለሞያዎችን ተግሳጽ ተግብሩ!
ሰላም እና ጤና ለአለም ህዝብ ሁሉ ይሆን ዘንድ በእየእምነታችሁ አብዝታችሁ ጸልዩ!!

@yetarikdersan
በቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል ለሌላ የውስጥ ደዌ ህመም የመጣች ታማሚ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ እንደሆነች ተረጋግጧል፡፡

22 የህክምና ባለሙያዎችም የኮሮና ህመምተኛ መሆኗ ከመታወቁ በፊት
ህክምና በሚያደርጉበት ወቅት እራስን የመጠበቂያ ቁሳቁስ ስላልነበራቸው
በተፈጠረ ንክኪ ኳራንቲን ተደርገዋል፡፡

የሚመለከተው አካል ለህክምና ባለሞያዎች ተገቢውን ጥንቃቂ እያደረግ እንዳልሆነ እያየን ነው።

#ትኩረትእናጥንቃቄ

እርቀታችንን እንጠብቅ!
የባለሞያዎችን ምክር እንስማ/እንተግብር!
ሰላም እና ጤና ለአለም ህዝብ ሁሉ ይሆን ዘንድ በእየእምነታችሁ አብዝታችሁ ጸልዩ!!

ምንጭ :- ጋዜጠኛ ጌጡ ተመስገን /
የኢትዮጵያ ሐኪሞች ህብረት እንደዘገቡት

@yetarikdersan
ይህን ወቅት በጋራ ሆነን እናልፈዋለን በሚል መሪ ቃል ጉራማይሌ የበጎ አድራጎት ድርጅት የቫይረሱን መስፋፋት ለመቀነስ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር እጅ በማስታጠብ እና ግንዛቤ በመፍጠር ቆይቷል ከአሁኗ ደቂቃ ጀምሮ ደግሞ ለወገኖቻችን
የምግብ ( ፓስታ ፣ ማካሮኒ ፣ ዘይት ፣ እና የመሳሰሉትን………

የሳኒታይዘሮች ፣ ሳሙና አልኮል ግላብ እና መሰል የንጽህና መገልገያ ቁሶችን የመሰብሰብ ስራ ጀምረዋል ………

እርሶም ይህ መልካም ተግባር ላይ በመሳተፍ የበኩልዎትን አስተዋፆ
ያደርጉ።

#ሼር በማድረግም ይተባበሩ!

"የተሰጠን እንድንሰጥ ነው"

አብረን በመስራት የቫይረሱን መስፋፋት አብረን እንቀንሳለን!!

ልታቀብሉን ለምትሹ የስልክ አድራሻችን እነሆ !
📲0955431015
📲0912319263

"ጉራማይሌ የበጎ አድራጎት ድርጅት"

ማናገር ከፈለጉም ቤታቸው እነሆ
@Guramylecharitableorganization
📜የዓድዋው ጀግና ዋግ ሹም ጓንጉል ብሩ📜

ዋግሹም ጓንጉል ብሩ ታላቅ የጦር ሰው እና ከዋግ ሹም ብሩ ገ/መድህን ልጆች አንደኛውና ታዋቂው ነበሩ።

ከዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ ጋር መልካም ግንኙነት በነበራቸው ጊዜ እንደ
አውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር ከ1889 እስከ 1895 ጃንጥራር
በሚል ማዕረግ የአምባሰል ገዥ በመሆን የአምባሰልን ህዝብ
በብልሀት አስተዳድረዋል።
.
ዋግሹም ጓንጉል ብሩ በ1895 እንደ አውሮፓ አቆጣጠር ሠራዊታቸውን ወደ ትግራይ እንዲያንቀሳቅሱ በዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ ታዘዋል።

የካቲት ፳፫ ቀን ፲፰፻፹፰ ዓ.ም ዋናው ጦርነት ዓድዋ ላይ ከመደረጉ በፊት አምባላጌ እና መቀሌ ላይ ሁለት ታላላቅ
ጦርነቶች ተደርገዋል።

ከእነዚህ ጦርነቶች ቀድሞ አባቶችና
እናቶቻችን ከየመኖሪያ ቀያቸው ተነስተው ጦርነቱ የተደረገበት ቦታ እስኪደርሱ ድረስ ለረዥም ወራት ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፈዋል።

በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ተክለጻዲቅ መኩሪያ ሲዘግቡ... "የኢትዮጵያ ወታደር የኢጣልያ አጥቂነት እንደታወቀና የክተት አዋጅ ከታወጀ ወዲህ ለዚህ ጦርነት ቀረብ ያለው የጎጃም፣ የበጌምድር፣ የወሎና የላስታው ከ300 እስከ 500 ኪ.ሜትር
ያህል የሸዋና የሃረር፣ የባሌ፣ የአሩሲ፣ የከንባታ፣ የሲዳሞ፣ የከፋ፣ የጅማ፣ የወለጋና የኢሉባቡር ጦር ከ600 እስከ 1000 ወይም እስከ 1500 ኪ.ሜትር ድረስ ርዝመት ያለውን አገር በእግሩ አቋርጦ ዘምቷል።

አብዛኛው አጭር ሱሪና ጥብቆ ለብሶ
በላዩ ላይ ነጠላ ደርቧል። የሚራመደው ከእንጨትና ከድንጋይ
እንቅፋት ጋር እየታገለ ውስጥ እግሩን እሾህ በሙቀት ጊዜ ረሞጫ እያቆሠለው ነው።

ተዋጊ ወታደር፣ ስንቅ አቀባዩ ገባር፣ ድንኳን ተካዩ አብዛኛውን ጊዜ በራሱ ወጪ ለስንቅ ያዘጋጀውን ጥራጥሬ እህል (ሽምብራ፣ አተር፣ ባቄላ) የተቆላ ወይም በእሳት በስሎ የተፈጨ የስንዴና
የገብስ ዱቄት በውሃ ነክሮ አድቦልቡሎ የሚበላውን በሶ በአንድ ትከሻው መዋጊያ መሳሪያውንና ጦሩን በሌላ እጁ ተሸክሞ ይጓዛል።

የጉዞውንም ድካም ለማዘናጋት ከወንዶቹ ውስጥ ሽለላና ፉከራ እያሰማ የሚጓዝ ነበረ። ከሴቶቹም ውስጥ
የሚያንጎራጉሩና አዋጊ ግጥም የሚገጣጥሙ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ወታደር ረዥሙን የወራት መንገድ በእግሩ ተጉዞ፣ የራሱን ጥራጥሬ እህል በልቶ፣ ንጹህ ውሃ ተጎንጭቶ ከባህር ማዶ በባቡርና በመርከብ ተጓጉዞ የመጣውን የተደራጀውን በጦር ትምህርት ቤት የተማረውንና በማናቸውም ምቾት ያልተለየውን የፈረንጅ ወራሪ ተዋግቶ በማሸነፍ ሃገራችንን ከባርነት ውርደት
በማዳን ለሚመጣው ትውልድ አኩሪና አስመኪ ታሪክ አወረሠ።"

በንጉሡና በንግስቲቱ እንዲሁም በየጦር መሪዎቹ ሥር በርካታ ወታደሮች ዘምተዋል ዋግሹም
ጓንጉል ብሩም 11,000 ወታደራቸውን አዝምተዋል።

እነ ጊድን ገብሬን ያካተተው ተዋጊው የዋግ ሹም ጓንጉል ብሩ ጦር
ሠራዊትም ከራስ መንገሻ ዮሐንስ ጦር ጎን በጎን ተሰልፎ በአምባላጌ ተራራ የውጊያ አውድማ ላይ ታላቅ ጀብድ ሰርቷል።
.
በዋናው የዓድዋ ጦርነት ዕለትም ዋግ ሹም ጓንጉል ብሩ ሠራዊታቸውን ከሌሎች ጀግኖች አርበኞች የጦር መሪዎች ጋር በማደባለቅ በጀኔራል አልበርቶኔ ይመራ የነበረውን የጣልያኖች የቀኝ ክንፍ ተዋጊ ጦር በማርያም ሸዊቶ የጦር ግንባር
በቆራጥነት በመዋጋት አሸንፈው ጀኔራል አልቤርቶኒን ማርከዋል።

በዚህ ወቅትም የዋግ ሹም ጓንጉል ብሩ ሠራዊት ብቻውን ከ400 በላይ የጣልያን ወታደሮችንና ባለ ማዕረግ የጦር መኮነኖችን ማርኳል።
.
የዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ ጸሐፌ ትዕዛዝ እንደገለጹትም ዋግ ሹም ጓንጉል ብሩ ከንጉሰ ነገስቱ በተሰጣቸው ትዕዛዝ መሠረት ከድል በኋላ ምርኮኞቹን ወደ ዋግ ሰቆጣ ይዘዋቸው ተጉዘዋል።

ዋግ ሹም ጓንጉል የጦር ሜዳ ጀግና መሆናቸው ከመታወቁም ባሻገር
በአስተዳደርም ዝነኛ እና ፍርድ አዋቂ እንደነበሩ ይተረክላቸዋል፤
የዳግማዊ ዓፄ ተክለ ጊዮርጊስ የወንድም ልጅ ስለነበሩ ዙፋን
ለመቀናቀን ይመኛሉ በማለት የሸዋ መኳንንት ይጠረጥሯቸው ነበር።

ምንጭ ፣ ልዩ ልዩ የታሪክ መዛግብትን አዋህደናል ( ከዚህ መነሻ ተነስተው ታሪኩን አስፋፍተው የመተረክ መብትዎ የተጠበቀ ነው)

"ክብር እና ሞገስ ለአርበኞቻችን"

@yetarikdersan
የዓድዋው ጀግና ዋግ ሹም ጓንጉል ብሩ

@yetarikdersan
📜ወራሪውን የጣሊያን ጦር ለመመከት አርበኞች ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰባሰቡባት ስፍራ “አንዲትግራር”📜

“አንዲትግራር” በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በሞጃና ወደራ ወረዳ እንግዳ ዋሻ አንቀላፊኝ ሜዳ በተባለች ስፍራ ላይ ኢትዮጵያውያን በአንድ ተሰባስበው ወራሪውን የጣሊያን ጦር ለመዋጋት የጦር ስትራቴጂ ቀይሰው የመጀመሪያው የአርበኞች ማህበር የመሰረቱባት ታሪካዊ ስፍራ ነው።

ወደ አንዲትግራር ለማቅናት ከደብረሲና ተነስተው እስከ ታሪካዊው ስፍራ ለመድረስ የአካባቢው ፒስታ መሰል አቧራማ ወጣ ገባ መንገድ ማቆራረጥ የግድ ይላል።

አካባቢው ተፈጥሯዊ መስህብ ያለው በመሆኑ ወጣ ገባና ጠጠረማ
መንገዱን አንዳያስቡ ያደርጋል።

አንዲትግራር በአካባቢው የሚገኝ እድሜ ጠገብ ባለ ብዙ ቅርንጫፎች የግራር ዛፍ ሲሆን ስፍራው የመጀመሪያው የኢትዮጵያ አርበኞች ማህበር የተመሰረተባት ቦታ እንደሆነ
የወረዳው ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት መረጃ ያመለክታል።

ጥር 1 ቀን1931 ዓ.ም በባላንባራስ ባሻህ ኃይሌ ሰብሳቢነት
‹‹አንዲትግራር›› ስር ተገናኝተው አርበኞች ተወያዩ፡፡ ራስ አበበ
አረጋይ፣ልጅ ግዛው ኃይሌ፣ ደጃዝማች ተሰማ እርገጤ፣ ፊታውራሪ ታደሰ በላይነህ፣ ልጅ ከፈለው ወልደፃዲቅ፣ አቶ ፀሃይ እንቁ ፃዲቅ፣ አቶ ፀኃይ እንቁ ስላሴ፣ ራስ መስፍን ሽመልስ እና
ሌሎችም የጦር አለቆች ጦራቸውን በመያዝ በግራሩ ስር መሰበሰባቸውን የአካባቢው አባቶች ይናገራሉ፡፡

የወረዳው ባህልና ቱሪዝም መረጃ እንደሚያመለክተው በአካባቢው አንዲት ግራር እንጂ ሌሎች ዛፎች አልነበሩም።

ግራሯ 200 ዓመት እድሜን ያስቆጠረች ስትሆን የአካባቢው
ማህበረሰብ የሽምግልና፣ የስብሰባ እና የሌሎችም ማህበራዊ ክንውኖች ማስፈጸሚያ ቦታ ነበረች።

ከኢትዮጵያ አርበኞች ማህበር ምስረታ በኋላም ቦታዋ አንዲትግራር በሚል በየአመቱ ጥር አንድ ቀን ታስቦ ይውላል።

ምንጭ ፦ የወረዳው ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት
በጌትነት ተስፋማርያም
ፎቶሀዱሽአብርሃ

"ዘላለማዊ ክብርና ሞገስ ለኢትዮጵያ ነፃነት ሰማዕታት"

@yetarikdersan
ወራሪውን የጣሊያን ጦር ለመመከት አርበኞች ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰባሰቡባት ስፍራ “አንዲትግራር”
#የአሁንገጽታ

ፎቶ ሀዱሽ አብርሃ

@yetarikdersan
📜ራስ አሞራው ውብነህ ተሰማ ጋርድ
ማን ናቸው??📜

ጀግናው ራስ ውብነህ ተሰማ በጎንደር ክ/ሃገር በወገራ አውራጃ ቆላ መረባ በ1884 ተወልደው በአካባቢው ባህልና እምነት መሰረት ተኮትኩተው ያደጉና በኢትዮጵያዊነት ተጠምቀው
ለኢትዮጵያውያን የኖሩ ስመ፟-ጥር ጀግና ናቸው።

‘አሞራው’ የሚለውን ስያሜ ያገኙትም በፈጠራ የእውሸት ድርሰት ተጀቡነው
ሳይሆን ሃገራችን ኢትዮጵያ በፋሺስት ወረራ ስር በወደቀችበት በዚያ የጭንቅ ጊዜ እንደወርቅ በእቶን ውስጥ በዕውነት አልፈው ነው። ይህ ማንነታቸው ነው በትውልድ መካከል ሰብሮ የመግባት ብቃት ያጎናጸፋቸው!።

በጥቅምት ወር 1931 አ.ም የጠላት ጦር ከጎንደር ተነስቶ በለሳ ደረሰ።

አሞራው ውብነህን "ካጥጥ መጠበቂያ"ከተባለው ተራራ አካባቢ ገጠመው።የፋሽስት ጦርም ተደምስሶ የጦር መሪወቹ ከጥቂት ወታደሮች ጋር በመሆን ለማምለጥ ሲሞክሩ አሳደው
ያዙዋቸው።አሞራው ውብነህ ከበለሳው ጦርነት በሁዋላም
ሰሜን ጃንአሞራና ደረስጌ ማርያም የነበረዉን ጦር ለመግጠም ገሰገሱ። በዚህን ጊዜ በጠላት ጦር በድንገት ተከበቡ።

ጀግናው አርበኛ አሞራው ውብነህ ግን ከበባውን ሰብረው በመውጣት ለሕዝቡ እንዲህ አሉት "ያገሬ የሰሜን ሕዝብ አይዞህ እርዳኝ፣ተባበረኝ የተከበበ አውሬ አያምልጠን "።እንደገና
በጀግኖቻቸውና በሕዝቡ ማካኝነት በራሳቸውም ስልት ተጠቅመው ጠላትን አስከብበው መውጫ ቀዳዳ
አሳጡት።በዚህም ወቅት እንድህ ተብሎ ተገጠመላቸው፦

የሰማውን እንጃ ይሮም ገስገሰ፣
የጦሩ መድሃኒት አሞራው ደረሰ።
ያየህም ተናገር የሰማህም አውራ፣
ተገናኝቶ ዋለ አሞራው ካሞራ።
ጎንደር ከግንቡ ላይ ያለው ነጭ አንበጣ
ከምን ሊገባ ነው አሞራው ስመጣ።
የሚገርመው ደግሞ ራስ አሞራው ውብነው ከኢጣልያን ጋር
ሲያደርጉት በነበሩባቸው ጦርነቶች ሁሉ ከሁለትና ከሶስት ቀና በላይ አይቆዩም ነበር።አይፈጅባቸው ነበር።ብዙም ጊዜ ሳይወስዱ
አመድ ያደርጉዋቸው ነበርና።

ከ 1928-1934 አ.ም ከኢጣልያ
ሰራዊት ጋር ባደረጉት የላቀ የጀግንነት ተግባር 'አሞራው ' የሚል ቅፅል ስም ተሰጥቶቸዋል። ጣልያኖች "ካልታሰበና ካልተጠበቀ ስፍራ እየተገኘ አደጋ እየጣለ ጦራችንን በከፍተኛ ደረጃ
የሚያጠቃ አሞራ ነው" ይሉት ነበር ።

ጀግናው ራስ አሞራው ከጦር ሜዳ ዉሎ ጀግንነት በተጨማሪ በየስፍራዉ ነጋሪት እያስጎሰሙ "ለሀገር እና ለነፃነት ስትል ለፋሽስት ኢጣልያ እንዳትገዛ ፣ለሀገር ሙት ተጋደል"በማለት እያበረታቱ ማእረግም እየሰጡ የጠላትን ከንቱ ምኞትና ፖለቲካ ባጭሩ እንዲቀጭ አድርግዋል።

ለሀገሪቱ ለፃነት በብዙ አቅጣጫ የታገሉ ስመጥር አርበኛ ለሞሆን የበቁ ታላቅ ሰው ናቸው።

ራስ አሞራው ውብነህ።
በ 1933 አ.ም የኢትዮጵያ አርበኞች ከ እንግሊዝ ወታደሮች ጋር በመሆን ፋሽስትን በማስለቀቅ ጎንደር ደረሱ።ውጊያው ከፍተኛ ዋጋ አስከፈል። ለወራት የቆየ ውግያም ተካሄደ።

ጀግናው ውብነህና አርበኞቹ በ ህዳር 19 ቀን 1934 አ.ም ከፍተኛ ውጊያ
አድርገው ጀኔራሉንና ተከታዮቹን ለመማረክ በቁ ።

በዚህም ጊዜ እንዲህ ተብሎ ተገጠመላቸው፦
በአርማጭሆ መንገድ፣
በወገራ መንገድ፣
በስመንም መንገድ፣
በጨረባም መንገድ፣
በበለሳም መንገድ አይተላለፉ፣
አሞራው አርበኛ ይማታል በክንፉ።
የሮማን ነጭ በሬ ተከቡዋል በብረት ፣
ሊበላው ነው አሉ አሞራው ዞረበት።

ከነፃነት በሁዋላ አቶ አለማየሁ ደርቤ (በሁዋላ ደጃዝማች )፣ከንጉሠ ነገሥቱ ዘንድ ታዘው በታህሳስ ወር 1934
አ.ም ራስ አሞራው ዉብነህን ይዘው እንዲመጡ ወደ ጎንደር ተላኩ።

ራስ አሞራው ውብነህም በአዲስ አበባ የንጉሠ ነገሥቱ ልዩ ግምጃ ቤት በነበረው ህንፃ ላይ አንድ ክፍል ቤት
ተሰጥቶዋቸው እንዲቀመጡ ተደረገ።

በዚህም ጊዜ፣ከነፃነት መልስ የተዋጉለት አላማ ሌላ መልክ እንደነበረው ተረዱ፣በነገሮች ያዝኑና ይበሳጩም ጀመር።ይባስ ተብሎም
በአርበኝነት ዘመናቸው የተሰጣቸውን ራስነት ዝቅ በማድረግ ደጃዝማች እንዲሰጣቸው ተደረገ።

ራስ አሞራውም በዚህን ጊዜ
"እኔ አኮ የማእረግ ስም አልፈልግም ጠላት ያውጣልኝ ስም
'አሞራው' ብቻ ይበቃኛል" በማለት ተናገሩ።

በታህሳስ ወር 1937 አ.ም ልዑል ራስ እምሩ ኃይለስላሴ የበጌምድርና የሰሜን ጠቅላይ ገዥ ሁነው ተሾሙ ።

ራስ አሞራው ውብነህም የጠቅላይ
ግዛቱ "ዳይሬክተር "ተብለው በጥር ወር 1937 አ.ም ጎንደር ገቡ።

ራስ እምሩ ለአንድ ዓመት ያህል ከሰሩ በሁዋላ በምትካቸው ቢትወደድ አንዳርጋቸውን መሳይ መጡ ።

የወራሪው የጣልያን አብዛኛው የጦር መሳርያ ሰፍሮ የነበረው ጎንደር ላይ ነበር ። ታድያ ንብረቱ ተጭኖ ወደ ሌላ ስፍራ እንዲወሰድ ከበላይ ትእዛዝ ተላለፈ።

ራስ አሞራው ታድያ "ይሄ ሀብት ሲመዘበር ቆሜ አላይም " በማለት በገዛ ፍቃዳቸው ስራዉን ለቀው ወደ አዲስ አበባ ይሄዳሉ።ከተወሰነ ጊዜም በሁዋላ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል ሆነው እንዲሰሩ ይደረጋሉ ።

ስመጥሩው አርበኛም ለሀብትም ለሹመትም ሳይሆን ለሕዝብ መብት በመከራከር አዘዉትረው ይታትሩ ጀመር ። ለዚህም ዋጋ ከፍለዉበታል። በደርግ
ዘምን ያደርጉት የነበረው ማህበራዊ እንቅስቃሴ በበጎ ያልተመለከቱላቸው የጊዜው ባለስልጣናት በ ሻምበል መላኩ ተፈራ አማካኝነት መኖርያ ቤታቸው ከሙሉ ንብረቱ ጋር
እንዲወረስ አድርገዋል።

ራስ አሞራው ውብነህ በጠና ታመው በተወለዱ በ 94 አመታቸው መስከረም 5 ቀን 1975 አም ከዚህ ዓለም በሞት
ተለዩ።

የቀብራቸው ስነ ስርዓትም የአርበኞች መካነ መቃብር በሆነው በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተፈፀመ። ራስ አሞራው ውብነህ የፋሽስትን ጦር የሰማይ አሞራ ሁነው የዘነጠሉት ሰው
ናቸው።

ምንጭ; "ያልተዘመረላቸው ቅጽ ሁለት" የተቀነጨበ
ደራሲ ፍፁም ወልደማርያም

@yetarikdersan
………🗞🗞🗞………
ከያንያን ስለራስ አሞራው ከተናገሯቸው መካከል፦

የሰማውን እንጃ ይሮም ገስገሰ፣
የጦሩ መድሃኒት አሞራው ደረሰ።
ያየህም ተናገር የሰማህም አውራ፣
ተገናኝቶ ዋለ አሞራው ካሞራ።
ጎንደር ከግንቡ ላይ ያለው ነጭ አንበጣ
ከምን ሊገባ ነው አሞራው ሲመጣ።

አሞራው ማን ነው? በሚል ርዕስ( ነጋ አባተ) ከ1997ምርጫ ሁለት አመት ቀደም ብሎ የተሰራውን ተውኔት ያዩ አርበኞች እና ጥበበኞች ስለጀግናው ከተናገሩት የተወሰደ፦

“ያቀረብክልን ቲአትር ከአንቀላፋንበት የሚያነቃንና ኢትዮጵያዊነት
ጥያቄ ውስጥ በወደቀበት በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያዊነታችንን አደመቅከን..
” ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ።

“ራስ አሞራውን አውቃቸዋለሁ ጥሩ ኢትዮጵያዊ ነበሩ በዚህ ባለንበት ጊዜ ሆነን የአባቶቻችንን ስራ ስንመለከት ደግሞ የተለየ ትርጉም አለው። ባጭሩ ያባቶችን ስራ ለአዲሱ ትውልድ
በማስተዋወቅ ረገድ ትልቅ ስራ ተሰርቷል።
” የተከበሩ የዓለም
ሎሬት ሜተር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ።

“ጸጋዬ ሞተ ብዬ አዘንኩ ለምን? ደፋር ጸሃፊዎች አይኖሩንም ብዬ ይህን ተውኔት ስመለከት ግን አሁን ጸጋዬ ቢሞት አይቆጭኝም ለካስ ተተኪ ትውልድ ማስነሳት ችለናል ብዬ
ተደሰትኩ..
” አርቲስትና ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሰሰ

“በተለይማ መዝጊያው መዝሙር የኢትዩጵያ ህዝብ መዝሙር
ቢሆን ብዬ ተመኘሁ…
” ጸሓፊ ተውኔት አያልነህ ሙላት

“ለካስ ኢትዮጵያዊነት አልሞተም እኔም በአንተና አብረውኽ
በሚሰሩት አርቲስቶች ኮራሁ.
” ድምፃዊ ታምራት ሞላ

"ዘላለማዊ ክብር እነሱ ወድቀው እኛ ቀና ብለን እንድንናገር ለተሰው ሁሉ"

@yetarikdersan
📜ቢትወደድ መንገሻ ጀምበሬ ማን ናቸው?📜

በ አፄ ሀይለስላሤ ዘመነ መንግስት የተለያዩ የማዕረግ ስሞች የነበሩ ሲሆን በደረጃ ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ ባላምባራስ፣ ግራዝማች፣ ቀኛዝማች ፣ደጃዝማች፣ ፊታዉራሪ ፣ቢትወደድ፣ ራስ ፣ራስ ቢትወደድ፣ ንጉስ፣ንጉሰ ነገስት ዐፄ በመባል ይሰየሙ ነበር።

በወቅቱ የጎጃም አካባቢ ግዥዎች
ቢትወደድ መንገሻ ጀምበሬ ፣ቢትወደድ
ነጋሽ በዛብህና ቢትወደድ አያሌዉ መኮነን ነበሩ። የእነርሱ የበላይ የነበሩት ደግሞ ራስ ሀይሉ በለዉ ነበሩ።

በሜጫ ጉታ አካባቢ የተወለዱት ቢትወደድ መንገሻ ጀምበሬ የራስ
ሀይሉ በለዉን ልጅ ወሮ ሰብለወንጌል ሀይሉን አግብተዉ ይኖሩ ነበር።

በ1928 ዓ.ም ጣሊያን ኢትዮጲያን ስትወር በልዑል ራስ እምሩ ሀይለስላሴ ዋና አዝማችነት ደጃዝማች መንገሻ ጀምበሬ የሜጫን አርበኛ ይዘዉ ከኢትዮጲያን አርበኞች ጋር በመሆን ወደ ሽሬ ዘምተዋል።

በሰዓቱ የኢትዮጲያ ጦር ድል አልቀናዉም ነበርና ወደ ሀገራቸዉ
ተመለሱ።

ቀጥሎም በ1929 ዓ.ም ጣሊያናዊዉ ካፒቴን ኮርቦ ባህርዳርን ያስተዳድር በነበረበት ጊዜ ደጃዝማች መንገሻ
ጀምበሬ፣ደጃዝማች ስብሀቱ ይግዛውን የይልማና ዴንሳ ጦር አዝማች፣ፊታዉራሪ መኮነን ዋሴና ሌሎችም ወደ ባህርዳር ካስጠራ በሗላ ፣ ደጃዝማች ስብሀቱ ይግዛውን ከነልጃቸዉና ፊታዉራሪ መኮነን ዉቤን ሲሰቅሏቸዉ፣ ደጃዝማች መንገሻ
ጀምበሬን ግን እዚያዉ ባህርዳር ከተማ እንዳይለቁ በሚል የቁም እስረኛ አደረጋቸዉ።

በዚህ ወቅት የሰከላ፣የፋግታ፣የሜጫ፣የአገዉ ምድርና የ አቸፈር ህዝብ በደብቅ ተሰብስበዉ የጣሊያንን ጦር ለማጥቃት ይነጋገሩ ነበር።

በመጨረሻም በስብሰባዉ ደጃዝማች መንገሻ ጀምበሬን የጦር መሪ አድርገዉ ለመዋጋት ወስነዉ ሽማግሌዎቹ ሄደው እንዲነግሩት ተደረገ። ደጃዝማች መንገሻ ጀምበሬም በሀሳቡ ተስማምተው ካፒቴን ኮርቦን
ስላመመኝ ሄጀ ፀበል እንድጠመቅ ፍቀድልኝ በማለት ካነጋገሩት በሗላ በዋስ አስፈቅደው ወደ ሀገራቸው ተመለሱ። ከዚያም ውስጥ ለውስጥ ጦራቸዉን ካደራጁ በሗላ በግልፅ
ሸፈቱ።ቀጥሎም ጣሊያንን ድል ነስተው
ከተመለሱ በሗላ በዐፄ ሀይለስላሴ ተጠርተዉ የቢትወደድነት ማዕረግ ተሰጣቸው።በመቀጠልም የጎጃም
ክፍለሀገር ምክትል ገዥ ሆነው እያስተዳደሩ እያለ ወደ አዲስአበባ ተዛውረው የህግ መወሰኛ ምክርቤት ሀላፊ ሆነው ሲሰሩ ቆዩ።

ከዚያም የወለጋ ክፍለሀገር ገዥ ሆነው በመስራት ላይ እያሉ ባደረባቸው ህመም ምክኒያት በ 1942 ዓ.ም
ከዚህዓለም በሞት ተለዩ።

በዳንግላ ከተማ በስማቸው
የተከፈተላቸው ትምህት ቤት እሁድ
ሚያዚያ 21/2012ዓ.ም 77 ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ያከብራል !!

ምንጭ
ቢትወደድ መንገሻ ጀንበሬ ት/ቤት

@yetarikdersan
በስማቸው የተሰየመው የዳንግላ መሰናዶ ት/ቤት

@yetarikdersan
📜የባላምባራስ ሻህእርገጥ
ስለአድዋ ጦርነት የዓይን
ምስክርነት 📜

ባ፲፰፻፸፱ ዓ ም ታኅሣሥ ፳፱ ቀን ጃንሆይ አጼ ምኒልክ ሐረር ጨለንቆ አሚር አብዱላሂን ድል አድርገው ወዲያው ባላምባራስ መኰንን ነበሩና ደጃዝማች ብለው ሐረርን ሾሟቸው።

በ፲፰፻፹፩ ዓ ም አጼ ዮሐንስ ጐጃም ነበሩና ጐጃምንና ሸዋን ለመውጋት ስላሰቡ ደጃዝማች መኰንን ከሐረር
ታዘው አዲሳበባ ወጥተው ግንደበረት ተቀምጠው በዚያ በኩል አጼ ዮሐንስ ወደሸዋ እንዳይመጡ ይጠባበቁ ነበር።

አጼ ዮሐንስም መምጣቱን ትተው ወደመተማ ደርቡሽን ሊወጉ ሄዱ። ከዚያው ከጦርነት መጋቢት ፩ቀን ባ፲፰፻፹፩ ዓ ም ሞቱ።

በዚሁ ቀን ደጃዝማች መኰንን ካጼ ምኒልክ ጋራ ወደሐይቅ ሄደው ሲመለሱ በግንቦት ወር እኔ ሻህ እርገጥ አሽከር ሆኜ ከደጃዝማች መኰንን ጋራ ወደሐረር መጣሁ።

በ፲፰፻፹፩ ዓ ም ሰኔ ፲፪ ቀን ቡርቃ አደርን። ሰኔ ፲፫ ቀን በሮዳ ገባን።
ታቦቱ ጊዮርጊስ ነበረና ሰኔ ፲፯ ቀን እኛው መገበርያውን ፈጭተን ተቀደሰ። መተከሉም በዚሁ ቀን ነው። . . . .

ወዲያው ሐምሌ ፭ቀን ወደኢጣልያ አገር ሮማ ሔዱ። በ፲፰፻፹፪ ዓ ም በግንቦት ከኢጣልያ አገር በምጽዋ
ተመልሰው ጃንሆይ አጼ ምኒልክ ቦሩ ሜዳ ድረስ ሄደው ከዚያ ተገናኝተው ጨርጨርን የራስ ዳርጌንና የደጃዝማች
ወልደ ገብርኤልን አገር በሐረር ላይ ጨምረው ራስ መኰንን ብለው ሾሟቸው።

ከዚህ በኋላ ደጃዝማች ሥዩምን ይዘህ ወደሐረር ሂድ ብለዋቸው ይዘው ወደሐረር ሲመጡ ጨርጨር ሐርዲም ሲደርሱ አሩሲ ከድቶ የራስ ዳርጌን አሺከሮች ፈጃቸው ቢሏቸው ደጃዝማች ሥዩምን በ፲፰፻፹፪ ዓ ም በሐምሌ ወር ለቀኛዝማች ወንድ ይራድ እሰር ብለው ሰጥተዋቸው ራስ መኰንን ወደአሩሲ ዘመቱ።

በ፲፰፻፹፫ ዓ ም ለመስቀል ሐረር ገቡ።
ከዚህ በኋላ ባ፲፰፻፹፰ ዓ ም መስቀልን ውለው ጣሊያንን ለመውጋት አጼ ምኒልክ ራስ መኰንን ግምባር አድርገው ተነሱ። እኛም አሽከሮቻቸው ከጌታችን ከራስ መኰንን ጋር ዘመትን።

የኅዳር ሚካኤል የጁ አላ እጅረት አደርን። ከዚያ ተነስተን ጐሊማ አደርን። ከዚያ ተነስተው መቃ ወሀ አደሩ።

ከመቃ ወሀ ተነስተው አላማጣ እሚባል ዳገት ጐራው አላስኬድ ብሎ ግማሹ አሸንጌ ባሕር ሰፈር ሆነ፤ ግማሹ
በየገደሉ አደረ።

ኅዳር ፲፰ቀን ረቡዕ በ፮ ሰዓት ራስ መንገሻ ጣሊያኖች እየተከተሉ ራስ መንገሻ ወደኛ ሲመጡ ራስ መኰንን ሰፈር ደረሱ። ከራስ መኰንን በተገናኙ ጊዜ እንዲህ ብለው አሸለሉ፤ ለየጁ ለጐንደር ለወሎ ለጐጃም ብነግረው ጩኸቴን ዝም አለኝ።

ከባሕር ዳር መጥቶ መኰንን አዳነኝ።
፪ኛ እንዲህ አሉ፤ እሪ በሉ ትግሮች እሪ በሉ፤ ለየጁ ንገሩ። የጆች እሪ በሉ፤ ለጐንደር ንገሩ።

ጐንደሮችም ጩሁ፤ ለወሎ ንገሩ።
ወሎች እሪ በሉ፤ ለጐጃም ንገሩ።
ጐጃም እሪ በሉ፤ ከክስክሱ ብረት ሐረር ለቃኘው ንገሩ። እሪ በሉ ሐረጌዎች፤ እሪ በሉ፤ ለንጉሠ ነገሥት ለዳኛው
ንገሩ። ይቆጣ የለሞይ ሲሰማ ላመሉ።

ከዚህ ወዲያ ያባ ቃኘው (= የራስ መኰንን) አሽከሮች እየታጠቁ ከሰፈር ተነስተው ወደጣሊያኑ ሲሄዱ ሰፈር አድርጐ ፍየልና በጉን አርዶ ቆዳውን ሳይገፍ የራስ መኰንን አሽከሮች ቢደርሱበት ትቶ ሸሸ። ከዚያ በኋላ ተከታትለው አባረው ወደሰፈር ተመለሱ። ፲ ቀን ያህል ቆይተው ራስ መኰንን የጦር አበጋዝነቱ የሳቸው ነበረና በውስጣቸው እነራስ ሚካኤልና እነራስ ወሌ፥ እነራስ ወልዴ፥ እነፊታውራሪ ገበየሁ፥ እነፊታውራሪ
ተክሌ፥ እነአድነው ጐሹ ነበሩ። ኅዳር ፳፰ ቀን አምባ አላጌ ከማጆር ቶዞሊ
(= Toselli) ጋር ጦርነት ሆነ።

የሰፈረበት ቦታ ቤተ ክርስቲያን አጠገብ ነበረና እኔም ከጌታዬ ከራስ መኰንን ከጦርነቱ ነበርሁና ከቤተ ክርስቲያኑ
ውስጥ ዱቄት ማስቀመጫ በግና ፍየል ማሰሪያ አድርጎት ጽላቱን ከዱቄቱ ማስቀመጫ ስር እኔ ሻህ እርገጥ አግኝቼ ጽላቱም ጊዮርጊስ ነበረ ድል ከሆነ በኋላ አንስቼ ላቶ ውበቴ ብነግራቸው ለምዳቸውን አውልቀው ሰጥተውኝ በዚያ ሸፍኜ ይዤ አቶ ውበቴ ለራስ መኰንን ነገሩ። ራስ መኰንንም እኔን አስቀርበው እንደምን አገኘኸው ብለው ጠየቁኝ።

ጣሊያን ዱቄት እሚያስቀምጥበት ስር ነው አልኳቸው። የክርስቲያን ምልክቱ ይህ ነው ብለውኝ፥ ይኸው ያነሳኸው ታቦት ቅዱስ ጊዮርጊስ ይጠብቅህ ብለውኝ፥ ቀኛዝማች ኃይለ ማርያም የእሚባል ትግሬ ራስ መኰንን ሳይደርሱ ጣሊያኖች ማርከውት የነፍስ አባቱ ከራስ መኰንን ጋር ሰይፋቸውን አንግተው ተሰልፈው ቆመው ነበርና፥ ይኸው የኔ አሽከር ጣሊያን እንዳለወገን አድርጐ ያረመኔ ሥራ ሠርቶ ታቦቱን ጥሎ የፍየልና የበግ ማሰሪያ የዱቄት ማስቀመጫ አድርጐት አንስቶ አምጥቶታልና ወደፊታችን ወዳለው ቤተ ክርስቲያን እንዲያገቡት
ይቀበሉት ብለዋቸው ተቀብለውኝ እንጣሎ ሚካኤል ወስደው አስገቡት።

ማጆር ቶዞሊ ሲሸሽ ፊታውራሪ አባ ውርጂ የተባሉት ደርሰውበት ተናንቀው ሁለቱም ገደል ገብተው ሞቱ። አንድ
ወታደር ሁለቱንም ገፏቸው ለራስ መኰንን ግዳይ ሊጥል እየፎከረ ሲመጣ በሕይወቱ የተማረከ ጣሊያን ከራስ መኰንን አጠገብ ነበረና ይህ ባርኔጣ የማጆር ቶዞሊ ነው ብሎ ቢነግራቸው ያንን ቦታውን ታውቀዋለህ ቢሉት አወን አውቀዋለሁ ቢል ሂድና አሳይ ብለውት ሰው ታዞ የሁለቱ
ሬሳ መጥቶ መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ተቀበረ።

ኅዳር ፳፱ ቀን ነው። ታኅሣሥ ፩ቀን ካላጌ ተነስተው እንጣሎ ሰፈሩ። ከዚያ
ተነስተው እንደርታ ሰፈሩ። ፳፮ ቀን እንደተቀመጡ ጃንሆይ አጼ ምኒልክ ጨለቆት ሰፈሩ። ታኅሣሥ ፳፰ቀን ገና ሆነ። ፳፱ ቀን ራስ መኰንን ወደጃንሆይ ሲሄዱ እኔ አብሬ ሄጄ ነበረ።

ከተገናኙ በኋላ የጣሊያን ዘበኞች
(=ወታደሮች) ከምሽግ ውጪ ተቀምጠው ነበርና ጃንሆይ አጼ ምኒልክ ራስ መኰንንን ሰው ላክ ብለዋቸው ቀኛዝማች ዋቄ ገድልን፥ አቶ ጋባዥን፥ አቶ ተገኔን፥ አቶ ስለሺን፥ አቶ ወዳጆን አዘዋቸው ሲሄዱ እኔም ካለቃዬ ጋር ሄጀ አቶ አይተንፍሱ፥ አቶ መሸሻ አሽከሩ አፈሳን ልከው
ዘበኛውን (= ወታደሩን) ካስነሱ በኋላ ከምሽጉ ገብቶ ከውጭ አንድ የዘበኛ መጠበቂያ ቤት ነበረና ከዚያ ውስጥ ድማሚት ቀብሮ ኖሮ እዚያውም ውስጥ እቃ ኖሮ ያንን ሲሻሙ ከምሽጉ ሆኖ ቢተኩስ ድማሚቱ ተነስቶ ባሻ ወልደ መስቀል አሽከሩ አፈሳን ሁለት ወታደሮች አራቱ ሞቱ፤ ፯ወታደሮች
ቆሰሉ። ከዚህ በኋላ ፊታውራሪ ኮላሴንና ፊታውራሪ ደስታ ሣህሉን ልከው ለነሱ አስረክበን ወደሰፈር መልስ ሆነ።

……ይቀጥላል……
ከዚህ በኋላ በተራ ሲጠበቅ ሰንብቶ ጥር ፫ቀን መቀሌ ራስ መኰንን አሽከሮቻቸውን ይዘው ሌሊት ምሽጉን ሊሰብሩ የሄዱ እለት እኔም አብሬ ሔጄ ምሽጉን መስበር አቃተ።

ሰዋችንም አለቀ። ብዙ መኳንንቶች ብዙ ወታደሮች አለቁ። እነቀኛዝማት በሻህ፥ እናቶ መሸሻ ሞቱ። ሬሳ ማንሳት ከልክሎ በ፰ኛው ቀን ተቀበሩ። እኔም ደገፉ የእሚባል ባልንጀራዬ በጥይት ሞቶ እሱን አነሳለሁ ብዬ ቆሰልሁ።

ጣሊያኖቹ ውሀ ተይዞባቸው የሚጠጡት አጥተው ሊያልቁ
ቢሆን እግዚኦ ብለው በዘበኛ በፊታውራሪ ደሳለኝ እየተጠበቁ ጉዞ ሆነ። ወደአውዜን አብርሃ ወአጽብሐ
ወደእሚባለው ስንደርስ ወደዋናው ወደጀኔራል ባኅርይ (Baratieri) ተቀላቀል ብለውት ሄዶ ተቀላቀለ።

ጃንሆይ አጼ ምኒልክ ከነሠራዊታቸው ወርን ተሻግረው አደሩ። ከዚያ ተነሥተው ፈረስ ሜዳ ሰፈሩ። ከፈረስ ሜዳ ተነስተው ገንደብታ ሰፈሩ። ከዚያ ተነስተው ራስ ሀጐስና ራስ ስብሐት ከጣሊያን ከድተው ወደራስ መኰንን ሰፈር ገቡ። ራስ መኰንን ታመው አጼ ምኒልክ ሰፈር ውለው ነበረና የራስ መኰንን ዘበኞች ወደአጼ ምኒልክ
ወሰዷቸው።

፰ቀን ያህል እንደተቀመጡ የካቲት ፲፬ ቀን ወደአድዋ ጉዞ ሆነ። ፲፭ ቀን አድዋ ሰፈር አደረጉ። የካቲት ፲፮ ቀን እሁድ
ራስ መኰንን ወደአስመራ ሊሄዱ ወደመረብ ጉዞ ሆነ።

ወዲያው ወደጃንሆይ ጣሊያኖች መጥተውባቸው ኖሮ መንገዱ ጐራ ነበረና ግማሹ ሰፍሮ ግማሹ ሲጓዝ የአጼ ምኒልክ መላእክተኛ መጥቶ የካቲት ፲፯ቀን መልስ ሆነ። አዷ ተመልሰው ሰፈሩ።

የካቲት ፲፰ቀን ሠራዊቱን ሽሬ ወደእሚባል አገር ዘረፋ ሰደዱት። የካቲት ፳፫ቀን እሁድ ግማሹ ገብቶ ግማሹ ሳይገባ መኳንንቱም አክሱም ጽዮን ሄዶ ነበርና ይኸንኑ አሰልሎ ጣሊያን ለጦርነት ተሰልፎ መጣ።

ያጼ ምኒልክ እድልና የኢትዮጵያ አርበኛ በእግዚአብሔር ኃይል ቅጽበት አልቆየም፤ ወዲያው ድል ሆነ።ንጉሠ
ነገሥቱም አርበኞቹም በደስታ ተመለስን።

ከዚህ በኋላ እስከ ፲፭ ቀን ቆይተን ወደሸዋ መልስ ሆነ። የጸሎተ ሐሙስ እንጣሎ ሰፈርን። የስቅለት እለትም አላጌን አልፈን ሰፈርን።

የቅዳሜ ስዑር እለት ወፍላ አሸንጌ ስር
ሰፍረን ትንሣኤን እዚያ ዋልንና ከዚያ ተነስተን መርሳ በእሚባል አገር ሰፈርን። እዚያ ታምሜ ቀረሁ። ባ፲፭ ቀን በጐ ሆኘ ፩ግንቦት ልደታ ደሴ ዋልሁ።

አጼ ምኒልክና ራስ መኰንን በጨፋ ከንቦልሻ ወደሸዋ ገቡ። እኔ የማውቀው እስከዚህ ድረስ ነው።

ሻህርገጥ እረኛው።

ምንጭ ፕ/ ር ጌታቸው ኃይሌ በethiopianregister ገጽ ላይ እንደፃፋት

@yetarikdersan
ፕ/ ር ጌታቸው ኃይሌ

@yetarikdersan
📜ደጃዝማች በቀለ ወያ(ሻቃ በቀለ)📜

በቀለ ወያ ከአባታቸው ወያ ኦብሴና ከወይዘሮ ብርቄ ጂሎ ጎዳና ነሐሴ 21 ቀን 1902 ዓ.ም በደቡብ ሸዋ ሶዶ ውስጥ ልዩ ስሙ ጎጌቲ ሲብስቶ በሚባል መንደር ተወለዱ፡፡ የዐማርኛ ት/ትን እቤታቸው ድረስ አስተማሪ ተቀጥሮላቸው አጠናቀቁ፡፡ በቀለ
በአባታቸው የሶዶ ጉራጌ (ክስታኔ) ሲሆኑ በእናታቸው ደግሞ ኦሮሞ ናቸው፡፡ በቀለ የ16 ዓመት ልጅ ሳሉ እናታቸው ከአጎታቸው ገ/ማርያም ጋሪ ዘንድ አኖሯቸው፡፡ በቀለም እንዳደጉ
የአጎታቸው እልፍኝ አስከልካይ ሆኑ፡፡

ደጃዝማች ገብረማርያም ከ1923 - 1926 ዓ.ም ድረስ የሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት እንደራሴ ሳሉ በቀለ ወያ ሻቃ የሚል የማዕረግ ስም ተሰጣቸው፡፡ በዚህም በረዳት ወታደርነትና በአስተዳደር ሥራ ላይ ተሰማርተው
ቆይተዋል፡፡

በ1927 ዓ.ም ደጃዝማች ገ/ማርያም የአገር አስተዳደር ሚኒስቴር ተብለው ሲሾሙ አብረዋቸው ወደ አዲስ
አበባ በመምጣት የታንክ መስበሪያ መሣሪያ አጠቃቀምን ለማጥናት በቁ፡፡

በ1928 ዓ.ም ፋሽስት ኢትዮጵያን ለመውረር ሲመጣ መጀመሪያ ወደ ሰሜን፥ ቀጥሎ ደግሞ በንጉሠ ነገሥቱ ታዘው ወደ ሲዳሞ በመሄድ በአጎታቸው ሥር ያለውን ጦር በመምራት ከፍተኛ
ጀብዱ ፈጽመዋል፡፡ ስለዚህ ሁኔታ ታደሰ ዘወልዴ ቀሪን ገረመው በተባለው መጽሐፋቸው እንዲህ ከትበዋል፦

“የጠላት ታንክ ወገንን በማጥቃቱ ደጃዝማች ገ/ማርያም ጋሪ በጣም ያዝኑ ነበር፡፡ አንድ ቀን አምስት ታንኮች በመደዳ ሆነው ጦሩን እያጠቁ ሲመጡ ‘በቀለ፥ ያንተ ብልኀት ለመቼ ሊሆነን
ነው ! አትለውም ወይ ! ወይኔ !’ እያሉ ደጃዝማች ገ/ማርያም ጋሪ ሲያዝኑ በቀለ ዝም ብሎ ይመለከት ነበር፡፡ ታንኮቹ ጠጋ ብለው በደንብ ሲታዩት በመድፍ የመጀመሪያውን አኮማተረው፤
ደግሞም የኋለኛውን ደገመው፡፡ እንደዚሁ በ5 ደቂቃ አምስቱንም
ታንክ አቃጥሎ ሲነድዱ፥ ‘ደጃዝማች ! ሄደው እሳት ይሙቁ’ አላቸው፡፡”

ሻቃ በቀለ የደጃዝማች ገ/ማርያም ጋሪ ጦር የመድፍ ክፍል ኃላፊ ሆነው በማገልገልና በሲዳሞ የጦር ግንባር ግንቦት 9 እና 11 ቀን 1928 ዓ.ም የደጃዝማች ገ/ማርያምን ጦር ለመውጋት የመጣውን ወራሪ ግንባር ገጥመው በመደምሰስ የጠላትን ጦር
መሣሪያ ማከማቻ አውድመዋል፡፡

በዚህ ጥረታቸው ከአጎታቸው
ገ/ማርያምና ከባልደረቦቻቸው ምስጋና ሲቸራቸው፥ በጦርነቱ ደግሞ ስምንት ባለ ውሃ ከባድ መትረየስና ዐሥራ አራት ቀላል ድግን አልቤን መትረየስ ሲማረክ፥ ሠላሳ የጣሊያን መኰንኖችና
በቊጥራቸው የበዙ የጠላት ወታደሮች ተደባይተዋል፡፡

ከዚያ በኋላ ከሰኔ 1 ቀን 1928 ዓ.ም እስከ መስከረም 23 ቀን 1929 ዓ.ም ብዙ ጦርነት ሲካሄድ፥ ከእነዚህ ዋነኛው የደባ ስሬ ጦርነት ነበር፡፡ በዚህ ጦር ደጃዝማች ገ/ማርያም ጋሪ ቢቆስሉም
ሻቃ በቀለ ደግሞ ከ12 በላይ ታንኮችን በመድፋቸው በማውደም የማይረሳ ታሪክ ሠርተዋል፡፡

በኅዳር ወር (13 - 19) ቀን 1929
ዓ.ም ድረስ በአለታ ወንዶ አካባቢ ተፈሪ ኬላ በተባለው ቦታ፥ ጥር 12 1929 ዓ.ም ደግሞ አርቤጎና ላይ፥ ጥር 15 ቀን 1929 ዓ.ም በደኤላ ጭሪ፥ ጥር 19 ቀን 1929 ዓ.ም በሂበኖ አሩሲ፥ የካቲት 5፥ 10 እና 11 ቀን 1929 ዓ.ም በላቂ ደንበል የፈጸሙት ድል ከቶውኑ አይረሳም፡፡

አጎታቸው ደጃዝማች ገ/ማርያም በየካቲት 13፥ 1929 ዓ.ም ጎጌቲ በነበረው ከባድ ጦርነት ሕይወታቸው አለፈ፡፡ በዚህም ሻቃ በቀለ በጣም አዘኑ፡፡ ሙሉውን ጦር በመረከብ ከአክስታቸው የወ/ሮ ቡኔ በዳኔ ልጅ ከነበሩት በዳኔ ጉደታና ከሌሎች አርበኞች በመመካከር ወታደራዊ ትጥቃቸውን አጥብቀው በትውልድ
ሀገራቸው ሶዶ ጠላትን ተቋቁመዋል፡፡

……ይቀጥላል………
………ከላይ የቀጠለ………

በዚሁ መሠረት ጦራቸውን በማደርጀት በየካቲት ወር 1930 ዓ.ም በሶዶና ሜጫ ወሰን ላይ ሁለት ባታልዮን የጠላት ጦር ገጥመው በድል ደምስሰዋል፡፡

በዚያው ጊዜ በአገምጃ ያካሄዱት
ጦርነት ከጧቱ 12 ሰዓት እስከ 9 ሰዓት ድረስ ለ10 ሰዓታት ያህል በአይሮፕላንና በመድፍ የመጣውን ጠላት ገጠሙ፡፡ በጦርነቱ ብዙ የሶዶ ጀግኖች ተረፈረፉ፡፡ ሆኖም ድሉ የርሳቸው ነበር፡፡ ይህን ጀግንነታቸውን የሰማ የሶዶ ሕዝብ በጅምላ ይጎርፍ
ጀመር፡፡ በሶዶ ቶሌና በረጲ ጦርነትም የሻቃ በቀለ ጦር የጠላትን ጦር ድል እየመታ ስለቀጠለ ጣልያን ፈርቶ ለ6 ወር ያህል ርቆ ሊቆይ ተገደደ፡፡ በሶዶ አጨበር፥ ቁሻትና ኢቲኒ ላይ ለ8 ሰዓት
ያህል የተፋፋመ ጦርነት ተካሂዶ ድሉ የሻቃ በቀለ ሠራዊት ነበር፡፡ በተጨማሪም በሶዶ ጫከ ደራራ፥ አገምጃ፥ በሶዶና በወለኔ ወሰን ላይ የሲ፥ ኦሞ፥ ጎደብ በተባሉ ቦታዎች አንጸባራቂ ድል ተጎናጽፈዋል፡፡

በወርኃ መስከረም 10 ቀን 1932 ዓ.ም ሶዶ ባንቱ በተባለ ቦታ ለ7 ሰዓታት ያህል ተዋግተው ድል በማድረጋቸው የሶዶ ሕዝብ በኩራት እንዲመካባቸው አስችሏል፡፡

አጎታቸው ከሞተ ወዲህ ሻቃ በቀለ ከጎረቤት አርበኞች ጋር ኅብረት መፍጠር ጀመሩ፡፡ በተለይም ከዘመዳቸው ገረሱ ዱኪ ጋር ተባብረው ጠላትን የመደምሰስ ዕቅድ በማውጣት ብዙ መክረዋል፡፡ በጋራም የጠላትን ጦር ይደመስሱ ነበር፡፡ ከገረሱ ዱኪ ጋር በበዳና አቄሮና ሶዶ ከፍተኛ ጦርነት ውስጥ ተዋግተዋል፡፡

ለዚህ ጦርነት ምክንያቱ ሙሴ ቀስተኛ የተባለ የጣልያን መልእክተኛ ነበር፡፡ ሙሴ ቀስተኛ ገረሱን ለማጥመድ
የተላከ ስለነበር በገረሱ ተነቅቶበት የሞት ውሳኔ ተበይኖበታል፡፡ ይህንን አስመልክቶ ጠላት የሙሴ ቀስተኛን ደም ለመበቀል ከጅማ፥ ከሲዳሞ፥ ከሐረር፥ ከአርሲና ከሸዋ ጦር አሰባስቦ
የገረሱን ጦር በመውጋት ከፍተኛ እልቂት አስከተለባቸው፡፡ ገረሱ
ሸሽተው ከሻቃ በቀለ ጋር በመገናኘት ለሦስት ቀንና ሌሊት አርባ አራት ባታልዮን ይገመት ከነበረ ጦር ጋር በጣም ዘግናኝ የሆነ ጦርነት ተፋልመዋል፡፡ በአይሮፕላንና መድፍ ብዙ ሠራዊት አለቀባቸው፡፡ መሣሪያቸውም በምርኮ ተወሰደ፡፡ ሻቃም ቀኝ እጃቸው ስለቆሰለ መድፍ እንደልብ ባለመተኮሳቸው ጦርነቱ
ለጊዜው ቆመ፡፡ በዚህ ምክንያት ጦሩ ተበተነ፡፡ በቀለም እስኪያገግሙ ድረስ ሸዋ ቡልጋ ሄደው ከአበበ አረጋይ ጋር
ተነጋግረው የጦር ስልት ነድፈዋል፡፡ መክረውም ወደ ሶዶ ተመልሰዋል፡፡

መጋቢት 17 ቀን 1932 ዓ.ም ሻቃ በቀለ ከቀኛዝማች በየነ ጉደታ ጋር ሳሉ ከጠላት ወገን ደብዳቤ ደረሳቸው፡፡
የደብዳቤውም መንፈስ እጅ ብትሰጡ ይሻላችኋልና አስቡበት የሚል ነበር፡፡ እነርሱም በደብዳቤው ድፍረት በሽቀው ትግላቸው የነጻነት መሆኑን በመድፍ መልስ ላኩላቸው፡፡ ስለዚህ መስከረም
22፥ 1932 ዓ.ም ጦር ተከፈተ፡፡ ሶዶ ውስጥ ረጲ የተባለ ቦታ ከቀኑ 2 ሰዓት ጀምሮ ከባድ ጦርነት ተፋፋመ፡፡ ብዙ የሻቃ በቀለ ጦር እየፎከረ በጀግንነት አለቀ፡፡ ቀኛዝማች በየነ ጉደታም
ቆስለው ወዲያውኑ እናታቸው ሀገር ሶዶ አገምጃ እንዲሄዱ ተደረገ፡፡ እዚያም ሳሉ የመግደል ሙከራ ገጠማቸው፡፡ ሸሽተውም ገረሱ ዱኪ ጋር መጡ፡፡ ቁስላቸውም ሲድን ወደ
በቀለ ወያ ለመሄድ መንገድ ሳሉ ጠላት ከበባቸው፡፡ በዚህም ከጠላት ወገን 20 መኰንኖችና ከ30 በላይ ወታደር ገድለው መሥዋዕትነት ሆነው አለፉ፡፡ አብረዋቸው የነበሩ ስድስት አርበኞችም አለቁ፡፡ ሻቃ በቀለ ልባቸው ክፉኛ አዘነ፡፡ ልባቸው ቂም አርግዞና ውስጣቸው በበቀል ሲናጥ ውሎ ሚያዝያ 23 ቀን 1932 ዓ.ም ዝቋላ ላይ በልዩ የጦርነት ስልት የጠላትን ሬሳ
አነባብረው የወንድሞቻቸውን ደም ተበቀሉ፡፡

ግንቦት 27 ቀን 1932 ዓ.ም ደግሞ ዝቋላ ወንበራ ሌላ ጦርነት አድርገው ድልን ተቀዳጅተዋል፡፡

በኮሎኔል አቡ የተባለውን በጣም ከባድ የተባለውን ጦር ገጥመው 26 የፋሽስት መኰንኖችና 60 ወታደሮች ገድለዋል፡፡

ታደሰ ዘወልዴ ጦርነቱን እንዲህ ሲሉ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፦
“በ18 ካሚዮን የነበሩትን ፋሽስቶች አንድ ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ጨረሷቸው፡፡ ወዲያውኑ አስክሬናቸው በፍጥነት ወደ ነበሩበት ካሚዮን እንዲሰበሰብ ከተደረገ በኋላ ናፍጣ
አርከፍክፈውና በእሳት አቀጣጥለው ሌሊቱን እንደጧፍ ሲነድ አደረ፡፡”

ይህን የሰሙ ፋሽስቶች ላብ አሰመጣቸው፡፡ በጎጃም በላይ ዘለቀ
የተፈራውን ያህል በሶዶ ደግሞ በቀለ ወያ በጠላት ወገን እጅግ ተፈሩ፡፡

ጣልያንም የሻቃ በቀለን ሠራዊት ላንዴ ሊደመስስ ብዙ የባንዳ ሠራዊትና ነጭ ወታደሮችን ከጅማ፥ ከሲዳሞ፥ ከናዝሬት፥ ከወሊሶ፥ ከአዲስ አበባ፥ ከአርሲ አሰባስቦ ቶሌ በተባለው ቦታ
12 ሰዓት የፈጀ ጦርነት ገጠሙ፡፡

በሁለቱም ወገን አለ የማይባል ጦር አለቀ፡፡ የጠላት ወገን ግን እንዳለመው አልተሳካለትም፡፡ ይልቁኑ የበቀለ ወያ ጦር ከገረሱ ዱኪ ጋር በመተባበር አሳድዶ እየወጋው ብዙዎቹን ማረከበት፡፡ ሻቃ በቀለ አምስቱንም ዓመት ሙሉ ለኢትዮጵያ ነጻነት
ቆስለዋል፥ ተንከራተዋል፥ በጀግንነትም የጠላትን ጦር ደምስሰዋል፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ ከስደት እንደተመለሱ በቀለ ወያ እነዚህን ማዕረጎች አግኝተዋል፦

1፦ በ1933 ዓ.ም በፊታውራሪነት ማዕረግ የሲዳሞ ጥብቅ አስተዳዳሪና የክብረ መንግሥት የወርቅ ማዕድን ኃላፊ፤
2፦ በ1933 ዓ.ም የሁለተኛ ሬዥማን አዛዥ፤
3፦ በ1934 ዓ.ም በወለጋ የሶዩ አውራጃ ገዥ፤
4፦ በ1935 ዓ.ም በደጃዝማችነት ማዕረግ የጨቦና ጉራጌ
አውራጃ ገዥ፤
5፦ በ1936 ዓ.ም የወላይታ አገረ ገዥ፤
6፦ በ1938 ዓ.ም በሐረር የጨርጨርና ኢሳ አውራጃ ገዥ በመሆን ሠርተዋል፡፡

ደጃዝማች በቀለ ወያ በሥራ ላይ እያሉ ባደረባቸው ጽኑ ሕመም ምክንያት ለሕክምና ወደ ስዊዘርላንድ በጉዞ ላይ ሳሉ ሚያዝያ 6፥ 1946 ዓ.ም አርፈዋል፡፡ አስክሬናቸውም ሚያዝያ 10 ቀን 1946 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ መጥቶ ብዙ ዘመድና አዝማድ፥
የመንግሥት ባለሥልጣናት፥ የአርበኞች ማኅበር አባላት፥ በግልና በዝና የሚያውቃቸው የአዲስ አበባ ሕዝብ በተገኘበት በሥላሴ ቤተ ክርስቲያን በደማቅ ሥነ ሥርዓት ታጅቦ አርፏል፡፡

ሻቃ በቀለ ወያ መቼም የማይረሱ ጀግና በመሆናቸው ይህ ግጥም ማስታወሻቸው ሆኖ ይኖራል፦
“አላስኬድም አለኝ አርኩ (ጣልያን) በመንገዱ፤
ያ ሻቃ በቀለ ና ወንዱ ና ወንዱ !”

ምንጭ፦
፩፦ ቀሪን ገረመው በታደሰ ዘወልዴ፤
፪፦ አባ ቦራ በታቦር ዋሚ፤
፫፦ የሻቃ በቀለ ወያ ታሪክ “የትውልድ አርአያ ” በሽፈራው መንገሻ፡፡

"ዘላለማዊ ክብርና ሞገስ ለኢትዮጵያ ነፃነት ሰማዕታት"

@yetarikdersan
ደጃዝማች በቀለ ወያ( ሻቃ በቀለ )

“አላስኬድም አለኝ አርኩ (ጣልያን) በመንገዱ፤
ያ ሻቃ በቀለ ና ወንዱ ና ወንዱ !”

@yetarikdersan