TIKVAH-ETHIOPIA
1.48M subscribers
56.4K photos
1.4K videos
202 files
3.83K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
" ኢትዮጵያ የ ' ብሪክስ ' ቡድንን የተቀላቀለችው በዋናነት በወቅታዊ የፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ማዕቀቦች ጫና ነው " - የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ማህበር የባለሙያዎች ዳሰሳ

ከ5 ሺህ 500 በላይ የኢኮኖሚ ባለሙያዎችን ያቀፈው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ማህበር ‘ የኢትዮጵያ ብሪክስ ቡድንን መቀላቀል ጥቅም እና ስጋት ’ን የፈተሸ የባለሙያዎች ዳሰሳ አድርጎ በዋና መስሪያ ቤቱ ይፋ አድርጓል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ በአካል ተገኝቶ በተከታተለው በዚህ ዳሰሳ የማህበሩ የምርምርና ፖሊሲ ትንተና ዳይሬክተር ደግዬ ጎሹ (ዶ/ር)፤ " በዳሰሳው 233 የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል " ብለዋል።

የግኝቱ ዋነኛ ነጥቦች ፦

- ከተሳታፊዎች መካከል :

* 49% የሚሆኑ ባለሙያዎች ኢትዮጵያ የብሪክስ ቡድንን የተቀላቀለችው በፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማዕቀቦች ተገፍታ ነው ብለዋል።

* 47% የሚሆኑት አዳጊ ኢኮኖሚ ስላላት ነው ብለዋል።

* 45.5% የጂኦፖለቲካዊ ምክንያቶችን አንስተዋል።

* 41% እና 39% እንደቅደም ተከተላቸው ከምዕራባውያን ጋር የግንኙነት መሻከር እና የውጭ ምንዛሪ እጥረትን በገፊ ምክንያትነት ጠቅሰዋል።

" ይሄ ትንሽ ተቃርኖ አለው። መንግስት የሚለው በራሳችን በጎ ተግባሯ (merits) ነው ይላል፤ ያመለከተችው በተፅዕኖዎቹ ነው፤ ለምን እንደተቀበሏት አይታወቅም። በእርግጥ ብሪክስ የተቀበላቸው ሀገራት በምን መስፈርት እንደገቡ ማንም አያውቀም " ሲሉ ዶ/ር ደግዬ ግኝቱን አስረድተዋል።

- ከተሳታፊ ባለሙያዎች ውስጥ ኢትዮጵያ ብሪክስን በመቀላቀሏ ከጉዳቱ ጥቅሙ ያመዝናል ያሉት 51% ሲሆኑ 25% የሚሆኑት በተቃራኒው እንደሚሆን ገምተዋል።

- #ዶላርን ከግብይት ስርዓት ውጪ ለማድረግ ስለተያዘው የብሪክስ ዕቅድ በተመለከተ ይሳካል የሚሉት ብዙኀኑ ቢሆኑም ይህ እንዲሳካ እስከ 15 ዓመታት ይፈጃል ያሉት 67% ናቸው።

ዳሰሳው ሌላኛው የተመለከተው ጉዳይ ኢትዮጵያ ብሪክስን በመቀላቀሏ ከምዕራባውያን ወገኖች ስለምታጣቸው ጥቅሞች እና ስለሚኖሩት ጫናዎች ነው።

በዚህም፦

* ብድር እና ድጋፎችን ለማግኘት ትቸገራለች ወይም ትከለከላለች የሚሉ ባለሙያዎች 56% ናቸው።

* 43% የሚሆኑት በሂደት ላይ ለሚገኙ ፕሮጀክቶች ገንዘብ ለማሰራጨት ትቸገራለች ብለዋል።

* 40% የሚሆኑት የብር የመግዛት አቅም እንዲዳከም ግፊት ይደረግባታል ብለዋል።

- ጫናዎችን በተመለከተ 66% የሚሆኑት ከምዕራባውያን ዘርፈ ብዙ ጫናዎችን ሲገምቱ፣ በአባላቱ መካከል የእርስ በእርስ የፖለቲካ ፍላጎት ግጭቶች እንዲሁም የብሪክስ ልማት ባንክ የሆነው " ኒው ዲቨሎፕመንት ባንክ " አቅም ውስንነት በተከታይነት ስጋቶች ሆነው ተቀምጠዋል።

የባለሙያዎች ዳሰሳው ያስቀመጣቸው ምክረ ሃሳቦች ፦

የኢኮኖሚ ባለሙያዎቹ ኢትዮጵያ በምዕራባውያን ቁጥጥር ስር ከሚገኙት ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት እንዲሁም ከብሪክስ ጋር መስራት ግዴታዋ እንደሆነ ገልፀው፤ ለረጅም ዓመታት ከምዕራባውያን ጋር ከነበራት ትስስር አሁን እንደተፃራሪ ወደሚታየው ብሪክስ ቡድን ስትገባ የሁለቱን አሰላለፍ ጥቅምና ጉዳት በትኩረት ለይቶ መንቀሳቀስ ትኩረት እንደሚፈልግ ተገልጿል።

እስከዛሬ ከምዕራባውያን የሚገኙ ጥቅሞችን ማካካስ ካልቻለ ተግዳሮቱ ይበዛል። የዶላርን የበላይነት መቀነስና ለንግድ የራሳቸውን ኖቶች መጠቀም የሚለውም ለኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ እጥረት የባሰ ራስምታት ስለሚሆን ከአባል ሀገራቱ የሚኖረውን አንድነትና ልዩነት በአግባቡ መፈተሽ ይገባል።

ባለሙያዎች በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስተማማኝነት ላይ ጥያቄ ያነሱ ሲሆን ከብሪክስ አባል ሀገራት ጋር የሚያሰራ የፋይናንስ ስርዓት ለመፍጠር መልሶ ማደራጀት ይፈልጋል ብለዋል።

#ቲክቫህኢትዮጵያ

@tikvahethiopia