Amhara Region Supreme Court
3.11K subscribers
1.6K photos
5 videos
14 files
199 links
Download Telegram
የማእከላዊ ጎንደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በ2018 በጀት ዓመት የፍርድ ቤቶች አፈጻጸም የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ የዋንጫ ተሸላሚ ሆነ

ባሕር ዳር፣ ጥቅምት 01/2019 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)

የአማራ ክልል ፍርድ ቤት የዳኞች ጉባኤ ከመስከረም 20 እስከ መስከረም 29/2019 ዓ.ም መካሄዱ ይታወቃል።

"የዳኝነት ተደራሽነትን ማስፋት፣ አገልግሎትን ማላቅ" በሚል መሪቃል ለአስር ተከታታይ ቀናት በተካሄደው የክልሉ ዳኞች ሁለተኛው ዓመታዊ ጉባኤ የመዝጊያ ሥነ-ሥርዓት መካከል አንዱ የዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች በበጀት ዓመቱ ባከናወኑት ስራ መሰረት የተሻለ አፈጻጸም ያስመዘገቡትን ለይቶ እውቅና እና ሽልማት መስጠት ሲሆን፣ በዚህም የማእከላዊ ጎንደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከ14ቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች የተሻለ አፈጻጸም በማስመዝገብ የዋንጫ ተሸላሚ መሆን ችሏል።

የፍርድ ቤቶቹ አፈጻጸም በአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች የማትጊያ ሥርዓት መወሰኛ መምሪያ በተቀመጡት መመዘኛ መስፈርቶች የተለካ መሆኑ በሽልማት ሥነ-ሥርዓቱ ወቅት ተገልጿል።

ከመለኪያ መስፈርቶቹ መካከልም፣ የዳኝነት አገልግሎት ቅልጥፍናን ማረጋገጥ፣ የዳኝነት አገልግሎት ጥራትን ማሻሻል፣የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነትን ማሻሻል፣ የፍርድ ምርመራ እና ኢንስፔክሽን ሥራ፣ የማትጊያ ሥርዓት፣ የአመራር ብቃት፣ የሰው ሀብት ልማት ሥራ፣ ብዝሃ የፍትሕ መስጫ ሥርዓቶችን ማጠናከር፣ የቅሬታ ማስተናገጃ ሥርዓት፣ የሀብት አስተዳደር እና የበጀት አጠቃቀም ይገኙበታል።

ለዝርዝሩ
https://www.facebook.com/share/p/1EzmckfPDW/
❤7
የአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች ከጥቅምት 2 ቀን 2019 ዓ.ም ጀምሮ ሙሉ ለሙሉ ወደ መደበኛ የዳኝነት አገልግሎታቸው ይመለሳሉ

ባሕር ዳር፣ ጥቅምት 1/ 2019 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከጥቅምት 2 ቀን 2019 ዓ.ም ጀምሮ ሁሉም የክልሉ ፍርድ ቤቶች ወደ መደበኛ የዳኝነት ሥራቸው እንደሚመለሱ ያስታውቃል።

በዳኞች ዓመታዊ የክረምት ዕረፍት ምክንያት ከነሐሴ 1 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በከፊል ዝግ ሆነው የቆዩት ፍርድ ቤቶች፣ የ2019 በጀት ዓመት መደበኛ የዳኝነት አገልግሎታቸውን ሙሉ በሙሉ በመጀመር ለባለጉዳዮች የሚሰጡትን አገልግሎት ያስቀጥላሉ።

ዓመቱን ሙሉ በመዝገብ ሥራ ላይ የቆዩት የክልሉ ዳኞች ከክረምት ዕረፍታቸው ጎን ለጎን በሙያዊ አቅም ግንባታና በዳኝነት አሠራር ማሻሻያ ላይ ያተኮሩ ሥልጠናዎችና ውይይቶችን ሲያካሂዱ ቆይተዋል።

ከመስከረም 20 እስከ 29 ቀን 2019 ዓ.ም ለአስር ተከታታይ ቀናት የተካሄደው የአማራ ክልል ፍርድ ቤት ዳኞች ሁለተኛው ዓመታዊ ጉባኤ የዚሁ ሂደት አንዱ አካል ነበር።

በጉባኤው የክልሉ ዳኞች የዳኝነት ሙያዊ አቅማቸውን ለማጎልበት፣ በአዳዲስ ሕጎችና አሠራሮች ላይ ያላቸውን ግንዛቤ ለማሳደግ እንዲሁም የዳኝነት አገልግሎቱን የበለጠ ቀልጣፋና ተደራሽ ለማድረግ የሚያግዙ ሥልጠናዎችን፣ ገለጻዎችንና ሙያዊ ውይይቶችን ተከታትለዋል።

በጉባኤው ማጠቃለያ ሥነ-ሥርዓት ላይ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው፣ በዳኞች የክረምት ዕረፍት ምክንያት በከፊል ዝግ ሆነው የቆዩት ፍርድ ቤቶች ወደ መደበኛ ሥራቸው ከጥቅምት 02/2019 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚመለሱ አስታውቀዋል።
ለዝርዝሩ
https://www.facebook.com/share/p/18a24WJbKA/
👍7❤2
የፌደራል እና የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንቶች የጣና ሀይቅ ገዳማትን እና ባሕር ዳር ከተማን ጎበኙ

ባሕር ዳር፣ ጥቅምት 02/2019 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)

የሀገር አቀፍ የሕግ ተርጎሚዎች ጉባኤ በባሕር ዳር ከተማ ሲካሄድ የቆየ መሆኑ ይታወቃል።

የጉባኤው ተሳታፊ የሆኑት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስን ጨምሮ፣ የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንቶች እና የአዲስ አበባ እና ድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንቶች የጣና ሀይቅ ደሴቶችን እና በባሕር ዳር ከተማ የተሰሩ መሠረተ ልማቶችን ጎብኝተዋል።

በብዙ ደሴቶች እና ገዳማት የተከበበውን የጣና ሀይቅ የጎበኙት ፕሬዘዳንቶቹ፣ የክብራን ገብርኤል ገዳም በመገኘት ቀደምት የሆነውን ቤተክርስቲያን እና በስፍራው የሚገኙ ቅርሶችን ጎብኝተዋል።

ፕሬዝደንቶቹ በባሕር ዳር ቆይታቸው፣ በከተማዋ የሚገኙ መሠረተ ልማቶችን የጎበኙ ሲሆን፣ የባሕር ዳር አለም አቀፍ ስቴዲየምን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

ከባህርዳር አለምአቀፍ ስታዲዮም በተጨማሪ፣ የአባይ ድልድይን ጨምሮ ሌሎች የከተማዋን መሰረተ ልማቶች ተመልክተዋል።

ባዩት ነገር የተደነቁ መሆናቸውን የገለጹት ፕሬዘዳንቶቹ፣ ለተደረገላቸው መልካም አቀባበል አመስግነዋል።
👍4❤2
የአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች መደበኛ የዳኝነት ሥራቸውን በይፋ ጀመሩ

ባሕር ዳር፣ ጥቅምት 2/2019 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)

በአማራ ክልል የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 282/2014 መሰረት ከነሃሴ 01 ጀምሮ እስከ መስከረም 30 ዓመታዊ የዳኞች የዕረፍት ወራቶች መሆናቸው ተደንግጓል።

አላማውም ዓመቱን ሙሉ በመዝገብ ሥራ ያሳለፉት የክልሉ ዳኞች እረፍት አድርገው በሙሉ አቅማቸው፣ በአዲስ ጉልበት እና የሥራ መንፈስ ወደ ዳኝነት ስራቸው ተመልሰው የተጣለባቸውን ሕገ መንግስታዊ ሃላፊነት በአግባቡ እና በላቀ ቅልጥፍና እንዲወጡ ማስቻል ነው።

በዚህም መሰረት፣ ከነሃሴ 01/2018 እስከ መስከረም 30/2019 ዓ.ም በከፊል ዝግ ሆነው የቆዩት የክልሉ ፍርድ ቤቶች፣ የ2019 በጀት ዓመት መደበኛ የዳኝነት አገልግሎታቸውን ሙሉ በሙሉ ጀምረዋል።

የክልሉን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጨምሮ በተዋረድ የሚገኙ ሁሉም የክልሉ ፍርድ ቤቶች ከዛሬ ጥቅምት 02/2019 ዓ.ም ጀምሮ ሙሉ አገልግሎት መስጠት የጀመሩ ሲሆን፣ ህብረተሰቡ ወጭ፣ ጊዜ እና ጉልበት ቆጣቢ አገልግሎት ማግኘት እንዲችል ቀልጣፋ፣ ዘመናዊ እና ተገማች የዳኝነት አገልግሎት መስጠት በሚያስችል ቁመና ተደራጅተው ይገኛሉ።

የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጡን ዘመን ባፈራቸው የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማቶች በማገዝ ላይ የሚገኘው የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ሕብረተሰቡ የላቀ የዳኝነት አገልግሎት፣ በአነስተኛ ጊዜ እና ጉልበት ማግኘት እንዲችል አማራጭ የዳኝነት አገልግሎት መስጫዎችን በማስፋፋት ላይ ይገኛል።
ለዝርዝሩ
https://www.facebook.com/share/p/1Cg8hAfxCF/
❤5👍2