Amhara Region Supreme Court
3.11K subscribers
1.6K photos
5 videos
14 files
199 links
Download Telegram
ለኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የቀድሞው ፕሬዝደንት አሸኛኘት ተደረገላቸው

ባሕርዳር፣ ጥቅምት 01/2019 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)

ሀገር አቀፍ የሕግ ተርጓሚዎች ልዩ ጉባኤ መስከረም 30/2019 ዓ.ም በባሕርዳር ከተማ መካሄዱ ይታወሳል።

የሀገሪቱ ፍርድ ቤቶች በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት በጋራ የሚተገብሩትን የትራንስፎርሜሽን ማእቀፍ ተወያይቶ ያጸደቀው ልዩ ጉባኤው፣ ለኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የቀድሞው ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ጋዛሊ አባሲማል የሽኝት መረሃግብር አካሂዷል።

የሀገሪቱ ፍርድ ቤቶች የትራንስፎርሜሽን ማእቀፍ ከሃሳብነት ተነስቶ እዚህ ደረጃ እስኪደርስ ከፌደራል እና ከሌሎች ክልሎች ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንቶች ጋር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል ያለው ሀገር አቀፍ የሕግ ተርጓሚዎች መድረክ፣ ክቡር አቶ ጋዛሊ የፍርድ ቤቶች አገልግሎት አሰጣጥ በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲሻሻል መድረኩ እያደረገ ላለው ጥረት በአመራርነት ዘመናቸው ላደረጉት አስተዋጽኦ ምስጋና ይገባቸዋል ብሏል።

በክቡር አቶ ጋዛሊ አባሲማል ቦታ ለተተኩት የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር ኦቶካና ኦዳ (ዶ/ር) መልካም የስራ ዘመን የተመኘው መድረኩ፣ የቀድሞው የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዝደንት የተመደቡበት አዲስ የስራ ሀላፊነት ስኬታማ እንዲሆንላቸው መልካም ምኞቱን ገልጿል።
የማእከላዊ ጎንደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በ2018 በጀት ዓመት የፍርድ ቤቶች አፈጻጸም የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ የዋንጫ ተሸላሚ ሆነ

ባሕር ዳር፣ ጥቅምት 01/2019 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)

የአማራ ክልል ፍርድ ቤት የዳኞች ጉባኤ ከመስከረም 20 እስከ መስከረም 29/2019 ዓ.ም መካሄዱ ይታወቃል።

"የዳኝነት ተደራሽነትን ማስፋት፣ አገልግሎትን ማላቅ" በሚል መሪቃል ለአስር ተከታታይ ቀናት በተካሄደው የክልሉ ዳኞች ሁለተኛው ዓመታዊ ጉባኤ የመዝጊያ ሥነ-ሥርዓት መካከል አንዱ የዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች በበጀት ዓመቱ ባከናወኑት ስራ መሰረት የተሻለ አፈጻጸም ያስመዘገቡትን ለይቶ እውቅና እና ሽልማት መስጠት ሲሆን፣ በዚህም የማእከላዊ ጎንደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከ14ቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች የተሻለ አፈጻጸም በማስመዝገብ የዋንጫ ተሸላሚ መሆን ችሏል።

የፍርድ ቤቶቹ አፈጻጸም በአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች የማትጊያ ሥርዓት መወሰኛ መምሪያ በተቀመጡት መመዘኛ መስፈርቶች የተለካ መሆኑ በሽልማት ሥነ-ሥርዓቱ ወቅት ተገልጿል።

ከመለኪያ መስፈርቶቹ መካከልም፣ የዳኝነት አገልግሎት ቅልጥፍናን ማረጋገጥ፣ የዳኝነት አገልግሎት ጥራትን ማሻሻል፣የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነትን ማሻሻል፣ የፍርድ ምርመራ እና ኢንስፔክሽን ሥራ፣ የማትጊያ ሥርዓት፣ የአመራር ብቃት፣ የሰው ሀብት ልማት ሥራ፣ ብዝሃ የፍትሕ መስጫ ሥርዓቶችን ማጠናከር፣ የቅሬታ ማስተናገጃ ሥርዓት፣ የሀብት አስተዳደር እና የበጀት አጠቃቀም ይገኙበታል።

ለዝርዝሩ
https://www.facebook.com/share/p/1EzmckfPDW/
❤7
የአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች ከጥቅምት 2 ቀን 2019 ዓ.ም ጀምሮ ሙሉ ለሙሉ ወደ መደበኛ የዳኝነት አገልግሎታቸው ይመለሳሉ

ባሕር ዳር፣ ጥቅምት 1/ 2019 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከጥቅምት 2 ቀን 2019 ዓ.ም ጀምሮ ሁሉም የክልሉ ፍርድ ቤቶች ወደ መደበኛ የዳኝነት ሥራቸው እንደሚመለሱ ያስታውቃል።

በዳኞች ዓመታዊ የክረምት ዕረፍት ምክንያት ከነሐሴ 1 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በከፊል ዝግ ሆነው የቆዩት ፍርድ ቤቶች፣ የ2019 በጀት ዓመት መደበኛ የዳኝነት አገልግሎታቸውን ሙሉ በሙሉ በመጀመር ለባለጉዳዮች የሚሰጡትን አገልግሎት ያስቀጥላሉ።

ዓመቱን ሙሉ በመዝገብ ሥራ ላይ የቆዩት የክልሉ ዳኞች ከክረምት ዕረፍታቸው ጎን ለጎን በሙያዊ አቅም ግንባታና በዳኝነት አሠራር ማሻሻያ ላይ ያተኮሩ ሥልጠናዎችና ውይይቶችን ሲያካሂዱ ቆይተዋል።

ከመስከረም 20 እስከ 29 ቀን 2019 ዓ.ም ለአስር ተከታታይ ቀናት የተካሄደው የአማራ ክልል ፍርድ ቤት ዳኞች ሁለተኛው ዓመታዊ ጉባኤ የዚሁ ሂደት አንዱ አካል ነበር።

በጉባኤው የክልሉ ዳኞች የዳኝነት ሙያዊ አቅማቸውን ለማጎልበት፣ በአዳዲስ ሕጎችና አሠራሮች ላይ ያላቸውን ግንዛቤ ለማሳደግ እንዲሁም የዳኝነት አገልግሎቱን የበለጠ ቀልጣፋና ተደራሽ ለማድረግ የሚያግዙ ሥልጠናዎችን፣ ገለጻዎችንና ሙያዊ ውይይቶችን ተከታትለዋል።

በጉባኤው ማጠቃለያ ሥነ-ሥርዓት ላይ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው፣ በዳኞች የክረምት ዕረፍት ምክንያት በከፊል ዝግ ሆነው የቆዩት ፍርድ ቤቶች ወደ መደበኛ ሥራቸው ከጥቅምት 02/2019 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚመለሱ አስታውቀዋል።
ለዝርዝሩ
https://www.facebook.com/share/p/18a24WJbKA/
👍7❤2
የፌደራል እና የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንቶች የጣና ሀይቅ ገዳማትን እና ባሕር ዳር ከተማን ጎበኙ

ባሕር ዳር፣ ጥቅምት 02/2019 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)

የሀገር አቀፍ የሕግ ተርጎሚዎች ጉባኤ በባሕር ዳር ከተማ ሲካሄድ የቆየ መሆኑ ይታወቃል።

የጉባኤው ተሳታፊ የሆኑት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስን ጨምሮ፣ የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንቶች እና የአዲስ አበባ እና ድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንቶች የጣና ሀይቅ ደሴቶችን እና በባሕር ዳር ከተማ የተሰሩ መሠረተ ልማቶችን ጎብኝተዋል።

በብዙ ደሴቶች እና ገዳማት የተከበበውን የጣና ሀይቅ የጎበኙት ፕሬዘዳንቶቹ፣ የክብራን ገብርኤል ገዳም በመገኘት ቀደምት የሆነውን ቤተክርስቲያን እና በስፍራው የሚገኙ ቅርሶችን ጎብኝተዋል።

ፕሬዝደንቶቹ በባሕር ዳር ቆይታቸው፣ በከተማዋ የሚገኙ መሠረተ ልማቶችን የጎበኙ ሲሆን፣ የባሕር ዳር አለም አቀፍ ስቴዲየምን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

ከባህርዳር አለምአቀፍ ስታዲዮም በተጨማሪ፣ የአባይ ድልድይን ጨምሮ ሌሎች የከተማዋን መሰረተ ልማቶች ተመልክተዋል።

ባዩት ነገር የተደነቁ መሆናቸውን የገለጹት ፕሬዘዳንቶቹ፣ ለተደረገላቸው መልካም አቀባበል አመስግነዋል።
👍4❤2