Estifanos Dereje
994 subscribers
407 photos
6 videos
4 files
22 links
"ማስተማርንም ሆነ መማርን እድሜ አይወስናቸውም፣ ዕውቀት በማንም ሊሰራጭ፣ ለማንም ሊበረከት ይችላል፡ በዘመናችን ቴክኒካዊ ክህሎት ከታች ወደ ላይ ነው የሚፈሰው። "
እጓለ ገብረ ዮሐንስ ዶ/ር
@RW16T
+251912087083
Download Telegram
ሶስተኛው የሐገር ፍቅር ፕሮግራም በጣም ልዩ ነበር:: አቶ ደረጄ ገብሬና ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ የአባትና የልጅ ስሜታቸውን ሲጋሩ አይተናል:: እጸገነት ከበደም እንዲሁ ተገኝታ ልዩ ወግ አውግታናለች::

ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ ከተናገራቸው ትልልቅ ቁምነገሮች የተወሰኑት:-

- የሐገር ፍቅርን ለመረዳት ታሪክን ማወቅ በጣም ተገቢ ነው::

- የሐገር ፍቅር በራሱ ቀስ በቀስ የሚመጣ ቢሆንም የታላላቅ ሰዎችን ታሪክ መስማትና ማየት በጣም በከፍተኛ ደረጃ የሐገር ፍቅርን ስሜት ይቆሶቁሳል:: ለዚህም ምሳሌ የተደረገው በአዲስ አበባ ዪኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት የረዳት ፕሮፌሰር ደረጄ ገብሬና ጥበቡ በለጠ በጋራ ያዘጋጁት ''ህይወቴ'' የተሰኘው የአርበኛው ተመስገን ገብሬ መጽሐፍ ነው::

- አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ ተስፋ ይታየኛል:: ከመጪው መስከረም ጀምሮ ብዙ የአሰራርና የተቋም ለውጥ ይኖራል:: ይህ ደግሞ ባለፉት 30 ዓመታት ያለነበረ ነው:: ስለዚህ ወጣቶች ተስፋ አላችሁ ተባብራችሁ : ተቻችላችሁ ስሩ::

- እንዲህ አይነቱ ዝግጅት ይበል የሚያስብል ነው:: በጣም ደስ ብሎኛል ዛሬ በርቱ!

አቶ ደረጄ ገብሬ ከተናገሩት:-

• ወጣቶች እንዲህ እንድትሆኑ አገሪቱ እንዲህ እንድትበላሽ ካደረጉ መሀከል የነጮቹ እጅ በጣም ሰፊ ነው::

• ሀገር መውደድ ማለት ሰውን መውደድ ማለት ነው::

• ታሪክ ምንግዜም መማሪያ እንጂ መማረሪያ አይደለም::

አርክቴክት አዲስ መብራቱ ከተናገረው:-

= የሐገር ፍቅርን በመጠኑም ቢሆን የተረዳ ሰው ታሪክም ቢያነብ ሌላም ቢያደርግ ባለው ችግር አይናወጥም: ጥሩና መጥፎውን ታሪክ ለመለየት ቀላልም ነው ተፈጥሯዊም ነው:: ነገርግን ይህ ሁሉ ከሐገር ፍቅር ስሜት በኃላ የሚሆን ነው::

# እጸገነት ከበደም እንዲሁ የሀገር ፍቅርን በተመለከተ ልዩ የሆነ ወግ በቅርብ ካሳተመችው ማለዳን መናፈቅ ከተሰኘው መጽሐፍ አጫውታናለች::
#ስለ«አልቦ ዘመድ» በጥቂቱ

ሀገራችን እንዲህ በተቸገረችበት በአሁኑ ሰዓት እንደ ታማኙ እንደ ቅዱስ ዮሐንስ የሚቆጠሩት እነ ሩሲያ፤ቻይና፤ሕንድ፤ቱርክና ኬንያ ከጎናችን ሲቆሙ ከጥንት ዘመን ጀምረው ዕንቁላል ጠባሽ፤ወሬ አመላላሽ የሆኑት አሜሪካና ጭፍሮቿ አገራችንን ክደው ለጠብ መነሣሣታቸው ግርም ይለኛል፡፡እነዚህን ከሐዲ አገሮች የመምህር ኤርምያስ መወድስ ቅኔ ይስማማቸዋል፡፡

አባቶቻችን ስለ ጊዜና ስለ ባለጊዜ ድርጊት ከሚናገሯቸው አባባሎች ውስጥ «ጊዜ ያነሣል ጊዜ ይጥላል ፤ሁሉም ያልፋል፤ አስኪያልፍ ግን ያለፋል፤የቀን ጀግና እንጂ የሰው ጀግና የለውም፤ አትዋል ይዋሉብህ አትምከር ይምከሩ፤ በቆፈሩት ጉድጓድ ሳይገቡም አይቀሩ፤ ጊዜ የሰጠው ቅል ደንጋይ ይሠብራል፤»የሚሉት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ለጠቢቡ ሰሎሞንም «ለሁሉም ጊዜ አለው » የምትል አባባል አለቺው፡፡
የሰው ልጅ በዘመኑ ኅሊናው በፈቀደለት መጠን ለሀገርም ለወገንም የሚጠቅም መልካም ነገር አድርጎ ቢያልፍ በትውልድ ዘንድ ለዘለዓለም በአርአያነቱ ሲወደስና ሲጠቀስ፤ ወገኑም በሥራው ሲኮራ ይኖራል፡፡ትላንት የማይደፈሩና ሥልጣናቸውም የማይገሠሥ ይመስሉ የነበሩ ክፉ አድራጊዎች በሕይወት እያሉና ከገጸ ምድር ሲጠፉም በእኩይ ድርጊታቸው ሲወቀሱና ሀገርንም ሲያሳፍሩ ይኖራሉ፡፡ይህንን የምለው ጊዜ ለትልቁም ለትንሹም የራስዋን ፍርድ ለመስጠት እንደማትቦዝን በጥቂቱ ለማሳየት ነው፡፡ የሰው ልጅ በሠራው ግፍ ከሚዛን ላይ ወጥቶ ዋጋ ይከፍልበታል፡፡ ባልሠራው ነገርም በግፍ ሰንሰለት ተይዞ በደል ቢፈጸምበት የበቀል አምላክ መልሱን ሳይውልና ሳያድር ይሰጠዋል፡፡፡፡
እናም ከክብር ወርደው ውርደት በገጠማቸው ጊዜ « አልቦ ዘመድ ጊዜ ተዋርዶ---( የሰው ልጅ በተዋረደ ጊዜ ዘመድ የለውም ) ብለው በራሳቸው ላይ የዛሬ ሦስት መቶ ዓመት ገደማ መወድስ ቅኔ የተቀኙት ዘመን አንሦቶ የጣላቸው የፍትሐ ነገሥቱ ሊቅ መምህር ኤርምያስ የተባሉት ዳኛ ናቸው፡፡ «አልቦ ዘመድ» በተሰኘውና በዚህ የመወድስ ቅኔ ርእስ መጽሐፋቸውን የሰየሙት አቶ ብርሃኑ ድንቄ እንደጠቀሱት እኒህ ሊቅ በጎንደር ዘመነ መንግሥት ዘፋኙ ዳዊት አየተባሉ ይጠሩ በነበሩት በዓፄ ዳዊት ጊዜ ፍትሐ ነገሥት አውጭና ተርጓሚ፤ የቤተ መንግሥቱም ባለሟል ነበሩ፡፡ሊቁ በንጉሡ የዙፋን ችሎት ለፍርድ በቀረቡ እሥረኞች ፊት ትልቁን የሕግ መጽሐፍ በወርቅና በብር በተጌጠ አትሮንስ ላይ ዘርግተው ጥዑም በሆነ አንደበታቸው በግእዝ ሲያስኬዱ ከቆዩ በኋላ እንደገና ወደ አማርኛ በመተርጎም«አንተ በሠራኸው ሥራ እድሜ ልክህን ትታሠራለህ፤ አንተ ደግሞ ይሙት በቃ ተፈርዶብሃል ( ይመውት ይልሃል)---እያሉ በእያንዳንዱ ዜጋ ላይ የመጨረሻውን የቅጣት ፍርድ የሚወስኑ ከፍተኛ ባለሥልጣን ስለነበሩ እርሳቸውን የማይፈራና የማያከብር፤ሲያያቸውም የማይርበደበድ ሰው አልነበረም፡
ሊቁ ለዜጎቹ የተጣመመ ፍርድ ይስጡ አይስጡ ባይታወቅም ከዕለታት በአንዱ ከዓፄ ዳዊት ጋር ይጣላሉ፡፡የጠቡ መነሻም በዘመኑ በአቡነ ኤዎስጣቴዎስና በአቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳማት መምህራን መካከል በሃይማኖት አስተምህሮ(ዶክትሪን)የተነሣ የከረረ ጠብ ተጣልተው ይጨቃጨቁ ስለነበር ነው፡፡በመሆኑም ስለ ምሥጢረ ሥጋዌና ስለ ትስብእተ መንፈስ ቅዱስ የተነሣውን ጠብ ለማብረድ ጉዳዩ ለችሎት ሲቀርብ ዓፄ ዳዊት የኤዎስጣቴዎሳውያን እምነት የተሻለ ስለመሰላቸው ( ለሥዕል፤ ለመስቀል መስገድ አይገባም የሚሉ) እነርሱን ደገፉ፡፡ የፍትሐ ነገሥቱ ሊቅ መምህር ኤርምያስ ግን ከንጉሡ ሐሳብ በመለየት የኤዎስጣቴዎሳውያን እምነት ከእምነታቸው ጋር የማይሔድ መሆኑን በአጽንዖት ተናግረው ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት እምነትና ከደብረ ሊባኖስ ገዳም መምህራን ጋር ተሰለፉ፡፡በዚህም ተወግዘውና የንጉሡ ቁጣ ደርሶባቸው እሥር ቤት እንዲገቡ ተደረገ፡፡በዚያ ዘመን በእምነትና በአስተሳሰብ ከመሪው የተለየ ሰው ታሥሮ መከራውን ይበላ ነበር ማለት ነው ፡፡ዓፄ ዳዊትም ሊቁን እሥር ቤት አስገብተው እንዲማቅቁ ያደረጓቸው የሃይማኖቱ ዶክትሪን አሳስቧቸው ሳይሆን በፖለቲካውና በአገዛዛቸው ላይ ሊያመጣ የሚችለውን ተጽእኖ በመፍራት መሆኑን ደራሲው አምባሳደር ብርሃኑ አሥምረውበታል፡፡
መምህር ኤርምያስ የዓፄ ዳዊት ባለሟል በነበሩበት ጊዜ አያሌ ዘመዶችና ወዳጆች ያጅቧቸውና ያከብሯቸው ነበር፡፡ እሥር ቤት በገቡበት ወቅት ግን እንደ ኢትዮጵያውያን ልማድ «እግዚአብሔር ያስፈታዎ» ብሎ የሚጠይቃቸው ከመጥፋቱ ባሻገር እንዲያውም ያልሠሩትን ወንጀል እየጨመረ፤ እየፈጠረና እያሳበቀ የሚከስሳቸው ሰው ስለበዛ የዚያኑ ያህል የንጉሡ ቁጣ ተባባሰና ጨከኑባቸው፡፡ንጉሡን በመፍራትም የሚጠይቃቸው ሰው ጠፋ፡፡ይህም ሁኔታ ከተከሰሱበት ክስ በላይ የመምህር ኤርምያስን ስሜት በእጅጉ ጎድቶት ነበር ይባላል፡፡ ሊቁ በቅኔያቸው ያንጸባረቁትም ይህንኑ ነው፡፡
ከጥቂት ጊዜ በኋላ ንጉሡ ዓፄ ዳዊት በድንገት ይሞታሉ፡፡የሞቱትም መርዝ በልተው ነው፡፡ ይህንን ያደረጉባቸውም የደብረ ሊባኖስ ደብተሮች ናቸው ተብሎ ተወራ፡፡ከዓፄ ዳዊት ቀጥሎ ዓፄ በካፋ ሲነግሡ የዘውዳቸውን ክብረ በዓል ምክንያት አድርገው አሥረኞች ሁሉ እንዲፈቱ የምሕረት አዋጅ ሲያሳውጁ በአጋጣሚው ተጠቅመው መምህር ኤርምያስም ከእሥር ቤት ወጡ፡፡ያልተጠበቀ ድንገተኛ እድል ነበር፡፡ የፍትሐ ነገሥቱ ሊቅ መምህር ኤርምያስ የተፈቱበት ዕለት እሑድ፤ቀኑ መስከረም ዐራት ፤በዓሉ የቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ ነበር፡ ፡ካህናቱ ጎንደር በዓታ ቤተክርስቲያን ውስጥ ማኅሌት ቆመው የተለመደውን ቃለ እግዚአብሔር ሲያደርሱ ከእስር ቤት የወጡት ሊቅ ለፈጣሪ ምስጋና ለማቅረብ ወደ በዓታ ገብተው ከካህናቱ ጋር እንደተቀላቀሉ በክብር የመወድስ ቅኔ አደራረስ ሰዓት ደረሰና ቅኔውን ለእርሳቸው ሰጡዋቸው፡፡
«አልቦ ዘመድ ጊዜ ተዋርዶ»
አልቦ ዘመድ ጊዜ ተዋርዶ;ወይከውን ባዕደ ጊዜ ተዋርዶ ዘመድ፡፡
እመሰ ይትሌዓል በንብረተ ሥጋ ማዕድ፤
ጥቀ ዘመዱ ወጥቀ ነገድ፡፡
ባዕድ ይዛመድ፡፡
እምኀበ አልቦ ነገድ ወእምኀበ አልቦ ትውልድ፡፡
ሶበሂ ተሰአልዎ ለሐዋርያ አይሁድ፡፡
ኀደገ ፈጣሪሁ ወቆመ ምስለ ባዕድ፡፡
ዘመድሰ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ ፡፡
ኢተፈልጠ ምስለ እሙ እስከነ መቃብር ይወርድ፡፡
የመወድሱ ትርጉም ፡-የሰው ልጅ በተዋረደ ጊዜ ዘመድ አይኖረውም፡፡ሰው በተዋረደ ጊዜ ምንም እንኳ ኃላፊና ጠፊ በሆነው የሥጋ ሀብቱና ማዕዱም ከፍ ያለ ቢሆን ዘመድ ሳይቀር( በችግር ጊዜ) ባዕድ ይሆናል፡፡ ዘመድም ነገድም ቢሆን ዘመድ፤ ትውልድ ሳይል ከባዕድ ጋር ይዛመዳል፡፡ አይሁድ ሐዋርያውን (ጴጥሮስን) በለመኑት( ባስጨነቁት ጊዜ) ፈጣሪውን ክዶና ትቶ ከባዕድ ጋር ተሰልፏል፡፡ ይልቅስ እውነተኛ ዘመድ የሚባለው ወልደ ነጎድጓድ ዮሐንስ ነው፡፡ምክንያቱም ወደ መቃብር እስከሚወርድበት ጊዜ ከእናቱ ( ከቅድስት ድንግል ማርያም ) አልተለየምና ነው፡፡
የመወድሱ ምሥጢር፡-ሰው ሲዋረድና በመከራ ላይ ሲወድቅ ዘመድ አዝማድ ሁሉ እንደሚርቀውና ወዳጅ ሁሉ እንደሚክደው ያመለክታል፡፡ሊቁ መምህር ኤርምያስ በታሠሩበት ዘመን ከደረሰባቸው ታሪክ በመነሣትና በመጽሐፍ ቅዱስ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 26 ቁጥር 75 ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያው ጴጥሮስን «ዛሬ ገና ዶሮ ሳይጮህ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ» ያለውን በመጥቀስ የተቀኙት ሰው ሁሉ ስለካዳቸውና እንደ ኢትዮጵያ ብቻቸውን ስለቆሙ ነው፡፡
ባለቅኔው በዚህ መወድስ «ዘመድ»የሚለውን ቃል ለአምስት፤ «ባዕድ» የሚለውን ደግሞ ለሦስት ጊዜ ተጠቅመውበታል፡፡ምክንያቱም በተዋረዱበትና በታሠሩበት ወቅት የዘመድን አለኝታነትና ረዳትነት ስለአላገኙ ነው፡፡ እውነተኛ ዘመድ ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተሰቀለበት ጊዜ በመስቀሉ ሥር ቆሞ አይሁድን ሳይፈራ፤ለነፍሱ ሳይሳሳ ሲያለቅስ የነበረው ቅዱስ ዮሐንስ ነው ብለው ሊቁ አመሥጥረዋል፡፡ ምክንያቱም ቅዱስ ዮሐንስ ጌታ«እነኋት እናትህ »ብሎ የሰጠውን አደራ በመቀበል እስከሞት ድረስ ለእናቱ ለቅድስት ድንግል ማርያም ታማኝ ሆኖ በመኖሩ ነው፡፡
እናም አምባሳደር ብርሃኑ እንደሚሉትና ከቅኔውም ምጣኔ ለመረዳት እንደሚቻለው በበዓታ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ይበል ይበል ማለፊያ ነው ተብሎ የተደነቀው መወድስ ስለሰው ልጅ ተፈጥሮና ጠባይ የሚያሳይና የሚያስተምር ፤ጥልቅ የፍልስፍና ስልትን የያዘ ከመሆኑ ባሻገር ደረሲው በራሳቸው ሕይወት ላይ የደረሰውን ድርጊት መነሻ አድርገው ስለተቀኙት ሁሉንም አድማጭ አሳዝኖትና አስደንቆት ነበር፡፡በጎንደር በዓታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ቅኔ ማኅሌት ውስጥ የተሰማው ቅኔም እዚያው በዚያው ብቻ ተደንቆ አልቀረም፡፡ይልቁንም ቃላዊ በሆነ አውሎ ነፋስ በፍጥነት እስከ ጎጃም ፤ ወሎ፤ ሸዋና ትግሬ እየተዛመተ ለመላው የኢትዮጵያ ቅኔ ሊቃውንት ተዳርሶና በየልባቸው ጽላት ተቀርጾ ሲነገር ኖሯል፡፡አሁን ደግሞ በጽሑፍ መልክ ተሰንዶ እየተሰራጨ ለዚህ ትውልድ ደርሷል፡፡
ደራሲ ብርሃኑ ድንቄ እንደሚያስታውሱት ጠለቅ ያለ የሳይኮሎጂና የፍልስፍናን ትምህርት የያዘው ይህ መወድስ(አልቦ ዘመድ ጊዜ ተዋርዶ) በብዙ ቅኔ ቤቶች የሚማሩ ጀማሪ ተማሪዎች ከዜማው ጋር በቃላቸው እንዲይዙት ይደረጉ ነበር፡፡በዚህ ዓይነት የኢትዮጵያ ቅኔ በውበቱ፤በድምጸቱ፤ በምጣኔው፤ በረቀቀ ምሥጢሩ ፤ በዜማ ልኩ፤ በሰምና ወርቅ መንገዱ--- የምዕራባውያን ሥልጣኔ ምንጭ ከሆኑት ከጥንታውያኑ ከክሪኮችና ከሮማውያን ቅኔና ፍልስፍና ይልቅ የመጠቀ ፤ እነርሱም ተመራምረውና አጥንተው ገና ያልደረሱበት ጥበብ መሆኑን አስረግጦ መናገር ይቻላል፡፡

ከታደለ ገድሌ ጸጋዬ ዶ.ር
Forwarded from Kebena House
የሀገር ፍቅር መርሀግብር በቀበና ቤት
አራተኛው ዙር ታህሣሥ 2 2014 ይካሄዳል።
እንዳያመልጥዎ!