Nolawi ኖላዊ
5.87K subscribers
717 photos
88 videos
95 files
946 links
ይህ ቻናል ኦርቶዶክሳዊ መንፈሳዊ ትምህርቶች የሚተላለፉበት ነው። እግዚአብሔር አገልግሎቱን ያስፋ!

0911699907 ዲያቆን አሸናፊ መኮንን
Download Telegram
የቤተ ክርስቲያን ታሪክ /15

/አንብቡ ፣ አንብቡ ፣ አንብቡ ፣ ኧረ እባካችሁ አንብቡ !!!/

ክርስቲያኖች በድምጥያኖስ ዘመን /81-96 ዓ.ም./

ከሮማ ቄሣሮች በክርስቲያች ላይ ስደት በማስነሣት የሚታወቀው ኔሮን ቄሣር መሆኑን አይተናል ። ኔሮን ቄሣር ሙዚቀኛና ዘፈን ወዳድ ነበር ። ከእርሱ በፊት የነበረውን ቀላውዴዎስ ቄሣርን እናቱ በመርዝ ገድላለት ሥልጣን ስለያዘ ሁሉን ተጠራጣሪ መሆን ጀመረ ። በክርስቲያኖች ላይ ብዙ እንከን ቢፈልግም ምንም ሊያገኝ አልቻለም ። ቤተ መንግሥቱን ለማስፋትና ለእብደቱ እፎይታን ለማግኘት በ64 ዓ.ም የሮምን ከተማ በእሳት አጋይቷታል ። ይህን ያደረጉት ክርስቲያኖች ናቸው በማለት ሕዝቡን ተበቀሉ ብዙ አዋጅ ነገረ ። በእርሱ ዘመን ክርስቲያን የሆኑ ሮማውያን ዜግነታቸውን ተነጠቁ ። ክርስቲያኖች ሰም እንዲጠጡና ሰም ተነክረው እንደ መብራት እንዲያበሩ ተደረገ ። ከአንበሳ ጅራት ጋር ክርስቲያኖች ታሰሩ ። ብዙ እብድ ውሾች ተዘጋጅተው ክርስቲያኖች እንዲለከፉ አደረገ ። አብደው ቅስማቸው ተሰብሮ እንዲሞቱ ይህን ክፋት ቀየሰ ። በኔሮን ቄሣር ዘመን በእሳት መቃጠል ቀላሉ የመግደያ ዘዴ በመሆኑ በዚህ የሞተ እንደ ዕድለኛ ይቆጠር ነበር ።

ከኔሮን በኋላ አንድ አንድ ዓመት ሁለት ቄሣሮች ቢነግሡም በመጨረሻ ቬስፓስያን ነገሠ ። እርሱም በልጁ በቲቶ አማካይነት ኢየሩሳሌምንና መቅደሱን አፈረሰ ። ከዚያ በኋላ በተነሡት በአምስት ቄሣሮች ዘመን የጎላ መከራ በክርስቲያኖች ላይ አልታየም ነበር ። የቬስፓስያን ልጅ ፣ ኢየሩሳሌምን ያፈረሰው የቲቶ ወንድም ድምጥያኖስ ከ81-96 ዓ.ም ቄሣር ሁኖ ነገሠ ።

ሮማውያን፡- “አዲስ ኅብረትና ክብ ሲያዩ ይፈራሉ ፣ ቀነናውያንንም ያስባሉ” ይባላል ። በዚህ ምክንያት የክርስቲያኖችን ስብስብ አልወደዱትም ። ክርስቲያኖችም የአይሁድ እምነት ሌላኛው ክፍል እንደሆኑ ያስቡ ነበር ። ክርስትና ራሱን ችሎ የሚቆም በብሉይ ተስፋና በአዲስ ኪዳን ፍጻሜ ላይ የተመሠረተ መሆኑን ያወቁት ዘግይቶ ነው ። ክርስቲያኖች የሮማን ግዛት ለማወክ በአይሁድ ተልእኮ ተሰጥቷቸው ወደ ዓለም እንደ ወጡ ቄሣሮች ያስቡ ነበር ። ይህን ከሚያስቡ አንዱ ድምጥያኖስ ነበር ።
ሮማውያን በሰሜን እስከ ጀርመን ሸለቆ ፣ በምዕራብ እስከ ፈረንሳይ ፣ በሰሜን ምሥራቅ ከኤፍራጥስ ወንዝ ጀምሮ ፣ በደቡብ ሜዲትራንያን የሚያዋስናቸው አገሮችን ሰሜን አፍሪካን ጨምሮ አምስት የሰሜን አፍሪካ አገሮችን ይገዙ ነበር ። እንግሊዝ ግሪክም የግዛታቸው አካል ነበሩ ። ታዲያ የዚህ ሁሉ ገዥ አምላክ መባል ይገባዋል ። ቄሣሩ ከአማልክት አንዱ ነው ፣ ስግደት ይገባዋል የሚል አዋጅ ማስነገር ጀመሩ ። ጢባርዮስ ቄሣር ራሱን “የአምላክ ልጅ ነኝ” እያለ ይጠራ ነበር ። “የአምላክ ልጅ አምላክ ነው” በማለትም መናገር ጀመረ ። ይህን ተከትሎ ድምጥያኖስ “ጌታና አምላክ - Lord and God” እያለ ራሱን መጥራት ጀመረ ። ክርስቲያኖች፡- “ኢየሱስ ጌታ ነው” ይሉ ስለ ነበር ከቄሣሮች ጋር በቀጥታ መጋጨት ውስጥ ገቡ ።

ከቬስፓስያን እስከ ድምጥያኖስ የመጨረሻ የሥልጣን ዓመታት ድረስ በነበሩት 27 የዕረፍት ዓመታት ክርስትና በቤተ መንግሥት ውስጥ ገብቶ ነበር ። ከተራው ሕዝብ ባሻገር ልዑላኑና ልዕልቶች ወደ ክርስትና እየመጡ ነበር ።ድምጥያኖስም ፍላብየስ ክሌመንተስ የሚባለውን ዘመዱን ክርስቲያን ነህ ብሎ አስገድሎታል ። ሚስቱ ፍላብያ ወደ ግዞት ተልካለች ። ለክርስቲያኖች የሰጠችው ርስቷም ለግባ መሬት ክርስቲያኖች ይጠቀሙበት ነበር ።

ድምጥያኖስ የራሱን ምስል አሠርቶ እንዲሰገድለትና እንዲመለክ ወደ ኤፌሶን ልኮ ነበር ። ይህንን የግብዝነት ተግባር ወንጌላዊው ዮሐንስና ክርስቲያኖች በግልጽ ተቃወሙ ። ዮሐንስም ተከስሶ ወደ ደሴተ ፍጥሞ እንዲጋዝ ተወሰነበት ። የአዲስ ኪዳን የመጨረሻ መጽሐፍና ብቸኛ የአዲስ ኪዳን የትንቢት መጽሐፍ የሚባለውን “ራእየ ዮሐንስ”ን የጻፈው በዚህ በፍጥሞ ደሴት ነው ። ድምጥያኖስ ከአባቱና ከወንድሙ በወረሰው የአይሁድ ጥላቻ ምክንያት ክርስትና በአይሁዶች የተመሠረተና የሮማን ግዛት ለማፍረስ የተሰባሰበ የፖለቲካ ስልት እንደሆነ ያስባል ። ግምጃ ቤቱም ተሟጦ ስለነበር አይሁዳውያን በኢየሩሳሌም ላለው መቅደስ ባሉበት አገር ሁነው ሁለት ዲናር የመገበር ልማድ ነበራቸውና ይህ ስጦታ ለእርሱ እንዲደረግ ማስገደድ ተያያዘው ። ክርስቲያኖችንም አማልክትን ስለማይቀበሉ “ሃይማኖት የለሽ” እያለ ይጠራቸው ነበር ። የክርስቲያኖችንም ንብረት እንዲወረስ ፣ ወደ ግዞት እንዲላኩም አዝዞ ነበር ። ክርስትና ባሪያና ጨዋ የሚል ልዩነት አልነበረውምና ከባሮች ብዙዎች ጳጳስ ሆኑ ። በሮም ውስጥ ከሚኖሩት ሰዎች ከግማሽ በላይ ባሮች ነበሩና ይህ ተግባር የሮም ቄሣሮችን ማወክ ጀመረ ። በ96 ዓ.ም በተነሣው የፖለቲካ ጠብ ድምጥያኖስ ተገደለና በምትኩ ለክርስቲያኖች ነጻነትን ያወጀው ፣ ወንጌላዊ ዮሐንስን ከግዞት የፈታው ፣ ለሁለት ዓመታት የነገሠው ኔርቫ ነገሠ ።

አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ መምህራን ዘመነ ሐዋርያት የሚሉት ከ33-70 ዓ.ም ያለውን ነው ። የመጨረሻው ሐዋርያ ወንጌላዊ ዮሐንስ የመጀመሪያውን ምእተ ዓመት ስለፈጸመና እስከ 98 ዓ.ም በሕይወት ስለነበረ ዘመነ ሐዋርያት እስከ 100 ዓ.ም ነው የሚሉም አሉ ። ዘመነ ሰማዕታት ተብሎ የሚጠራው 160-312 ዓ.ም. ያለው ጊዜ ነው ። የኮፕት ቤተ ክርስቲያን ግን ዘመነ ሰማዕታት የምትለው 284-313 ዓ.ም. ነው ። ምዕራባውያን ደግሞ ከ96-113 ዓ.ም ያለውን ዘመነ ሰማዕታት ይሉታል ። ከድምጥያኖስ እስከ ዶቅልጥያኖስ ዘመን ማለት ነው ። የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ከዶቅልጥያኖስ ዘመን ጀምራ ዘመነ ሰማዕታት ትላለች ። ዶቅልጥያኖስ 284-305 ዓ.ም. በሥልጣን የቆየ ቄሣር ነው ። ክርስትናን ከምድረ ገጽ አጠፋለሁ ብሎ የፎከረ ሲሆን ማጥፋት አቅቶት ክርስትና ወደ ቤቱ ስለገባ ተጨንቆ ሥልጣን ለቀቀ ። ታዲያ የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ታላቅ የመከራ ዘመን የነበረውን ዘመነ ዶቅልጥያኖስን ዘመነ ሰማዕታት በማለት እንደ ዘመን መጀመሪያ አድርጋ ወስዳው ነበር ። ኋላ ላይ ግን፡- “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብዙ ቸርነት አድርጎልናል ፣ ከቸርነቱ አንጻር መከራው ትንሽ ነው ፤ መከራን ሁልጊዜ ለምን እናስታውሳለን ? ወደ ተደረገልን ቸርነት እንመለስ” ብለዋል ። ዘመነ ሰማዕታትን ግን ያስቡታል ።

ኔሮን ቄሣር በሮም ላይ ክርስቲያኖችን ሲያሳድድ ድምጥያኖስ ግን በመላው ዓለም የሚገኙ ክርስቲያኖችን ያሳድድ ነበር ።

ይቀጥላል
ዲአመ
ውድ የኖላዊ ቻናል ተከታታዮች ቀጥሎ "የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ ታሪክ" ክፍል 7 የመጨረሻው ክፍል በድምፅ ይቀርብላችኋል። በትጋት ተከታተሉ
በዲያቆን አሸናፊ መኮንን የተዘጋጁ 37 መጻሕፍትን አንብበዋል? ለመንገድዎ ብርሃን የሚሰጡ እነዚህን መጻሕፍት ለማግኘት ከፈለጉ:-

አራት ኪሎ አርበኞች ሕንፃ ሥር
ቤርያ መጻሕፍት መደብር ጎራ ይበሉ። ክፍለ አገር ካሉም በፖስታ ቤት ለመላክ ይቻላል። በተጨማሪ

0910531997 / 0911699907
ይደውሉ።

የተባረከ ጊዜ
ልሳን ዛሬ አለ ወይ ?

ልሳን ማለት ቋንቋ ማለት ነው ። ሐዋርያው፡- “በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር” ይላል ። 1ቆሮ. 13፡1 ። ልሳን ባለቤት ያለው ሲሆን ባለቤቶቹም ሰውና መላእክት ናቸው ። እግዚአብሔር በሰዎች አለመታዘዝ ምክንያት ቋንቋን በባቢሎን ደባልቋል ። በበዓለ ሃምሳ ደግሞ ቋንቋን ሀብተ መንፈስ ቅዱስ አድርጎ ሰጥቷል ። አንድ አምባሳደር የሚላክበትን አገር ቋንቋ ማወቅ እንዳለበት ሁሉ ሐዋርያትም ወደ ዓለም ሲላኩ የዓለምን ቋንቋ ማወቅ ነበረባቸው ። የላካቸው ትልቁና የዘላለሙ መንግሥት በቋንቋ ጸጋ ሞልቶ ሰዷቸዋል ። የልሳን ጸጋ ዓላማው ወንጌልን ለማስተላለፍ ነው ። ልሳንን በሚመለከቱ በዘመናችን የተሳሳቱ ትምህርቶችና ልምምዶች ይታያሉ ። ልሳንን የሚቀበሉ የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት ሦስት ዓይነት ልሳን እንዳለ ይናገራሉ ። ከእግዚአብሔር ፣ በልምምድና ከሰይጣን የሚነገሩ ልሳኖች እንዳሉ ያስተምራሉ ። ስለዚህ ከሦስቱ ሁለቱ ተቀባይነት የሌለው እንደሆነ ያምናሉ ። ሁለት ሦስተኛው ሐሰት ከሆነ ልሳንን መመርመር ያስፈልጋል ማለት ነው ።

ልሳን በዘመናችን አለ ወይ ? የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ነውና በዘመናችን ካለ አንቀበልም ማለት አንችልም ። ልሳን ቋንቋ በመሆኑ መናገርና መስማትን ካላሟላ ልሳን ነው ማለት አይቻልም ። ሐዋርያው፡- “ነፍስ የሌለበት ነገር እንኳ ዋሽንትም ክራርም ቢሆን ድምፅ ሲሰጥ የድምፁን ልዩነት ባይገልጥ በዋሽንት የሚነፋው ወይስ በክራር የሚመታው መዝሙር እንዴት ይታወቃል? ደግሞም መለከት የማይገለጥን ድምፅ ቢሰጥ ለጦርነት ማን ይዘጋጃል?” በማለት ይናገራል 1ቆሮ. 14፡7-8 ። ከዋሽንትና ከመለከት ድምፅ ያነሰ ልሳን ፣ ልሳን ተብሎ መጠራት አይችልም ። ተናጋሪው ሲናገር ሰሚዎቹ ካልሰሙት ልሳን አይደለም ። ምክንያት በልሳን ያለው ጩኸት ሳይሆን የመንፈስ ቅዱስ መልእክት ነው ። የልሳኑን ትርጉም ካላወቀው ሰው በግሉም ሊጸልይበት አይገባም ይላል ። የምንጸልየው በአእምሮም በመንፈስም ነውና ። ስለዚህ ትርጉሙን እስኪያውቀው መጸለይ እንጂ በግል መጠቀምም አይቻልም ። 1ቆሮ. 14 ፡ 13-15 ።

ልሳንን የመዳንን ምልክት አድርጎ ማቅረብ ፍጹም ስህተት ነው ። ጌታችን የዳኑትን በፍሬአቸው ታውቁአችኋላችሁ አለ እንጂ በልሳናቸው ታውቋችኋላችሁ አላለም ። ማቴ. 7፡16 ። ልሳን የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ነው ።ጸጋ ማለት አንዱ የሌለውና ሌላኛው ያለው ማለት ነው ። ሐዋርያው፡- “ሁሉስ በልሳኖች ይናገራሉን?” ይላል 1ቆሮ. 12፡30 ። ሁሉ በልሳን የማይናገሩ ከሆነ ልሳን የመዳን ምልክት ሊሆን በፍጹም አይችልም ። ደግሞም፡- “ልሳኖች ቢሆኑ ይቀራሉ” ይላል 1ቆሮ. 13፡8 ። ስለዚህ ሁሉ ወንጌልን ከሰማ በኋላ የሐዋርያት ዘመን ሳይፈጸም የልሳን ጸጋ እየቀረ መጥቷል ።

ልሳን እንዲሰጠን ሱባዔ መግባት ይገባልን ? ስንል የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ባለቤቱ በጎደለው ቦታ ላይ የሚሾመው ብልት በመሆኑ ሱባዔ መግባት የሚያስፈልገው አይደለም ። በብርቱ መፈለግ ካለብን ትንቢት መናገር ወይም ስብከትን እንድንሻ ተነግሯል ። 1ቆሮ. 14፡1 ። ምክንያም በስብከት ሁሉ ስለሚታነጽ ስብከት ከልሳን በላይ ለቤተ ክርስቲያን ሕንጸት አስፈላጊ ነው ። ልሳን ግን ለአማንያን ሳይሆን ለአሕዛብ ምልክት ነው ። እግዚአብሔር በቋንቋችን የሚያናግረን ቢፈልገን ነው ብለው አሕዛብ ንስሐ እንዲገቡ የተሰጠ ምልክት ነው ። “እንግዲያስ በልሳኖች መናገር ለማያምኑ ምልክት ነው እንጂ ለሚያምኑ አይደለም፥ ትንቢት ግን ለሚያምኑ እንጂ ለማያምኑ አይደለም” ይላል ። 1ቆሮ. 14፡ 22 ።

ምእመናን ሊጋደሉ የሚገባው ለመንፈስ ቅዱስ ፍሬ እንጂ ለጸጋ አይደለም ። ጸጋ መንፈስ ቅዱስ ባወቀ የምንቀበለው ነው ። ጸጋ የሌለው ክርስቲያን የለም ፣ ፍሬ የሌለው ክርስቲያን ግን ይኖራል ። ፍሬ ችላ ተብሎ ስለ ጸጋ ማውራት ከእውነቱ ለመሸሽ የሚደረግ ጥረት ነው ። ወንጌል በሁሉ ቋንቋ ስለተነገረ ፣ ከሁሉም ቋንቋ ሰባኪ ስለተገኘ ልሳን በዚህ ዘመን አንገብጋቢ አይደለም ። አለን ከተባለ ደግሞ ልሳኑ ባለቤት ያለው ነውና ሊፈተሽ ይችላል ። ዛሬ የሚደመጡት ልሳኖች ግን ባለቤት አልባ ናቸው ። በአፍህ ላይ የመጣውን ቃል ደጋግመህ በል እየተባለ በልምምድ የሚመጣ ነው ። ልምምድ ከሆነ ጸጋ መሆኑ ቀረ ። በዚያውም ለሰይጣን ፈተና መጋለጥ ይመጣል ። እግዚአብሔር ሲሰጠን እንቀበላለን እንጂ እጅ ጠምዝዘን የምንወስደው ሀብተ መንፈስ ቅዱስ የለም ።

በዓለም ላይ ቋንቋ አይደገምም ። አሳብ ይደገማል ። ቅድም ያወራችሁትን ቋንቋውን ሙሉ በሙሉ መድገም አትችሉም ። አሳቡን ግን መድገም ትችላላችሁ ። ይህ የቋንቋ ሕግ ነው ። ልሳን እየተባለ የሚነገረው ግን የሚደጋገም ቋንቋ በመሆኑ አብረው የሚኖሩ ሕፃናት ሳይቀር ደግመው ይሉታልና ቋንቋ አይደለም ። ደግሞም ልሳኑ መልእክት ማስተላለፊያ ነው ። ለምሳሌ በዚያ ልሳን “የኬንያ ሕዝብ ንስሐ ግቡ” የሚል ከሆነ ሃያ ዓመት አዲስ አበባ ላይ ተቀምጦ “የኬንያ ሕዝብ ንስሐ ግቡ” እያለ ነውና ዓላማውን ስቷል ።

በእውነት ብዙ ወገኖቻችን በየጓዳው ባለ ልምምድ ለክፉ ሰይጣን እየተዳረጉ ነው ። ቢኖር በጣም ደስ ይለን ነበር ። አያስፈልጋችሁም ከተባልን በተሰጠን ጸጋ መጠቀም ተገቢ ነው ። “መንገድ ላይ ስሄድ ፣ ሳሎን ውስጥ ተቀምጬ ልሳን ተሞላሁ” ሲሉ የነበሩ አሁን ይቅርታ እየጠየቁ ባለበት ዘመን ልሳንን መለማመድ ዕድሜን ማቃጠል ነው ። አገሩን የናደው ሐሰተኛ ትንቢትና ልሳን እንደሆነ እያየን ነው ። የሚያስፈልገን ፍቅር የተባለው ፍሬ እንጂ ጸጋስ አላነሰንም ። ፍሬ ተጋድሎ ይፈልጋል ፣ ጸጋ ግን የምንቀበለው ነው ።

እግዚአብሔር ሆይ ዓይነ ልቡናችንን አብራልን !
ጳጕሜን 1 ቀን 2011 ዓ.ም.
ዲአመ
Channel photo updated
Channel photo updated