የስብዕና ልህቀት
21 subscribers
1 link
Download Telegram
ያልተፈተሹ ባህሪያት

“ትዕግስት ስጠኝ ብለን ስንጠይቅ፤ የሚሰጠን እረጅም ሰልፍ ነው” ትላለች ጸሀፊ ትሬሲ ማክሚላን። ትዕግስትን ስንጠይቅ የሚሰጠን ትዕግስትን የምንለማመድበት መድረክና ትዕግስትን የምናዳብርባቸው ሁኔታዎች እንጂ ትዕግስት ልክ እንደተሰጥዎ ከላይ አይቸረንም። ለዛሬ ጽሁፌ መነሻ የሆነኝ ሀሳብ እንደሚከተለው ነው።

አንዳንዴ እራሳችንን ባላሰብነው ሁኔታ ውስጥ እናገኘውና ከራሳችን የማንጠብቀው ባህሪ ሲንጸባረቅብን እንደነግጣለን። ለወትሮ እኮ እንዲህ አልነበርኩም በማለት ግራ ይገባናል። ተሳድበን የማናውቅ ሰዎች በሆነ አጋጣሚ ሌላውን ሰው ስናጥረገርገው፤ ትዕግስተኛ ነን ብለን የምናስብ ሰዎች ቀጠሮዋችን እረፈደ ብለን የታክሲውን ሹፌር ስናመናጨቀው፤ ቂመኛ አይደለሁም ስንል የከረምን ሰዎች የወደድነው ሲከዳን ለበቀል ስናደባ፤ በደላችንን ይቅር በለን እያልን ጠዋት ማታ እየጸለይን የበደሉንን ሰዎች ይቅር ማለት ሲከብደን፤የሌሎች ሰዎች ማግኘት ያስደስተናል የምንል ሰዎች እኛ የተመኘነውን ሌላው ሰው ላይ ስናየውና ሲከፋን፤ ፈራጅ አይደለንም ስንል ከርመን የእኛ ህልውና ሲነካ የፍርድ ወንበር ላይ ቁጢጥ ስንል፤ ባህሪያችን ለገዛ እራሳችን እጅግ ግራ ያጋባል።

ማንነታችን የሚገለጸው እኛ ስለራሳችን ባለን አመለካከት ወይም ሌሎች ሰዎች ስለኛ ባላቸው አመለካከት ሳይሆን፤ እኛ ለሁኔታዎች በምንሰጠው ምላሽ ነው። ሰው እንቃለው የሚል ሰው ባያጋጥምም ፤ ሰው እጠላለሁ የሚል ሰው ስምተን ባናውቅም ሰው የሚንንቅና የምንጠላ ሰዎች ግን አንጠፋም። ከእኔ ከእራሴ ጭምር በውስጣችን መጥፎ ስሜት ያድራል ብለን ማሰቡ ይከብደናል፤ ይከብደናል ብቻም ሳይሆን ለማሰብም አንፈልግም። እውነታው ግን ከዚህ የተለየ ነው። “እኔ” ብለን የምንጠራው ማንነት በአብዛኛው የተገነባው ባልተፈተሹ ባህሪያቶቻችን ነው። ስለራሳችን ስናወራ በአብዛኛው የምናወራው በሀሳብ ስለገነባነው ማንነት እንጂ፤ በተግባር ስለምነተገብረው ባህሪዎቻችን አይደለም።

እኔ እንዲህ ነኝ ብሎ በድፍረት መናገሩ ከባድ የሚሆነውም ለዚህ ነው፤ ሁላችንም ያልተፈተኑ ባህሪያቶችን አጭቀን ስለምንቀሳቀስ። አብዛኛው ባህሪያቶቻችንና አስተሳሰቦቻችን በቲዎሪ ደረጃ እንጂ በሙከራ የተረጋገጡ አይደሉም። መልካምነታችን፤ ትዕግስተኛነታችን፤ ፍትሃዊነታችን፤ ሰው አክባሪነታችን፤ እውነተኛነታችን ተገቢውን ፈተና አላለፉም። ፈተና ስል እውነተኛ ባህሪዎቻችንን እንድናጸባርቅ የሚያስገድዱን ሁኔታዎችን ነው። ጊዜ ስለተረፈን ከኋላችን ያለውን ተሰላፊ ከፊታችን ስላስቀደምነው ትዕግስተኛ ልንባል እንችላለን? በፍጹም!!! የማንኛችንም መልካምነትና ጥንካሬ በመልካም አጋጣሚዎች ሊረጋገጥልን አይችልም። በፈተናዎችና በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ የምናሳያቸው ባህሪያቶች ይበልጥ እኛን ይገልጹናል።

ለዚህ ነው አንዳንዴ ውሳኔዎቻችንና ድርጊቶቻችን የሚያስደነግጡን። ተፈትነን ያገኘናቸው ባህሪዋቻችን ስላልሆኑ ልንጠቀምባቸው በሚገባን ቦታ ይጠፉብናል። ይህንን ማወቁ ምን ይጠቅምናል? ለሁለት ነገር ይጠቅመናል ብዬ አስባለው። አንደኛው ከውሸተኛ ማንነት ቀስ እያለ ያላቅቀናል፤ ሙሉ በሙሉ መላቀቅ ለሰው ልጅ ቢከብድም። የሚሰማንን ስሜት በካድን ቁጥርና “እኔ እኮ እንዲህ አይደለሁም” በማለት እራሳችንን በተከላከልን ቁጥር ባህሪያችንን ማሻሻል አስቸጋሪ ይሆንብናል። ከእራሳችን ጋር እየተቆራረጥን በቅዠት አለም ውስጥ መኖሩን እንለምደዋለን።በሌላ በኩል ማንነትና ባህሪያችንን ለሁኔታዎች ከምንሰጠው ምላሽ ተነስተን መዳኘት ከቻልን፤ ከእውነተኛ ምንነታችን ጋር እንቀራረባለን። የትኛው ባህሪያችን ላይ ይበልጥ ማሻሻል እንዳለብን ግልጽ ይሆንልናል። ስለራሳችን ባህሪ እርግጠኛ ሆኖ መናገሩ የሚያስከፍለው ዋጋ አለ፤ እሱም ወደ እውነት የሚወስደውን ጎዳና ያጠብብናል።እውንተኛ ማንነታችንን ለማወቅ ከፈለግን ስለራሳችን የምናስበውን ሳይሆን፤ ለሁኔታዎችና ለአጋጣሚዎች የምንሰጠውን ምላሽ ልናስተውል ግድ ይለናል። ሁለተኛው ጥቅም “እኔ ብሆን ኖሮ” በሚለው የፍርድ ዱላ እርስ በራሳችን ከመፈነካከት ያድነናል።

“ የሰው ባህሪያት በሁኔታዎችና በአጋጣሚዎች አይፈጠርም፤ በሁኔታዎችና በአጋጣሚዎች ይጋለጣል እንጂ”- ዚግ ዚግለር
👍1
Channel photo updated
Channel name was changed to «የስብዕና ልህቀት»
#ጤነኛው_ድሀ_እና_በሽተኛው_ሀብታም

ጤናው የተጓደለ ሀብታምና ጤናው የተሟላ ድሀ ነበሩ፡፡ ሁለቱም እርስ በርስ ይቀናናሉ፡፡ ሀብታሙ ሰው ለጤናው ሲል ሀብቱን አሳልፎ ቢሰጥ ይወዳል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ድሀው ለገንዘብ ሲል ጤናውን ቢሰጥ ይመርጣል፡፡
ፈላጊና ተፈላጊን የሚያገናኝ በዓለም ታዋቂ የሆነ የቀዶ ጥገና ሐኪም የአንድን ሰው አእምሮ ለሌላ ሰው የመተካት ጥበብን ማግኘቱ ተሰማ፡፡ ድሀውና ሀብታሙም ሰው በሐኪሙ አማካይነት ድሀው ጤናውን ለሐብታሙ አሳልፎ ሊሰጥ፣ ሀብታሙም ለጤና ሲል ሀብቱን በሙሉ ለድሀው ሊሰጥ ተስማምተው ተዋዋሉ፡፡ ከቀዶ ጥገናው በኋላ ሀብታሙ ሰው ከጥሩ ጤና ጋር ድሀ ሲሆን፣ ድሀው ደግሞ ጤናውን አጥቶ ሀብታም ሆነ፡፡
ቅይይሩ ስኬታማ ነበር፡፡

ከዚህ በኋላ የተፈጠረውን ታሪክ እንመልከት፡-
በፊት ሀብታም የነበረው ሰው ሁልጊዜም የስኬታማነት አስተሳሰብ ስለነበረው ሌላ ሀብት መሰብሰብ ቻለ፡፡ ምንም እንኳን የስኬት አመለካከት ቢኖረውም፣ ስለጤናው ግን ዘንግቶ አያውቅም፡፡ ሁልጊዜ ያመኛል ብሎ ፍርሃት ያድርበታል፡፡ ትንሽ ህመም ሲሰማውም አጋኖ ነው የሚመለከተው። ይህ አመለካከቱ ቀልጣፋ የነበረውን አካል እያደከመው መጣ፡፡ በሌላ አገላለፅ ሀብታም፣ ግን በሽተኛ ሆነ፡፡

ወደ አዲሱ ሀብታም ግለሰብ ደግሞ እንሂድ፡፡ ይህ ሰው ሁልጊዜም የነበረው አመለካከት የድህነት ነው፡፡ ባገኘው ሀብት የተመጣጠነ አዲስ የሕይወት ደረጃ ከመመስረት ይልቅ ገንዘቡን የማይረባ ቦታ ላይ ይበትነው ገባ፡፡ ሞኝና ገንዘብ አይጣጣሙም የሚለው የድሮ አባባል በዚህ ሰው ላይ ሰራ። በአጭር ጊዜ ውስጥ ገንዘቡ ሁሉ አለቀና ወደ ድህነቱ ተመለሰ፡፡ ሰውነቱስ? የህመም ስሜት ተሰምቶት አያውቅም፡፡ ራሱን ጤነኛ አድርጎ ይመለከታልና አእምሮው የተቀየረ ቢሆንም እንኳን ጤንነቱ ግን ትቶት አልሄደም፡፡ ተረቱ ሁለቱም ሰዎች ወደ ቀድሞ ቦታቸው መመለሳቸውን አውስቶ ያበቃል፡፡ ከዚህ ተረት ምን ትማር ይሆን? “አንተነትህ በአስተሳሰብህ ይለካል!” ወይም “የምታስበውን ትሆናለህ!”
7⃣ ዐይን-ገላጭ የጃፓኖች የሕይወት ጭብጥ!

1⃣ IKIGAI

፨ በሕይወት ውስጥ ዓላማህን ድረስበት።
፨ ሰርክ ማለዳ የመንቃትህን ምክንያት እወቅ።
፨ አስፈላጊነትህን (ለዓለም)፣ ጥንካሬህን፣ ዝንባሌህን የተወዳጀ የሆነ ነገር አስስ። ይሄ ነው ለሕይወትህ ትርጉም የሚሰጣት።

2⃣ SHIKITA GA NAI

፨ መለወጥ የማይቻልህን ነገር ተወው፣ ልቀቀው።
፨ ካንተ ቁጥጥር ውጪ አንዳንድ ነገሮች መኖራቸውን እና ያም ያለ መሆኑን ተረዳ። ሂድ እና መቀየር በምትችለው ነገር ላይ ትኩረት አድርግ።

3⃣ WABI-SABI

፨ በጎዶሎነት ውስጥ ሠላምን አግኝ።
፨ ራስህ እና ሌሎችን ጨምሮ በሕይወት ውስጥ ምንም ነገር ፍፁም አለመሆኑን ተገንዘብ።
፨ ለእንከን-የለሽነት ከመትጋት ይልቅ ሕይወትን ልዩ በሚያደርጋት ጎዶሎነት ውስጥ ደስታን አጣጥም።

4⃣ GAMAN

፨ በፈታኝ ጊዝያቶች ክብርህን ጠብቅ።
፨ ፈተና ውስጥ እንኳ ብትሆን የሥሜት-ብስለትህን እና ራስ-ገዝነትህን አሳይ።
፨ ታጋሽ፣ ፅኑ፣ ተረጂ ለመሆን እንዳትዘነጋ።

5⃣ OUBAITIORI

፨ ራስህን ከማንም ጋር እንዳታወዳድር።
፨ ሁሉም የተለየ ጊዜ-ቤት እና ልዩ ጎዳና አለው።
፨ ራስህን በሌላው ለመለካት ከመሞከር ይልቅ በራስህ መሻሻሎች ብቻ ማተኮርህ አስፈላጊ ነው።

6⃣ KAIZEN

፨ ሰርክ በሁሉም የሕይወትህ ክፍል ውስጥ መሻሻሎችን ፈልግ!
፨ ጥቃቅን ለውጦች እንኳ መጠራቀም ችለው በጊዜ ሂደት ውስጥ ግዙፍ ለውጥ ያመጣሉ።

7⃣ SHU-HA-RI

"ተማሪዎቹ ሲዘጋጁ መምህሩ ይገኛል።"
―Teo Te Ching

👉 (እንዴት) ስለመማር እና በዘዴው ስለመጠበብ ማወቂያ መንገድ ነው። ከዕውቀቱ ለመድረስ ሶስት ደረጃዎች አሉት።

፨ SHU: የአንዱን አዋቂ (master) ትምህርት በመከታተል መሰረቶቹን መቅሰም!
፨ HA: ከአዋቂው የተቀሰመውን ትምህርት ከሙክረት በማዋሃድ የተግባር ልምምድ መጀመር።
፨ RI: ይሄ ደረጃ የሚያጠነጥነው ፈጠራዎች ላይ እና ትምህርቶቹን በተለያዩ መስኮች የመተግበር ችሎታ ላይ ነው።
የማስተካከል ድንቅ ጥበብ

በመጀመሪያ ለሕይወታችን እቅድ እንሰራለታለን፡፡ አንደኛ እቅድ ትምህርት፣ ስራ፣ የፍቅር ሕይወት፣ ቤተሰብ እያልን እናድጋለን፡፡ ከዚያም ወደ ሕይወት ግቦቻችን እንደርሳለን። በእርግጥ እንደዚያ እንደማይሰራ እንደምታውቅ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ሕይወታችን ማባሪያ በሌለው ብጥብጥና ግርግር ውስጥ ታልፋለች፡፡ የሕይወታችን አብዛኛውን ጊዜያችንን የምናጠፋውም ባላየናቸው የሕይወት ውጣ ውረዶች የሚመጡብንን ፈተናዎች በመታገል ነው፡፡

በህይወት ውስጥ ወሳኙ ነገር መነሻው ሳይሆን ከመነሻው በኋላ የሚመጡት የማስተካከያ ጥበቦች መሆናቸውን ተምሬያለሁ። ከብዙ ቢሊዮን ዓመታት በኋላ ተፈጥሮም ይህን - የተማረች ትመስላለች። ህዋሳት በተከፈሉ ቁጥር የመቅዳት ሂደት ስህተቶች (copying errors) ቀጣይነት ባለው መልኩ በዘረመላዊ ቁሶች ውስጥ እየተፈጠሩ ይሄዳሉ፡፡ ስለሆነም በእያንዳንዱ ህዋስ ውስጥ እነዚህን ስህተቶች ወደኋላ ተመልሰው የሚያስተካክሉ ሞለኪዮሎች አሉ። የዲ ኤን ኤ ጥገና ባይኖር ኖሮ ልክ እንደተወለድን በሰዓታት ውስጥ በካንሰር አማካይነት መሞታችን አይቀርም ነበር፡፡ የበሽታ መቋቋም ሥርዓታችን የሚሰራውም በተመሳሳይ መልኩ ነው። ችግሮች ቀድመው የማይታዩ በመሆናቸው ምክንያት ቀድሞ የተዘጋጀ ማስተር ፕላን የለም፡፡ ቫይረሶችና ባክቴሪያዎች በየጊዜው እየመጡ ሰውነታችንን ያጠቃሉ። የመከላከል ሥርዓታችንም ሁልጊዜ ይሄንን በማስተካከል ይሰራል።

ስለዚህ ወደፊት ሁለት በጣም የማይጣጣሙ ጥንዶች መካከል የሰመረ ትዳር መመስረቱን ስትሰማ ብዙ አትደነቅ፡፡ ይህ የስሪትን (set up) አጋኖ የማየት አይነተኛ ምሳሌ ነው፡፡ በግልጽ ካወራን የትኛውም ሰው ለትንሽ ሰዓት በግንኙነት ውስጥ ከቆየ ያለማስተካከያና ያለማሻሻያ ግንኙነቱ መቀጠል የማይችል መሆኑን ይረዳል። የትኞቹም ጓደኝነቶች ማደግ አለባቸው፡፡

ብዙውን ጊዜ ከማያቸው የተሳሳቱ አረዳዶች መካከል አንዱ ‹ጥሩ ሕይወት ማለት የተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ መኖር ማለት ነው› የሚለው ድምዳሜ ነው፡፡ ይህ ስህተት ነው፡፡ ጥሩ ሕይወት . የሚመጣው ቀጣይነት ባላቸው የዘወትር ማሻሻያዎች ውስጥ በማለፍ ነው፡፡

እና እኛ ለማስተካከልና ለመሻሻል የምናቅማማው ለምንድን ነው? ምክንያቱም እያንዳንዷን የማስተካከያ ስራ የምንረዳት በመስመራችን ላይ እንደተገኘ ድክመት ስለሆነ ነው፡፡ በእርግጠኝነት እቅዳችን እየሰራ አለመሆኑን እንናገራለን፡፡ በዚህም የውርደት ስሜት ይሰማናል፡፡ እውነታው ግን ሌላ ነው፡፡ እቅድ እንደወረደ ሰርቶ አያውቅም፡፡ ድንገት ያለምንም እንከን ሰርቶ የሚያውቅ ከሆነም እንኳን ሁኔታው ፍፁም አጋጣሚ ነው፡፡

ታዋቂው የአሜሪካ ጀኔራልና በኋላም ፕሬዝደንት) ዋይት ኤዘንሃወር እንዳለው “እቅዶች ምንም አይደሉም፧ ማቀድ ግን ሁሉ ነገር ነው፡፡” ነገሩ ወጥ የሆነ ፅኑ እቅድ ስለመያዝ አይደለም፤ በተደጋጋሚ እና ሁልጊዜ የሚኖር የማቀድና የማሻሻል ሂደት እንጂ።

“ወታደሮችህ ልክ የጠላትን ጦር ሲያገኙ” ይላል ኤዘንሃወር “የትኛውም እቅድ ጥቅም አልባ ይሆናል፡፡

ህገ መንግስታት ሁሉም ህጎች የሚያርፉባቸውን መሰረቶች የሚጥሉ የበላይ ሰነዶች ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ሁሉም ህገ መንግስታት በመሻሻል ሂደት ውስጥ ያልፋሉ። ለምሳሌ በ1787 የፀደቀው የአሜሪካ ህገ መንግስት እስካሁን ባለው ዘመኑ 27 ጊዜ ተሻሽሏል። የስዊዘርላንድ ህገ መንግስትም ከ1848 በኋላ ሁለት ትልልቅ ማሻሻያዎችን (revisions) እና በርካታ ጥቃቅን ማስተካከያዎችን አስተናግዷል፡፡ የጀርመኑ የ1949 ህገ መንግስት በበኩሉ 60 ያህል ማሻሻያዎች አይቷል፡፡

ይህ ውርደት ወይም ድክመት አይደለም፡፡ ትርጉም የሚሰጥ ሂደት እንጂ። የማስተካከል አቅም የየትኛውም
ዴሞክራሲያዊ ማህበረሰብ መሰረት ነው፡፡  ዴሞክራሲ የሚገነባው በማስተካከያ ስርዓቶች ውስጥ ነው፡፡ በወጉ የሚስራው ብቸኛው የመንግስት አይነትም ይሄ ነው፡፡

እንዳለመታደል ሆኖ በሌሎች ሁኔታዎች ላይ ያላን የማስተካከል ፍላጎት ደግሞ ዝቅ ያለ ነው፡፡ የትምህርት ስርዓታችንን
መጥቀስ ይቻላል። የትምህርት ስርዓታችን በእውነታ እውቀት እና በሰርተፍኬት (ስሪት) ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ በዲግሪ እና በስራ ቦታ ውጤታማነት መካከል ያለው ክፍተት ግን ብዙ ነው። ይሄንን እያስተካከልን አይደለም፡፡

በባህሪ እድገታችንም ውስጥ ተመሳሳይ ነገር አለ፡፡ አንድ ብልህና አስተዋይ የምትለው ሰው እንደሚኖርህ እርግጠኛ ነኝ፡፡ የዚህ ሰው አስተዋይ መሆን ዋና ምክንያቱ ምን ይመስልሃል? ስሪቱ? .
(ትክክለኛ ዘር፣ ጥሩ አስተዳደግ፣ ጥራት ያለው ትምህርት) ወይስ የማስተካከል ልምዱ? (በሕይወቱ የሚያያቸውን ክፍተቶችን በየጊዜው እያስተካከለ የመሄድ ችሎታው?)


ሲጠቃለል; ለማስተካከል ያለንን መጥፎ አተያይ ማስወገድ አለብን። ትክክለኛውን - ህግ እንከተላለን ብለው እየታገሉ እድሜያቸውን ከሚያቃጥሉ ሰዎች ይልቅ በጊዜ ራሳቸውን ማስተካከል የጀመሩ ሰዎች የበለጠ ተጠቃሚ ናቸው። ፍፁም የሚባል ልምምድ እና ህግ የለም። የሕይወት ግቦችም ከአንድ በላይ ናቸው። ፍፁም የቢዝነስ ስትራቴጂ የሚባል ነገርም የለም። ትክክለኛ የሚባል አንድ ስራ ብቻም እንዲሁ።
ሁሉም ተረቶች ናቸው። እውነታው ይሄ ነው። በአንድ እርምጃ ትጀምራለህ፤ በየደረጃው እያስተካከልክ ትጓዛለህ፡፡ አለም የበለጠ ውስብስብ እየሆነች በሄደች ቁጥር መነሻ ነጥብህ ጠቃሚነቱን እያጣ ይሄዳል። ስለዚህ “በፍፁም ስሪትህ” ላይ ኃይልህን አታባክን፤ በስራም ቢሆን፣ በግል ሕይወትም ቢሆን፡፡ ከዚያ ይልቅ በአግባቡ እየሰሩ ያልሆኑ ነገሮችን ማስተካከልን ተማር፤ ተለማመድ። ይህንንም በፍጥነት እና ያለ ምንም የጥፋተኝነት ስሜት አድርገው፡፡

✍️ሮልፍ ዶብሊ
👍3