Great Ethiopian Run (ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ)
6.05K subscribers
2.46K photos
190 videos
6 files
276 links
Official Great Ethiopian Run Telegram Channel.

Call 0116635757 for more details.
Download Telegram
አትሌት መሰረት ደፋር ለ16ሺህ ሴቶች 5ኪ.ሜ. ሩጫን ከ’35 ደቂቃ በታች’ የማጠናቀቅ ፈተናን አቀረበች፡፡

ከተለያዩ የስራ ዘርፎች የተመረጡ ተምሳሌት ሴቶች የውድድሩ አንድ አካል በመሆን ስኬታቸው የሚወደስበት ፕሮግራም በሩጫው ቀን ይከናወናል።

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የሚያዘጋጀውና መጋቢት 13 ቀን 2018 ዓ.ም. ለሚካሄደውና 16,000 ሴቶች ለሚሳተፉበት የ2018 ሳፋሪኮም ቅድሚያ ለሴቶች 5ኪ.ሜ. የሩጫ ውድድር ልምምድ ቀጥሏል። የሁለት ጊዜ ኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤቷ የውድድሩ አምባሳደር መሰረት ደፋር ሴቶች አስቀድመው እንዲለማመዱ እና እንዲሮጡ ለማበረታታት ዓመታዊውን የ’35 ደቂቃ በታች’ ፈተና ይፋ አድርጋለች።

ተሳታፊዎች ይህንን ግብ እንዲመቱና በስፖርት የዳበረ ዘመናዊ የአኗኗር ዘይቤን እንዲለማመዱ ለመርዳት፣ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ለ4 ተከታታይ ሳምንታት የሚቆይ የስልጠና መርሃ ግብር በማከናወን ላይ ነው። ስልጠናው በሙያዊ አሰልጣኞችና አሯሯጮች (pace-makers) የሚታገዝ ሲሆን፣ በመሰረት ደፋር የአራት ሳምንታት የልምምድ ምክሮች የታጀበ ነው።

እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ የውድድሩ መነሻና መድረሻ በቅርቡ እድሳት በተደረገለት ቦሌ አትላስ አካባቢ የሆነው ይህ ውድድር ከስፖርታዊ እንቅስቃሴ ባለፈ የሴቶች ስኬት የሚዘከርበት ፣ ስራቸው የሚነገርበት እና ዕውቅና የሚያገኝበት እንዲሁም አንዳቸው ሌላቸውን የሚያበረቱበት ልዩ መድረክ ሆኖ ለ22 ዓመታት ቀጥሏል።

ዘንድሮም በ‘ተምሳሌት ሴቶች’ (Icons Women) መሐከል የሩጫ ውድድር የሚከናወን ሲሆን፣ የአሸናፊዎች የገንዘብ ሽልማት በስማቸው ለመረጡት የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ይለገሳል። በ23ኛው ዓመት ሩጫ ውድድር ላይ ከስምንት የተለያዩ ዘርፎች የተመረጡ ታዋቂ እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ሴቶች ይሳተፋሉ። ዘርፎቹም፦ ከኪነጥበብ፣ ከበጎ አድራጎት፣ ከመምህራን፣ ከሰራ አመራሮች፣ ከሚዲያ ባለሙያዎች፣ ከስራ ፈጣሪዎች፣ ከጤና ባለሙያዎች እና ከማህበራዊ ሚድያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች የተውጣጡ ናቸው። በዚህም መሰረት፦ ሉላ ገዙ፣ እማሆይ ዜና ማርያም፣ ሊያ ሳሙኤል፣ ቤተልሄም ደሴ፣ መቅደስ ሙሉጌታ (መቅዲዬ) እና ቤቲ ጂ በውድድሩ ላይ በተምሳሌት ሴቶች ዘርፍ ከሚሳተፉ ባለሞያዎች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።

ለውድድሩ የተመዘገቡ ተሳታፊዎች ከመጋቢት 2 እስከ 4 ቀን 2018 ከአለም ሲኒማ ጋር ቲሸርታቸውን መውሰድ እንደሚችሉም ታውቋል፡፡ ውድድሩ በሳፋሪኮም፣ ኤም-ፔሳ፣ ዲ.ኬ.ቲ (DKT)፣ ዳሽን ባንክ፣ አክቲቭ (Aktive)፣ የአየርላንድ ኤምባሲ፣ ዩኒሴፍ (UNICEF)፣ ፋብ የውበት ሳሙና፣ ቶፕ ውሃ፣ ህያት ሬጀንሲ፣ ኢቲቪ እና አፍራን ሆስፒታል አጋርነት ይዘጋጃል።
9👍9
ጋዜጣዊ መግለጫ

የ23ኛው ሳፋሪኮም ቅድሚያ ለሴቶች 5 ኪ.ሜ ሩጫ የቅድመ-ውድድር ጋዜጣዊ መግለጫ በእቴጌ መነን የልጃገረዶች ትምህርት ቤት በደመቀ ሁኔታ ተካሄደ

እሁድ መጋቢት 13 ቀን 2018 ዓ.ም. የሚካሄደውን የ2018 ሳፋሪኮም ቅድሚያ ለሴቶች  ኪ.ሜ. የጎዳና ላይ ሩጫ አስመልክቶ፤ የመጨረሻው የቅድመ-ውድድር ጋዜጣዊ መግለጫ ዛሬ በታሪካዊው እቴጌ መነን የልጃገረዶች ትምህርት ቤት ተካሒዷል።

በዝግጅቱ ላይ የውድድሩ አምባሳደር የሆነችው አትሌት መሰረት ደፋር እና የቀድሞ የትምህርት ቤቱ ተማሪ የነበሩት ታዋቂዋ ፖለቲከኛ ወ/ሮ ብርቱካን ሚደቅሳ እንዲሁም ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

"ሴቶች በዓላማ ጠንክረው ከሰሩ ያሰቡበት ደረጃ መድረስ ይችላሉ፤ እናንተ ለሀገር ተስፋዎች ናችሁና በርቱ" ስትል አትሌት መሰረት ደፋር በመድረኩ ላይ ንግግር አድርጋለች።

ሌላው በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የአ.አ. ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አሰግደው ኃ/ጊዮርጊስ "እቴጌ መነን ወደ ትክክለኛ ማንነቱ የተመለሰ ታሪክ ሆኗል ፤ ጎበዝ፣ አስተዋይ እና የወደፊቷ ኢትዮጵያ መሪ የሆኑ ሴቶች እየተማሩበት ነው። ስፖርት በጤና እና ስነምግባር የበለፀገ ማህበረሰብን ይፈጥራል ዛሬ አብረን የተሳተፍንበት እንቅስቃሴ የዚህ ማሳያ ነው። መጋቢት 13 የሚኖረው ሩጫ ከምንም በላይ አብሮነታችንን የምናሳይበት እንዲሆን አብረን እንሰራለን" ብለዋል።

የቀድሞ የፖለቲካ ሰው ብርቱካን ሚደቅሳ ቀደም ሲል ይማሩበት በነበረው በዚህ ትምህርት ቤት ተገኝተው ለተማሪዎቹ እና ለመምህራኑ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ ለአሁኑ ትውልድ ተማሪዎች ማበረታቻ እንዲሆን አዲስ ካሳተሙትን 'መመለስ' የተሰኘ መጽሐፍ የተወሰነ ክፍልን በማንበብ የራሳቸውን ታሪክ ከማጋራታቸው ባሻገር መፅሐፋቸውን በስጦታነት ለት/ቤቱ አበርክተዋል።

በልዩ ዝግጅቱ ማጠቃለያ ላይ በትምህርት ቤቱ ተማሪዎች መሀከል ጠንካራ የፉክክር መንፈስ የታየበት የዱላ ቅብብል የሩጫ ውድድር የተካሄደ ሲሆን፣ ይህም በውድድሩ ዋዜማ በትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ ዘንድ ልዩ መነቃቃትን ፈጥሯል።

ስለ የ2018 ሳፋሪኮም ቅድሚያ ለሴቶች  ኪ.ሜ. አጠቃላይ መረጃ

* የውድድሩ ቀን፦ እሁድ መጋቢት 13 ቀን 2018 ዓ.ም።
* መነሻ እና መድረሻ፦ ቦሌ አትላስ ሆቴል አካባቢ።
* ተሳታፊዎች፦ 16,000 ሴቶች፣ ከ150 በላይ ጠንካራ ተፎካካሪ አትሌቶች እና ከ25 ተምሳሌት ሴቶች።

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ለ23 ዓመታት ያለማቋረጥ ሲያካሂደው የቆየው ይህ ውድድር፣ ዘንድሮም "በመላ ኑሪ በኮንፊደንስ ሩጪ" በሚል የውድድር መልዕክት በደመቀ ሁኔታ ለመካሄድ ዝግጅቱን አጠናቋል።
👍1210
ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለ1447ኛው ዒድ አል-ፈጥር በዓል በሰላም አደረሳችሁ።

ዒድ ሙባረክ!

#GreatEthiopianRun
👍83
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚንስትር ክብርት ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሚገኘውን የካንሰር ህሙማን ማዕከል ጎበኙ።

መጋቢት 13 ቀን 2018 ዓ.ም. ከሚካሄደው የ2018 ሳፋሪኮም ቅድሚያ ለሴቶች 5ኪ.ሜ. ሩጫ አስቀድሞ በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ውስጥ የሚገኘውን የካንሰር ህሙማን ማዕከል ላይ ጉብኝት ተደርጓል። 

በጉብኝቱ ከዶ/ር ኤርጎጌ በተጨማሪም የአዲስ አበባ ሜዲካል ኮሌጅ ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ብርሀኑ ደስይበለው እና የአክቲቭ መስራች ኤሌ አኒሰን ተገኝተዋል።

‘AKTIVE AGAINST CANCER’ በዘንድሮ 2018 ሳፋሪኮም ቅድሚያ ለሴቶች 5ኪ.ሜ. ውድድር ላይ ሴቶች የካንሰር ህመምን ቀድሞ ለመከላከል ሩጫን በማዘውተር ጤናቸውን ይጠብቁ ዘንድ መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉ።

ዛሬም በጉብኝቱ ላይ ዶ/ር ኤርጎጌ "የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር እንደዚህ ያሉ ትብብሮችን ሁልጊዜ ይደግፋል ፤ ይህ ለኢትዮጵያ ሴቶች ትልቅ ትርጉም አለው ቅድሚያ ለሴቶች 5ኪ.ሜ. ዉድድር ሴቶችን የሚያበረታታ መድረክ ነው" በማለት ገልፀዋል።

ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴ ለካንሰር ማዕከሉ ያደረገውን ድጋፍ በማመስገን ንግግር ያደረጉት የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ብርሀኑ ሰንደቅ "ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ስለ ካንሰር ግንዛቤ ለመፍጠር ብዙ ተስፋ አለን" ብለዋል።

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ሩጫ ካንሰርን ለመከላከል ብሎም በማገገም ሒደት ውስጥ ባለው ጠቀሜታ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ለመስራት የሚችልበትን ስምምነት ለአራት ተከታታይ አመታት ከአክቲቭ አጌንስት ካንሰር ጋር ፈፅሟል።

የ2018 ሳፋሪኮም ቅድሚያ ለሴቶች 5ኪ.ሜ.  ነገ መነሻ እና መድረሻውን ቦሌ አትላስ በማድረግ ለ23ኛ ጊዜ ይከናወናል።
7👍5
አትሌት በርነሽ ደሴ ለተከታታይ ዓመት የሳፋሪኮም ቅድሚያ ለሴቶች 5 ኪ.ሜ. አሸናፊ ሆነች

የ2018 ሳፋሪኮም ቅድሚያ ለሴቶች 5ኪ.ሜ. ውድድር ዛሬ በድምቀት መነሻና መዳረሻውን ቦሌ አትላስ በማድረግ በዛሬው ዕለት ተካሂዷል።

በሩጫው ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ውድድሩን ከማስጀመራቸው አስቀድሞ ባደረጉት ንግግር “ሴቶች በጥበብ ይኖራሉ፤ በራስ መተማመን ይሠራሉ፤በራስ መተማመን ይሮጣሉ፤ ይችላሉም!“ ብለዋል።

በውድድሩ 16 ሺህ ሴቶች የተሳተፉ ሲሆን በአትሌቶች ዘርፍ ያለፈው ዓመት አሸናፊ የነበረችው በርነሽ ደሴ ከፀደይ ባንክ አትሌቲክስ ክለብ 15:22.91 በመግባት አሸናፊ ሆናለች።

ሮቤ ዲዳ 15:23.90 በመግባት 2ኛ ስትሆን በመድረኩ ተጠባቂ የነበረችው ሰናይት ጌታቸው 15:30.35 በመግባት 3ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

በባለፈው አመት ለአሸናፊ አትሌቶች የነበረው የ50 ሺህ ሽልማት በዚህ አመት በዕጥፍ አድጎ 100 ሺህ ብር ለአሸናፊዋ አትሌት ተበርክቷል።

በውድድሩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ክብርት ወ/ሮ አዳነች አቤቤን ጨምሮ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስቴር ዲኤታ አቶ መኪዩ መሀመድና ሌሎችም የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።

የ23ኛው ዓመት ውድድር "በመላ ኑሪ በኮንፊደንስ ሩጪ" በሚል የውድድር መልዕክት ሲከበር የውድድሩ አምባሳደር አትሌት መሰረት ደፋርን ጨምሮ ታላላቅ አትሌቶችም የታደሙበት ነበር።
18👍5
ባንክ ኦፍ አሜሪካ በኢትዮጵያ ከሩጫ ጋር እያሳደገ የሚገኘው አጋርነት አካል አድርጎ የቅድሚያ ለሴቶች 5ኪ.ሜ. የስያሜ አጋር ሆነ

ከመጋቢት 2019 (March 2027) ጀምሮ ባንክ ኦፍ አሜሪካ ከአፍሪካ ትልቆቹ የሴቶች-ብቻ ሩጫ ውድድሮች አንዱ የሆነው ውድድር የስያሜ አጋር (Presenting Partner) ይሆናል።

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከባንክ ኦፍ አሜሪካ ጋር እያሳደገ የሚገኘው አጋርነት አካል ሆኖ፣ ዓመታዊው ቅድሚያ ለሴቶች 5ኪ.ሜ. ውድድርም አዲስ የስያሜ ስፖንሰር (presenting sponsor) እንደሚኖረው ዛሬ ይፋ አድርጓል፡፡ በህዳር ወር 2018ዓ.ም. የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ መታወቂያ የሆነው የ10ኪ.ሜ. የጎዳና ሩጫ የስያሜ አጋር (Presenting Partner) እንደሚሆን ያሳወቀው ባንኩ፣ የቅድሚያ ለሴቶች 5ኪ.ሜ.ን መጨመሩ የበለጡ ሰዎችን ወደረዥም ርቀት ሩጫ ለማምጣት የያዘውን ተልዕኮ እንዲያሰፋ እና በማህበረሰቡ ዘንድ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ እንዲያጠናክር ያስችለዋል፡፡

የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የአዲስ አበባ ሶስቱም ትልልቅ የሩጫ ሁነቶች (events) ፤ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ 10ኪ.ሜ.፣ የልጆች ሩጫዎች እና የቅድሚያ ለሴቶች 5ኪ.ሜ. ውድድሮች ላይ ባንክ ኦፍ አሜሪካ አዲሱ የስያሜ አጋር (Presenting Partner) ይሆናል።

ማህበረሰብን ያስቀደመ መርሆን መሰረት ያደረገው አጋርነት በርካታ ግቦችን ለማሳካት አቅዷል፡፡ ባንክ ኦፍ አሜሪካ በ10ኪ.ሜ. እና የልጆች ሩጫዎች ላይ ነፃ ተሳትፎዎችን በገንዘብ በመደገፍ የተሳታፊነትን ተደራሽነት የማስፋት ግብን ያግዛል፡፡ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ቀጣዩን የሯጮች ትውልድ የማበርታት ተልዕኮም ከባንኩ ልጆች እና ወጣቶች በስፖርት እንዲሳተፉ የበለጡ እድሎችን ከማቅረብ ዓለምአቀፍ ስትራቴጂ ጋር ይዛመዳል፡፡ ባንክ ኦፍ አሜሪካ በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ለሚዘጋጁ ውድድሮች የሚውሉ ቴክኖሎጂዎችን ለማዘመን የሚያስችል ሀብትም ያቀርባል፤ ይህም በተራው የተሳታፊዎች ቁጥር ይበልጥ እንዲጨምር ያደርጋል፡፡

የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዋና ስራ አስኪያጅ ዳግማዊት አማረ፣ ባንክ ኦፍ አሜሪካ የቅድሚያ ለሴቶች 5ኪ.ሜ. አዲሱ የስያሜ አጋር መሆኑን ይፋ ሲያደርጉ ‹‹ባለፉት ሀያ ዓመታት የልጃገረዶች እና ሴቶች ዓመታዊ ሩጫችንን ለማሳደግ ብዙ ወጪ ፈሰስ አድርገናል፡፡ አሁን በባንክ ኦፍ አሜሪካ የአጋርነት ድጋፍ ደግሞ የበለጡ እድሎች ይከፈቱልናል፡፡ ባንክ ኦፍ አሜሪካ ለሩጫዎቻችን እና በሩጫዎቻችን አማካይነት ልናገለግላቸው ለምንሻው ማህበረሰቦች እንዲሁም ከሴቶች እና ልጆች ጋር ላሉን ሰፊ ስራዎች አብረውን ለመስራት ላሳዩት ቁርጠኝነት ላመሰግናቸው እፈልጋለሁ›› ብለዋል፡፡

በማርች 8 ከሚከበረው ዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን ጋር ተያይዞ የሚዘጋጀው የቅድሚያ ለሴቶች 5ኪ.ሜ. ባለፈው እሁድ 23ኛ ውድድሩን ሲያደርግ፣ ከ12ሺህ የበለጡ ተሳታፊዎችም ውድድሩን አጠናቅቀዋል፡፡ ከኢትዮጵያ የፖሊቲካ፣ ቢዝነስ እና ባህል ህይወት ብዙ ስመ-ጥር እንስቶችን እንዲሁም በኢትዮጵያ እያገለገሉ የሚገኙ በርካታ የውጪ አምባሳደሮችን የሚያሳትፈው ውድድር ተካፋዮቹ በኢትዮጵያ የሚኖሩ ሴቶችን ስኬቶች ለማክበር ሲሰባሰቡ የተለየ አይነት የህብረት ስሜት እንዲሰማቸው እንደሚያደርግ ተስተውሏል፡፡

የቅድሚያ ለሴቶች 5ኪ.ሜ. ሩጫ አምባሳደር እና የጥንድ የኦሊምፒክ 5000ሜ ሻምፒዮኗ መሰረት ደፋር በእሁዱ ውድድር ወቅት ስትናገር ‹‹ይህ ውድድር ሁሌም የተለየ ነው፡፡ በሁሉም የማህበረሰቡ ክፍሎች ወስጥ የሚገኙ ሴቶችን ስኬቶች ለማክበር እና ለሌሎቾ ሴቶች ስኬታማ የመሆን በራስ መተማመንን ለመስጠት አስደናቂ መድረክ ነው፡፡ ሁሌም በየዓመቱ እኛን ሴቶችን ማነሳሳት አይሳነውም›› ብላለች፡፡

ባንክ ኦፍ አሜሪካ አዲስ እና ጠለቅ ያለ የደንበኛ ግንኙነትን የመፍጠር፣ የቡድን አጋሮችን የማሳተፍ እና በሀገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘላቂ የኢኮኖሚ ተፅዕኖን የማገዝ እንቅስቃሴው አካል አድርጎ በስፖርት ውስጥ ካሉ እጅግ ታዋቂ ብራንዶች ጋር በአጋርነት ይሰራል፡፡

ባንክ ኦፍ አሜሪካ ዓለምአቀፋዊውን የብርታት መድረኩን በኢትዮጵያ ሁለቱም ውድድሮች - በአፍሪካ ትልቁ የጎዳና ሩጫ በሆነው የኖቬምበሩ ዓለምአቀፍ የ10ኪ.ሜ. እና የመጋቢቱ የቅድሚያ ለሴቶች 5ኪ.ሜ. - ላይ ከሚወዳደሩ የቀጣይ ትውልድ ሯጮች ጋር በማስተሳሰር ስፖርት እንዴት ዕድሎችን ሊፈጥር እንደሚችል እና ሰዎች እና ማህበረሰቦችን እንደሚያዋህድ ማሳየቱን ቀጥሏል፡፡

ባንክ ኦፍ አሜሪካ ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር ካለው አጋርነት ባሻገር በሩጫ፣ እግር ኳስ እና ጎልፍ ከዓለም አቀፍ ብራንዶች እና ሁነቶች ጋር በአጋርነት ይሰራል፡፡ እነዚህም Boston Marathon presented by Bank of America፣ Bank of America Chicago Marathon እና Chicago Distance Series፣ የ2026 የፊፋ ዓለም ዋንጫ፣ የአሜሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና ሁሉም 27 የአሜሪካ ብሔራዊ ቡድኖች እንዲሁም በጎልፍ የማስተርስ ውድድር እና Augusta National Women’s Amateur ናቸው፡፡
6👏6👍2
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች የ4 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ አበረከተ

አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
መጋቢት 17 ቀን 2018 ዓ.ም.

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ‘ሌሎችን ለመርዳት እሮጣለሁ’ በተሰኘው የ2018 ሶፊማልት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አለምአቀፍ 10ኪ.ሜ. የበጎ አድራጎት ዘመቻው አማካኝነት ያሰባሰበውን 4 ሚሊዮን ብር በቼሻየር ኢትዮጵያ መናገሻ ቢሮ በተከናወነ ደማቅ ስነ-ስርዓት ለተመረጡ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች አስረክቧል።

በዘንድሮው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ-ግብር ድጋፍ የተደረገላቸው ተቋማት ቼሻየር ኢትዮጵያተስፋ ማህበራዊና ልማት ማህበርየኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌደሬሽን እና እዘነት አካል ጉዳተኞች ህፃናት እና ወላጆች መርጃ ድርጅት በኢትዮጵያ ናቸው።

​በርክክብ ስነ-ስርዓቱ ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ባስተላለፉት መልዕክት "ዛሬ ማዕከሉን ተገኝቼ በመጎብኘቴ በጣም ደስ ብሎኛል ፤ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከስፖርታዊ እንቅስቃሴው ባሻገር ህዝብን ከማስተሳሰር ባለፈ፣ ችግረኞችን ለመርዳት የሚያደርገው ጥረት ለሌሎችም አርአያ የሚሆን ተግባር ነው።በቀጣይም ሌሎች በርካታ ተቋማትን ማገዛችንን እንቀጥላለን" ብለዋል።

​አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ በበኩሉ "ይህን 'ሌሎችን ለመርዳት እሮጣለሁ’ ዘመቻን ስንጀምር ዓላማችን ስፖርታዊ ውድድሩ ለወገኖቻችን መድረሻ እንዲሆን ነበር። ዛሬ ላይ በየአመቱ ተጠናክሮ መቀጠሉ አስደሳች ነገር ነው። ከምንሰበስበው ገንዘብ በላይ ለበጎ አድራጎት ድርጅቶቹ በሚሰጠው ትኩረት ትልቅ ኩራት ይሰማኛል" ሲል ገልጿል።

​በዕለቱ በግላቸው ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ ላሰባሰቡና ለዘመቻው ስኬት ጉልህ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ግለሰቦች ልዩ ዕውቅና ተሰጥቷል። ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ወደፊትም ስፖርትን ከበጎ አድራጎት ጋር በማስተሳሰር ማህበራዊ ግዴታውን መወጣቱን እንደሚቀጥልም በዚሁ ወቅት ተገልጿል።

​ይህ ‘ሌሎችን ለመርዳት እሮጣለሁ’ የተሰኘው ዘመቻ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድርን ከማዘጋጀት ባሻገር ማህበራዊ ኃላፊነቱን ከሚወጣባቸው መንገዶች ዋነኛው ሲሆን፤ ከተጀመረም 20 ዓመታትን አስቆጥሯል። ባለፉት ሁለት አስርተ ዓመታት ውስጥ ብቻ ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ከተለያዩ ድርጅቶችና ግለሰቦች በማሰባሰብ ለተለያዩ ተቋማት ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል። ዘመቻው ከገንዘብ ድጋፍ ባለፈ ተቋማቱ ተከታታይ የድጋፍ ምንጭና የመገናኛ ብዙኃን ሽፋን እንዲያገኙ በማድረግ ለህጻናት፣ ለሴቶች፣ ለአካል ጉዳተኞችና ለተፈናቃዮች የላቀ ፋይዳ ያለው ስራ ሲያከናውን ቆይቷል።
👍123👏2