Finote Hiwot የቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኀኔ ዓለምና ደብረ ትጉሃን ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ሕይወት ሰንበት ትምህርት ቤት ።
12.7K subscribers
11K photos
57 videos
90 files
1.07K links
በፌስቡክ ያግኙን፤ https://www.facebook.com/FinoteHiwotSundaySchool
Download Telegram
#ኢ. #ና. #ን. #አ.  ‹‹#የጻፍሁትን_ጽፌያለሁ::››
#ኢ
፩ኛ) #፠#ኢየሱስ_
፠ አካላዊ ቃል እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ ከሥጋ ማርያም ጋር ተዋሕዶ፤ ከሁለት አካል አንድ አካል፥ ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ ሆኖ፤ በዘመነ ሥጋዌ ከተጠራባቸው ስሞች መካከል፤ ኢየሱስ፥ ክርስቶስ፥ አማኑኤል፥ መድኀኔ ዓለም፥ መድኅን፥ የሰው ልጅ፥ የእግዚአብሔር ልጅ፥ ቃል፥ እግዚአብሔር ወልድ፥ አንድዬ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ፥ ጌታ፥ … የሚሉ ዋነኞቹ ናቸው፡፡
፠ ኢየሱስና ክርስቶስ የሚሉት ስሞች ከጥንት ጀምሮ (የሰው አእምሮ ገና ያልበሰለ፤ ክፉዎች አይሁድም ነገሩን ለፌዝ፥ ለቧልት ያውሉት ነበርና፤ ምንም እንኳን በግልጽ ባየገለጹም)፤ በነቢያት የተነገሩና በመላእክት የተበሠሩ፤ የጌታን አምላክነት የሚያሳዩ፤ የጌታን አዳኝነት የሚያመለክቱ ስሞች ናቸው፤ /መ.አውሳብዮስ/፡፡   ለምሳሌ፤ ልበ አምላክ ዳዊት ‹‹እምቅድመ ፀሐይ ሀሎ ስሙ፤ ስሙ ከፀሐይ በፊት ነበረ፡፡›› /መዝ 71÷17/ ብሏል፤ እንዲሁም ነቢዩ ሙሴ በምሳሌ ጠርቶታል፤ የሊቀ ካህንነቱ አገልግሎት ሊቀ ካህኑ የክብርና የከፍታ ምልክት፣ የነዌ ልጅ ኢያሱም የአዳኛችንን ምሳሌ ተሸክሞ ነበር፡፡›› /ዘጸ. 25፥40፣ ዘሌ. 4፥5፡16፤ 6፥22/ ብሏል ይህንንም የመልክአ ኢየሱስ ደራሲም ‹‹አክሊለ ስምከ እንዘ ይትቄጸል በርእሱ፤ አኅጉረ ፀር ወረሰ ኢያሱ፡፡›› (የስምህን አክሊል በራሱ ላይ አድርጎ የጠላትን ሀገሮች ኢያሱ ወርሷል) ብሎ አመስጥሮታል፡፡
• ይህንን ከዓለም በፊት የነበረውን ስሙን ከሰማይ ተቀብሎ ለእመቤታችን እንዲናገር የተላከው መልአክ፤ መጋቤ ሐዲስ ቅዱስ ገብርኤል ሲሆን ‹‹ስሙን የመሰየም›› ሥልጣን የተሰጣት ደግሞ እመቤታችን ናት፡፡ ˝ኢየሱስ ትይዋለሽ˝ /ሉቃ 1÷31/
#ኢየሱስ_ማለትም(ትርጓሜውም)፤
ሀ) መድኃኒተ ሥጋ ፥ መድኃኒተ ነፍስ ማለት ነው፡፡
* በዕብራይስጥ የሹኣ፥ ኢያሱ ወይም «ያሕዌ መድኃኒት ነው» የሚል ትርጉም አለው።
፠ እርግጥ ነው፥ በትንቢት፥ በምሳሌና በጥላ ቀድሞ ለተነሡት « አዳኞች» ኢያሱዎች ተሰጥቷል። (ለምሳሌ ዘካርያስ 3፥1 ላይ ሊቀ ካህናቱን ኢያሱን ያስታውሷል።) ሆኖም ግን እነዚህ « አዳኞች» ያዳኑት የእግዚአብሔርን ሕዝብ ነው፡፡ ያዳኑትም የእግዚአብሔርን ኃይልና ረድኤት አጋዥ በማድረግ ነው፤ ያዳኑት(የታደጉትም) ከምድራዊ ጠላቶቻቸው ስለሆነ ማዳናቸው ውሱን ነው፡፡
*አማናዊው ኢያሱ አዳኛችን ግን ያዳነው « ሕዝቡን» (የራሱን ሕዝብ) ነው። ያዳነውም እግዚአብሔር ተጠቅሞበት ሳይሆን ራሱ እግዚአብሔር ስለሆነ መድኃኒት ሆኖ ነው። ሕዝቡን ያዳነውም «ከኃጢአታቸው» ነው። ይህ አነጋገር የሚገባው ለእግዚአብሔር ብቻ ነው። በመሆኑም እንደቀድሞዎቹ እግዚአብሔር በምሳሌና በጥላ ሳይሆን ራሱ በመካከላችን በማደሩ ‹‹አማኑኤል እግዚአብሔር ከእኛ ጋር፡፡›› እንደ ሆነና በዚህም የነቢዩ የኢሳይያስ ትንቢት ፍጻሜ እንዳገኘ ነበር የእግዚአብሔር መልአክ የገለጠው። ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ማዳኑም የአምላክነቱ መገለጫ ነው።
ለ) ሕዝቡን በኃጢአታቸው ከመጣባቸው ፍዳ የሚያድናቸው መድኀኒት ማለት ነው፡፡ /ማቴ 1፥21፣ ተረፈ ኤርምያስ) (ዳግመኛም ወገኖቹን ከኃጢአታቸው የሚያድናቸው ኢየሱስ ይባላል፡፡ /ቅ.ኤፍሬም/፡፡) (‹‹ኢየሱስ ስዱድ ተስፋሆሙ ለስዱዳን›› /ሰቈቃወ ድንግል/)
ሐ) ኃጢአታችንን የሚያስተሠርይልን ማለት ነው፤ ‹‹አመ ይእኅዝዎ ለኢየሱስ ፀሐይ ጸልመ›› /ቅዱስ ያሬድ፥ ድጓ/
መ)  ዳግማይ አዳም ማለት ነው (የኢየሱስ የስሙ ቊጥር ከአዳም የስም ቊጥር ጋር የተባበረ ነውና)
*ኢየሱስ፡- አ=40, የ=90, ሰ=7, ሰ=7 ድምር =144፤
*አዳም፡-አ=40, ደ=100, መ=4 ድምር =144
*ዳግማይ አዳም የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ አዳምን ወደ ኤዶም ገነት አገባው ማለቱ
ኤዶም፡-አ=40, ደ=100, መ=4 ድምር =144

#ና.
፪ኛ) #፠#ናዝራዊ_፤ ከናዝሬት የመጣ /ማቴ 2፥ 23/፤ በሌላም ትርጕምም ቸር፥ እረኛ፣ በዕብራይስጥ ደግሞ የተለየ ፣ አክሊል የተቀዳጀ ፣ የተቀደሰ ማለት ነው፡፡
፠ ‹‹ኢየሱስ ናዝራዊ አምላኮሙ ለናዝራውያን›› እንዲል /አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ፤ መጽሐፈ ምሥጢር/
፠ ማቴ. 2÷23 «በነቢያት ናዝራዊ ይባላል የተባለው ይፈጻም ዘንድ ናዝሬት ወደ ምትባል ከተማ መጥቶ ኖረ፡፡››
፠ ትንቢቱ (በማቴዎስ ወንጌል የተገለጠው) ልጄ እንደ ሶምሶን ናዝራዊ ይባላል የሚል ነው፤ ነገር ግን በ66ቱም ሆነ በ81ዱ መጻሕፍት አይገኝም፤ መጽሐፉ በምርኮ ጊዜ ጠፍቷል፤ ይህም ከ66ቱ መጻሕፍት ሌላ መጽሐፍ የለም ለሚሉ ወገኖች ማስረጃ እንደሆነ አስተውል፡፡
*፠* በመጽሐፍ ቅዱስ ስማቸው የተጠቀሰው ናዝራውያን 2ት ናቸው እነርሱም ሶምሶንና ጌታችን፤ በምን ይመሳሰላሉ ቢሉ::
**ሶምሶን በተናቀች በአህያ መንጋጋ ጠላቶቹን እንዳጠፋ፤ ጌታም አይሁድ፣ አጋንንት፣ መናፍቃን በናቁት ሞቱ ሞትን አጥፍቷል፡፡ /መሳ. 15÷9-19/
**ሶምሶን በሕይወተ ሥጋ ካጠፋቸው አሕዛብ ይልቅ በሞቱ ያጠፋቸው ይበዛሉ፡፡ ጌታም በሕይወተ ሥጋ ሳለ ካጠፋቸው አጋንንት ይልቅ በሞቱ ያጠፋቸው ይበዛሉ፡፡ /ምሳ. 16÷23-31/
#ና.
፫ኛ) #፠#ንጉሥ_፤ አፄ፣ ባለዘውድ፣ ሹም፣ አለቃ፣ ማለት ነው፡፡ /ንጉሦሙ ለእስራኤል ውእቱ ይብሉ ሆሳዕና በአርያም እንዲል፡፡/
#አ
፬ኛ) #፠#አይሁድ_፤ ማለት የታመኑ፣ ምስጉኖች፣ ምዕመናን ማለት ነው፡፡
፠ አይሁድ የሚከው ቃል እስከ ባባሎን ምርኮ ድረስ ከ12ቱ ነገደ ያዕቆብ (እስራኤል) የይሁዳ ብቻ ነበረ፡፡ ከምርኮ በኋላ እስከ ክርስቶስ ድረስ ግን ለእስራኤል ሁሉ (ለ12ቱም ነገድ) መጠሪያ ሆኗል፡፡ /ዘፍ. 29፥ 35/
#የአይሁድ_ንጉሥ (#ማዕከላዊ_ስም)
፠ ሰብአ ሰገል ስም ማዕከላዊ (የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ) እያሉ ነው ለጌታ መብዓ ይዘው የመጡት፤ ስለምንድነው ቢሉ?
* አምላክ (ስም ላዕላዊ) እያሉ ያልመጡበት፤ ሰማይና ምድር የማይችለው ምን ወስኖት ምን ችሎት ነው ብለው እንዳይዘባበቱባቸው፡፡ አንድም ትንቢት የተነገረልን ሱባዔ የተቈጠረልን እኛ እያለን እንዴት ለእነርሱ ተገለጠላቸው ብለው እንዳይዘባበቱባቸው፤ አንድም አሕዛብ ናቸው በየት አውቀውት ብለው እንዳዘብቱባቸው ነው፡፡
* የተወለደው ሕፃን (ስም ታህታዊ) እያሉ ያልመጡት፤ በእስራኤል ሃገር በአንድ ቀን ውስጥ ብዙ ሕፃናት ተወልደው ብዙ ሕፃናት ይሞታሉ፤ ስንቱን እናውቅላችኋለው ባሏቸው ነበርና፡፡

/በቀጨኔ ደ.ሰላም መድኀኔዓለምና ደ.ት.ቅ.ገብርኤል ቤ.ክ ፍኖተ ሕይወት ሰ.ት.ቤት ፤    ትምሕርት ዋና ክፍል ፥ ንዑስ ክፍል /ሕትመት እና ሚዲያ/  የተዘጋጀ ::
   #share
Contact: https://t.me/finotehiwot1927
.Facebook...
https://www.facebook.com/FinoteHiwotSundaySchool
.YouTube... https://www.youtube.com/channel/UCWVKGH0mSJl47u44uopEb2w,
.Telegram...
https://t.me/finotehiwotee
http://tiktok.com/@finotehiwot
     www.finotehiwotsundayschool.com
#ቀዳሚት_ሥዑር_ (#ሥዑር_ቅዳሜ)፤  #ገብረ_ሰላመ_፤ (#ለምለም_ቅዳሜ)
#ሰንበት_ዐባይ #ቅዱስ_ቅዳሜ#ቀዳሚት_ሰንበት

#ቀዳሚት_ሰንበት፤ እግዚአብሔር ፍጥረታትን ፈጥሮ ከፈጸመ በኋላ ያረፈባት ስለሆነች፤ የእግዚአብሔር የዕረፍት ዕለት፤ ቀዳሚት ሰንበት (የዕረፍት ቀን) ትባላለች፡፡

#ሰንበት_ዐባይ (ታላቋ ሰንበት)፤ የመጀመሪያዋ ሰንበት በመሆኗ ታላቋ ሰንበት ትባላላች፡፡

#ቀዳሚት_ሥዑር_ (#ሥዑር_ቅዳሜ)፤ እግዚአብሔር ሥነ ፈጥረትን ከመፍጠር ዕረፍት እንዳደረገባት ዅሉ፣ የፍጥረት ርእስ የኾነውን አዳምን ለማዳን ሕማምና ሞት የተቀበለው አምላካችን ክርስቶስ በከርሰ መቃብር አርፎባታል፡፡ (ማቴ. ፳፯፥፷፩)፡፡
፠ ‹ሥዑር› የተባለችበት ምክንያትም በዓመት አንድ ቀን ስለምትጾም (የጾም ቀን በመኾኗ) ነው፡፡
የጌታችን እናት ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ወዳጆቹ ቅዱሳን ሐዋርያትና ሌሌችም የጌታ ወዳጆች ጌታችን ተላልፎ ከተሰጠበት ዕለት ጀምሮ ብርሃነ ትንሣኤውን እስኪያዩ ድረስ እህል ውኃ በአፋቸው አልዞረም፡፡ ይመኩበትና ተስፋ ያደረጉት የነበረ አምላካቸው በመቃብር ስላረፈ ዕለቷን ሞቱን በማሰብና ትንሣኤውን በመናፈቅ በጾም አክብረዋታል፡፡
፠ የቻልን ሕዝበ ክርስቲያንም ይህን መነሻ በማድርግ ከዐርብ ጀምረን በማክፈል (በመጾም) እህል ውኃ ሳንቀምሱ ለሁለት ቀናት እናድራለን (እንካፍላለን)፡፡ እንደ ዋልድባና ማኅበረ ሥላሴ ባሉ ገዳማት ያሉ ታላላቅ አባቶችና ወንድሞች ደግሞ ከሆሳዕና አንዳንዶችም ከዕለተ ረቡዕ ጀምረው ለ7ት ቀናት ወይም ለ3ት ቀናት ያከፍላሉ፡፡

#ገብረ_ሰላመ_፤ (#ለምለም_ቅዳሜ)
ቅዳሜ የጠዋቱ ጸሎት ሲፈጸም ካህናቱ ‹‹ገብረ ሰላመ በመስቀሉ፤ (በመስቀሉ ሰላምን አደረገ፥ መሠረተ)›› እያሉ በቤተ ክርስቲያን ለተሰበሰቡ ምእመናን የምሥራች ቄጠማ ያድላሉ፡፡
፠ ቄጠማው በኖኅ ዘመን በንፍር ውኃ ምደር በተጠለቀለቀች ጊዜ፤ ኖኅ ወደ መርከብ ይዟቸው ከገባው እንስሳት መካከል የውኃውን መጉደል ለመረዳት ርግብን በመርከብ መስኮት አሾልኮ ልኮ እርሷም ቄጠማ በአፏ ይዛ በመመለስ የምሥራች ምልክት፥ የውኃውን መድረቅ እንደተነገረችውና እንደተደሰተ ሁሉ (ዘፍ. ፱፥፩-፳፱)፡፡ ‹‹በክርስቶስ ሞት፤ ሞተ ነፍስ ከሰው ልጆች ተወገደ፤›› ስንል ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቅዳሜ ጠዋት ደባትር መዘምራን ዝማሬን ካቀረቡ በኋላ ለልጆቿ ቄጠማ ታድለናለች፡፡ የምሥራች ተምሳሌት የኾነውን ቄጠማም፤ ከሲኦል ቃጠሎ ወደ ጥንተ ማኅደራችን ገነት መመለሳችንን  ለመመስከር በግንባራችን እናስረዋለን፡፡

#ቅዱስ_ቅዳሜ፤ ለ5500 በሲኦል ሲማቅቁ የነበሩ ነፍሳትን ሰላም ለሁላችሁን ይሁን ብሎ ወደ ገነት አስገብቷቸዋልና፤ ይህች ቅዳሜ ቅዱስ (የተለየች) ቅዳሜ ትባላለች፡፡

አውረድዎ፥ አውረድዎ፥ አውረድዎ እምዕፅ፤
ወአምጽኡ አፈዋተ ከርቤ ሕዉስ፡፡

ሃሌ ሉያ ዮሴፍ ወኒቆዲሞስ ገነዝዎ ለኢየሱስ፤
በሰንዱናት ለዘተንሥአ እሙታን፡፡
፠ በፌስቡክ ሊያገኙን ከፈለጉ፤ https://www.facebook.com/የቀጨኔ-ደብረ-ሰላም-መድኀኔዓለምና-ደብረ-ትጉሃን-ቅዱስ-ገብርኤል-ቤተ-ክርስቲያን-ፍኖተ-ሕይወት-ሰንበት-ትምህርት-ቤት-1620932764891482/
፠ በቴሌግራም ሊያገኙን ከፈለጉ፤ https://t.me/medihanaelem
፠ በዩቲዩብ ሊያገኙን ከፈለጉ፤ Https://m.youtube.com/channel/UCWVKGH0mSJl47u44uopEb2w
🌿🌿🌿🌿🌿🌿🌿🌿🌿
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

በማኅሌት ዜማ የቤተክርስቲያን ጌጥ የሆነ ሊቁ ካህን
የመንፈሳዊ ቅኔ ጀማሪ
የዜማ ምልክቶች መሥራች
በትዕግሥቱ ዓለምን የናቀ መናኝ

የአባታችን ቅዱስ ያሬድን ዜማ በታላላቅ መምህራን እና ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን የሚዳሰስበት ልዩ ሴሚናር ተሰናድቷል፡፡

🗓እሑድ ግንቦት 4 ቀን
🕘ከ09፡00 ጀምሮ በውሉደ ያሬድ ሰንበት ትምህርት ቤት አዳራሽ አይቀርም!

ቅዱስ ያሬድ የተሠወረበትን ዓመታዊ በዓል ምክንያት በማድረግ

ዜማ አርያም
    ልዩ መንፈሳዊ ጉባኤ

🗓ከግንቦት 1 እስከ 11 በየቀኑ በልዩ ልዩ መርሐ ግብሮችን ይጠብቆታል፡፡


"ጽዮንን የሚወዳት አይደክምም"
                          ቅዱስ ያሬድ   

🌿🌿🌿🌿🌿🌿🌿🌿🌿
ꔰ ꔰꔰእንኳን ለእመቤታችን 2031ኛ ዓመት በዓለ ልደት አደረሳችሁꔰ ꔰꔰ
ꔰ  #ልደታ_ለማርያም  ꔰ
#ልደቷ_መጽሐፍ_ቅዱስ_ላይ_ከሌለ_ተቀባይነት_እንዴት_ይኖረዋል? ꔰ
ሰላም ለልደትኪ እማኀፀነ ድክምት ሥጋ
ድኅረ ኀለፋ ውርዙት ወድኅረ ትክቶ ኃደጋ
#የግንቦት_ልደታ_ለማርያም_ክብረ_በዓልና_የእመቤታችን_በዓላት
በቀደመዉ ዘመን በዘመነ ብሉይ ‹‹የቤተ መቅደስ መታደስ በዓል›› ይከበር እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳል፡፡ ይህ በዓል እስከ ጌታችን ዘመንም ይከበር ነበር፡፡ /ዮሐ. 10፥22/ በሐዲስ ኪዳን እውነተኛ የእግዚአብሔር ማደሪያ ቤተ መቅደስ ለሆነችዉ እመቤታችን በስሟ በዓል ሊደረግላት ይገባል፤ ‹‹የጻድቅ መታሰቢያ ለዘላለም ይኖራል›› እንዳለ ቅዱስ ዳዊት መዝ. 111፥7በተአምረ ማርያም ላይ በዝርዝር እንደተቀመጠዉ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም 33ት በዓላት አሏት፡፡ ከእነዚህ በዓላት ሁሉ አስበልጣ የምትወደዉ በዓለ ልደቷን እንደሆነ በአጼ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት ከዐረብኛ ወደ ግእዝ በተተረጎመዉ እመቤታችን በተለያዩ ሀገራት ያደረገቻችዉን ገቢረ ተአምራት በኢትዮጵያ ከተፈጸሙት ጋር አካቶ የያዘው ተአምረ ማርያም በዝርዝር ያስረዳል፡፡

#ልደቷ_መጽሐፍ_ቅዱስ_ላይ_ከሌለ_ተቀባይነት_እንዴት_ይኖረዋል?
      በመጽሐፍ ቅዱስ ያልተካተቱና ምሉዕነት የሌላቸዉ ታሪኮች በአዋልደ መጻሕፍት እንደሚሟሉ ራሱ መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳል ለምሳሌ ስለ ቅዱስ ዳዊት የሚናገረዉ መጽሐፈ ዜና መዋዕል ‹‹የንጉሡም የዳዊት የፊተኛዉና የኋለኛዉ ነገር በነቢዩ በናታን ታሪክ እንዲሁም በባለ ራእዩም በጋድ ታሪክ ላይ ተጽፏል›› ይላል፡፡ 1ኛ ዜና 29፥29

#የእመቤታችን_የልደቷ_ታሪክ
የእመቤታችን ወላጆች በአብዛኛዉ አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ‹‹ሐና››ና ኢያቄም/ዮአኪን በሚለዉ ስም የሚጠሩ ሲሆን ሐና በቤተልሔም ተወልዳ እንዳደገች ታሪክ ያስረዳል፡፡ በናዝሬት ገሊላ ለመሥዋዕት የሚሆኑ በጎች የሚያቀርብ እንዲሁም እረኛ የነበረዉን ኢያቄምንም አግብታለች፡፡ ቅድስት ሐና ወደ ቤተ መቅደስ ስትሔድ እርግብን አይታ ታለቅስ ነበር፡፡ ከብዙ ልመና በኋላ ቅድስት ድንግል ማርያምን ግንቦት አንድ ቀን በደብረ ሊባኖስ ወልደዋል፡፡
ስለ ሐና መካንነት ወደ ቤተ መቅደስ ሄደዉ መባዕ ሲያቀርቡ ካህኑ ያልተቀበላቸዉ መሆኑን በብስራተ መልአክ ልጅ እንደሚወልዱ እንደተነገራቸዉ በእኛ ቤተ ክርስቲያን የሚተረከዉና በሌሎች ኦርቶዶክሳዊያን አብያተ ክርስቲያናት የሚነገረዉ ታሪክ ተመሳሳይ ነዉ፡፡

#እመቤታችን_የት_ተወለደች?
እመቤታችን ስለተወለደችበት ስፍራ በዓለም የተለያዩ ሐሳቦች ይስተጋባሉ፡፡ ሌላዉ ቀርቶ በዶግማ አንድነት ባላቸዉ አኃት አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ በእንዲህ ዓይነት ታሪክ ነክ ጉዳዮች ላይ ልዩነት መኖራቸዉ የተለመደ ክስተት ነዉ፡፡ የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሁለት ሐሳቦች የሚያነሱ ሲሆን፤ አንደኛዉ ‹‹ድንግል ማርያም ብስራተ መልአክ በሰማችበት ናዝሬት ተወልዳለች›› የሚል ነዉ፡፡ ሁለተኛዉ ሐሳብ ደግሞ ‹‹ከሦስተኛዉ ክ/ዘመን ወዲህ የማርያም መግቢያ ተብሎ በሚታወቀዉ ከኢየሩሳሌም የቅድስት ሐና የክሩሲድ ቤ/ክ በታች ነዉ የተወለደችዉ የሚል ነዉ፡፡
የግብጽ ስንክሳር የእመቤታችን የትዉልድ ስፍራ በናዝሬት ነዉ ይላል፡፡ የኢትዮጵያ ስንክሳር ግን በቀደምትነታቸዉ ተጠብቀዉ የቆዩ ከመሆናቸዉ አንጻር ተአማኒነታቸዉ የጎላ መሆኑን ያሳያል፡፡ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት የእመቤታችን የትዉልድ ስፍራ ሊባኖስ የተባለዉ ተራራማ ሀገር ነዉ፡፡ ሊባኖስ ከገሊላ በስተ ሰሜንና ከፊንቄ በስተምስራቅ ይገኛል፡፡ ‹‹ሙሽራየ ሆይ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነይ›› መኃ. 4፥7 የሚለዉ ቃለ ትንቢት ምሥጢርም የአመቤታችን መካነ ልደት የሊባኖስ ተራራ ስለመሆኑ የሚያጠይቅ እንደሆነ ምስክርነታቸዉ የታመነ የቤተ ክርስቲያን ሊቃዉንት ያስረዳሉ፡፡

#የልደታ_ለማርያም_በዓል_መቸ_ነዉ?
እንደተወለደችበት ሥፍራ የእመቤታችን የልደት ቀን እንዲሁ አወዛጋቢ ነዉ፡፡ በ6ኛዉ ና7ኛዉ መቶ/ክ/ዘመን ነዉ የሚሉ የተለያዩ ሃሳቦች የተጻፉ ሲሆን Encyclopaedic of Christian antiquities ደግሞ በ431 ዓ/ም ከተካሄደዉና ንስጥሮስ ከተወገዘበት ከጉባኤ ኤፌሶን በኋላ ነዉ ይላል፡፡ በዓለም ቅዱሳንን የሚያከብሩ አብያተ ክርስቲያናት የቅዱሳንን በዓለ እረፍታቸዉን የሚያከብሩ ሲሆን ልደታቸዉ የሚከበረዉም በሦስተኛ ደረጃ የመጥምቀ መለኮት ቅ/ ዮሐንስ፤ በሁለተኛ ደረጃ የእመቤታችን ቅ/ድንግል ማርያም ልደት ነዉ፡፡ በአንደኛ ደረጃ ለስም አጠራሩ ክብር ይግባዉና የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ነዉ፡፡
የአመቤታችን ልደት በምዕራባዊያን አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ኬ.ክ በመጋገር፡ የአመቤታችን ትንሽ ሀዉልት በማቆም ዐስር ሻማዎችን በማብራት ያከብራሉ፡፡

#የድንግል_ማርያም_ልደት_ለምን_ይከበራል?
* ስለ መጥምቁ ዮሐንስ ልደት በመልአኩ ቅ/ገብርኤል አንደበት‹‹በመወለዱ ብዙዎች ደስ ይላቸዋል›› በማለት ተነግሯል (ሉቃ 1-14)፤ ምክንያቱም ቅ/ዮሐንስ የጌታ መንገድ ጠራጊ፥ የአዋጅ ነጋሪ በመሆኑ ነዉ፡፡ የቅዱስ ዮሐንስ መወለድ ለብዙዎች ደስታ ምክንያት ከሆነ፤ የድንግል ማርያም ልደትማ ምንኛ የሚያስደስት ይሆን!?፡፡ስለሆነም ከጌታ ቀን ቀጥሎ የምንደሰትበት ትልቁ ቀን የእርሷ የልደት ቀን ነዉ፡፡
* የቀርጤሱ ቅ/እንድርያስ ስለ ከበረ ልደቷ እንዲህ ብሏል ‹‹ይህ በዓል በሐዲስና በብሉይ ኪዳን መካከል መገኛ ሆነ፡፡ ምሳሌዎቹ በእዉነታ፣ አሮጌዉ በአዲስ ቃል ኪዳን ተተኩ፡፡ ፍጥረት ሁሉ በደስታ ይዘምራል የዚህን ቀንም ደስታ ይካፈላል፡፡ ይህ መቅደሱን የሰራበት ዕለት ነዉ፡፡ ይህ ዕለት ትልቅ ሕንፃ የታነጸበትና ፍጡር የፈጣሪ ማደሪያ ለመሆን የተዘጋጀበት ዕለት ነዉ፡፡››ብሏል
* እመቤታችን  ለፀሐዩ መምጣት የተዘረጋች ሰማይ፤ በቅድመ አያቶቿ በነ ቴክታና ጰጥሪቃ ሕልም እንደታየችዉ በሌሊት የምታበራ ጨረቃ፤ የብሉይ ኪዳን ማብቂያ የሐዲስ ኪዳን መጀመሪያ ናትና ልደቷ ለሰዉ ልጅ ሁሉ ደስታ ነዉ፡፡
* ነቢያት በብዙ ሕብረ አምሳል የተናገሩላት ‹‹መሠረቶቿ የተቀደሱ ተራራዎች ናቸዉ››፤ ‹‹ከእሴይ ስር በትር ትወጣለች አበባዋም ከግንዱ ይወጣል››፤ ‹‹ሙሽራየ ሆይ ከሊባኖስ ነይ››፤ …. ብለዉ የተናገሩላት ቅ/ድ/ማርያም ልደቷ የትንቢታቸዉ ፍፃሜ ነዉና ታላቅ ደስታቸዉ ደስታችንም ነዉ፡፡ (መዝ. 86፥1፣ ኢሳ. 11፥1፣ መኃ. 4፥7)ጂነአ
* በዓለም ላይ የብዙ ታዋቂ ሰዎች ልደት ከሞቱም በኋላም ጭምር በታላቅ ድምቀት ይከበራል፤ ታዋቂ ያልሆኑ ሰዎች ልደትም እንዲሁ ይታሰባል፡፡ ለሰዉ ልጅ መዳን ምክንያት የሆነች የአምላክ እናት የተወለደችበት ቀን ግን ምንኛ ሊከበር ይገባዉ ይሆን!

#የግንቦት_ልደታ_በዓል_አከባበር
ሐናና ኢያቄም ከአይሁድ ለማምለጥ ተሰደዉ በአድባረ ሊባኖስ ስር  እመቤታችንን ወለዱ በወቅቱ ከቤት የወጡት ለሽሽት ነበርና ስንቅ ስላልያዙ ምግባቸዉ ‹‹ንፍሮና ጥራጥሬ›› ነበር፡፡ ይኼንን ትዉፊት በመያዝ በዓሉ ከቤት ዉጭ ንፍሮ እየተበላ ይከበራል፡፡ ሆኖም ግን በበጎ ነገሮች ሰበብ ክፉ ዓላማዉን ማስፈጸም የሚፈልገዉ ዲያቢሎስ በማር መሃል መርዝን ከሚጨምርባቸዉ መንፈሳውያት በዓላት አንዱ የግንቦት ልደታ የእመቤታችን በዓል ነዉ፡፡ አንዳንዶች በድፍረት ለአድባር ለዉጋር ነዉ ፣ቆሌዉን ለመለመን ነዉ፣ እያሉ ንፍሮ የሚበትኑ፣ ፈንድሻ የሚጥሉ፣ ቡና የሚረጩ፣ ቂቤ የሚቀቡ፣ የከብት ደም የሚያፈሱ፣  እነዚህ በእርግጥም ጣዖት አምላኪዎች ናቸዉ፡፡
ሰላም ለልደትኪ እማኀፀነ ድክምት ሥጋ
ድኅረ ኀለፋ ውርዙት ወድኅረ ትክቶ ኃደጋ
ማርያም ሥመሪ ወጸሐቂ እንበለ ንትጋ ፤
ለማየ ንጽሕኪ ትረስዩኒ ፈለጋ፤
እስመ ንጽሕ   ይሁብ ምገሰ ወጸጋ፡፡


/በቀጨኔ ደ.ሰላም መድኀኔዓለምና ደ.ት.ቅ.ገብርኤል ቤ.ክ ፍኖተ ሕይወት ሰ.ት.ቤት ፤      የተዘጋጀ ::


  #share
Contact: https://t.me/finotehiwot1927
.Facebook...
https://www.facebook.com/FinoteHiwotSundaySchool
.Telegram...  https://t.me/medihanaelem
http://tiktok.com/@finotehiwot
     www.finotehiwotsundayschool.com 
YouTube    https://www.youtube.com/channel/UCWVKGH0mSJl47u44uopEb2w
Telegram (https://t.me/finotehiwot1927)

ፍኖተ ሕይወት ሰንበት ት.ቤት .