Ethiopian Red Cross Society
6.26K subscribers
3.68K photos
82 videos
486 links
This is Ethiopian Red Cross Society Headquarters' Telegram channel, which was set up to discuss humanitarian issues and the organization's humanitarian assistance efforts.
Download Telegram
👍8❤3
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ወላይታ ዞን ቅርንጫፍ ጽ/ቤት 11ኛ ጠቅላላ ጉባዔውን አካሄደ፡፡

ጠቅላላ ጉባዔውን በንግግር የከፈቱት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የቦርድ አቃቤ ነዋይ አቶ ዘላለም ዘሪሁን እንዳሉት፣ የክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ በአዲስ መልክ እየተደራጀ በመሆኑ ነባር የዞን ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ የማኅበሩን አባላት ቁጥር ለማሳደግ የሚደረገው ጥረትም ተጠናክሮ ሊሰራበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ዱንዳ በጉባዔው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ አምቡላንሶችን በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል እንዲሁም የማኅበሩን ሰብዓዊ ተልዕኮ በህብረተሰቡ ውስጥ ለማስረፅ ተናቦና ተቀናጅቶ መስራት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል። የህብረተሰቡን ተሳትፎ ለማስፋት የቀይ መስቀል ክበባትን በትምህርት ቤቶች ማቋቋም እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡

የወላይታ ዞን ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ደስታ ዳና በበኩላቸው፣ እያንዳንዱ የማኅበሩ ተግባር የህብረተሰቡን ባለቤትነት ባረጋገጠ መልኩ መከናወን እንደሚገባው በመግለፅ፣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋርም ተቀናጅቶ መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በዕለቱ የተጓደሉ የቦርድ አመራሮችን ለመተካት አዳዲስ የቦርድ አባላት የተመረጡ ሲሆን፣ በአባላት ማበራከት ከፍተኛ አፈፃፀም ላስመዘገቡ የወረዳ መዋቅሮች የዋንጫና ሰርተፊኬት ተበርክቶላቸዋል፡፡

በጉባዔው ላይ የጠቅላላ ጉባኤው አባላትን ጨምሮ የተጋበዙ የዞን እና ወረዳ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
👍7❤1
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ከኔዘርላንድስ ቀይ መስቀል ጋር በመተባበር ከአውሮፓ ህብረት የሰብአዊ እርዳታ (ECHO) በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በሶማሌ ክልል፣ ሸበሌ ዞን፣ ጎዴ እና ኤሌሌ ወረዳዎች ለሚገኙ ለድርቅ አደጋ ተጋላጭ አባወራዎች ሁለገብ የገንዘብ ድጋፍ አደረገ፡፡

በአካባቢው ካለፈው ጥቅምት እስከ ታህሣሥ ወር ይጠበቅ የነበረው ዝናብ ባለመጣሉ ሊከሰት የሚችልን የድርቅ አደጋ ለመከላከል በአጠቃላይ በሁለቱ ወረዳዎች 1,800 አባወራዎች የገንዘብ ድጋፉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርገዋል፡፡

በኤሌሌ ወረዳ ቦቅ ቢላል ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ፈርዶሳ ኡስማን ድጋፉን አስመልክቶ እንደተናገሩት፣ "ቀይ መስቀል 11,300 ብር የሰጠን ሲሆን፣ ይህም ያለብንን የምግብና ውሃ ችግር ለመፍታት ይጠቅመናል፡፡ ከብቶቻችንም የሞቱብን በመሆኑ ድጋፉ ለኑሮአችን የሚያስፈልገንን ወጪ ለመሸፈን ይጠቅመናል፡፡ ለተደረገልን ድጋፍም እናመሰግናለን" ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በድርቅ እና በሌሎች አደጋዎች ለጉዳት የተጋለጡ ወገኖቻችንን ህይወት ለመታደግ ድጋፍ በማድረግ ላይ ሲሆን፣ በእነዚህ ሁለት ወረዳዎች ለሰጠው ምላሽ ድጋፍ ላደረጉለት ለአውሮፓ ህብረት የሰብአዊ እርዳታ እና ለኔዘርላንድ ቀይ መስቀል ምስጋናውን ያቀርባል፡፡
👍14