Dn Abel Kassahun Mekuria
18.5K subscribers
658 photos
61 videos
1 file
971 links
ይህ ኦርቶዶክሳዊ የሆኑ የተለያዩ ትምህርቶችን የሚያገኙበት በባለቤቱ የተከፈተ ቻነል ነው።

ይወዳጁን

ለፌስቡክ ገጽ
https://www.facebook.com/AbelKassahunMekuria12?mibextid=ZbWKwL

ለyoutube
https://youtu.be/s6Cn-jMYjrk?si=Tw7lXr62xkGQtL9_

ለInstagram
https://www.instagram.com/abelkassahunm?igsh=OW
Download Telegram
የቅዱስ ኤፍሬም ድርሳናት ፍሬ

በትውልድ እንግሊዛዊው እና ለብዙ ዘመናት የፕሮቴስታንቲዝም አንዱ ቅርንጫፍ በሆነው የአንግሊካን እምነት ውስጥ የቆየው ዕውቁ ሊቅ ሰባስትያን ብሮክ ቅዳሜ ግንቦት 18 (May 25)፣ 2024 ዓ. እ.የሶርያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባል በመሆን በቅብዓ ሜሮን ከብሮ ዋለ።

ሰባስትያን በኦርቶዶክሱ ዓለም በሶርያ የሚገኙ ጥንታዊ የሆኑ የነ ቅዱስ ኤፍሬም ድርሳናትን ከጥልቅ ሐተታዎች ጋር በመተርጎም እና የሶርያን ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ሕይወት በማጥናት በሰፊው ይታወቃል። በዚህ ዙሪያ የሠራቸው እና ያሳተማቸው የጥናት እንዲሁም ትርጉም መጻሕፍት ዝርዝር ብቻ ወደ ሠላሳ ገጽ ይሆናሉ። የሶርያም ቤተ ክርስቲያንም ለዚህ ድካሙ የቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ሜዳልያ (Medal of St. Ephrem the Syrian) የተባለውን በክብር አበርክታለታለች።

እነዚያን ወርቅ የሆኑ አጥንት ድረስ ዘልቀው የሚወጉ የማር ኤፍሬምን ድርሳናት ከውጭ (በሃይማኖት) ሆኖ መተርጎሙ ሁሌ ያሳዝነኝ ነበር። ታምሞ ግን የሚድንበትን መድኃኒት ተሸክሞ እንደሚቸገር ምስኪን ሰው አድርጌም አስበው ነበር። ድርሳናቱ መቼ ነው ወደሚድንበት መርከብ እየመሩ የሚያስገቡት ብዬ ብዙ ጊዜ እጠይቅ ነበር።

ያለፈው ቅዳሜ ግን ይህን ኀዘን የሚሽር የምሥራች ሰማሁ። ለካስ ቅዱሱ የቀጠረለት ቀን ነበር?! ይኸው የኤፍሬም ቀለም የበላውን (ያቃጠለውን) ምሁር ከኦርቶዶክሳዊው ካህን ስር በትሕትና በርከክ ብሎ አየሁት።

ይህ መመለስ የቅዱሱ ምልጃ እና በቅዱስ ኤፍሬም ድርሳን ያለቀሱ የብዙ የዋሃን ምእመናን እንባ ውጤት ነው።

የአበው ድርሳን አሁንም በሥራ ላይ ነው!!!

ዲያቆን አቤል ካሣሁን
selam@dnabel.com
176❤‍🔥18👏8👍4🥰3
“የእግዚአብሔር ጆሮዎች ለመስማት ድምፅን የሚጠባበቁ ይመስላቸዋልን? እንዲህስ ካልሆነ ታዲያ የእነርሱ ጮኾ መጸለይ ጎረቤቶቻቸውን የሚያበሳጭ ነገር ከመሆን በቀር ሌላ ምን ጥቅም አለው?”

ሊቁ ጠርጠሉስ፣ በእንተ ጸሎት

https://t.me/Dnabel
106🥰33👏8
ፍርድ የእግዚአብሔር ነው፡፡ እኛ ግን ወንድሞቻችን ላይ በመጨከን ስንት ጊዜ በክርስቶስ የፍርዱ ዙፋን ላይ ተቀመጥን? የሰውን ድካም ሳንረዳ ፈጥነን በመፍረድ ስንት ጊዜ ራሳችንን በእግዚአብሔር ቦታ አስገባን? እስኪ ዮሴፍን እናስበው፡፡

ወደ ግብጽ ባሪያ አድርገው በግፍ የሸጡት ወንድሞቹ ከአባታቸው ሞት በኋላ እርሱ ወደ ተሾመበት ግብጽ መምጣት በፈለጉ ጊዜ፣ የክፋታችንን ብድራት ያስከፍለናል ብለው ስለፈሩ ‹‹በደላችንን ተውልን›› ሲሉ መልእክተኛ ልከውበት ነበር፡፡ የዋሁ ዮሴፍም ይህንን ሲሰማ እያለቀሰ እንዲህ አላቸው ‹‹አትፍሩ፤ እኔ በእግዚአብሔር ፋንታ ነኝን?››፤ አይደለም ሳታውቀው ዐውቀኸው እንኳን በበደለህ ወገንህ ላይ ለመፍረድ ልብህ በከጀለህ ጊዜ ለራስህ የዮሴፍን ጥያቄ ጠይቀው፡፡

‹‹እኔ በእግዚአብሔር ፋንታ ነኝን?›› (ዘፍ 50፡19)

ዲያቆን አቤል ካሣሁን
abelmekuria2@gmail.com
194🙏34😢116👍5🔥2🥰2👏1👌1
የኖኅ መርከብ ፍጥረታትን ሁሉ ከጥፋት ውኃ ከማዳኗ ጀርባ እንዴት እነዚያን ሁሉ ግዙፋን፣ ማዕከላውያን እና ቀሊላን የምድር ፍጥረታት የምትሸከም እና ለሁሉ የምትበቃ መርከብ ሆና ታነጸች የሚለው በጣም የሚያስደንቅ ነገር ነው።

በእርግጥ የመርከቢቱን ርዝመት፣ ወርድ እና ከፍታዋን መጥኖ እንዲህ ሥራ ያለው፤ ከእጸዋትም መርጦ “ከጎፈር እንጨት” አዘጋጅ ብሎ ያዘዘው “የፈጠራቸው እና የሚያውቃቸው አምላክ ስለሆነ” መርከቡ ባይሸከማቸውና ባይበቃቸው ነበር የምንገረመው።

ዛሬ ግን በኖኅና በልጆቹ ሳይሆን በመለኰት እጅ ስለ ታነጸችው ሕያው መርከብ፥ ወርድና ቁመቷ፣ ጎንና ስፋቷ በሰው መጠን ስለሆነው ስለምትናገረዋ ነባቢት ሐመር ድንግል ማርያም እያሰበ ኅሊናዬ ከመደነቅ አልፎ ተጨነቀ። የኖኅ መርከብ እነዚያን ፍጥረታት መሸከም እንድትችል በመጠንም፣ በስፋትም ትልቅ ሆና ነበር የታነጸችው። ድንግል ማርያም ግን ከዕብራውያን ሴቶች የተለየ ግዘፍ ሳይኖራት፣ በዓለም ያሉትን አንስት በአካል መጠን ሳትበልጣቸው በውስጧ ወርድ ቁመት፣ ላይ ታች፣ ግራ ቀኝ የሌለው፤ እንኳን የኖኅ መርከብ ዓለማት የማይወስኑትን አምላክ ተሸከመችው። ስለዚህ ድንቅ ነገር ከአባ ሕርያቆስ ጋር ሆኖ “ከስፋት ጋር የሆድ መጥበብ” እንደ ምን ያለ ነው? ብሎ ከመገረም በቀር ምን ልንል እንችላለን?

የኖኅ መርከብ ምንም ሞገድ ባይሰባብራት ውኃ ባያሰጥማትም እሳት ግን በውስጧ አልያዘችም ነበር። ፊቱ እሳት፣ ልብሱ እሳት፣ ቀሚሱ እሳት የሆነ አምላክ ያደረባት፤ መለኰታዊ ነበልባል የተሳፈረባት የማትቃጠለው መርከብ ድንግል ማርያም ናት!!!


ዲያቆን አቤል ካሣሁን
የካቲት ፫ - ፳፻፲፰ ዓ. ም.
https://t.me/Dnabel
199🙏19🥰9👍3🔥1
+++ "የምወደው ልጄ ይህ ነው" +++

ጌታችን ከሐዋርያቱ መካከል "አዕማድ መስለው የሚታዩ ያዕቆብና ጴጥሮስ፣ ዮሐንስንም" ወደ ቅዱሱ የታቦር ተራራ ብቻቸውን ይዟቸው ወጣ።(ገላ 2፥9) ከተራራውም ጫፍ ሲደርሱ ሦስቱ ደቀ መዛሙርት የመምህራቸው ፊት እንደ ፀሐይ ሲያበራ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ሲሆን ተመለከቱ። እነሆም ከቀደሙት ጻድቃን ታላላቆቹ ሙሴና ኤልያስ በታቦር ተገኝተው ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው።

እነዚህ የብሉይ ኪዳን ነቢያት የትንቢታቸው ፍጻሜ ከሆነው ክርስቶስ ጋር ምን ተነጋገሩ? መቼም በጊዜው ከጌታ ጋር ውለው ያድሩ እንደ ነበሩት ተማሪዎቹ ሐዋርያት "አትሙትብን" አይሉትም። በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት ሱባኤ የያዙለትና ደጅ የጠኑት የድኅነት ተስፋ እናዳይፈጸም "ይቅር አትሙት" እንዴት ይላሉ? ስለዚህ ከብሔረ ሕያዋን የመጣው ኤልያስና ከብሔረ ሙታን የመጣው ሙሴ በአንድ ላይ "በኢየሩሳሌም ሊፈጸም ስላለው ስለ መውጣቱ (ስለ መከራው፣ ሞቱ)" ያነጋግሩት ነበር።(ሉቃ 9፥31)

በታቦር ተራራ ላይ የብሉይ ኪዳንና የሐዲስ ኪዳን መልእክተኞች ተገናኙ። በባሕር ላይ በእግሩ የተራመደው ጴጥሮስ፣ የኤርትራን ባሕር እጁን ዘርግቶ የከፈለው ሙሴን አየው።(ማቴ 14፥29፣ ዘጸአ 14፥21) የሰማርያ ሰዎች በተቃወሙ ጊዜ "እሳት ከሰማይ ወርዶ ያጥፋቸው" ያሉ ያዕቆብና ዮሐንስ፣ ከሰማይ እሳት አዝንሞ ሃምሳ አንዱን ወታደሮች ያስበላ ኤልያስን ተመለከቱት።(ሉቃ 9፥54፣ 2ኛ ነገ 1፥10)
… ይቀጥላል
60🙏8
ሁለቱ ምስክሮች እንደ ተሰወሩም ወዲያው ቅዱስ ጴጥሮስ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ብትወድስ ሦስት ዳሶች እንሥራ ብሎ ጌታውን ጠየቀ። ሐዋርያው በዚህ ተራራ ላይ መቅረት የፈለገው ያለ ምክንያት አይደለም። መድኃኒታችን አስቀድሞ ወደ ኢየሩሳሌም ይሄድ ዘንድ ከሽማግሎችና ከካህናት አለቆች ከጻፎችም ዘንድ ብዙ መከራ ይቀበልና ይሞት ዘንድ እንዳለው ሲነግራቸው ቅዱስ ጴጥሮስ "አይሁንብህ፤ አይድረስብህ" ሲል ሊከላከለው ሞክሮ ነበር። ለዚህም በጊዜ "ወደ ኋላዬ ሂድ፥ አንተ ሰይጣን፤ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና ዕንቅፋት ሆነህብኛል" ተብሎ ተገስጾበታል።(ማር 9፥31-33) ይሁን እንጂ አሁንም ቅዱስ ጴጥሮስ ያለውን ሁሉ እድል ተጠቅሞ ጌታን ወደ ኢየሩሳሌም ከመሄድና በካህናት አለቆች እጅ ተላልፎ ከመሰጠት ማስቀረት ስለሚፈልግ "ጌታ ሆይ፦ በዚህ(በታቦር ተራራ) መሆን ለእኛ መልካም ነው" ብሎ ተናገረ።

እርሱም ይህን ገና ሲናገር ሳለ እነሆ፥ ብሩህ ደመና ጋረዳቸው። ከደመናው "በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት" የሚል ድምፅ መጣ። ሐዋርያቱ ይህን ድምጽ የሰሙት ሙሴ እና ኤልያስ ከክርስቶስ ተለይተው ከሄዱ፣ እነርሱም ወድቀው ከነበሩበት ከተነሡ በኋላ ነው። ይህም ከደመናው ውስጥ ሲወጣ ስለ ሰሙት ቃል "ለማን የተነገረ ይሆን?" ብለው እንዳይጠይቁና ምስክርነቱ ለክርስቶስ ብቻ የተሰጠ መሆኑን በማያሻማ ሁኔታ እንዲረዱ ነው። በዚሁም ላይ ደመናው ወርዶ የጋረደው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ብቻ ሳይሆን ሐዋርያቱንም ጭምር ነበር። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንደሚነግረን ደመናው ጌታን ብቻ ጋርዶት ቢሆን ኖሮ፣ ሐዋርያቱ "እርሱን ስሙት" የሚለውን ቃል ራሱ ክርስቶስ ለራሱ የተናገረው ሊመስላቸው በቻለ ነበር።
ቅዱስ ጴጥሮስ "አትሙት" ያለው መምህሩን በፍጹም ልቡ ስለሚወደው መሆኑ አያጠራጥርም። ነገር ግን ጴጥሮስ ጌታን የቱንም ያህል ቢወደው፣ ፍቅሩ ግን ከወለደው ከባሕርይ አባቱ ከአብ አይደለም ሊበልጥ ሊነጻጸርም አይችልም። ታዲያ አብ በእርሱ ደስ የሚለው፣ የሚወደው፣ አንድያ ልጁ እንዲሞት ፈቃዱ ከሆነ፣ የአብን ያህል ሊወደው የማችለው አረጋዊው ጴጥሮስ ለምን "አትሙት" እያለ ይቃወማል?!

አብ ምትክ የሌለው ልጁ ወልድ ሰው ሆኖ በክፉዎች እጅ ሲንገላታ እና እስከ መስቀል ሞት ሲደርስ እያየ ዝም ያለው ስለማይወደው አይደለም። ዓለም ያለ ልጁ መከራና ሞት ስለማትድን ነው እንጂ። ከዚህ ምን እንማራለን? ዛሬም ወደ መከራ የምንገባ የጸጋ ልጆቹ የምንሆን እኛ ክርስቲያኖች "እግዚአብሔር እንዲህ ስሆን ዝም ያለኝ ስለማይወደኝ ነው" አንበል። ባገኘን ጥቂት የሥጋ መከራና ሕመም የሚበልጠውን የነፍስ ጤና የምንሸምት ከሆነ እግዚአብሔር ዝም ይላል። ዝም የሚለው መከራችንን ስለማያይ ሳይሆን ከመከራው ጀርባ ያለው ዓላማ ታላቅና የተቀደሰ እንደ ሆነ ስለሚያውቅ ነው።

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
ነሐሴ 13፣ 2014 ዓ.ም.
ደብረ ታቦር፣ እስራኤል

ቤተሰብ ይሁኑ
121🙏21👍4
በክንፎቻቸው ተሸፋፍነው በፊቱ የሚቆሙለት ቅዱሳን መላእክት፣ ፈጣሪያቸው "እኔ በምድር ወዳጅ አለኝ። እርሱም አብርሃም ነው" ብሎ በነገራቸው ጊዜ እጅግ በመደነቅ ወደ አብርሃም ሄደው "አብርሃም አርከ እግዚአብሔር"/"አብርሃም የእግዚአብሔር ወዳጅ"/ እያሉ ዘምረውለት ነበር። በእውነት እግዚአብሔር "ወዳጅ አለኝ" ስላላቸው እንዲህ የተደነቁ መላእክት፣ "እኔ በምድር እናት አለኝ" ሲላቸው ምን ያህል ተገርመው ይሆን? እመቤታችንንስ በምን ዓይነት ቃል አመስግነዋት ይሆን?

በዛሬው እለት የአምላክን እናት ልዩ በሆነ ምስጋና እና እልልታ ያሳረጓት መላእክት፣ በምድር ሳለች "እይዋት የአምላክን እናት በምድር ትመላለሳለች" እያሉ በስስት የሚያይዋትና መምጣቷን የሚጠባበቁ እመቤታቸው ነበረች። ለዚህም ነው አባቶቻችን በሌሊት ማኅሌት "ተበሃሉ በሰማያት እለ ኪያኪ አፍለሱ፣ ማርያምሰ እንተ በምድር ታንሶሱ" እያሉ ሲወርቡ ያደሩት።

እኛም ንግሥታችንን ወደ ልጇ እልፍኝ ለሸኘንበት፣ መላእክትም እርሷን በደስታ ለተቀበሉባት ለበዓለ ዕርገቷ እንኳን በሰላም አደረሰን!!!

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
ነሐሴ 16፣ 2014 ዓ.ም.
ኢየሩሳሌም፣ እስራኤል
222🙏22👍5
አባ ረሳሁት 🙄
195😢60👍15💔11
በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በግብጽ ስለ ተፈጸመ አንድ ታሪክ ላስታውሳችሁ። በላዕላይ ግብጽ ይኖር የነበረ አንድ ምስጉን ካህን በጊዜው የከተማው ከንቲባ ወደ ሆነው ባለሥልጣን ቢሮ ሄዶ ቤተ ክርስቲያንን በሚመለከት ለከንቲባው ጥያቄ ያቀርብለታል። ይሁን እንጂ ከንቲባው ግን በንቀት ያን የእግዚአብሔር ካህን እያመናጨቀ በጥፊ መትቶ ከቢሮው ያስወጣዋል። በዚህ ድርጊት እጅግ ልቡ ያዘነውም ካህን እንባውን እያፈሰሰ ለአገልግሎት ወደሚጠበቅበት የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ገብቶ የጸሎት ሥርዓቱን አስጀመረ። ካህኑ በቤተ ክርስቲያን ሆኖ ሲጸልይ ሳለ ያ ከንቲባ በመንገድ ሲሄድ ድንገት ዙሪያው ጨለመበት፣ በፈረስ የተቀመጠ አንድ ሰውም ከመንገዱ አስቁሞ "ለምን ካህኑን እንደዚያ አዋርደህ ሰደብህ?" ሲል ጠየቀው። ከንቲባውም ገና መልስ መስጠት ሳይጀምር ያ ፈረሰኛ ፊቱን በጥፊ ጸፋው። ከምቱ ጥንካሬም የተነሣ አንድ ዓይኑ ጠፋ። ይህ እንደ ሆነም ወዲያው ጨለማው ተገፈፈ። ያ ፈረሰኛ ማን ነው?

ካህኑ ሄዶ እንባውን ካፈሰሰለት ከሰማዕቱ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ውጭ ማን ሊሆን ይችላል።



ዲያቆን አቤል ካሳሁን
abelmekuria2@gmail.com
አዲስ አበባ
243🥰14🙏8🔥5👍4👏4🤩2
ዝምታ ራሳችንን የምናይበት ጥሩ መጽሔት(መስታወት) ነው። አብዛኛውን ሰዓት በወሬ ተጠምዶ የሚውል ሰው ራሱን የሚመለከትበት እድል አይኖረውም። በሌሎች ኃጢአት ሲፈርድ፣ ሲተችና ሲያማ ስለሚውል የራሱን ስህተትና ውድቀት ለማወቅ ይቸገራል። ቀኑን ሙሉ እንዲሁ ሲያወራ የሚውል ሰው የሚያሳዝነው ዝም አለማለቱ ብቻ ሳይሆን የሚጠቅም ነገር የማይናገር መሆኑም ጭምር ነው። ነገር ግን ማር ይስሐቅ እንደሚለው "አንድ ሰው ከሰዎች ጋር ብዙ ማውራት ባቆመ ጊዜ ወደ ራሱ ይመለሳል። በእግዚአብሔርም ፊት ምግባሩን ማቅናት ይጀምራል"

የሥጋ አንደበታችንን መቆጣጠርና ዝም ማስባል ስንችል የነፍስ ጆሮአችን ንቁህ መሆን ይጀምራል። ስለዚህም ነፍሳችን ሳይሰለች ከልባችን ደጅ ቆሞ የሚያንኳኳውን የመልካሙን እረኛ ድምጽ ትሰማለች። ደጇንም ከፍታ ታስገባዋለች። ከእርሱም ጋር ለእራት ትሰየማለች።(ራእይ 3፥20) በእውነት ይህ እንደ ምን ያለ መታደል ነው? ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር "የዝምተኛ ሰው ጆሮ የእግዚአብሔርን ድንቆች ትሰማለች" ያለው ለዚህ ይሆን?!

ዲያቆን አቤል ካሣሁን
abelzebahiran@gmail.com
85🙏17🥰7👍3