የህይወት ቃል / Word of life
3.08K subscribers
2.22K photos
9 videos
4 files
38 links
ይህ የቴሌግራም ቻናል በየእለቱ ህይወት ከሆነው ከእግዚአብሔር ቃል አጠር ያለ መልእክት የሚቀርብበት ነው። ይህንን ቻናል በመቀላቀልና አብረን ይህንን የህይወት ቃል እንድንመረምር እናድማችኋለን። ጥያቄ ወይም አስተያየት ቢኖራችሁ በዚህ አድራሻ ጻፉልን። @melakalex ወይም +254724416340
Download Telegram
እግዚአብሔር በእኛ ይኖራል
የዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ክፍል - 1 ዮሐንስ 1-5

አስተማሪዋ በክፍል ውስጥ ለነበሩት ትንንሽ ልጆች "ለማየት በጣም የምትፈልጉት ምንድነው?" ብላ ጠየቀቻቸው። ከተማሪዎቹም አንዱ እጁን በፍጥነት እወጣና “እኔ በጣም ማየት የምፈልገው እግዚአብሔርን ነው” ብሎ መለሰላት።
ይሄ ልጅ እግዚአብሔርን ለማየት አጥብቆ በመፈለግ ብቸኛ አይደለም። ብዙዎች እግዚአብሔርን ለማየት ዕድሉን ብናገኝ በጣም ደስ እንደሚለን አስባለሁ። ታላቁ መሪ ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር አፍ ለአፍ ለማውራት ዕድል ካገኙ ጥቂት ሰብአዊ ፍጡራን መካከል አንዱ ሲሆን እርሱም እግዚአብሔርን ለማየት በመጓጓት ጠየቀ። እግዚአብሔርም ራሱን በገለጠለት ጊዜ የሆነው እንዲህ ተጽፎልናል።
“ከዚያም እግዚአብሔር በደመና ወረደ፤ በዚያም ከእርሱ ጋር ቆሞ ስሙን እግዚአብሔርን ዐወጀ። እርሱም በሙሴ ፊት እንዲህ እያለ እያወጀ አለፈ፤ “እግዚአብሔር ሩኅሩኅ ቸር አምላክ እግዚአብሔር ለቍጣ የዘገየ፣ ፍቅሩና ታማኝነቱ የበዛ፣” ዘጸ. 34:5-6.
ይህ የሚገርም መገለጥ ነው። እግዚአብሔር ራሱን ለባሪያው ለሙሴ በገለጠ ጊዜ ያወጀው የፍቅር ማንነቱን እንደሆነ ልብ ይሏል። እንደዚሁም ፊሊጶስ ጌታችን ኢየሱስ ሊለያቸው እንደሆነ በነገራቸው ጊዜ “ጌታ ሆይ፣ አብን አሳየንና ይበቃናል” አለው። “ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “አንተ ፊልጶስ! ይህን ያህል ጊዜ ከእናንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን? እኔን ያየ አብን አይቷል” ዮሐ. 14:8-9 በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የተገለጠው የመለኮት ማንነት ደግሞ ራሱን አሳልፎ የሚሰጠው ድንቅ ፍቅር ነበር።
እንግዲያውስ በሙሴም ሆነ በፊልጶስ እግዚአብሔርን ለማየት ለቀረበው ጥያቄ የተሰጠው ምላሽ የሚያሳየን ፍቅር የእግዚአብሔር ማንነት መገለጫ መሆኑን እና በፍቅርም ውስጥ እግዚአብሔር እንደሚኖር ነው። እውነተኛ ፍቅር ባለበት በዚያ እግዚአብሔር አለ። ፍቅር የመለኮት ማደሪያ መቅደስ የክብሩም አንጸባራቂ መስታወት ነው። ለዚህ ነው ቃሉ እንዲህ የሚለን፦ “እግዚአብሔርን ያየ ከቶ ማንም የለም፤ እርስ በርሳችን ብንዋደድ ግን እግዚአብሔር በእኛ ይኖራል፤ ፍቅሩም በእኛ ፍጹም ይሆናል።” (1 ዮሐ. 4:12)። ጭው ባለ በረሃ የሚገኙ “የምድረ በዳ ገነት” የሚባሉ አረንጓዴ ስፍራዎች አሉ። ታዲያ በምድረ በዳ የሚጓዝ ሰው በሩቅ ይህንን አረንጓዴ ስፍራ ሲያይ ስለ አንድ ነገር እርግጠኛ ይሆናል። ይሄውም በዚያ ስፍራ ውሃ መኖሩን ነው። በእርግጥም በዚያ በምድረ በዳ ውስጥ ከፈለቀው ምንጭ የተነሳ ነው በዙሪያው ህይወት ያላቸው እጽዋት በቅለው በምድረ በዳው መካከል የአትክልት ስፍራ ብቅ ያለው። ልክ እንደዚሁም ፍቅር ባለበት የፍቅር ምንጭ እግዚአብሔር በዚያ አለ።
ከእግዚአብሔር የተወለዱ ሁሉ በዚህ ምድር በሚኖሩበት ጊዜ የእነርሱ ህብረት በምድረ በዳ እንዳለችው ገነት ሊሆን ይገባል። በጥላቻ፣ በመገፋፋት፣ በመጠላለፍና በመገዳደል በተሞላችው እንደ ምድረ በዳ በሆነችው በዚህች ዓለም ውስጥ መኖር የሰለቻቸው፣ የፍቅርን ጥላ የፈለጉ፣ ፍቅርን የተጠሙ ከሩቅ የሚያዩት የምድረ በዳ ገነት የክርስቲያኖች የፍቅር ህብረት ሊሆን ይገባል። እነርሱም ወደዚያ መጥተው የእግዚአብሔርን ፍቅር ከዚያ ህብረት ሊያገኙ ይገባል።
“እርስ በርሳችን ብንዋደድ እግዚአብሔር በእኛ ይኖራል። ፍቅሩም በእኛ ፍጹም ይሆናል”
እግዚአብሔር የወደደን ያንን ፍቅር ለሌሎች እንድናጋራ ነው። ያን ጊዜ ነው ፍቅሩ ፍጹም የሚሆነው። የእርሱ ራስ ወዳድነት የሌለበት ፍቅር እኛን ራስ ወዳዶች ሊያደርገን ፈጽሞ አይችልም። ይልቁንም እኛም በተመሳሳዩ ፍቅር ሌሎችን ከራስ-ወዳድነት በጸዳ መንፈስ እንድንወድ አቅም ይሆነናል። ይህ ሲሆን ደግሞ ያ የእርሱ ፍቅር በእኛ ፍጹም ይሆናል። ግቡን ይመታል።
ዛሬ እግዚአብሔር ፍቅሩን በእኛ ውስጥ በመግለጥ በእኛ መኖር ይፈልጋል። ታዲያ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስጋን ለብሶ ወደ ምድር በመጣበት ጊዜ ማደሪያን አጥቶ በከብቶች በረት እንደተወለደው፣ ዛሬም በልባችን ውስጥ ጥላቻ እና ክፋት ሞልቶ ማደሪያ ያጣ ይሆን?

አባት ሆይ፣ አንተን ማየት ብንችል ምንኛ እንደምንወድ አንተ ታውቃለህ። ከእኛም ጋር እንድትሆን እንሻለን። ነገር ግን አንተን ማየት የምንችለው እና አንተም ከእኛ ጋር የምትሆነው በፍቅርህ ስንኖር እንደሆነ ስለ ተረዳን ይህንን በህይወታችን እንድንለማመድ፣ በልባችን ዙፋን ላይ እንድናነግስህ በጸጋህ እርዳን። አሜን!
🙏8👍5
በፍቅር ኑሩ
የዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ክፍል - 2 ዮሐንስ ፤ 3 ዮሐንስ

“እውነተኛ ፍቅር ማለት የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መፈጸም ነው። ይህም ትእዛዝ በመጀመሪያ እንደ ሰማችሁት “በፍቅር ኑሩ” የሚል ነው።” 2 ዮሐ. 1:6
አስቀድሞ የነገጎድጓድ ልጅ በመባል ይታወቅ የነበረው ቁጡና ግልፍተኛው ዮሐንስ በክርስቶስ ኢየሱስ ተገልጦ ባየው የእግዚአብሔር ፍቅር ህይወቱ ከተቀየረ በኋላ ስለ ፍቅር ደጋግሞ የተናገረና የፍቅር ደቀ መዝሙር በመባል ለመጠራት የበቃ ሰው ነበር። በተለይ “እግዚአብሔርን አውቀዋለሁ” “ከሞት ወደ ህይወት ተሻግሬያለሁ” “በብርሃን አለሁ” እያልን፣ ነገር ግን ፍቅር ከሌለን እና እርስ በርሳችን የማንዋደድ ከሆነ የምንለውን እንዳልሆንን ይልቁንም ራሳችንን እያታለልን እንደሆነ ቃሉ ያስተምረናል። የሚከተሉትን ጥቅሶች እግዚአብሔር ልባችንን እንዲመረምርና ዓይናችንንም እንዲከፍትልን በመጸለይ ደጋግመን እናንባቸው፦
“በብርሃን አለሁ የሚል፣ ወንድሙን ግን የሚጠላ አሁንም በጨለማ ውስጥ አለ። ወንድሙን የሚወድ በብርሃን ይኖራል፤ በእርሱም ዘንድ የመሰናከያ ምክንያት የለውም። ነገር ግን ወንድሙን የሚጠላ በጨለማ ውስጥ ነው፤ በጨለማ ይመላለሳል፤ ጨለማው ስላሳወረውም የት እንደሚሄድ አያውቅም።” 1 ዮሐ. 2:9-11
“ወንድሞቻችንን ስለምንወድ ከሞት ወደ ህይወት እንደ ተሻገርን እናውቃለን፤ ፍቅር የሌለው ሁሉ በሞት ይኖራል። ወንድሙን የሚጠላ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳይም የዘለዓለም ህይወት እንደሌለው ታውቃላችሁ።” 1 ዮሐ. 3:14-15
“ወዳጆች ሆይ፤ ፍቅር ከእግዚአብሔር ስለ ሆነ እርስ በርሳችን እንዋደድ፤ የሚወድ ሁሉ ከእግዚአብሔር የተወለደ ነው፤ እግዚአብሔርንም ያውቃል። የማይወድ ግን እግዚአብሔርን አያውቅም፤ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና።” 1 ዮሐ. 4:7
“ደግ ሥራ የሚሠራ ሁሉ የእግዚአብሔር ነው። ክፉ ሥራ የሚሠራ ግን እግዚአብሔርን አላየውም።” 3 ዮሐ. 1፡11
እነዚህ ጥቅሶች በአንድ ድምጽ የሚያስተጋቡት እውነት ቢኖር እኛ ራሳችንን መንፈሳዊ እና ሃይማኖተኛ አድርገን ብንቆጥርም እንኳን፣ ፍቅር ከሌለን እና እርስ በርሳችን የማንዋደድ ከሆነ በጨለማ የምንዳክር፣ በሞት ውስጥ የምንኖር፣ እግዚአብሔርንም ፈጽሞ የማናውቅ መሆናችንን ነው።
አስቀድሞ ወደ ወደደን እና ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከሞት ወደ ህይወት እንሻገር ዘንድ አንድ ልጁን ወደ ላከልን አምላክ በእምነት ስንቀርብ የልጅነት ማዕረግ ይሰጠናል። የፍቅር ሁሉ ምንጭ የሆነው እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ፍቅሩን በልባችን ያፈስሳል። እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈ፦ “እግዚአብሔር በሰጠን በመንፈስ ቅዱስ ፍቅሩን በልባችን አፍስሷልና።” ሮሜ 5:5
ከዚህም የተነሳ ከእርሱ የመወለዳችን እና የእርሱ ልጆች የመሆናችን ዋነኛው ማረጋገጫ የዚህ በልባችን የፈሰሰው ፍቅር በህይወታችን ተገልጦ መታየት ነው። ይህ ፍቅር ከሌለን፣ ውስጣችን በጥላቻ የተሞላ ከሆነ፣ ጥል፣ አድመኝነት፣ ቅናት፣ ምቀኝነት፣ ቂምና በቀል ውስጣችንን ከሞሉት፣ ቆም ብለን የጉዞ አቅጣጫችንን በመቀየር፣ የፍቅር ምንጭ ወደ ሆነው የፍቅር አምላክ በንስሃ ልንቀርብ እና ፍቅሩን በልባችን እንዲያፈስልን ልንጠይቀው ይገባል።

አባት ሆይ፣ ቃልህ “በፍቅር ኑሩ” እንደሚል ፍቅርህን በመንፈስ ቅዱስህ በልባችን እንድታፈስሰውና እኛም እርስ በርሳችን በመዋደድ በፍቅርህ እንድንኖር እርዳን። አሜን!
10🙏4
አትፍራ
የዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ክፍል - ራዕይ 1-5
“አትፍራ፤ የመጀመሪያውም የመጨረሻውም እኔ ነኝ፤ እኔ ሕያው ነኝ፤ ሞቼ ነበር፤ እነሆ አሁን ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ድረስ ሕያው ነኝ፤ የሞትና የሲኦል መክፈቻም በእጄ ነው።” ራዕይ 1:17-18
ፍርሃት በመጀመሪያ ከታዩት የኃጢአት በሽታ ምልክቶች መካከል አንዱ ሲሆን፣ እግዚአብሔር አዳምና ሔዋንን ለማናገር ወደ ኤደን ገነት በመጣ ጊዜ ከመተላለፋቸው የተነሳ ፈርተው ተደበቁ (ዘፍ. 3)። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሰው ልጅ ከተለያዩ ነገሮች የተነሳ ፍርሃትን ሲያስተናግድ ኖሯል። ነገር ግን ከፍርሃት መንስኤዎች መካከል እጅግ ጠንካራው “የሞት ፍርሃት” ሲሆን ብዙዎችን ዘመናቸውን ሁሉ ባርያ አድርጎ የሚያሰቃይ ፍርሃት ነው። ሞትን አሸንፎ ከሞት ፍርሃት ባርነት ነጻ ለመውጣት እጅግ ብዙ የተጣረ ቢሆንም ነገር ግን ከሰው ዘንድ የሆነ ነጻ አውጪ ሊገኝ አልተቻለም። አይቻልምም። ለዚህ ችግራችን መፍትሔ የተበረከተልን በአፍቃሪው ጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። በዕብራዊያን 2:14-15 ይህ መፍትሔ እንዲህ ተጽፎልናል።
"ልጆቹ በሥጋና በደም እንደሚካፈሉ እርሱ ራሱ (ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ) ደግሞ ያንኑ ተካፈለ፤ ይኸውም በሞት ላይ ኀይል ያለውን ዲያቢሎስን በሞቱ ኀይል እንዲደመስስ ነው፤ እንዲሁም በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ በሞት ፍርሀት ባርነት የታሰሩትን ነጻ እንዲያወጣ ነው።"
ጌታችን ኢየሱስ የእኛን ሥጋ ለብሶ በመስቀል ላይ በመሞት “በሞት ላይ ኀይል ያለውን ዲያቢሎስን በሞቱ ኀይል” ደመሰሰው። በሞቱ ሞትን አሸነፈ። የመቃብሩን ድንጋይ ፈንቅሎ በተነሳ ጊዜ የሞት እና የሲኦል መክፈቻ ቁልፍን በእጁ ይዞ ወጣ። በሞት ፍርሃት ባርነት የታሰሩትን ሁሉ ነጻ ሊወጡ የሚችሉበት ድል ተመዘገበ። ይህ ነው ታላቁ የምስራች!
ጌታችን ኢየሱስም በፍጥሞ ደሴት በስደት ተወርውሮ ለነበረው ለአዛውንቱ ደቀ መዝሙር ለዮሐንስ በተገለጠለት ጊዜም ይህንን ድንቅ የምስራች ነበር ያወጀው! አትፍራ፤ የመጀመሪያውም የመጨረሻውም እኔ ነኝ፤ እኔ ሕያው ነኝ፤ ሞቼ ነበር፤ እነሆ አሁን ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ድረስ ሕያው ነኝ፤ የሞትና የሲኦል መክፈቻም በእጄ ነው። ራእይ 1: 17-18
ዛሬም ከዚህ የሞት ፍርሃት ባርነት ነጻ የሚያወጣን ሞቶ የነበረው፣ ነገር ግን ሞትን በሞቱ ድል ነስቶ የተነሳው የሞትና የሲኦል መክፈቻ ቁልፍ በእጁ ያለው፣ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ሕያው የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። ህይወታችን በእርሱ ከተሰወረ ከሞት ወደ ህይወት ተሻግረናል። ሞት በእኛ ላይ ኃይል የለውምና በሞት ጥላ ሸለቆ መካከል እንኳን ብንሄድ ክፉውን አንፈራም።
የሞትና የሲኦልን ቁልፍ በእጅህ የያዘከው ውዱ ጌታዬ ሆይ፣ እኔንም በዚያው እጅህ መዳፍ ላይ እንደቀረጽከኝ በማመን ከሞት ፍርሃት ባርነት ነጻ የወጣ ህይወት እንድኖር እርዳኝ። አሜን!
15🙏5👍1
በበጉ ደም
የዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ክፍል - ራዕይ 6-11
“እነዚህ ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው፤ ልብሳቸውንም በበጉ ደም አጥበው አንጽተዋል።” ራእይ 7:14
ስኮት ማክናይት እ.ኤ.አ በ1997 በደም ካንሰር መያዙ ተነገረው። ወዲያም የካንሰር ሴሎቹን ለመግደል የጨረር እና የመድሃኒት ህክምናን ጀመረ። ምንም እንኳን ህክምናው ከባድ የነበረም ቢሆን በጤናው ላይ ለውጥ መታየቱ አስደሳች ሆነ። ሆኖም ግን በዓመቱ ተመሳሳይ የካንሰር ሴሎች ቁጥራቸው በዝቶ በሰውነቱ ውስጥ ተከሰቱ። በመቀጠል የተደረገለት የህክምና እርዳታ ከመቅኔው ውስጥ የደም ሴል ተወስዶ፣ ሴሉን ከካንሰር ነጻ በማድረግ ሌሎች የደም ሴሎችን ሁሉ በጨረር ከገደሉ በኋላ ያንን ያጸዱትን ሴል እንደገና ወደ አካሉ ማስገባት ነበር። ይህንንም በማድረግ ከካንሰር የጸዳው ሴል እየተራባ በንጹህ የደም ሴል ሰውነቱ እንዲሞላ ተስፋ ተደረገ ። ይሁን እንጂ፣ ይህም ቢሆን አልተሳካም፣ ምክንያቱም መቅኔው አሁንም የካንሰር ሴሎችን ማምረት ስላላቆመ። በመጨረሻ የግድ አዲስ የደም ሴል ከሌላ ሰው መቀበል ብቸኛው አማራጭ ሆነ ።
እህቱ ኮኒ ይህንን ለማድረግ የምትችል መሆኗ ተረጋገጠ። ንቅለ ተከላው በመጀመሪያ የእርሱን በካንሰር የተበከሉ የደም ሴሎች የተቻለውን ሁሉ በመግደል ከዚያም የእህቱን ንጹህ የደም ሴል በመትከል ተጠናቀቀ። በእርግጥም አዲሱ እና ንጹሁ ሴል እያደገ፣ የካንሰር ሴሎቹን እያጸዳ ሄደ። በመጨረሻም ከካንሰር ነጻ ሆነ። ስኮት ማክናይት ከዚህ ታሪኩ ጋር የክርስቶስ ደም የሰራውን በማመሳሰል፣ የጌታችን የኢየሱስ ደም በኃጢአት ካንሰር የተበከልነውን የሰው ልጆችን ሁሉ ለማንጻት የተሰጠን ብቸኛው መፍትሔ እንደሆነ ይገልጻል። በእርግጥም ከኃጢአት ሁሉ የሚያነጻን የልጁ የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ብቻ ነው። (1 ዮሐ. 1:7)።
አፍቃሪ አባታችንም እንዲህ በማለት ግብዣውን ያቀርብልናል፦ “‘ኑና እንዋቀስ’ ይላል እግዚአብሔር፤ ‘ኃጢአታችሁ እንደ ዐለላ ቢቀላ እንደ በረዶ ይነጣል፤ እንደ ደም ቢቀላም እንደ ባዘቶ ነጭ ይሆናል።’” ኢሳ. 1:18
ይህንን ጥሪ ተቀብለን በእምነት ወደ ክርስቶስ መስቀል ብንቀርብ፣ በደሙ ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል። በመጨረሻም የዘለዓለማዊ መንግስቱ ወራሾች እንሆናለን። እንዲህም ይባልልናል “እነዚህ ነጭ ልብስ የለበሱት እነማን ናቸው? ከወዴትስ መጡ?” … እነዚህ ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው፤ ልብሳቸውንም በበጉ ደም አጥበው አንጽተዋል። (ራእይ 7:13፣ 14) ክብር በደሙ ላነጻን ለታረደው በግ ይሁን! አሜን።
በደሙ ከመንጻታችን የተነሳ ደግሞ በመጨረሻ የምናገኘውን ታላቅ በረከት ቅዱስ ቃሉ እንዲህ በማለት ያበስረናል፦
“ስለዚህ በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት ሆነው ሌሊትና ቀን በመቅደሱ ያገለግሉታል፤ በዙፋኑ ላይ የተቀመጠውም መጠለያቸው ይሆናል። ከእንግዲህ ወዲህ አይርባቸውም፤ አይጠማቸውም፤ ፀሐይ አይመታቸውም፤ ሙቀት አያገኛቸውም፤ በዙፋኑ መካከል ያለው በግ እረኛቸው ይሆናል፤ ወደ ህይወት ውሃ ምንጭም ይመራቸዋል፤ እግዚአብሔር እንባን ሁሉ ከዓይናቸው ይጠርግላቸዋል።” ራእይ 7:15-17

አባት ሆይ፣ በልጅህ በክርስቶስ ኢየሱስ ስላበረከትክልን ከኃጢአት የመንጻት ዕድል እያመሰገንንህ፣ በዚህ ዕድል በእምነት ተጠቃሚዎች መሆን እንድንችል በጸጋህ እርዳን። አሜን!
13🙏5👍4
በግንባሩ ወይም በእጁ
የዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ክፍል - ራዕይ 12-15
ከዘለዓለማዊ ፍቅሩ የተነሳ “ ከመንገዳቸው ተመልሰው በሕይወት እንዲኖሩ እንጂ በክፉዎች ሞት ደስ አልሰኝም።” (ህዝ. 33:11) በማለት የሚናገረው እግዚአብሔር በኃጢአት ላይ የመጨረሻውን እርምጃ ከመውሰዱ በፊት የፍቅር ማስጠንቀቂያውን ለዓለም እያስደመጠ ይገኛል። በራእይ 14:6-12 የምናገኘው የሦስቱ መላእክት መእክትም ይህንን አምላካዊ የፍቅር ማስጠንቀቂያ ያስተጋባል። የመጀመሪያው መልአክ ሰማይንና ምድርን፣ ባህርንና በውስጣቸው ያለውን ሁሉ ለፈጠረው ብቻ እንድንሰግድ ያስጠነቀቀን ሲሆን፣ ሁለተኛው መልአክ ደግሞ አምልኳችንን ለሌሎች የምንሰጥ ከሆነ ይህ መንፈሳዊ አመንዝራነት እንደሆነ በመግለጽ ያስጠነቅቀናል። በመጨረሻ ወደዚህ ትእይንት የሚቀላቀለው ሦስተኛው መልአክ ደግሞ ለአውሬው ምስል እንዳንሰግድ ምልክቱንም በግንባራችንና በእጃችን እንዳንቀበል ያስጠነቅቀናል።
ራእይ ምዕራፍ 12 እና 13ን ስናነብ ሦስት አውሬዎችን እናገኛለን። የመጀመሪያው በራእይ 12 ላይ የምናገኘው ከሰማይ የተጣለው የቀደመው እባብ የተባለው ዘንዶው ሲሆን፣ በራእይ 13 ላይ ደግሞ የእርሱ ተባባሪ የሆኑትን፣ አንደኛው ከባህር ሌላኛው ደግሞ ከምድር የወጡ ሁለት አውሬዎችን እናገኛለን። የእነዚህን ሦስት አውሬዎች መግለጫ ጠጋ ብለን ስናጠና ማንነታቸውን ከአብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ ጋር በማመሳሰል ያቀረቡና ለእርሱ ብቻ የሚገባውን አምልኮ ለራሳቸው የፈለጉ እንደሆኑ እንመለከታለን። በመጨረሻም ሦስቱ በመተባበር በምድር የሚኖሩ ሰዎችን በማስገደድ ይህንን የተሳሳተ አምልኮ እንዲለማመዱ እንደሚያደርጓቸው ትንቢቱ ይናገራል።
ይሁን እንጂ፣ በማታለልም ይሁን በማስገደድ ወደ እኛ በሚመጣ በማኛውንም አይነት የተሳሳተ አምልኮ ልምምድ ውስጥ እንዳንገባ ማስጠንቀቂያው ተሰጥቶናል። እንደዚሁም፣ ከአምልኮ ጋር ተያይዞ የቀረበውን በግንባር እና በእጅ ምልክትን ስለ መቀበል የተነገረውን በደንብ ልናስተውለው ይገባል። በዘዳግም 6 ላይ ሙሴ ለእስራኤል ህዝብ ተስፋ ወደ ተገባላቸው ምድር ከመግባታቸው በፊት በከፍተኛ አጽንኦት ያሳሰባቸው ነገር ቢኖር፣ እግዚአብሔርን ብቻ እንዲያመልኩ፣ ይኸውም እርሱን በፍጹም ልባቸው እንዲወዱት ሲሆን፣ የአምላካቸውንም ትእዛዝ “በእጅህ ላይ ምልክት አድርገህ እሰራቸው፤ በግንባርህም ላይ ይሁኑ። ” (ቁ. 8)። በማለት አዟቸው ነበር። ይህ የሚያሳየው እግዚአብሔርን ስናመልክ እርሱ አስተሳሰባችንን እና ድርጊታችንን ሊቆጣጠረው እንደሚገባ ነው። ታዲያ በተመሳሳዩ፣ ሰይጣንም እርሱን እንድናመልክና ምልክቱንም በግባራችን እና በእጃችን እንድንይዝ ሲፈልግ በአስተሳሰባችንና በድርጊታችን የእርሱን ፈቃድ እንድንፈጽም መፈለጉን ነው። እንግዲያውስ ምርጫው የእኛ ነው። ለእስራኤላውያን፣ የምታመልኩትን ዛሬ ምረጡ እንደተባሉ፣ እኛም በየዕለቱ በአስተሳሰባችንና በድርጊታችን የምንገዛለትን ለመምረጥ ዕድሉ ተሰጥቶናል። እግዚአብሐርን በፍጹም ልባችን በመውደድ የእርሱን ትእዛዝ በግንባራችን እና በእጃችን በመያዝ ለአውሬው ከመስገድ ምልክቱንም በግንባራችን እና በእጃችን ከመቀበል እንድናመልጥ ጌታ ዛሬ ይጠራናል።
አባት ሆይ፣ በየዕለቱ አንተን ማምለክን ምርጫችን እንድናደርግ በአስተሳሰባችን እና በድርጊታችን ለአንተ ፈቃድ የተገዛ ህይወት እንድንኖር፣ በማታለልም ሆነ በማስገደድ አንተን ከማምለክ ዘወር እንድንል የሚያደርገንንም ፈተና እንድናሸንፍ በጸጋህ እርዳን። አሜን!
11🙏5👍1
ከእርስዋ ውጡ!
የዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ክፍል - ራዕይ 16-18
ራእይ ዮሐንስን ስናነብ በምዕራፍ 12 ላይ በምናገኛት ብርሃንን የተላበሰች ንጹህ ሴት እና በምዕራፍ 17 እና 18 ላይ በቀረበችው አመንዝራ ሴት መካከል ያለውን ተቃርኖ ልብ ልንለው ይገባል። የመጀመሪያዋ ሴት የምትወክለው የክርስቶስ ሙሽራ የሆነችውን ቤተ ክርስቲያንን ሲሆን ከክርስቶስ ጋር በእውነተኛ እምነት የተቆራኙ ሁሉ የእርሷ ዘሮች ናቸው። በተቃራኒው አንመዝራይቱ ሴት የምትወክለው ለእግዚአብሔር ብቻ የሚገባውን ስግደት በአንድም ሆነ ሌላ መንገድ ለሌሎች በመስጠት በጣኦት አምልኮ ውስጥ የተዘፈቀን ኃይማኖታዊ ስርዓት ነው። ብቻውን አምልኮ ከሚገባው ሰማይን እና ምድርን፣ ባሕርን እና የውሃ ምንጮችን ከፈጠረው ከእግዚአብሔር ሌላን ማምለክ አመንዝራነት ወይም ዝሙት ነው። ለዚህ ነው እግዚአብሔር እንዲህ ባለው አምልኮ ውስጥ ገብተው ስለ ነበሩት ህዝቡ “ከእኔ ዘወር ባለ አመንዝራ ልባቸውና ጣዖትን በተከተለ አመንዝራ ዓይናቸው የቱን ያህል እንዳሳዘኑኝ...” (ህዝ. 6:9) በማለት የተናገረው።
እንግዲያውስ እግዚአብሔርን የሚያስቆጣው የባቢሎን የዝሙቷ ወይን ጠጅ አምልኳችንን ከእግዚአብሔር ዘወር አድርገን ወደ ሌላ የምናደርግበት አካሄድ ነው። ይህን የባቢሎን የዝሙት የወይን ጠጅ ዛሬም ህዝቦች ሁሉ እየጠጡት እንደሆነ በራእይ 14 ላይ የምናገኘው የሁለተኛው መልአክ መልእክት ያስረዳናል። በእርግጥም ከእግዚአብሐር ይልቅ ገንዘብ፣ ዝና፣ ስልጣን፣ መዝናኛና የመሳሰሉት ነገሮች ሲመለኩ በዚያ የባቢሎን የዝሙት የወይን ጠጅ እየተጠጣ ነው። የባቢሎን የዝሙት የወይን ጠጅ በሃይማኖተኞችም ዘንድ እየተጠጣ የሚገኝበት ሁኔታ አለ። ይህም የሚሆነው እውነትን ከሃሰት በመቀየጥ፣ አምልኮን ለእግዚአብሔርና ለእግዚአብሔር ብቻ ከመስጠት ይልቅ ከእርሱ ጋር ተደብለው አምልኳችንን የሚቀራመቱ ሌሎች ነገሮችን በልባችን ስናስቀምጥ ነው። አምልኮን ሰማይንና ምድርን፣ ባሕርንና የውሃ ምንጮችን ከፈጠረው ከእግዚአብሔር ውጪ ለሆነ ለማንኛውም አካል እንዲሰጥ የሚያስተምር የሃይማኖት ስርአት የባቢሎንን የዝሙት የወይን ጠጅ የሚያከፋፍል ይሆናል።
ይህ ሁለተኛው መልእክ እንዳወጀው እንዲህ ያለውን የሃሰተኛ አምልኮ ወይን ጠጅ የምታመርተው ባቢሎን በእግዚአብሔር ፍርድ ተጎብኝታ መውደቋ አይቀሬ ነው። በራዕይ 18 ላይ የምናገኘው ከሰማይ የወረደው ሌላ መልዓክም ተመሳሳዩን የባቢሎን መውደቅ ዐዋጅ ከፍ ባለ ድምጽ ያስተጋባል። በመሆኑም፣ ዛሬ የልባችንን ዙፋን ሊቆጣጠሩ የሚፈልጉ፣ አምልኳችንን ሊቀራመቱ በዙሪያችን ብዙ ተፅእኖ የሚያሳድሩብን ነገሮች ሁሉ መጨረሻቸው ጥፋት ነው። አምልኮ ለሚገባው ለእግዚአብሔር ብቻ አምልኳችንን መስጠት ግን ዘለዓለማዊ ትርፍ እና በረከት አለው። ሲድራቅ ሚሳቅ እና አብድናጎ በባቢሎን ይህንን የባቢሎንን የዝሙት የወይን ጠጅ እንዲጠጡ አስገዳጅ ሁኔታ ገጥሟቸው ነበር። እነርሱ ግን ንጉሱ ላቆመው ምስል በመስገድ በእውነተኛው አምላካቸው ላይ ዝሙት መፈጸምን ፈጽሞ አልፈቀዱም። የመጨረሻ ዕድል በተሰጣቸው ጊዜ እንኳን እንዲህ በማለት ነበር የመለሱት፦ “ናቡከደነፆር ሆይ፤ በዚህ ጒዳይ ላይ ስለ ራሳችን መልስ መስጠት አያስፈልገንም። ንጉሥ ሆይ፤ በሚንበለበለው የእቶን እሳት ውስጥ ብንጣል፣ የምናመልከው አምላክ ሊያድነን ይችላል፤ ከእጅህም ያድነናል። ነገር ግን ንጉሥ ሆይ፤ ባያድነንም እንኳ፤ አማልክትህን እንደማናገለግል፣ ላቆምኸውም የወርቅ ምስል እንደማንሰግድ ዕወቅ።” ዳን. 3:16-18
እኛም እንዲህ በጽናት በመቆም ሰማይንና ምድርን፣ ባሕርንና የውሃ ምንጮችን ለፈጠረው ለእግዚአብሔር ብቻ እንድንሰግድ እና ክብርን እንድንሰጥ ይገባል። በዚህ በመጨረሻ ዘመን ለምንኖር እግዚአብሔር በቃሉ በኩል እንዲህ በማለት ለሚያቀርብልን ወሳኝ ጥሪ ተገቢውን አፋጣኝ ምላሽ እንስጥ፦
“ሕዝቤ ሆይ! በኃጢአትዋ እንዳትተባበሩ፤ የመቅሠፍትዋም ተካፋዮች እንዳትሆኑ፤ከእርስዋ ውጡ! … በእሳትም ትቃጠላለች፤ በእርስዋ ላይ የሚፈርድባት ጌታ አምላክ ብርቱ ነው።” ራእይ 18፡4፣ 8

አባት ሆይ፣ አንተን ብቻ በልባችን ዙፋን ላይ እንድናነግስ፣ በማኛውም አይነት መልክና ቅርጽ ከሚመጣ የጣኦት አምልኮ እንድንሸሽ፣ ለአንተና ለአንተ ብቻ የተገዛን ህይወት ዕለት ዕለት እንድንኖር እርዳን። አሜን!
11🙏5👍1
ለብዙዎቻችን መጀመር የሚቀለንን ያህል መጨረስ የዚያን ያህል ቀላል ሆኖ አናገኘውም። ከዚህም የተነሳ በጅምር የተውናቸው ብዙ ነገሮች በህይወታችን አሉ። በአንጻሩ፣ የጀመርነውን ነገር ጨርሰን “ተፈፀመ” ማለት ስንችል ክንዋኔያችን የሚፈጥርልን የድል አድራጊነት ስሜት ላቅ ያለ ነው። የምናመልከው ኃያሉ አምላካችን ጀምሮ የማይጨርስ ሳይሆን፣ ዓላማውን ከግብ የሚያደርስ ግሩም አምላክ ነው። በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ ሦስት ታላላቅ ስራዎችን ጌታችን በድል አድራጊነት እንደፈጸመ እናነባለን።
1. የፍጥረት ስራ ፍጻሜ
“እግዚአብሔር ይሠራ የነበረውን ሥራ በሰባተኛው ቀን ላይ ፈጽሞ ነበር” (ዘፍ. 2:2) እግዚአብሔር ያረፈው፣ የሰራው ስራ አድክሞት ሳይሆን ፍጹም የሆነን ስራ በመስራት፣ በሰራው ላይ ምንም የሚጨመርበት ነገር ባለመኖሩ ነበር። ይሁንና በመልኩና በአምሳሉ የፈጠረው ሰው በአመጽ ጎዳና በመሄድ ኃጢአት ወደ ዓለም በገባ ጊዜ ፍጹም የሆነው ፍጥረተ-ዓለም ተበላሸ። ለዚህም ችግር ቢሆን መፍትሔ ያለው አምላክ፣ የሰውን ልጅ ከኃጢአት የሚታደግበትን ዕቅድ አዘጋጀ።
2. የማዳን ስራ ፍጻሜ
በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስጋ መልበስ እና የሁላችንንም ኃጢአት ተሸክሞ በመስቀል ላይ ነፍሱን መስጠት የተከናወነው ይህ የእግዚአብሔር የማዳን ዕቅድ ሲጠናቀቅ፣ ጌታችን በቀራኒዮ “ተፈጸመ” በማለት የድልን አዋጅ አወጀ። በዚያ መስቀል ላይ ለዓለም ሁሉ ኃጢአት ስርየት የሚሆን ብርቱ ኃይል ያለው ደም ፈሰሰ። የተሸነፈ መስሎ ጌታችን አሸነፈ።
3. በፍርድ ስራ ፍጻሜ
ይህ በመስቀል ላይ ሆኖ በጭንቅ እና በጣእር የሁላችንን ኃጢአት ተሸክሞ “ተፈጸመ” ያለው ጌታ፣ በመጨረሻ ደግሞ ኃጢአትን ከዩንቨርስ ሁሉ ጠራርጎ በማስወገድ፣ አዲስ ሰማይ እና አዲስ ምድርን በመፍጠር እንዲህ ብሎ ያውጃል፦
“ተፈፀመ፤ አልፋና ዖሜጋ፣ የመጀመሪያው እና የመጨረሻው እኔ ነኝ፤” ራዕይ 21:6
ምንም እንኳን ይህ ሦስተኛው አዋጅ ገና ያልታወጀ ቢሆንም፣ የፍጥረትን እና የማዳንን ስራ በተሳካ ሁኔታ የፈጸመው እርሱ የቀረውን የመጨረሻውን አዋጅ “ተፈጸመ” በማለት እንደሚያውጅ ፈጽሞ ጥርጣሬ ሊገባን አይገባም። ይልቁንም፣ ለኃጢአታችን ስርየት በፈሰሰው ደሙ ዕለት ዕለት እየታጠብን በቅርብ ደግሞ ኃጢአትን ከዩንቨርስ ሊያጠፋ የሚመጣውን ጌታ ለመገናኘት እንዘጋጅ።
አባት ሆይ፣ የመጨረሻውን “ተፈፀመ” ከማወጅህ እና ኃጢአትን በጽድቅ ፈርደህ ከማስወገድህ በፊት፣ ከኃጢአታችን እንድንበት ዘንድ በቀራኒዮ “ተፈፀመ” ብለህ በመረቅህልን አዲስና ህያው መንገድ ወደ አንተ ዕለት ዕለት እንድንቀርብ እርዳን። አሜን!
👍9🙏54
ከዓመቱ መጀመሪያ እስከ ዓመቱ መጨረሻ

በቀን መቁጠሪያችን ዓመቱን አንድ ብለን ጀምረን እስከ ዓመቱ መጨረሻ መድረስ ቆም ብለን “እስትንፋሳችንና መንገዳችንን በእጁ የያዘውን” ፈጣሪና አዳኝ አምላካችንን እንድናመሰግን ግድ ይለናል።

ሙሴ እስራኤላውያን ተስፋ ወደ ተሰጣቸው ምድር ከመግባታቸው ጥቂት ቀደም ብሎ፣ ከፊት ለፊታቸው ስለሚገጥማቸው ነገር በማሳሰብ እንዴት አካሄዳቸውን ከእግዚአብሔር ጋር ሊያደርጉ እንደሚገባ ነግሮአቸው ነበር።
እንዲህም አላቸው:-
“ የምትገባባት ምድር እንደ ወጣህባትና ዘርህን ዘርተህባት በእግርህ ውሃ እንዳጠጣሃት የአትክልት ቦታ እንደ ግብፅ ምድር አይደለችም። ዮርዳኖስን ተሻግረህ ልትወርሳት ያለችው ምድር ግን፣ ከሰማይ ዝናብ የምትጠጣ፣ ተራሮችና ሸለቆች ያሉባት ምድር ናት። ይህች ምድር አምላክህ እግዚአብሔር የሚንከባከባት፣ ከዓመቱ መጀመሪያ እስከ ዓመቱ መጨረሻ የአምላክህ የእግዚአብሔር ዐይን ምንጊዜም የማይለያት ናት።” ዘዳ 11: 11፣12

ምንም እንኳን እስራኤላውያን ዮርዳኖስን ተሻግረው የሚወርሱት መሬት እንደ ግብጽ ሜዳማና በመስኖ ውሃ የለመለመ የአትክልት ቦታ ባይኖረውም፣ ተራሮችና ሸለቆዎች ያሉበት ፈታኝ መልክዐ ምድራዊ አቀማመጥ ቢኖረውም፣ ከየትኛውም ሥፍራ የተሻለ የሚያደርገው ግን አንድ ትልቅ ልዩነት ነበረው። ይሄውም፣ በዚያ በተራራማና ሸለቋማ ስፍራ ከሚገኘው የእግዚአብሔር ሕዝብ የተነሳ “ ከዓመቱ መጀመሪያ እስከ ዓመቱ መጨረሻ የእግዚአብሔር ዐይን ምንጊዜም የማይለው” ቦታ መሆኑ ነበር።

ይህ ስለ ጥንት እስራኤላውያን የተነገረው ቃል በዚህ ዘመን በክርስቶስ ደም ተዋጅተን የእርሱን በጎነት እንድናውጅ ለተጠራን የእግዚአብሔር ሕዝቦች ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው። እኛም ብንሆን ጌታችን ኢየሱስ "ወደ አለም ሁሉ ሂዱ" ብሎ የእርሱ መንግስት አምባሳደሮች አድርጎ ሲልከን ብዙ ተራሮችና ሸለቆዎች እንደነበሩባት ከንዓን፣ እኛም ብዙ ተግዳሮት እንደሚገጥመን አስቀድሞ ነግሮናል። ነገር ግን በሚገጥመን በማንኛውም ሸለቆም ሆነ ተራራ ተስፋ እንዳንቆርጥ “እኔ እስከ አለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋራ ነኝ” በማለት ቃል ገብቶልናል። (ማቴ 28:20) ከዚህም የተነሳ፣ በየትኛውም ስፍራ ብንሆን፣ በተራራም ሆነ በሸለቆ፣ “ ከዓመቱ መጀመሪያ እስከ ዓመቱ መጨረሻ የእግዚአብሔር ዐይን ምንጊዜም” በእኛ ላይ መሆናቸውን እናስታውስ።

1, የእግዚአብሔር ዐይኖች ደግሞ የሚምሩን ዐይኖች ናቸው

“ ያልጠፋነው ከእግዚአብሔር ታላቅ ፍቅር የተነሣ ነው፤
ርኅራኄው አያልቅምና።
ማለዳ ማለዳ አዲስ ነው፤
ታማኝነትህም ብዙ ነው።
ራሴን እንዲህ አልሁት፤ “እግዚአብሔር ዕድል ፈንታዬ ነው፤
ስለዚህ ተስፋ አደርገዋለሁ።
እርሱን ተስፋ ለሚያደርጉት፣
ለሚፈልገውም ሰው እግዚአብሔር መልካም ነው።” ሰቆ ኤር 3: 22-25

2, የእግዚአብሔር ዐይኖች የሚመሩን ዐይኖች ናቸው።

“ አስተምርሃለሁ፤ በምትሄድበትም መንገድ እመራሃለሁ፤
እመክርሃለሁ፤ በዐይኔም እከታተልሃለሁ።” መዝ 32:8

3, የእግዚአብሔር ዐይኖች የሚያበረቱን ዐይኖች ናቸው።

“ በፍጹም ልባቸው የሚታመኑበትን ለማበርታት የእግዚአብሔር ዐይኖች በምድር ሁሉ ላይ ይመለከታሉና። ” 2 ዜና 16:9


ተራራና ሸለቆ በበዛበት በዚህ ዓለም ጉዞአችን፣ የሚምሩን፣ የሚመሩን እና የሚረዱን የእግዚአብሔር ዐይኖች ከዓመቱ መጀመሪያ እስከ ዓመቱ መጨረሻ ምንግዜም ከእኛ ጋር ሆነው እዚህ ስለደረሰን ክብር ሁሉ ለእግዚብሔር ይሁን!


አባት ሆይ፣ በእርግጥም ከዓመቱ መጀመሪያ እስከ ዓመቱ መጨረሻ የሚምሩ፣ የሚመሩና የሚረዱ ዐይኖችህ በእኛ ላይ ሆነው እዚህ ስለደረስን እያመሰገንህ፣ ሁልጊዜ አካሄዳችንን ከአንተ ጋር በማድረግ ሕይወታችንን ሙሉ በሙሉ ላንተ በማስረከብ ዕለት ዕለት ለክብርህ እንድንኖር በጸጋህ እርዳን። አሜን።
17🙏11👍6
የእውነተኛ ደስታ ምንጭ
የዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ክፍል መዝ 1:1-3


አሮጌውን አመት ሸኝተን አዲስ አመት ስንቀበል አየሩ በመልካም ምኞት መግለጫዎች ይሞላል። “አዲሱ አመት የሰላም፣ የጤና፣ የደስታ ይሁንልን” እንባባላለን። ይህ ምኞታችን ግን በምኞት ብቻ የምናገኘው እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ታዲያ እነዚህን የተመኘናቸውን ነገሮች ልናገኝ የምንችለው ከየትና እንዴት ይሆን? ለዚህ ጥያቄ ከመጽሐፍ ቅዱሳችን መዝሙር አንድን ስናነብ መልስ እናገኛለን።
ይህ መዝሙር በመጀመሪያ በተጻፈበት በዕብራይስጥ ቋንቋ የሚጀምረው “ ብፁዕ ነው ያ ሰው” በማለት ሲሆን “ብፁዕ” የሚለው ቃል ደግሞ ትርጉሙ በእውተኛ እርካታ፣ ደስታና ሰማያዊ በረከት የተትረፈረፈ ሕይወት የሚኖር ማለት ነው። ይህ መዝሙር እንዲህ ያለው ሰው ሕይወቱ ምን እንደሚመስል ሲገልጽ ሦስት ዋና ነገሮችን አጉልቶ ያሳየናል።

1 የማይሄድ፣ የማይቆምና የማይቀመጥ
ይህ ብፁዕ ሰው “በክፉዎች ምክር የማይሄድ፣ በኀጢአተኞች መንገድ የማይቆም፣ በፌዘኞችም ወንበር የማይቀመጥ፣” ሲሆን በአጭሩ ከእግዚአብሔር ከሚያርቀው ከማንኛውም ነገር የራቀ ሰው ነው። መሄድ፣ መቆምና መቀመጥ አንዱ ወደ ሌላው የሚመራ የፈተናን ቁልቁለት ያሳያል። እግዚአብሔር ብቻ የሚሰጠውን እውነተኛ ደስታና እርካታ ማግኘት ከፈለግን ከንቱ የሆነውን የክፋትና የኀጢአት መንገድ ምርጫችን ልናደርግ አይገባም። ምንም እንኳን በኀጢአት የሚገኝ ደስታ ቢያጓጓንም ያ ደስታ ጊዜያዊና ለከፋ ሰቆቃም የሚዳርግ እንደሆነ እናስታውስ።

2 ደስ የሚሰኘውና የሚያሰላስለው
በእውነተኛ ደስታና እርካታ የተሞላ ሰው ከክፋት የራቀ ብቻ ሳይሆን ወደ እግዚአብሔር ምሪት የቀረበ ሕይወትን የሚመራም ነው። “የእግዚአብሔር ሕግ” ተብሎ የተተረጎመው “አድርግ አታድርግ” የሚለውን ብቻ የሚያመለክት ሳይሆን ይልቁንም በጠቅላላው የእግዚአብሔርን ቃል የሚያካትት ነው። በደስታና በእርካታ የተሞላ ሕይወት መኖር ከፈለግን በእግዚአብሔር ቃል ደስ ሊለን ቃሉንም በቀንና በሌሊት ልናሰላስለው ይገባል። ማሰላሰል በቅድሚያ የእግዚአብሔርን ቃል በልባችን በመሰወር የሚጀምር ሲሆን ከዚያም ያንን በቃላችን የያዝነውን የእርሱን ቃል በሃሳባችን ማውጣትና ማውረድን አፋችንም ደጋግመን መናገርን ይጠይቃል። ለመሆኑ እምሮአችንን እየተቆጣጠረን ያለ ነገር፣ በቀንና በሌሊት የምናስበው ምን ይሆን?

3 የሚሰራው ሁሉ የሚከናወንለት
“ እርሱ በወራጅ ውሃ ዳር እንደ ተተከለች፣ ፍሬዋን በየወቅቱ እንደምትሰጥ፣ ቅጠሏም እንደማይጠወልግ ዛፍ ነው፤” ቁ. 3 ይህ ምሳሌያዊ መግለጫ ከክፋት በመራቅና በእግዚአብሔር ቃል ምሪት የሚኖርን ሰው ሕይወት በውሃ ዳር በተተከለች ዛፍ የመሰለው ሲሆን ውሃው ደግሞ የእግዚአብሔርን ቃል ያሳያል። ልክ ዛፉዋ ሁልጊዜው ውሃ ከማግኘቷ የተነሳ ቅጠሏ እንደማይጠወልግና ፍሬም እንምደትሰጥ እኛም ከእግዚአብሔር ቃል ጋር በቀንና በሌሊት የተቆራኘን ስንሆን በምንሰራው ሁሉ የተከናውነልን እንሆናለን። ስኬታችን የሚለካው ደግሞ በምድራዊ ዋንጫና ሜዳልያ ሳይሆን በዘላለማዊ አክሊል ይሆናል።

አባት ሆይ፣ በእውነተኛ ደስታና እርካታ የተሞላ ሕይወት መኖር እንድንችል ከክፋት መንገድ በመራቅ በቀንና በሌሊት ያንተን ቃል በደስታ በማሰላሰልና ለፈቃድህ የተገዛን ሕይወት መኖር እንድንችል በጸጋህ እርዳን።
20🙏15👍3
ገለባ ወይስ ፍሬያማ
የዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ክፍል መዝ 1:4-6

ምንም እንኳን በሕይወት ጎዳና ላይ ስንጓዝ ብዙ አይነት አማራጭ ያለን ቢመስለንም፣ እውነታው ግን እንዲህ አይደለም። ብዙ የሚመስሉት መንገዶች በሁለት ጎራ የሚከፈሉ ናቸው። መዝሙረ ዳዊት አንድ እነዚህን ሁለት መንገዶች፣ መገለጫቸውንና መዳረሻቸውን በግልጽ ያሳየናል።

1 መንገዶቹ
በዚህ መዝሙር መጨረሻ ላይ የእነዚህ ሁለት መንገዶች ስያሜ የቀረበ ሲሆን አንደኛው የጻድቃን መንገድ ሁለተኛው ደግሞ የክፉዎች መንገድ ይባላሉ። በመጽሐፍ ቅዱሳችን መንገድ የሚለው ቃል አኗኗርን ወይም የሕይወት ዘይቤን ያመለክታል። ስለዚህም የጻድቃን መንገድ ሲል የጻድቃን አኗኗር፣ ሕይወታቸውን የሚመሩበትን ዘይቤ የሚጠቁም ነው። የክፉዎችም መንገድ ልክ እንደዚያው ነው። በዚህ አገላለጽ ኑሮአችን በጉዞ የተመሰለ ሲሆን ይህ ጉዞም ከእነዚህ ከሁለቱ መንገዶች በአንዱ ላይ እየተጓዝን እንገኛለን። ታዲያ ራሳችንን መጠየቅ ያለብን ትልቁ ጥያቄ የሚከተለው ሊሆን ይገባል፦ “የእኔ የሕይወት ጉዞ በየትኛው መንገድ ላይ ነው?”

2 መገለጫቸው
እነዚህን ሁለት የሕይወት መንገዶች በደንብ እንረዳቸው ዘንድ መዝሙረኛው ምስል ከሳች በሆነ መግለጫ ይስላቸዋል። የጻድቃን መንገድ “በወራጅ ውሃ ዳር በተተከለች፣ ፍሬዋን በየወቅቱ በምትሰጥ፣ቅጠሏም በማይጠወልግ ዛፍ” የተመሰለ ሲሆን የክፉዎች መንገድ ግን “ነፋስ ጠራርጎ በሚወስደው ገለባ” ተመስሎ ቀርቦአል። እነዚህ መግለጫዎች በሁለቱ መንገዶች መካከል ያለውን እጅግ ጉልህ የሆነ ልዩነት ቁልጭ አድርገው ያሳዩናል። የጻድቃን መንገድ የለመለመ የሚያፈራ ሕይወት ሲሆን ፣ በተቃራኒው የክፉዎች ሕይወት ደግሞ ሕይወት የሌለው ደርቆ ነፋስ የሚወስደው ገለባ ነው። በእርግጥም የሁላችንም ሕይወት ከእነዚህ ከሁለቱ አንዱን የሚመስል ነው። ወይ ፍሬያማ ሕይወት እንኖራለን አለያም ፋይዳ የሌለው ገለባን ሕይወት እንመራለን። አሁንም ቆም ብለን ራሳችንን ልንፈትሽበት የሚገባ ጥያቄ ቢኖር እንዲህ የሚል ነው፦ “ሕይወቴ ፍሬያማ ነው ውይስ ገለባ?”

3 መነሻና መዳረሻቸው
በመዝሙረ ዳዊት አንድ ላይ ሌላ ልብ ልንለው የሚገባን ወሳኝ እውነት የእነዚህን ሁለት መንገዶች መነሻና መዳረሻ ነው። የጻድቃን መንገድ መነሻው የእግዚአብሔርን ፈቃድ ከማወቅና በዚያም ደስ ከመሰኘት ሲሆን የክፉዎች መንገድ ግን ለዚህ አምላክ ጀርባን ከመስጠት በራስ ከመመካት የሚነሳ ነው። መዳረሻቸው ቢሆን የሰሜንና የደቡብ ያልህ እጅግ የተራራቀ ነው። የክፉችዎ መንገድ መዳረሻዋ ጥፋት ሲሆን የጻድቃን መንገድ ግን ከእግዚአብሔር ጋር ወደ ጠበቀ ግንኙነትን ይመራል። በእርግጥም ትርጉም ያለው ሕይወት መምራት የምንችለው ከሕይወታችን ምንጭ ከሆነው ከእግዚአብሔር ጋር የጠበቀ ግንኙነት ሲኖረን ብቻ ነው። ከእርሱ ተነጥለን የምንኖረው ኑሮ የገለባ ሕይወት ነው። ብዙ ሃብት፣ እውቀትና ዝና ቢኖረን ያለ እግዚአብሔር ሁሉ ገለባ ናቸው። የሁልጊዜ ምርጫችን በመልኩና በአምሳሉ የፈጠረን፣ የክቡር ደሙ የዋጀን፣ ለታላቅ ርስትም የጠራን አፍቃሪ አባታችን እግዚአብሔር ይሁንልን ።

አባት ሆይ፣ ከአንተ ስንገነጠል ገለባ፣ ከአንተ ጋር ደግሞ ስንጣበቅ ፍሬያማ ሕይወት እንደምንኖር ባስተማርከን መሰረት ሕይወታችን ባንተ ውስጥ እንድትሰወር፣ እኛም አንተን ዘወትር በፊታችን አድርገን፣ በጻድቃን መንገድ እንድንጓዝ እርዳን። አሜን።
16👍8🙏2
ተጠንቀቁ
የዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ክፍል- መዝ 2

በዩንቨርስ ውስጥ ታላቅ ጦርነት እየተካሄደ እንዳለ እናውቅ ይሆን? ይህ ጦርነት በሰማይ የጀመረ ሲሆን እግዚአብሔር እጅግ ውብ አድርጎ ከፈጠራቸው መላእክቱ መካከል የእርሱን ክብር እንዲጋርድ ትልቅ ሥልጣን የተሰጠው ኪሩብ በአምላክ ላይ በአመጸ ጊዜ የተጠነሰሰ ተጋድሎ ነው። (ኢሳ 14፤ ሕዝ 28) በተለይም የምንኖርባት ዓለም በዚህ ተጋድሎ ውስጥ ከገባችበት ጊዜ አንስቶ ይህ ፍልሚያ በእያንዳንዳችን ሕይወት ውስጥ እየተካሄደ ይገኛል። ሁለተኛው የዳዊት መዝሙር በክፉና በመልካም ኃይላት መካከል በሚካሄደው በዚህ ተጋድሎ ውስጥ ልዑል አምላክ የሚከተሉትን ሦስት ዋና ነገሮች እንደሚያደርግ ያስተምረናል ፦

1 ይፈርዳል
ምንም እንኳን የክፉ ኃይላት በእግዚአብሔር መንግስት ላይ ጭፍን ጥላቻቸውን እንዲገልጹ ቢፈቅድላቸውም፣ ከእርሱ እጅ ግን ፈጽሞ ሊያልመጡ አይችሉም። በቁጥር 4 እና 5 ላይ እንዲያውም ያለ አቅማቸው በሚንጠራሩት፣ እሳትን ሊጎርሱ ስለሚሞክሩት ዐመጸኞች እንዲህ ተጽፎአል፦
“በሰማይ ዙፋን ላይ የተቀመጠው ይሥቃል፤
ጌታም ይሣለቅባቸዋል።
ከዚያም በቍጣው ይናገራቸዋል፤
በመዓቱም ያስደነግጣቸዋል፤”
የፍቅር ማንነቱ ለእግዚአብሔር በዐመጽ እንዳይደሰት ይልቁንም በጻድቅ ፍርዱ እንዲያጠፋው ግድ ይለዋል።

2 ይገዛል
እግዚአብሔር በክፉ ኃይላት ላይ የሚፈርድ ብቻ ሳይሆን፣ የራሱንም ንጉስ፣ የቀባውን መሪ በማስነሳት ስኬትንና ድልን እንደሚሰጠው ይሄው መዝሙር ይነግረናል።
“ለምነኝ፤
መንግሥታትን ርስት አድርጌ፣
የምድርንም ዳርቻ ግዛት እንዲሆንህ እሰጥሃለሁ።” ቁ. 8
ምንም እንኳን ይህ መዝሙር እግዚአብሔር በምድር ላይ ሕዝቡን እንዲጠብቁ ላስነሳቸው እንደ ዳዊት ላሉት የንግስና በዓል ላይ እንዲዘመር የተጻፈም ቢሆን፣ በዋናነት የሚጠቁመው ግን ወደ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ከክፉ ኃይላት በሚሰነዘር በምንም አይነት አስቸጋሪ ተቃውሞ ውስጥ ብንሆን ጌታችን ኢየስሱ ክርስስቶ የሰላም አምላክ ራሱ ፈጥኖ ዲያቢሎስን ከእግራችን በታች ይቀጠቅጠዋል (ሮሜ16)።

3 ይጣራል
በመጨረሻ፣ በዚህ መዝሙር ላይ በጭፍን ጥላቻ፣ ያለአቅማቸው ከእግዚአብሔር ጋር ጦርነት ለገጥሙት ሁሉ አምላክ የፍቅር ጥሪን ያቀርብላቸዋል ።
“ስለዚህ እናንት ነገሥታት ልብ በሉ፤
እናንት የምድር ገዦችም፣ ተጠንቀቁ።
እግዚአብሔርን በፍርሀት አገልግሉት፤
ለእርሱ መራድም ደስ ያሰኛችሁ። …
ቍጣው ፈጥኖ ይነድዳልና።
እርሱን መጠጊያ የሚያደርጉ ሁሉ የተባረኩ ናቸው።” ቁ. 10-12
እርሱ ማንም እንዲጠፋ አይፈልግምና “ተጠንቀቁ” በማለት ምንም ከቁጣው ለማምለጥ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ይነግራቸዋል። ይውሄም ለእግዚአብሔር መገዛትና እርሱን መጠጊያ ማድረግ ናቸው።

አባት ሆይ፣ አንተ በጽድቅ የምትፈርድ፣ በክብር የምትገዛና በፍቅር የምትጠራን አምላክ መሆንህን በማስተዋል፣ ላንተ በመገዛትና አንተን መጠጊያ በማድረግ መኖር እንድንችል እርዳን።
🙏106👍3