የህይወት ቃል / Word of life
3.07K subscribers
2.22K photos
9 videos
4 files
38 links
ይህ የቴሌግራም ቻናል በየእለቱ ህይወት ከሆነው ከእግዚአብሔር ቃል አጠር ያለ መልእክት የሚቀርብበት ነው። ይህንን ቻናል በመቀላቀልና አብረን ይህንን የህይወት ቃል እንድንመረምር እናድማችኋለን። ጥያቄ ወይም አስተያየት ቢኖራችሁ በዚህ አድራሻ ጻፉልን። @melakalex ወይም +254724416340
Download Telegram
ወደ ቅዱስ ህይወትም የጠራን
የዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ክፍል- 2 ጢሞ 1-4
"እኛ ስላደረግነው አንዳች ነገር ሳይሆን ከዕቅዱና ከጸጋው የተነሣ ያዳነን ወደ ቅዱስ ህይወትም የጠራን እርሱ ነው"፡፡ 2 ጢሞ. 1፡9
ምንም እንኳን ገና ጠላቶቹ ሳለን በጸጋው ቢመርጠንና ቢጠራንም፣ ሁልጊዜ በዚያ የጠላትነት መንፈስ እንድንኖር ግን የጸጋው አላማ አይደለም። ምንም እንኳን ገና በኃጢአት ጎዳና ስንቅበዘበዝ በጸጋው በደላችንን ሁሉ ይቅር ብሎ ከእርሱ ጋር እንደገና ሕብረት እንዲኖረን ቢያጸድቀንም፣ እየተቅበዘበዝን እንድንኖር ግን የጸጋው አላማ አይደለም።
ምንም እንኳን ገና ደካሞች ሳለን ጸጋው በሰማያዊው ስፍራ ያስቀመጠንና የርስቱ ወራሾች ያደረገንም ብንሆን፣ በዚያ ድካም ተጎሳቁለን እንድንኖር የጸጋው አላማ አይደለም፡፡ ይልቁንም ጸጋው ገና ጠላቶቹ፣ ኃጢአተኞችና
ደካሞች ሳለን ተቀብሎን ወደ ቅዱስ ህይወት የሚመራን ነው፡፡ ለመሆኑ ይህ ቅዱስ ህይወት ምን አይነት ህይወት ነው?
ቲቶ 2፡ 11-12 ለዚህ ጥያቄ አጥጋቢ መልስ ይሰጠናል፡፡ እነዚህን ቁጥሮች ስናነብ ሁለት ነገሮችን ልብ እንበል፡፡ የመጀመሪያው ልንክደው የሚገባን አይነት ህይወት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ልንከተለው/ልንኖረው የሚገባን ህይወት ነው።
"ድነት የሚገኝበት የእግዚአብሔር ጸጋ ለሰዎች ሁሉ ተገልጦአልና፤ ይህም ጸጋ በኃጢአት መኖርንና አለማዊ ምኞትን ክደን በአሁኑ ዘመን ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ፣ በእውነተኛ መንፈሳዊ ህይወት እንድንኖር ያስተምረናል፤" ቲቶ 2፡ 11፣12
ጸጋው በኃጢአት መኖርንና አለማዊ ምኞትን እንድንክድ ይጠራናል። ‘በኃጢአት መኖር’ ተብሎ የተተረጎመው ቃል ‘ያለ እግዚአብሔር’ ወይም ‘በእግዚአብሔር ላይ በማመጽ’ የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን፣ ጸጋ በዚህ አይነት
ሕይወት እንድንቀጥል ሳይሆን እንዲህ ያለውን ህይወት እንድንክድ ያስተምረናል፡፡ አለማዊ ምኞት ደግሞ ለጊዜው ቢያስደስትም አላፊና ጠፊ ነውና የበለጠውን ደስታና ሰላም በመናፈቅ ልንክደው ይገባል። ጸጋው "ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ፣ በእውነተኛ መንፈሳዊ ህይወት" የተሞላን ህይወት እንድንኖር ይጠራናል። “በእውነተኛ መንፈሳዊ ህይወት” ተብሎ የተተረጎመው ቃል ከላይ “በኃጢአት መኖር” ተብሎ የተነገረው ቃል ተቃራኒ ሲሆን ከእግዚአብሔር ጋር ለእርሱ ክብር በሚሰጥ መንገድ አብሮ መጓዝን ያመለክታል፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር የሚኖረን እንዲህ ያለ ሕብረት ደግሞ ራሳችንን ወደ መግዛትና ወደ ጽድቅ ይመራናል፡፡ጸጋ የሚያስተምረንና ውስጣችንን የሚያነሳሳው እንዲህ ያለውን ህይወት
እንድንኖር ነው፡፡
ይህ ወደ ቅዱስ ህይወት የጠራን ጸጋው እንዴት በቀጣዩ የድነት ጉዞ እንደሚመራንና እንደሚረዳን ማጥናታችንን ስንቀጥል በሚቀጥሉት ጥናቶች አራት ተያያዥ ሃሳቦችን እንመለከታለን፡፡ እነዚህም ጸጋው እንደሚያቆመን፣ እንደሚያንጸን፣ እንደሚያጸናንና እንደሚያትረፈርፈን የሚያስተምሩን ናቸው፡፡
በቆላ 2፡ 7 ላይ ጳውሎስ እንዲህ በማለት ይገልጽልናል፡- እንግዲህ ጌታ ክርስቶስ ኢየሱስን እንደ ተቀበላችሁት እንዲሁ በእርሱ ኑሩ፤
(1) በእርሱ ተተክላችሁ (ስር ሰዳችሁ)ና ፤ (2)ታንጻችሁ፣ እንደ ተማራችሁት በእምነት ፤ (3)ጸንታችሁ፣ (4)የተትረፈረፈ ምስጋና እያቀረባችሁ ኑሩ።፡
እነዚህ አራት ሃሳቦች እንዴት የጸጋው ፍሬዎች እንደሆኑ ጥናታችንን ስንቀጥል እንመለከታለን።
ወደ ቅዱስ ህይወት ስለጠራን ጸጋው እግዚአብሔር ይመስገን።
አባት ሆይ፣ ጸጋህ ህይወቴን እንዲቀድስልኝ፣ ልክደው የሚገባኝን ህይወት በመካድ፣ ልኖረው የሚገባኝን ህይወት ደግሞ መኖር እንድችል አንተው እርዳኝ። አሜን።
👍10🙏31
በእምነት እና በትእግስት የተስፋውን ቃል መውረስ
የዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ክፍል - 2 ጴጥሮስ 1-3፤ ይሁዳ 1
ተስፋ ማድረግ እምነትን እና ትእግስትን ይጠይቃል። በዕብራውያን ምዕራፍ 6:11-12 የሚገኘው የእግዚአብሔር ቃል ይህንን እውነት እንዲህ ይገልጸዋል፦ “የተሰጠው ተስፋ እስኪፈጸም ድረስ እያንዳንዳችሁ እንዲህ ያለውን ትጋት እስከ መጨረሻ እንድታሳዩ እንመኛለን። በእምነትና በትዕግሥት የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን እንድትመስሉ እንጂ ዳተኞች እንድትሆኑ አንፈልግም።”
እግዚአብሔር የሰጠንን ክቡር ተስፋ፣ ይሔውም የማይጠፋ፣ የማይበላሽ እና የማይለወጥን ርስት ተስፋ መውረስ የምንችለው በእምነት እና በትእግስት ስንጸና ነው።
ታዲያ የተስፋውን ቃል መውረስ የሚጠይቀውን እምነት እና ትእግስት በሕይወታችን ለማሳደግ የሚከተሉትን እውነታዎች ሁል ጊዜ ማሰብ ይጠይቃል።
1. የተስፋን ቃል የሰጠን እርሱ ታማኝ እንደሆነ እንመን
ብዙ የውሸት ተስፋዎች አየሩን በሞሉበት በዚህ ጊዜ ልባችን ሁል ጊዜ ተጠራጣሪ ለመሆን ይፈተናል። ነገር ግን
“ይዋሽ ዘንድ እግዚአብሔር ሰው አይደለም፤ ይጸጸትም ዘንድ የሰው ልጅ አይደለም፤ ተናግሮ አያደርገውምን? ተስፋ ሰጥቶስ አይፈጽመውምን?” (ዘኁ. 23:19) “የተስፋን ቃል የሰጠን ታማኝ ነው።” (ዕብ. 10:23)።
2. የሰጠንም ተስፋ ሕያው፣ ጽኑ እና አስተማማኝ መሆኑን እንረዳ
እግዚአብሔር የሰጠን ተስፋ አላፊና ጠፊ የሆነ ምድራዊ ቁስ ወይም የዚህ ዓለም ከንቱ ብልጭልጭ አይደለም። ይልቁንም የዘለዓለም ህይወት እንዲሁም የማይጠፋ፣ የማይበላሽ እና የማይለወጥ ርስት ክቡር ተስፋ ነው የሰጠን! ስለዚህም ተስፋው ጽኑና አስተማማኝ ነው። “ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ለሕያው ተስፋና ለማይጠፋ፥ እድፈትም ለሌለበት፥ ለማያልፍም ርስት እንደ ምሕረቱ ብዛት ሁለተኛ ወለደን” (1 ጴጥ. 1:5) “እኛም የነፍስ መልሕቅ የሆነ ጽኑ እና አስተማማኝ ተስፋ አለን፤” (ዕብ. 6:19)
3. ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ እንደማይዘገይ እናስታውስ (2 ጴጥ. 3:9)
ጌታ የሰጠንን ተስፋ በትእግስት ለመጠበቅ እንዳንችል ብዙ ጊዜ የምንፈተነው ጌታ የዘገየ እየመሰለን ነው። አብርሃም እና ሣራ የተሰጣቸውን ተስፋ በትእግስት መጠበቅ ተስኗቸው በራሳቸው የዘየዱት ብልሃት ስቃይን እንጂ ስኬትን አላመጣላቸውም። ይልቁንም የእነርሱ ስሌት ሁሉ ሊሰራ በማይችልበት ጊዜ፣ ጌታን ብቻ በትእግስት ሲጠብቁ ቃል የተገባላቸውን በረከት ተቀበሉ። እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈው፦ “እርሱ (አብርሃም) ከታገሰ በኋላ ተስፋውን አገኘ።” (ዕብ. 6:16)። እኛም ጌታ የዘገየ መስሎን ትእግስታችን እንዳይሟጠጥ “ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ እንደማይዘገይ” ሁል ጊዜ ራሳችንን ማስታወስ ይኖርብናል።
“ወዳጆች ሆይ፤ በጌታ ዘንድ አንድ ቀን እንደ ሺህ ዓመት፣ ሺህ ዓመትም እንደ አንድ ቀን መሆኑን ይህን አንድ ነገር አትርሱ። አንዳንድ ሰዎች የዘገየ እንደሚመስላቸው ጌታ የተስፋ ቃሉን ለመፈጸም አይዘገይም፤ ነገር ግን ማንም እንዳይጠፋ ፈልጎ፣ ሁሉ ለንስሐ እንዲበቃ ስለ እናንተ ይታገሣል።” 2 ጴጥ. 3:8-9
የተስፋን ቃል የሰጠን ታማኝ እንደሆነ፣ የሰጠንም ተስፋ ጽኑ እና አስተማማኝ መሆኑን ስንረዳ እንደዚሁም እርሱ ስለ ተስፋ ቃሉ እንደማይዘገይ ሲገባን፣ የተስፋውን ቃል መውረስ የሚጠይቀውን እምነትና ትእግስት በህይወታችን እንለማመዳለን።
አባት ሆይ፣ በቃልህ እንደ መከርከን “በእምነትና በትዕግሥት የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን” እንድንሆን በጸጋህ እርዳን። አሜን!
13🙏5👍2
እግዚአብሔር በእኛ ይኖራል
የዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ክፍል - 1 ዮሐንስ 1-5

አስተማሪዋ በክፍል ውስጥ ለነበሩት ትንንሽ ልጆች "ለማየት በጣም የምትፈልጉት ምንድነው?" ብላ ጠየቀቻቸው። ከተማሪዎቹም አንዱ እጁን በፍጥነት እወጣና “እኔ በጣም ማየት የምፈልገው እግዚአብሔርን ነው” ብሎ መለሰላት።
ይሄ ልጅ እግዚአብሔርን ለማየት አጥብቆ በመፈለግ ብቸኛ አይደለም። ብዙዎች እግዚአብሔርን ለማየት ዕድሉን ብናገኝ በጣም ደስ እንደሚለን አስባለሁ። ታላቁ መሪ ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር አፍ ለአፍ ለማውራት ዕድል ካገኙ ጥቂት ሰብአዊ ፍጡራን መካከል አንዱ ሲሆን እርሱም እግዚአብሔርን ለማየት በመጓጓት ጠየቀ። እግዚአብሔርም ራሱን በገለጠለት ጊዜ የሆነው እንዲህ ተጽፎልናል።
“ከዚያም እግዚአብሔር በደመና ወረደ፤ በዚያም ከእርሱ ጋር ቆሞ ስሙን እግዚአብሔርን ዐወጀ። እርሱም በሙሴ ፊት እንዲህ እያለ እያወጀ አለፈ፤ “እግዚአብሔር ሩኅሩኅ ቸር አምላክ እግዚአብሔር ለቍጣ የዘገየ፣ ፍቅሩና ታማኝነቱ የበዛ፣” ዘጸ. 34:5-6.
ይህ የሚገርም መገለጥ ነው። እግዚአብሔር ራሱን ለባሪያው ለሙሴ በገለጠ ጊዜ ያወጀው የፍቅር ማንነቱን እንደሆነ ልብ ይሏል። እንደዚሁም ፊሊጶስ ጌታችን ኢየሱስ ሊለያቸው እንደሆነ በነገራቸው ጊዜ “ጌታ ሆይ፣ አብን አሳየንና ይበቃናል” አለው። “ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “አንተ ፊልጶስ! ይህን ያህል ጊዜ ከእናንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን? እኔን ያየ አብን አይቷል” ዮሐ. 14:8-9 በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የተገለጠው የመለኮት ማንነት ደግሞ ራሱን አሳልፎ የሚሰጠው ድንቅ ፍቅር ነበር።
እንግዲያውስ በሙሴም ሆነ በፊልጶስ እግዚአብሔርን ለማየት ለቀረበው ጥያቄ የተሰጠው ምላሽ የሚያሳየን ፍቅር የእግዚአብሔር ማንነት መገለጫ መሆኑን እና በፍቅርም ውስጥ እግዚአብሔር እንደሚኖር ነው። እውነተኛ ፍቅር ባለበት በዚያ እግዚአብሔር አለ። ፍቅር የመለኮት ማደሪያ መቅደስ የክብሩም አንጸባራቂ መስታወት ነው። ለዚህ ነው ቃሉ እንዲህ የሚለን፦ “እግዚአብሔርን ያየ ከቶ ማንም የለም፤ እርስ በርሳችን ብንዋደድ ግን እግዚአብሔር በእኛ ይኖራል፤ ፍቅሩም በእኛ ፍጹም ይሆናል።” (1 ዮሐ. 4:12)። ጭው ባለ በረሃ የሚገኙ “የምድረ በዳ ገነት” የሚባሉ አረንጓዴ ስፍራዎች አሉ። ታዲያ በምድረ በዳ የሚጓዝ ሰው በሩቅ ይህንን አረንጓዴ ስፍራ ሲያይ ስለ አንድ ነገር እርግጠኛ ይሆናል። ይሄውም በዚያ ስፍራ ውሃ መኖሩን ነው። በእርግጥም በዚያ በምድረ በዳ ውስጥ ከፈለቀው ምንጭ የተነሳ ነው በዙሪያው ህይወት ያላቸው እጽዋት በቅለው በምድረ በዳው መካከል የአትክልት ስፍራ ብቅ ያለው። ልክ እንደዚሁም ፍቅር ባለበት የፍቅር ምንጭ እግዚአብሔር በዚያ አለ።
ከእግዚአብሔር የተወለዱ ሁሉ በዚህ ምድር በሚኖሩበት ጊዜ የእነርሱ ህብረት በምድረ በዳ እንዳለችው ገነት ሊሆን ይገባል። በጥላቻ፣ በመገፋፋት፣ በመጠላለፍና በመገዳደል በተሞላችው እንደ ምድረ በዳ በሆነችው በዚህች ዓለም ውስጥ መኖር የሰለቻቸው፣ የፍቅርን ጥላ የፈለጉ፣ ፍቅርን የተጠሙ ከሩቅ የሚያዩት የምድረ በዳ ገነት የክርስቲያኖች የፍቅር ህብረት ሊሆን ይገባል። እነርሱም ወደዚያ መጥተው የእግዚአብሔርን ፍቅር ከዚያ ህብረት ሊያገኙ ይገባል።
“እርስ በርሳችን ብንዋደድ እግዚአብሔር በእኛ ይኖራል። ፍቅሩም በእኛ ፍጹም ይሆናል”
እግዚአብሔር የወደደን ያንን ፍቅር ለሌሎች እንድናጋራ ነው። ያን ጊዜ ነው ፍቅሩ ፍጹም የሚሆነው። የእርሱ ራስ ወዳድነት የሌለበት ፍቅር እኛን ራስ ወዳዶች ሊያደርገን ፈጽሞ አይችልም። ይልቁንም እኛም በተመሳሳዩ ፍቅር ሌሎችን ከራስ-ወዳድነት በጸዳ መንፈስ እንድንወድ አቅም ይሆነናል። ይህ ሲሆን ደግሞ ያ የእርሱ ፍቅር በእኛ ፍጹም ይሆናል። ግቡን ይመታል።
ዛሬ እግዚአብሔር ፍቅሩን በእኛ ውስጥ በመግለጥ በእኛ መኖር ይፈልጋል። ታዲያ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስጋን ለብሶ ወደ ምድር በመጣበት ጊዜ ማደሪያን አጥቶ በከብቶች በረት እንደተወለደው፣ ዛሬም በልባችን ውስጥ ጥላቻ እና ክፋት ሞልቶ ማደሪያ ያጣ ይሆን?

አባት ሆይ፣ አንተን ማየት ብንችል ምንኛ እንደምንወድ አንተ ታውቃለህ። ከእኛም ጋር እንድትሆን እንሻለን። ነገር ግን አንተን ማየት የምንችለው እና አንተም ከእኛ ጋር የምትሆነው በፍቅርህ ስንኖር እንደሆነ ስለ ተረዳን ይህንን በህይወታችን እንድንለማመድ፣ በልባችን ዙፋን ላይ እንድናነግስህ በጸጋህ እርዳን። አሜን!
🙏8👍5
በፍቅር ኑሩ
የዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ክፍል - 2 ዮሐንስ ፤ 3 ዮሐንስ

“እውነተኛ ፍቅር ማለት የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መፈጸም ነው። ይህም ትእዛዝ በመጀመሪያ እንደ ሰማችሁት “በፍቅር ኑሩ” የሚል ነው።” 2 ዮሐ. 1:6
አስቀድሞ የነገጎድጓድ ልጅ በመባል ይታወቅ የነበረው ቁጡና ግልፍተኛው ዮሐንስ በክርስቶስ ኢየሱስ ተገልጦ ባየው የእግዚአብሔር ፍቅር ህይወቱ ከተቀየረ በኋላ ስለ ፍቅር ደጋግሞ የተናገረና የፍቅር ደቀ መዝሙር በመባል ለመጠራት የበቃ ሰው ነበር። በተለይ “እግዚአብሔርን አውቀዋለሁ” “ከሞት ወደ ህይወት ተሻግሬያለሁ” “በብርሃን አለሁ” እያልን፣ ነገር ግን ፍቅር ከሌለን እና እርስ በርሳችን የማንዋደድ ከሆነ የምንለውን እንዳልሆንን ይልቁንም ራሳችንን እያታለልን እንደሆነ ቃሉ ያስተምረናል። የሚከተሉትን ጥቅሶች እግዚአብሔር ልባችንን እንዲመረምርና ዓይናችንንም እንዲከፍትልን በመጸለይ ደጋግመን እናንባቸው፦
“በብርሃን አለሁ የሚል፣ ወንድሙን ግን የሚጠላ አሁንም በጨለማ ውስጥ አለ። ወንድሙን የሚወድ በብርሃን ይኖራል፤ በእርሱም ዘንድ የመሰናከያ ምክንያት የለውም። ነገር ግን ወንድሙን የሚጠላ በጨለማ ውስጥ ነው፤ በጨለማ ይመላለሳል፤ ጨለማው ስላሳወረውም የት እንደሚሄድ አያውቅም።” 1 ዮሐ. 2:9-11
“ወንድሞቻችንን ስለምንወድ ከሞት ወደ ህይወት እንደ ተሻገርን እናውቃለን፤ ፍቅር የሌለው ሁሉ በሞት ይኖራል። ወንድሙን የሚጠላ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳይም የዘለዓለም ህይወት እንደሌለው ታውቃላችሁ።” 1 ዮሐ. 3:14-15
“ወዳጆች ሆይ፤ ፍቅር ከእግዚአብሔር ስለ ሆነ እርስ በርሳችን እንዋደድ፤ የሚወድ ሁሉ ከእግዚአብሔር የተወለደ ነው፤ እግዚአብሔርንም ያውቃል። የማይወድ ግን እግዚአብሔርን አያውቅም፤ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና።” 1 ዮሐ. 4:7
“ደግ ሥራ የሚሠራ ሁሉ የእግዚአብሔር ነው። ክፉ ሥራ የሚሠራ ግን እግዚአብሔርን አላየውም።” 3 ዮሐ. 1፡11
እነዚህ ጥቅሶች በአንድ ድምጽ የሚያስተጋቡት እውነት ቢኖር እኛ ራሳችንን መንፈሳዊ እና ሃይማኖተኛ አድርገን ብንቆጥርም እንኳን፣ ፍቅር ከሌለን እና እርስ በርሳችን የማንዋደድ ከሆነ በጨለማ የምንዳክር፣ በሞት ውስጥ የምንኖር፣ እግዚአብሔርንም ፈጽሞ የማናውቅ መሆናችንን ነው።
አስቀድሞ ወደ ወደደን እና ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከሞት ወደ ህይወት እንሻገር ዘንድ አንድ ልጁን ወደ ላከልን አምላክ በእምነት ስንቀርብ የልጅነት ማዕረግ ይሰጠናል። የፍቅር ሁሉ ምንጭ የሆነው እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ፍቅሩን በልባችን ያፈስሳል። እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈ፦ “እግዚአብሔር በሰጠን በመንፈስ ቅዱስ ፍቅሩን በልባችን አፍስሷልና።” ሮሜ 5:5
ከዚህም የተነሳ ከእርሱ የመወለዳችን እና የእርሱ ልጆች የመሆናችን ዋነኛው ማረጋገጫ የዚህ በልባችን የፈሰሰው ፍቅር በህይወታችን ተገልጦ መታየት ነው። ይህ ፍቅር ከሌለን፣ ውስጣችን በጥላቻ የተሞላ ከሆነ፣ ጥል፣ አድመኝነት፣ ቅናት፣ ምቀኝነት፣ ቂምና በቀል ውስጣችንን ከሞሉት፣ ቆም ብለን የጉዞ አቅጣጫችንን በመቀየር፣ የፍቅር ምንጭ ወደ ሆነው የፍቅር አምላክ በንስሃ ልንቀርብ እና ፍቅሩን በልባችን እንዲያፈስልን ልንጠይቀው ይገባል።

አባት ሆይ፣ ቃልህ “በፍቅር ኑሩ” እንደሚል ፍቅርህን በመንፈስ ቅዱስህ በልባችን እንድታፈስሰውና እኛም እርስ በርሳችን በመዋደድ በፍቅርህ እንድንኖር እርዳን። አሜን!
10🙏4
አትፍራ
የዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ክፍል - ራዕይ 1-5
“አትፍራ፤ የመጀመሪያውም የመጨረሻውም እኔ ነኝ፤ እኔ ሕያው ነኝ፤ ሞቼ ነበር፤ እነሆ አሁን ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ድረስ ሕያው ነኝ፤ የሞትና የሲኦል መክፈቻም በእጄ ነው።” ራዕይ 1:17-18
ፍርሃት በመጀመሪያ ከታዩት የኃጢአት በሽታ ምልክቶች መካከል አንዱ ሲሆን፣ እግዚአብሔር አዳምና ሔዋንን ለማናገር ወደ ኤደን ገነት በመጣ ጊዜ ከመተላለፋቸው የተነሳ ፈርተው ተደበቁ (ዘፍ. 3)። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሰው ልጅ ከተለያዩ ነገሮች የተነሳ ፍርሃትን ሲያስተናግድ ኖሯል። ነገር ግን ከፍርሃት መንስኤዎች መካከል እጅግ ጠንካራው “የሞት ፍርሃት” ሲሆን ብዙዎችን ዘመናቸውን ሁሉ ባርያ አድርጎ የሚያሰቃይ ፍርሃት ነው። ሞትን አሸንፎ ከሞት ፍርሃት ባርነት ነጻ ለመውጣት እጅግ ብዙ የተጣረ ቢሆንም ነገር ግን ከሰው ዘንድ የሆነ ነጻ አውጪ ሊገኝ አልተቻለም። አይቻልምም። ለዚህ ችግራችን መፍትሔ የተበረከተልን በአፍቃሪው ጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። በዕብራዊያን 2:14-15 ይህ መፍትሔ እንዲህ ተጽፎልናል።
"ልጆቹ በሥጋና በደም እንደሚካፈሉ እርሱ ራሱ (ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ) ደግሞ ያንኑ ተካፈለ፤ ይኸውም በሞት ላይ ኀይል ያለውን ዲያቢሎስን በሞቱ ኀይል እንዲደመስስ ነው፤ እንዲሁም በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ በሞት ፍርሀት ባርነት የታሰሩትን ነጻ እንዲያወጣ ነው።"
ጌታችን ኢየሱስ የእኛን ሥጋ ለብሶ በመስቀል ላይ በመሞት “በሞት ላይ ኀይል ያለውን ዲያቢሎስን በሞቱ ኀይል” ደመሰሰው። በሞቱ ሞትን አሸነፈ። የመቃብሩን ድንጋይ ፈንቅሎ በተነሳ ጊዜ የሞት እና የሲኦል መክፈቻ ቁልፍን በእጁ ይዞ ወጣ። በሞት ፍርሃት ባርነት የታሰሩትን ሁሉ ነጻ ሊወጡ የሚችሉበት ድል ተመዘገበ። ይህ ነው ታላቁ የምስራች!
ጌታችን ኢየሱስም በፍጥሞ ደሴት በስደት ተወርውሮ ለነበረው ለአዛውንቱ ደቀ መዝሙር ለዮሐንስ በተገለጠለት ጊዜም ይህንን ድንቅ የምስራች ነበር ያወጀው! አትፍራ፤ የመጀመሪያውም የመጨረሻውም እኔ ነኝ፤ እኔ ሕያው ነኝ፤ ሞቼ ነበር፤ እነሆ አሁን ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ድረስ ሕያው ነኝ፤ የሞትና የሲኦል መክፈቻም በእጄ ነው። ራእይ 1: 17-18
ዛሬም ከዚህ የሞት ፍርሃት ባርነት ነጻ የሚያወጣን ሞቶ የነበረው፣ ነገር ግን ሞትን በሞቱ ድል ነስቶ የተነሳው የሞትና የሲኦል መክፈቻ ቁልፍ በእጁ ያለው፣ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ሕያው የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። ህይወታችን በእርሱ ከተሰወረ ከሞት ወደ ህይወት ተሻግረናል። ሞት በእኛ ላይ ኃይል የለውምና በሞት ጥላ ሸለቆ መካከል እንኳን ብንሄድ ክፉውን አንፈራም።
የሞትና የሲኦልን ቁልፍ በእጅህ የያዘከው ውዱ ጌታዬ ሆይ፣ እኔንም በዚያው እጅህ መዳፍ ላይ እንደቀረጽከኝ በማመን ከሞት ፍርሃት ባርነት ነጻ የወጣ ህይወት እንድኖር እርዳኝ። አሜን!
15🙏5👍1
በበጉ ደም
የዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ክፍል - ራዕይ 6-11
“እነዚህ ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው፤ ልብሳቸውንም በበጉ ደም አጥበው አንጽተዋል።” ራእይ 7:14
ስኮት ማክናይት እ.ኤ.አ በ1997 በደም ካንሰር መያዙ ተነገረው። ወዲያም የካንሰር ሴሎቹን ለመግደል የጨረር እና የመድሃኒት ህክምናን ጀመረ። ምንም እንኳን ህክምናው ከባድ የነበረም ቢሆን በጤናው ላይ ለውጥ መታየቱ አስደሳች ሆነ። ሆኖም ግን በዓመቱ ተመሳሳይ የካንሰር ሴሎች ቁጥራቸው በዝቶ በሰውነቱ ውስጥ ተከሰቱ። በመቀጠል የተደረገለት የህክምና እርዳታ ከመቅኔው ውስጥ የደም ሴል ተወስዶ፣ ሴሉን ከካንሰር ነጻ በማድረግ ሌሎች የደም ሴሎችን ሁሉ በጨረር ከገደሉ በኋላ ያንን ያጸዱትን ሴል እንደገና ወደ አካሉ ማስገባት ነበር። ይህንንም በማድረግ ከካንሰር የጸዳው ሴል እየተራባ በንጹህ የደም ሴል ሰውነቱ እንዲሞላ ተስፋ ተደረገ ። ይሁን እንጂ፣ ይህም ቢሆን አልተሳካም፣ ምክንያቱም መቅኔው አሁንም የካንሰር ሴሎችን ማምረት ስላላቆመ። በመጨረሻ የግድ አዲስ የደም ሴል ከሌላ ሰው መቀበል ብቸኛው አማራጭ ሆነ ።
እህቱ ኮኒ ይህንን ለማድረግ የምትችል መሆኗ ተረጋገጠ። ንቅለ ተከላው በመጀመሪያ የእርሱን በካንሰር የተበከሉ የደም ሴሎች የተቻለውን ሁሉ በመግደል ከዚያም የእህቱን ንጹህ የደም ሴል በመትከል ተጠናቀቀ። በእርግጥም አዲሱ እና ንጹሁ ሴል እያደገ፣ የካንሰር ሴሎቹን እያጸዳ ሄደ። በመጨረሻም ከካንሰር ነጻ ሆነ። ስኮት ማክናይት ከዚህ ታሪኩ ጋር የክርስቶስ ደም የሰራውን በማመሳሰል፣ የጌታችን የኢየሱስ ደም በኃጢአት ካንሰር የተበከልነውን የሰው ልጆችን ሁሉ ለማንጻት የተሰጠን ብቸኛው መፍትሔ እንደሆነ ይገልጻል። በእርግጥም ከኃጢአት ሁሉ የሚያነጻን የልጁ የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ብቻ ነው። (1 ዮሐ. 1:7)።
አፍቃሪ አባታችንም እንዲህ በማለት ግብዣውን ያቀርብልናል፦ “‘ኑና እንዋቀስ’ ይላል እግዚአብሔር፤ ‘ኃጢአታችሁ እንደ ዐለላ ቢቀላ እንደ በረዶ ይነጣል፤ እንደ ደም ቢቀላም እንደ ባዘቶ ነጭ ይሆናል።’” ኢሳ. 1:18
ይህንን ጥሪ ተቀብለን በእምነት ወደ ክርስቶስ መስቀል ብንቀርብ፣ በደሙ ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል። በመጨረሻም የዘለዓለማዊ መንግስቱ ወራሾች እንሆናለን። እንዲህም ይባልልናል “እነዚህ ነጭ ልብስ የለበሱት እነማን ናቸው? ከወዴትስ መጡ?” … እነዚህ ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው፤ ልብሳቸውንም በበጉ ደም አጥበው አንጽተዋል። (ራእይ 7:13፣ 14) ክብር በደሙ ላነጻን ለታረደው በግ ይሁን! አሜን።
በደሙ ከመንጻታችን የተነሳ ደግሞ በመጨረሻ የምናገኘውን ታላቅ በረከት ቅዱስ ቃሉ እንዲህ በማለት ያበስረናል፦
“ስለዚህ በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት ሆነው ሌሊትና ቀን በመቅደሱ ያገለግሉታል፤ በዙፋኑ ላይ የተቀመጠውም መጠለያቸው ይሆናል። ከእንግዲህ ወዲህ አይርባቸውም፤ አይጠማቸውም፤ ፀሐይ አይመታቸውም፤ ሙቀት አያገኛቸውም፤ በዙፋኑ መካከል ያለው በግ እረኛቸው ይሆናል፤ ወደ ህይወት ውሃ ምንጭም ይመራቸዋል፤ እግዚአብሔር እንባን ሁሉ ከዓይናቸው ይጠርግላቸዋል።” ራእይ 7:15-17

አባት ሆይ፣ በልጅህ በክርስቶስ ኢየሱስ ስላበረከትክልን ከኃጢአት የመንጻት ዕድል እያመሰገንንህ፣ በዚህ ዕድል በእምነት ተጠቃሚዎች መሆን እንድንችል በጸጋህ እርዳን። አሜን!
13🙏5👍4
በግንባሩ ወይም በእጁ
የዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ክፍል - ራዕይ 12-15
ከዘለዓለማዊ ፍቅሩ የተነሳ “ ከመንገዳቸው ተመልሰው በሕይወት እንዲኖሩ እንጂ በክፉዎች ሞት ደስ አልሰኝም።” (ህዝ. 33:11) በማለት የሚናገረው እግዚአብሔር በኃጢአት ላይ የመጨረሻውን እርምጃ ከመውሰዱ በፊት የፍቅር ማስጠንቀቂያውን ለዓለም እያስደመጠ ይገኛል። በራእይ 14:6-12 የምናገኘው የሦስቱ መላእክት መእክትም ይህንን አምላካዊ የፍቅር ማስጠንቀቂያ ያስተጋባል። የመጀመሪያው መልአክ ሰማይንና ምድርን፣ ባህርንና በውስጣቸው ያለውን ሁሉ ለፈጠረው ብቻ እንድንሰግድ ያስጠነቀቀን ሲሆን፣ ሁለተኛው መልአክ ደግሞ አምልኳችንን ለሌሎች የምንሰጥ ከሆነ ይህ መንፈሳዊ አመንዝራነት እንደሆነ በመግለጽ ያስጠነቅቀናል። በመጨረሻ ወደዚህ ትእይንት የሚቀላቀለው ሦስተኛው መልአክ ደግሞ ለአውሬው ምስል እንዳንሰግድ ምልክቱንም በግንባራችንና በእጃችን እንዳንቀበል ያስጠነቅቀናል።
ራእይ ምዕራፍ 12 እና 13ን ስናነብ ሦስት አውሬዎችን እናገኛለን። የመጀመሪያው በራእይ 12 ላይ የምናገኘው ከሰማይ የተጣለው የቀደመው እባብ የተባለው ዘንዶው ሲሆን፣ በራእይ 13 ላይ ደግሞ የእርሱ ተባባሪ የሆኑትን፣ አንደኛው ከባህር ሌላኛው ደግሞ ከምድር የወጡ ሁለት አውሬዎችን እናገኛለን። የእነዚህን ሦስት አውሬዎች መግለጫ ጠጋ ብለን ስናጠና ማንነታቸውን ከአብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ ጋር በማመሳሰል ያቀረቡና ለእርሱ ብቻ የሚገባውን አምልኮ ለራሳቸው የፈለጉ እንደሆኑ እንመለከታለን። በመጨረሻም ሦስቱ በመተባበር በምድር የሚኖሩ ሰዎችን በማስገደድ ይህንን የተሳሳተ አምልኮ እንዲለማመዱ እንደሚያደርጓቸው ትንቢቱ ይናገራል።
ይሁን እንጂ፣ በማታለልም ይሁን በማስገደድ ወደ እኛ በሚመጣ በማኛውንም አይነት የተሳሳተ አምልኮ ልምምድ ውስጥ እንዳንገባ ማስጠንቀቂያው ተሰጥቶናል። እንደዚሁም፣ ከአምልኮ ጋር ተያይዞ የቀረበውን በግንባር እና በእጅ ምልክትን ስለ መቀበል የተነገረውን በደንብ ልናስተውለው ይገባል። በዘዳግም 6 ላይ ሙሴ ለእስራኤል ህዝብ ተስፋ ወደ ተገባላቸው ምድር ከመግባታቸው በፊት በከፍተኛ አጽንኦት ያሳሰባቸው ነገር ቢኖር፣ እግዚአብሔርን ብቻ እንዲያመልኩ፣ ይኸውም እርሱን በፍጹም ልባቸው እንዲወዱት ሲሆን፣ የአምላካቸውንም ትእዛዝ “በእጅህ ላይ ምልክት አድርገህ እሰራቸው፤ በግንባርህም ላይ ይሁኑ። ” (ቁ. 8)። በማለት አዟቸው ነበር። ይህ የሚያሳየው እግዚአብሔርን ስናመልክ እርሱ አስተሳሰባችንን እና ድርጊታችንን ሊቆጣጠረው እንደሚገባ ነው። ታዲያ በተመሳሳዩ፣ ሰይጣንም እርሱን እንድናመልክና ምልክቱንም በግባራችን እና በእጃችን እንድንይዝ ሲፈልግ በአስተሳሰባችንና በድርጊታችን የእርሱን ፈቃድ እንድንፈጽም መፈለጉን ነው። እንግዲያውስ ምርጫው የእኛ ነው። ለእስራኤላውያን፣ የምታመልኩትን ዛሬ ምረጡ እንደተባሉ፣ እኛም በየዕለቱ በአስተሳሰባችንና በድርጊታችን የምንገዛለትን ለመምረጥ ዕድሉ ተሰጥቶናል። እግዚአብሐርን በፍጹም ልባችን በመውደድ የእርሱን ትእዛዝ በግንባራችን እና በእጃችን በመያዝ ለአውሬው ከመስገድ ምልክቱንም በግንባራችን እና በእጃችን ከመቀበል እንድናመልጥ ጌታ ዛሬ ይጠራናል።
አባት ሆይ፣ በየዕለቱ አንተን ማምለክን ምርጫችን እንድናደርግ በአስተሳሰባችን እና በድርጊታችን ለአንተ ፈቃድ የተገዛ ህይወት እንድንኖር፣ በማታለልም ሆነ በማስገደድ አንተን ከማምለክ ዘወር እንድንል የሚያደርገንንም ፈተና እንድናሸንፍ በጸጋህ እርዳን። አሜን!
11🙏5👍1
ከእርስዋ ውጡ!
የዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ክፍል - ራዕይ 16-18
ራእይ ዮሐንስን ስናነብ በምዕራፍ 12 ላይ በምናገኛት ብርሃንን የተላበሰች ንጹህ ሴት እና በምዕራፍ 17 እና 18 ላይ በቀረበችው አመንዝራ ሴት መካከል ያለውን ተቃርኖ ልብ ልንለው ይገባል። የመጀመሪያዋ ሴት የምትወክለው የክርስቶስ ሙሽራ የሆነችውን ቤተ ክርስቲያንን ሲሆን ከክርስቶስ ጋር በእውነተኛ እምነት የተቆራኙ ሁሉ የእርሷ ዘሮች ናቸው። በተቃራኒው አንመዝራይቱ ሴት የምትወክለው ለእግዚአብሔር ብቻ የሚገባውን ስግደት በአንድም ሆነ ሌላ መንገድ ለሌሎች በመስጠት በጣኦት አምልኮ ውስጥ የተዘፈቀን ኃይማኖታዊ ስርዓት ነው። ብቻውን አምልኮ ከሚገባው ሰማይን እና ምድርን፣ ባሕርን እና የውሃ ምንጮችን ከፈጠረው ከእግዚአብሔር ሌላን ማምለክ አመንዝራነት ወይም ዝሙት ነው። ለዚህ ነው እግዚአብሔር እንዲህ ባለው አምልኮ ውስጥ ገብተው ስለ ነበሩት ህዝቡ “ከእኔ ዘወር ባለ አመንዝራ ልባቸውና ጣዖትን በተከተለ አመንዝራ ዓይናቸው የቱን ያህል እንዳሳዘኑኝ...” (ህዝ. 6:9) በማለት የተናገረው።
እንግዲያውስ እግዚአብሔርን የሚያስቆጣው የባቢሎን የዝሙቷ ወይን ጠጅ አምልኳችንን ከእግዚአብሔር ዘወር አድርገን ወደ ሌላ የምናደርግበት አካሄድ ነው። ይህን የባቢሎን የዝሙት የወይን ጠጅ ዛሬም ህዝቦች ሁሉ እየጠጡት እንደሆነ በራእይ 14 ላይ የምናገኘው የሁለተኛው መልአክ መልእክት ያስረዳናል። በእርግጥም ከእግዚአብሐር ይልቅ ገንዘብ፣ ዝና፣ ስልጣን፣ መዝናኛና የመሳሰሉት ነገሮች ሲመለኩ በዚያ የባቢሎን የዝሙት የወይን ጠጅ እየተጠጣ ነው። የባቢሎን የዝሙት የወይን ጠጅ በሃይማኖተኞችም ዘንድ እየተጠጣ የሚገኝበት ሁኔታ አለ። ይህም የሚሆነው እውነትን ከሃሰት በመቀየጥ፣ አምልኮን ለእግዚአብሔርና ለእግዚአብሔር ብቻ ከመስጠት ይልቅ ከእርሱ ጋር ተደብለው አምልኳችንን የሚቀራመቱ ሌሎች ነገሮችን በልባችን ስናስቀምጥ ነው። አምልኮን ሰማይንና ምድርን፣ ባሕርንና የውሃ ምንጮችን ከፈጠረው ከእግዚአብሔር ውጪ ለሆነ ለማንኛውም አካል እንዲሰጥ የሚያስተምር የሃይማኖት ስርአት የባቢሎንን የዝሙት የወይን ጠጅ የሚያከፋፍል ይሆናል።
ይህ ሁለተኛው መልእክ እንዳወጀው እንዲህ ያለውን የሃሰተኛ አምልኮ ወይን ጠጅ የምታመርተው ባቢሎን በእግዚአብሔር ፍርድ ተጎብኝታ መውደቋ አይቀሬ ነው። በራዕይ 18 ላይ የምናገኘው ከሰማይ የወረደው ሌላ መልዓክም ተመሳሳዩን የባቢሎን መውደቅ ዐዋጅ ከፍ ባለ ድምጽ ያስተጋባል። በመሆኑም፣ ዛሬ የልባችንን ዙፋን ሊቆጣጠሩ የሚፈልጉ፣ አምልኳችንን ሊቀራመቱ በዙሪያችን ብዙ ተፅእኖ የሚያሳድሩብን ነገሮች ሁሉ መጨረሻቸው ጥፋት ነው። አምልኮ ለሚገባው ለእግዚአብሔር ብቻ አምልኳችንን መስጠት ግን ዘለዓለማዊ ትርፍ እና በረከት አለው። ሲድራቅ ሚሳቅ እና አብድናጎ በባቢሎን ይህንን የባቢሎንን የዝሙት የወይን ጠጅ እንዲጠጡ አስገዳጅ ሁኔታ ገጥሟቸው ነበር። እነርሱ ግን ንጉሱ ላቆመው ምስል በመስገድ በእውነተኛው አምላካቸው ላይ ዝሙት መፈጸምን ፈጽሞ አልፈቀዱም። የመጨረሻ ዕድል በተሰጣቸው ጊዜ እንኳን እንዲህ በማለት ነበር የመለሱት፦ “ናቡከደነፆር ሆይ፤ በዚህ ጒዳይ ላይ ስለ ራሳችን መልስ መስጠት አያስፈልገንም። ንጉሥ ሆይ፤ በሚንበለበለው የእቶን እሳት ውስጥ ብንጣል፣ የምናመልከው አምላክ ሊያድነን ይችላል፤ ከእጅህም ያድነናል። ነገር ግን ንጉሥ ሆይ፤ ባያድነንም እንኳ፤ አማልክትህን እንደማናገለግል፣ ላቆምኸውም የወርቅ ምስል እንደማንሰግድ ዕወቅ።” ዳን. 3:16-18
እኛም እንዲህ በጽናት በመቆም ሰማይንና ምድርን፣ ባሕርንና የውሃ ምንጮችን ለፈጠረው ለእግዚአብሔር ብቻ እንድንሰግድ እና ክብርን እንድንሰጥ ይገባል። በዚህ በመጨረሻ ዘመን ለምንኖር እግዚአብሔር በቃሉ በኩል እንዲህ በማለት ለሚያቀርብልን ወሳኝ ጥሪ ተገቢውን አፋጣኝ ምላሽ እንስጥ፦
“ሕዝቤ ሆይ! በኃጢአትዋ እንዳትተባበሩ፤ የመቅሠፍትዋም ተካፋዮች እንዳትሆኑ፤ከእርስዋ ውጡ! … በእሳትም ትቃጠላለች፤ በእርስዋ ላይ የሚፈርድባት ጌታ አምላክ ብርቱ ነው።” ራእይ 18፡4፣ 8

አባት ሆይ፣ አንተን ብቻ በልባችን ዙፋን ላይ እንድናነግስ፣ በማኛውም አይነት መልክና ቅርጽ ከሚመጣ የጣኦት አምልኮ እንድንሸሽ፣ ለአንተና ለአንተ ብቻ የተገዛን ህይወት ዕለት ዕለት እንድንኖር እርዳን። አሜን!
11🙏5👍1
ለብዙዎቻችን መጀመር የሚቀለንን ያህል መጨረስ የዚያን ያህል ቀላል ሆኖ አናገኘውም። ከዚህም የተነሳ በጅምር የተውናቸው ብዙ ነገሮች በህይወታችን አሉ። በአንጻሩ፣ የጀመርነውን ነገር ጨርሰን “ተፈፀመ” ማለት ስንችል ክንዋኔያችን የሚፈጥርልን የድል አድራጊነት ስሜት ላቅ ያለ ነው። የምናመልከው ኃያሉ አምላካችን ጀምሮ የማይጨርስ ሳይሆን፣ ዓላማውን ከግብ የሚያደርስ ግሩም አምላክ ነው። በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ ሦስት ታላላቅ ስራዎችን ጌታችን በድል አድራጊነት እንደፈጸመ እናነባለን።
1. የፍጥረት ስራ ፍጻሜ
“እግዚአብሔር ይሠራ የነበረውን ሥራ በሰባተኛው ቀን ላይ ፈጽሞ ነበር” (ዘፍ. 2:2) እግዚአብሔር ያረፈው፣ የሰራው ስራ አድክሞት ሳይሆን ፍጹም የሆነን ስራ በመስራት፣ በሰራው ላይ ምንም የሚጨመርበት ነገር ባለመኖሩ ነበር። ይሁንና በመልኩና በአምሳሉ የፈጠረው ሰው በአመጽ ጎዳና በመሄድ ኃጢአት ወደ ዓለም በገባ ጊዜ ፍጹም የሆነው ፍጥረተ-ዓለም ተበላሸ። ለዚህም ችግር ቢሆን መፍትሔ ያለው አምላክ፣ የሰውን ልጅ ከኃጢአት የሚታደግበትን ዕቅድ አዘጋጀ።
2. የማዳን ስራ ፍጻሜ
በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስጋ መልበስ እና የሁላችንንም ኃጢአት ተሸክሞ በመስቀል ላይ ነፍሱን መስጠት የተከናወነው ይህ የእግዚአብሔር የማዳን ዕቅድ ሲጠናቀቅ፣ ጌታችን በቀራኒዮ “ተፈጸመ” በማለት የድልን አዋጅ አወጀ። በዚያ መስቀል ላይ ለዓለም ሁሉ ኃጢአት ስርየት የሚሆን ብርቱ ኃይል ያለው ደም ፈሰሰ። የተሸነፈ መስሎ ጌታችን አሸነፈ።
3. በፍርድ ስራ ፍጻሜ
ይህ በመስቀል ላይ ሆኖ በጭንቅ እና በጣእር የሁላችንን ኃጢአት ተሸክሞ “ተፈጸመ” ያለው ጌታ፣ በመጨረሻ ደግሞ ኃጢአትን ከዩንቨርስ ሁሉ ጠራርጎ በማስወገድ፣ አዲስ ሰማይ እና አዲስ ምድርን በመፍጠር እንዲህ ብሎ ያውጃል፦
“ተፈፀመ፤ አልፋና ዖሜጋ፣ የመጀመሪያው እና የመጨረሻው እኔ ነኝ፤” ራዕይ 21:6
ምንም እንኳን ይህ ሦስተኛው አዋጅ ገና ያልታወጀ ቢሆንም፣ የፍጥረትን እና የማዳንን ስራ በተሳካ ሁኔታ የፈጸመው እርሱ የቀረውን የመጨረሻውን አዋጅ “ተፈጸመ” በማለት እንደሚያውጅ ፈጽሞ ጥርጣሬ ሊገባን አይገባም። ይልቁንም፣ ለኃጢአታችን ስርየት በፈሰሰው ደሙ ዕለት ዕለት እየታጠብን በቅርብ ደግሞ ኃጢአትን ከዩንቨርስ ሊያጠፋ የሚመጣውን ጌታ ለመገናኘት እንዘጋጅ።
አባት ሆይ፣ የመጨረሻውን “ተፈፀመ” ከማወጅህ እና ኃጢአትን በጽድቅ ፈርደህ ከማስወገድህ በፊት፣ ከኃጢአታችን እንድንበት ዘንድ በቀራኒዮ “ተፈፀመ” ብለህ በመረቅህልን አዲስና ህያው መንገድ ወደ አንተ ዕለት ዕለት እንድንቀርብ እርዳን። አሜን!
👍9🙏54
ከዓመቱ መጀመሪያ እስከ ዓመቱ መጨረሻ

በቀን መቁጠሪያችን ዓመቱን አንድ ብለን ጀምረን እስከ ዓመቱ መጨረሻ መድረስ ቆም ብለን “እስትንፋሳችንና መንገዳችንን በእጁ የያዘውን” ፈጣሪና አዳኝ አምላካችንን እንድናመሰግን ግድ ይለናል።

ሙሴ እስራኤላውያን ተስፋ ወደ ተሰጣቸው ምድር ከመግባታቸው ጥቂት ቀደም ብሎ፣ ከፊት ለፊታቸው ስለሚገጥማቸው ነገር በማሳሰብ እንዴት አካሄዳቸውን ከእግዚአብሔር ጋር ሊያደርጉ እንደሚገባ ነግሮአቸው ነበር።
እንዲህም አላቸው:-
“ የምትገባባት ምድር እንደ ወጣህባትና ዘርህን ዘርተህባት በእግርህ ውሃ እንዳጠጣሃት የአትክልት ቦታ እንደ ግብፅ ምድር አይደለችም። ዮርዳኖስን ተሻግረህ ልትወርሳት ያለችው ምድር ግን፣ ከሰማይ ዝናብ የምትጠጣ፣ ተራሮችና ሸለቆች ያሉባት ምድር ናት። ይህች ምድር አምላክህ እግዚአብሔር የሚንከባከባት፣ ከዓመቱ መጀመሪያ እስከ ዓመቱ መጨረሻ የአምላክህ የእግዚአብሔር ዐይን ምንጊዜም የማይለያት ናት።” ዘዳ 11: 11፣12

ምንም እንኳን እስራኤላውያን ዮርዳኖስን ተሻግረው የሚወርሱት መሬት እንደ ግብጽ ሜዳማና በመስኖ ውሃ የለመለመ የአትክልት ቦታ ባይኖረውም፣ ተራሮችና ሸለቆዎች ያሉበት ፈታኝ መልክዐ ምድራዊ አቀማመጥ ቢኖረውም፣ ከየትኛውም ሥፍራ የተሻለ የሚያደርገው ግን አንድ ትልቅ ልዩነት ነበረው። ይሄውም፣ በዚያ በተራራማና ሸለቋማ ስፍራ ከሚገኘው የእግዚአብሔር ሕዝብ የተነሳ “ ከዓመቱ መጀመሪያ እስከ ዓመቱ መጨረሻ የእግዚአብሔር ዐይን ምንጊዜም የማይለው” ቦታ መሆኑ ነበር።

ይህ ስለ ጥንት እስራኤላውያን የተነገረው ቃል በዚህ ዘመን በክርስቶስ ደም ተዋጅተን የእርሱን በጎነት እንድናውጅ ለተጠራን የእግዚአብሔር ሕዝቦች ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው። እኛም ብንሆን ጌታችን ኢየሱስ "ወደ አለም ሁሉ ሂዱ" ብሎ የእርሱ መንግስት አምባሳደሮች አድርጎ ሲልከን ብዙ ተራሮችና ሸለቆዎች እንደነበሩባት ከንዓን፣ እኛም ብዙ ተግዳሮት እንደሚገጥመን አስቀድሞ ነግሮናል። ነገር ግን በሚገጥመን በማንኛውም ሸለቆም ሆነ ተራራ ተስፋ እንዳንቆርጥ “እኔ እስከ አለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋራ ነኝ” በማለት ቃል ገብቶልናል። (ማቴ 28:20) ከዚህም የተነሳ፣ በየትኛውም ስፍራ ብንሆን፣ በተራራም ሆነ በሸለቆ፣ “ ከዓመቱ መጀመሪያ እስከ ዓመቱ መጨረሻ የእግዚአብሔር ዐይን ምንጊዜም” በእኛ ላይ መሆናቸውን እናስታውስ።

1, የእግዚአብሔር ዐይኖች ደግሞ የሚምሩን ዐይኖች ናቸው

“ ያልጠፋነው ከእግዚአብሔር ታላቅ ፍቅር የተነሣ ነው፤
ርኅራኄው አያልቅምና።
ማለዳ ማለዳ አዲስ ነው፤
ታማኝነትህም ብዙ ነው።
ራሴን እንዲህ አልሁት፤ “እግዚአብሔር ዕድል ፈንታዬ ነው፤
ስለዚህ ተስፋ አደርገዋለሁ።
እርሱን ተስፋ ለሚያደርጉት፣
ለሚፈልገውም ሰው እግዚአብሔር መልካም ነው።” ሰቆ ኤር 3: 22-25

2, የእግዚአብሔር ዐይኖች የሚመሩን ዐይኖች ናቸው።

“ አስተምርሃለሁ፤ በምትሄድበትም መንገድ እመራሃለሁ፤
እመክርሃለሁ፤ በዐይኔም እከታተልሃለሁ።” መዝ 32:8

3, የእግዚአብሔር ዐይኖች የሚያበረቱን ዐይኖች ናቸው።

“ በፍጹም ልባቸው የሚታመኑበትን ለማበርታት የእግዚአብሔር ዐይኖች በምድር ሁሉ ላይ ይመለከታሉና። ” 2 ዜና 16:9


ተራራና ሸለቆ በበዛበት በዚህ ዓለም ጉዞአችን፣ የሚምሩን፣ የሚመሩን እና የሚረዱን የእግዚአብሔር ዐይኖች ከዓመቱ መጀመሪያ እስከ ዓመቱ መጨረሻ ምንግዜም ከእኛ ጋር ሆነው እዚህ ስለደረሰን ክብር ሁሉ ለእግዚብሔር ይሁን!


አባት ሆይ፣ በእርግጥም ከዓመቱ መጀመሪያ እስከ ዓመቱ መጨረሻ የሚምሩ፣ የሚመሩና የሚረዱ ዐይኖችህ በእኛ ላይ ሆነው እዚህ ስለደረስን እያመሰገንህ፣ ሁልጊዜ አካሄዳችንን ከአንተ ጋር በማድረግ ሕይወታችንን ሙሉ በሙሉ ላንተ በማስረከብ ዕለት ዕለት ለክብርህ እንድንኖር በጸጋህ እርዳን። አሜን።
17🙏11👍6