የኀብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን - አዲስ አበባ
823 subscribers
2.14K photos
47 videos
265 links
Download Telegram
ምርትን ከአምራቹ፥ ለሸማቹ፤ ከገበሬው ለነዋሪው!

በውቢቷ ከተማ አዲስ አበባ፣ በአምስቱም መግቢያ በሮች የሚገኙ የገበያ ማዕከላት፣ ለከተማዋ የኢኮኖሚ ዋስትና ከመሆናቸው በላይ ለሸማቹ ሕበረተሰብ እየሰጡ ያሉትን እፎይታ የጎላ ነው፡፡

እነዚህ ማዕከላት፣ ከየአቅጣጫው ከሚመጡ አምራቾች ጋር ቀጥተኛ ትስስር በመፍጠር፣ የግብርና ምርቶችና የእንሰሳት ተዋጽኦዎችን ሳይዘገዩና ትኩስነታቸውን ሳይቀንሱ፣ ወደ ከተማዋ እንዲገቡ በማድረግ ነዋሪው ኪሱ ሳይጎዳ ጤናውን እንዲጠብቅ አስችለዋል፡፡

በተለይም፣ በከተማዋ መሀል የሚፈጠረውን የምርት እጥረት ከመቅረፍ በተጨማሪ፣ በጅምላና በችርቻሮ ንግድ መካከል ያለውን የደላላ ሰንሰለት በማሳጠር ብሎም በመቁረጥ ለነዋሪው በተመጣጣኝ ዋጋ ምርት እንዲቀርብ በማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡

በአምስቱም አቅጣጫዎች የሚገኙት እነዚህ የንግድ ማዕከላት ከኢኮኖሚ ፋይዳቸው በተጨማሪ፣ ለአካባቢው ነዋሪ ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር አዲስ አበባ ከጎረቤት ክልሎች ጋር ያላትን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር አጠናክረዋል፡፡
2👍1
የኀብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን - አዲስ አበባ
Photo
እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል አደረሳችሁ፣ አደረሰን!

የትንሣኤ በዓል በክርስቲያኖች ዘንድ ልዩ ቦታ ያለው በዓል ነው። ሞት የተሻረበትና ሕይወት ዋስትና ያገኘበት ነው። ከሞት ባሻገር ሕይወት፣ ከመቃብር ባሻገር ትንሣኤ መኖሩ የታወጀበት ነው። ሞት መጨረሻ መቃብር መዳረሻ አለመሆናቸው የተረጋገጠበት ነው። በአዳም ምክንያት ወደ ምድር የወረደው ሰው፣ በክርስቶስ ምክንያት ወደላይ የወጣበት ነው።

የዘንድሮውን ትንሣኤ የምናከብረው ሀገራችን ኢትዮጵያ በሚያልፍ ፈተና ውስጥ እንዳለች እያሰብን ነው። መንገዳችን ረጅም፣ ጉዟችን ፈታኝ መሆኑን እናውቃለን። ብርሃን እንዳናይ የሚጋርዱ፣ በጥልቁ ጨለማ ጠፍተን እንድንቀር አሥረው ለመያዝ የሚሞክሩ ወጥመዶች ብዙ ናቸው። ወደ ተስፋ ምድር እንዳንሻገር የሚጎትቱ ሰበቦች ሞልተዋል። ዳሩ ግን ከሕማማቱ ወዲያ ትንሣኤ፣ ከዕንቅፋቱ ባሻገር ስኬት እንደሚጠብቀን አምነን እንታገላለን።

በትንሣኤው ዋዜማ - ርግጠኞች፣ ተስፈኞች፣ ተስፋ ቆራጮች፣ ወሬኞች፣ ተስፋ አስቆራጮች፣ ተጠራጣሪዎች ነበሩ። ርግጠኞቹ የሕማማቱ ፈተና እንደሚያልፍ ርግጠኞች ነበሩ። የዕለተ ስቅለት መከራ፣ለዕለተ ትንሣኤ ዋዜማ ለመሆኑ ርግጠኞች ነበሩ። የድንጋዩ በር፣ የበሩ ማኅተም እና የመቃብሩ ጠባቂዎች ትንሣኤውን እንደማያስቀሩት ርግጠኞች ነበሩ። የሚናፈሰው ወሬ እና የሚሠራጨው አሉባልታ እድሜው አጭር መሆኑን ርግጠኞች ነበሩ። ርግጠኞችም ስለሆኑ መሥዋዕትነትን ለመክፈል ዝግጁዎች ነበሩ። እውነቱን ለመመስከር ቆራጦች ነበሩ። በመስቀሉ ሥር ለመገኘት ደፋሮች ነበሩ።

ተስፈኞቹ የርግጠኞቹን ያህል ሳያዩ የሚያምኑ አልነበሩም። ግን አንዳች መልካም ነገር ይጠብቁ ነበር። የተሰጠውን ትምህርት፣ የተደረገውን ተአምራት ሰምተዋል፤ አይተዋል፤ አንዳች ነገርም ጠብቀዋል። ነገር ግን ተገቢውን መሥዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁዎች አልነበሩም። እውነትን ለመድፈር ቆራጦች አልነበሩም። ሐሰቱን ለመጋፈጥ ዐቅም አላገኙም። ቢያንስ ግን አንደበታቸውን ከክፉ ከልክለዋል።

ተጠራጣሪዎች አጥር ላይ የነበሩ ናቸው። በጥብርያዶስ ይበላሉ፣ በጎልጎታ ይክዳሉ። በሆሳዕና ይዘምራሉ፣ በሊቶስጥራ ይሸሻሉ፡፡ ተአምር ለማየት ይመጣሉ፣መከራ ለማየት ይሳቀቃሉ፡፡ ከደስታው አውጡልኝ፣ ከመከራው ጦመኛ ነኝ የሚሉ ናቸው።

ተስፋ ቆራጮች በሚያዩትና በሚሰሙት ቶሎ የሚወሰዱ ናቸው። በእውነትና በሐሰት፣ በፍርሃትና በጽናት መካከል ያለው ድንበር የጠፋባቸው ናቸው። ሕማማቱ ሲመጣ በቶሎ ወደ ትዝታ ገቡ። ሁሉንም ነገር የትናንት ታሪክ ብቻ አድርገው ወሰዱት። ሁሉንም ነገር “ልጡ የተራሰ፣ መቃብሩ የተማሰ” አድርገው ቆጠሩት። ከግራ ከቀኝ የሚሰሙት አሉባልታ፣ ከፊት ከኋላ የሚመጣው ጫጫታ፤ ከወዲህ ከወዲያ የሚማጣው እሳት፣ ከዚህም ከዚያም የሚያዩት መዓት አስፈራቸው። ነገን አስረሳቸው። በዚህ የተነሣ ተስፋ ቆርጠው ወደ ኋላ ተመለሱ።

ወሬኞች ድሮም ወሬ ስቧቸው የመጡ ናቸው። ምን አለ ምን ተባለ ብለው የተሰባሰቡ ናቸው። የሰሙትንም ያልሰሙትንም፤ የሚያውቁትንም የማያውቁትንም፤ እውነቱንም ሐሰቱንም እያደባለቁ ኢየሩሳሌምን በወሬ ሞሏት። ቢያንስ ከትንሣኤው 15 ዓመት በኋላ ወንጌሉን የጻፈው ማቴዎስ፣ እስከዚያ ዘመን ድረስ ወሬው ብዙ ተቀባይ እንደነበረው ገልጧል።

ተስፋ አስቆራጮች ዓላማቸው ሰውን ሁሉ ከትንሣኤ መንገድ ማራቅ ነበር። እነርሱም አይሄዱ፣ ሰውም አያስኬዱ። ከመጀመሪያው አልተቀበሉትም፤ በኋላም አልፈለጉትም። ብዙ ሰዎች እንደተከተሉት ሲያውቁ ደግሞ ቅናት አቃጠላቸው፤ ክፋት አንገበገባቸው። ክርስቶስን ከሰሱ፤ ራሳቸው ምስክር ሆኑ፤ በመጨረሻም ራሳቸው ፈረዱ። መቃብሩን ዘጉ፤ ጠባቂ አስቀመጡ። በማኅተም አሸጉ። ነገር፣ ያለቀና የተቆረጠ መሰላቸው።

የትንሣኤ በዓል የእነዚህን ሁሉ እውነተኛ ማንነት የገለጠ ነው። ርግጠኞች የቆራጥነታቸው ውጤት በትንሣኤ አገኙ። ተስፈኞች እንዲህ ለሚያልፍ ጊዜ ባለመጽናታቸው አዘኑ። ተስፋ ቆራጮች አሻግሮ ማየት አቅቷቸው ከቦታቸው በመጥፋታቸው ተፀፀቱ። ወሬኞች በትንሣኤው እውነት የተነሣ ያ ሁሉ ወሬ እንደ ናቡከደነፆር ሐውልት ሲፈረካከስ አዩት። ተስፋ አስቆራጮች የገደሉት ክርስቶስ ሲነሣ፣ የዘጉት መቃብር ሲከፈት፣ ያተሙት ማኅተም ሲቀደድ፣ የመደቧቸው ጠባቂዎች ሲሸሹ በዓይናቸው በብረቱ አዩ። ትንሣኤው የሚነገር ሐቅ፣ የሚታይ እውነት ሆነ። ተጠራጣሪዎች ግን አሁንም አጥራቸው ላይ ሆነው ከግራም ከቀኝም ሳይሆኑ ቀሩ።

የኢትዮጵያችንም ነገር እንዲሁ ነው። በኢትዮጵያ ለውጥ ርግጠኞች የሆኑት ዋጋ ይከፍላሉ፤ ርግጠኝነትን ፈርተው ተስፈኞች የሆኑት ቢያንስ አንደበታቸውን ከክፉ ይጠብቃሉ፡፡ ተስፋ ቆራጮች ነገን ማየት ስለሚሳናቸው መንገዳቸውን ይቀይራሉ፡፡ ወሬኞች አውርቶ አዳሪዎች በመሆናቸው የወሬ እንጀራ ይጋግራሉ። ተስፋ አስቆራጮች “ወተቱን አጥቁረው፣ ማሩን አምርረው” የዋሖችን አታለሏቸው፡፡ ተጠራጣሪዎች አንዴ ትኩስ አንዴ ቀዝቃዛ ሲሆኑ፣ ለብ ብለው ቀሩ።

ኢትዮጵያችን ግን ትንሣኤዋን እያየች ነው። መግነዙን ፈትታዋለች፣ መቃብሩን ከፍታዋለች፤ ማኅተሙን ቀዳዋለች። ወሬኞች ከመቃብር ጠባቂዎች ጋር ተማክረው የሚያወሩትን ወሬ የምትሰማበት ጆሮ የላትም። ትንሣኤዋን አይለውጠውምና። እሷ ከዚህ በኋላ የምትጠብቀው ዕርገትን ነው። የምትጓዘው ኃይል እንደሚወርድላት አረጋግጣ ነው። ወደኋላ መመለስ የለም። ሕማማት አልፏል፤ዓርብም አልፏል፤ ቅዳሜም አልፏል። ትንሣኤ መጥቷል። በትንሣኤ ሌሊት የተኙ አልሰሙ ይሆናል። በተስፋ አስቆራጮች ተታለው የሄዱ ዜናው አልደረሳቸው ይሆናል። ትንሣኤ ግን እውን ሆኗል።

ከቻላችሁ አጥር ላይ ያላችሁ ውረዱ። ተስፈኞች ርግጠኞች ሁኑ። ተጠራጣሪዎች እመኑ። ወሬኞች ከአፍ ወደ መዳፍ ተለወጡ። ምክንያቱም - ኢትዮጵያ ወደ ትንሣኤ ተቃርባለች።

የኢትዮጵያ ትንሣኤ ከሚበሰርባቸው ምዕራፎች አንዱ ግንቦት ላይ የሚካሄደው ምርጫ ነው። ትንሣኤን ያለ ሕማማት እንደማናስበው ሁሉ ዴሞክራሲንም ከውጣ ውረድ ነጥሎ ማየት አይቻልም። በዓለም ላይ በደልዳላ መንገድ ተጉዞ ዴሞክራሲን የገነባ ሀገር የለም። ዴሞክራሲና ብልጽግና ያለ ጽናት አይሳኩም። ከእኛ በፊት ዐመጻውን በትዕግሥት የመከቱ ተሻግረዋል፤ ሑካታውን በጽናት ያለፉ አሳክተዋል። ብንመኝም ፈተናውን አናስቀርም፤ መጽናት ግን እንችላለን። ከድህነት መውጫው ብርታታችን፣ ወደ ዴሞክራሲ መድረሻችው ትዕግሥታችን እንደሆነ አምነን ለኢትዮጵያ ትንሣኤ በሙሉ ልባችን እንትጋ!!

በድጋሚ መልካም የትንሣኤ በዓል ይሁንልን።

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ሚያዝያ 03 ቀን 2018 ዓ.ም

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን!

ሁልጊዜም በበዓላት ወቅት እንደምናደርገው፣ ዛሬ በትንሣኤ በዓል ዋዜማ በከተማችን የተለያዩ አካባቢዎች በጎ ፈቃደኞችን በማስተባበር የገነባናቸውን 215 ዘመናዊ የመኖሪያ ቤቶች፤ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ለሚገኙ ለአቅመ ደካሞች፣ ለአካል ጉዳተኞች፣ ለአገር ባለውለታዎችና ለልማት ተነሺዎች ከሙሉ የቤት ቁሳቁስና ከበዓል መዋያ ጋር አበርክተናል።

በከተማችን የበጎ ፈቃድ ተግባር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተና ባህል እየሆነ መምጣቱ የሚያስደስት ነው። ይህንን በጎ ተግባር በተለያየ መልኩ ለደገፋችሁ ልበ ቀና በጎ ፈቃደኞች፣ ተቋማትና አመራሮች በሙሉ በተለይም ከ 80 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ላደረገው የኦሮሚያ ባንክ በተጠቃሚዎች ስም ከልብ የመነጨ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።

የትንሣኤ በዓል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሁሉ በፍቅር ራሱን እስከ መስቀል የሰጠበት እና በትንሣኤ የምሥራች የተበሰረበት ነው። በመሆኑም በዓሉን ስናከብር በትሳኤን ዓላማ እና ምሳሌነት መሰረት በታላቅ ፍቅር እና መተሳሰብ ሊሆን ይገባል። ድጋፍ ለሚሹ ወገኖቻችን ያለንን መተሳሰብ በተግባር የምንገልጽበት፣ አንዳችን ለሌላችን የደስታ፣ የሰላም እና የአብሮነት ምክንያት የምንሆንበት በዓል እንዲሆንልን እመኛለሁ።
መልካም በዓል!

ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!

ከንቲባ አዳነች አቤቤ
የኀብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን - አዲስ አበባ
Photo
ሰው ተኮር አመራር በተግባር፤ የዜጎች የልብ ስብራት ሲጠገን!

ዓመታት በፈተናና በትግል ቢታጀቡም፣ የሰው ልጅ ጽናት ግን የማይፈታ ስር እንዳለው የወ/ሮ መስከረም ታሪክ ምስክር ነው። በልጅነታቸው ከአልጋ ላይ ወድቀው በደረሰባቸው የአካል ጉዳት ምክንያት ህይወት ገና በጠዋቱ ዳገት የሆነባቸው ወ/ሮ መስከረም አዱኛ፣ ተስፋ ሳይቆርጡ ለቤተሰባቸው ደጀን በመሆን በሰው ቤት ልብስ እያጠቡ በጉልበታቸው እንጀራን፣ በጽናታቸው ደግሞ የቤተሰባቸውን ህልም ሲያቀኑ ኖረዋል።

ይሁን እንጂ ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ የገጠማቸው ህመም ካልጋ ላይ አውሏቸው፣ ያ ይተጉበት የነበረው ጉልበት ሲዝልና ቤት ተከራይቶ የመኖር ተግዳሮት ሲደራረብባቸው ህይወታቸው ዳግም በጨለማ ተዋጠ። ያሳለፉት መከራና የታገሉት ድህነት ጫናው ቢበረታም፣ በፈጣሪ ላይ ያላቸው እምነትና አንድ ቀን ነገሮች መልካም ይሆናሉ የሚለው ተስፋ ግን ከውስጣቸው እንዳልጠፋ ይናገራሉ።

ዛሬ ያ! የጨለመው ህይወቴ በድንገት በታላቅ የደስታ ብርሃን ተተክቷል ይላሉ በደስታ እንባ። ምክንያታቸው ደግሞ በስቃይ ይገፉት የነበረው የመከራ ዘመን አብቅቶ፣ የመኖሪያ ቤት ባለቤት የሆኑበት ታሪካዊ ቀን በመሆኑ። ከንቲባ አዳነች አቤቤ በትንሳኤው ዋዜማ የቤት ቁልፍ ሲያስረክቧቸው፣ የአመታት ሸክማቸው በቅፅበት ከጫንቃቸው ላይ ወረደ።

ወ/ሮ መስከረም ደስታቸውን ለመግለጽ ቃላት አጥተው እጃቸውን ወደ ላይ ዘርግተው ፈጣሪን እያመሰገኑ የሚያሳዩት ትዕይንት፣ ከመኖሪያ ቤት በላይ ትልቅ የሰብአዊነት ትርጉም አለው። "ሰው ተኮር" የሆነው የከተማ አስተዳደራችን ማህበራዊ ፕሮግራም ለአቅመ ደካሞች ምን ያህል የህይወት ትርጉም እንዳለውና የተሰበረን ልብ እንደሚጠግን የሚያሳይ ህያው ምሳሌ ነው። በዛሬው እለት ልክ እንደ ወ/ሮ መስከረም በከተማ አስተዳደሩ የትንሳኤ ገፀ በረከት የ215 አቅመ ደካሞች፣ አረጋውያን፣ አካል ጉዳተኞችና የሀገር ባለውለታዎች የልብ ስብራት በበጎነት ተጠግኖ ተስፋቸው ለምልሟል።

በጎነት መልሶ ይከፍላል!

#በጎነት #ትንሳኤ #አዲስአበባ #ሰብአዊነት
2
ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ፤ እንኳን ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል በሰላም አደረሳችሁ።

የትንሣኤ በዓል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሁሉ መዳን ያለውን ፍቅር እስከ መስቀል ሞት የገለጸበትና የሞት ድል የተበሰረበት ታላቅ ዕለት ነው። በመሆኑም በዓሉን ስናከብር በታላቅ ፍቅር፣ በትሕትና እና በመተሳሰብ ሊሆን ይገባል።

ድጋፍ ለሚሹ ወገኖቻችን ያለንን አጋርነት በተግባር የምንገልጽበት፣ አንዳችን ለሌላችን የደስታ፣ የሰላም እና የአብሮነት ምክንያት የምንሆንበት በዓል እንዲሆንልን እመኛለሁ።
መልካም በዓል!

ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ከንቲባ አዳነች አቤቤ
2👍1
ዛሬ በጉለሌ ክፍለ-ከተማ ተገኝተን 27ኛውን የተስፉ ብርሃን የምገባ ማዕከል ስራ በማስጀመር ከማዕከሉ ተጠቃሚዎች ጋር የትንሳዔ በዓልን በጋራ አክብረናል።

በጉለሌ ክፍለከተማ ሶስተኛ ቅርንጫፍ የሆነውን ይህ 27ኛው የተስፉ ብርሃን የምገባ ማዕከል ስራ በማስጀመር፣ የምገባ ማዕከሉ ተጠቃሚ ከሆኑ ለማህበራዊ ችግር ከተጋለጡ ፣ አልባሽ አጉራሽ ለሌላቸው የሀገር ባለውለታ፣ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖቻች ፣ ከአረጋዊያን እና ከአካል ጉዳተኞች ወገኖቻችንን እንኳን አደረሳችሁ ብለን በዓሉን በጋራ አክብረናል።

በዓሉ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ያለአንዳች ልዩነት ለሰው ልጆች ሁሉ ራስን እስከ መስጠት ያሳየንን ፍቅር፣ በአብሮነት በፍቅና በመተሳሰብ ምሳሌነቱ በመከተል ልንኖር እንደሚገባ የሚስተምር በዓል ነው።

እኛም በ28ቱም የተስፉ ብርሃን የምገባ ማዕከል በዚሁ በትንሳኤ በዓል ብቻ ሳይሆን ሁሌም ወገኖቻችን ስንመግብ ለዜጐቻችን ክብራችንና ፍቅራችንን የምንገልጥበትና ማህበራዊ ፍትህን የምናነግስበት ተግባር ነው።
በዓሉን ምክንያት በማድረግ በሁሉም ክፍለ ከተሞች መዓድ የማቋደስ መርሐ-ግብር በማዕከላቱ እየተከናወኑ ይገኛሉ።

“መስጠት አያጎድልም” በሚል መርሕ የተደረገላቸዉን ጥሪ በመቀበል የገነቡት በጎ ፈቃደኛ “የአዲስ ቪው ሆቴል ባለቤት አቶ አብይ አበራ” እና በየቀኑ ለሚመመገብ የተረከበዉን “አኳስ ኮንስትራክሽን ፒ ኤል ሲ ባለቤት አቶ ወሰንን” በተጠቃሚዉ ወገን፣ በከተማ አስተዳደሩና በራሴ ስም ምስጋናዬን አቀርባለሁ።

በዓሉ የመተባበር፣ የመደጋገፍ እና የፍቅር በዓል ይሁንልን! መልካም በዓል።

ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ከንቲባ አዳነች አቤቤ
2
የአካባቢያችንን ገጽታ ለመቀየርና የተሻለ የመኖሪያ አካባቢ ለመፍጠር የጀመርነው የተቀናጀ የልማት ስራ በነዋሪዎቻችን ንቁ ተሳትፎ ተጠናክሮ ቀጥሏል። እያንዳንዱ የህብረተሰብ ክፍል በጉልበቱ፣ በእውቀቱና በገንዘቡ እያደረገ ያለው ያልተቆጠበ ድጋፍ ለስራችን መሳካት ትልቁን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል።

ይህ በጋራ የመልማት ባህላችን የአካባቢያችንን የመሰረተ-ልማት ጥያቄዎች በራስ አቅም ለመፍታት እንደምንችል ትልቅ ማሳያ ነው። ዛሬ የምናደርገው ርብርብ ነገ ለልጆቻችን የምታምርና ምቹ የሆነች አዲስ አበባን ለማውረስ የሚደረግ ትልቅ ኢንቨስትመንት በመሆኑ ኩራት ይሰማናል።

በአንድነት ከቆምን የማንለውጠው ነገር የለም፤ የአካባቢያችን ልማት በጋራ እጃችን ነው!

#የህብረተሰብተሳትፎ #የአካባቢልማት #ልማትበጋራ #ኢትዮጵያ
በመዲናችን አዲስ አበባ በዚህ ሚያዝያ ወር ሶስት ዓለም አቀፍ ስፖርታዊ ኩነቶች ይከናወናሉ።

በዚህ ወር ከሚካሄዱ ሶስት ዓለምአቀፍ ስፖርታዊ ኩነቶች ውስጥ አንዱ በመጪው ቅዳሜ የሚካሄደው የአዲስ አበባ ግራንድ ፕሪ የአንድ ቀን የአትሌቲክስ ውድድር ነው።

ይህ ውድድር በመዲናችን አዲስ አበባ ሲካሄድ የመጀመሪያው ሲሆን ለዘርፍ መንግስት በሰጠው ትኩረት የስፖርት መሰረተ ልማቶች መስፋፋት እንደ ምክንያት ሊገለጽ ይችላል።

ውድድሩ ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ እና ብዙ ተከታይ ያላቸው አትሌቶች ይሳተፉበታል። የአዲስ አበባ ግራንድ ፕሪ ሚያዝያ 10 በአዲስ አበባ ስታዲዮም የሚካሄድ ይሆናል።

በዚሁ ሚያዝያ ወር ከሚካሄዱ ውድድሮች ውስጥ ሲቲ ማውንቴን ባይክ ኢሊሚኔተር ዓለም አቀፍ የብስክሌት ውድድር እና ግራንድ ኢትዮጵያን ረን የሚካሄዱ ይሆናል።

ከተማ አስተዳደሩ ውድድሩን ለማሳካት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቂ ዝግጅቶች ከማድረግ በዘለለ በኢትዮጵያ ያሉትን የስፖርት መሰረተ ልማቶች ለማስተዋወቅ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ።
👍2