የኀብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን - አዲስ አበባ
823 subscribers
2.14K photos
47 videos
265 links
Download Telegram
ለበዓላት ግብኣት አለኝታ መሆን የቻለው የከተማ ግብርና!

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለከተማ ግብርና ልዩ ትኩረት በመስጠት እና የተቀናጀ የአኗኗር ዘይቤን በመፍጠር በርካታ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል፡፡

በተለይም በሌማት ትሩፋት ስራ፣ ሰዎች በምግብ ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን መመግብ እንዲችሉ፣ በሚኖሩበት አካባቢ እና ባላቸው አነስተኛ ቦታ ለዕለት-ተዕለት የምግብ ፍጆታ የሚውሉ የግብርና ምርቶችን እንዲያመርቱ የግብአት ድጋፍና ክትትል እያደረገ ይገኛል፡፡

በዚህም የእንስሳት ማድለብ፣ የዶሮ እርባታ፣ የወተት ላም እርባታ እና ንብ ማነብን ጨምሮ፣ አትክልትና ፍራፍሬዎች በስፋት እንዲመረቱ በማድረግ፣ የቤተሰብን ፍላጎት ከማሳካት በሻገር ለገበያ በማቅረብ ብዙዎች ተጨማሪ ገቢ እና የስራ ዕድል እንዲያገኙ ምክንያት ሆኗል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ በተለይም በበዓላት ወቅት ተፈላጊነታቸው የሚጨመሩ እንደ ዶሮ፣ እንቁላል፣ አትክልትና ፍራፍሬ ያሉትን ለተጠቃሚው በቀጥታ እንዲደርስ ለማድረግ በሁሉም ክፍለ ከተሞች የገቢያ ቦታዎችን በማዘጋጀት ሸማቹና ተገልጋዩ በቀጥታ እንዲገናኙ እያደረገ ይገኛል፡፡

ከዚህ ቀደም፥”ኢትዮጵያ በቤተሰብ ደረጃ በምግብ ራስን መቻል ካረጋገጠች በሀገር ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለው ጥረት እንደሚሳካ” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መግለጻቸው ልብ ይለዋል።
👍2
የኀብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን - አዲስ አበባ
Photo
"ማዕድ ማጋራት" የኢትዮጵያዊነት የሞራል ልዕልናና የሰው ተኮር ጉዞ ስኬት

መጋቢት 2010 ዓ.ም በኢትዮጵያ ማኅበራዊ ምህዳር ውስጥ የተከሰተው ለውጥ፣ ዜጎችን ከችግር አረንቋ ለማውጣት የተወጠነ ትልቅ የተስፋ ብርሃን ይዞ ብቅ ያለ የታሪክ አሻራ ነው። በዚህ ስምንት ዓመት የጉዞ መስመር ውስጥ "ሰው ተኮር" የሚለው መርህ በንድፈ-ሐሳብ ብቻ ሳይታጠር፣ በኑሮ ጫና ለደከሙና ለተጎሳቆሉ ወገኖች የተዘረጋ የፍቅር እጅ ሆኖ ታይቷል። በተለይም በበዓላትና በተለያዩ ወቅታዊ ፈተናዎች ምክንያት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎች የሚሰማቸውን የስነ-ልቦና ስብራት ለመጠገን የተወጠነው የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብር፣ በኢትዮጵያዊያን ልብ ውስጥ ያለውን "የመተሳሰብ" ጥንታዊ እሴት ዳግም እንዲያንሰራራ አድርጓል። ይህ ተግባር መንግሥት ለአገልጋይነትና ለዜጎች ሰብዓዊ ክብር የሰጠውን የላቀ ዋጋ የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ፣ የወንድማማችነትንና የእህትማማችነትን ጥምረት በጽኑ መሠረት ላይ ያቆመ የፍቅር መገለጫ ነው።

ይህ ግዙፍ ሰብዓዊ ንቅናቄ ባለፉት ስምንት ዓመታት ውስጥ ያስመዘገበው ውጤት በቁጥር ሲሰላ፣ ከመጋቢት 2010 እስከ 2018 አጋማሽ ድረስ በአማካኝ ከ950 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረገ ሲሆን የለውጡ መንግሥት ለሕዝብ ማህበራዊ ደህንነት ያለውን ቁርጠኝነት ያመለክታል። የችግር ድቅድቅ ጨለማ በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ባሉ እናቶችና አባቶች ቤት ውስጥ ሲያንዣብብ፣ የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብር እንደ ደራሽ ብርሃን በመፈንጠቅ የቤታቸውን ማዕድ ብቻ ሳይሆን የልባቸውን ስብራት ጭምር ጠግኗል። በሺዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦች በበዓላት ወቅት የሚሰማቸውን የብቸኝነት ስሜት ወደ የጋራ ደስታ የለወጠው ይህ ተግባር፣ የለውጡ ጉዞ ዋነኛ ፍሬ ተደርጎ ሊወሰድ የሚገባው የድል አምድ ነው።

በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ያለውን የማይጠፋ የቸርነትና የበጎ ፈቃደኝነት ባህል ዳግም ለቀሰቀሰው ለዚህ ትልቅ ስኬት ከ16.5 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሀብት ጥቅም ላይ ውሏል። ይህ ሀብት ከበጎ ፈቃደኛ ለጋሾችና ከግል ባለሀብቶች የተገኘ ሲሆን፣ ማኅበረሰቡ ለጋራ ዕድገትና ለመተሳሰብ ያለውን ዝግጁነትና አንድነት በጉልህ ያሳየ ተግባር ነው።

በመጋቢት ወር የተዘራው የመተሳሰብ ዘር ዛሬ ላይ ፈርጥሞና አብቦ ኢትዮጵያ ወደፊት ለምትገነባው ጠንካራ ማኅበራዊ ሥርዓት እንደ ዋስትና የሚያገለግል ነው። ይህ ከገንዘብ በላይ የሆነ የልብ ትስስር፣ ዜጎች በችግር ጊዜ የሚደጋገፉበት፣ በደስታ ጊዜ አብረው የሚፈኩበትና በጋራ የድል ፍሬዎች የሚደምቁበት አዲስ የብሔራዊ አንድነት መገለጫ ሆኖ ይቀጥላል።
👍2
ድጋፍ–ለዓቅመ-ደካሞች እና ድጋፍ ለሚሹ ሁሉ!

በአዲስ አበባ፥ በበዓላት ዋዜማ ለዓቅመ-ደካሞች እና ድጋፍ-ለሚሹ ሁሉ የሚደረገው ድጋፍ፣ የከተማዋን የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባህል በተግባር የሚያሳይ ትልቅ ማህበራዊ እሴት ነው።

ከተማ አስተዳደሩ፣ ከግብረ-ሰናይ ድርጅቶችና ባለሀብቶች በመቀናጀት፣ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ነዋሪዎች፣ አረጋውያንና ወላጅ አልባ ሕፃናት መሰረታዊ የሆኑ የበዓል መዋያ ምርቶችን በነጻ ያጋራል ወይም በታላቅ ቅናሽ ያቀርባሉ።

ይኽም፥ በኢኮኖሚ አቅም ማነስ ምክንያት፣ በዓሉን ማክበር ለሚከብዳቸው ወገኖች ትልቅ ተስፋና እፎይታን እየፈጠረ ሲሆን፤ ድጋፉ በዓሉን በደስታ እና ሳይጎድልባቸው እንዲያከብሩ እያደረገ የሚገኝ፤ የበጎነት ውብ ገፅታዋ እየኾነ ነው ፡፡

“50 ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ፤ ለ50 ሰው ጌጥ”ነውና አባባሉ፣ በከተማችን አዲስ አበባ መደጋገፍ፣ መተባበር እና መተጋገዝ፥ ድጋፍ ለሚሹ ዓቅመ-ደካሞች ተስፋ፣ የበዓል ፌሽታ መኾን ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡

“በጎነት አያጎድልም”!
1
ምርትን ከአምራቹ፥ ለሸማቹ፤ ከገበሬው ለነዋሪው!

በውቢቷ ከተማ አዲስ አበባ፣ በአምስቱም መግቢያ በሮች የሚገኙ የገበያ ማዕከላት፣ ለከተማዋ የኢኮኖሚ ዋስትና ከመሆናቸው በላይ ለሸማቹ ሕበረተሰብ እየሰጡ ያሉትን እፎይታ የጎላ ነው፡፡

እነዚህ ማዕከላት፣ ከየአቅጣጫው ከሚመጡ አምራቾች ጋር ቀጥተኛ ትስስር በመፍጠር፣ የግብርና ምርቶችና የእንሰሳት ተዋጽኦዎችን ሳይዘገዩና ትኩስነታቸውን ሳይቀንሱ፣ ወደ ከተማዋ እንዲገቡ በማድረግ ነዋሪው ኪሱ ሳይጎዳ ጤናውን እንዲጠብቅ አስችለዋል፡፡

በተለይም፣ በከተማዋ መሀል የሚፈጠረውን የምርት እጥረት ከመቅረፍ በተጨማሪ፣ በጅምላና በችርቻሮ ንግድ መካከል ያለውን የደላላ ሰንሰለት በማሳጠር ብሎም በመቁረጥ ለነዋሪው በተመጣጣኝ ዋጋ ምርት እንዲቀርብ በማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡

በአምስቱም አቅጣጫዎች የሚገኙት እነዚህ የንግድ ማዕከላት ከኢኮኖሚ ፋይዳቸው በተጨማሪ፣ ለአካባቢው ነዋሪ ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር አዲስ አበባ ከጎረቤት ክልሎች ጋር ያላትን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር አጠናክረዋል፡፡
2👍1
የኀብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን - አዲስ አበባ
Photo
እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል አደረሳችሁ፣ አደረሰን!

የትንሣኤ በዓል በክርስቲያኖች ዘንድ ልዩ ቦታ ያለው በዓል ነው። ሞት የተሻረበትና ሕይወት ዋስትና ያገኘበት ነው። ከሞት ባሻገር ሕይወት፣ ከመቃብር ባሻገር ትንሣኤ መኖሩ የታወጀበት ነው። ሞት መጨረሻ መቃብር መዳረሻ አለመሆናቸው የተረጋገጠበት ነው። በአዳም ምክንያት ወደ ምድር የወረደው ሰው፣ በክርስቶስ ምክንያት ወደላይ የወጣበት ነው።

የዘንድሮውን ትንሣኤ የምናከብረው ሀገራችን ኢትዮጵያ በሚያልፍ ፈተና ውስጥ እንዳለች እያሰብን ነው። መንገዳችን ረጅም፣ ጉዟችን ፈታኝ መሆኑን እናውቃለን። ብርሃን እንዳናይ የሚጋርዱ፣ በጥልቁ ጨለማ ጠፍተን እንድንቀር አሥረው ለመያዝ የሚሞክሩ ወጥመዶች ብዙ ናቸው። ወደ ተስፋ ምድር እንዳንሻገር የሚጎትቱ ሰበቦች ሞልተዋል። ዳሩ ግን ከሕማማቱ ወዲያ ትንሣኤ፣ ከዕንቅፋቱ ባሻገር ስኬት እንደሚጠብቀን አምነን እንታገላለን።

በትንሣኤው ዋዜማ - ርግጠኞች፣ ተስፈኞች፣ ተስፋ ቆራጮች፣ ወሬኞች፣ ተስፋ አስቆራጮች፣ ተጠራጣሪዎች ነበሩ። ርግጠኞቹ የሕማማቱ ፈተና እንደሚያልፍ ርግጠኞች ነበሩ። የዕለተ ስቅለት መከራ፣ለዕለተ ትንሣኤ ዋዜማ ለመሆኑ ርግጠኞች ነበሩ። የድንጋዩ በር፣ የበሩ ማኅተም እና የመቃብሩ ጠባቂዎች ትንሣኤውን እንደማያስቀሩት ርግጠኞች ነበሩ። የሚናፈሰው ወሬ እና የሚሠራጨው አሉባልታ እድሜው አጭር መሆኑን ርግጠኞች ነበሩ። ርግጠኞችም ስለሆኑ መሥዋዕትነትን ለመክፈል ዝግጁዎች ነበሩ። እውነቱን ለመመስከር ቆራጦች ነበሩ። በመስቀሉ ሥር ለመገኘት ደፋሮች ነበሩ።

ተስፈኞቹ የርግጠኞቹን ያህል ሳያዩ የሚያምኑ አልነበሩም። ግን አንዳች መልካም ነገር ይጠብቁ ነበር። የተሰጠውን ትምህርት፣ የተደረገውን ተአምራት ሰምተዋል፤ አይተዋል፤ አንዳች ነገርም ጠብቀዋል። ነገር ግን ተገቢውን መሥዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁዎች አልነበሩም። እውነትን ለመድፈር ቆራጦች አልነበሩም። ሐሰቱን ለመጋፈጥ ዐቅም አላገኙም። ቢያንስ ግን አንደበታቸውን ከክፉ ከልክለዋል።

ተጠራጣሪዎች አጥር ላይ የነበሩ ናቸው። በጥብርያዶስ ይበላሉ፣ በጎልጎታ ይክዳሉ። በሆሳዕና ይዘምራሉ፣ በሊቶስጥራ ይሸሻሉ፡፡ ተአምር ለማየት ይመጣሉ፣መከራ ለማየት ይሳቀቃሉ፡፡ ከደስታው አውጡልኝ፣ ከመከራው ጦመኛ ነኝ የሚሉ ናቸው።

ተስፋ ቆራጮች በሚያዩትና በሚሰሙት ቶሎ የሚወሰዱ ናቸው። በእውነትና በሐሰት፣ በፍርሃትና በጽናት መካከል ያለው ድንበር የጠፋባቸው ናቸው። ሕማማቱ ሲመጣ በቶሎ ወደ ትዝታ ገቡ። ሁሉንም ነገር የትናንት ታሪክ ብቻ አድርገው ወሰዱት። ሁሉንም ነገር “ልጡ የተራሰ፣ መቃብሩ የተማሰ” አድርገው ቆጠሩት። ከግራ ከቀኝ የሚሰሙት አሉባልታ፣ ከፊት ከኋላ የሚመጣው ጫጫታ፤ ከወዲህ ከወዲያ የሚማጣው እሳት፣ ከዚህም ከዚያም የሚያዩት መዓት አስፈራቸው። ነገን አስረሳቸው። በዚህ የተነሣ ተስፋ ቆርጠው ወደ ኋላ ተመለሱ።

ወሬኞች ድሮም ወሬ ስቧቸው የመጡ ናቸው። ምን አለ ምን ተባለ ብለው የተሰባሰቡ ናቸው። የሰሙትንም ያልሰሙትንም፤ የሚያውቁትንም የማያውቁትንም፤ እውነቱንም ሐሰቱንም እያደባለቁ ኢየሩሳሌምን በወሬ ሞሏት። ቢያንስ ከትንሣኤው 15 ዓመት በኋላ ወንጌሉን የጻፈው ማቴዎስ፣ እስከዚያ ዘመን ድረስ ወሬው ብዙ ተቀባይ እንደነበረው ገልጧል።

ተስፋ አስቆራጮች ዓላማቸው ሰውን ሁሉ ከትንሣኤ መንገድ ማራቅ ነበር። እነርሱም አይሄዱ፣ ሰውም አያስኬዱ። ከመጀመሪያው አልተቀበሉትም፤ በኋላም አልፈለጉትም። ብዙ ሰዎች እንደተከተሉት ሲያውቁ ደግሞ ቅናት አቃጠላቸው፤ ክፋት አንገበገባቸው። ክርስቶስን ከሰሱ፤ ራሳቸው ምስክር ሆኑ፤ በመጨረሻም ራሳቸው ፈረዱ። መቃብሩን ዘጉ፤ ጠባቂ አስቀመጡ። በማኅተም አሸጉ። ነገር፣ ያለቀና የተቆረጠ መሰላቸው።

የትንሣኤ በዓል የእነዚህን ሁሉ እውነተኛ ማንነት የገለጠ ነው። ርግጠኞች የቆራጥነታቸው ውጤት በትንሣኤ አገኙ። ተስፈኞች እንዲህ ለሚያልፍ ጊዜ ባለመጽናታቸው አዘኑ። ተስፋ ቆራጮች አሻግሮ ማየት አቅቷቸው ከቦታቸው በመጥፋታቸው ተፀፀቱ። ወሬኞች በትንሣኤው እውነት የተነሣ ያ ሁሉ ወሬ እንደ ናቡከደነፆር ሐውልት ሲፈረካከስ አዩት። ተስፋ አስቆራጮች የገደሉት ክርስቶስ ሲነሣ፣ የዘጉት መቃብር ሲከፈት፣ ያተሙት ማኅተም ሲቀደድ፣ የመደቧቸው ጠባቂዎች ሲሸሹ በዓይናቸው በብረቱ አዩ። ትንሣኤው የሚነገር ሐቅ፣ የሚታይ እውነት ሆነ። ተጠራጣሪዎች ግን አሁንም አጥራቸው ላይ ሆነው ከግራም ከቀኝም ሳይሆኑ ቀሩ።

የኢትዮጵያችንም ነገር እንዲሁ ነው። በኢትዮጵያ ለውጥ ርግጠኞች የሆኑት ዋጋ ይከፍላሉ፤ ርግጠኝነትን ፈርተው ተስፈኞች የሆኑት ቢያንስ አንደበታቸውን ከክፉ ይጠብቃሉ፡፡ ተስፋ ቆራጮች ነገን ማየት ስለሚሳናቸው መንገዳቸውን ይቀይራሉ፡፡ ወሬኞች አውርቶ አዳሪዎች በመሆናቸው የወሬ እንጀራ ይጋግራሉ። ተስፋ አስቆራጮች “ወተቱን አጥቁረው፣ ማሩን አምርረው” የዋሖችን አታለሏቸው፡፡ ተጠራጣሪዎች አንዴ ትኩስ አንዴ ቀዝቃዛ ሲሆኑ፣ ለብ ብለው ቀሩ።

ኢትዮጵያችን ግን ትንሣኤዋን እያየች ነው። መግነዙን ፈትታዋለች፣ መቃብሩን ከፍታዋለች፤ ማኅተሙን ቀዳዋለች። ወሬኞች ከመቃብር ጠባቂዎች ጋር ተማክረው የሚያወሩትን ወሬ የምትሰማበት ጆሮ የላትም። ትንሣኤዋን አይለውጠውምና። እሷ ከዚህ በኋላ የምትጠብቀው ዕርገትን ነው። የምትጓዘው ኃይል እንደሚወርድላት አረጋግጣ ነው። ወደኋላ መመለስ የለም። ሕማማት አልፏል፤ዓርብም አልፏል፤ ቅዳሜም አልፏል። ትንሣኤ መጥቷል። በትንሣኤ ሌሊት የተኙ አልሰሙ ይሆናል። በተስፋ አስቆራጮች ተታለው የሄዱ ዜናው አልደረሳቸው ይሆናል። ትንሣኤ ግን እውን ሆኗል።

ከቻላችሁ አጥር ላይ ያላችሁ ውረዱ። ተስፈኞች ርግጠኞች ሁኑ። ተጠራጣሪዎች እመኑ። ወሬኞች ከአፍ ወደ መዳፍ ተለወጡ። ምክንያቱም - ኢትዮጵያ ወደ ትንሣኤ ተቃርባለች።

የኢትዮጵያ ትንሣኤ ከሚበሰርባቸው ምዕራፎች አንዱ ግንቦት ላይ የሚካሄደው ምርጫ ነው። ትንሣኤን ያለ ሕማማት እንደማናስበው ሁሉ ዴሞክራሲንም ከውጣ ውረድ ነጥሎ ማየት አይቻልም። በዓለም ላይ በደልዳላ መንገድ ተጉዞ ዴሞክራሲን የገነባ ሀገር የለም። ዴሞክራሲና ብልጽግና ያለ ጽናት አይሳኩም። ከእኛ በፊት ዐመጻውን በትዕግሥት የመከቱ ተሻግረዋል፤ ሑካታውን በጽናት ያለፉ አሳክተዋል። ብንመኝም ፈተናውን አናስቀርም፤ መጽናት ግን እንችላለን። ከድህነት መውጫው ብርታታችን፣ ወደ ዴሞክራሲ መድረሻችው ትዕግሥታችን እንደሆነ አምነን ለኢትዮጵያ ትንሣኤ በሙሉ ልባችን እንትጋ!!

በድጋሚ መልካም የትንሣኤ በዓል ይሁንልን።

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ሚያዝያ 03 ቀን 2018 ዓ.ም

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን!

ሁልጊዜም በበዓላት ወቅት እንደምናደርገው፣ ዛሬ በትንሣኤ በዓል ዋዜማ በከተማችን የተለያዩ አካባቢዎች በጎ ፈቃደኞችን በማስተባበር የገነባናቸውን 215 ዘመናዊ የመኖሪያ ቤቶች፤ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ለሚገኙ ለአቅመ ደካሞች፣ ለአካል ጉዳተኞች፣ ለአገር ባለውለታዎችና ለልማት ተነሺዎች ከሙሉ የቤት ቁሳቁስና ከበዓል መዋያ ጋር አበርክተናል።

በከተማችን የበጎ ፈቃድ ተግባር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተና ባህል እየሆነ መምጣቱ የሚያስደስት ነው። ይህንን በጎ ተግባር በተለያየ መልኩ ለደገፋችሁ ልበ ቀና በጎ ፈቃደኞች፣ ተቋማትና አመራሮች በሙሉ በተለይም ከ 80 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ላደረገው የኦሮሚያ ባንክ በተጠቃሚዎች ስም ከልብ የመነጨ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።

የትንሣኤ በዓል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሁሉ በፍቅር ራሱን እስከ መስቀል የሰጠበት እና በትንሣኤ የምሥራች የተበሰረበት ነው። በመሆኑም በዓሉን ስናከብር በትሳኤን ዓላማ እና ምሳሌነት መሰረት በታላቅ ፍቅር እና መተሳሰብ ሊሆን ይገባል። ድጋፍ ለሚሹ ወገኖቻችን ያለንን መተሳሰብ በተግባር የምንገልጽበት፣ አንዳችን ለሌላችን የደስታ፣ የሰላም እና የአብሮነት ምክንያት የምንሆንበት በዓል እንዲሆንልን እመኛለሁ።
መልካም በዓል!

ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!

ከንቲባ አዳነች አቤቤ