ድልድይ | Dildiy | Bridge
1.45K subscribers
417 photos
87 videos
1 file
117 links
DILDIY

Whispers of the soul. Echoes of the universe.

Exploring consciousness, love, interconnectedness, and the mystery of existence through philosophy, mysticism & science.

Every thought is a bridge. Every question is a path. Every soul is connected.
Download Telegram
.
.
.

የሻይ ቡና ቆይታችን ሲጠናቀቅ የነበረኝ ግምት ወደ ቤቷ እንደምሸኛት ነበር...

ያ ግን አልሆነም...

"እኔ 'ምልህ፣ ባለፈው የሩሚን መጽሐፍ ሰጥሻለሁ ብለኸኝ ነበር አይደል?" አለችኝ...

"አዎን"

"ዛሬ እፈልገዋለሁ፣ ልትሰጠኝ ትችላለህ?"...

"እንዴታ... እሰጥሻለሁ እንጂ... ግን አሁን..." የሞባይሌን ሰዓት አየሁት... ከምሽቱ 12:30...

"አሁን ምን?" እንደመከፋት አለች...

"መሽቷል ብዬ ነው... ቤቴ ሩቅ አይደል፣ ስንመለስ ይመሽብሻል"... ቀበጣጠርኩ... ጥያቄዋ ድንገት ትንፋሽ ያሳጣኝ መሰለኝ...

"ግድየለም አንድ ታክሲ አይደል?... እንደርሳለን፣ ደግሞም ብዙ አልመሸም"... 

[ጉድ ፈላ!!... ምን አስባ ነው?...]

"ለምን ነገ አላመጣልሽም ማር"... ፊቷን በጥንቃቄ አጠናሁት...

"አይሆንም ዛሬ ነው የምፈልገው!" ፈርጠም አለች... 

በአንድ ጊዜ ፍርሃትና ጭንቀት ቅኝ ግዛታቸው አደረጉኝ... የእርሷን በጣሪያዬ ስር መገኘት እንደ ልዩ ስጦታ የምቆጥረው ነገር ቢሆንም ቤት እንሂድ ስላለችኝ ብቻ ፈንጥዤ እንሂድ የማልልበት ምክንያት ነበረኝ... 

ውዝግብ ውስጥ እንደገባሁ ሲገባት "ምነው ችግር አለ?" አለችኝ...

"ኧረ ምንም ችግር የለም... ብቻ..."

"ብቻ ምን?... ቤትህ መምጣቴ አያስደስትህም?" ኮስተር ብላ ነበር...

"እንዴት እንደዚያ ታስቢያለሽ?... ያውም አንቺ ፈልገሽ?... በጣም ነው እንጂ የሚያስደስተኝ..." 

[ለምንድነው ግን እንዲህ የምታስጨንቀኝ?...]

"የደበቅሃት አለች እንዴ?" ብላ በዓይኗ ሳይቀር ጠየቀችኝ...

"ማሂ!" ጮህኩባት... "ምንድነው የምታወሪው?"... 

አብሮ ያለመሄድ ፍላጎት ባሳየሁዋት ቁጥር እንዲህ ዓይነት ግምት እንዳትይዝ ስፈራ ነበር...

___

ሃሳቧን ማስቀየር ስላልቻልኩ ታክሲ ይዘን ወደ ሰፈሬ አመራን... የተኮራረፍን ይመስል አንዳች አልተነፈስንም... ታክሲው ቀስ እንዲል የጀመርኩት ጸሎት ከማረጉ በፊት መንገዱ አለቀ...

"ወራጅ አለ" አልኩ... ረዳቱ ታክሲውን ደብድቦ አስቆመው... ወረድን... ጭንቀቴ ግን እኔን ታክሲ አድርጎ ጉዞውን ቀጥሏል...

እየመራሁ የኪራይ ቤቴ አደረስኳት... እንደተዘጋጋን... ሆኖም በሩን ለመክፈት አቅም አጣሁ... [እጄ እንደ መንቀጥቀጥ አለብኝ]

"እኔ ልክፈትልህ እንዴ?" አሾፈችብኝ...

ወደ ውስጥ ገባን...

'ያንተ ያለህ!'... የፈራሁት ይህን ነበር...

ቤታችንን ውስጥ ሌላ ሰው ሲገኝ ብቻ የሚፈጠር ትርምስ አለ ልበል?... በአዘቦቱ ምንም የማይረብሸኝ ቤት ፍቅረኛዬን ይዤበት ስገባ አህያ የወለደበት መስሎ ጠበቀኝ...

[ሳይታጠቡ አንድ ስርቻ ውስጥ የታጎሩ፣ ቢወረወሩ ግንባር ለመፈንከት አቅም የማያጡ ካልሲዎች... ባዶ የወተትና እርጎ ማሸጊያ ፕላስቲኮች፣ መወልወያ የናፈቀው ወለል፣ ከአልጋ እስከ ምንጣፍ የተዘረጋ የልብስ ኤግዚቢሽን... የፌስታል መዓት... የሻማ ቁራጭ፣ የክብሪት እንጨት፣ ብዙ የሃይላንድ ዕቃ፣ በአቧራ የተሸፈነ የመጽሐፍ መደርደሪያ፣ ድር የጎበኘው ግርግዳ... የታፈነ አየር... ምኑ ቅጡ...]

'እንዴት እስከዛሬ አላስተዋልኩትም?'

ትዝ ሲለኝ ቁጭ በይ እንኳ አላልኳትም... የቤቴን ሁኔታ በዓይኖቿ ስታበጥር ነበር... አንድ ወንበር ስቤ በሶፍት ለማጽዳት ስሞክር "ተወው ተወው አልቀመጥም፣ ይልቅ ሸኘኝ..." አለችኝ... በጣም ደነገጥሁ...

"እንዴ፣ ማሂ! በቃ?... ለዚህ ነው የመጣሽው?" ግራ ተጋባሁ... 

"የምፈልገውን አግኝቻለሁ፣ ይልቅ መሽቷል እንሂድ" ፊቷን አዙራ ወደ በሩ አመራች... መጽሐፉን እንኳ አልጠየቀችኝም...

"ማሂዬ፣ ይቅርታ፣ ቤቴ ደብሮሽ ነው አይደል? በእናትሽ አትቀየሚኝ፣ ቤቴ ሰው ይመጣል ብዬ ስላላሰብኩ ነው ቸል ያልኩት፣ ላስተካክለው እችላለሁ..." መረጋጋት ተቸገርኩ...

"የመጣሁት መጽሐፍ ፈልጌ አይደለም፣ ሰው አይመጣበትም የምትለውን ቤትህን እንዴት እንደምትይዘው ማየት ፈልጌ እንጂ..."

"አልገባኝም..." ብስጭት ውስጥ እየገባሁ ነበር...

"አየህ... አንተ ማለት 'ማንም አያየኝም' ስትል የምታደርገውን ነህ... መምጣቴን አውቀህ ብትሰተር በእኔ ፊት ለማስመሰል እንጂ የሆንከውን ለመኖር ነው ልል አልችልም ነበር... ድንገት መምጣት ያስፈለገኝ ለዚህ ነው..."

ዝም አልኩ... ጸጥ ረጭ!!... ቤቴም ተባበረችኝ... ውጪውም አገዘኝ... በዚህ ሁኔታ ዝም ያልኩበትን ሁኔታ በጭራሽ አላስታውስም... እፍረት ጨመደደኝ...

"እንሂድ?" አለችኝ ደግማ፣ ደረጃውን እየወረደች...

ልሸኛት ወጣሁ... ታክሲ ተራ እስክንደርስ ምንም አላወራንም...

"ሁለት ሰው?" አለ ረዳቱ እንዳየን...

"አንድ ብቻ!..." ፈጥና መለሰችና ነጠለችኝ... ለነገሩ ታክሲውም ያለው የአንድ ሰው ቦታ ነበር...

ከመግባቷ በፊት እንደተለመደው አቅፋ እንድታሰናብተኝ፣ እንደምወደው አንገቷን እንድስማት ጓጉቼ ነበር...

አልሆነም...

ቻው እንኳ ሳትለኝ ዘው ብላ ገባች... 

ታክሲው ይዟት ተፈተለከ... ባለሁበት ደርቄ ቀረሁ... 

___

አንድ ፈተና ብቻ ሰጥታኝ ከ 100 አረመችው... እርሱንም ወደቅሁ...


"ሰዎች ለእኔ ያላቸውን ፍቅር የምመዝነው ለራሳቸው ባላቸው ክብር ውስጥ ነው" ብላኝ ነበር...

___

@bridgethoughts
👏107🥰3🔥1🥴1
.
.
.

ቅድሚያ የሰጠኸው ሰው - ከፊትህ አክብሮትን ሳይሆን ፍርሃትን ካነበበ፣

አደራ የሰጠኸው ሰው - የልብህን ማመን ሳይሆን የድርጊትህን ሞኝነት ካሰበ፣

ሙሉ ጊዜህን የሰጠኸው ሰው - ፍቅርህ ሳይሆን ስራፈትነትህ ከተሰማው፣

ገንዘብህን የሰጠኸው ሰው - ችሮታህን ረስቶ መጠኑ አንሶ ከታየው፣

የረሳህለት ሰው - ይቅር እንዳልከው ሳይሆን እንዳልተሰማህ ካመነ፣

ያገለገልከው ሰው - እርዳታህን ትቶ ግዴታህን ብቻ ካሰበ፣

ከበላይህ ያለ ሰው - የሃሳብህን ፋይዳ ከቆምክበት መደብ ካለካካ፣

የእጅህን ንጽህና የሚያውቅ - ዕድል ስላላገኘህ እንጂ መስረቅ ስላልፈለክ አይደለም ብሎ ካሰበ፣

ቆርሰህ ያካፈልከው - የሰጠኸውን ሳይሆን ከእጅህ የቀረውን ካስተዋለ፣

ግማሽ መንገድ የሄድክለት - ከጠበቀህ በቆመበት፣

ለወፌ ቆመች ተለጉሞ - ይድፋህ ለማለት ካደረ ቆሞ፣

እንዲለወጥ እጅ ያላቀበለ - ለትችት ከተቀባበለ፣

ባወቅሁሽ ናቅሁሽ ያንተን ጡብ ንቆ - የሩቅ መናኛ ካየህ አድንቆ፣

.
.
.

ወዳጄ ችግር አለ... 
___

@bridgethoughts
👍108🙏2👌2🥰1
.
.
.

ነገሩን እንዴት መሰለህ የማየው...


የሆነ ሰው አለ አይደል - ደጋግመህ የምታልፍበት መንገድ ላይ የሚቀመጥ... እናም ባየህ ቁጥር "ይሄ ልጅ ሁልጊዜ በዚህ በኩል ሲያልፍ አየዋለሁ" እያለ የሚገረም... የአንተን በዚያ መመላለስ ያወቀው እኮ እርሱም ሁልጊዜ በዚያ የሚቀመጥ ስለሆነ ነው...


ወይም ደግሞ...


"ምን ያፈጥብኛል?" የምትል እንስት ማፍጠጥህን ሳታይህ በምን አወቀች?... በምንም ልታውቅ አትችልም... [ስለዚህ ጉዳዩ ላይ ተባብራለች...]


ነገሩ 'አንተ በሌለህበት መስታወቱ ምን ያንጸባርቃል?' የሚል እሳቤን ይፈጥራል... መስታወቱ ፊት ከሌለህ መስታወቱ 'የመሰወተውን' ልታውቅ አትችልም ማለት ነው... (የመሰወተው ይባላል እንዴ?...)


ነገሩን ወደ ኑረት እንጎትተው...


የሆነ ብሽቅ ሰው ሰደበህ ወይም 'ስምህን አጠፋ' እንበል... [ስምህን በእርሳስ አትፃፍ ብዬህ አልነበር?...ሃሃሃ]... ራስህን ለመከላከል አልያም 'የክብር' ነገር ሆኖብህ ምላሽ ለመስጠት ወሰንክ...


ዌል፣ ምላሽህን መስታወቱ ፊት እንደመቆም አድርገህ ብታስበው ግጭት የመፈጠር ዕድሉ ሰፊ ነው... ነገሩን አልሰማኸው ወይም ትተኸው ቢሆንስ ኖሮ?... በቃ ሰላም!!...


ሃበሻ ድንቅ ብሂል አለችው... 'መተው ነገሬን ከተተው' የምትል... [በዕለታዊ እንቅስቃሴዬ ሁሉ ምርኩዝ የምትሆነኝ mystical ቃል ናት... እርሷን የረሳሁ ዕለት ነው suffer የማደርገው... የምስራቁን ዓለም ትምህርት በሙሉ በአንድ አቢሲኒያዊ ዘዬ ጠቅልል ብባል 'መተው - ነገሬን ከተተው' ነው የምለው'... እንዴት ዓይነት libration መሰለህ - መተው!!!...]


ምንም ነገር የሚኖረው ስንኖር ነው... [ነገሩን በደንብ አስበው የምር... አሁን በዙሪያህ ያለው ነገር ያላንተ ምንድነው?... ስለኖርክ ብቻ ያለ አይመስልህም?... ይገባኛል 'ባልኖርም መኖሩን አላስቀርም' የሚል ሃሳብ እንደፈተነህ... የረሳኸውን ግን ላስታውስህ... 'መኖር' የኖረው 'ኖረህ' ስላየኸው ነው...] አንድ ጊዜ በመኖር 'ያወቅነውን' ነገር እንደሌለ መቀበል ይቸግረናል...


[እዚህች ጋ ትንሽ ተፈላሰፍ... የምታየውን ነገር አንድ ሚሊየን ሰው እያየው ቢሆን እንኳ ያንተን perspective የሚመስል ላይኖር ይችላል... ወይም ደግሞ ወጋየሁ 'ፍቅር እስከ መቃብርን' እየተረከ የሚሰሙት እልፍ ሰዎች - እልፍ ሰብለወንጌልን ነው በምናባቸው የሚስሉት... (ምናብ ለዘላለም ይኑር!... እነ ETV መጥተው 'ሰብለ ይህች ናት' ሲሉህ ግን የምናብህን ሰብለን እየሰረቁህ እንደሆነ አትርሳ... የጋሽ ሐዲስን መጽሐፍ ስታነብ መቼና የቱን የምትስለው፣ ሰውና መልክዓ-ምድሩን የምትኩለው አንተ ነህ... 'ኢቲቢ' ስታይ ግን የዳይሬክተሩ ሰብለ ናት የምትሰጥህ... ምናብህን ከሚበሉ መስኮቶች ራቅ ወዳጄ)... ይህችን 'ወሽመጥ ሃሳብ' ለጊዜው ዝጋትና ያቺ ሁሉ የምናብ ሰብለ የኖረችው በማን መኖር ነው ብለህ ጠይቅ...]


ምን መሰለህ?... 'በሚቀጥሉት ፭ ሰከንዶች ውስጥ ስለ ዝሆን አታስብ' ብልህ በእርግጠኝነት ከዝሆን ውጭ ማሰብ አትችልም... ጥያቄው ግን - 'ስለ ዝሆን ምንም ዕውቀት ባይኖርህስ?' የሚል ነው... ስለምን ታስባለህ?... አስቀድሞ እውቀቱ በሌለህ ነገር ላይ ብዙም አትቸገርም...


ነገሩን መረር እናድርገው እንግዲህ...


በሰዎች አንዳች ተግባር ስትፈርድ ውስጥህ ያለው ተመሳሳይ የጥፋት ስሜት አጋዥ ሆኖ ይቆማል... ምን ማለቴ መሰለህ?... ሰዎችን የምትኮንንበት ጥፋት በሙሉ አንተም ውስጥ አለ... 


ሩሚ እንዲህ ይላል... “The fault you see in your brother is really in you.” 


አየህ - 'ከደሙ ንጹህ ነኝ' ዓይነት እጅ ልቅለቃ ብዙ አያዋጣም... ብዙዎቻችን ሌሎች ዓይን ውስጥ ያለ ብናኝ እንከን ሳይቀር ማየት የማያስችለን ምሰሶ ዓይናችን ውስጥ ተጋድሟል... 


የ Lao Tzu ቃል ለዚህ ፈውስ ነው... “Knowing others is intelligence. Knowing yourself is wisdom.”

___

ምን እያልኩ ነበር?... [እንጃ... ጠፋብኝ...]

___

[ይህችን ሃሳብ የሰኞ ዋዜማ 'ተብሰልስሎት' በላት... የተጀመረም ያለቀም ነገር የላትም... ሃሳብ ከጫረች በቃት! - ዓላማዋን አሳክታለች...]

___

@bridgethoughts
12🔥4🙏3👌1
.
.
.

በሰዎች አዕምሮ ውስጥ መንጎዳጎድ ደስ ይለኛል... በተለየ ሁኔታ ቀልቤን የሚስብ ሰው ሳገኝ 'ምን እያሰበ ይሆን?' ማለት አዘወትራለሁ...

___

'ወክ' እያደረግሁ ነው...


አሁን ለምሳሌ ይሄ ከፊቴ እያለፈ ያለው ሰውዬ ከሰው ጋር እያወራ እንዳለ ሁሉ እጁን እንዲህ የሚያወናጭፈው ምን እያሰበ ነው?... ተመልካች ጉድ እስኪለው፣ ለራሱ እንኳ እስኪገርመው 'ለብቻው' ሚያወጋው ምን ገጥሞት ነው?... ጎጆው ስንት ቀዳዳ ቢከፍትበት - ወገንስ ምን ያህል ቢከፋበት ይሆን?...

የተዋት ሚስቱ ናት የተወችው ኑረት እንዲህ 'ምታወራጨው?... የአለቃው ንግግር ብስጭት ነው፣ የበደለው ጎረቤቱ ቁጭት አቅሉን ያቀጨጨው?... 

ከቶ ራሱን እንዳይቆጣጠር ያደረገው ምንድነው?... ልማድ ወይስ ጉድለት?... ህመም ወይስ ጭንቀት?...

___


ከባሻገር...

እኒያን ጥንዶች እንዲህ ያወሻሸቃቸው ምንድነው?... የፍቅር ቀለበት ወይስ የስሜት ዘለበት?... የዕድሜ ልክ ፈፋ ወይስ የወራት አረፋ?...

እንግዳ ደራሽ ቢጠይቅ ምንና ምን ነን ይላሉ?... መውደድ ያቆራኘን ጥንዶች ወይስ መንገድ ያገናኘን ቧልቶች?...

እርሷ ዓይኖቹን ስታይ የምታስበው ምንድነው?... እርሱ ጉንጯን ሲስም የሚያልመው መቼን ነው?... የጋራ ነገ አላቸው?... እርሷ በነፍሱ ዘንድ ቦታዋ ምንድነው?... እርሱ በእቅፏ ውስጥ ጥጋቱ ወዴት ናት?... በሕይወቱ ውስጥ ሹፌር ናት ተሳፋሪ?... ለዕለታቶቿ አባሪ ነው ኗሪ?... 

___


ያ የጎዳና ተዳዳሪ ልጅ ምንድነው የሚያስበው?... ይህን ቤንዚን ሲስብ ምንድነው 'ሚሰማው?... ብርድ ይረሳበታል ወይስ ሆድ ይሸነግልበታል?... ቀኑን ያሳልፍበታል ወይስ ራሱ ያልፍበታል?... 


በአባት የታቀፈ ልጅ ከአጠገቡ ሲያልፍ ምን ይሰማዋል?... በእናት ስስት የተጌጠ ህፃን ምን ያስታውሰዋል?... 

___

እኒያ ከበተስኪያን ደጅ የቆሙ እናት ምን እየለመኑ ይሆን?... ከሚጨናበሱ ዓይኖቻቸው፣ ማድያት ካጠቆረው ፊታቸው ዘንድ ተስፋ ምንድን ናት?... 


ፈንጠር ብላ የምታነባዋ ወጣት ሴት መሻቷ ምን ይሆን?... ከገረገራው ያቆማት፣ ዓይኗን በእንባ ያጠባት ምን ሊሆን ይችላል?... 


ጉንጯን እየሰረሰረ የሚወርደውን የእንባ ጎርፍ የትኛው ሃዘኗ ፈጠረው?... የሚንሰቀሰቅ ሰውነቷንስ በደል ማን ጨክኖ ወለደው?... የባሌን ልብ መልስልኝ ይሆን የምትለው?... ይህን ፈተና ከኔ አርቀው ይሆን የምትለው?... መውጫውን አሳየኝ ይሆን 'ምትለው?... ምንድነው የሆነችው?...

___


ያቺ ስልክ እንጨት ተደግፋ የቆመች ሴተኛ አዳሪ ስለ ለሊቷ ምን እያሰበች ይሆን?... ዛሬስ 'ሚተኛት ምን ዓይነቱ ነው?... ጨካኝ ነው አዛኝ?... ማጋጭ ነው ባካኝ?... በልቧ የሚመላለሰው ጸሎት ምን ይሆን?... 'ከማላውቀው ሰው የማይታወቅ ዓመል፣ ከሚያውቀኝ ሰው የወሬ ደለል - ከልለኝ' ይሆን የምትል?...


ባለትዳሮች ምን ምን ይሏታል?... 'ሚንቃት ስታይ ምኗን ያንቃታል?...

___
.
.
.

እርሱ ምን እያሰበ ይሆን?...
.
.
.

እርሷስ ምን እያሰበች ይሆን?...

___

ከሰው ልጅ የአረማመዱ ቅኝት፣ ከአዋዋል ከአነጋገሩ ስምረት፣ ከኑሮ ከጎጆ ታዛው፣ ከልብሱ ከከፈን ደብዛው - ባሻገር...

ብዙ ተረክ ብዙ ታሪክ አለ... 
ብዙ ሃዘን ብዙ ስብራት አለ...
ብዙ ቁስል ብዙ ህመም አለ...
በሆድ ይፍጀው የታዘለ...


አሁን አንቺ ምን እያሰብሽ ነው?...

___

@bridgethoughts
12🤔31🙏1
.
.
.

አንዳንዴ ግን አስባታለሁ...


ወዳጅነታችን መራራቅ ያደበዘዘው፣ የሌላነትም ያጠየመው ነው... እንዲያም ሆኖ ግን አስባታለሁ... የጋራ ነገ እንደሌለን እርግጠኛ ሆኜም ሁሌ አስታውሳታለሁ...


ከግዙፍ የመርሳት አባዜዬ የተፋቱ ሽርፍራፊ ትዝታዎቿ ድንገት ፊቴ ይደቀናሉ...


አስባታለሁ...


አብራኝ እንደማትሆን እያወቀች ትዝታዎቿን እኔ ዘንድ የተወችበትን ብልሃት ብበሳጭበትም አስታውሳታለሁ...


ሄዶ ላለመረሳት፣ 'ርቆ ላለመፋቅ በአዕምሮዬ የሞጀረቻችው መቆሳቁሶች ብዙ ናቸው!...


ባለፈው ወር...


እዚያ የምታውቁት ካፌ ውስጥ ቁርስ ለመብላት ተቀምጬ እያለ አንዲት መለሎ ሴት ስትገባ አየሁ... ስትር ያለው ቁመናዋ እያባበለኝ በፈራ ተባ መሽኮርመም ውስጥ ሆኜ እያየሁዋት ቆየሁ... ከአጠገቤ አለፈች... አንገቴን ወደኋላ ማዞር ፈልጌ ነበር... እፍረት ጨምድዶኝ ተውኩት... 


የሽቶዋ መዓዛ ግን 'ማለፍ ክልክል ነው' እንዳሉት ሁሉ አፍንጫዬ ላይ ተሰንቅሮ ቀረ... እናም አልፋ እንዳላለፈች ገባኝ...


'ይህን ሽቶ የት ነበር የማውቀው?'... 


አዎን - መሲ ጋ ነው... በተመረጡ የመገናኛ ቀኖቻችን ሁሉ ይህን ሽቱ ነበር ነስነስ አድርጋ የምትመጣው... ተንኮሏ ግን... ምናል አንድ ዓይነት ሽቱ ብቻ ባትቀባ?... [እንዳልረሳት አይደል?...] አፍንጫዬስ ምን ቢሆን ነው ይህን ሽቱ ነጥሎ ማጥፋት ያቃተው?...


ባለፈው ሳምንት...


ከጓደኛዬ ጋር በታክሲ እየሄድን ወግ እንጠርቃለን... ተመስጬ እያወራሁ ሳለ ከወደ ሬዲዮው የተወነጨፈው ዜማ ቀልቤን ወሰደው...


'አንድ ሰው'... የፍቅረአዲስ እንጉርጉሮ... የሆነ ዓይነት ኃይል ስቱዲዮ ተቀምጦ፣ በ remote control ልሳኔን የዘጋው መሰለኝ... መሲ ይህን ሙዚቃ በጣም ትወደው ነበር...


"... አሃሃሃ አንድ ሰው - አሃሃሃ በየጨዋታው ላይ
አሃሃሃ አንድ ሰው - ባይመጣ ትዝታ
አሃሃሃ አንድ ሰው - አሃሃሃ እቃኘው ነበረ
አሃሃሃ አንድ ሰው - ባቲን ለደስታ..."


የወሬዬ በድንገት መቆም ከፊት ያሉ ተሳፋሪዎችን ሁሉ ሳያስገርም አልቀረም... ጓደኛዬ 'ቀጥል እንጂ' እንደማለት በፊቱ አናገረኝ... በረጅሙ ተንፍሼ 'ቆይ ይሄ ብሔራዊ መዝሙር ይለቅ' አልኩት... ተረድቶኛል...


"... ባለጊዜው መጥቶ - ዋውዬ... ዛሬ ባለቀኑ
ተሸኝቷል ትናንት - ዋውዬ... ቀርቶ ሰቀቀኑ
ከርሞ ሲመጣበት - ዋውዬ... ዘንድሮም ይረሳል
እንዲህ ያልፋል እንጂ - ዋውዬ... ቀን መች ይመለሳል..."


አዎን አይመለስም!... እኔን ያመላልሳል እንጂ... ግን እርሷ ይህን ሙዚቃ ከኔ ጋር እያለች እንዲያ በስሜት የምታንጎራጉረው ለምን ነበር?...


በሃሳብ ከመንጎድ ያናጠበኝ ከፊትለፊታችን ቁጭ ብላ ወሬያችንን በትኩረት ትሰማ የነበረች ወጣት የስልክ ጥሪ ነበር...


"... ወደ ኋላ ሄደሽ - በሃሳብ ከማለም
ቀኑ እንዳይመሽብሽ - ትናንት ዛሬ አይደለም..."


በዚህ ዘመን ይህን ሙዚቃ ከመስማት አልፎ የስልኩ ጥሪ የሚያደርግ ወጣት መኖሩ እያስገረመኝ ከነባር ሃሳቤ ተፋታሁ... 


ወሬዋን ስትጨርስ ጠብቄ 'የስልክ ጥሪሽ ያምራል' አልኳት...


"ከአንተ ወሬ አይበልጥም" አለች ፍልቅልቅ እያለች... 


መውረጃችን ሲደርስ ጓደኛዬ ፈጠን ብሎ 'ሌላ ጊዜ ተመሳሳይ ወሬ ካስፈለገሽ በዚህ ቁጥር ደውይ' ብሎ ስልክ ቁጥሬን ሰጣት... የሆነ ሰው ጥንድ ሆኜ ማየት ምኞቱ ነው...

___

ዛሬ ረፋድ...

ስልኬ ለስለስ ብላ አንኳኳች... የእረፍት ቀን ነው ብዬ አልጋዬን ሙጥኝ እንዳልኩ ነበር... ስልኬን አነሳሁ፣ የማላውቀው ቁጥር ነበር...

"ሄሎ..." አልኩ... ከወዲያ በኩል ባለፈው ታክሲ ውስጥ ሆኜ የሰማሁት የስልክ ጥሪ ሙዚቃ ተቀበለኝ... ስለማንነቷ ማብራራት አላስፈለጋትም...

___

የትናንትን ሸክም ሳታራግፍ የዛሬን ሰላም ማጣጣም አትችልም፤ በትናንት ጽልመት የተመሰጡ ዓይኖች የዛሬን ውበት ማየት አይችሉም...

ወደ ነገ የሚጓዝ የትናንትን ጓዝ መጣል አለበት...

___

@bridgethoughts
10🥰1👌1
.
.
.

ከፊትለፊቴ ነው፣ ፍሬን የበጠሰ መኪና ድንገት የነጠቀው... ማንም ቦታው ላይ አልነበረም... ሮጬ ሄድኩ... ሆኖም በደም የጨቀየ ሰውነቱን ልነካ አልደፈርኩም... እጆቼ ተንቀጠቀጡብኝ... ደግሞስ ምን አደርግለታለሁ?... 


በሰከንዶች ውስጥ ዕልፍ ነገሮች ተለዋውጠዋል... 


ልብሶቹ አጥንት፣ ስጋና ደም ተላቁጠውበታል... ፊቱ እሳት ያገኘው ፕላስቲክ መስሏል... የሰውነት ክፍሎቹ ተሰባብረው ደቀዋል...


ዓይኖቹ ሊያወሩኝ እንደሚፈልጉ ነገሩኝ... መንቀሳቀስ አይችልም... ዝቅ አልኩ፣ አፉን የሞላው ደም ቱግ እንደሚል ጀበና እያስቸገረው አጉተመተመ... የምጥ ያህል በከበደ ትግል ውስጥ ሆኖ ደጋግሞ የነገረኝን ገጣጥሜ ልሰማው ሞከርኩ...


"ለልጄ እያየሁህ ነው በለው" ነበር ያለኝ...


ትንፋሹ ለመጀመሪያ ጊዜ ቀጥ አለች...


ይህን እንዲለኝ ነበር ነፍሱ የጠበቀችው?... 


የማላውቀውን ሰው መልዕክት ተሸክሜ የማላውቀው ልጁን በሕሊናዬ አመላለስኩ... በአካል ኑረት አብሮት ባይዘልቅ በመንፈስ ጎዳናው እጁን ይዞት እንዳለ እንዲሰማው ፈልጓል...


በዚህች የቅጽበት ዕድሜ፣ በአስደንጋጭ ክስተት ውስጥ፣ ምንም መሆን በማይችልበት ሁኔታ፣ 'ልጄ' የማለትን አቅምና ትውስታ እንዴት አገኘ?... ነፍሱ በምን ፍጥነት የስጋ ሞቱን ነገረችው?...


ውስጤ ብዙ ጥያቄዎች ተመላለሱ... ፈዝዤ ሳለሁ አካባቢው በጩኸት ተናጠ... እንደመንቃት አልኩ... ሰዎች ከበቡን... ልራመድ ስሞክር ግን እግሮቼ ጠፉብኝ... ደንዝዘው ነበር... 


"ለልጄ እያየሁህ ነው በለው"


ልረሳ በማልችለው ፊት፣ ሊረሳ በማይችል ቃል፣ ቀድሞ ዕውቂያ የሌለን ሰው በልቤ ሰሌዳ ላይ ላይጠፋ እንደተከተበ ገባኝ... 

____

[Re-ለአባቶች ቀን]

___

@bridgethoughts
❤‍🔥8👍3🙏21
.
.
.

የተናገራት ነገር ከንክኗታል... ደጋግማ ሰውነቷን ትመለከታለች... የሰውየው አስተያየት ምቾት አልሰጣትም... 


ከጓደኛዬ ጋር ካፌ ውስጥ ተቀምጠን ነበር... 


ከውጭ የተቀመጠ አንድ ደንበኛ ልጅቱን የሆነ ነገር ተናግሯት ስትረበሽ አየን... ቃል በቃል ከእርሱ አፍ ባንሰማም ከሰሞኑ በገጠማት ሚጢጢ ህመም ምክንያት ለአመል ያህል 'የቀነሰ' ሰውነቷ ላይ መዘባበቱ ግን ገብቶናል ...


ነገሩ ተፈጥሮአዊ ቢሆንም ሰውየው እንዲህ ሊረዳው የፈለገ አይመስልም... ጭራሽ በወጣች በገባች ቁጥር ሊያሳቅቃት ይሞክር ነበር...


[ህመሙ ከፈጠረባት ድካም በላይ የሰውየው ንግግር ሸክም ሲሆንባት ተሰማን...]


ልጅቱ እኮ በጣም ቆንጆ ናት!!


እርሱ ግን ይሄ አልታየውም... ወይም ደግሞ በእርሱ ቤት ጨዋታ ማሳመሩ ነው...


ልጅቱ እኮ እጅግ ትሁት ናት!!


እርሱ ግን ይሄ አልታየውም... ወይም ደግሞ ያዘነላት መስሎ አንጀት መብላቱ ነው...


ልጅቱ እኮ ዛሬም እንዳማረባት ነው!!


ሰውየው ግን ይህ ግድ አልሰጠውም... ወይም ደግሞ ለሰው ስሜት ፍጹም ደንታ ቢስ ነው...


እናም ማሳቀቅ ብቻ ነው የቻለበት...

___


Unfortunately ለሴት ልጅ የውበትና የማማር ጉዳይ 'አሳሳቢ' ርዕስ ነው... እንደ ወንድ ልጅ Careless ልትሆን የማትፈቅድበት ጉዳይዋ እንደሆነም ይታወቃል...


እናም...


'ዛሬ እንዴት እንዳማረብሽ!' ተብሎ ጨዋታ ይጀመራል... 'ትህትናሽ እኮ የትም አይገኝም' ተብሎ በውዳሴ ይለኮሳል... 'ልብሱን እኮ አሳመርሽው' ማለትም የአባት ነው...


ስለምን...


['ቁንጅና ታጥቦ ባይጠጣም' - ሰውን ስለ ገጹ ውበት አውስቶ ማጉላት ስለ ክሳቱ አውርቶ ከማድማት ይሻላልና]


[አልባስ ከከፈንነት ባይዘልም - ሰውን በልብሱ አመካኝቶ ማድነቅ ገላህ ሳሳ ብሎ ከማድቀቅ ይሻላልና]


ግና እርሱ...


"ከስተሻል" ነው ያላት... [በትክክል ያላትን እዚህ መድገም ነውር ሆኖብኝ ነው]


እናም እርሷ...


በጣም ደበራት!!... 


[ሕመሟን ተኝቶ ማዳመጥ ትታ ነው ስራ የገባችው... ከአልጋ ሰው መርጣ ነው በዚህ የተገኘችው... ግና ያልጠበቀችው ሆነና ከፋት...]

___

ነገሩ ተራ አጋጣሚ ሊመስል ይችላል... ስለተለመደም ትኩረት ባይስብ አይገርምም... [በዚህ እግረ መንገድ ግን ልምምዳችን መነቀፍ ይኖርበታል...]


ምን መሰለህ?...


ስንገናኝ ቀልባችን የሚወሰደው በተራ ነገሮቻችን የመሆኑ ጉዳይ የሚያስቆዝም ነው... በአላፊ ጠፊው ላይ እናተኩራለን... በከንቱ ጉዳዮቻችን ላይ እንመሰጣለን... ያልበላንን እናካለን... የሰውን ቅስም እንሰብራለን...


ግልጽ እኮ ነው... "ስጋ ባዳ ነው"... ይመጣል ይሄዳል... ስለወፈሩ ሙላት፣ ስለከሱም ጉድለት የለም... 


ሰው ያደረጉን ቁምነገሮቻችን ያሉት እኮ በማይታየው ነገራችን ውስጥ ነው... ደግነታችን፣ ቅንነታችን፣ ታማኝነታችን፣ ፍቅራችን ውስጥ... እኒህን ማየት አንችልም - መረዳት እንጂ...

___

[አየህ የልጅቱ ህመም ጊዜያዊ ነው... በድካም ስለተፈጠረ የሁለትና ሦስት ቀን ዕረፍት ከነመፈጠሩ ያጠፋዋል...]


የምላስ ወለምታ ግን እረፍት አይረታውም...


ስናሳጥረው...


ሰዎች ጉድለቴ የሚሉትን ነገር ማስታወስ ልክ አይደለም... 'በሰው ቁስል እንጨት የመስደድ' ቅሽምና ከሌለብህ በቀር...


ልትረዳው አልያም ልትቀይርለት በማትችለው ሁኔታ ውስጥ ያለን ሰው ብሶት ማባባስ በጎ አይደለም... በጥላቻ ካልታወርክ በቀር...


በቆዳህ ጥራት፣ በስጋህ ክብደት፣ በሃብትህ ብዛትም ሆነ በወንበርህ ክብደት መመካት ስህተት ነው... 'ሰከንዶች የሸሸጉትን አውቃለሁ' የማለት ድፍረት ካልሆነ በቀር...

___
 

ሁላችንም ሁሉን ነገር በተመሳሳይ መንገድ አንረዳም... የሸክም ልምዳችን ልዩ ልዩ ነው... አንዳንዶቻችን ስንጥር ያጎብጠናል፣ ሌሎቻችን ግንድ ይሰግድልናል...


እናም ይህን አስታውስ...


የቃል ክብሩ - ሳይቀል መነገሩ!!...

___

@bridgethoughts
10💊3👍1🔥1
“Think of Others”

__


As you prepare your breakfast — think of others.
Don’t forget to feed the pigeons.


As you conduct your wars — think of others.
Don’t forget those who want peace.


As you pay your water bill — think of others.
Think of those who have only the clouds to drink from.


As you go home, your own home — think of others — don’t forget those who live in tents.


As you sleep and count the stars, think of others — there are people who have no place to sleep.


As you liberate yourself with metaphors think of others — those who have lost their right to speak.


And as you think of distant others — think of yourself and say‘I wish I were a candle.

___

By: Mahmoud Darwish

___

[Mahmoud Darwish (1941–2008) was a Palestinian poet, essayist, and one of the most celebrated literary voices of the Arab world. He’s often called the poet of exile, the voice of Palestine, and a modern mystic of resistance and longing.]

___

@bridgethoughts
2🕊1
እዚህ መንደራችን ውስጥ @HiwotWog ቻናል ላይ አጫጭር ታሪኮች ስትከትብ የምታውቋት ደራሲት ሕይወት እምሻው:


'ነገ ከስራ በኋላ አብራችሁኝ ብትሆኑ:

ቡና ፉት እያላችሁ፣

ወግ እየጠረቃችሁ

ጮርናቄ እየገመጣችሁ

፭ መፃሕፍት ሸምታችሁ ትደሰታላችሁ' ብላችኋለች...

___

ቦታ - አራት ኪሎ [ኢክላስ ሕንፃ - ዋልያ መፃሕፍት መደብር]

ሰዓት - ማምሻ 11:00

የመግቢያ ዋጋ - ምንም አይጠየቁም፣ ይልቅ ለመገኘትዎ ዋጋ ይቀበላሉ።

___

https://t.me/HiwotWog
🥰5🔥21
.
.
.

Default setting
___

ከሃሳብ የሚያረጅ ስልተ-ምት አለ... ከቋንቋ የሚጠልቅ ጸጥታ አለ... በጎህ መቅደድ እርጋታ፣ በምትወድቅ ቅጠል ዥውታ፣ በሚመላለስ ትንፋሽ ፋታ፣ አንድ ስም የለሽ መሆንታ (being) አለ... ተፈጥሮአዊነት!!... ከስርዓቷ ጋር መዛነቅ፣ ከቅኝቷ ጋር መስማማት፣ ከአደራረጓ ጋር ስሙር መሆን...


የሆነ ጊዜ ከዚህ ተፈጥሮአዊ ቅንብር (setting) ጋር ያለ ድካም ሕብር እንፈጥር ነበር... ሰዓታት ከመተለማቸው በፊት፣ ጫጫታ ከመንገሱ በፊት፣ የሆነ ሰው ለመሆን ከመራወጣችን በፊት... ከኑረት ጡዘት፣ ከውድድር ቅኝት፣ ከፉክክር ውጥረታችን በፊት ከተፈጥሮ ስልተ-ምት ጋር ተጣጥሞሽ ነበረን...


ዛሬ ይሄ የለም... 


ራሳችንን ዕረፍት አልባ አድርገነዋል... መንፈሳችንን በታትነነዋል... ለነፍሳችን ዓለም ባዕድ ሆነናል... የፈጠርነው ስርዓት ከተፈጥሮ ዝማሜ ለይቶን ሳይበቃው ስጋችንን እያጎሳቆለ ነው... ግንኙነታችንን እያቀጨጨ ነው...


የምር... ነፍሳችን ታፍናለች...


የሆነ ዓይነት መደንዘዝ ውስጥ እንዳለን ብናውቅም ስህተት ነው ለማለት ወኔ አላገኘንም... አንዳች መርግ ቢጫነንም መጉበጣችንን መቀበል አንፈልግም... የተፈጥሮን ስልተ-ምት ንቀን የፈጠርናቸው ሁሉም ስርዓቶች መልሰው እየበሉን ነው... ሆኖም በስሪታቸው ጥመት ላይ ስላልተግባባን በፈጠሩብን መዓት ላይ የጋራ አቋም አልያዝንም...


በቤትህ፣ በሰፈርህ፣ በከተማህ፣ በሃገርህ፣ በዓለም ዙሪያና በምድሪቱ ሁሉ ምን እየሆነ እንዳለ ተመልከት... አዕምሮና ልብህ ይስማሙልሃል?... በምትሰማው ወሬ፣ በምታየው ተግባር፣ በምትኖረው ኑሮ ደስተኛ ነህ?...


በጭራሽ!... የአኗኗራችንን ሙሉ ጤነኛነት justify የሚያደርግ አንድም ምክንያት የለም... 


[የሆነ ነገራችንንማ አሞናል...]

___

እዚህች ጋ አንዳንድ ጉዳዮች እናንሳና የተፈጥሮን ቅኝት ዓለሚቱ function በምታደርግበት መነጽር እንመልከት...
__


@bridgethoughts
🔥43👍3
.
.
.

ፍጥነትን በምትሸልም ዓለም ውስጥ ነው የምንኖረው... እናም ሁሉም ነገር ይቸኩላል... ማሽኑ ይቸኩላል፣ እግረኛው ይቸኩላል፣ ንግግራችን ይቸኩላል፣ ማዕዳችን ይቸኩላል፣ ወዳጅነታችን ይቸኩላል፣ ጥላቻችን ይቸኩላል፣ ተግባራችን ይቸኩላል... የማይጣደፍ ነገር የለም...


እንቅስቃሴን ከለውጥ ሂደት ጋር እናምታታለን... ጫጫታን ከሃቂቃ ልክ እናዛንፋለን... ስክነትን ከጡዘት ጋር እናጋባለን... በንቃት ለመተንፈስ፣ ከልቡና ሆነን ለመስማት፣ ስሜታችንን ለማድመጥ በቂ ጊዜ የለንም... 


[ይህ ምን ወለደ?... ጤናህን፣ ግንኙነትህን፣ ስሜትህን - አጢንና ምላሹን ለራስህ ስጥ...]

__

የተፈጥሮን ያልተነካካ ስርዓት (default setting) በመኖር ውስጥ ተጨማሪ ነገር ግድ አይደለም... አበቦች እንዲያብቡ 'ማሽነሪ' አይፈልጉም... ምድር ዙረቷን እንድትጠብቅ 'ሶፍትዌር' አትሻም... ጨረቃና ከዋክብት ለመድመቅ 'ካላንደር' አይጠይቁም... ወንዞች እንዲፈሱ 'ቱቦ' አያስፈልጋቸውም...


[እኔና አንተ ንቁ ሆነን ለመቆየት እንኳ ስንት ነገር ነው የሚያስፈልገን?...]


"Nature is pleased with simplicity. And nature is no dummy." — Isaac Newton

__

የዓለም ስርዓት ግለኝነትን ያበረታል፤ ተፈጥሮአዊነት ግን በሕብር ብቻ ይገለጣል... በጫካ ውስጥ አንዱም ፍጡር የብቻ ዓለም የለውም... ዛፎች የሚተነፍሱትን እንስሳቱ ይስቡታል፣ የአራዊቱ ውጋጅ ምድርን ያለሰልሳል... በተፈጥሮ ውስጥ ቅርጹን የሚቀይር እንጂ የሚጠፋ ነገር የለም... 


ባልተረዳነው ጊዜ እንኳ የሚሰራ፣ ልንተማመንበት የሚገባ ታላቅ አስተውሎት ተፈጥሮ ውስጥ አለ... የኛን ቁጥጥር የማይፈልግ፣ ሁሉን በሰዓቱ የሚከውን፣ በፍጽምና የሚጓዝ አስደማሚ ጥበብ ተፈጥሮ ውስጥ አለ...


የምታዋጣው ክህሎት ሳይኖር የደም ዝውውርህ ይሳለጣል፣ ልብ በማትለው ጊዜም ቢሆን ትንፋሽህ ገብቶ ይወጣል፣ የሰውነትህ ክፍሎች (ልብህ፣ ኩላሊትህ፣ ጉበትህ...) ከአንተ ቁጥጥር ውጪ ሆነው መደበኛ ተግባራቸውን ይከውናሉ...


“Look deep into nature, and then you will understand everything better.” — Albert Einstein


ተፈጥሮ ውስጥ እያከማቹ መዝለቅ የለም፣ እየተው መሄድ እንጂ... ዛፎች ቅጠላቸውን ያረግፋሉ - በስብሰው ምድርን ያለማሉ፣ ፍሬያቸውን ይጥላሉ - ሌላ ዘር ይተካሉ፣ ብስሉን ይሰጣሉ - ረሃብ ይከላሉ... ደመና ይዘንባል፣ ከዋክብት ይወድቃሉ፣ ምድር ከፈኗን ትጥላለች...


[እኔና አንተስ?... ትርፋችንንም አንጋራም!... ይሄ ምን ወለደ?...]

___

ተፈጥሮ በውድድር ስርዓት እርስ በእርስ አትባላም - ሚዛን አኑራ ትጓዛለች እንጂ... መስመር አስምራ ድንበር ገፉብኝ አትልም - ልዩነት አጥፍታ ታጣምራለች እንጂ... 


ተፈጥሮአዊነት ኋላ-ቀርነት አይደለም፣ አሁንና እዚህ መገኘት ብቻ እንጂ... ስልጣኔዎቻችንን መናቅ አይደለም፣ ጌቶቻችን እንዲሆኑ አለመፍቀድ እንጂ... ኑረትን ማጣጣል አይደለም፣ አማናዊውን ማንነት አለመርሳት እንጂ... 


ነገሩ እኮ መመለስ ነው... ፊትን ወደ ቤት ማዞር!!... ወደ ጥንተ ማንነታችን መጓዝ...

____

አስተውለህ ካየህ...

በስልጣኔ ስም ኑረትን አወሳስበናታል... በውድድር ስም ዓለሚቱን ሲዖል አድርገናታል... ሃብት በማካበት ስም ንፍገትን አንብረናል... ምድሪቱ የገጠሙዋትን ፈተናዎች በሙሉ ብትመረምር የሰው ልጅ የተፈጥሮን ስርዓት ትቶ 'የኔ' የሚለውን ዘዬ በመከተሉ ምክንያት የገባበት ጭንቅ ጎልቶ ይታይሃል...


ጦርነት፣ ረሃብ፣ ስደት፣ እርዛት፣ አምባገነንነት፣ ጭካኔ፣ ጥላቻ... የሁሉም ምንጭ እኛው ነን... ችግሩ ያለው የፈጠርነው የዓለም ስርዓት ላይ እንጂ የተፈጥሮ 'ኢፍትሐዊነት' ላይ አይደለም...


ወደ ቤታችን እንመለስ... የተፈጥሮን default setting እንኑር...

___

ይህ ከዓለም ክፋት የመመነን ጥሪ አይደለም... በውስጧ ሆኖ የመንቃት ደወል እንጂ... ጨለምተኝነት፣ ኢ-ዘመናዊነት፣ አልያም የለውጥን ተፈጥሮአዊነት የመካድ ጉዳይ አይደለም... የእርጋታ፣ የመጠየቅ፣ ትንፋሽ የመውሰድ፣ የተማሩትን ትቶ ከተፈጥሮ ስልተ ምት ጋር የመጣማት ፍንጭ እንጂ...
 

[በግዳጅ ውስጥ የመኖር ጭቆና ሳይሆን በፍቃድ የመፍሰስ ሕልውና ነው... በፍርሃት የመጓዝ ድንብርብር ሳይሆን በነፃነት ከፍ የማለት ግብር ነው...]


ይህ የምልሰት ግብዣ ነው... አዲስ ነገር የመሆን ሳይሆን ወደ ቦታ የመመለስ ጥሪ... ስር የመትከል፣ መሬት የመርገጥ፣ የመስከን ደወል...

___

@bridgethoughts
7👍6💊4