ድልድይ | Dildiy | Bridge
1.45K subscribers
417 photos
87 videos
1 file
117 links
DILDIY

Whispers of the soul. Echoes of the universe.

Exploring consciousness, love, interconnectedness, and the mystery of existence through philosophy, mysticism & science.

Every thought is a bridge. Every question is a path. Every soul is connected.
Download Telegram
.
.
.

እንቅልፌ መዘረፉ ሲገባኝ ቁርስ ፍለጋ ወጣሁና አንድ ካፌ ውስጥ ተሰተርኩ... ወደ ቀልቤ ስመለስ የተከፈተው 'ሙዚቃ' ጆሮዬን ሲያግለው ተሰማኝ... እንኳን ለካፌ ለመሸታ ቤት አይመጥንም... ደግሞ እኮ ረፋድ ነው... [የሙዚቃ ምርጫ - ቦታ፣ ጊዜና ሁኔታ የሚተሳሰሩበት እውቀት መሆኑ ሊቀር ነው በቃ?...] የምንግዴ ዘመን...


እናንተዬ ሙዚቃዎቻችን ግን እንዲህ የጣዕም ምች የመታቸው ምን ሆነው ነው?... ከስንት አንድ እኮ ነው ጆሮ ገዝቶ ልባችሁን ለመድረስ የሚሞክረው?... [እባካችሁ የቆዩትን ስናወድስ 'ድሮን ናፋቂ' አትበሉን...]

___


ቁርሴን እንደነገሩ በልቼ ለአንድ ጉዳይ ወደ መገናኛ ለመሄድ ታክሲ ውስጥ ገባሁ... ሰው ወንበሮቹን ሞልቶ ሲተርፍ ጉዞ ጀመርን... መጣበባችን አነጫንጮን ሳንጨርስ ሹፌሩ ቴፑ ላይ ፍላሹን ሰካና በጩኸት ደበላለቀን... 


'ኧረ ቀንሰው...' ጥቂት ሰዎች ተቆጡ... ደስ ሳይለው ድምጹን ጢንጥዬ ዝቅ አደረገው... ተሳፋሪው ያልመረጠውን 'ጫጫታ' እየሰማ እየተጓዝን ነው... ሹፌሩ 'ጥሩ ሙዚቃዎችን አሳልፍ' የተባለ ይመስል ስርዓት ያላቸውን ዘፈኖች Next ይላቸዋል... በዚህ መሃል ፊቱ ካለ ሚኒባስ ጋ ተላትሞ ነበር...  [አረ ባክህ መሪህ ላይ አተኩር]... 


እንዲህ ሹፌርና ዲጄ ሆኖ እያደነቆረን ስንሄድ በመሃል አንዱ ተሳፋሪ ጥሪው የሚጮህ ስልኩን አንስቶ በሚጮህ ድምጽ ከወዲያኛው ሰው ጋር ማውራት ጀመረ... ደዋዩ ብቻ ሳይሆን ስልኩም አሳዘነችኝ... [ሁሌ እየጮኸባት ታዲያ ምጽ...]


በዚህ ተገርሜ ሳልጨርስ ከጎኔ ያለው ልጅ ስልኩን አውጥቶ የ Tiktok ምስሎችን እያየ ይፈግግ ጀመረ... በየመሃሉ አንድ ደስ የማይል የሳቅ ድምጽ የሁሉም ምስሎች አጃቢ ሆኖ ይሰማል... እንኳን ምስሉን ለማያይ ተሳፋሪ እያየ ላለውም የሚጨንቅ ድምጽ ነው... ስልችት አለኝ... [በጋርዮሽ ቦታዎች ላይ እንኳ የግላችንን ነገር ear phone ሰክተን እንስማ እንጂ ጎበዝ...]

___

ከታክሲው ወርጄ ለጉዳዬ ተፍ ተፍ ማለት ጀመርኩ... 


መገናኛን የሚያጨናንቃት የሰው ብዛት ብቻ የሚመስለው አይጠፋ ይሆናል... እውነቱን ለመናገር ግን መገናኛን እንዲያ ያስጨነቃት ጩኸትም ጭምር ነው... 


ሚኒባስ ላይ በተጠመደ Montarbo የሚስተጋባ የእርዱኝ ልመና ከእንጉርጉሮ ጋር፣ በዋሽንት ሙዚቃ የሚለምን የኔቢጤ፣ 'ኢየሱስን ተቀበሉ' የሚል ሰባኪ፣ የአይጥና የበረሮ ማጥፊያ ግዙን የሚሉ ብዙ ስፒከሮች፣ የረዳቶች ጥሪ፣ በየሰበቡ ክላክስ የሚያደርጉ ተሽከርካሪዎች [ወይኔ! የሃይገርና ሲኖ ጡሩምባ]... መገናኛን የሞላት በአጭሩ የተበከለ ድምጽ ነው... 


ቀኑ ያልተባረከለት ሰው ሆንኩኝ...

___


ከማበዴ በፊት ወደ ቤቴ ተመለስኩ... ምሳዬን እያበሰልኩ ሳለሁ ከቤቴ በላይ ያለው ቸርች ሞንታርቦውን ደቅኖ በሚያስገመግም ድምጽ 'አንድ ሁለት ሦስት - ቼክ ማይክ ቼክ...' ሲል ሰማሁት... ቀጥሎ የመጣውን መግለጽ ያዳግተኛል... ምድር ራሱ የጨነቃት ያህል ትርበደበድ ነበር... ኡኡኡ የሚል ኦርጋን ድምጽ፣ ስፒከር የሚተረትር ጩኸት፣ 'ሰይጣን' በመፈክር 'የሚያስለቅቅ' ሰባኪ... ለሰዓታት ሰፈሩ ቀውጢ ሆኖ ቆየ...


እንደገባኝ ጩኸት በኑሮአችን ውስጥ 'The new normal' ሆኗል... አንዳንዴ ድምጹ አንተን ብቻ ይሆናል የሚረብሸው... ሐይማኖታዊ ከሆነ አንዳች እርኩስ መንፈስ ስላለብህ እንዳልተመቸህ የሚነግርህ አታጣም... የሙዚቃው ስልት እንዳልተመቸህ ስትገልጽ 'ሙዚቃ ስለማታውቅ ነው' የሚልህ እንደማይጠፋው ሁሉ...


[ሐይማኖተኞች እንኳ ስክነት እንዴት ይጠፋቸዋል?... 'መንፈሳዊ ነን' ይሉ አይደል?... ጩኸት ከመንፈሳዊነት ጋር ምን የጋራ አካፋይ አለው?... ታዲያ የት ሄደን እንረጋጋ ጎበዝ?...]

___


ማምሻም ሆነ...


Walk ለማድረግ ወጣሁ... 'ጸጥታ ሲያምርህ ይቅር' ተብዬም አይደል?... የአምቡላንስ ሳይረን፣ የሰርግ መኪኖች ክላክስ፣ እግርኳስ የሚታይባቸው ቤቶች ስፒከር ጩኸት፣ ከየንግድ ቤቱ የሚለቀቅ ኳኳቴያም ሙዚቃ - እየተቀባበሉ ተንጫጩብኝ...


ሁሉም አገልግሎት ሰጪ በጩኸት ነው የሚጠራህ... ካልጮኸ የምትሰማው አይመስለውም... ለነገሩ እኛም ለምዶብን ዝም ሲል 'ምነው ጭር አለ?' እንላለን...


[Ear phone ጆሮዬ ላይ ሰካሁ... ከውጭው ጩኸት ወደ ውስጤ ዝምታ እመለስ እንደሁ ብዬ...] 

___


ወደ ማታ - ጉዞ ወደ ቤቴ...


ያ የለሊቱ ድምጽ ማጉያ፣ ተረኛውን መርሃግብር ለማይመለከታቸው ሰዎች ለማጉላት እያሟሟቀ ነበር... 

___

ወዳጆቼ፣ ፀጥታ በአልበም መልክ የሚሸጥበት ን ቦታ ታውቁ ይሆን?...

___

@bridgethoughts
👍54👌4🥰1🙏1
ቀንህ ተለዋዋጭ በሆነ የስሜት ነውጥ ውስጥ ያልፋል... ገጽህ ለገጠመህ ነገር ሁሉ መስታወት ሆኖ ይከሰታል... ሰው ነህና ለስሜት ምላሽ እስከሰጠህ ድረስ በአንድ ቀን ጥልቅ ህመምና ጥልቅ ደስታ፣ ብዙ ሳቅና ብዙ እንባ ሊገጥምህ ይችላል...


ተፈጥሮአዊ ነው!!...


[ቀጥሎ የሚሆነውን ልታውቅ አትችልም፤ የሆነውን ትቆጣጠራለህ እንጂ...]


ችግሩ ግን...


🌻 በተበሳጨህ ጊዜ ያገኙህ ሰዎች ደግነትህን ሳያውቋት ሊያሙህ ይችላሉ፤

🌻 በደስታህ ጊዜ ያወቁህ ደግሞ ልትናደድ እንደምትችል ይረሳሉ፤



እውነቱን ለመናገር...

[ሰዎች በፈለጉህ ጊዜ እንድትሆንላቸው ለሚፈልጉት ነገር እንጂ አንተ ዘንድ ላለው የስሜት ለውጥ ቦታ የላቸውም!!]

____

@bridgethoughts
🥰11👍2👌2
.
.
.

ምንም ነገር በራሱ መጥፎ አይደለም - ዕይታ ግን ያጠለሸዋል... ያለ ምክንያት የሆነ አንዳች የለም - የዕውቀት ማነስ ግን ያሳንሰዋል... ሁሉም ለስምረት የተገለጠ ነው... 


[ያልገባን እንጂ ትርጉም የሌለው ነገር የለም...]


ይጠቅማል ብለን ስናስብ እንጠቀመዋለን... አይረባንም ስንል እንተወዋለን... ነገሩን መጠቀማችን አዋቂ እንደማያስብለን ሁሉ መተዋችንም ጥቅም አልባ አያደርገውም...


ሁሉንም ነገር ሁልጊዜ አንረዳም... ስላልገባን የተውነው እንጂ ሳይፈይድ የተፈጠረ አልታየም... ስለነበረ ያወቅነው እንጂ ሲገባን መኖር የጀመረ የለም...


ሳንዘጋጅ የጎበኘን እውቀት አልባሌ ይመስላል... ያልገባንን መናቅ ማወቅን ይተካል... [ግርምቢጥ]


በኑረት ውስጥ ተራራ ያለውን ፋይዳ ማንም አያስበውም... የጥንብ አንሳ መኖር ልብ ባይ የለውም... የዱር እንሳሳ ህላዌ ለመንገደኛ ሩቅ ነው... የትንኝ መራባት ለአልፎ ሂያጅ ትርፍ ነው...


ግና... በተሳሳረ ዓለም ውስጥ የአንዱ መኖር ለሌላው፣ የዚያኛው ኑረት ለዚህኛው መሰረታዊ ነው... ተፈጥሮ ትርፍ ነገር የላትም...


የነገሮችን መንታነት ብቻ በማየት ስለተጠመድን እንጂ የአንዱ መኖር የታወቀው በሌላኛው ጥምረት ነው... ብርሃን የደመቀው ከጨለማ እንቅብ ነው...


በጥልቀት እስክንረዳው ድረስ በጎ ወይም መጥፎ የሚባል ነገር የለም... በጎን እንድናውቅ 'መጥፎው' - መጥፎን እንድንለይ በጎው እየጠቀመ በማይነጣጠል መንታነቱ ይቀጥላል...

___


ይልቅ መጥፎነት የተሳሳተ ቅልቃሎት ውጤት ይመስለኛል፤ ነገሮችን ከተፈጥሮአዊ ቅኝታቸው ውጭ የማዳቀል ስህተት... 


በተናጥል አንዳች እንከን የሌላቸው ነገሮች እንበለ ጥበብ አልያም በክፋት ሃሳብ ሲጣመሩ መጥፎነት ይወልዳሉ... 


ለምሳሌ...


ለየብቻ ተሰርተው ስትበላቸው የሚጣፍጡህ ምግቦች ተዳቅለው ሲቀርቡልህ ቃናቸውን አትወድ ይሆናል፤ ይህ ግን የምግቦቹን ጥሩ አለመሆን አያመለክትም... ከመቀላቀላቸው በፊት በተናጥል ቀምሰህ ወደሃቸው ነበርና... 


[ማርና ቅቤን አዳቅለህ፣ ወተትና ጠላ ደባልቀህ፣ በሶና በርበሬ አላቁጠህ፣ ስኳርና ጨውን ፈጭተህ... ማሰብ ትችላለህ]

___

ይሄ ግን ስለ ምግብ አይደለም...

___

[ዕለታቶችህን የሞላው ፈተና የቱ ነው?...]

___


ተቀላቃዮቹን ሳታወግዝ ቅልቅሉን ፈትሽ... [ስሙር ነው?...]

___

@bridgethoughts
11🙏2👌2💊1
ለጥንቃቄ...
___

የማይጠየቁ ጥያቄዎች...

__

1. ሰላማዊ እንቅልፍ ተኝተህ ስምህን አስር ጊዜ ጠርቶ ቀስቅሶህ ልክ ስትነቃ "ውይ! ተኝተሀል እንዴ?" የሚል ሰው አያበግንህም? ባልተኛ ነው የቀሰቀስከኝ ታድያ?...
___

2. "የማትፈልገው እንትን አለህ?" (ሲጀመር የማልፈልገው ነገር አይኖረኝም! ከኖረኝ በኋላ እንደማልፈልገው ካወቅሁም እስካሁን እጥለው ነበር)
___

3. ሻወር ቤት ገብተህ አንዱ ያንኳኳና "Friend ጨርሰሻል?" ይልሃል... (ከጨረስኩ ምን እሰራለሁ?)
___

4. በር ሳንኳኳ ከውስጥ "ማነው?" እያለ ሊከፍት የሚመጣ ሰው ይገርመኛል! ሌባ ብሆን "ሌባ ነኝ!" እንድለው ነው? መክፈቱ ካልቀረ ማንስ ብሆን ምን ይጠቅመዋል? "መጣሁ!" ማለት አይሻልም?...
___

5. "አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ?" ብለህ አትጠይቅ! 'አንድ' ካልክ እኮ በቃ "አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ?" ስትል ጥያቄህን ጨረስክ...
___

6. ቂቅ ብለህ ዘንጠህ መጥተህ "አምሮብኛል አይደል?" ብለህ ከነ መልሱ አትጠይቀኝ... "አምሮብኛል?" የሚለው ጥያቄ ብቻ ይበቃል አይደልን ከጨመርክ እኮ ሼም ይዞኝ "አዎ" እንድል እያስገደድከኝ ነው... ወይም ደግሞ እንዳማረብህ አውቀሀል ማለት ነው... ታዲያ ለምን ታደርቀኛለህ?...
___

7. እርቦኝ፣ ጠምቶኝ፣ ደክሞኝ ልክ ቤት ስገባ 'መጣህ?' አትበሉኝ.. እንግዲህ እኔ እስከማውቀው ድረስ ስለመጣሁ ነው የታየኋችሁ! ይልቅ የሚበላ የሚጠጣውን አቅርባችሁ ፈውሱኝ...
___

8."ሰዓት ስንት ነው?" ስልህ "አሁን?" አትበለኝ... ታዲያ መቼ ሊሆን ይችላል? ወይስ አቆጣጠሩን ስለማታውቅበት ጊዜ ለመፍጀት ነው?
___

9. 'Password'ህን ንገረኝ? አይባልም... ከነገርኩህማ ምኑን password ሆነው ታዲያ?
___

10. 'ምን ልጋብዝህ?' አይባልም... ግብዣ በጋባዥ እንጂ በተጋባዥ ውሳኔ አይካሄድም... ሼም ይዞኝ የወረደ ነገር እንዳዝ ፈልገህ ካልሆነ በስተቀር!
___

11. ለቅሶ ቤት ሄደህ የአሟሟቱን detail አትጠይቅ! ማስተዛዘን እኮ ሃዘን ማረሳሳት እንጂ ማባባስ አይደለም...
___

[ይህ ጽሑፍ የድልድይ አይደለም፤ ቆየት ባለ ጊዜ ከፌስቡክ ገጽ የተወሰደ ነው...]
___

@bridgethoughts
👍87👏5🆒1
ሞባይሉን ጆሮው ላይ ደቅኖ ከስልኩ ወዲያ ጫፍ ያለውን የድምጽ ምንጭ ይቀዳል... 


ስልክ ያልያዘበት እጁ እንደ ጉድ እየደነሰ ነው... ጥርሶቹ አፉ ጠቧቸው ከከንፈሩ ጋር ትግል ገብተዋል... ዓይኖቹ ፍትት ብለው ይስቃሉ... የፊቱ ፍካት አንድ ከተማ ያበራል...


ዓይኖቼን ከእርሱ መንቀል አልቻልኩም... ልጁ የሆነ የሚጋባ መንፈስ አለው...


የሁኔታውን ሰበዝ በስልኩ ሞገድ በኩል ዘርግቼ ከወዲያ ጫፍ ያለውን የደስታ ምንጭ ማንነት ለመገመት ሞከርኩ...


መጠራጠር አልፈለግሁም... 


እንዲህ ወደ እንቦቃቅላ ዘመን መልሶ ለማፍነከነክ ከእርስዋ ውጪ ማን ተጠያቂ ሊሆን ይችላል?...


እኛም አንድ ሰሞን እንዲህ አድርጎን ነበራ...

___

@bridgethoughts
4🤗4🥰3👍1🔥1
.
.
.

የሻይ ቡና ቆይታችን ሲጠናቀቅ የነበረኝ ግምት ወደ ቤቷ እንደምሸኛት ነበር...

ያ ግን አልሆነም...

"እኔ 'ምልህ፣ ባለፈው የሩሚን መጽሐፍ ሰጥሻለሁ ብለኸኝ ነበር አይደል?" አለችኝ...

"አዎን"

"ዛሬ እፈልገዋለሁ፣ ልትሰጠኝ ትችላለህ?"...

"እንዴታ... እሰጥሻለሁ እንጂ... ግን አሁን..." የሞባይሌን ሰዓት አየሁት... ከምሽቱ 12:30...

"አሁን ምን?" እንደመከፋት አለች...

"መሽቷል ብዬ ነው... ቤቴ ሩቅ አይደል፣ ስንመለስ ይመሽብሻል"... ቀበጣጠርኩ... ጥያቄዋ ድንገት ትንፋሽ ያሳጣኝ መሰለኝ...

"ግድየለም አንድ ታክሲ አይደል?... እንደርሳለን፣ ደግሞም ብዙ አልመሸም"... 

[ጉድ ፈላ!!... ምን አስባ ነው?...]

"ለምን ነገ አላመጣልሽም ማር"... ፊቷን በጥንቃቄ አጠናሁት...

"አይሆንም ዛሬ ነው የምፈልገው!" ፈርጠም አለች... 

በአንድ ጊዜ ፍርሃትና ጭንቀት ቅኝ ግዛታቸው አደረጉኝ... የእርሷን በጣሪያዬ ስር መገኘት እንደ ልዩ ስጦታ የምቆጥረው ነገር ቢሆንም ቤት እንሂድ ስላለችኝ ብቻ ፈንጥዤ እንሂድ የማልልበት ምክንያት ነበረኝ... 

ውዝግብ ውስጥ እንደገባሁ ሲገባት "ምነው ችግር አለ?" አለችኝ...

"ኧረ ምንም ችግር የለም... ብቻ..."

"ብቻ ምን?... ቤትህ መምጣቴ አያስደስትህም?" ኮስተር ብላ ነበር...

"እንዴት እንደዚያ ታስቢያለሽ?... ያውም አንቺ ፈልገሽ?... በጣም ነው እንጂ የሚያስደስተኝ..." 

[ለምንድነው ግን እንዲህ የምታስጨንቀኝ?...]

"የደበቅሃት አለች እንዴ?" ብላ በዓይኗ ሳይቀር ጠየቀችኝ...

"ማሂ!" ጮህኩባት... "ምንድነው የምታወሪው?"... 

አብሮ ያለመሄድ ፍላጎት ባሳየሁዋት ቁጥር እንዲህ ዓይነት ግምት እንዳትይዝ ስፈራ ነበር...

___

ሃሳቧን ማስቀየር ስላልቻልኩ ታክሲ ይዘን ወደ ሰፈሬ አመራን... የተኮራረፍን ይመስል አንዳች አልተነፈስንም... ታክሲው ቀስ እንዲል የጀመርኩት ጸሎት ከማረጉ በፊት መንገዱ አለቀ...

"ወራጅ አለ" አልኩ... ረዳቱ ታክሲውን ደብድቦ አስቆመው... ወረድን... ጭንቀቴ ግን እኔን ታክሲ አድርጎ ጉዞውን ቀጥሏል...

እየመራሁ የኪራይ ቤቴ አደረስኳት... እንደተዘጋጋን... ሆኖም በሩን ለመክፈት አቅም አጣሁ... [እጄ እንደ መንቀጥቀጥ አለብኝ]

"እኔ ልክፈትልህ እንዴ?" አሾፈችብኝ...

ወደ ውስጥ ገባን...

'ያንተ ያለህ!'... የፈራሁት ይህን ነበር...

ቤታችንን ውስጥ ሌላ ሰው ሲገኝ ብቻ የሚፈጠር ትርምስ አለ ልበል?... በአዘቦቱ ምንም የማይረብሸኝ ቤት ፍቅረኛዬን ይዤበት ስገባ አህያ የወለደበት መስሎ ጠበቀኝ...

[ሳይታጠቡ አንድ ስርቻ ውስጥ የታጎሩ፣ ቢወረወሩ ግንባር ለመፈንከት አቅም የማያጡ ካልሲዎች... ባዶ የወተትና እርጎ ማሸጊያ ፕላስቲኮች፣ መወልወያ የናፈቀው ወለል፣ ከአልጋ እስከ ምንጣፍ የተዘረጋ የልብስ ኤግዚቢሽን... የፌስታል መዓት... የሻማ ቁራጭ፣ የክብሪት እንጨት፣ ብዙ የሃይላንድ ዕቃ፣ በአቧራ የተሸፈነ የመጽሐፍ መደርደሪያ፣ ድር የጎበኘው ግርግዳ... የታፈነ አየር... ምኑ ቅጡ...]

'እንዴት እስከዛሬ አላስተዋልኩትም?'

ትዝ ሲለኝ ቁጭ በይ እንኳ አላልኳትም... የቤቴን ሁኔታ በዓይኖቿ ስታበጥር ነበር... አንድ ወንበር ስቤ በሶፍት ለማጽዳት ስሞክር "ተወው ተወው አልቀመጥም፣ ይልቅ ሸኘኝ..." አለችኝ... በጣም ደነገጥሁ...

"እንዴ፣ ማሂ! በቃ?... ለዚህ ነው የመጣሽው?" ግራ ተጋባሁ... 

"የምፈልገውን አግኝቻለሁ፣ ይልቅ መሽቷል እንሂድ" ፊቷን አዙራ ወደ በሩ አመራች... መጽሐፉን እንኳ አልጠየቀችኝም...

"ማሂዬ፣ ይቅርታ፣ ቤቴ ደብሮሽ ነው አይደል? በእናትሽ አትቀየሚኝ፣ ቤቴ ሰው ይመጣል ብዬ ስላላሰብኩ ነው ቸል ያልኩት፣ ላስተካክለው እችላለሁ..." መረጋጋት ተቸገርኩ...

"የመጣሁት መጽሐፍ ፈልጌ አይደለም፣ ሰው አይመጣበትም የምትለውን ቤትህን እንዴት እንደምትይዘው ማየት ፈልጌ እንጂ..."

"አልገባኝም..." ብስጭት ውስጥ እየገባሁ ነበር...

"አየህ... አንተ ማለት 'ማንም አያየኝም' ስትል የምታደርገውን ነህ... መምጣቴን አውቀህ ብትሰተር በእኔ ፊት ለማስመሰል እንጂ የሆንከውን ለመኖር ነው ልል አልችልም ነበር... ድንገት መምጣት ያስፈለገኝ ለዚህ ነው..."

ዝም አልኩ... ጸጥ ረጭ!!... ቤቴም ተባበረችኝ... ውጪውም አገዘኝ... በዚህ ሁኔታ ዝም ያልኩበትን ሁኔታ በጭራሽ አላስታውስም... እፍረት ጨመደደኝ...

"እንሂድ?" አለችኝ ደግማ፣ ደረጃውን እየወረደች...

ልሸኛት ወጣሁ... ታክሲ ተራ እስክንደርስ ምንም አላወራንም...

"ሁለት ሰው?" አለ ረዳቱ እንዳየን...

"አንድ ብቻ!..." ፈጥና መለሰችና ነጠለችኝ... ለነገሩ ታክሲውም ያለው የአንድ ሰው ቦታ ነበር...

ከመግባቷ በፊት እንደተለመደው አቅፋ እንድታሰናብተኝ፣ እንደምወደው አንገቷን እንድስማት ጓጉቼ ነበር...

አልሆነም...

ቻው እንኳ ሳትለኝ ዘው ብላ ገባች... 

ታክሲው ይዟት ተፈተለከ... ባለሁበት ደርቄ ቀረሁ... 

___

አንድ ፈተና ብቻ ሰጥታኝ ከ 100 አረመችው... እርሱንም ወደቅሁ...


"ሰዎች ለእኔ ያላቸውን ፍቅር የምመዝነው ለራሳቸው ባላቸው ክብር ውስጥ ነው" ብላኝ ነበር...

___

@bridgethoughts
👏107🥰3🔥1🥴1
.
.
.

ቅድሚያ የሰጠኸው ሰው - ከፊትህ አክብሮትን ሳይሆን ፍርሃትን ካነበበ፣

አደራ የሰጠኸው ሰው - የልብህን ማመን ሳይሆን የድርጊትህን ሞኝነት ካሰበ፣

ሙሉ ጊዜህን የሰጠኸው ሰው - ፍቅርህ ሳይሆን ስራፈትነትህ ከተሰማው፣

ገንዘብህን የሰጠኸው ሰው - ችሮታህን ረስቶ መጠኑ አንሶ ከታየው፣

የረሳህለት ሰው - ይቅር እንዳልከው ሳይሆን እንዳልተሰማህ ካመነ፣

ያገለገልከው ሰው - እርዳታህን ትቶ ግዴታህን ብቻ ካሰበ፣

ከበላይህ ያለ ሰው - የሃሳብህን ፋይዳ ከቆምክበት መደብ ካለካካ፣

የእጅህን ንጽህና የሚያውቅ - ዕድል ስላላገኘህ እንጂ መስረቅ ስላልፈለክ አይደለም ብሎ ካሰበ፣

ቆርሰህ ያካፈልከው - የሰጠኸውን ሳይሆን ከእጅህ የቀረውን ካስተዋለ፣

ግማሽ መንገድ የሄድክለት - ከጠበቀህ በቆመበት፣

ለወፌ ቆመች ተለጉሞ - ይድፋህ ለማለት ካደረ ቆሞ፣

እንዲለወጥ እጅ ያላቀበለ - ለትችት ከተቀባበለ፣

ባወቅሁሽ ናቅሁሽ ያንተን ጡብ ንቆ - የሩቅ መናኛ ካየህ አድንቆ፣

.
.
.

ወዳጄ ችግር አለ... 
___

@bridgethoughts
👍108🙏2👌2🥰1
.
.
.

ነገሩን እንዴት መሰለህ የማየው...


የሆነ ሰው አለ አይደል - ደጋግመህ የምታልፍበት መንገድ ላይ የሚቀመጥ... እናም ባየህ ቁጥር "ይሄ ልጅ ሁልጊዜ በዚህ በኩል ሲያልፍ አየዋለሁ" እያለ የሚገረም... የአንተን በዚያ መመላለስ ያወቀው እኮ እርሱም ሁልጊዜ በዚያ የሚቀመጥ ስለሆነ ነው...


ወይም ደግሞ...


"ምን ያፈጥብኛል?" የምትል እንስት ማፍጠጥህን ሳታይህ በምን አወቀች?... በምንም ልታውቅ አትችልም... [ስለዚህ ጉዳዩ ላይ ተባብራለች...]


ነገሩ 'አንተ በሌለህበት መስታወቱ ምን ያንጸባርቃል?' የሚል እሳቤን ይፈጥራል... መስታወቱ ፊት ከሌለህ መስታወቱ 'የመሰወተውን' ልታውቅ አትችልም ማለት ነው... (የመሰወተው ይባላል እንዴ?...)


ነገሩን ወደ ኑረት እንጎትተው...


የሆነ ብሽቅ ሰው ሰደበህ ወይም 'ስምህን አጠፋ' እንበል... [ስምህን በእርሳስ አትፃፍ ብዬህ አልነበር?...ሃሃሃ]... ራስህን ለመከላከል አልያም 'የክብር' ነገር ሆኖብህ ምላሽ ለመስጠት ወሰንክ...


ዌል፣ ምላሽህን መስታወቱ ፊት እንደመቆም አድርገህ ብታስበው ግጭት የመፈጠር ዕድሉ ሰፊ ነው... ነገሩን አልሰማኸው ወይም ትተኸው ቢሆንስ ኖሮ?... በቃ ሰላም!!...


ሃበሻ ድንቅ ብሂል አለችው... 'መተው ነገሬን ከተተው' የምትል... [በዕለታዊ እንቅስቃሴዬ ሁሉ ምርኩዝ የምትሆነኝ mystical ቃል ናት... እርሷን የረሳሁ ዕለት ነው suffer የማደርገው... የምስራቁን ዓለም ትምህርት በሙሉ በአንድ አቢሲኒያዊ ዘዬ ጠቅልል ብባል 'መተው - ነገሬን ከተተው' ነው የምለው'... እንዴት ዓይነት libration መሰለህ - መተው!!!...]


ምንም ነገር የሚኖረው ስንኖር ነው... [ነገሩን በደንብ አስበው የምር... አሁን በዙሪያህ ያለው ነገር ያላንተ ምንድነው?... ስለኖርክ ብቻ ያለ አይመስልህም?... ይገባኛል 'ባልኖርም መኖሩን አላስቀርም' የሚል ሃሳብ እንደፈተነህ... የረሳኸውን ግን ላስታውስህ... 'መኖር' የኖረው 'ኖረህ' ስላየኸው ነው...] አንድ ጊዜ በመኖር 'ያወቅነውን' ነገር እንደሌለ መቀበል ይቸግረናል...


[እዚህች ጋ ትንሽ ተፈላሰፍ... የምታየውን ነገር አንድ ሚሊየን ሰው እያየው ቢሆን እንኳ ያንተን perspective የሚመስል ላይኖር ይችላል... ወይም ደግሞ ወጋየሁ 'ፍቅር እስከ መቃብርን' እየተረከ የሚሰሙት እልፍ ሰዎች - እልፍ ሰብለወንጌልን ነው በምናባቸው የሚስሉት... (ምናብ ለዘላለም ይኑር!... እነ ETV መጥተው 'ሰብለ ይህች ናት' ሲሉህ ግን የምናብህን ሰብለን እየሰረቁህ እንደሆነ አትርሳ... የጋሽ ሐዲስን መጽሐፍ ስታነብ መቼና የቱን የምትስለው፣ ሰውና መልክዓ-ምድሩን የምትኩለው አንተ ነህ... 'ኢቲቢ' ስታይ ግን የዳይሬክተሩ ሰብለ ናት የምትሰጥህ... ምናብህን ከሚበሉ መስኮቶች ራቅ ወዳጄ)... ይህችን 'ወሽመጥ ሃሳብ' ለጊዜው ዝጋትና ያቺ ሁሉ የምናብ ሰብለ የኖረችው በማን መኖር ነው ብለህ ጠይቅ...]


ምን መሰለህ?... 'በሚቀጥሉት ፭ ሰከንዶች ውስጥ ስለ ዝሆን አታስብ' ብልህ በእርግጠኝነት ከዝሆን ውጭ ማሰብ አትችልም... ጥያቄው ግን - 'ስለ ዝሆን ምንም ዕውቀት ባይኖርህስ?' የሚል ነው... ስለምን ታስባለህ?... አስቀድሞ እውቀቱ በሌለህ ነገር ላይ ብዙም አትቸገርም...


ነገሩን መረር እናድርገው እንግዲህ...


በሰዎች አንዳች ተግባር ስትፈርድ ውስጥህ ያለው ተመሳሳይ የጥፋት ስሜት አጋዥ ሆኖ ይቆማል... ምን ማለቴ መሰለህ?... ሰዎችን የምትኮንንበት ጥፋት በሙሉ አንተም ውስጥ አለ... 


ሩሚ እንዲህ ይላል... “The fault you see in your brother is really in you.” 


አየህ - 'ከደሙ ንጹህ ነኝ' ዓይነት እጅ ልቅለቃ ብዙ አያዋጣም... ብዙዎቻችን ሌሎች ዓይን ውስጥ ያለ ብናኝ እንከን ሳይቀር ማየት የማያስችለን ምሰሶ ዓይናችን ውስጥ ተጋድሟል... 


የ Lao Tzu ቃል ለዚህ ፈውስ ነው... “Knowing others is intelligence. Knowing yourself is wisdom.”

___

ምን እያልኩ ነበር?... [እንጃ... ጠፋብኝ...]

___

[ይህችን ሃሳብ የሰኞ ዋዜማ 'ተብሰልስሎት' በላት... የተጀመረም ያለቀም ነገር የላትም... ሃሳብ ከጫረች በቃት! - ዓላማዋን አሳክታለች...]

___

@bridgethoughts
12🔥4🙏3👌1
.
.
.

በሰዎች አዕምሮ ውስጥ መንጎዳጎድ ደስ ይለኛል... በተለየ ሁኔታ ቀልቤን የሚስብ ሰው ሳገኝ 'ምን እያሰበ ይሆን?' ማለት አዘወትራለሁ...

___

'ወክ' እያደረግሁ ነው...


አሁን ለምሳሌ ይሄ ከፊቴ እያለፈ ያለው ሰውዬ ከሰው ጋር እያወራ እንዳለ ሁሉ እጁን እንዲህ የሚያወናጭፈው ምን እያሰበ ነው?... ተመልካች ጉድ እስኪለው፣ ለራሱ እንኳ እስኪገርመው 'ለብቻው' ሚያወጋው ምን ገጥሞት ነው?... ጎጆው ስንት ቀዳዳ ቢከፍትበት - ወገንስ ምን ያህል ቢከፋበት ይሆን?...

የተዋት ሚስቱ ናት የተወችው ኑረት እንዲህ 'ምታወራጨው?... የአለቃው ንግግር ብስጭት ነው፣ የበደለው ጎረቤቱ ቁጭት አቅሉን ያቀጨጨው?... 

ከቶ ራሱን እንዳይቆጣጠር ያደረገው ምንድነው?... ልማድ ወይስ ጉድለት?... ህመም ወይስ ጭንቀት?...

___


ከባሻገር...

እኒያን ጥንዶች እንዲህ ያወሻሸቃቸው ምንድነው?... የፍቅር ቀለበት ወይስ የስሜት ዘለበት?... የዕድሜ ልክ ፈፋ ወይስ የወራት አረፋ?...

እንግዳ ደራሽ ቢጠይቅ ምንና ምን ነን ይላሉ?... መውደድ ያቆራኘን ጥንዶች ወይስ መንገድ ያገናኘን ቧልቶች?...

እርሷ ዓይኖቹን ስታይ የምታስበው ምንድነው?... እርሱ ጉንጯን ሲስም የሚያልመው መቼን ነው?... የጋራ ነገ አላቸው?... እርሷ በነፍሱ ዘንድ ቦታዋ ምንድነው?... እርሱ በእቅፏ ውስጥ ጥጋቱ ወዴት ናት?... በሕይወቱ ውስጥ ሹፌር ናት ተሳፋሪ?... ለዕለታቶቿ አባሪ ነው ኗሪ?... 

___


ያ የጎዳና ተዳዳሪ ልጅ ምንድነው የሚያስበው?... ይህን ቤንዚን ሲስብ ምንድነው 'ሚሰማው?... ብርድ ይረሳበታል ወይስ ሆድ ይሸነግልበታል?... ቀኑን ያሳልፍበታል ወይስ ራሱ ያልፍበታል?... 


በአባት የታቀፈ ልጅ ከአጠገቡ ሲያልፍ ምን ይሰማዋል?... በእናት ስስት የተጌጠ ህፃን ምን ያስታውሰዋል?... 

___

እኒያ ከበተስኪያን ደጅ የቆሙ እናት ምን እየለመኑ ይሆን?... ከሚጨናበሱ ዓይኖቻቸው፣ ማድያት ካጠቆረው ፊታቸው ዘንድ ተስፋ ምንድን ናት?... 


ፈንጠር ብላ የምታነባዋ ወጣት ሴት መሻቷ ምን ይሆን?... ከገረገራው ያቆማት፣ ዓይኗን በእንባ ያጠባት ምን ሊሆን ይችላል?... 


ጉንጯን እየሰረሰረ የሚወርደውን የእንባ ጎርፍ የትኛው ሃዘኗ ፈጠረው?... የሚንሰቀሰቅ ሰውነቷንስ በደል ማን ጨክኖ ወለደው?... የባሌን ልብ መልስልኝ ይሆን የምትለው?... ይህን ፈተና ከኔ አርቀው ይሆን የምትለው?... መውጫውን አሳየኝ ይሆን 'ምትለው?... ምንድነው የሆነችው?...

___


ያቺ ስልክ እንጨት ተደግፋ የቆመች ሴተኛ አዳሪ ስለ ለሊቷ ምን እያሰበች ይሆን?... ዛሬስ 'ሚተኛት ምን ዓይነቱ ነው?... ጨካኝ ነው አዛኝ?... ማጋጭ ነው ባካኝ?... በልቧ የሚመላለሰው ጸሎት ምን ይሆን?... 'ከማላውቀው ሰው የማይታወቅ ዓመል፣ ከሚያውቀኝ ሰው የወሬ ደለል - ከልለኝ' ይሆን የምትል?...


ባለትዳሮች ምን ምን ይሏታል?... 'ሚንቃት ስታይ ምኗን ያንቃታል?...

___
.
.
.

እርሱ ምን እያሰበ ይሆን?...
.
.
.

እርሷስ ምን እያሰበች ይሆን?...

___

ከሰው ልጅ የአረማመዱ ቅኝት፣ ከአዋዋል ከአነጋገሩ ስምረት፣ ከኑሮ ከጎጆ ታዛው፣ ከልብሱ ከከፈን ደብዛው - ባሻገር...

ብዙ ተረክ ብዙ ታሪክ አለ... 
ብዙ ሃዘን ብዙ ስብራት አለ...
ብዙ ቁስል ብዙ ህመም አለ...
በሆድ ይፍጀው የታዘለ...


አሁን አንቺ ምን እያሰብሽ ነው?...

___

@bridgethoughts
12🤔31🙏1
.
.
.

አንዳንዴ ግን አስባታለሁ...


ወዳጅነታችን መራራቅ ያደበዘዘው፣ የሌላነትም ያጠየመው ነው... እንዲያም ሆኖ ግን አስባታለሁ... የጋራ ነገ እንደሌለን እርግጠኛ ሆኜም ሁሌ አስታውሳታለሁ...


ከግዙፍ የመርሳት አባዜዬ የተፋቱ ሽርፍራፊ ትዝታዎቿ ድንገት ፊቴ ይደቀናሉ...


አስባታለሁ...


አብራኝ እንደማትሆን እያወቀች ትዝታዎቿን እኔ ዘንድ የተወችበትን ብልሃት ብበሳጭበትም አስታውሳታለሁ...


ሄዶ ላለመረሳት፣ 'ርቆ ላለመፋቅ በአዕምሮዬ የሞጀረቻችው መቆሳቁሶች ብዙ ናቸው!...


ባለፈው ወር...


እዚያ የምታውቁት ካፌ ውስጥ ቁርስ ለመብላት ተቀምጬ እያለ አንዲት መለሎ ሴት ስትገባ አየሁ... ስትር ያለው ቁመናዋ እያባበለኝ በፈራ ተባ መሽኮርመም ውስጥ ሆኜ እያየሁዋት ቆየሁ... ከአጠገቤ አለፈች... አንገቴን ወደኋላ ማዞር ፈልጌ ነበር... እፍረት ጨምድዶኝ ተውኩት... 


የሽቶዋ መዓዛ ግን 'ማለፍ ክልክል ነው' እንዳሉት ሁሉ አፍንጫዬ ላይ ተሰንቅሮ ቀረ... እናም አልፋ እንዳላለፈች ገባኝ...


'ይህን ሽቶ የት ነበር የማውቀው?'... 


አዎን - መሲ ጋ ነው... በተመረጡ የመገናኛ ቀኖቻችን ሁሉ ይህን ሽቱ ነበር ነስነስ አድርጋ የምትመጣው... ተንኮሏ ግን... ምናል አንድ ዓይነት ሽቱ ብቻ ባትቀባ?... [እንዳልረሳት አይደል?...] አፍንጫዬስ ምን ቢሆን ነው ይህን ሽቱ ነጥሎ ማጥፋት ያቃተው?...


ባለፈው ሳምንት...


ከጓደኛዬ ጋር በታክሲ እየሄድን ወግ እንጠርቃለን... ተመስጬ እያወራሁ ሳለ ከወደ ሬዲዮው የተወነጨፈው ዜማ ቀልቤን ወሰደው...


'አንድ ሰው'... የፍቅረአዲስ እንጉርጉሮ... የሆነ ዓይነት ኃይል ስቱዲዮ ተቀምጦ፣ በ remote control ልሳኔን የዘጋው መሰለኝ... መሲ ይህን ሙዚቃ በጣም ትወደው ነበር...


"... አሃሃሃ አንድ ሰው - አሃሃሃ በየጨዋታው ላይ
አሃሃሃ አንድ ሰው - ባይመጣ ትዝታ
አሃሃሃ አንድ ሰው - አሃሃሃ እቃኘው ነበረ
አሃሃሃ አንድ ሰው - ባቲን ለደስታ..."


የወሬዬ በድንገት መቆም ከፊት ያሉ ተሳፋሪዎችን ሁሉ ሳያስገርም አልቀረም... ጓደኛዬ 'ቀጥል እንጂ' እንደማለት በፊቱ አናገረኝ... በረጅሙ ተንፍሼ 'ቆይ ይሄ ብሔራዊ መዝሙር ይለቅ' አልኩት... ተረድቶኛል...


"... ባለጊዜው መጥቶ - ዋውዬ... ዛሬ ባለቀኑ
ተሸኝቷል ትናንት - ዋውዬ... ቀርቶ ሰቀቀኑ
ከርሞ ሲመጣበት - ዋውዬ... ዘንድሮም ይረሳል
እንዲህ ያልፋል እንጂ - ዋውዬ... ቀን መች ይመለሳል..."


አዎን አይመለስም!... እኔን ያመላልሳል እንጂ... ግን እርሷ ይህን ሙዚቃ ከኔ ጋር እያለች እንዲያ በስሜት የምታንጎራጉረው ለምን ነበር?...


በሃሳብ ከመንጎድ ያናጠበኝ ከፊትለፊታችን ቁጭ ብላ ወሬያችንን በትኩረት ትሰማ የነበረች ወጣት የስልክ ጥሪ ነበር...


"... ወደ ኋላ ሄደሽ - በሃሳብ ከማለም
ቀኑ እንዳይመሽብሽ - ትናንት ዛሬ አይደለም..."


በዚህ ዘመን ይህን ሙዚቃ ከመስማት አልፎ የስልኩ ጥሪ የሚያደርግ ወጣት መኖሩ እያስገረመኝ ከነባር ሃሳቤ ተፋታሁ... 


ወሬዋን ስትጨርስ ጠብቄ 'የስልክ ጥሪሽ ያምራል' አልኳት...


"ከአንተ ወሬ አይበልጥም" አለች ፍልቅልቅ እያለች... 


መውረጃችን ሲደርስ ጓደኛዬ ፈጠን ብሎ 'ሌላ ጊዜ ተመሳሳይ ወሬ ካስፈለገሽ በዚህ ቁጥር ደውይ' ብሎ ስልክ ቁጥሬን ሰጣት... የሆነ ሰው ጥንድ ሆኜ ማየት ምኞቱ ነው...

___

ዛሬ ረፋድ...

ስልኬ ለስለስ ብላ አንኳኳች... የእረፍት ቀን ነው ብዬ አልጋዬን ሙጥኝ እንዳልኩ ነበር... ስልኬን አነሳሁ፣ የማላውቀው ቁጥር ነበር...

"ሄሎ..." አልኩ... ከወዲያ በኩል ባለፈው ታክሲ ውስጥ ሆኜ የሰማሁት የስልክ ጥሪ ሙዚቃ ተቀበለኝ... ስለማንነቷ ማብራራት አላስፈለጋትም...

___

የትናንትን ሸክም ሳታራግፍ የዛሬን ሰላም ማጣጣም አትችልም፤ በትናንት ጽልመት የተመሰጡ ዓይኖች የዛሬን ውበት ማየት አይችሉም...

ወደ ነገ የሚጓዝ የትናንትን ጓዝ መጣል አለበት...

___

@bridgethoughts
10🥰1👌1
.
.
.

ከፊትለፊቴ ነው፣ ፍሬን የበጠሰ መኪና ድንገት የነጠቀው... ማንም ቦታው ላይ አልነበረም... ሮጬ ሄድኩ... ሆኖም በደም የጨቀየ ሰውነቱን ልነካ አልደፈርኩም... እጆቼ ተንቀጠቀጡብኝ... ደግሞስ ምን አደርግለታለሁ?... 


በሰከንዶች ውስጥ ዕልፍ ነገሮች ተለዋውጠዋል... 


ልብሶቹ አጥንት፣ ስጋና ደም ተላቁጠውበታል... ፊቱ እሳት ያገኘው ፕላስቲክ መስሏል... የሰውነት ክፍሎቹ ተሰባብረው ደቀዋል...


ዓይኖቹ ሊያወሩኝ እንደሚፈልጉ ነገሩኝ... መንቀሳቀስ አይችልም... ዝቅ አልኩ፣ አፉን የሞላው ደም ቱግ እንደሚል ጀበና እያስቸገረው አጉተመተመ... የምጥ ያህል በከበደ ትግል ውስጥ ሆኖ ደጋግሞ የነገረኝን ገጣጥሜ ልሰማው ሞከርኩ...


"ለልጄ እያየሁህ ነው በለው" ነበር ያለኝ...


ትንፋሹ ለመጀመሪያ ጊዜ ቀጥ አለች...


ይህን እንዲለኝ ነበር ነፍሱ የጠበቀችው?... 


የማላውቀውን ሰው መልዕክት ተሸክሜ የማላውቀው ልጁን በሕሊናዬ አመላለስኩ... በአካል ኑረት አብሮት ባይዘልቅ በመንፈስ ጎዳናው እጁን ይዞት እንዳለ እንዲሰማው ፈልጓል...


በዚህች የቅጽበት ዕድሜ፣ በአስደንጋጭ ክስተት ውስጥ፣ ምንም መሆን በማይችልበት ሁኔታ፣ 'ልጄ' የማለትን አቅምና ትውስታ እንዴት አገኘ?... ነፍሱ በምን ፍጥነት የስጋ ሞቱን ነገረችው?...


ውስጤ ብዙ ጥያቄዎች ተመላለሱ... ፈዝዤ ሳለሁ አካባቢው በጩኸት ተናጠ... እንደመንቃት አልኩ... ሰዎች ከበቡን... ልራመድ ስሞክር ግን እግሮቼ ጠፉብኝ... ደንዝዘው ነበር... 


"ለልጄ እያየሁህ ነው በለው"


ልረሳ በማልችለው ፊት፣ ሊረሳ በማይችል ቃል፣ ቀድሞ ዕውቂያ የሌለን ሰው በልቤ ሰሌዳ ላይ ላይጠፋ እንደተከተበ ገባኝ... 

____

[Re-ለአባቶች ቀን]

___

@bridgethoughts
❤‍🔥8👍3🙏21
.
.
.

የተናገራት ነገር ከንክኗታል... ደጋግማ ሰውነቷን ትመለከታለች... የሰውየው አስተያየት ምቾት አልሰጣትም... 


ከጓደኛዬ ጋር ካፌ ውስጥ ተቀምጠን ነበር... 


ከውጭ የተቀመጠ አንድ ደንበኛ ልጅቱን የሆነ ነገር ተናግሯት ስትረበሽ አየን... ቃል በቃል ከእርሱ አፍ ባንሰማም ከሰሞኑ በገጠማት ሚጢጢ ህመም ምክንያት ለአመል ያህል 'የቀነሰ' ሰውነቷ ላይ መዘባበቱ ግን ገብቶናል ...


ነገሩ ተፈጥሮአዊ ቢሆንም ሰውየው እንዲህ ሊረዳው የፈለገ አይመስልም... ጭራሽ በወጣች በገባች ቁጥር ሊያሳቅቃት ይሞክር ነበር...


[ህመሙ ከፈጠረባት ድካም በላይ የሰውየው ንግግር ሸክም ሲሆንባት ተሰማን...]


ልጅቱ እኮ በጣም ቆንጆ ናት!!


እርሱ ግን ይሄ አልታየውም... ወይም ደግሞ በእርሱ ቤት ጨዋታ ማሳመሩ ነው...


ልጅቱ እኮ እጅግ ትሁት ናት!!


እርሱ ግን ይሄ አልታየውም... ወይም ደግሞ ያዘነላት መስሎ አንጀት መብላቱ ነው...


ልጅቱ እኮ ዛሬም እንዳማረባት ነው!!


ሰውየው ግን ይህ ግድ አልሰጠውም... ወይም ደግሞ ለሰው ስሜት ፍጹም ደንታ ቢስ ነው...


እናም ማሳቀቅ ብቻ ነው የቻለበት...

___


Unfortunately ለሴት ልጅ የውበትና የማማር ጉዳይ 'አሳሳቢ' ርዕስ ነው... እንደ ወንድ ልጅ Careless ልትሆን የማትፈቅድበት ጉዳይዋ እንደሆነም ይታወቃል...


እናም...


'ዛሬ እንዴት እንዳማረብሽ!' ተብሎ ጨዋታ ይጀመራል... 'ትህትናሽ እኮ የትም አይገኝም' ተብሎ በውዳሴ ይለኮሳል... 'ልብሱን እኮ አሳመርሽው' ማለትም የአባት ነው...


ስለምን...


['ቁንጅና ታጥቦ ባይጠጣም' - ሰውን ስለ ገጹ ውበት አውስቶ ማጉላት ስለ ክሳቱ አውርቶ ከማድማት ይሻላልና]


[አልባስ ከከፈንነት ባይዘልም - ሰውን በልብሱ አመካኝቶ ማድነቅ ገላህ ሳሳ ብሎ ከማድቀቅ ይሻላልና]


ግና እርሱ...


"ከስተሻል" ነው ያላት... [በትክክል ያላትን እዚህ መድገም ነውር ሆኖብኝ ነው]


እናም እርሷ...


በጣም ደበራት!!... 


[ሕመሟን ተኝቶ ማዳመጥ ትታ ነው ስራ የገባችው... ከአልጋ ሰው መርጣ ነው በዚህ የተገኘችው... ግና ያልጠበቀችው ሆነና ከፋት...]

___

ነገሩ ተራ አጋጣሚ ሊመስል ይችላል... ስለተለመደም ትኩረት ባይስብ አይገርምም... [በዚህ እግረ መንገድ ግን ልምምዳችን መነቀፍ ይኖርበታል...]


ምን መሰለህ?...


ስንገናኝ ቀልባችን የሚወሰደው በተራ ነገሮቻችን የመሆኑ ጉዳይ የሚያስቆዝም ነው... በአላፊ ጠፊው ላይ እናተኩራለን... በከንቱ ጉዳዮቻችን ላይ እንመሰጣለን... ያልበላንን እናካለን... የሰውን ቅስም እንሰብራለን...


ግልጽ እኮ ነው... "ስጋ ባዳ ነው"... ይመጣል ይሄዳል... ስለወፈሩ ሙላት፣ ስለከሱም ጉድለት የለም... 


ሰው ያደረጉን ቁምነገሮቻችን ያሉት እኮ በማይታየው ነገራችን ውስጥ ነው... ደግነታችን፣ ቅንነታችን፣ ታማኝነታችን፣ ፍቅራችን ውስጥ... እኒህን ማየት አንችልም - መረዳት እንጂ...

___

[አየህ የልጅቱ ህመም ጊዜያዊ ነው... በድካም ስለተፈጠረ የሁለትና ሦስት ቀን ዕረፍት ከነመፈጠሩ ያጠፋዋል...]


የምላስ ወለምታ ግን እረፍት አይረታውም...


ስናሳጥረው...


ሰዎች ጉድለቴ የሚሉትን ነገር ማስታወስ ልክ አይደለም... 'በሰው ቁስል እንጨት የመስደድ' ቅሽምና ከሌለብህ በቀር...


ልትረዳው አልያም ልትቀይርለት በማትችለው ሁኔታ ውስጥ ያለን ሰው ብሶት ማባባስ በጎ አይደለም... በጥላቻ ካልታወርክ በቀር...


በቆዳህ ጥራት፣ በስጋህ ክብደት፣ በሃብትህ ብዛትም ሆነ በወንበርህ ክብደት መመካት ስህተት ነው... 'ሰከንዶች የሸሸጉትን አውቃለሁ' የማለት ድፍረት ካልሆነ በቀር...

___
 

ሁላችንም ሁሉን ነገር በተመሳሳይ መንገድ አንረዳም... የሸክም ልምዳችን ልዩ ልዩ ነው... አንዳንዶቻችን ስንጥር ያጎብጠናል፣ ሌሎቻችን ግንድ ይሰግድልናል...


እናም ይህን አስታውስ...


የቃል ክብሩ - ሳይቀል መነገሩ!!...

___

@bridgethoughts
10💊3👍1🔥1