ዐውደ ምሕረት
3.72K subscribers
924 photos
24 videos
271 files
177 links
"ቤተ ክርስቲያን ባሕረ ጥበባት
አትመረመርም እጅግ ጥልቅ ናት"
Download Telegram
ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ዘመናቱን በአራቱ ወንጌላውያን ከፍላ ዓመቱን ደግሞ በአራቱ ወቅቶች ሰድራ ወቅቱን ተንተርሳ ለልጆቿ ለአምሯቸው በተመቸ ልባቸውን በማረከ መልኩ ቃለ ወንጌልን ትመግባቸዋለች።

ዛሬ ግን በሰው ልጆች ሕይወት ውስጥ ብዙ ግዜ ስለማይስተዋሉ ተጨማሪ ሁለት ዘመኑችን እንመለከታለን ዘመነ ሳውል እና ዘመነ ጳውሎስን።

#የዘመነ_ሳውል መገለጫዎች

*ጭፍን ጥላቻ
*መደብደብ
*ማስደብደብ
*መግደል
*ማስገደል መንግሥት ሥልጣንን በመጠቀም የግድያ ደብዳቤ በክርስቲያኖች ላይ ማጻፍ
*ሰው ስለ እምነቱ እና ስለ አመለካከቱ ማሳደድ ማፈናቀል ንብረቱን ማውደም

“ሳውል ግን ቤተ ክርስቲያንን ያፈርስ ነበር፤ ወደ ሁሉም ቤት እየገባ ወንዶችንም ሴቶችንም እየጐተተ ወደ ወኅኒ አሳልፎ ይሰጥ ነበር።”
#ሐዋ 8፥3

ሳውል ግን የጌታን ደቀ መዛሙርት እንዲገድላቸው ገና እየዛተ ወደ ሊቀ ካህናት ሄደ፥ በዚህ መንገድ ያሉትንም ሰዎች ወንዶችንም ሴቶችንም ቢያገኝ፥ እያሰረ ወደ ኢየሩሳሌም ያመጣቸው ዘንድ በደማስቆ ላሉት ምኵራቦች ደብዳቤ ከእርሱ ለመነ። ሲሄድም ወደ ደማስቆ በቀረበ ጊዜ ድንገት በእርሱ ዙሪያ ከሰማይ ብርሃን አንጸባረቀ፤ በምድርም ላይ ወድቆ ሳለ፦ ሳውል ሳውል፥ ስለ ምን ታሳድደኛለህ? የሚለውን ድምፅ ሰማ። ጌታ ሆይ፥ ማን ነህ? አለው። እርሱም፦ አንተ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ፤ የመውጊያውን ብረት ብትቃወም ለአንተ ይብስብሃል አለው። #ሐዋ 9÷15
#የዘመነ_ጳውሎስ መገለጫዎች

*መደብደብ
*መሰደድ
*መታሰር
*መታረድ

" እንደ እብድ ሰው እላለሁ፤ እኔ እበልጣለሁ፤ በድካም አብዝቼ፥ በመገረፍ አብዝቼ፥ በመታሰር አትርፌ፥ በመሞት ብዙ ጊዜ ሆንሁ። አይሁድ አንድ ሲጎድል አርባ ግርፋት አምስት ጊዜ ገረፉኝ። ሦስት ጊዜ በበትር ተመታሁ፤ አንድ ጊዜ በድንጋይ ተወገርሁ፤ መርከቤ ሦስት ጊዜ ተሰበረ፤ ሌሊትና ቀን በባሕር ውስጥ ኖርሁ።
#2ኛ_ቆሮ 11÷23-25


እንባቢ ሆይ ዘመንህ የማነው? የሳውል ወይስ የጳውሎስ ዘመን?

አ.አ ኢትዮጵያ
ተክለ ኤል ኃ/ማርያም
ሐምሌ ፮ ቀን /፳ ፻ ፲ ፫ /ዓ.ም
" #ዘር_ያልተዘራብሽ_እርሻ_አንቺ_ነሽ "
___________________________
ሶሪያዊው #ቅዱስ_ኤፍሬም
#ውዳሴ_ማርያም ዘሰሉስ

_በድጋሚ ለአንባቢያን የቀረበ______

በሥነ ፍጥረት ትምህርት በእጅ የሚለቀሙ በማጭድ የሚታጨዱ በምሳር የሚቆረጡ
በሥራቸው ፣በግንዳቸው፣ በቅርንጫፋቸው የሚያፈሩ ልዮ ልዮ አትክርት ፣አዝርዕት
በጠቅላላው የእጽዋት ዘሮች የተፈጠሩት በዕለተ ማክሰኞ ነው:: በግዕዙ ዕለተ ሰሉስ
ይለዋል በልማዱ ማክሰኞ በትክክለኛው አጠራር ግን ማግስተ ሰኞ ነው የሚባለው የሰኞ
ማግስ ማለቱ ነው::
የሰሉስ ወይም የማግስተ ሰኞ (የማክሰኞ) ዕለት ፍጡራን ከላይ የተዘረዘሩት የእጽዋት
ዘሮች ሲሆኑ ነገር ግን ለመገኘታቸው ምክንያት የሚሆናቸው የዘራቸው ያጠጣቸው
ያበቀላቸው ገበሬ አልነበረም ። አስገኚያቸው ፈጣሪያቸው ልዑል እግዚአብሔር ብቻ ነው
በዚህም የማክሰኞ ዕለት እርሻ ከሌሎቹ አርሻና የእርሻ ምርቶች ለየት ይላል ። ከማክሰኞ
ዕለት እርሻ በቀር ዘር ሳይዘራበት ገበሬ ሳይተክልበት አድጎ ለምልሞ የታየ የእርሻ ዓይነት
የለምና ። እግዚአብሔር አምላክ ሥነ ፍጥረቱን በሦስት መንገድ ፈጥሯል ይህውም በሐልዮ
ወይም (በማሰብ) ሁለተኛ በነቢብ ወይም (በመናገር) ሦስተኛ በገቢር ወይም (በተግባር
፣በሥራ ፣በመሥራት) ነው። ታድያ የዕለተ ማክሰኞ ፍጥረታት በነቢብ የተፈጠሩ ፍጥረታት
ናቸው ። እግዚአብሔርም፦ ምድር ዘርን የሚሰጥ ሣርንና ቡቃያን በምድርም ላይ እንደ
ወገኑ ዘሩ ያለበትን ፍሬን የሚያፈራ ዛፍን ታብቅል አለ፤ እንዲሁም ሆነ ። ምድርም ዘርን
የሚሰጥ ሣርንና ቡቃያን እንደ ወገኑ ዘሩም ያለበትን ፍሬን የሚያፈራ ዛፍን እንደ ወገኑ
አበቀለች። እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ። ዘፍ 1÷11-12
ይህች የዕለተ ማክሰኞ እርሻ የመጀመሪያይቱ ምድርም እየተባለችም ትጠራለች ። ገበሬ
ሳይተክላት ዝናብ ለዘር ጠል ለመከር ሳታገኝ በመብቀሏ ቅድመ ምድር የመጀመሪያይቱ
ምድር ተባለች :: የሚገርመው በዚህ ወቅት የብርሃናት ምንጮች ፀሐይ ጨረቃና ከዋክብት
ገና አልተፈጠሩም ነበር ዝናብም በምድር ላይ ዘንቦ አያውቅም ነበር። ፀሐይ ጨረቃና
ከዋክብት የተፈጠሩት በዕለተ ዕረቡ ነው ስለዚህ በመጀመሪያይቱ ምድር ለማክሰኞ እርሻ
መገኘት አስተዋጽዖ አላደረጉም ያለ ውኃ ያለ ፀሐይ በቅለው ለምልመው ተገኙ እንጂ።
አቡሹ ሳይንስ እጽዋት ያለ ውኃ እና ያለ ፀሐይ መብቀል እንደሚችሉ ገና አልደረሰበትም
ምን አልባት ወደፊት ድሆ ድሆ ሲደርስበት እንደ ለመደው አዲስ ግኝት ብሎ በየ ሚዲያው
ሠላማችንን መንሳቱ እና ከሃይማኖት ዕውቀት በላይ ነኝ በማለት ቤተ ክርስቲያንን
መጨቆኑና ኃላ ቀር አድርጎ መቁጠሩ አይቀርም ። ቤተ ክርስቲያን ግን ባሕረ ጥበባት ነች
አትመረመርም:: ያለ ውኃ አብቅላ ያለ ፀሐይም አብስላ ልጆቾን ከርሃበ ሥጋ ከርሃበ ነፍስ
ታሳርፋቸዋለች ለምሳሌ ቢሉ ቃለ እግዚአብሔሯ አንዱና ዋናው ማሳያ ነው ማለት
እንችላለን ። ቃለ እግዚአብሔር ያለ ዝናብ እና ያለ ፀሐይ የሚያለመልም የሥጋም የነፍስም
ምግብ ነው “እርሱም መልሶ፦ ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ
ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአል አለው።” ማቴ 4፥4
በምሥጢር "ጥንተ ምድር " ወይም ይህች የመጀመሪያይቱ ምድር (የማክሰኞ እርሻ)
የምትባል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ነች:: በዚህም እመቤታችን ጥንተ ምድር
የማክሰኖ እርሻ ተብላ ትጠራለች። ጥንተ ምድር ያለ ዘር ያለ ገበሬ ያለ ዝናብ ያለ ፀሐይ
በግብረ መንፈስ ቅዱስ (በመንፈስ ቅዱስ ሥራ) ለምልማ አፍርታ እንደተገኘች እመቤታችን
ቅድስት ድንግል ማርያምም ገበሬ የሚባል ወንድ ዘር የሚባል ዘርኃ ብዕሲ ሳይጎበኛት
እንዲሁ በግብረ መንፈስ ቅዱስ (በመንፈስ ቅዱስ ሥራ ) ፀንሳ አብባ ተገኝታለች ። ይህ
ምሥጢር በእውነት ድንቅ ነው መላከ እግዚአብሔር ለእራሷ ለድንግል ማርያም ፀጋን
የተመላሽ ሆይ ደስ ይበልሽ የልዑል ኃይል ይጋርድሻል መንፈስ ቅዱስም ይጸልልብሻል
ትጸንሻለሽ ወንድ ልጅንም ትወልጃለሽ ሲላት እንዴት ይህ ይሆናል ሴት ያለ ወንድ ምድር ያለ
ዘር ልታፈራ ይቻላታልን አለችሁ ? መላኩም ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም ጥንተ
ምድርን ያለዘር ሳራን ያለ ሙቀት ልምላሜ ዘመድሽ ኤልሳቤጥን በስተ እርጅናዋ ያጸነሰ
አንቺንም ያለ ወንድ ዘር ማጸነስ አይሳነውም አላት ያን ጊዜ እውነት ነው ለእግዚአብሔር
የሚሳነው ነገር የለም "ይኩነኒ በከመ ትቤለነ " አለችሁ በዚሁ ቅጽበትም ወልድ ኢየሱስ
ክርስቶስ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ በማህጸኟ ተቀረጸ። ቅዱስ ጳውሎስም ይህ ያለ
ዘር የመጽነስን ምሥጢር ይህ ምሥጢር ያለ ጥርጥር ድንቅ ነው ሲል ግሩም አርጎ
ገልጦታል::“እግዚአብሔርንም የመምሰል ምሥጢር ያለ ጥርጥር ታላቅ ነው፤ በሥጋ
የተገለጠ፥ በመንፈስ የጸደቀ፥ ለመላእክት የታየ፥ በአሕዛብ የተሰበከ፥ በዓለም የታመነ፥
በክብር ያረገ።” ሲል 1ኛ ጢሞቴዎስ 3፥16 ። ሶርያዊው ሊቅ ቅዱስ ኤፍሬም በማክሰኞ
ዕለት ውዳሴው የማክሰኞን እርሻ የምትባል መቤታችንን "ዘር ያልተዘራብሽ እርሻ አንቺ ነሽ "
ብሎ በግሩም አመስግኘቀታል እርሻ እርሻ ለመባል ዘር ሊዘራበት ያስፈልገዋል እመቤታችን
ግን ዘር ያልተዘራባት ግን አፍርታ የተገኘች እርሻ ነችና ዘር ልተዘራብሽ እርሻ አንቺ ነሽ አላት
ያለ መታረስ ማፍራት ያለ ሰስኖተ ድንግልና መጸነስ ድንግል ሲሆኑ እናት እናትም ሲሆኑ
ድንግል የመሆን ፀጋ ከሰው ልጆች መካከል ከድንግል በስተቀር ለመን ተሰጠ? ለማንም።
ሆ ድንግል ሆይ አንቲ መንክረ መንክራት።
ቅዱስ ዳዊት “ምድር ፍሬዋን ሰጠችእግዚአብሔር አምላካችንም ይባርከናል”(መዝ.66፥6)
ተብሎ እግዚአብሔር የሚመሰገንበት ሳምንት ነው፡፡ ፍሬውም ከቁር ከበረዶና ከትል ተርፎ
ለጎተራ እንዲበቃ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በጸሎተ ቅዳሴዋ “በእንተ ፍሬ ምድር ናስተበቊእ
ከመ እግዚአብሔር ይሁብ ፍሬሃ ለምድር፣ ለዘርና ለመከር ሊሆን እግዚአብሔር ለምድር
ፍሬዋን ይሰጣት ዘንድ ስለምድር ፍሬ እንማልዳለን” በማለት አምላኳን ትማጸናለች፡፡
ልጇቿ ምእመናንም “ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት እንዳይሆን ጸልዩ” (ማቴ.
24፥20) ሲል መድኃኔዓለም እንዳስተመረው የሃይማኖት ፍሬ ምግባርን፣ ቱሩፋትን ሳይሠሩ
በልምላሜ (በሃይማኖት) ብቻ ሳሉ እንዳይጠሩ ለንስሐ ለሥጋ ወደሙ እንዲበቁ
በማስተማር ነገረ ምጽአቱን በማዘከር “ድልዋኒክሙ ንበሩ፣ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ ” በማለት
ታስተምራለች፡፡ ስለዚህ ይህ ክፍለ ክረምት የዕለተ ምጽአት ምሳሌ ነው፡፡ ወቅቱ የአዝመራ
ወቅት ነው፡፡ ፍሬ መለያ እንደሆነ ሁሉ የሰው ሥጋ ከተቀበረና ትቢያ ከሆነ በኋላ ተነስቶ
በዕለተ ምጽአት በጽድቅና በኃጢአት ይለያልና፡፡(ማቴ.25፥32)
“በመንገድም አጠገብ በለስ አይቶ ወደ እርስዋ መጣ፤ ከቅጠልም ብቻ በቀር ምንም
አላገኘባትምና፦ ለዘላለሙ ፍሬ አይገኝብሽ አላት። በለሲቱም ያንጊዜውን ደረቀች።”
ማቴዎስ 21፥19 ሰው በሃይማኖቱ ቀጥተኛ እውነተኛ ከሆነ አይፈረድበትም በምግባሩ ግን
ይኮነናል ሃይማኖት ቅጠል ምግባር ፍሬ ነች:: “ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደ ሆነ እንዲሁ
ደግሞ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው።” ያዕቆብ 2፥26 “አሁንስ ምሳር በዛፎች ሥር
ተቀምጦአል፤ እንግዲህ መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቈረጣል ወደ እሳትም
ይጣላል።” ማቴዎስ 3፥10
ቅዱስ ጳውሎስም ክርስቲያኖች በሃይማኖት ሲኖሩ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬን እንዲያፈሩ
ምግባራትን እንዲያደርጉ " የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ቸርነት፥
በጎነት፥ እምነት፥ የውሃት፥ ራስን መግዛት ነው። እንደዚህ ያሉትን የሚከለክል ሕግ የለም።
ሲል ማፍራት ብቻ ሳይሆን ምን ዓይነት ፍሬም ማፍራት እንደሚገባ ዘርዝሮ ነግሮናል
ገላ5÷22 አስቀድሞ በኢሳይያስ ነቢይ ላይም አድሮ " እሺ ብትሉ ለእኔም ብትታዘዙ
የምድርን በረከት ትበላላችሁ እንቢ ብትሉ ብታምጹ ግን ሰይፍ ይበላችዋል " ብሎ እሺ
ብለን ታዘን የምድርን በረከት እንድንበላ አስቦናል ኢሳ 1÷19 ወላዲ መጥቅ ዮሐንስም
በምስክርነቱ “መንሹም በእጁ ነው፥ አውድማውንም ፈጽሞ ያጠራል፥ ስንዴውንም
በጎተራው ይከታል፥ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል።” ማቴዎስ 3፥12
ወላዲተ አምላክ እመቤታችን ዋግ እንዳልመታው ውርጭም እንዳላገኘው ስንዴ እኛንም ንጽሕ ስንዴ አድርጋ ጎተራ በተባለች መንግሥተ ሰማያት እንድንገባ የማክሰኞ እርሻ የእመቤታችን በረከት ይደርብን::
.....ይቆየን......

አ.አ ኢትዮጵያ
ተክለ ኤል ኃ/ማርያም
ሐምሌ ፮ /፳ ፻ ፲ ፫ ዓ.ም
#ኃበ_ብዙኃን_አባታችን_አብርሃም ደግሶ ያበላቸው ዘንድ እንደ ወትሮው ይጠብቅ የነበረው ብዙ ሰዎችን ነበር።
ጸላዬ ሰናያት የበጎ ነገር ሁሉ ጠላት ዲያቢሎስ ግን ከመንገድ ቆሞ እራሱን በምትአት ገምሶ ደሙን አፍስሶ እያንጠባጠበ ወደ አብርሃም የሚመጡትን እንግዶች የድሮ አብርሃም ያለ መስሏችሁ ወደ አብርሃም አትሂዱ አብርሃም የድሮ ደግነቱን ትቷል።
#ይህው_እኔም እንደ ወትሮው መስሎኝ ያበላኛል ያጠጣኛል ብዬ ወደ እርሱ ብሄድ እራሴን ገምሶ ደሜን አፍሶ መለሰኝ ይላቸው ጀመር ። ሕዝቡም መቼም ደግ ሰው አይበረክትም እያሉ እያዘኑ ተመለሱ።
#ምስኪኑ_አብርሃም ግን እነርሱ መጥተው ሳይበሉማ እኔ አልበላም ብሎ ሳይበላ ፣ሳይጠጣ ከነገ ዛሬ ይመጣሉ እያለ ሦስት ቀን በተስፋ ጠበቃቸው ማንም ግን ዝር አላለም።
በሦስተኛው ቀን በቀትር ሰዓት ከድንኳኑ በር ቁጭ ብሎ ሳለ ከመምሬ የአድባር ዛፍ ሥር ሦስት ሽማግሌ ሰዎችን ተመለከተ ሰው የተራቡ አይኞቹም በደስታ ተሞሉ ሰው መቀበል የለመዱ እጆቹ ተዘረጉ እግሮቹም ወደ ፊት ሮጡ። በቀረባቸውም ጊዜ ስለ ግርማቸው ከፊታቸው ተምበርክኮ ሰገደላቸው።
#ጥቂት_ውኃ ይምጣላችሁ፥ እግራችሁን ታጠቡ፥ ከዚህችም ዛፍ በታች ዕረፉ፤ ቍራሽ እንጀራም ላምጣላችሁ፥ ልባችሁንም ደግፋ ከዚያም በኋላ ትሄዳላችሁ፤ ስለዚህ ወደ ባሪያችሁ መጥታችኋልና ። እነርሱም፦ እንዳልህ አድርግ አሉት።
አብርሃምም ወደ ድንኳን ወደ ሣራ ዘንድ ፈጥኖ ገባና፦ ሦስት መስፈሪያ የተሰለቀ ዱቄት ፈጥነሽ አዘጋጂ፥ ለውሺውም፥ እንጎቻም አድርጊ አላት።
#አብርሃምም ወደ ላሞቹ ሮጠ፥ እጅግ የሰባም ታናሽ ጥጃ ያዘና ለብላቴናው ሰጠው፥ ያዘጋጅም ዘንድ ተቻኰለ። እርጎና ወተትም ያዘጋጀውንም ጥጃ አመጣ፥ በፊታቸውም አቀረበው፤ እርሱም ከዛፉ በታች በፊታቸው ቆሞ ነበር፥ እነርሱም በሉ። የዛሬ ዓመትም ልጅ በመስጠት ወደእርሱ በረድኤት እንደሚመጡ ቃል ገብተውለት ተሰናብተውት ሄዱ ።

ሰው ብቀህ ሰው ቀርቶብ ብዙ ጊዜ ሐዝነህ ታውቅ ይሆናል ነገር ግን ሁል ጊዜ ሰው ሲቀር እግዚአብሔር ይመጣልና ሰው በቀረብህ ጊዜ ደስ ይበልህ! ሰው በዲያቢሎስ የሐሰት ወሬና ምክር ከመንገድ ሊቀር ይችላል ሰው ቀረ ብለህ ግን የቀደመ ልማድህን አትተው ሳትበላ የምጠብቃቸው ከሆነ ቢመጡም ቢቀሩም ሳትበላ ጠብቃቸው እነርሱ ቢቀሩ ሥላሴ አይቀሩምና! ግን ወዳጄ ሥላሴ ሲመጡ እኔ ሥላሴ ነኝ እያሉ ላይመጡ ይችላሉ ።

#የተቀዳደደ ልብስ ለብሰው ጎልዳፉ አንደበት ይዘው አንድ ወይም ሦስት ሆነው ሊመጡ ይችላሉ ያን ጊዜ በእነርሱ ደስ ብሎህ ለሌላው የምታደርገውን ሳታጓድል አድርገህ ደስ አሰኝተህ ላካቸው እንጂ እኔ የጠራሁት ነጭ ለባሽ የመጣብኝ ብጣሽ ለባሻ ብለት ከመቀበል ወደ ኋላ አትበል። "ተርቤ አላበላህኝም፥ ተጠምቼ አላጠጣህኝምና፥ እንግዳ ሆኜ አልተቀበልከኝምና " ትባለለህና #ማቴ 24÷42

“ የወንድማማች መዋደድ ይኑር። #እንግዶችን_መቀበል አትርሱ፤ #በዚህ_አንዳንዶች_ሳያውቁ_መላእክትን እንግድነት ተቀብለዋልና።” #ዕብ 13፥1-2
" ሰው ሲቀር እግዚአብሔር ይመጣል! "
አ.አ ኢትዮጵያ
ተክ ኤል ኃ ማርያም
ሐምሌ ፯/ቀን ፳ ፻ ፲ ፫ ዓ.ም
#አንዳንድ ልጆች ከወላጆቻቸው የሚበልጡበት ጊዜ አለ አንዳንድ ወላጆች ደግሞ በነገሮች ዕይታ ከልጆቻቸው የሚያንሱበትም ጊዜ አለ ። እናታችን ቅድስት ኢየሉጣ ይህን በመገንዘቧ ነበር ልጇን ሕፃኑ ቂርቆስን ስለ መልካም ምክሩ ልጇ ሆኖ ሳለ አባቴ ብላ ለመጥራት የተገደደችሁ ።
በእርግጥም የሥጋ ሞት እጅግ መራራና አስፈሪ ነው ። መድኅን ዓለም ክርስቶስ እንኳን ወዶ ፣ፈቅዶ የሞታችንን ጽዋ ሊጠጣልን ለካሳ፣ ለቤዛ መጥቶ ሳለ ጊዜው ደርሶ በአሙስ ምሽት የአይሁድ ወታደሮች ሊይዙት ሲመጡ ግን በአትክልት ቦታ በጌቴ ሰማኔ ሆኖ "አባት ሆይ ብትወድስ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ " ሲል ጸሎትን አድርጓል። #ማቴ 26÷39
#ይህም የሚያሳየን በመከራችን ጊዜ ወደ ሰማይ አባታችን መጸለይ እንደሚገባን ብቻ ሳይሆን የሥጋ ሞት ምነኛ አሰቃቂ ና አስፈሪ እንደሆነ ጭምር የሚያሳይ ነው ። ስለሆነም የቅድስት እየሉጣ ፍርሃት አያስደንቅም የሚያስደንቀውስ የልጇ እሳት መድፈር ነው ። “ አባት ሆይ፥ ይህን ከጥበበኞችና ከአስተዋዮች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግናለሁ፤ አዎን አባት ሆይ፥ ፈቃድህ በፊትህ እንዲህ ሆኖአልና።” #ሉቃስ 10፥21
በቤተክርስቲያናችን ታሪክ ገና በአፍላ ዕድሜያቸው በበሳልነታቸውና በአስተሳሰብ አድማሳቸው የተነሳ አረጋዊ ወይም ሽማግሌ ተብለው የተጠሩ ቅዱሳን አሉ ለምሳሌ ወደ ሀገራችን ከመጡ ከዘጠኑ ቅዱሳን መካከል ሮማዊው ኮከብ ዘሚካኤል(አቡነ አረጋዊ ዘደብረ ዳሞ) ማንሳት ይቻላል:: ዘሚካኤል አረጋዊ የሚል ስያሜን ያገኙት ገና አስራ አምስት ዓመት እንኳን ሳይሞላቸው ነበር።
#ቅዱስ_ወንጌል ከአንዱ ከተማ ቢያሳድዷችሁ ወደ ሌላይቱ ከተማ ሽሹ እንዳለ ከሮም መኮንን ሸሽታ ወደ ሌላ ሀገር ልጇን ይዛ ብትሄድ ያን የሸሸችሁ ክፉ መኮንን በዚህም ሀገር አገኛት የምታመልከውን አምላክ ክዳ የእርሱን ጣዖት እድታመልክም ጠየቃት ቅድስት ኢየሉጣ ግን ከእግዚአብሔር በቀር ሌሎች አማልክትን ማምለክ የሚገባ ወይም የማይገባ መሆኑን ይህን የሦስት ዓመት ልጄን ጠይቀው እርሱ ይንገርህ አለችሁ
መኮንኑም ቅዱስ ቂርቆስን በተመለከተው ጊዜ ፊቱ ብሩህና ደስተኛ ሕፃን እንደሆነ አስተዋለ ቀርቦም አንተ ደስተኛ ሕፃን እንዴት ነህ ሲል የማግባባት ሰላምታን አቀረበለት ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ ግን አዎን የኔ ደስታ ተጠብቆልኛል አንተ ግን ከዚህ እኩይ ሥራህ ካልተመለስ ልቅሶና ጥርስ ማፏጨት ጥልቅ ሐዘንም ይቆይሃል መጽሐፍ ለዝንጉዎች ተድላና ደስታ የላቸውም ይላልና አለው።“ለክፉዎች ሰላም የላቸውም ይላል አምላኬ።” #ኢሳ 57፥21
#መኳንንቱንና ጣዖታቱንም ሁሉ እረገማቸው ከኃይሉም ጽናት የተነሳ ሁሉ አደነቁ እግዚአብሔር ንግግርንና ኃይልን ሰጥቶታልና "ስለ እኔ ወደ ገዥዎች ወደ ነገሥታትም ትወሰዳላችሁ ። አሳልፈውም ሲሰጡአችሁ፥ የምትናገሩት በዚያች ሰዓት ይሰጣችኋልና እንዴት ወይስ ምን እንድትናገሩ አትጨነቁ፤ በእናንተ የሚናገር የአባታችሁ መንፈስ ነው እንጂ፥ የምትናገሩ እናንተ አይደላችሁምና። ተብሎ እንደተጻፈ #ማቴ 10÷18-20
መኮንኑም የሕፃኑን ንግግር በሰማ ጊዜ አፈረ ታላቅ የውኃ ጋን አዘጋጅታችሁ ውኃው እስከሚፍለቀለቅ በእሳት ላይ ጣዱት ውኃውም ሲፈላ ሕፃኑንና እናቱን በዚያ ጨምሯቸው ብሎ አዘዘ ።
#ጭፍሮችም እንደተባሉት አደረጉ የውኃው ፍላትም ድምጹ እንደ ክረምት ጊዜ ነጎድጓድ የሚያስፈራና የሚያስገመግም ሆነ ይህ ጊዜ የሕፃኑ እናት ቅድስት ኢየሉጣ ፈራች ሃይማኖቷም ከልቧ ተሸረሸረ ልጄ ሆይ ይህ ነገር ይቅርብን ንጉሥ ያለንን እንፈጽም አለችው።
ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ ግን ወደ ሰማይ አንጋጦ መላእክትን በጽረ አርያም ፣ ሐዋርያትን በስብከተ ዓለም ፣ ጻድቃንን በገዳም፣ ሰማዕታትን በደም ያጸናህ እናቴንም በሃይማኖት አጽናት ሲል ስለ እናቱ የእምነት መጉደል ወደ ፈጣሪው ጸለየ።
#እግዚአብሔርም የእናቱን ዐይነ ልቡና ገልጦ ለቅዱሳን ሰማዕታቱ ያዘጋጀውን የጽድቅ አክሊልን አሳያት ያን ጊዜ ቅድስት እየሉጣ በመንፈስ ተጽናናች ፣ በሃይማኖት ጸናች ንጉሡንና ጣዖታቱን ናቀች ልጇ ቂርቆስንም " #ልጄ_ስትሆን_አባት_ሆንክኝ " አለችሁ ተያይዘውም በእሳት ወደ ተፍለቀለቀው የውኃ ጋን ውስጥ ገቡ
#ከእግዚአብሔር_የተላከ_የመላእክት_አለቃ_ቅዱስ ገብርኤልም ከዐይን ጥቅሻ ፈጥኖ መጥቶ #በጌታችን_በመድኃኒታችን_በኢየሱስ_ክርስቶስ_መስቀል ያን ፍል ውኃ እንደ ክረምት ጊዜ ውርጭ አቀዘቀዘው። ሕፃኑና እናቱም ያለ ምንም ጉዳት ከጋኑ ወጡ። " #የእግዚአብሔር_መላእክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል ያድናቸውማል " እንዲል #መዝ 33÷7
.......... #ይቆየን............
#የእግዚአብሔር ቸርነት የመላእኩ ጠባቂየት የቅዱሳኑ የእናትና ልጅ በረከታቸው አይለየን !

አ.አ ኢትዮጵያ
ተክለ ኤል ኃ/ማርያም
ሐምሌ ፲ ፰/፳ ፻ ፲ ፫ ዓ.ም
#አዲስ_መልአክ
#ተክለ_ኤል
__________
ተፈጥሮ ከመላእክት ወገን ያልሆነ ሰው ሆኖ ሳለ ነገር ግን በሃይማኖቱ ጽናት በምግባሩ ቅንሐት እና በተጋድሎዎ ብዛት ምድራዊ ሲሆን ሰማያዊ አዳማዊ ሲሆን መላእካዊ ለመሆን የበቃ ሐዲስ መላእክ ነው :: ተክለ ኤል

ቅዱሳን መላእክት በዘር የተገኙ አይደሉም ተክለ ኤል ( #ተክለ_ሃይማኖት ) ግን ከሕግ ዘር የተገኘ ሰው የሆነ አዲስ መላእክ ነው ::

#ተክል › ማለት ፍሬያማ ዕንጨት፣ ዛፍ፣ ቅመም፣ ቅጠላ ቅጠል፣፣ የሚሸተት፣ቢበሉት ጥጋብ ፣ቢያርፉበት ጥላ የሚሆን ገነታዊ ዕፅ፣ እንዲሁም ሕግ ሥርዓት ማለት ነው /ማቴ.፲፭፥፲፫/፡፡

" #ኤል " ማለት ደግሞ እግዚአብሔር ማለት ነው :: ስመ መላእክት ስመ እግዚአብሔርን ያዘለ በመሆኑ የሁሉም ቅዱሳን መላእክ ስም "ኤል" የሚል መቀጽል አለው #ለምሳሌ :-ሚካ-ኤል ፣ ገብር-ኤል ፣ ዑራ -ኤል፣ ወዘተ .... ስለዚህ ተክለ ኤል ስንልም #የእግዚአብሔር _ተክል ማለታችን ነው :: ታላቁ ሊቅ ቅዱስ #ባስልዮስ ዘ ቄሳሪያ እኔስ #እግዚአብሔር ባልኩ ጊዜ #አብ_ወልድ_መንፈስ_ቅዱስ ማለቴ ነው ብሎ እንደተናገረ እኛም እግዚአብሔር ስንል አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ማለታችንነውና #ተክለ_ኤል ስንለውም የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ተክል ማለታችን ጭምር ነው::

#ቦታው በሸዋ ክፍለ ሀገር ዛሬ ኢቲሳ በመባል በሚታወቀው ከከሰም ጅረት አካባቢ ባለ ቦታ በጥንቱ ፈጠጋር ቡልጋ በደብረ ጽላልሽ አውራጃ ዞረሬ በተባለው ሥፍራ ነው ። በዚሁ ሥፍራ (ዘርዐ ዮሐንስ) ፀጋ ዘአብ የሚባል የቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ካህን የነበረ ጻድቅ ሰው ነበር "ጸጋ ዘአብ " ማለት የአብ ሥጦታ ማለት ነው ካህኑ ጸጋ ዘአብ በሃገሩ ደጋግ ከሆኑ ሰዎች ወገን ሣራ የምትባል ሴት አገባ ።

ሁለቱም ፈሪያ እግዚአብሔር ያደረባቸው በጎ ሥራን የሚሠሩ ሰዎች ነበሩ የፀጋ ዘአብ ሚስት ሣራ ሃይማኖት ከምግባር መልክና ደም ግባት ከሙያ ጋር አሟልቷ የሰጣት ሴት ነበረች ። አማቷ የፀጋ ዘአብ አባት " ወረደ ምሕረት " የሥራዋን ደግነት አይተው " እግዚኀረያ " ብለው ስም አወጡላት ጌታ የመረጣት ማለታቸው ነው።

#በሊቀ_መላእክት_በቅዱስ_ሚካኤል አብሳሪነት ከአባታቸው ከካህኑ ጸጋ ዘአብና ከእናታቸው ከቅድስት እግዚእ ኀረያ መጋቢት 24 ቀን ተፀንሰው ታኅሣሥ 24 ቀን 1197 ዓ.ም ተወለዱ ወላጆቻቸውም ፍስሐ ፂዮን ።(የጽዮን ደስታዋ)ብለው ሰየሟቸው፡፡ ጻድቁ በተወለዱ በሦስተኛው ቀን ከእናታቸው ዕቅፍ ወርደው ‹‹ አሐዱ አብ ቅዱስ አሐዱ ወልድ ቅዱስ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ›› ማለትም ‹‹አንዱ አብ ቅዱስ ነው አንዱ ወልድ ቅዱስ ነው አንዱ መንፈስ ቅዱስ ቅዱስ ነው›› በማለት የፈጠራቸውን አምላክ አመስግነዋል። ይህን ጊዜ እናታቸው እግዚ ኀረያም በመገረም ሆና " ይህ ሥራ የአባት ነው ላንተ የሚገባህ ጡት መጥባት ነው" ብላ ጡቷን አጎረሰችሁ ፡፡

#ቅዱሳን_መላእክት ቀን ከሌት #ቅዱስ_ቅዱስ_ቅዱስ እያሉ ያመሰግናሉ ኢሳ 6፥÷6 ይህም የህጻኑ ሁኔታ መላእካዊ ግብሩን ገና በህጻንነት የገለጠ ሁኔታ ነበር። ካህኑ ፀጋ ዘአብ የወቅቱን የቤተ ክርሰቲያን አገልግሎታቸውን ጨርሰው ወደ ቤታቸው ሲገቡ ሚስታቸው እግዚ ኀረያ በመገረም ሆና የሦስት ቀን ልጃቸው ፍስሐ ፂዮን እንዴት ባለ ምሥጋና ፈጣሪያቸውን እንዳመሰገነ ነገረቻቸው ጸጋ ዘአብም ህጻኑን ተቀብለው ታቅፈው እየሳሙ ልጄ ሺህ ዘመን ኑርልኝ እንዲ እያልክ በቤተ መቅደስ ስትቀድስ አይህ ዘንድ እመኛለው አሉ።
‹‹ #ተክለ_ሃይማኖት ›› ብሎ #የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ፍስሐ ፂዮን የሚለውን ስሙን በፈጣሪው ትዛዝ መሠረት ጠራቸው፡፡ በተወለዱ በ15 ዓመታቸው ዲቊናን፤ በ22 ዓመታቸው ደግሞ ቅስናን ከግብፃዊው ጳጳስ ከአባ ጌርሎስ ወይም (አባ ቄርሎስ) ዘንድ ተቀብለዋል፡፡

ሐዋርያዊ ተግባርንም በከተታ እና በፈጠጋር (በጽላልሽና በአካባቢዋ፣በዳሞት በምድረ ወላይታና አካባቢው ፣በአምሓራና በሸዋ በሐይቅ ቅዱስ እስጢፋኖስ፣ በኣድያማተ ትግራይ፣በገዳመ ዋሊ (ዋልድባ) ፣በገነተ ማርያም ላስታ በደብረ ዘመዶ ማርያም ገዳም በዚያው በላስታ፣ በኤርትራ ገዳማት ፣በደብረ ዳሞ አቡነ አረጋዊ ገዳም ወዘተ በአገሪቱ ወንጌል ባልተዳረሰበት ቦታ ሁሉ እየተዘዋወሩ ኢትዮጵያ አንዲት የሐዋርያት ወንጌል ሰፍተዋታል ።
#ጻድቁ_አባታችን ሕይወታቸዉን ሙሉ ለእግዚአብሔር በመስጠት፣ እንደ በሬ ተጠምደው፣ እንደ ገበሬ ታጥቀው፣ ይህንን ዓለም ንቀው፣ በጾም በጸሎት ተወስነው በብሕትውና በመኖራቸው፤ እርሳቸው በአሚነ ሥላሴ ጸንተው ሌሎችንም እንዲጸኑና እንዲያምኑ በማድረጋቸው፤ እንደዚሁም እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት ወንጌልን በመላው ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ በመስበክ በጌታችን በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ድውያነ ሥጋን በተአምራት፣ ድውያነ ነፍስን በትምህርት የፈወሱ ሰባኬ ወንጌል በመኾናቸው ‹‹ #ተክለ_ሃይማኖት ›› ተብለው ይጠራሉ::

#በየ_ደረሱበትም ከሥራው ጽናት ከተአምራቱ ብዛት የተነሳ አንተ ሰውነህን ወይስ መላእክ ነህ ንገረን ይሉት ነበር በዚህም በደብረ ዳሞት አቡነ አረጋዊ ገዳም 10 ዓመት ከቆዮ በኃላ ተሰናብቷቸው ሊሄድ ተነሳ ሁሉም ከፍቅሩ ጽናት የተነሳ አለቀሱለት አበምኔቱም ይህን ሰው ኃጢያቴ አባሮታልና ወየውልኝ ብሎ መነኮሳቱን ሰብስቦ ሊሸኙት ተነሱ ከገዳሞም ያለ እረጅም ገመድ (ጠፈር) መውረድም ሆነ መውጣት አይቻልም ነበርና የመውረጃውን ገመድ (ጠፍር) ይዞ ይወርድ ዘንድ ጀመረ ጥንተ ጠላት ዲያቢሎስ ገመዱን ከካስማው ላይ ቆረጠው አባታችንም ይህን አስደንጋጭ ክስሀት ተከትሎ የተሰጣቸው የፀጋ ክንፍ በገዐድ ተገለጠ አበ ምኔቱና መነኮሳቱም ከገዳሙ አፈፍ ሆነው የሚሆነውን ያዮ ነበር ጻድቁም እንደ ሰማያዊ መላእክ በክንፉቸው በረው በደህና ከመሬት ደረሱ መነኮሳቱም መንክር እግዚአብሔር በላዕለ ቅዱሳኒሁ ብለው አደነቁ::
ከዚህም ባለፈ ህዳር 24ቀን መላእኩ ከምድራዊ ቦታቸው ነጥቆ ወስዶ ከሱራፌል ጋር ቀላቀላቸው በልጅነት አንደበታቸው አሐዱ አብ ቅዱስ አሐዱ ወልድ ቅዱስ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ ቅዱስ ብለው ያመሠገኑት አግአስተ ዓለም ቅድስት ሥላሴን ዛሬ ደግሞ በዙፋኑ ላይ እናዳለ እያዮት በከንፈሮቻቸው ሰለሱት ቀደሱት በወርቅ ማዕጥንትም ዙፋኑን አጠኑ ።ወደ ቀደመም ኑሯቸው መላኩ መለሳቸውና ተጋድሏቸውን ቀጠሉ።

#በገዳመ አስቄጥስ ግብጽ እና ከኢየሩሳሌም።ጉብኝት በኃላ እየዞሩ ወንጌልን ለማስተማር ባይቻላቸው ስለዚህ በአንድ ቦታ መቆምን መረጡ ከፊት ከኃላ ከግራ ከቀኝ የሚያነቃ የሶር ሶማያ ስለው በመትከል በደብረ አስቦ በደብረ አስቦ ዋሻ ከዘረጉ ሳያጥፉ ከቆሙ ሳይቀመጡ ለ22 ዓመታት በጸሎት ጸኑ ጥር 4 ቀን 12 88ዓ.ም በ92 ዓመት ሲሆናቸው አንዲቱ የእግራቸው አገዳ ከመቆም ብዛት ተሰብራ ወደቀች ጸሎታቸውንም ሳያቆርጡ በአንድ እግራቸው 7 ዓመት አክለው በጸሎት ተጎ በድምሩም 29 ዓመት በጸሎት ተጋደሉ :: ከፈጣሪ ዘንድም ብዙ ጸጋና ቃል ኪዳን ከተቀበሉ በኃላ በ99ዓመት ከ10ወር ከ10ቀናቸው ነሐሴ 24 ቀን በክብር አርፈዋል:: እንደ ሰው በምድር ተወልደው እንደ መላክት የኖሩ አዲስ መላክ ያልናቸውም ለዚሁ ነው።

የጻድቁ አባት የአቡነ #ተክለ_ሃይማኖት እረድኤት በረከታቸው በአማላጅነታቸው የምትገኝ ጸጋ ለዘለዓለሙ ከእኛ ጋር ትኑር .....አሜን!
አ.አ ኢትዮጵያ
ተክለ ኤል ኃ/ማርያም
ጥቅምት 2013ዓ.ም
#ይህን ያለው ሻለቃ ኃይለ ገብረ ሥላሴ አይደለም ። እንዲ ያለው የደማስቆው ሯጭ ቅዱስ ጳውሎስ ነው ። “በእሽቅድምድም ስፍራ የሚሮጡት፥ ሁሉ እንዲሮጡ ነገር ግን አንዱ ብቻ ዋጋውን እንዲቀበል አታውቁምን? እንዲሁም ታገኙ ዘንድ ሩጡ።” #1ኛ ቆሮ 9፥24 ክርስቲያኖች የዚህች ዓለም ዙር እስኪያልቅ ድረስ በትጋት እና በውድድር መንፈስ መሮጥ አለባቸው ። ያሸነፉ ሁሉ እንጂ የሮጡ ሁሉ ጥሩ ዋጋን አይሸለሙም። “ እላችኋለሁና ጽድቃችሁ ከጻፎችና ከፈሪሳውያን ጽድቅ ካልበለጠ፥ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም።” #ማቴ 5፥20 በእርግጥ የኑሮ ሩጫ ለየ ቅል ነው እግዚአብሔር ወንዱን ከሴቱ ሕጻኑን ከአዋቂው ደምሮ በአንድ መስፈርት አያወዳድርም ለሁሉም እንደስራው መደብ በጽድቅ ይፈርድለታል እንጂ። ጻድቁ ወደፊት ይጽደቅ ቅዱሱም ወደፊት ይቀደስ ጠማማውም ወደ ፊት ይጥመም "እነሆ በቶሎ እመጣለሁ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍለው ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ዘንድ አለ እንዳለ ራእይ .ዮሐ22÷12

#ቅዱስ_ጳውሎስ ምርጥ ዕቃዬ ከመባሉ በፊት ሳዉል ይባል ነበር። ሁል ጊዜ ለኦሪት ሕግ የሚቀና ስለነበር ክርስቶስን እንከተላለን የሚሉ ክርስቲያኖች ሲመጡ ከኦሪቷ ሕግ ያፈነገጡ ስለመሰለው እነርሱን ያጠፉ ዘንድ ሌሊትና ቀን ሳይታክት ተሯሩጧል ። #ሐዋ 8፥3

ክርስቲያኖችን ለማሰር ብዙ ጊዜ ሮጧል፤ ክርስቲያኖችን ለማስደብደብ ብዙ ጊዜ ጥሯል፤ ክርስቲያኖችን ለማሳደድ ብዙ ጊዜ ሽምጥ ጋልቧል፤ክርስቲያኖችም በድንጋይ ተወግረው ሲሞቱ የገዳዮችን ልብሶች በደስታ ጠብቆል። ሳውል በዚህ ነገር ሁሉ ሮጧል ግን በምድርም ሆነ በሰማይ ኒሻን የሚሸልመው አልነበረም።

#በመጨረሻ ግን ክርስቲያኖችን ጨርሶ ይፈጅ ዘንድም የፍቃድ ደብዳቤ ሊያጽፍ ወደ ደማስቆ ሽምጥ ጋለበ በአጥፊነት መንፈስም ሮጠ #ሐዋ 9÷15

ወደ ከተማዋ ሲገባ ግን በታላቅ ብርሃን ተመታ ከፈረሱም ወድቆ ከብርሃኑ ጸዳል የተነሳ ዐይኑ ታውሮ ማየት ተሳነው ወዲያውም ሳውል ሳውል ስለምን ታሳድደኛለህ የሚል ቃል ሰማ።

#የማሳድድህ_አንተ ማነህ ? ብሎ ጠየቀ የምታሳድደኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነኝ የመውጊያውን ብረት ብትረግጥ ላንተ ይብስብሃል አለው ሳውልም ጌታ ሆይ ምን አደርግ ዘንድ ትወዳለህ አለው ወደ ደማስቆም ግባ ሐናንያ የሚባል የእግዚአብሔር ሰው ታገኛለህ እርሱ ይፈውስሃል አለው ።

ሳዉልም ከምድር ተነሳ ዐይኖቹም እንደታወሩ ነበሩ እየመሩም ወደ ከተማዋ አገቡት ለሐናንያም የጠርሴስ ሰው ሳውል ወደ እርሱ እንደሚመጣ በራዕይ ተነገረው ።

#ሐናንያ_ግን ስለ ሳውል ክፋት ብዙ ይሰማ ነበርና እንዴት እፈውሰው ዘንድ ይገባልን አለው ። ጌታም ይህ በአሕዛብም በነገሥታትም በእስራኤልም ልጆች ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነውና ሂድ፤ ስለ ስሜ ስንት መከራ ሊቀበል እንዲያስፈልገው እኔ አመለክተዋለሁና አለው። #ሐዋ 9÷ 13-15

#እግዚአብሔር እንዲህ ነው እያሳደድከውም ይወድሃል እየገደልከው ያኖርሃል እያሰርከው ይፈታሃል እየሸሸህው በፍቅር ይከተልሃል ሰዎች እንደ ሸክም ሲቆጥሩህ ሁሉን ቻይ ትከሻህ ያለው ይሆናል ብሎ ይመሰክርልሃል ሰው ኃጢያተኛ እያለህ እርሱ ግን ምርጤ ይልሃል። #እግዚአብሔር እንዲህ ነው!
ሐናንያም ሄዶ ወደ ቤቱ ገባ፥ እጁንም ጭኖበት፦ ወንድሜ ሳውል ሆይ፥ ታይ ዘንድና መንፈስ ቅዱስ ይሞላብህ ዘንድ ላከኝ አለ። #ወዲያውም_እንደ_ቅርፊት_ያለ ከዓይኑ ወደቀ፥ ያን ጊዜም ደግሞ አየ፤ ተነሥቶም ተጠመቀ፥ በክፉት መንገድ ሮጦ ያተረፈው እውርነትን ተረዳ አሁን ግን በጽድቁም መንገድ መሮጥን መረጠ።“
#እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በመንገድ ላይ ቁሙ #ተመልከቱም፥ የቀደመችውንም መንገድ ጠይቁ፤ መልካሚቱ መንገድ ወዴት እንደ ሆነች እወቁ፥ በእርስዋም ላይ ሂዱ፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ እነርሱ ግን ” ያለ ዐይን መመልከት፣ መሄድ እንዲሁም መሮጥ አይቻልም።
በሥጋ ለመሮጥ ዓይነ ሥጋ በመንፈሳዊ ሕይወት ለመሮጥ ዐይነ ልቡና ሊኖረን ይገባል ያለ ዐይን እንኳን መሮጥ በደህንነትና በምቶት መራመድ አይቻልም። ዐይን ለሰውነት ሁሉ ወሳኝ አካል ናት በእርግጥ ዐይን አይሮጥም የሚሮጠው እግር ነው ሆኖም መነሻውን መገስገሻውንና መዳረሻውን ዐይን ካላመለከተችሁ እግር ወስዶ ወስዶ ገደል ይከታል ። “ዕውርም ዕውርን ቢመራው ሁለቱም ወደ ጉድጓድ ይወድቃሉ አለ።” #ማቴ 15፥14
ስለሆነም በእግረ ሥጋ ለመሮጥ ዐይነ ሥጋ በእግረ ልቡና ለመሮጥ ዐይነ ልቡና የግድ ያስፈልገናል። #ታገኙ_ዘንድ_ሩጡ " ብሎ ስለ መንፈሳዊ ሩጫ የመከረን ቅዱስ ጳውሎስ ከሥጋው ዐይንና ከልቦናው ዐይን ላይ ጋርዶት የነበረው ቅርፊት ከወደቀለት በኋላ ነው።
#አሁን የሚያሯሩጠው ሳውል ተብሎ አይጠራም ፤ አሁን የሚያሳድደው ሳውል መባሉ ቀርቷል፤አሁን ደብዳቢ መሆኑ አብቅቷል። አሁን ስለ ስሙ ከቦታ ቦታ የሚሯሯጥ ምርጥ ዕቃ ጳውሎስ ሆኗልና አሁን ስለስሙ ከሀገር ወደ ሀገር የሚንከራተት ስደተኛው ሆኗልና ። 2ቆሮ 11÷23-27
ዋጋ ለማግኘት መሮጥ እንዳናይ የጋረደንን ግርዶሽ ከመጣል ይጀምራል ። ከሳውል ዐይን ቅርፊት መሳይ ነገር ወደቀ ሲል ከአስተሳሰቡና ከልቦናውም ዐይን ጭምር ቅርፊቱ እንደወደቀለት ማስተዋል ያስፈልጋል። ክርስቶስን ወዶ እናቱን ማሳደድ ክርስቶስን ወዶ ክርስቲያኖችን መጥላት ይህ የልቡና ግርዶሽ ፣ ይህ የልቡና ሽፋን፣ ይህ የዕሊና ቅርፊትም ነውና። #እግዚአብሔር እንደ ሳውል ነቅሎ ይጣልላቸው አጥርተው ያዮ ዘንድም የተንሸዋረረ ዐይነ ልቦናቸውን ሐናንያ በመሰሉ የቅዱሳኑ ጸሎትና ምልጃ ያብራላቸው።

#ሃይማኖት የሌላችሁ ወደ ሃይማኖት ሩጡ
#ሃይማኖት ያላችሁ ወደ ምግባር ገስግሱ
#ምግባር ያላችሁ ወደ ትሩፉት ፍጠኑ ወደ ገነት በር ትደርሳላችሁ ተከፍቶም ታገኙታላችሁ ከየት ናችሁ የሚላችሁም አይኖርም። ያን ጊዜ የደማስቆውን ሯጭ ታኙታላችሁ አብራችሁትም “ መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፥ ሩጫውን ጨርሼአለሁ፥ ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ፤” ትላላችሁ ። #2ኛ ጢሞ 4፥7


አ.አ ኢትዮጵያ
ተክለ ኤል ኃ/ማርያም
ሐምሌ ፳፮/፳ ፻ ፲ ፫ ዓ.ም
#ስለ_ታቦቲቱ የባዕዳኑ ምልከታ !
______________________________

( The sign and the seal /ታቦተ ጽዮንን ፍለጋ )
ግራሃም ሐንኰክ

ታላቁ የመጻሕፍ ቅዱስ ምሥጢር
________________________ ገጽ 3-4

#በዘመነ ኦሪት እስራኤልላዊያን የቃል ኪዳኑን ታቦት የእግዚአብሔር ማደሪያ በመሆኑ የሚያመልኩትና በምድር ላይ ያኖረው ምልክቱንና ማኀተሙን እንዲሁም የኃይሉ መገለጫ ነው ብለው ያምኑ ነበር።
አሥርቱ ቃላት የተፃፉባቸው ሁለት ክንድ ርዝማኔ አንድ ክንድ ተኩል ቁመትና ወርድ ያለው በውስጥና በውጭ በወርቅ የተለበጠ ነው ከተቀጠቀጠ ንፁህ ወርቅ የተሠሩ ሁለት ኪሩቤል አንዱ ኪሩብ በአንድ ወገን ሁለተኛው ኪሩብ በሌላ ወገን ክንፎቻቸውን ወደ ላይ ዘርግተው ወደ መክደኛው በትይዮ ሲመለከቱ የሚያሳይ ነው ።
#መጽሐፍ_ቅዱስና ሌሎችም ጥንታውያን መዛግብት እንደሚሉት ታቦተ ሕጉ በሚንቀለቀል ብርሃኑና እሳቱ በነቀርሳ በእባጭ ና በለምጽ የመምታት የማቃጠል ተራራዎችን ወደ ሜዳማነት የመለወጥ ፣ ወንዞችን የማድረቅ ታላላቅ ሠራዊትን የመደምሰስ ፣ከተማዎችን የማፈራረስ ኃይል አለው።
እነዚሁ ምንጮች አክለውም ታቦተ ሕጉ የአይሁዶች የእምነት መሠረት እንደሆነ ና ንጉሥ ሰሎሞንንም የመጀመሪያውን ቤተ መቅደስ በኢየሩሳሌም ያሠራው ይህንኑ ታቦት በክብር ለማኖር አስቦ መሆኑን ይገልጻሉ።
#ይሁንና_ከክርስቶስ_ልደት በፊት በአንድ ሺህና ስድስት መቶ ዓመታት መካከል በገበረው ጊዜ ይህ እጅግ ድንቅና ተአምራዊ ታቦት የትና ወዴት እንደሄደ ሳይታወቅ በመሠወሩ ጉዳዩ ለብዙ ሺህ ዓመታት እንቆቅልሽ ሆኖ ቆይቷል ማስረጃው እንደሚጠቁመው በ587ዓመቸ ዓለም የናቡ ከደ ነጾር ሠራዊት ኢየሩሳሌምን ባቃጠለ ጊዜ ታቦቱ በቦታው አልነበረም ።
በጦርነቱ የተማረኩት እስራኤላውያን ከባቢሎን ወደ ሀገራቸው ኢየሩሳሌም በ538ዓመተ ዓለም ተመልሰው ሁለተኛውን ቤተ መቅደስ በሠሩበት ወቅትም ታቦቱ በዚያ አልነበረም ። ይህም ቀደም ሲልታቦቱ በባቢሎናዊያን አለመዘረፉን ያረጋግጣል።
#በካሊፎርኒያ ዮኒቨርስቲ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ሪቻርድ ኤሊየት ፍሬድማን በ1987ይህን ጉዳይ አስመልክተው ሲጽፋ "የታቦቱ መጥፋት ከመጽሐፍ ቅዱስ አስደናቂው ምሥጢሮቾ እንደ አንዱ ይቆጠራል"ብለዋል።
ብሉይ ኪዳን መጻሕፍ ውስጥ እስከ ንጉሥ ሰሎሞን ዘመነ መንግሥት (970-931 ቅድመ ልደተ ክርስቶስ) ድረስ ከሁለት መቶ ጊዜ በላይ ስለ ታቦቱ ተጠቅሷል። ከዚህ ብልህና አስተዋይ መሪ ዘመነ መንግሥት በኋላ ግን ታሪኩ አንድም ጊዜ እንኳን ተነስቶ አያውቅም። ይህን የመሰለ ክቡርና ውድ ቅርስ በተለይም ደግሞ ሃይማኖታዊ ከበሬታ ያለው በብሉይ ኪዳን የኋለኞቹ መጻሕፍት ጨርሶ አለመወሳቱ የሚያስገርም ነው።
#በዚህ የተነሳ በዘመኑ የነበሩ ጸሐፍትና ቀሳውስት የዚህን ቅዱስ ቅርስ የመሰወር ምሥጢር ላለማሳወቅ ከፍተኛ የሆነ የመሸፋፈን ጥረት ያደረጉ አስመስሎባቸዋል። የተሰወሩ ቅርሳ ቅርሶችን የሚያስሱ ወገኖች የዚህን ታላቅ ቅርስት መሰወር አውቀው በርካታ ዘመቻዎችን ቢያካሂዱም አንዳቸውም አልተሳካላቸውም።
በ1981/የጠፋው ታቦት ዘራፊዎች/( #Raiders_of_the_Lost_Ark ) በሚል ርእስ ሐሪሰን ፎርድ እንደኢንዲያና ጆንሰ ሆና የተወነችበት የሆሊውድፊልም ውስጥ በአሜሪካና በአውሮፓ ለዕይታ ቀርቦ ነበር። እኔም 1983 ናይሮቢ ውስጥ ይህንኑ ፊልም የማየት ዕድሉ አጋጥሞኝ ነበር።
#ፊልሙን ካየው በኋላ የታቦቱን ዱካ አነፍንፌ የለማግኘት ሀሳብ አደረብኝ።ከጥቂት ወራት በኋላም ሀሳቤን ለመተግበሮ ወደ ኢትዮጵያ አመራሁኝ። ጉዞዬንም ወደ ትግራይ አቅንቼ የኢትዮጵያውያን ቅድስት ከተማ የምትባለውን አክሱምን ጎበኘሁ። በዚህ ጊዜ ነበር ጠባቂውን መነኩሴ ያገኘኋቸው።
( The sign and the seal /ታቦተ ጽዮንን ፍለጋ)
በግራሃም ሐንኰክ
............... #ይቀጥላል ..........
በቀጣይ
#ታቦቲቱ በኦሪቱ_ምልከታ
#ታቦቲቱ በአዲሳት ምልከታ
#ታቦቲቱ_በኢትዮጵያውያን እምነትና መልከታ
#ሞት_በጥር_ነሐሴ_መቃብር

መቼም ዞሮ ዞሮ ከቤት ኖሮ ኖሮ ከመሬት የሚቀር የለም :: ሞትን ሳይቀምሱ በሥጋ የተሰወሩ ቅዱሳን ሰዎች ቢኖሩም በመጨረሻ ግን የሞትን ጽዋ መጠጣታቸው ግድ ነው ሞት ወደ ክርስቶስ መሄጃ መንገድ መሸጋገሪያ ድልድይ ነውና:: ለዚህ ነው ሐዋርያው "፤ ልሄድ ከክርስቶስም ጋር ልኖር እናፍቃለሁ፥ " ያለው #ፊል ፩ ÷ ፳፫
#የዛሬን አያድርገውና ሞት እንዲ ተዋርዶ እና ዝቅ ብሎ መንገድ ተብሎ እንደ ተራ ከመጠራቱ በፊት እጅግ አስፈሪ ነበር :: ሰዎች መልካምም ይሁኑ እኩያት በሞት ተግዘው ሲዖል ወስዶ መማቀቃቸው አይቀርም ነበር "፤ ሁላችን እንደ ርኩስ ሰው ሆነናል፥ ጽድቃችንም ሁሉ እንደ መርገም ጨርቅ ነው፤ ሁላችንም እንደ ቅጠል ረግፈናል #ኢሳ ፷ ፬ ÷፮ እንዲል ነብዮ ::
በኋላ ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህች ምድር መምጣት ሞት የቀደመ መፈራቱን አጣ በትንሳኤ ተደመሰሰ በዚህም አስቀድመው እንኳንስ በደላችን ጽድቃችን እንኳ ሳይቀር እንደ
መርገም ጨርቅ ተቆጠረብን እንዳላሉ "፤ ሞት ሆይ፥ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ፥ ድል መንሣትህ የት አለ? " እያሉ የሞትን ኃይል አቃለሉት #፩ቆሮ ፲፭÷፶፭
#ሞት በራሱ ምንም ያልሆነ የልደት ተቃራኒ ነው ነገር ግን በግብሩ ሞት ተብሎ የሚጠራው ዲያቢሎስ ነው:: ሞት የሁሉ ገዥ ሆኖ ሰልጥኟል የክብር ባለቤት መድኃን ዓለም ክርስቶስ ሳይቀር በፈቃዱ ሞትን ቀምሷል :: ይህም ከመላእክት እንኳ በጥቂቱ አነሰ ተብሎ እንዲነገርለት አድርጓል ሞት ሁሉን እንዲገዛ ያሰለጠነው እርሱ እራሱ ነው። ቢሆንም ግን ቅሉ ክብር ይግባውና ከሞት ያንሳል አያሰኘውም::

#መጻሕፍትም ይህን ግልጽ ሲያደርጉልን እንዲ ብለዋል "፤ የኃለኛው ጠላት የሚሻረው ሞት ነው ሁሉን ከእግሩ በታች አስገዝቶአልና። ነገር ግን። ሁሉ
ተገዝቶአል ሲል፥ ሁሉን ካስገዛለት በቀር መሆኑ ግልጥ ነው። " #፩ቆሮ ፲፭ ÷፳፯ ሞት ለፈጣሪ ዓለማት ብቻም ሳይሆን ለእናቱ ለምክንያተ ድኅይን ለምትባል ለእመቤታችን ለማርያምም አልተመለሰም ::

#እመቤታችን_ቅድስት_ድንግል_ማርያም በምድር ላይ ስልሳ አራት ዓመታትን ቆይታለች ማለትም ከእናት ከአባቷ ቤት ሦስት ዓመት ከሰባት ወር፣ በቤተመቅደስ ፲፪ ዓመት፣ በቤተ ዮሴፍ ፴፬ ዓመት ከሦስት ወር፣ ከጌታችን እርገት በኋላ ከወንጌላዊው ዮሐንስ ጋር ፲፬ ዓመት ኖራለች፡፡ ጥር ፳፩ በእሑድ ቀን ጌታ እልፍ አዕላፋት መላእክቱን
አስከትሎ መጥቶ እናቴ ሆይ ከዚህ ዓለም ድካም ላሳርፍሽ መጣሁ አላት።

ልጄ ሰማይና ምድር የማይወስኑህ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በማህጸኔ ተሸክሜ በድንግልና ወልጄህ እሞታለሁን? አለችው። እውነት ነው ሊቁ ቅዱስ ያሬድም ይህ ነገረ ሞቷን &ሞትሰ ለመዋቲ
ይደሉ ሞታ ለማርያም የዐጽብ ለኲሉ፤( ሞት ለማናቸውም ሰው ሁሉ የተገባ ነው የማርያም
ሞት ግን ሁሉን ያስደንቃል ) ሲል አድንቋል ከዛም በሲዖል የሚሰቃዩ ነፍሳትን አሳይቶ እናቴ ሆይ ሞትሽ ለእነዚህ ቤዛ ይሆንላቸዋል አላት።

#እሊህን_ከማርክልኝስ ይሁን አንድ ጊዜ
አይደለም ሰባት ጊዜ ልሙት አለችው። ቅድስት ሥጋዋን ከቅዱስ ነፍሷ ለይቶ በዝማሬ መላእክት አሳረጋት። "ሞትኪሰ ማርያም ይመስል ከብካበ" የማርያምስ ሞት ሠርግን ይመስላል እንዲሉ አበው የእመቤታችን እረፍት እንባ መራጨት፣ ጠጉር መንጨት፣ ደረት መድቃት እንዳለበት የሰው ሞት አልነበረም፡፡ ይልቁንም አንደ ሠርግ ቤት መላዕክት
በውዳሴ፤ በማህሌት፣ በዝማሬ፣ በምስጋና ወደ ሰማይ ሸኟት እንጂ ቅዱስ ያሬድም "ተለዐለት እምድር ወበህየ ነበረት ዘምስለ ወልዳ በየማነ አብ ወመንፈስ ቅዱስ" እመቤታችን ድንግል ማርያም ከምድር ወደ ሰማይ ከፍ ከፍ አለች፡፡
በዚያም ከልጇ ጋር በአብና በመንፈስ ቅዱስ ቀኝ ተቀመጠች በማለትም ዘምሯል፡፡ "፤የቅዱሳኑ ሞት
በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው።" መዝ ፻፲፮ (፻፲፯) ÷፲፭ አስቀድመው ሐዋርያት ሥጋዋን በአጎበር አድርገው ወደ ጌቴሰማኒ ይዘው ሲሄዱ ብዙ ተግዳሮት ገጥሞቸው ነበር:: አይሁድ ቀድሞ ልጇን ተነሳ ዐረገ እያሉ ሲያውኩን ይኖራሉ አሁን ደግሞ እሷን ተነሳች ዐረገች እያሉ ሊያውኩን አይደለምን? ኑ በእሳት እናቃጥላታለን ብለው ተነሱ።
#ታውፋንያ የሚባል አይሁዳዊ ተራምዶ አጎበሩን ጨበጠው። መልአክ መጥቶ በሰይፍ ሁለት እጁን ቀጣው ከአጎበሩ ተንጠልጥሎ ቀረ ። በድያለሁ ማሪኝ ብሎ ቢማጸናት እጁ ተመልሶለታል። ከዚህ በኋላ ዮሐንስን ጨምሮ በደመና ነጥቆ ከገነት አግብቶ ከዕፀ ሕይወት ሥር አኖራት። ቅዱስ ዮሐንስን እንደምን ሆነች አሉት ከገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር አለች አላቸው ቅዱስ ዮሐንስ አይቶ እኛ ሳናይ ብለው በነሐሴ መባቻ ጾም ጀመሩ ሁለት ሱባዔ ሲፈጸምም እሑድ አምጥቶ
ሰጥቷቸው ቀብረዋታል በሦስተኛው ቀን ማክሰኞ “ #ከመ_ትንሣኤ_ወልዳ ” እንደ ልጇ ባለ ትንሣኤ ተነሥታለች።
ቅዱስ ቶማስ አልነበረም ደመና ጠቅሶ ከሀገረ ስብከቱ ሲመጣ ስታርግ አገኛት ቀድሞ የልጅሽን ትንሳኤ ሳላይ ቀረሁ ዛሬም ደግሞ ያንችን ትንሳኤ ሳላይ ቀረሁን ብሎ “ወፈቀደ ይደቅ እምደመናሁ” ከሀዘኑ የተነሳ ሊወድቅ ወደደ እመቤታችንም አይዞህ
አትዘን እሊያ ትንሳኤየን ዕርገቴን አላዩም አንተ አይተሃል ተነሣች ዐረገች ብለህ ንገራቸው ብላ የያዘችውን ሰበን ሰጥታ ሰደደችው። ከዚህ በኋላ ሂዶ የእመቤታችን ነገር እንደምን ሆነ? አላቸው አግኝተን ቀበርናት አሉት #ሞት_በጥር_በነሐሴ_መቃብር ተው ይህ ነገርስ
አይመስለኝም አላቸው ። ቅዱስ ጴጥሮስ አንተ እንጅ ልማድህ ነው አንተ ብቻ ተጠራጥረህ አትቀርም ሰውን ሁሉ ስታጠራጥር ትኖራልህ ብሎ ተቆጥቶ ወደ መቃብሩ ሂዶ ቢከፍተው አጣት ደንግጦ ቆመ ሐዋርያው ቶማስም አታምኑኝም ብዬ እንጅ #እመቤታችንስ ተነሣች ዐረገች አላቸው የያዘውንም ሰበን ሰጣቸው ለበረከትም ተካፍለውታል።
#በዓመቱ ሐዋርያት ቅዱስ ቶማስ ትንሣኤሽን ዕርገትሽን አይቶ እኛ ሳናይ ብለው ጾም ጀመሩ በ፲፮ ኛው ቀን እመቤታችንን መንበር አድርጎ ቅዱስ ጴጥሮስን ካህን ዘይትራድኦ ቅዱስ እስጢፋኖስን ሠራዒ ዲያቆን አድርጎ በዚያው ላይ ቀድሶ አቁርቧቸዋል። ፍቅሯን በልቡናችን ጣዕሟን
በአንደበታችን ያትምልን
......... #ይቆየን .........
#የእመቤታችን_አማላጅነት_የልጇም_ይቅርታና_ቸርነት_አይለየን አሜን!

አ.አ ኢትዮጵያ
ተክለ ኤል ኃ/ማርያም
ጥር ፳፩ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም