ዐውደ ምሕረት
3.42K subscribers
939 photos
24 videos
271 files
208 links
"ቤተ ክርስቲያን ባሕረ ጥበባት
አትመረመርም እጅግ ጥልቅ ናት"
Download Telegram
"ዐርገ በስብሐት ውስተ ሰማያት" የዘወትር ጸሎታችን ነው።አስቀድሞ በማኅፀነ #ድንግል ሥጋችንን ቃል ስለተዋሐደው በባሕርይ አምላክነት (በፈጣሪነት) ዐርጓል (ከፍ ከፍ ብሏል)።ሆኖም ግን እስከ ትንሣኤ ድረስ የትሕትናን ሥራ ከልዕልና ጋር ሲሠራ ቆይቷል።ከትንሣኤ በኋላ እስከ ዐርባ ቀን ድረስ ምሥጢረ መንግሥተ ሰማያትን ለቅዱሳን #ሐዋርያት ሲያስተምር ቆይቶ በአርባኛው ቀን በግርማና በስብሐት ወደ ሰማይ ዐረገ፤በአባቱም ቀኝ ተቀመጠ።

‎አካላዊ ቃል ከድንግል #ማርያም ነሥቶ የተዋሐደው ሥጋ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አንድ የሆነው ማለትም ምልዐትን፣ ስፋትን ፣ርቀትን የአብ ልጅነትን ገንዘብ ያደረገው ቃል ሥጋን በተዋሐደበት (ጌታ በተፀነሰበት) ቅጽበት ነው።ዳግመኛ በትሕትና ሥራ ላይገለጥ ከብሮ የታየበት በዓሉ ደግሞ ዕርገት ነው።

‎ "ታስበው ዘንድ ሰው ምንድነው" እንዳለ ቅዱስ ዳዊት እንዲህ ባለ ክብር ሰውነታችንን ያከብር ዘንድ በእውነት እኛ ምንድነን?ዛሬ የእኛ ሰውነት በቅዱሳን በመላእክት ታጅቦ ወደ ሰማይ ወጣ።ድል ነሥቶ በአብ ቀኝ ተቀመጠ።

‎ "በክብር በምስጋና ወደ ሰማይ ዐረገ በአባቱም ቀኝ ተቀመጠ" ስንል ክርስቶስ ከአባቱ ቀኝ ተለይቶ ኖሮ ኋላ
‎ወደ አባቱ ቀኝ የሄደ አይደለም።ሰው የሆነበትን ዓላማ ፈጽሞ ሰይጣንን አሥሮ ሰውን ነፃ አውጥቶ በድል ነሺነት በአባቱ ቀኝ ተቀመጠ ማለታችን ነው።

#ዕርገትን ስናስብ

#የእግዚአብሔርን ውለታ እናስባለን (እኛን ያከበረበትን ክብር)
#ያዘጋጀልንን መንግሥተ ሰማያት እናስባለን።ተስፋችን ይለመልማል።
‎“ሄጄም ስፍራ ባዘጋጅላችሁ፥ እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ።”(ዮሐ 14፥3) "ሄጄም" ሲል ዕርገቱን ተናገረ።
#የዳግም ምጽአትን ፍርድን በማሰብ ራሳችንን እናዘጋጃለን።
‎“የገሊላ ሰዎች ሆይ፥ ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ ስለ ምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው #ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፥ እንዲሁ ይመጣል አሉአቸው።”(ሐዋ 1፥11)
#በመንግሥተ ሰማያት የሚኖረንን ዕርገታዊ ሕይወት እናስባለን።
‎ በክብር ላይ ክብር፣በጸጋ ላይ ጸጋ፣በጣዕም ላይ ጣዕም፣በመዓዛ ላይ መዓዛ በማያቋርጥ ከፍ ማለት መኖራችንን ተስፋ እናደርጋለን።
‎ "የሙታንን መነሣት የሚመጣውንም ሕይወት ተስፋ እናደርጋለን" "የሚመጣው ሕይወት" ምንድንነው?ከትንሣኤ በኋላ የሚኖረን የማያቋርጥ ሱታፌ #አምላክ (#እግዚአብሔርን መምሰል) ነው እንጂ!!!

‎ ከበዓለ ዕርገቱ ረድኤት በረከት ያሳትፈን!!
#ኢዮብ ክንፈ
‎ ግንቦት 21/2017 ዓ.ም


የአፎምያ ጥያቄ የባሕራን መልስ
#ቅዱስ_ሚካኤል
እርግብ የምታገባው አንድ ብቻ ነው። ቢሞት እንኳን ሌላ መጥቶ እንዳይተናኮላት ምላሷን ትሰነጥቃለች። ድንገት ቢመጣባት በደንብ መጮህ እንድትችል እና ሌሎች መጥተው ደርሰውላት እንዲያባርሩላት ነው። ቅድስት አፎምያን እንደ እርግ የምትኖር ደገኛ ሴት ነበረች።

የኬልቅያ መስፍን የነበረው የምትወደው ባሏ አስተራኒቆስ በሞት ከተለያት በኋላ በዕውቅ አስሎ የሰጣትን የቅዱስ ሚካኤል ሥዕል ይዛ በጾም በጸሎት ተስና ስትኖር ጸላዬ ሰናያት የመልካም ነገሮች ሁሉ ጠላት የሆነ ሰይጣን ዲያቢሎስ ደግ መነኩሴ መስሎ መቶ ጾም ጸሎት እንድትተው ሌላ ባል አግብታ ተድላ ደስታ እንድታደርግ መከራት እርሷ ግን አባ አለባበሶት ደግ ነበር ንግግሮት ግን የከፋ ነው። ጾም ፣ጸሎት ና ምጽዋት ደገኛ ሥርዓት አይደሉምን? ስለምንስ ዳግመኛ እንዳገባ ይመክሩኛል በሉ ከኔ ወግዱልኝ ብላ አሳፍረችው። ይህን ግዜ የደበቀውን ሰይጣናዊ ግብር ገልጦ ቆቡን ጥሎ ከቁራ ሰባት ጅ ጠቆረ ሰኔ አሥራሁለት ቀን ተመልሼ እመጣለሁ አጠፋሻለሁም ብሎ ዝቶባት እንደ ጢስ ተኞ እንደ ትብያ ተኖ ጠፍቶ ሄደ ።

ሰይጣን ዲያቢሎስ እንዳለሁም ግብሩን ለውጦ በሰኔ አሥራ ሁለት ቀንም የመላእከት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልን መስሎ ባማረና በተዋበ ልብስ ወደ ቤቷ መጥቶ ተገለጠላት “ይህም ድንቅ አይደለም፤ ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና።” ተብሎ እንደተጻፈ 2ኛ ቆሮ 11፥14

ቤቴን በብርሃንህ የሞላህ አንተ ማነህ ? አለችሁ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ነኝ ይህ ከብርሃኔ ተረጂ አላት ቆየኝ መጣው ብላ የቅዱስ ሚካኤል ወዳጂ የነበረው ባሏ አስተራኒቆስ አስሎ ነሰጣትን የቅዱስ ሚካኤልን ሥዕለ አድህኖ ይዛ መጣች ። እያመሳሰለችሽ ንጉሥ ለጭፍሮቹ መታወቂያ ማኅተቡን አትሞ አስይዞ ይልካቸዋል የእግዚአብሔር መላእክ ቅዱስ ሚካኤል ከሆንክ ማዕተመ መስቀልህ የንጉሥህ መታወቂያ በትረ መስቀልህ የታለ ?አለችሁ። እርሱም ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና እኛ በእግዚአብሔር ፊት የምንቆም መላእክት መስቀል መያዝ ለምናችን ጨርሶ አያስፈልገንም አላት ይህን ጊዜ አንተማ መላእኩ ቅዱስ ሚካኤል አይደለህም አላምንህም አለችሁ ያን ጊዜ እንዳ ወቀችበት ሲረዳ ግብሩ ቀይሮ በብርሃን የመላው ቤቷን በጽልመት መላው ቀንዱ በቀለ ፣ጥፍሩ እረዘረዘ፣ ዐይኑ ፈጠጠ ፣ጥርሱ ገጠጠ አንቺንስ ካላጠፋሁ ሠላሜን አላገኝም ብሎ ተወርውሮም አንቆ ያዛት ቅድስት እናት አፎምያም እውነተኛው ታላቁ መላእክ ቅዱስ ሚካኤል ሆይ እርዳኝ ብላ በጣር ውስጥ ሆና ተጣራች እውነተኛው የእግዚአብሔር መላእክም ከዐይን ጥቅሻ ፈጥኖ መጣና ዲያቢሎስን ረግጦ ያስጨንቀው ገባ ሰይጣንም ሚካኤል ሆይ ጊዜዬ ሳይደርስ እንዳታጠፋኝ በፈጣሪህ እለምንሃለው እያለ ጮኸ ቅዱስ ሚካኤልም ለቀቀው በኖ ተኖ ጠፋ ቅድስት እናት አፎምያንንም ያረጋጋት ጀመር ። “ #የእግዚአብሔር_መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፥ ያድናቸውማል።” እዳለ መጻሕፍ #መዝ (33) 34፥7

*አንባቢ ሆይ አንተስ በክርስቶስ ክርስቲያን ነኝ ትላለህንን እንግዲያውስ መስቀልህ የታል?
*አንባቢት ሆይ የንጉሥሱ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ትያለሽን? መልካም ትያለሽ ግን የንጉሡ ደመ ማዕተብ በትረ መስቀልሽ ከወዴት አለ? የአፎምያ ጥያቄ ይህ ነበር መስቀልህ የታለህ? ለአፎምያ ትክለኛ ጥያቄ መልስ የሆናት እውነተኛው ቅዱስ ሚካዬል በትረ መስቀሉን ጨብጦ ይዞ በመታየት ነው።ወዳጄ የድልህ ዐርማ የሆነውም " ሁልጊዜ በልብህ አኑረው፥ በአንገትህም እሰረው። ስትሄድም ይመራሃል፤ ስትተኛ ይጠብቅሃል፤ ስትነሣ ያነጋግርሃል። " #ምሳ 6÷21-22 የደሃ አደጊቱ ልጅ ባሕራንም የሞት ደብዳቤውን ተቀብሎ የደስታ የፍስሐ የሰርግ ደብዳቤ አድርጎ የመለሰለት የደስታ ሁሉ መልስ ቅዱስ ሚካኤል በዚህች ዕለት በነገዱ ሁሉ ላይ የተሾመበት የሹመቱ በዓል ነው!

መንፈስ ቅዱስ ያወቀውን ሰይጣን የሸመቀውን ከጠላት የተንኮል እንቆቅልሽ ሁሉ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል የደስታ መልስ ይሁንልን!

አ.አ ኢትዮጵያ
ተክለ ኤል ኃይለ ማርያም
ሰኔ ፲ ፪ ቀን /፳ ፻ ፲ ፫ ዓ.ም
የዘማሪ ዳዊት ክብሩ Zemari Dawit Kibru Official Telegram Channel
Photo
“ስለ እናንተ ሲያማልዱ፥ በእናንተ ላይ ከሚሆነው ከሚበልጠው ከእግዚአብሔር ጸጋ የተነሣ ይናፍቁአችኋል።” (ቅዱስ ጳውሎስ 2ኛ ቆሮ 9፥14)
--------------------------------

☞ ጻድቃን "አያማልዱም" የሚለውን ክርክር ተወውና የዘፍጥረትን መጽሐፍ ገልጠህ ፈጣሪህን ጠይቅ። ደጋጎች አይደለም ማልደው ለጥፋት በተዘጋጀች ከተማ ቢኖሩ እንኳን በከተማይቱ ስለመኖራቸው ብሎ ምሕረትን ያወርዳል።

☞ እግዚአብሔር ሰዶምና ገሞራን በኃጢአታቸው ምክንያት በእሳትና በዲን አቃጥሎ ከመቅጣቱ አስቀድሞ ለወዳጁ ለአብርሃም "እኔ የማደርገውን ከአብርሃም እሰውራለሁን? አብርሃም በእውነት ታላቅና ብርቱ ሕዝብ ይሆናልና፥ የምድር አሕዛብም ሁሉ በእርሱ ይባረካሉና። ጽድቅንና ፍርድን በማድረግ የእግዚአብሔርን መንገድ ይጠብቁ ዘንድ ልጆቹንና ከእርሱ በኋላ ቤቱን እንዲያዝዝ አውቃለሁና፤ ይህም እግዚአብሔር በአብርሃም ላይ የተናገረውን ነገር ሁሉ ያመጣ ዘንድ ነው።" ካለ በኋላ "የሰዶምና የገሞራ ጩኸት እጅግ በዝቶአልና፥ ኃጢአታቸውም እጅግ ከብዳለችና፥ እንግዲህስ ወደ እኔ እንደ መጣች እንደ ጩኸትዋ አድርገው እንደ ሆነ ወርጄ አያለሁ፤ እንዲሁም ባይሆን አውቃለሁ።" በማለት ነገረው። ይህ ነገር በእግዚአብሔር የተነገረው አብርሃም ደጋግሞ ምን ብሎ እንደጸለየ ታስተውላለህን? "አምሳ ጻድቃን በከተማይቱ ውስጥ ቢገኙ በውኑ ሁሉን ታጠፋለህን? ከተማይቱንስ በእርስዋ ስለሚገኙ አምሳ ጻድቃን አትምርምን?"….... ዳግመኛም "ከአምሳው ጻድቃን አምስት ቢጐድሉ ከተማይቱን ሁሉ በአምስቱ ምክንያት ታጠፋለህን? "… ሦስተኛም "ጌታዬ አይቆጣ እኔም እናገራለሁ፤ ምናልባት ከዚያ ሠላሳ ቢገኙሳ?… አራተኛም፦ "እኔ ደግሞ አንድ ጊዜ ብቻ ብናገር ጌታዬ አይቆጣ፤ ምናልባት ከዚያ አሥር ቢገኙሳ?" አለ።" ቅዱሱ ሰው አብርሃም በመጨረሻ የጸለየውን ጸሎት ልብ በል "በእነዚህ በሁለት ታላላቅ ከተሞች አሥር ጻድቃንን ብታገኝ አትምርምን?" የሚል ነው። እግዚአብሔር ምን ብሎ የመለሰ ይመስልሃል? "አምሳ ሳይሆን አሥርም ጻድቃን ባገኝ እምራለሁ!!!" (ዘፍ 18:17-25)

☞ እስቲ ልጠይቅህ ዛሬ ግብረ ሰዶማዊነት የት ደርሶዋል? በደጅህ አልደረሰምን? ለቀደሙት ስለገባው ቃልኪዳን ታግሦዋል እንጂ ሰዶማውያኑ በጠፉበት ግብረ ሰዶም ዓለሙ ይጠፋ እንደነበር የታወቀ ነው። ጠቢቡ ሰሎሞን “ጻድቃን በበዙ ጊዜ ሕዝብ ደስ ይለዋል።” (ምሳ 29፥2) ብሎ ለምን ተናገረ? በጻድቃን ብዛት ሀገር እንደምትድን በተረዳ ነገር ስላወቀ አይደለምን?

☞ የጻድቃን ልመና ብቻ ሳይሆን መኖር እንኳን ከጥፋት ይታደግሃል። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “እነዚያ ቀኖችስ ባያጥሩ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም ነበር፤ ነገር ግን እነዚያ ቀኖች ስለ ተመረጡት ሰዎች ያጥራሉ።” ብሎ በምሥጢረ ምጽዓት ትምህርቱ እንዳስተማረ። (ማቴ 24፥22) እግዚአብሔር ለወዳጆቹ በሚገባው ቃልኪዳን ቁጣውን በምሕረት በትእግሥት እንደሚለውጥ መከራውን እንደሚያሳጥር ይህ የጌታ ቃል ምስክር ነው። ዓለም አልገባውም እንጂ ሐሳዊ መሲሕ የሚሠለጥንባቸው እነዚያ አስጨናቂ ወራት እንኳን የሚያጥሩት በጽኑ እምነታቸው በቀና ምግባራቸው እርሱን ላስደሰቱት ወዳጆቹ በገባው ቃልኪዳን ነው።

መድኅን ዓለም ክርስቶስ ሕያዋን ቅዱሳኑን "ሙታን" ለሚሉ ሰዱቃውያን “እኔ የአብርሃም አምላክ፥ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ የሚል ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ እናንተ የተባለውን አላነበባችሁምን? የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም።” ብሎ የተናገረውን ቃል ልብ በልና ሙታን እንደሌሉን አውቀህ ወደ ሕይወት የተሻገሩበትን የዕረፍታቸውን ቀን እንደ ዳዊት “የቅዱሳኑ ሞት በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው።” (መዝ116፥15) እያልክ እየዘመርክ አክብር። (ማቴ 22፥31-32)

እባክዎን ቃለ እግዚአብሔርን በማጋራት ለወዳጆችዎ ያድርሱ።

ቢትወደድ ወርቁ
ሠኔ 24 ቀን 2017 ዓ ም
(ሥዕለ ተክለ ሃይማኖት በ Coptic ቤተ ክርስቲያን ሠዐሊ ዐይን)
በዚህ ዕለት ሐምሌ 7 ቀን #ቅድስት_ሥላሴ በአብርሃም ቤት የገቡበት እና ሣራ ይስሐቅን እንደምትወልድ የተናገረበት ዕለት ነው፡፡

ዳግመኛም በዚህ ዕለት ልደቱ እና ዕረፍቱ በአንድ ቀን የገጠመለት የእመቤታችን ወዳጅ ፣ ኢትዮጲያዊው ቄርሎስ የተባለ የሃይማኖት ጠበቃ ፣ ቅዱስ እና ሊቅ #አባ_ጊዮርግስ_ዘጋስጫ ዓመታዊ ክብረ በዓል ነው።

#ቅድስት_ሥላሴ

አባታችን አብርሃም ከተመሳቀለ ጐዳና ላይ ድንኳን ሠርቶ መንገደኞችን ዅሉ በእንግድነት እየተቀበለ ሲያስተናግድ ይኖር ነበር፡፡ ጥንተ ጠላታችን ሰይጣን ለተንኮል አያርፍምና ይህንን መልካም ግብሩን ለማሰናክል አሰበ፡፡ አስቦም አልቀረ፤ የተጐዳ ሰው መስሎ ከጐዳና ቆሞ አብርሃም እንግዳ መቀበል እንደ ተወ፤ እርሱ ሊበላ ሊጠጣ ከቤቱ ቢሔድ ራሱን ፈንክቶ፣ ደሙን አፍሶ፣ አጥንቱን ከስክሶ፣ ልብሱን ገፎ እንደ መለሰው ወደ አብርሃም ቤት ለሚሔዱ ሰዎች ይናገር ጀመር፡፡ በዚህ የተነሣም እንግዳ ወደ አብርሃም ቤት አልመጣ አለ፡፡ በዚህ ጊዜ አብርሃምም ማዕደ እግዚአብሔርን ያለ ምስክር (ያለ እንግዳ) አልመገብም ብሎ ሦስት ቀን ሳይመገብ ጾሙን አደረ፡፡ በሦስተኛው ቀን ይህን ደግነቱን እግዚአብሔር ተመልክቶ በሦስት ሰዎች አምሳል አንድም በሥላሴው (በሦስትነቱ) ከአብርሃም ቤት ገብቷል (ቅዳሴ ማርያም አንድምታ ትርጓሜ፣ 4 ፥32 )፡፡

በኦሪት ዘፍጥረት 18 ፥ 1 -19 ተጽፎ እንደምናገኘው በቀትር ጊዜ አብርሃም በድንኳኑ ደጃፍ ተቀምጦ ሳለ እግዚአብሔር በሦስት ሰዎች አምሳል በመምሬ አድባር ዛፍ ተገልጦለታል፡፡ አብርሃምም ሦስት ሰዎች ቆመው ባየ ጊዜ ሊቀበላቸው ከድንኳኑ ደጃፍ ተነሥቶ ወደ እነርሱ ሮጠ፡፡ ወደ ምድርም ሰገደና ‹‹አቤቱ በፊትህስ ሞገስ አግኝቼ እንደ ኾነ ባርያህን አትለፈኝ?›› ብሎ ተማጸነ፡፡ በመቀጠል አብርሃም ‹‹ጥቂት ውኃ ይምጣላችሁ፤ እግራችሁን ታጠቡ፤ ከዚህችም ዛፍ በታች ዕረፉ፡፡ ቍራሽ እንጀራም ላምጣላችሁ፤ ልባችሁንም ደግፉ፡፡ ከዚያም በኋላ ትሔዳላችሁ፡፡ ስለዚህ ወደ ባርያችሁ መጥታችኋልና›› ሲላቸው እነርሱም ‹‹እንዳልህ አድርግ›› ብለውታል፡፡

ከዚያ በኋላ እግዚአብሔር አብርሃምን ጠርቶ ‹‹ሚስትህ ሣራ ወዴት ናት?›› አለው፡፡ አብርሃምም ከድንኳኑ ውስጥ እንዳለች ነገረው፡፡ እግዚአብሔርም ‹‹የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ጊዜ ወደ አንተ በእውነት እመለሳለሁ፤ ሚስትህ ሣራም ልጅን ታገኛለች›› ብሎ ለአብርሃም አበሠረው፡፡ ሣራ ይህንን ቃል በሰማች ጊዜ ባለቤቷም አርጅቶ፤ እርሷም የሴቶች ግዳጅ ትቷት ነበርና ‹‹‹ሲያረጁ አምባር ይዋጁ› እንዲሉ ‹‹እስከ ዛሬ ድረስ ቆንጆ ነኝን? ጌታዬ አብርሃምስ ገና ጐረምሳ ነውን?›› ብላ በማሰቧና መውለዷን በመጠራጠሯ ሳቀች፡፡ እግዚአብሔርም ምሥጢሩን በአጽንዖት ለማስረዳትና አስረግጦ ለመንገር አብርሃምን ‹‹ሣራ ለምን ትስቃለች? በውኑ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን?›› አለው፡፡ ሣራም ስለፈራች ‹‹አልሳቅሁም›› አለች፡፡ እግዚአብሔርም መሳቋን እንዳወቀባት ከነገራት በኋላ በድጋሜ በዓመቱ ወደ አብርሃም ቤት እንደሚመጣና ሣራ ወንድ ልጅ (ይስሐቅን) እንደምትወልድ አብሥሯቸዋል፡፡

የቅድስት ሥላሴ ረድኤታቸው አይየን!
የቅዱስ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ አማላጅነቱ አትለየን ። ሀገራችንን ቅድስት ኢትዮጺያን ሊለያይ የሚሽቀዳደመውን ዲያብሎስን በመስቀሉ ይምታልን።

©️ ዮቶር ደሳለኝ
#መልካም_በዓል
#ጸልዩ_በእንተ_ቤተክርስቲያን_ቅድስት@zdk24_5_21_official