"፩ እምነት" ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ Channel
20.3K subscribers
3.73K photos
35 videos
29 files
498 links
This is a channel dedicated to sharing Orthodox Christian teachings and programs.

Among these are:

➯ Commemoration of the Saints (daily synaxarium), religious teachings, hymns, various Orthodox PDFs,
current Orthodox Christian information, etc.
Download Telegram
...የሚወድቀውን የአካል ቊራጭ እያነሳች በልብሷ ትቋጥረው ነበር። በዚህ ዓይነት ችግርና ፀሐይ ሐሩር የብዙ ጐዳና ጉዞ ተጉዛ ከአሰበችበት አገር ደረሰች። በደብረ ሊባኖስ አቅራቢያ ወይም አካባቢ ስትደርስ የራስ ፀጒራን ይዛው በነበረ ምላጭ ላጨች ልብሷንም አውልቃ ለነዳያን አከፋፈለች የያዘችውንም ገንዘብ በመንገድ ላይ ላገኘችው ሁሉ መፅውታ ጨረሰች። ከዚያም አስቀድማ ያዘጋጀችውን ልብስ ምንኵስና ማለት ቀሚስዋን አጥልቃ አጽፋን ተጐናጽፋ ቆቧን ደፍታ ደብረ ሊባኖስ ከሴቶች ገዳም ደረሰች። የገዳሙ መነኰሳትም በታላቅ ክብር ተቀብለው ወደበዓታቸው አስገቧት...

➯እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ለሳጥናኤል ምሕረት እንደለመነች፦ ከዕለታት በአንድኛው ቀን እናታችን ክርስቶስ ሠምራ ጓንጉት በምትባል ደሴት ውስጥ ዓርብ ዕለት ከቀኑ በስድስት ሰዓት ላይ ስለሰው ልጆች ስትጸልይ ሣለ። ዓለሙ ሁሉ ከንቱ እንደሆነና የሰውም ልጅ ሕይወት እንደጥላ ኃላፊ ጠፊ መሆኑን ፈጽማ ተመለከተች። ነቢዩ ዳዊት "ሰው ከንቱ ነገርን ይመስላል ዘመኑ ወይም ሕይወቱ እንደጥላ ያልፋል" ሲል ተናግሯልና። ዳግመኛም "ሰው ክብር እንኳ ቢሆን ሊኖር አይችልም እንደሚጠፋ ወይም ማስተዋል እንደሌለው እንስሶች መሰለ...አለ ክቡር ዳዊት። ስለዚህም ሁሉ ነገር አቤቱ ማራቸው ይቅርም በላቸው መፃተኛዋ ባሪያህንም ኃጢአቷን አታስብባት እያለች ወደፈጣሪዋ መሪር ዕንባን አለቀሰች። ያን ጊዜ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በታላቅ ግርማ ወደስዋ መጣ። በታላቅ ግርማ ሆኖ ባየችውም ጊዜ ደነገፀች ከእግሩ ሥርም ወደቀች። ከዚህ በኋላ ነውር በሌለባቸው ንዑዳት ክቡራንና ንጹሐን በሆነ እጆቹ አነሣት። ቀጥሎም "ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ አትደንግጭ ነገር ግን የልብሽን ሃሳብ ንገሪኝ" አላት። እስዋም "አቤቱ ባሪያህንስ በባለሟልነት ካሠለጠንካት አባታችን አዳምን በአርአያህና በአምሣልህ ስለምን ፈጠርከርው። በእንጨት መስቀልስ ላይ ለምን ተሰቀልክ ስለአዳምና ስለልጆቹ አይደለምን?" አለችው። "አዋን ስለነሱ ስል ተሰቅያለሁ" አላት። "እግዲያውስ መሰቀልህ ወይም የተሰቀልከው ስለነሱ ከሆነ ከአቤል ጀምሮ እስከ ዛሬ የሞቱን ከዛሬም በኋላ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ የሚሞቱትን አቤቱ ማራቸው ይቅርም በላቸው" አለችው። "አንተ ቸር ይቅር ባይ መዓትህ የራቀ ምሕረትህ የበዛ ነህና ከአንተ ሌላ አምላክ የሌለ እውነተኛ አምላክ ነህ ሁሉ ይቻልሃልና የሚሣንህ ነገር ከቶ የለምና ዓለም በጠቅላላዋ በእፍኝህ አትሞላም" በማለት እያለቀሰች ለመነችው። በዚያ ጊዜ ጌታ መልሶ "ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ እስኪ አንቺ ራስሽ ፍረጅ አዳም ከነልጆቹ ከሠራው ኃጢአት እና እኔ በጰንጤናዊው በጲላጦስ ዘመን በቀያፋና በሐና አደባባይ በዕለተ ዓርብ ከተቀበልኩት ሕማማተ መስቀል ቢመዘን የትኛው ይመዝን ይመስልሻል?" አላት። ይህንም ባላት ጊዜ ደነገጠችና ከመሬት ላይ ወደቀች። በዚህ ጊዜ ቅዱሳት በሆኑ እጆቹ ከወደቀችበት አነሣትና "እንግዲህ ይህን ሁሉ መከራ የተቀበልኩ ለማን ወይም በማን ምክንያት ይመስልሻል" አላት።

➯ጌታም "ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ እስኪ የልብሽን ሃሳብ ወይም ፍላጐትሽን ንገሪኝ" አላት። በዚህን ጊዜ "አቤቱ ፈጣሪየ ፈቃድህስ ቢሆን የአዳም ልጆች ከሥቃይ ከኵነኔ ይድኑ ዘንድ ዲያብሎስን ይቅር ትለው ወይም ትምረው ዘንድ እለምንሃለሁ። የኃጥእን መመለሱን እንጂ ጥፋቱን አትወድምና" አለችው። "የምለምንህ ወይም ማረው የምልህ ዲያብሎስን ወድጄው አይደለም ነገር ግን እርሱ ከተማረ በአዳም ልጆች ላይ ሥቃይና ኵነኔ ሊኖር አይችልም ብየ በመገመት እንጂ። የነሱ ሥጋ ሥጋየ እንደሆመኑ መጠን የኔም ሥጋ ሥጋህ ነውና" አለችው። ይህንም ባለችው ጊዜ ጌታ ፍግግ ብሎ "ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ ሌሎች ካንቺ በፊት የነበሩ ካንቺም በኋላ የሚነሱ የማያስቡትን እጅግ የሚያስደንቅ ልመና አቀረብሽ" አላት። ይህንም ካለ በኋላ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ጠርቶ "ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ዲያብሎስን ማርልኝ ስትል ልመና አቅርባለችና እሺ ካላት ታወጣው በንድ ወደሲዖል ይዘሃት ሂድ" ብሎ አዘዘው። በዚህ ጊዜ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል እሺ ብሎ ሰግዶ እጅ ነሥቶ ወደሲዖል ይዞአት ሄደ። አብረው በሚጓዙበትም ጊዜ "እንግዲህ ዲያብሎስ ከታረቀ ወይም ከተማረ የሰው ልጆች ሁሉ ያርፋሉ" እያለች ለመላእክት አለቃ ለቅዱስ ሚካኤል ታሳስበው ነበር። ይህን አምላክነትን ሲሻ ከክብሩ የተዋረደ ዲያብሎስ ምሕረት ለማግኘት ይሻ መስሏት ነበርና።

➯ከሲዖል አፋፍ በደረሱም ጊዜ የተመለከተችው ሥቃይ ተነግሮ የማያልቅ ነው ሰዎች ከሰዎች ጋር እንደውሻ ይናከሱ ነበር። የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል "ምሕረት የሚፈልግ ከሆነ እስኪ በይ ዲያብሎስ ብለሽ ጥሪው" አላት። በዚህ ጊዜ በመላእክት ቋንቋ ሦስት ጊዜ "ሣጥናኤል ሣጥናኤል ሳጥናኤል" በማለት ጠራችው። ዲያብሎስም "ከዚህ በብዙ ሠራዊት ላይ ነግሼ ከምኖርበት አገር ማን ነው እሱ የሚጠራኝ" እያለ በታላቅ ቃል አሰምቶ ተናገረ። ከዚህም በኋላ "ለብዙ ዘመን ስፈልግሽ ወይም ሳድንሽ ቆይቼ ነበር ዛሬ ግን ከምኖርበት ቤቴ ድረስ መጣሽን" አላት። እርሷም "ጌታ ይቅርታ አድርጓልሃልና ከዚህ ከሥቃይና ከመከራ ቦታ ከወገኖችህ ጋራ ና ፈጥነህ ውጣ" አለችው። ይህንም በለችው ጊዜ ልቡ እንደ እሳት ነደደ አፈፍ ብሎ ተረማምዶ በግራ እጁዋን ይዞ ከሲዖል ረግረግ ውስጥ ወረወራት። በዚያን ጊዜ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል የእሳት ሰይፍ ይዞ ከኋላ ከኋላዋ ይከተላት ነበርና ይህን ምሕረት የሌለው ዕቡይ ዲያብሎስ በያዘው ሰይፍ ቢቀጣው የሲዖል ደጃፍ ተከፈተች። በዚህ ሰዓት ታላቅ ጨኸትና ውካታ ወይም መደበላለቅ ሆነ በሲዖል ያሉ የሰዎች ነፍሳት እንደንብ ከበቧት ወይም ሠፈሩባት። በዚያን ጊዜ በቅዱስ ሚካኤል ክንፍና በስዋም በተሰጣት ክንፈ ረድኤት ከሲዖል የወጡት ነፍሳት ቁጥር ዓሥር ሺህ ያህል ነበር። እነዚህ ከመከራ ያመለጡ ከሥቃይ የወጡ ነፍሳትን ባየች ጊዜ እጅግ አድርጋ ተደሰተች ከደስታዋም ብዛት የተነሣ የእናቱን ጡት እየጠባ እንደሚዘል እምቦሳ ጥጃ በመካከላቸው ትዘል ነበር።

➯ከዚህም በኋላ ወደ ፈጣሪዋ ሄዳ "አቤቱ ፍርድህ ከቶ እንደዚህ ነውን?" እያለች አደነቀች።ጌታም "ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ ዲያብሎስን ድል አድርገሽ ጥቂት ምርኮን አገኘሽን" አላት። እስዋም "አዋ ጌታዬ በኃይልህና በቸርነትህ አገኘሁ" አለችው። ከዚህ በኋላ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሚካኤል ጠርቶ "እሊህን ነፍሳት ዓለም ሳይፈጠር ወደ አዘጋጀሁላት ወደ ክርስቶስ ሠምራ መኖሪያ ቦታ ውሰዳቸው" አለው። በዚህ ጊዜ "አቤቱ ፈጣሪየ የእኔ መኖሪያየ ወዴት ነው?" አለችው። ጌታም "መኖሪያሽ ከእናቴ ከድንግል ማርያም ጋራ ነው እነሆ በትረ ማርያም ብየ ሰየምኩሽ መቀመጫሽን ወይም ደረጃሽን ከእርስዋ ቀጥሎ ሁለተኛ አደረግሁልሽ የባለሟልነት ግርማ አጐናጸፍኩሽ አንቺን የሚወዱ ሁሉ የተመሰገኑ ናቸው" አላት። ይህንም ባላት ጊዜ ፈጽማ ደስ ተሰኘች ወደ ኋላዋም መለስ ብላ ብትመለከት ለዓይን የሚያንፀባርቁ ዓሥር አክሊላት አየች። በየአንዳንዳቸው አክሉል ላይ ዐራት ከዋክብት አሉባቸው የእሊህ ከዋክብት ቊጥራቸው ሲደመር አርባ ይሆናል። በዚህ ጊዜ ከስዋ ጋራ የነበረውን መልአክ "እሊህ በላያቸው ብርሃናውያን ከዋክብት ያሉባቸው አክሊላት ለማን የተዘጋጁ ናቸው ሰውነቴ እጅግ አድርጋ ወዳቸዋለችና" አለችው። የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም "ላንቺ ቢሆን ደስ አይልሽምን?" አላት። እርስዋም "አዎን ጌታየ ለኔ ቢሆን እወዳለሁ"አለችው። "እንግዲያስ ላንቺ የተዘጋጁ ናቸው" አላት።...
.....➯"በምን ሥራዬ ለኔ ተሰጡኝ" አለችው። "ዐሠርቱ ቃላት ኦሪትን ስድስቱን ቃላተ ወንጌል ጠብቀሽ ቤትሽን ጥለሽ ይህን ዓለም ንቀሽ አጥቅተሽ የክርስቶስን ቀምበር ተሸክመሽ ፈጣሪሽን ስለተከተልሽው ነው" አላት። ይህንንም በአላት ጊዜ እጅግ አድርጋ ተደሰተች ሁሉን ማድረግ የሚችል እግዚአብሔርንም ፈጽማ አመሰገነች።
#ቅዱስ_ቶማስ_ዘመርዓስ

➯ዳግመኛም በዚህች ቀን የክርስቶስ ምስክሩና ሐዋርያው የሆነ የመርዓስ ኤጲስቆጶስ ተጋዳይ ቅዱስ አባት ቶማስ አረፈ። የዚህንም አባት ትሩፋቱንና ገድሉን ሰው ተናግሮ ሊፈጽመው አይችልም እርሱ አስቀድሞ በጾም በጸሎት በስጊድ ቀንና ሌሊትም በመራራት ተጠምዶ የሚኖር ነው ። ከዚህም በኃላ መርዓስ ለሚባል አገር ኤጲስቆጶስ ይሆን ዘንድ የክብር ባለቤት ጌታችን መረጠው መንጋውንም እንደ ሐዋርያት ጠበቀ። ከሀዲ ዲዮቅልጥያኖስም በነገሠ ጊዜ ክርስቲያኖችን ያሠቃያቸው ዘንድ ከመኳንቶቹ አንዱ ወደዚያች አገር ደረሰ እርሱም ቅዱስ ቶማስን ወደርሱ ያቀርቡት ዘንድ ጭፍሪቹን ላከ እነርሱም እየደበደቡ በምድር ላይ እየጎተቱ ወሰዱት ደሙም እንደውኃ ፈሰሰ።

➯ከዚህም በኃላ መኮንኑ ቅዱስ ቶማስን ለአማልክት ስገድ አለው ቅዱሱም እንዲህ ብሎ መለሰለት እኔ ከሕያው እግዚአብሔር ልጅ ከጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ለረከሱ ጣዖታት የሚሰግድ ሁሉ የተረገመ ነውና።

➯መኰንኑም ተቆጥቶ እጅግ የበዛና ዕፁብ ድንቅ የሆነ ሥቃይን አሠቃየው የነዳጅ ድፍድፍና አፍልተው በላዩ በአፉና በአፍንጫው ውስጥ ጨመሩ እንዲህም እያደረጉበት እስከ ብዙ ዘመናት ኖረ።

➯የእሊህ ከሀዲያን ልባቸው እንደ ድንጊያ የጸና ስለሆነ ቅዱስ ቶማስ ቶሎ እንዲሞት አልፈለጉም። ሌሎች ብዙዎች ሰዎችን ያሰፈሩአቸው ዘንድ የክብር ባለቤት ክርስቶስንም ይክዱት ዘንድ የሥቃዩን ዘመን አስረዘሙ እንጂ።

➯እርሱ የክብር ባለቤት በሆነ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል የጸና ነውና ማሠቃየቱን ከሀድያን በተቸነፉ ጊዜ ስለ ስሕተታቸውም ይዘልፋቸው ስለነበር ስለዚህ በጨለማ ቦታ ጣሉት በዚያም ሃያ ሁለት ዓመት ኖረ።

➯ከሀድያንም በየዓመቱ ወደርሱ ገብተው ከሕዋሳቱ አንዱን ይቆርጣሉ። በዚያም ቦታ አፍንጫውን ከንፈሮቹን ጆሮዎቹን እጆቹንና እግሮቹን ቆረጡ መንጋዎቹም ያረፈ መስሏቸው በየዓመቱ መታሰቢያውን ሲያደርጉ ኖሩ። ነገር ግን አንዲት ክርስቲያናዊት ሴት በጣሉት ጊዜ ስለአየችው ቦታውን ታውቅ ነበር እርሷ በሌሊት ወደርሱ ተሠውራ በመሔድ ትመግበዋለች ። ጻድቅ ቁስጠንጢኖስም እስከ ነገሠና የቀናች የክርስቶስን ሃይማኖት ክብር እስከ ገለጠ ድረስ እንዲህ ሲሠቃይ ኖረ።

➯ይህም ንጉሥ ክርስቶስን በመታመን የታሠሩ እሥረኞችን ሁሉ በሀገሮች ሁሉ በወህኒ ቤት ያሉትን ይፈቷቸው ዘንድ አዘዘ።

➯ይችም ሴት ሒዳ ስለ ቅዱስ ቶማስ ከእርሱ የሆነውን ሃያ ሁለት ዓመት ተጥሎ እንደኖረ ለካህናቱ ነገረቻቸው በውስጡ ወደሚኖርበትም ቦታ መራቻቸው። እነርሱም አንሥተው ተሸከሙት እየዘመሩና እያመሰገኑ ወደ ቤተ ክርስቲያን አደረሱት በቤተ መቅደሱም ፊት ለፊት በወንበሩ ላይ አስቀመጡት ምእመናንም ሁሉ ወደርሱ እየመጡ ከእርሱ ይባረኩና የተቆረጡ ሕዋሳቱን ይሳለሙ ነበር።

➯ንጉሥ ቂስጠንጢኖስም የከበሩ የሦስት መቶ ዐሥራ ስምንት ኤጲስቆጶሳትን የአንድነት ጉባኤን በኒቅያ አገር በሰበሰበ ጊዜ ይህ የከበረ ቶማስ ከእሳቸው አንዱ ነው።

➯ንጉሡም ወደ እንርሱ ገብቶ ሰላምታ ሰጣቸውና ከእርሳቸውም ቡራኬ ተቀበለ። የዚህ የቅዱስ ቶማስን ተጋድሎውን በነገሩት ጊዜ ወደርሱ ቀርቦ ሰገደለት ሕዋሰቱም ከተቆረጡበት ላይ ተሳለመው አዝኖና እጅግም አድንቆ ሕዋሳቱን ዳሠሠው ፊቱንና ዐይኖቹን አሻሸው።

➯ከሀዲ አርዮስንም ተከራክረው ከረቱ በኃላ አውግዘው ለይተው ከወገኖቹ ጋር ከቤተ ክርስቲያን አሳደዱት። ከዚህም በኃላ መንፈስ ቅዱስ እንደ አስተማራቸውና እንደመራቸው የሃይማኖትን ትምህርት በአንደበታቸው ተናገሩ ሕግና ሥርዓትን ሥጋዊና መንፈሳዊ ፍርድንም ሠሩ።

➯ከዚህም በኋላ ቅዱስ ቶማስ ወደ መንበረ ሢመቱ ሔደ ካህናቱንና መንጋዎቹን ሁሉ ሰብስቦ አነበበላቸው እርሱንም እንዲአስተውሉት እንዲጠብቁትም በመጠበቅም እንዲጸኑ አዘዛቸው። ጥቂት ዘመናትም ከኖረ በኃላ በሰላም በፍቅር አረፈ የሹመቱም ዘመን አርባ ዓመት ነው በዚህም እግዚአብሔርን አገለገለው።


➯ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን። በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

መጋቢት 24 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

1.ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት (ጽንሰቱ)
2.ቅዱሳን እግዚእ ኃረያና ጸጋ ዘአብ
3.ቅዱስ አባ መቃርስ ሊቀ ጳጳሳት

ወርኀዊ በዓላት

1.ቅዱስ አጋቢጦስ ጻድቅ
2.ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
3.ቅዱስ ሙሴ ፀሊም
4.ቅዱስ ቶማስ ዘመርዐስ
5.ቅዱስ አብላርዮስ ታላቁ
6.ሃያ አራቱ ካኅናተ ሰማይ

➯"በረከት በጻድቅ ሰው ራስ ላይ ነው። የኀጥአንን አፍ ግን ግፍ ይከድነዋል። የጻድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነው። የኀጥአን ስም ግን ይጠፋል።"
(ምሳሌ ፲፥፮/10:6)

#ስንክሳር ነሐሴ 24 እና #ገድለ_ቅድስት_ክርስቶስ_ሠምራ

@AndEmnet
"፩ እምነት" ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ Channel pinned «#ዝክረ_ነሐሴ_24/፳፬ (ስንክሳር) እንኳን ለታላቁ ለከበረ ለሐዲስ ሐዋርያ #ለአባታችን_ተክለሃይማኖት ለዕረፍታቸው፣ ለከበረች #ለቅድስት_ክርስቶስ_ሠምራ ለዕረፍቷ መታሰቢያ፣ የክርስቶስ የመርዓስ ኤጲስቆጶስ #ለቅዱስ_አባት_ቶማስ ለእረፍቱ መታሰቢያ በዓል በሰላም አደረሳችሁ አደረሰን። "በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።" #ጻድቁ_አቡነ_ተክለሃይማኖት ➯ነሐሴ ሃያ አራት በዚህችም…»
#ዝክረ_ቅዱሳን_ነሐሴ_26/፳፮ (ስንክሳር)

እንኳን ለአብርሃም ሚስት ለተመሰገነች #ለቅድስት_ሣራ ለመታሰቢያዋ፣ ለከበረ #ለአባ_ሞይስስና_እኅቱ_ሣራ በሰማዕትነት ላረፉበት፣ ለከበሩ መነኰሳት #ለቅዱሳን_አጋቦስና_ቴክላ በሰማዕትነት ላረፉበት፣ ለከበሩ አባቶቻችን #ለአቡነ_ኢየሱስ_ሞዐ እና #ለአቡነ_ሀብተ_ማርያም ለተፀነሱበት ዕለት መታሰቢያ በዓል በሰላም አደረሳችሁ አደረሰን፡፡

"በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።"

#ቅድስት_ሣራ (ስንክሳር)

➯ነሐሴ ሃያ ስድስት በዚህች ቀን ለአብርሃም ሚስት ለተመሰገነች ሣራ መታሰቢያዋን እናደርግ ዘንድ የቤተ ክርስቲያን መምህራን አባቶች አዘዙ።

➯ይቺንም ክብርተ ማሕፀን የሆነች ጡቶቿም የተባረኩ ክብርት ሣራን የጌራራ ንጉሥ አቤሜሌክ ባል እንዳላት ሳያውቅ በወሰዳት ጊዜ እንዳይቀርባት እግዚአብሔር ገሠጸው በደዌም ቀሠፈው ባሏ አብርሃምም በጸለየለት ጊዜ ከደዌው ተፈወሰ ከዚህም በኋላ ከብዙ ገንዘብ ጋራ ወደ ባሏ መለሳት።

➯ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር በሦስትነቱ ተገልጦ ወደ ቤቷ እንግድነት በመጣ ጊዜ ለአብርሃምም የይስሐቅን መወለድ በነገረው ጊዜ ሣራም በድንኳኑ ውስጥ ሳቀች እንዲህ ስትል እስከ ዛሬ ገና ነኝን ጌታዬም አርጅቷል።

➯እግዚአብሔርም አብርሃምን እንዲህ አለው ሣራን ለብቻዋ ምን አሳቃት እስከ ዛሬ ገና ነኝን ጌታዬም አርጅቷል እኔም አሁን አርጅቻለሁ ብላ በውኑ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን። ከዚህም በኋላ ሣራ ፀንሳ እግዚአብሔር ባለው ወራት በርጅናዋ ለአብርሃም ወንድ ልጅን ወለደች።

➯ይስሐቅም በአደገ ጊዜ ልጅዋ ይስሐቅን ከእስማኤል ጋራ ሲጫወት አየችው። አብርሃምንም ሣራ እንዲህ አለችው ይቺን ባሪያ ከነልጅዋ አባራት የባሪያ ልጅ ከልጄ ከይስሐቅ ጋራ አይወርስምና። ይህም ነገር ለአብርሃም ስለ ልጁ እስማኤል እጅግ ጭንቅ ሆነበት።

➯እግዚአብሔርም አብርሃምን እንዲህ አለው የዚህ ልጅ የዚችም ባሪያ ነገር በፊትህ ጭንቅ አይሁንብህ የምትልህን ሁሉ ሣራን ስማት ከይስሐቅ ዘር ይተካልሃልና።

➯ይህም ነገር ታላቅ ምሥጢር አለው የተመሰገነ ጳውሎስ ቅድስት ሣራን የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ አድርጓታልና። ከዚህም በኋላ በበጎ እርጅና በአረፈች ጊዜ ከኬጢያዊ ኤሞር ልጆች በገዛው ቦታ ቀበራት።
#ቅዱሳን_ሞይስስና_እህቱ_ሣራ (ስንክሳር)

➯በዚህች ቀን የከበረ አባ ሞይስስና እኅቱ ሣራ በሰማዕትነት ሞቱ። የእሊህም ቅዱሳን ወላጆቻቸው ደጎች እጅግም ባለጸጎች ናቸው። የከበረ ሞይስስ ወላጆቹ ከአረፉ በኋላ እኅቱ ሣራን ሊአጋባትና ወላጆቹ የተዉትን ገንዘብም ሊሰጣት እርሱም ወደ ገዳም ሒዶ ሊመነኵስ አሰበ።

➯ይህን አሳቡንም በነገራት ጊዜ እንዲህ ብላ መለሰችለት እኔን ልታጋባኝ ከወደድክ አስቀድሞ አንተ አግባ አርሱም እንዲህ አላት እኔ ብዙ ኃጢአት ሠርቻለሁ ስለዚህ ኃጢአቴን ለመደምሰስ እመነኵስ ዘንድ እሻለሁ ማግባት አይቻለኝም የነፍሴን መዳኛ አስባለሁ እንጂ ።

➯ሁለተኛም እንዲህ ብላ መለሰችለት አንተ ነፍስህን ስታድን እኔን በዓለም ወጥመድ ውስጥ እንዴት ትጥለኛለህ። እርሱም እንዲህ አላት ምንኵስና ከፈለግሽ ስለ ራስሽ የምታውቂ አንቺ ነሽ እኔም የወደድሺውን አደርግልሻለሁ።

➯እንዲህም አለችው ለነፍስህ የምታደርገውን ለኔም እንዲሁ አድርግ እኛ ሁለታችን ከአንድ ባሕርይ ከአንድ አባት ከአንዲት እናት የተገኘን ነንና የልቧንም ቆራጥነት አይቶ ወዲያውኑ ከእርሷ ጋራ ተነሣ ገንዘባቸውንም ሁሉ ለድኆችና ለምስኪኖች በተኑ።

➯ከዚህም በኋላ እኅቱ ሣራን ወሰዳት ከእስክንድርያ ከተማ ውጭ ወዳለ የደናግል ገዳም ውስጥ አስገባት እርሱም ከወንዶች ገዳም ገብቶ በዚያ ተጋድሎን ተጋደለ። እንዲሁ እኅቱም ጽኑዕ በሆነ ገድል ተጠምዳ እየተጋደለች ሁለቱም ሳይገናኙ ዐሥር ዓመት ኖሩ።

➯በሊቀ ጳጳሳት አባ ድሜጥሮስ የሹመት ዘመን ሳዊርያኖስ የሚባል ከሀዲ ተነሥቶ የክርስቲያንን ወገኖች ማሠቃየት ጀመረ። ከመነኰሳት ገዳማትም ብዙዎች በሰማዕትነት ሞቱ። አባ ሞይስስም ተነሣ ሊሰናበታትም ወደ እኅቱ ሣራ ላከ በሰማዕትነት መሞት እንደሚሻም ነገራት።

➯ሣራ እኅቱም በሰማች ጊዜ ወዲያውኑ ተነሣች ሒዳ በሰማዕትነት ትሞት ዘንድ እንድታሰናብታት እመ ምኔቷን ለመነቻት እመ ምኔቷም ጸለየለችላት ሰላምታም ሰጥታ አሰናበተቻት እርሷም ደናግሉን ሁሉ ተሰናበተቻቸው።

➯ከዚህም በኋላ ወደ ወንድሟ ሔደች በጐዳናም አገኘችውና እርስ በርሳቸው ሰላም ተባባሉ ወደ እስክንድርያ ከተማም ገብተው በመኰንኑ ፊት ቁመው በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመኑ መኰንኑም ጽኑዕ ሥቃይን አሠቃያቸው ከዚህም በኋላ ራሳቸውን በሰይፍ አስቆረጠ። በመንግሥተ ሰማያትም የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበሉ።
#መነኰሳት_አጋቦስና_እህቱ_ቅድስት_ቴክላ (ስንክሳር)

➯በዚህችም ቀን የከበሩ መነኰሳት አጋቦስና ቴክላ በሰማዕትነት ሞቱ። እሊህም ቅዱሳን በከሀዲው ሉልያኖስ ዘመን መከራ በመቀበል ተጋደሉ ። ከመኳንንቶቹም አንዱ ጽኑዕ ሥቃይን አሠቃያቸው ። ሥቃያቸውም በአሰለቸው ጊዜ ለአንበሶች ጣላቸውና ገድላቸውን ፈጽመው የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበሉ።
#አቡነ_ኢየሱስ_ሞዐ (ስንክሳር)

➯በዚህች ቀን አባታቻን አቡነ ኢየሱስ ሞዐ የተፀነሱበት ዕለት ነው፡፡ ቅዱሱ አባት ሀገራቸው ጎንደር ክፍለ ሀገር ስማዳ ወረዳ ሲና ዳኅና በሚባል ቦታ ነሐሴ 26 ቀን ተፀንሰው ግንቦት 26 ቀን 1210 ዓ.ም ከአባታቸው ዘክርስቶስና ከእናታቸው እግዚእ ክብራ ተወለዱ። የተወለዱትም በቅዱስ ነአኲቶ ለአብ ዘመነ መንግስት ነው፡፡ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት የቆብ አባት ሲሆኑ ታላቁን ሐይቅ ቅዱስ እስጢፋኖስን ገዳም የቆረቆሩ ደገኛ አባት ናቸው፡፡

➯ዕድሜያቸው 30 ዓመት እስከሚደርስ ድረስ ከቤተሰቦቻቸው ትምህርተ ሃይማኖትንና ግብረ ገብን ሲማሩ ከቆዩ በኋላ በ1240 ዓ.ም ይህንን ዓለም በመተው ወደ ደብረ ዳሞ ገዳም ገቡ፡፡ በደብረ ዳሞ ገዳም መነኰሳቱን እየረዱ፣ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት እያጠኑ፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን እየገለበጡ ለሰባት ዓመታት ከቆዩ በኋላ የደብረ ዳሞ 3ኛ አበ ምኔት ከሆኑት ከአባ ዮሐኒ እጅ ምንኩስናን በ1247 ዓ.ም ተቀበሉ፡፡

➯አንድ ቀን ሌሊት መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ወደርሳቸው መጥቶ ‹‹የስምህ መክበርያ ወደሆነው ሐይቅ ወደ ተባለው ሥፍራ ሂድ›› አላቸው፡፡ አባታችንም ‹‹ቦታውን እንዴት ዐውቀዋለሁ?›› በማለት መልአኩን ቢጠይቁት ‹‹ተነሥ! ጉዞህን ጀምር ቦታውን እኔ አሳይሃለሁ›› አላቸው፡፡ አባ ኢየሱስ ሞዓ በመልአኩ እንደታዘዙት ከበዓታቸው ተነሥተው ተከተሉት፡፡ የብዙ ወራት መንገድ የሆነውን ጐዳናም በስድስት ሰዓት አደረሳቸው፡፡ በዚያን ወቅት ከሐይቅ ገዳም በስተ ሰሜን ወደነበረው ጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን ደረሱ፡፡ ወደ ሐይቅ እስጢፋኖስ ከመግባታቸው በፊት ለ6 ወራት ያህል በጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን አገልግለዋል፡፡ ያገለግሉበት በነበረው ቤተ ክርስቲያን ቀን ቀን ሕዝቡን ሲያስተምሩ በመዋል ሲመሽ ወደ ሐይቁ በመግባት ሲጸልዩ ያድሩ ነበር፡፡ በሐይቅ እስጢፋኖስና በዙርያው ለነበሩ አበውም ማታ ማታ አንድ ብርሃን ወደ ሐይቁ ሲገባ ጠዋት ጠዋትም ሲወጣ ይታያቸው ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ አባታችን በገዳሙ አባቶች ልመናና በልዑል እግዚአብሔር ትዕዛዝ ወደ ሐይቅ ገዳም ገብተው አበምኔት ሆኑ፡፡........
➯ሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም ከደሴ 30 ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኝ ሲሆን የመሠረቱት ካልዕ ሰላማ የተባሉ ግብፃዊ ጻድቅ ናቸው፡፡ ሐይቅን አባ ሰላማ ካልዕና ዐጼ ድል ነአድ በ862 ዓ.ም ነው የቆረቆሩት። ገዳሙን ካቀኑት በኋላ ‹‹የማንን ታቦት እናስገባ?›› ብለው ሲያስቡ ቶራ የምትባል እንስሳ ጭነት ተጭና ከመካከላቸው ተገኘች፤ ጭነቱን አውርደው ቢያዩት በሐር ጨርቅ የተጠቀለለ የቅዱስ እስጢፋኖስንና የቅዱስ ጊዮርጊስን ሁለት ታቦት አገኙ፡፡ በላዩም ላይ ‹‹ይህንን ታቦት በኢየሩሳሌም የሚኖሩ የተሰወሩ ቅዱሳን ከእግዚአብሔር ታዘው የላኩት ነው›› የሚል ጽሑፍ አገኙ፡፡

➯ይህ ከሆነ ከ400 ዘመን በኋላ ነው አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ወደዚህ ቦታ የመጡት፡፡ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ለ52 ዓመት ቀን ቀን መንፈሳዊ ሥራቸውን እየሠሩ ሌሊት ሌሊት ሐይቁ ውስጥ ቆመው ሲጸልዩ ያድራሉ፡፡ አባ ኢየሱስ ሞዐ በሐይቅ እስጢፋኖስ በአበ ምኔትነት በቆዩባቸው 45 ዓመታት ከየገዳማቱ ቅዱሳን መጻሕፍትን በመገልበጥና በማሰባሰብ የመጀመርያው ዘመናዊ የቤተ ክርስቲያን ቤተ መጻሕፍት በሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም እንዲቋቋም አድርገዋል፡፡ በዚሁ ገዳም ውስጥ የመጀመርያውን የቤተ ክርስቲያን ቋሚ ትምህርት ቤት በማቋቋም 800 መነኮሳትን በትምህርተ ሃይማኖት አሠልጥነው በንቡረ ዕድነት ማዕረግ ሾመው በመላ ሀገራችን እንዲሠማሩ አድርገዋቸዋል፡፡

➯ከእነዚህም ተማሪዎቻቸው መካከል አቡነ ተክለ ሃይማኖት (ደብረ ሊባኖስ)፣ አቡነ ኂሩተ አምላክ (ጣና ሐይቅ ዳጋ እስጢፋኖስ)፣ አቡነ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ (ቦረና)፣ አባ በጸሎተ ሚካኤል (ቦረና)፣ አቡነ ገብረ እንድርያስ (ቦረና)፣ አቡነ ሕዝቅያስ (ቦረና)፣ አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ (ዳውንት)፣ አቡነ አሮን (መቄት- ጣራው ክፍት የሆነው)፣ አቡነ ተክለ ኢየሱስ ሞዐ (ሐይቅ)፣ አቡነ አላኒቆስ (ትግራይ)፣ አቡነ በግዑ (ሐይቅ)፣ አቡነ ሠረቀ ብርሃን (ሐይቅ)፣ አቡነ ብስጣውሮስ (ሐይቅ)፣ አቡነ ዮሴፍ (ላስታ) ዋና ዋናዎቹና በጣም ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ጻደቁን ንጉሥ ዐፄ ይኩኖ አምላክንም በትምህርተ ሃይማኖት አንጸውና ኮትኩተው ያሳደጉት ጻድቁ አባታችን ናቸው፡፡ እነዚህም ልጆቻቸው እያንዳንዳቸው እጅግ አስገራሚ ገድል ያላቸው የከበሩ ቅዱሳን ናቸው፡፡

➯አቡነ ተክለ ሃይማኖት ወደ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ መጥተው በሐይቁ ዳር ቆመው ሳለ ቅዱስ ሚካኤል መጥቶ በእግሩ በውኃው ላይ እየሄደ እያሳያቸው ተከትለውት እንዲሄዱ ነገራቸው። አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖትም ሐይቁን በእግራቸው ተራምደው ተሻግረው አቡነ ኢየሱስ ሞዐን አገኟቸው፡፡ እርሳቸውም አቡነ ተክለ ሃይማኖት ወደ እርሳቸው እየመጡ እንደሆነ በመንፈስ ዐውቀው ነበርና ሲያገኟቸው በጣም ተደስተው ከተቀበሏቸው በኋላ አመነኩሰዋቸዋል፡፡ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ እጅግ በጣም ብዙ መነኮሳትን አፍርተዋል፡፡ የመጀመሪያው መነኩሴ አባ እንጦንስ ነው፡፡ እንጦንስ መቃርስን፣ መቃርስ ጳጉሚስን፣ ጳጉሚስ ቴዎድሮስን፣ አቡነ አረጋዊንና 8ቱን ቅዱሳን አመነኮሱ፡፡ አቡነ አረጋዊም ወደ ኢትዮጵያ በ460 ዓ.ም መጥተው ክርስቶስ ቤዛን፣ አባ ክርስቶስ ቤዛም መስቀለ ሞዐን፣ መስቀለ ሞዐም አባ ዮሐኒን፣ አባ ዮሐኒም አባ ኢየሱስ ሞዐን፣ አባ ኢየሱም ሞዐም አቡነ ተክለ ሃይማኖትን አመነኮሱ፡፡ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ምን ያህል ቀደምትና ባለ ታሪክ አባት እንደሆኑ ከዚህ መረዳት ይቻላል፡፡

➯በዮዲት ጉዲት እጅጉን ተጐድታ የነበረችው ሀገራችን ዳግም የወንጌሉ ብርሃን እንዲበራባት ሊቃውንት፣ እንዳይታጡባት፣ ቅዱሳት መጻሕፍት እንዳይቆነጻጸሉ፣ መነኮሳት አባቶች ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ወርደው ገዳማትን እንዲያስፋፉ ያደረጉት አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ለቤተ ክርስቲያናችንና ለሀገራችን ትልቅ ባለውለታ ናቸው፡፡ በተለይም በሐይቅ እስጢፋኖስ ያፈሯቸውን 800 ሊቃውንት በመላዋ ኢትዮጵያ በመሰማራታቸው ዛሬ የምናያቸውን አብዛኛዎቹን ገዳማትና ቅዱሳት መጻሕፍት አቆይተውልናል፡፡ አባታችን ለ45 ዓመታት ሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳምን በአበ ምኔትነት እያስተዳደሩ ከቆዩ በኋላ ኅዳር 26 ቀን 1292 ዓ.ም በዕለተ እሑድ ዐርፈዋል፡፡ ባረፉበት ዕለትም በወቅቱ በቦታው የታየው ብርሃን ሀገሪቱን መልቶ ታይቷል፡፡
#አቡነ_ሀብተ_ማርያም (ስንክሳር)

➯ዳግመኛም በዚህች ቀን ቅዱስ አባታችን አቡነ ሀብተ ማርያም ፅንሰታቸው ነው። አባታቸው ፍሬ ቡሩክ እናታቸው ዮስቴና የሚባሉ በሕገ እግዚአብሔር፣ በሃይማኖት፣ በትሩፋትና በምግባር ጸንተው የሚኖሩ ደጋግ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ ቅዱስ አባታችን ፅንሰታቸው ነሐሴ 26፣ ልደታቸው ግንቦት 26፣ ዕረፍታቸው ኅዳር 26 ነው፡፡ አቡነ ሀብተ ማርያምን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ‹‹አምስት መቅሰፍታት እንዲጠፉ በደጄ በደብረ ሊባኖስ ተቀበርልኝ›› ብለው የለመኗቸው ታላቅ አባት ናቸው፡፡

➯የአቡነ ሀብተ ማርያም እናት ቅድስት ዮስቴና ጻድቁ አቡነ ሀብተ ማርያምን ከመውለዷ በፊት ‹‹ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢገዛ ነፍሱን ካጣ ምን ይጠቅመዋል?›› የሚለውን የወንጌል ቃል አስባ መንና ወደ በረሃ የገባች ቢሆንም በበረሃ ውስጥ ከሰው ተለይቶ የሚኖር የበቃ ባሕታዊ በዋሻ ውስጥ አገኘችና ለምነና ወደ በረሃው እንደመጣች ነገረችው፡፡ ባሕታዊውም በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ካመለከተ በኋላ ‹‹ምንኩስና ለአንቺ አልተፈቀደልሽም፣ ወደ ቤትሽ ግቢ፣ ከሕጋዊ ባልሽ ወንድ ልጅ ትወልጃለሽ እርሱም ለዓለም ሁሉ የሚጠቅም፣ ሰው ሁሉ የሚማፀነው፣ ገድሉ ትሩፋቱ በዓለም የሚነገርለት፣ በነፍስም በሥጋም የሚያማልድ፣ እንደ መልአክትም ክንፈ ጸጋ የሚሰጠው በምድር ሆኖ መንበረ ጸባኦትን የሚያይ ወንድ ልጅ ትወልጃለሽ›› በማለት ትንቢት ከነገራት በኋላ ቅድስት ዮስቴና ወደ ቤቷ ተመለሰች፡፡ እርሷም ሀብተ ትንቢት እስከመሰጠት ድረስ የደረሰች በሃይማኖት በምግባር በትሩፋት ያጌጠች ሆነች፡፡

➯ቅድስት ዮስቴናም ወደ ቤቷ ከተመለሰች በኋላ አቡነ ሀብተ ማርያም ተወለዱና ወላጆቻቸው ፈሪሃ እግዚአብሔርን እያስተማሩ አሳደጓቸው፡፡ ከዕለታት በአንድ ቀን ካህናቱ በቤተ ክርስቲያን ምህላ ሲያደርሱ ‹‹እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ›› እያሉ ሲጸልዩ ሰምተው በልቡናቸው ‹‹ይህች ጸሎት በጣም ጥሩ መልካም ጸሎት ናት፤ እኔ ይህችን ጸሎት መርጫታለሁ፤ በዚህ ጸሎት ዓለም ከአሳችነት ኅሊና በሚመጣውም ዓለም ከገሃነም እሳት እንድንድንባት አውቃለሁ›› አሉ፡፡ ይህችንም ጸሎት ማዘውተር ጀመሩ፡፡ እናትና አባታቸውም በተኙ ጊዜ ሌሊት ለጸሎት ተነሥተው በዚህ ጸሎት ፈጣሪአቸውን ያመሰግኑ ነበር፤ ስግደትን ይሰግዳሉ ነገር ግን እናትና አባታቸው ከእንቅልፋቸው በነቁ በጊዜ ሮጠው ወደ መኝታቸው ሄደው ይተኛሉ፡፡ የጽድቅ ሥራቸውንም ከአምላካቸው በቀር ማንም አያውቅባቸውም ነበር፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ አባታቸው ፍሬ ብሩክ የበግ ጠባቂ አደረጋቸው፡፡ እግዚአብሔር ግን በኋላ ለብዙዎች ስውራን ቅዱሳንና በዓለም ለሚኖሩ ምዕመናን በጎች ጠባቂ ያደርገው ዘንድ ወዶ መርጦታልና ያ ቀን እስኪደርስ ድረስ ፈጣሪያችን አቡነ ሀብተ ማርያምን ይጠብቃቸው ነበር፡፡.........
.......➯ከዕለታትም በአንደኛው ዕለት አባታቸን በጎችን ሲጠብቁ ሌሎች እረኞች በአመጻ ከሰው ሰርቀው ቆርጠው ያመጡትን እሸት ‹‹ና እንብላ›› አሏቸው፡፡ አባታችን ግን ‹‹ከየት እንዳመጣቸሁት ምንም ስለማላውቅ አልበላም›› አሏቸው፡፡ እረኞቹም ሀብተ ማርምን በቁጣ ዐይን እያዩአቸው ተቀምጠው ሲበሉ አባታችን ‹‹የማንችለው ዝናብ መጥቷልና ተነሡ በፍጥነት ወደቤታችን እንሂድ›› አሏቸው፡፡ እረኞቹም ‹‹ሰማዩ ብራ ነው ምንም ደመና የለውም፤ ነፋስም አይነፍስም፡፡ እኛ የማናየው አንተ ብቻ የምታየው ምን ነገር አለ?›› እያሉ በአባታችን ላይ ተዘባበቱባቸው፡፡ አባታችን ግን በጎቻቸውን እያስሮጡ በፍጥነት ወደ ቤታቸው ሄዱ፡፡ ወዲያውም በጣም ኃይለኛ ዝናብ ዘነበ፡፡ የጥፋት ውኃው በላያቸው እስኪፈጸምባቸው ድረስ እነዚያን እረኞች ከቦታቸው አልተነቃነቁም ነበርና በጥፋቱ ውኃ አለቁ፡፡ በዚያችም ሌሊት አቡነ ሀብተ ማርያን ከሰማይ ሦስት ጊዜ ‹‹ሀብተ ማርያም ሀብተ ማርያም›› የሚል ድምፅ ጠራቸው፡፡ አባታችንም እንደ ሳሙኤል ‹‹ጌታዬ ባሪያህ ይሰማሃል ተናገር›› ሲሉ ጌታችን አናገራቸው፡፡ ‹‹ከዚህ በኋላ ለሚሰሙህ ለመረጥኳቸው ቃሌን ትነግራቸው ዘንድ ከእኔም ጋር በምሥጢር በባለሟልነት ትነጋገር ዘንድ መርጨሃለሁ›› አላቸው፡፡

➯ከጥቂት ቀንም በኋላ አባታችን በጎችን እየጠበቁ ሳሉ አንድ አመጸኛ መጣና በትራቸውን በኃይል ነጥቆ ወሰደባቸው፡፡ አቡነ ሐብተ ማርያምም ‹‹በሕያው እግዚአብሔር አምልሃለሁ እቋቋምህ ዘንድ ኃይል የለኝምና በትሬን መልስልኝ›› ቢሉት የትዕቢትን ቃል ተናገራቸው፡፡ አባታችንም ‹‹እምቢ ካልክስ እሺ የእግዚአብሔርን ኃይል ታያለህ›› አሉት፡፡ ወዲያም ያ አመጸኛ ላዩ ታች፣ ታቹ ላይ፣ ግራው ቀኝ፣ ቀኙ ግራ ሆኖ በአየር ላይ ተሰቅሎ ዋለና እየጮኸ አባታችንን ለመናቸው፡፡ አባታችንም ‹‹የቀጣህ እግዚአብሔር ይቅር ይበልህ›› ባሉት ጊዜ ከተሰቀለበት ወርዶ በእግሩ ቆመ፡፡ በዚያ የነበሩና ይህንን ተአምር ያዩ እረኞችም እጅግ ፈርተው ሄደው ለወላጆቻቸው ያዩትን ተናገሩ፡፡ የሀገሩ ሰዎችም ‹‹ቀድሞ እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ እያለ ሲጸልይ ሲሰግድ አይተነዋል አሁንም ጠላቱን በነፋስ የሚቀጣ ይህ ልጅ ወደፊት ምን ይሆን!›› እያሉ አደቁ፡፡ ወላጆቻቸውም ይህን በሰሙ ጊዜ በግ ጠባቂነቱን አስተዋቸውና ወስደው ለመምህር ሰጧቸው፡፡ አቡነ ሀብተ ማርያምም የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ሁሉ በሚገባ ተማሩ፡፡

➯ከዚህም በኋላ አባታቸው ከሀገሪቱ ታላላቅ ሰዎች አንዷን እጮኛ አጨላቸው፡፡ ነገር ግን አቡነ ሀብተ ማርያም ‹‹አባቴ ሆይ እኔ ራሴን ለክርስቶስ በድንግልና ለመኖር አጭቻለሁ፣ ተራክቦዬም ቃለ ወንጌልን መስማት እንጂ ሌላ አይደለምና ለምን እንዲህ ትለኛለህ?›› አሉት፡፡ አባታቸውም ይህን ሲሰማ ተቆጥቶ ያለ አቡነ ሀብተ ማርያም ፈቃድ ሙሽራይቱን ለማምጣት ሄደ፡፡ አባታችን ግን ሀገር ጥለው ለመሰደድ ከቤት ተደብቀው ወጡ፡፡ መንፈስ ቅዱስም በመብረቅ አምሳል አባታቸውን ገስጻቸውና በዚህ ድንጋጤ ምክንያት ከዚህ ኃላፊ ዓለም ዐረፈ፡፡

➯አባታችንም የአባታቸውን ዕረፍት ሳያዩ አፋር ወደምትባል ሀገር ሄደው አባ ሳሙኤል ከሚባል ደግ መነኩሴ ቦታ ገብተው መነኩሴውን እያገለገሉት ኖሩ፡፡ አንድ ቀን አባታችን እንስራ ተሸክመው ውኃ ይቀዱ ዘንድ ወደ ወንዝ ወረዱና ውኃውን ቀድተው ሲመለሱ ድንጋይ አደናቀፋቸውና እንስራው ከላያቸው ላይ ወደቀ፡፡ ነገር ግን መሬት ከመድረሱ በፊት አባታችን ፈጥነው የጌታችን ስም በጠሩ ጊዜ እንስራው ወድቆ ሳይሰበር ተመልሶ በትከሻቸው ላይ ተቀመጠ፡፡ አባ ሳሙኤልም ይከተሏቸው ነበርና ይህን ጽኑ ተዓምር አይተው እጅግ አደነቁ፡፡

➯እንዲሁ ከዕለታት በአንድ ቀን በሌሊት መብራት ለአባ ሳሙኤል እያበሩ ሳለ መብራቱ ከእጃቸው ላይ ወድቆ ጠፋ፡፡ መምህሩም አባ ሳሙኤል ቁጡ ነበረና ስለ መምህራቸው ቁጣ በጣም ደንግጠው ወድቆ የጠፋውነ መብራት ፈጥነው ባነሱት ጊዜ መብራቱ በእግዚአብሔር ተዓምር ራሱ በርቶ ታየ፡፡ አባ ሳሙኤልም ይህን ተዓምራት አይቶ እጹብ እጹብ በማለት ‹‹የዚህ ቅዱስ ልጅ መጨረሻ ምን ይሆን?›› ብሎ ካደነቀ በኋላ ‹‹የዓለም ሁሉ የጥበብ መብራት ይሆናል›› ሲል ትንቢት ተናገረላቸው፡፡ እመቤታችን ለአባ ሳሙኤል ተገልጣላቸው የአቡነ ሀብተ ማርያምን ክብር ነግራዋለች፡፡ አባታችንም አባ ሳሙኤልን 12 ዓመት ከትሕትና ጋር እየታዘዙ ቤተ ክርስቲያንን እያገለገሉ ኖረው ከዚህ በኋላ በእግዚአብሔር ፈቃድ ወጥተው ሄደው እለ አድባር በተባለ ገዳም መኖር ጀመሩ፡፡ ከቦታውም ደርሰው ጥቂት ከቆዩ በኋላ እግዚአብሔር ከመረጣቸው ከአባ መልኬጼዴቅ እጅ የምንኩስናን ስርዓት ተቀበሉ፡፡ ይኸውም የሚዳው አቡነ መልኬጼዴቅ በደጃቸው የተቀበረውን ሰው አፈር የማያስበሉት ጻዲቅ ናቸው፡፡ ይህንንም የጻድቃኑን አባትና ልጅነታቸውን መሠረት በማድረግ የይሰበይ አቡነ ሀብተ ማርያም ገዳም ካህናት፣ መሪጌቶችና ዲያቆናት ግንቦት 4 ቀን ወደ ሚዳ መራቤቴ በመሄድ የአቡነ መልኬጼዴቅን በዓል እጅግ በደማቅ ሁኔታ ያከብራሉ፡፡

➯አቡነ ሀብተ ማርያምም ምንኩስናን ከተቀበሉ በኋላ ገድላቸውንና ትሩፋታቸውን በማብዛት በሳምንት አንድ ጊዜ ቅጠልን ብቻ የሚመገቡ ሆኑ። አርባ አርባ ቀን ሰማንያ ሰማንያ ቀንም የሚጾሙበት ጊዜ ነበር። በሌሊትም ወደ ጥልቅ ባሕር እየገቡ መዝሙረ ዳዊት፣ አራቱን ወንጌላትና ሌሎች የጸሎት መጽሐፍትን ይደግሙ ነበር፡፡ ፊታቸውም እንደ ንጋት ምሥራቅ ኮከብ ያበራ ጀመር።

➯ከዚህም በኋላ ወደ ምሥራቅ ሄደው ጎሐርብ ወደምትባል ሀገር ደረሱ። በዚያም በዓት አጽንተው ሲጸልዩ ጌታችን ቅዱስ ገብርኤልንና ቅዱስ ሚካኤልን በቀኝና በግራ አስከትሎ ተገለጠላቸውና ‹‹ወዳጄ ሀብተ ማርያም ሆይ ሰላም ላንተ ይሁን›› አላቸው። ያን ጊዜ አባታችን ከፈጣሪአቸው ግርማ የተነሳ ደንግጠው ከመሬት ወድቀው እንደ በድን ሆኑ። ጌታችንም አንስቶ ክቡራን በሆኑ እጆቹ አጸናቸውና ‹‹የመጣሁት ለጸናህ ነው ሰውነትህንም እንደ ንስር ላድሳት ነው እንጂ ላጠፋህ አይደለም፡፡ ድካምህና ገድልህ ሁሉ ለዘለዓለም መታሰቢያ ሊሆን በኢየሩሳሌም ሰማያዊት ተጽፎልሃል ብዬ በእውነት እነግርሃለሁ። ለአንተ ለወደድኩህና ለመረጥኩህና ወዳጄ የማቴዎስንና የማርቆስን ወንጌል ባነበብክ ጊዜ ተጭነህ ወደምትሄድበት ቦታ የሚያደርስህ የብርሃን ሰረገላ ሰጥቼሃለሁ። እንደ አንተም ካሉ በዋሻ በመሬት ፍርኩታ ከሚኖሩ ከመረጥኳቸው ቅዱሳን ጋር ትገናኝ ዘንድ ወደ አራቱም አቅጣጫ ትበር ዘንድ የብርሃን ሠረገላ ሰጥቼሃልሁ። ዳግመኛም የሉቃስንና የዮሐንስን ወንጌል ባነበብክ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ትሄድ ዘንድ የእሳት ሠረገላ ሰጥቼሃለሁ›› አላቸው። ዳግመኛም ‹‹በጸሎትህ አምኖ በጎ ሥራ ለሚሠራ ሁሉ፣ ስምህን የጠራውን ዝክርህን ያዘከረውን ሁሉ የሀብተ ማርያም አምላክ ሆይ ከጠላት እጅ አድነኝ ያለኝን በኅሊና ያሰበውን በልቡናው የወሰነውን እፈጽምለታለሁ። አንተን ገድልህንና ቃል ኪዳንህን የናቀውን ያቃለለውን ሁሉ ፍጹም መበቀልን እበቀለዋለሁ። እንደ ወዳጄ እንደ ፊቅጦርም በእናቴ በማርያም ድንግል አተምኩህ›› ካላቸው በኋላ ቅዱስ ሚካኤል ከእርሳቸው እንዳይለይ የዘወትር ጠባቂ አድርጎ ሰጣቸውና በታላቅ ግርማ ወደ ሰማይ ዐረገ።

➯አባታችንም ከጌታችን ይህን ቃል ኪዳን ከተቀበሉ በኋላ ነፍሳቸውን ‹‹ነፍሴ ሆይ ከፈጣሪሽ ከእግዚአብሔር ጋር ፊት ለፊት አፍ ለአፍ ትነጋገሪ ዘንድ ደፍረሻልና በጎም ሥራ ሳይኖርሽ ከፈጣሪሽ ቃልኪዳን ተቀብለሻልና ከዛሬ ጀምሮ እንደ መላእክት ዘወትር አትተኝ›› እያሉ ተጋድሏቸውን አብዝተው ቀጠሉ።......
....➯መልአኩ ቅዱስ ሚካኤልም አባታችንን እንደ ጓደኛ ሆኖ ዘወትር ይጎበኛቸው ነበር፡፡ ቅዱሳን አባታቸንን ሊጎበኟቸው መጥተው ከደጅ ቆመው እንደሆነ ቅዱስ ሚካኤል አባታችንን ‹‹እከሌ ጉዳዩ እንዲህ ነው እንዲህ ብለህ ተናገረው…›› እያለ ያማክራቸው ነበር፡፡ እሳቸውም ቅዱስ ሚካኤል ካዘዛቸው በቀር ምንም አይሠሩም ነበር፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትንም ባነበቡ ጊዜ ኃይለ ቃሉን እየተረጎመ ምሥጢራትን ይነግራቸዋል፤ የተሰወረውንም ይገልጥላቸዋል፡፡ ከእንስሳት ጩኸት ጀምሮ ከዱር አራዊት ድምፅና እስከ አእዋፍ ቋንቋ ያለውን ያስረዳቸው ነበር፡፡

➯ይኸውም መልአክ አንድ ቀን አቡነ ሀብተ ማርያምን ወደ ቤተ ክርስቲያን አስገብቷቸው ሥጋ ወደሙን ለመቀበል ተዘጋጅተው ሳለ ወንጌል የሚነበብበት ሰዓት ሲደርስ ያልተማረ ቄስ የክርስቶስ ጌትነቱን የምትናገር ወንጌልን ሲያነብ ‹‹ወዮሴፍ ብእሲሃ ለማርያም ጻድቅ ውእቱ›› የሚል ከቄሱ አፍ ይህን ንባብ አባታችን ሲሰሙ እጅግ ደንግጠው ወንጌል ወደሚነበብበት ስፍራ ሄደው የሚያነበውን ቄስ ገሠጹት፡፡ ‹‹ወዮሴፍሰ ፈሃሪሃ ለማርያም ጻድቅ ውእቱ በል እንጂ ብእሲሃ አትበል›› ብለው መከሩት፡፡ ቄሱም አቡነ ሀብተ ማርያም እንዳዘዙት ከስህተቱ ወደ ቀና ንባቡ ተመለሰ፡፡ ይህን ጊዜ ጌታችን ለአባታችን ድጋሚ ተገልጦላቸው ‹‹ሀብተ ማርያም ሆይ ይህን ትምህርትህን ወድጄ አመሰገንኩህ፣ የእናቴን የድንግል ማርያምን የድንግልናዋን ንጽሕና ስለ አከበርክ እኔም በመንግስተ ሰማያት ፈጽሜ አከብርሃለሁ›› አላቸው፡፡ ዳግመኛም ጌታችን ‹‹አሁንም ዮሴፍ ብእሲሃ ለማርያም የሚሉትን ሁሉ ለያቸው እንጂ አትተዋቸው፤ እንዲህ የሚል ጽሑፍም ብታገኝ እንዳይኖር እርሱን ፍቀህ ፈሃሪሃ ለማርያም የሚለውን ጻፍ›› ብሎ አባታችንን ካዘዛቸው በኋላ ሰላምታ ሰጥቷቸው ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡ አባታችንም በዚህ ጊዜ ፊታቸው ላይ ብርሃን ስለተሳለባቸውና እንደ ፀሐይ ስላበራ ሰዎችም አይተው ባደነቁ ጊዜ ወደ በዓታቸው ገቡና ጌታችንን ‹‹አቤቱ ጌታዬ ሆይ በሰው ፊት ክብሬን አትግለጥብኝ ሰውርልኝ፣ በቸርነትህም አድነኝ›› ብለው ጸለዩ፡፡ እንዲህም ብለው በጸለዩ ጊዜ ፊታቸው መልኩ ተለውጦ እንደ ቀድሞው ሆነ፡፡

➯ከዕለታትም በአንደኛው ቀን አባታችን ታመው ተኝተው ሳለ ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስ መጥተው ሥጋ ወደሙን አቀብለዋቸዋል፡፡፡ አባታችን በጸሎት ላይ ሳሉ ቅዱስ ሚካኤል ነጥቆ ወደ ሰማይ ወስዶ ቅዱሳን የሚኖሩባቸውን ዓለማት፣ መንግስተ ሰማያትን እንዲሁም ኃጥአን የሚኖሩበትን ሲኦልን አሳያቸው፡፡ በገነት ያሉትንም ከአዳም ጀምሮ እሳቸው እስካሉበት ጊዜ እስከ አቡነ መርሐ ክርስቶስ ድረስ ያሉትን ቅዱሳን አሳያቸው፡፡ ከዚህም በኋላ በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት ቆመው ሳለ ሰይጣንም መጥቶ በእግዚአብሔር ፊት ቆመና ‹‹አቤቱ ጌታዬ ሆይ በሀብተ ማርያም ላይ እንደ ኢዮብ ብዙ መከራ አጸናበት ዘንድ ፍቀድልኝ›› ብሎ እየጮኾ ሲናገር አባታችን እጅግ ፈርተው አለቀሱ፡፡ እግዚአብሔር ግን በሰይጣን ላይ ተቆጥቶ ‹‹በነፍሱም በሥጋውም መከራ ታጸናበት ዘንድ አልፈቅድም›› አለው፡፡ ‹‹እኔ ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ መርጨዋለሁና በንጽሕናና በቅድስና ኃጢአት እንዳይሠራ ዘወትር እጠብቀዋለሁ፤ በእርሱ ላይ ማሰልጠንስ ይቅርና በሀብተ ማርያም ጸሎት በተማጸነኝ ሁሉ ላይ እንኳን አላሠለጥንህም›› አለው፡፡ ሰይጣንም ይህን ቃል ሰምቶ አፍሮ እያዘነ ሄደ፡፡

➯አቡነ ተክለ ሃይማኖትም ከእርሳቸው በኋላ በመንበራቸው ከተሾሙት ከስምንቱ መምህራን ጋር ለሀብተማርያም ተገለጡላቸው፡፡ እነርሱም ኤልሳዕ፣ ፊሊጶስ፣ ሕዝቅያስ፣ ቴዎድሮስ፣ ዮሐንስ፣ ዮሐንስ ከማ፣ እንድርያስና መርሐ ክርስቶስ ናቸው፡፡ እነዚህም መልካቸው እንደ ፀሐይ ያበራ ልብሳቸው እንደ መብረቅ ያንጸባርቅ ነበር፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖትም ልብሳቸው የእሳት ላንቃ የከበበው መልኩም ነጭ የሆነ የሚያስደንቅ ሆኖ ‹‹በቅድምና ለነበረ ለአብ በቅድምና ለነበረ ለወልድ በቅድምና ለነበረ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይገባል›› እያለ ልብሳቸው በሰው አንደበት ያመሰግን ነበር፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖትም አቡነ ሀብተ ማርያምን ‹‹ልጄ ሀብተ ማርያም ሆይ! ፈጣሪዬ እግዚአብሔር ስለወደደህ ብዙ ምርኮ እንዳገኘህ በአንተ ፈጽሞ ደስ ይለኛል፡፡ ነገር ግን የምለምንህ ነገር አለና እሺ በለኝ›› አሏቸው፡፡

➯አቡነ ሀብተ ማርያምም ‹‹ጌታዬ ነገሩ ምንድን ነው?›› ሲሏቸው አቡነ ተክለሃይማኖት ‹‹ከተቀበርኩበት ቦታ እንድትቀበር ቃል ኪዳን ግባልኝ›› አሏቸው፡፡ አቡነ ሀብተማርያምም ‹‹አባቴ ሆይ ይህንን አደርግ ዘንድ ስለምን ትወዳለህ?›› አሏቸው፡፡ አቡነ ተክለሃይማኖትም በሀገሬ ላይ የታዘዙ አምስት መቅሰፍቶች አሉና ስለዚህ ነው እነዚህም አንዱ መብረቅ ነው፤ ሁለተኛውም ቸነፈር ነው፤ ሦስተኛውም ረሃብ ነው፤ አራተኛውም ወረርሽኝ ነው፤ አምስተኛውም የእሳት ቃጠሎ ነው፡፡ የአንተ አጽም በውስጡ የተቀበረ እንደሆነ አጥንቴ የተቀበረባት ሀገሬ ከነዚህ መቅሰፍታት ትድናለች›› አሏቸው፡፡

➯አቡነ ሀብተ ማርያምም ‹‹ንዑድ ክቡድ የምትሆን አባቴ ሆይ ልዩ ክቡር በሚሆን በአንተ አጽም መቀበር ያልዳነች በእኔ አጽም መቀበር ድኅነት ታገኛለችን? ይህንስ ተወው›› ብለው በተከራከሯቸው ጊዜ አቡነ ተክለ ሃይማኖትም መልሰው ‹‹ልጄ ሀብተ ማርያም ሆይ አንተ የማታውቀው ከፈጣሪያችን ከእግዚአብሔር የተሰጠህ እኔ የማውቀው ክብር አለህና ስለዚህ ነው፡፡ ይልቁንስ እንዳልኩህ በተቀበርኩበት ቦታ እንድትቀበርልኝ ቃልኪዳን ግባልኝ›› ብለው ማለዷቸው፡፡ ይህንንም ሲባባሉ እንዲህ የሚል ቃል መጣላቸው፡- ‹‹ከወዳጄ ከሀብተ ማርያም አንደበት ይህ ቃልኪዳን አይወጣም፣ ዳግመኛም ወዳጄ ተክለ ሃይማኖት ሆይ! እርሱ በወደደው የሚቀበር አይደለምና እኔ ከተቀበርኩበት እንድትቀበር ብለህ የምታስገድደው ለምንድን ነው? እኔ በወደድሁት ቦታ ይቀበራል እንጂ›› የሚል ቃል ተነገረ፡፡ አቡነ ተክለሃይማኖትም እየለመኑናና እየሰገዱ ከሥላሴ ዙፋን ፊት ተንበረከኩ፡፡ ሦስተኛውም ‹‹ይሁን እንዳልከው ይቀበርልህ›› የሚል ቃል ተሰማ፡፡ ዳግመኛም ‹‹በአንተም አጽም በሀብተ ማርያምም አጽም ቦታህ ከመቅሰፍታት ትዳንልህ፤ ልጆችህ ግን በቸነፈር ደዌ ቢሞቱ ከሰማዕትነት ተቆጥሮላቸው ወደ መንግሥተ ሰማያት እንዲገቡ በራሴ ምዬ ቃልኪዳን ገብቼልሃለሁ›› አላቸው፡፡ በዚህም ጊዜ አቡነ ተክለሃይማኖት እጅግ ደስ ተሰኝተው ሦስት ጊዜ ሰገዱ፡፡

➯ከዚህም በኋላ መልአኩ ለአቡነ ሀብተ ማርያም ክብሯ እንደ ጽርሐ አርያም የሆነች አገርን አሳያቸው፡፡ ሥፍር ቁጥር የሌላቸውም ቅዱሳን መላእክት በውስጧ ተድላ ደስታ ያደርጉባት ነበር፡፡ አባታችንም መልአኩን ‹‹ይህች ክብሯ ፍጹም የሆነችን አገር ማን ትባላለች በውስጧ ለመኖር በእጅጉ ወድጃለሁና›› ብለው ሲጠይቁት መልአኩም ‹‹ይህችማ አገር የአባትህ የተክለ ሃይማኖት አጽም ያረፈባት ደብረ ሊባኖስ ናት፤ ከእርሱም ጋር በክብር እስክትነሣ ድረስ በውስጧ ትቀበርባት ዘንድ ለአንተም ተሰጥታሃለችና ደስ ይበልህ፡፡ አባትህም እንደ ኢየሩሳሌም እንደትሆንለት ቃልኪዳን ተቀብሎባታል›› አላቸው፡፡......
.....➯በአንደኛውም ቀን አቡነ ሀብተ ማርያም ከሌሎች ቅዱሳን ጋር ሆነው ሲሄዱ ብዙ አጋንንት እየተደነባበሩ ወደ ታች ሲወርዱ ተመለከቱና አባታችን ሥራቸውን ለማየት ተከተሏቸው፡፡ አንዱንም ኃጥእ ይዘው ነፍሱን ከሥጋው ለዩዋትና ወደ ሲኦል አወረዷት፡፡ አባታችንም ከሌሎቹ ቅዱሳን ጋር ሆነው ያችን ነፍስ ይምርላቸው ዘንድ ጌታችንን በጸሎት ማለዱት፡፡ ነገር ግን ‹‹ለጣዖት ስትሰግድ ስለኖረች ይህችን ነፍስ አልምራትምና አትድከሙ›› የሚል ቃል ከልዑል እግዚአብሔር ዘንድ መጣላቸው፡፡ ቅዱሳኑም ‹‹ልመናችንን የማትቀበል ከሆነ በከንቱ ሰብስበኸናል›› ብለው ቢያዝኑ እግዚአብሔርም ‹‹ሕገ እግዚአብሔርን የዘነጉ ሰዎችን ቅጣት እንድታዩ ነው›› አላቸው፡፡ እነርሱም ሕገ እግዚአብሔርን የዘነጉ ሰዎችን ሲቀጣቸው ለደጋጎቹ ሰዎች ደግሞ መልካሙን ዋጋቸውን ሲሰጣቸው አይተው አንድ ሆነው አመስግነውታል፡፡

➯ከዚህም በኋላ መልአኩ ቅዱስ ራጉኤል አንዱን ሰው በመብረቅ ቀሰፈውና ቅዱስ ሚካኤል ሄዶ ቅዱስ ራጉኤልን ሲከራከረው አባታችን ተመለከቱ፡፡ ቅዱስ ሚካኤል ‹‹የእኔ አገልጋይ ነውና ለምን ገደልከው?›› ሲለው ቅዱስ ራጉኤልም ‹‹ሰንበት ሳይለይ ዝሙትን መሥራት የለመደ ሥራውም ዝሙት ስለሆነ በፈጣሪዬ ታዝዤ ነው የገደልኩት፡፡ ኃጥአንን ሊያጠፋ እንጂ ጻድቃንን ለመቅጣት መብረቅ እንዳይታዘዝ አንተስ ታውቅ የለም እንዴ?›› አለው፡፡ ይህንንም ተባብለው ከሥላሴ ፊት ሰግደው ቅዱስ ሚካኤል የተገባለትን ቃልኪዳን በማሳሰብ ምልጃውን አቀረበ፡፡ እግዚአብሔርም በጎና ክፉ ሥራዋን ባስመዘነ ጊዜ በጎ ሥራዋ ስለበለጠ ቅዱስ ሚካኤል ያችን ነፍስ ታቅፎ ወስዶ ለቅዱስ ገብርኤል ሰጠው፡፡ ሰባቱም ሊቃነ መላእክት እየተቀባበሉ ወስደው ከመስቀል ዘንድ አደረሷት፡፡ ለቅዱስ መስቀልም ካሰገዷት በኋላ አሳልመዋት በቅዱስ ሚኤካል አማላጅነት ወደ ገነት አስገቧት፡፡ አቡነ ሀብተ ማርያምም ይህን በተመለከቱ ጊዜ ቅዱስ ሚካኤልን ‹‹መስቀል ታሳልሟት ዘንድ ያችን ነፍስ ወደ መስቀል ለምን ወሰዳችኋት?›› ብለው ጠየቁት፡፡ መልአኩም ‹‹በትልቅም በትንሽም ነገር ክርስቲያናዊትን ነፍስ የሚቃወም ቢመጣባት ድል የምትነሳበትን በመስቀል ፍርድ ይታይላታልና ስለዚህ ነው፡፡ የሚከራከራት ቢኖር ግን እንዳየኸው ወደ መስቀል ባደረሷት ጊዜ የሚቃወማት ሰይጣን ፈጥኖ ይርቅላታል ዳግመኛም ሊከራከራት አይችልም›› አላቸው፡፡

➯ከአቡነ ሀብተማርያም በረከት ለመቀበል ብዙ ቅዱሳን ከሮም፣ ከግብፅ፣ ከአስቄጥስና ከሲሐት ገዳም ወደ አባታችን ዘንድ ይመጡ ነበር፤ ከየሀገራቸውም በአንበሳ ተቀምጠው የሚመጡ አሉ፤ ክንፍ ተሰጥቷቸው እንደ ንስር የሚበሩም አሉ፤ ብፁዕ አቡነ ሀብተ ማርያምም የቅዱሳኑን ብቃት አይተው ‹‹ሥራችሁ እንዲህ እንዲህ ሲሆን ለምን ወደኔ መጣችሁ?›› ብለው ሲጠይቋቸው ቅዱሳኑም ‹‹በማንኛውም ሥራ እግዚአብሔርን በለመነው ጊዜ በኢትዮጵያ የሚኖር እንደ ሙሴ ያለ ሀብተ ማርያም የሚባል ወዳጄ አለና ሁሉን ስለሚነግራችሁ ዘወትር እርሱን ጠይቁ ብሎ ስላዘዘን ወደ አንተ መጣን›› አሏቸው፡፡ አባታችንም ቅዱሳኑን ከባረኳቸውና ከእነርሱም ከተባረኩ በኋላ አባታችን ለቅዱሳኑ የሚመጣውን እንዳለፈ የሚደረገውንም እንደተደረገ አድርገው ይነግሯቸዋል፡፡ ቅዱሳኑም ከልጅነታቸው ጀምረው እስከዚያች ቀን ድረስ የሠሩትን ሥራ ሁሉ ይነግሯቸዋል፡፡ እነርሱም እጃቸውን እየሳሙ በረከታቸውን ይቀበሉ ነበር፡፡ እንደዚሁም አቡነ ሀብተ ማርያም ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል እየተራዱዋቸው ቀድሰው በሚያቆርቡ ጊዜ ተሰውረው የሚኖሩ 500 ስውራን ቅዱሳን መጥተው ሥጋ ወደሙን ከአባታችን እጅ ተቀበሉ፡፡ ቀድሰውም ወደበዓታቸው እንደገቡ እመቤታችን ተገልጣላቸው ‹‹በነገውም ዕለት ቅዳሴዬን ቀድስ፣ ይህም ቅዳሴ መዓዛ ቅዳሴ ነውና፡፡ የዓለም መሠረት ማርያም ወደኔ ነይ ብለህ በጠራኸኝ ጊዜ ነቢያትን ሐዋርያትን አስከትዬ መጥቼ እባርክሃለሁ›› አለቻቸው፡፡ አባታችንም ‹‹በነገው ዕለት ሌላ ተረኛ ቄስ ይቀድሳልና ይህ እንዴት ይሆንልኛል?›› አሏት፡፡ እመቤታችንም ‹‹ፈቃዴ ስለሆነ አንተ እንድትቀድስ አደርጋለሁ›› አለቻቸው፡፡ በነጋታው ተረኛው ቄስ ከእንቅልፉ በነቃ ጊዜ ቸኩሎ እየተፋጠነ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲገሰግስ ወድቆ ጥርሱ ደማና ስለ ሥጋ ወደሙ ቅዳሴ እጅግ ደንግጦ ወደ አባታችን መጥቶ ‹‹ቅዳሴው በእኔ ስም ከሚታጎል አንተ ቀድስልኝ›› አላቸው፡፡ አባታችንም አስቀድማ እመቤታችን የነገረቻቸውን ነገር አስበው እያደነቁ ሄደው ቀደሱ፡፡ እመቤታችንም ነቢያትን ሐዋርያትን አስከትላ መጥታ ባረከቻቸው፡፡


➯ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

#ስንክሳር ነሐሴ 26 እና #ከገድላት_አንደበት