Alex Abreham (አቡቹ) በነገራችን ላይ...
1.4K subscribers
99 photos
2 videos
2 files
9 links
ዙቤይዳ እና ሌሎች
ዶክተር አሸብር እና ሌሎች
እናት ሀገር ፍቅር
አንፈርስም አንታደስም...
በሚሉ ጣፋጭ ወጎቹና ግጥሞቹ ምናውቀው አሌክስ አብርሀም በማህበራዊ ድህረ-ገፅ , ከመፅሐፎቹ እዲሁም የሚሰጣቸዉን ጥልቅ ሒሶች ለእኛ አድናቂዎች የምናደርስበት ቻናል ነዉ::
-----------------------
አሌክስን ለሚወድ ብቻ
---------//-----------
አሌክስ ማለት በቃ አሌክስ ብቻ ነው
Download Telegram
ድብቁ ባለ አስር ፎቅ እስር ቤት በመሃል አዲስ አበባ!
((ዜና አንባቢዎቹ ብልት ላይ የሲሊንደር በርሚል ተንጠልጥሎ በግድ ዜና ያነቡ ነበር !))
(አሌክስ አብርሃም)
@AlexAberham
------------//------------
ያው ሁላችንም እንደምናውቀው ኢትቪ ብዙ ዶክሜንታሪዎችን ሰርቶ ሲያሳየን ኑሯል ! የምናስታውሰውን እንቁጠር ብንል እንኳን ከ 1993ቱ
የዩኒቨርስቲ ተቃውሞ ጋር ተያይዞ ምናይነት ሌባና ትምህርት አልሳካላቸው ያለ ተማሪዎች ረብሻ እንዳስነሱ ፣ ቀጥሎ ደግሞ እነዛው ሌባዎቹ
እና ትምህርት ያልተሳካላቸው ተማሪዎች እግረ መንገዳቸውንም የኦነግ አፍራሽ ሴራ ተሸክመው ለጥፋት መንቀሳቀሳቸውን ነግሮን ጉድ
ብለናል ! በዛው አፉ የተማሪዎች እንቅስቃሴ በአንባ ገነኖች እንዴት በሳዛኝ ሁኔታ እየታፈነ እንደሆነ አሁን እያወራን ነው! አሁንም ጉድ በለናል!
አንዴ ደግሞ በሰራው ዶክሜንታሪ ኦነግ እንዴት ሰላማዊ ዜጎችን በአሰቃቂ ሁኔታ እንደጨፈጨፈ አሳይቶን መከላከያ ሰራዊታችን ዘምቶ
በጫካ ውስጥ እንዴት ድራሻቸውን እንዳጠፋቸው የሬንቦን ፊልም የሚመስል በኦሮሚያ ጫካዎች ውስጥ የተሰራ ጀብዱ አሳይቶን አሁን
ተመልሶ የኦነግን የነጻነት ትግልና ለኦሮሚያ ህዝብ ያደረገውን ተጋድሎ ባለፍ ገደም እየዘገበ ነው!
የእስልምና መፍተሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎችን በካቴና ጠፍንጎ እስላማዊ ሃረካት ፣አዲስ አበባን እንደባግዳድ ይሁን እንደሶሪያ ሊያደርጉ ሲሉ
<<ቀጨም>> አደረግናቸው በማለት ተሰምቶ የማያልቅ ግፍና የስም ማጥፋት ካደረሰባቸው በኋላ አሁን እንደውም አዲስ አበባን ጀነት
ሊያደርጓት ነበር ሊለን የሚዳዳው ዘገባ ራሳቸው ላይ ሰርቶ እያሳየን ነው !
ኢሳያስ አፈወርቂንማ ተውት ሁለት መንገድ አለ አንዱ የእግዜብሔር መንገድ ሌላው የኢሳያስ እስክንል ሰይጣን አድርጎ ስሎ 20 ዓመታት
ካሳየን በኋላ አሁን ቁመተ መለሎው ጎረቤታችን የኢትዮጲያ ጠባቂ መልዓክ ናቸው ሊለን እየታተረ ነው!
ስለአባይ ግድብማ ምን ያልተሰራ ያልተነገረ ፉከራና ሽለላ ነበር ብራችንን ያስቀማን ኢቲቪ ነበር ባጭሩ ! የሌለ ያልተሰራ ነገር እያሳየ !
እንግዲህ ጓዶች ይሄን ሁሉ ጉድ ያሳለፈ ኢቲቪ ዋናው እስረኛ ራሱ ነበር ! ምን እናውቃለን ዜና አንባቢዎቹ ከወገብ በላይ ነው ሽክ በለው
የሚታዩት፣ ከወገብ በታች ያንን ሁሉ ውሸት እንዲያነቡ ብልታቸው ላይ የሲሊንደር በርሚል ተንጠልጥሎባቸው ቢሆንስ? በሃይላንድ ውሃ
ብቻማ መቶ ሚሊየን ህዝብ ላይ አይጨክኑም!
የጋዜጠኞቹ የእግር ጥፍር ይታይልን በፒንሳ እየነቀሉ ዶክሜንታሪ አሰርተዋቸው ቢሆንስ? አይ ኢቲቪማ ወደውጭ ከማየቱ በፊት እዛ
ጨለማ ህንጻ ውስጥ ይሰራ የነበረው ጉድ እያንዳንዱ ዜና እያንዳንዱ ውሸትና የተሳሳተ መረጃ መነሻው በዶክሜንታሪ መልክ ይሰራልን!
እንደዛ ካልሆነ አሁንም ምን እየሰራ እንደሆነ አናውቅማ ! ከምር ግን ኢቲቪ እንዴት መረጃ ያጣምም እንደነበር ማን እንደነበር ይነዛ ሁሉ
የውሸት ዘገባዎች አዘጋጅ . . . ! ኢቲቪ ከራሱ ከጀመረ ለውጡ ይገባናል ! አሁንም ሌሎች ላይ እንዲህ ተሰራና እንዲህ ሆነ ማለት ብቻ ግን
በቂ አይደለም! እንዳንተማመን አድርጎናል በጥሩም ሆነ መጥፎ ታሪካችን እንኳን እንዳንስማማ ታሪካችንን አደፈራርሶ እርስበርስ ለቀጣይ
ዓመታት እንዳንተማመን የሚያደርግ ስራ ሰርቷል ! ዋናው ከራሱም አልፎ የህዝቡን አእምሮ በፍርሃት፣ በመለያየት ፣በመጠላላት ፣ በዘረኝነት፣
በሃሰት መረጃ ለዓመታት ያሰረው እንደጥቁር ጭንብል የህዝብን አይን ጋርዶ ለባለስልጣናትና ለአገር አፍራሽ ሁሉ ከለላ የነበረው ድብቁ
ባለአስር ፎቅ እስር ቤት ራሱ ኢቲቪ ነበር!! !
@AlexAberham
አንድ ጭብጨባ ምንዛሪው ስንት ገባ?
(አሌክስ አብርሃም)
@AlexAberham
(((((((አብይየ የኔ ጌታ እንኳን አንድ ዶላር ከእድሜየ ላይ አምስት ዓመት ተቀንሶ ላንተ ይሰጥልኝ))))))))ካሉ ብዙዙዙዙዙዙ ሚሊየን
ኢትዮጲያዊያን ወገኖች መካከል ሁለት ሽ ስምንት መቶ ሰዎች ብቻ ናቸው ያችን አንድ ዶላር ጨክነው የላኩት ! ሚስኪን አገር ዶላር በጆንያ
እያስወጣች በዋሌት እንኳ መቀበል አልሆነላትምኮ ! እኔ የምለው ይሄ ሰውየኮ ኮሮጆዋ ተራግፎ ባዶ የቀረች አገር ጠ/ሚኒስትር እንጅ
የካፌ አስተናጋጅ አይደለምኮ በያገኛችሁበት ታጨበጭቡለታላችሁ አቤት ምን ልታዘዝ ይላል ትዛዝና ጥያቄ ታዥጎደጉዳላችሁ ከጎንህ ነን
ትላላችሁ ሳንቲም ሲባል ኢንጅሩ!! ጭብጨባችሁ ይመንዘር ? ማነህ ዲሲ ላይ ለጭብጨባ ባነሳሃው መዳፍህ በቀዘፍከው አየር ሱናሜ
ያስነሳህ ፣ ሜኔሶታ በጭብጨባህ የበረዶ ግግር ያቀለጥክ አትላንታ ጽንስ በሚያስወርድ ጭብጨባ ከተማ የናጥክ ጭብጨባህ ተመንዝሮ
ቦኖ ውሃ ይተከል? ወይስ መንገድ ይሰራበት ? የት አለህ ? ?
አይዞህ አቡቹ ባውቶብስም ቢሆን ያሰብንበት እንደርሳለን! እጃችንን ወደእግዚአብሔር እንዘረጋለን !! ያኔ የማክያቶ ሂሳብ ሳይሆን
የመከራችንን ሃሳብ እንደሰንኮፍ የሚነቅል ማዳኑ ከላይ ይመጣል !!
👇👇👇👇👇👇👇
……ዝም……

የዛሬን አያርገው፤
አጫዋች ነበርኩኝ።
ሀሳቤ ቢቀጥን፤
ዝምታን መረጥኩኝ።
ዝምታ ስጀምር፤
ከአፌ ነበረ።
እየቆየሁ ሲሄድ፤
አይኖቼም ዝም አሉ።
አይኖች ዝም… ይላሉ?
ብሎ ጠያቂ፤
አላዋቂ ናቂ፤
ተገርሞ ይሆናል፤
አላወቀም እንጂ ፤
ልቤ አለምን ንቋል።
በደጇ አያልፍም፤
በሯ ጋ' ላይደርስ
መሃለ
እግሬም፤ዝም ብሏል!
የአይኔ ዝምታ፤ከየቱ ይገርማል?

© አብርሀም የሙሉ ልጅ
@AlexAberham
@AlexAberham
" ስለ ፍቅሯ ሞተ "
.
//ምንተስኖት_ዋቆ//

ገና አፍላ ሳለሁ ፣በሙሉ አይኔ ላይሽ ፣ እሳሳልሻለሁ ፡፡
እኔም _ _ _
አፍቃሪሽ ሳልሆን ፣ ሎሌሽን መስዬ ፣
በአንቺነትሽ ታዛ ፣ ስኖር ተጠልዬ ፡፡
በፍቅርሽ ታመምኩኝ ፣
ሞቼ ተቀበርኩኝ ፣
"ስሞት እንዳትረሺኝ" ፣ ብዬ ተናዘዝኩኝ ፡፡
ግና እንዲህ ሆኖ ፣
ነፍሴ በ'አንቺ ችሎት ፡ ላይፀድቅ ተኮንኖ ፤
ቀብሬ ላይ ቆመዉ ፣ አፅሜ ላይ ተረቱ ፣
'ስለፍቅሯ ሞተ' ፣ ብለዉ ተዛበቱ ፡፡
# ተፈጠመ
በፊዚክስ ህግ አንድ ሰው አንድን እቃ ወደላይ አንስቶ መልሶ እዛው ካስቀመጠው <<ሰራ ሰራ አይባልም>>
(አሌክስ አብርሃም)
@AlexAberham
--------//-----------
አንዳንድ ድርጊቶች አሉ ብዙ ሰው የሚወዳቸው ግን ምንም ሰው የማይጠቀምባቸው! ተራ የፖለቲካ ፍጆታዎች ! አለ አይደል እየሰራን ነው
ካላመናችሁ ፎቷችንን ተመልከቱ አይነት ! ለምሳሌ እኛ ዩኒቨርስቲ በነበርንበት ሰዓት በጣም ብዙ ባለስልጣናት << ድንገት የተማሪዎችን ካፌ
ጎበኙ ተማሪዎች በምግቡ ጥራት ላይ ያላቸውን ቅሬታም ሰሙ>> የሚል ዜና በያመቱ ይሰማና ኮስማና ተማሪዎች መካከል ሱፍ የለበሱና
የገደል ስባሪ የሚያህሉ ባለስልጣን ፎቶ አብሮ ጋዜጣ ላይ ይወጣል ! ምግቡ ግን አንድም ቀን ተስተካክሎ አያውቅም! አፍንጫህን ይዘህም
ቢሆን እየበላህ ትመረቃታለህ! (አንብቡልኛ ከላይ ፊዚክስ ምን አለ?)
ሰሞኑን እንደትልቅ ጉዳይ የሚናፈሰውን ይህን ላቅመ ዜና ያልደረሰ ዜና ደግሞ ተመልከቱ ! <<የትራንስፖርት ሚኒስትር ወ/ሮ ዳግማዊት
ጠዋት ላይ በላምበረት መናሃሪያ ድንገት ጉብኝት አደረጉ ! ሚኒስትሯ በመነሃሪያው ባደረጉት ጉብኝት የአገልግሎት አሰጣጥ እና የመልካም
አስተዳደር ችግሮችን መመልከት ችለዋል! >> ይልና የወ/ሮ ዳግማዊት ፎቶ እንደደህና ለቅሶ ደራሽ በጥቁር ልብስ ካንዲት ሚስኪን ሴት
ጎን ጎንበስ ብለው ይታያል! እሽ ምኑ ነው የሚያስገርመው? ሲጀመር ባለስልጣኗ ኢትዮጲያ ውስጥ እንኳን አገር አቋራጭ ትራንስፖርት
የከተማ ታክሲ ለመያዝ ህዝቡ እንዴት ፍዳውን እንደሚበላ አያውቁም ነበር ? ቀላልኮ ነው ካሜራ ማንም ሳያስከትሉ ላምበረት ድረስም
ሂደው ዜና ሳያሰሩ የቢሯቸውን መስኮት ከፍተው ቁልቁል ቢመለከቱ ያዲሳባ ሚስኪን ህዝብ ታክሲ ጥበቃ ተሰልፎ በጸሃይና አቧራ ፍዳውን
ሲበላ ይመለከቱ ነበር !
ኢትዮጲያ ውስጥ በባለስልጣናት ያልተጎበኘ ችግር የለም !! ከመጉብኘት አልፎ አንዳንድ ችግሮች እንደቁልቢ በየዓመቱ ባለስልጣናት
ይሳለሟቸዋል! ጎበኙ ሄዱ መጡ ባለስልጣኑን ራሱን ከማስተዋወቅና አጉል ከማዋደድ ያለፈ ምንም ፋይዳ የለውም! የሚቀርብላቸውን
ሪፖርት ካላመኑ እንኳን ጠንካራ ሚዲያ በመዘርጋትና እንዲህ አይነት ችግሮችን በስርዓት እንዲዘግብ ማድረግ ሚዲያው ለማንም
የማይንበረከክ ለእውነት የቆመ እንዲሆን ማድረግ ፣ ችግሩ ሰው ሰራሽ ከሆነም ጠንካራ ህግ አስፈጻሚዎችን ኢምፓወር በማድረግ
ጥፋተኞችን አገልግሎቱን የሚረብሹትን ለህግ ማቅረብ ! ከዚህ በተረፈ ሚኒስትር ችግር በተፈጠረበት ሁሉ እየዞረ ፎቶ መነሳትና
እንደማንትስ ሾው ካሜራ ፊት ማለቃቀስ ሳይሆን አጠቃላይ ችግሩን ለመፍታት ሲስተም መቅረጽ መፍተሄ ማዘጋጀትና በዘርፉ ለሚፈጠሩ
ችግሮች ወሳኝ እና ፈጣን የተጠና ምላሽ የሚሰጥ ሴክተር መስሪያ ቤት መፍጠር ዋና ስራው ይመስለኛል! ከዚህ ውጭ በሚዲያ ችግሩን
አንስቶ መልሶ ማስቀመጥ ፊዚክስ እንዳለው ((ሰራ መስራት አይደለም !)) ከፎቶ በላይ ከዜና በላይ በህዝብ ልብ ወስጥ የሚቀመጥ
ህዝብንም ከእንግልትና መጉላላት የሚያድን ድርጊት የሚከውኑበት መልካም የሰራ ጊዜ ይሁንልዎት ከብርት ሚኒስትር !
@AlexAberham
👇👇👇👇👇👇👇👇👇👇👇
👆👆👆👆👆👆👆👆
በፊዚክስ ህግ አንድ ሰው አንድን እቃ ወደላይ አንስቶ መልሶ እዛው ካስቀመጠው <<ሰራ ሰራ አይባልም>>
(አሌክስ አብርሃም)
@AlexAberham
Share
👇👇
@AlexAberham
የቆሙትን ምክር መስማት ከተሳነን ከተገደሉት እንማር!!
(አሌክስ አብርሃም)
@AlexAberham
-------//-------+
<<ለምን ጭራቅ አይሆንም መንግስት ከሌላት አገር ክፉ መሪ ያላት አገር ትሻላለች! ቢያንስ የሚታወቅ ገዳይ አለህ ! ማን ለምን
እንደተኮሰው የማታውቀው የከባድ መሳሪያ ጥይት የቤትህን ጣሪያ ደርምሶ ቤተሰብህን ወደቁርጥራጭ ስጋነት ሲቀይር ታያለህ እንደዛ ነው
የሆንኩት እኔ ! አራት ልጆቸን አቅመደካማ አባቴንና ሚስቴን ባንድ ሰከንድ አጣሁ ! ራት እየበላን ነበር ! ይሄው ነው >>አንድ በሊቢያ የእርስ
በርስ ጦርነት የተፈናቀለ ሊቢያዊ የተናገረው ነው!
ሊቢያ ያች ውብ ከተማ ባምባ ገነን መሪዋ እንቢ ባይነት እንጂ በድህነት ስሟን የማይነሳው ሊቢያ ! ከዓመታት በፊት አንባገነን መሪያችን ኋላ
ቀር አድርጎናል፣ በአዲስ ስርዓት መተካት አለብን ባሉና ደማቸው በፈላ ወጣቶች መንገዶቿ ተሞሉ ! አለም አቀፉ ማህበረሰብ ወጣቶቹን
ከማበረታታት አልፎ የእብድ ገላጋይ ሁኖ ለእርስ በርስ ጦርነቱ መሳሪያ ረዳ ! አይዟችሁ ባዮች እና ጥራዝ ነጠቅ የፖለቲካ ተንታኞች
መድሪቱን ሞሏት ! ! በየቦታው ተቃውሞ በየቦታው የተኩስ ድምጽ ሆነ ! <<አንባገነኑ ኋላቀሩና አገር የበደለው መሪ>> በቁጡዎቹ አመጸኞች
እንደእንስሳ መንገድ ለመንገድ ተጎትቶ ተገደለ! ፊሽታና ጭፈራ ለሊቢያም አዲስ ቀን ሆነ ተባለ !! ዓለም ሁሉ እንኳን ደስ አላችሁ የዘመናት
ጨቋኛችሁ ተወገደ የሚል መልእክቱን አጎረፈ ! ጦርነቱ ግን አላቆመም፣
መጀመሪያ አማጺያኑ ለሁለት ተከፈሉና እርስ በእርስ ለስልጣን መታኮስ ጀመሩ፣ቀጥሎ ሶስት ትልቅ ቡድኖች ተፈጠሩ ፣ አራት ፣አምስት እያሉ
ቀጠሉ! አልቃይዳ እና ሊሎቹም ቡድኖች እንደተለቀቀ ቤት ተንጋግተው ገቡ ! ዛሬ በሊቢያ ስንት የተደራጁ ቡድኖች እንዳሉ ፈጣሪ ይወቀው !
ዛሬ ሊቢያ በቁሟ አጽሟ የቀረ የእውነት ከዓመታት በፊት የነበረች ከተማ ሳትሆን አስፈሪ የጦርነት ፊልም ለመስራት የሆሊውድ ሰዎች
የሰሯት ፍርስራሽ የፊልም ከተማ ተመስላለች ! አለም አቀፍ የሽብር ቡድኖች መናሃሪያ ናት ፣ አደንዛዥ እጽና የጦር መሳሪያ ገበያ ፣ ብሎም
የሰው አካል እየተበለተ የሚሽጥባት የሰው ቄራ እልፍ ብሎም ሰው እንደከበት በቁሙ የሚሸጥባት ተወዳዳሪ የሌላት የሰቆቃ ምድር !!
ያኔ አገራችንን እንቀይር ብለው ከተነሱት ዛሬ ግማሾቹ በጦርነቱ አልቀዋል ፣ የቀሩት ተሰደዋል ፣ ትቂቶችም ዛሬም መሳሪያ ተሸክመው የሰቆቃ
እና የስጋት ህይዎት ይገፋሉ ! እንቀይራታለን ያሏት አገር እንኳን ልትቀየር ለሌላው ህዝብም ጦሷ ተርፏል ! ጦሱ ከተረፋቸው ህዝቦች
መካከል እኛም አለንበት !34 ዜጎቻቸን ባደባባይ ዓለምን ባሳቀቀ መንገድ ታርደዋል! ዛሬ ይህን ጉዳይ ያነሳሁትም ለዚሁ ነው ከ 3ዓመታት
በኋላ እነዚህ በግፍ የተገደሉ ወንድሞቻችን እጽም በጅምላ የተቀበረበት መቃብር ተገኝቷል ! እንደቀልድ አንድ እርሻ ቦታ አካባቢ በአንድ
ጉድጓድ ውስጥ ሰብስበው አፈር መልሰውባቸው ነው የተገኘው! አጽማቸው ወደአገር ቤት ይላካል ተበሏል!
የእነዚህ ለጆች አጽም አጽም በቻ አይደለም ለዓለማችን ሰቆቃ እማኝ ነው ! ዛሬ እኛ ኢትዮጲያዊያን በየቦታው የጦርነት ከበሮ እየጎሰምን
ነው ! እዛም እዚህም በጦርነት ነገር እንደሚቀየር የሚያምኑ ግልፍተኞች እየተበራከቱ ነው ! ከእርስ በርስ ጦርነት ሰቆቃ ብቻ እንደምናተርፍ
ለማወቅ እጃችን ላይ ተሰብስቦ ከሚሰጠን የወገኖቻችን አጽም በላይ ሌላ እማኝ አያስፈልገንም! ከጦርነት ምንም አናተርፍም!ምንም!!
ጦርነት በምንም ሁኔታ አይቻር ! ከተጫረ ግን ከእልቂቱ የማንም ብሔር መሆን አያድንም ፣ የምንም እምነት ተከታይ በመሆንም ከመቅሰፍቱ
ተራፊ መሆን አይቻልም ! ችግራችንን ተነጋግረን ከመፍታት ባለፈ ወደማንም የምንተኩሰው ጥይት ማንንም ሳይሆን እኛን ራሳችንን
እንደሚገድል መርሳት የለብንም! ጅል ብቻ ነው የውሃን ጥልቀት በሁለት እግሩ የሚለካው ! ሰላም ሰላም ሰላም ብቻ!! ይህን ማድረግ
ባንችል እንኳን ያለን አማራጭ እንድንችል በሰላም መጣር በቻ ነው!
👇👇👇👇👇👇👇👇
የቆሙትን ምክር መስማት ከተሳነን ከተገደሉት እንማር!!
(አሌክስ አብርሃም)
@AlexAberham
share
👇👇👇👇👇👇
@AlexAberham
@AlexAberham
አቦ ዛሬ ለጥፍ ለጥፍ ብሎኛል! ልጁ ግን ላላማው ፍንክች የማይል ጀግና ነው !የፖሊሶቹን ፊት ስታዩ በሳክስፎን ትዝታ የሚጫዎትላቸው
እኮነው የሚመስለው!ደህና እደሩ በቃ!
Share👇👇👇
@AlexAberham
ብትሸጡ ዋጋችሁ ስንት ነው ?
(አሌክስ አብርሃም)
@AlexAberham
----------//---------
የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት እንደጉድ እየተከበረ ነው !እኔኳን በዓል የማልወደው ሰውየ ምስጥ ብየ እየተደሳሰትኩበት ነው ! ርችቱ እዚህ አገር
ህዝቡ በሙሉ ሸህ መሃመድ ሁሴን አላሙዲን ነው እንዴ ያስብላል! በየሄዳችሁበት ያንን የሸራተንን ርችት የሚያካክል ፍንዳታ ጋር ሰማዩ
በውብ የእሳት ቀለማት ይሞላል ፣ የምግቡንና የጣፋጩን ነገርማ ተውት! ያለምንም ግነት በዚህ በዓል ተርፎ የሚደፋው ምግብ ድፍን
አገሬን ሁለት ቀን ቀልቦ ባሳደረ ነበር! በተለይ እዚህ አሜሪካ የምትባል ጥጋበኛ አገር ገንዳውን ሞልቶ የተከመረ የበርገርና ፒዛ ትራፊ ሳይ
አገሬ ላይ አራት ጎአምሶችና ሁለት ቆንጆ ሴቶች ዛሬ አለማችንን እንቅጭ ተባብለን ሰሃን የምታህል አንድ ፒዛ ከበን የተነሳነውን ፎቶ ፌስቡክ
ላይ ይምንለጥፍበት ዘመን ውልብ ይልብኛል ! የሚጣለው የቤትእቃማ ግርርርርም ነው የሚላችሁ ! አንዳንዴ ጽድት ያለ ሙሉ ሶፋ፣ 55
ኢንች ቲቪ ከነማስቀመጫው ፣ ከትልቅ ፍሪጅና ከተጠቀለለ የፋርስ ምንጣፍ ጋር አለፍ በሎ ምን የመሰለ ስቶቭ ጋር ተጥሎ ያጋጥማችኋል
<<በነጻ ውሰዱት>> ከሚል ጽሁፍ ጋር ሚስት ነገር ይዛችሁ መጥታችሁ ትዳር መጀመር ሁሉ ሊያስመኛችሁ ይችላል!
እየቀለድኩ አይደለም! አገር ቤት ሰዎች ተጋደሉበት ሲባል የምትሰሙት መኪና አለ አይደል አንዳንድ ወገኖቻችን እጃቸውን በመስኮት ብቅ
አድርገው ሚስኪን ታክሲ ጠባቂ ሰልፈኛ ላይ የሚላጡበት አይነት በቃ የዛ አይነት መኪና መስኮት ላይ <<ትንሽ የሞተር ችግር ብቻ አለበት
በነጻ ውሰዱት>> የሚል ወረቀት ተለጥፎ ስታዩ ያንኑ መኪና ተደግፋችሁ እንዳስቴር አወቀ <<አገሬሬሬሬሬሬሬሬ >> ብላችሁ መዝፈን
ያምራችኋል! መኪና ለመጣል ራሱ መክፈል አለባቸዋ! ወገኖቸ ይህን የምነግራችሁ እናተን ለስደት ለማነሳሳት አይደለም! እቃ ይጣላል
ብለህ ስትመጣ ራስህን የሚያስጥል ምሬትም ሊገጥምህ ይችላል!(መቸመ ምቀኝነት ነው የሚመስልህ ሲመክሩህ ሃሃ) የዓለም ነገር
ግርም ስለሚለኝ ብቻ ነው! ፈልጉ ታገኛላችሁ የሚለው ቅዱስ ቃል አሜሪካ ለሚኖር ሰው ልክ ይመጣል!
ለማንኛውም ሁሉም ነገር አንጻራዊ ነው! አገር ቤት ነብስ የሚያስከፍል በቃ ጥሪቴ ንብረቴ የምትሉት የምትከበሩበት የምትመኩበት ነገር
እዚህ ገንዳ ላይ ተጥሎ ፈላጊ ሲያጣ ታያላችሁ ! ሰው ራሱ ዋጋው ከቦታ ቦታ ሲለያይ ትመለከታላችሁ አገር ቤት ዩ ዩ እያሉ ህጻናት
የሚከተሉት <<ፈረንጅ>> ስለተባለ ሃብታም ችግር ሲያልፍ የማይነካው የሚመስልህ ሚስኪን ነጭ ሱሪው ተቀዶና ጺሙ ጀልቶ ጎዳናውን
ሞልቶ የምበላው የለኝም ያለህን ጣልልኝ ሲልህ ባይኑ ዩ ዩ ኣያለ ሲከተልህ ታይና ሁሉ ነገር ዋጋው የጊዜና የቦታ እንጅ የነገሩ ክብርም
ውርደትም አለመሆኑ ይገበሃል! እና ክቡራንና ክቡራት ዛሬ ላይ ዋጋችሁ እጅግ ውድ ስለሆነ እንዳትኮፈሱ ህይዎት ገበያ ነው ! ዛሬ ላይ
እዚህ ገባ የማትባሉ ሰዎች ከሆናችሁም የእናተ መርከስና ተራነት ሳይሆን የተሸጣችሁበት ገበያ ባህሪ መሆኑን ተገንዘቡ !ብትሸጡ ዋጋችሁ
ስንት ነው? ተውት አትገምቱ ምንም ሁኑ ምን ሁሉም ቦታ እኩል ዋጋ ያላችሁ ፍጥረቶች ለመሆን የትም በምንም ሁኔታ ዋጋው ክብሩ
የማይቀንስ ብቸኛ የውድነት ሚዛን እግዚአብሔር በህይወታችሁ ይኑር ! አበቃ !!አዲሱ የፈረንጆች ዓመት እንዲህ አናግሮናል ! ለምታከብሩት
መልካም ዓዲስ አመት !
@AlexAberham
ትዳርና የፊልም ኢንዳስትሪያችን!
(አሌክስ አብርሃም)
@AlexAberham
-----------//-------------
በዓለማችን ላይ በሆሊውድም ሆነ በሌሎች የፊልም ካምፓኒዎች ታዋቂ የሆኑ እንስቶች በልጅነታቸው በወጣትነታቸው ብሎም በስተርጅና
ይህይዎት ዘመን ታዋቂ እንደሆኑ በሙያቸው ዘላቂ እውቅና ሲቸራቸው እስከሞትም በሙያቸው ህዝብ ሲያገለግሉ የሚገባቸውም ክብር
ሲሰጣቸው እንመለከታለን ! ባገራች የፊልምና ፋሽን ኢንዳስትሪ ውስጥ ግን ትልቅ ቦታ ያላቸው ታዋቂ ሴቶች ካገቡ ወይም ልጅ ከወለዱ
በኋላ በተለይ የፊልም ኢንዳስትሪው ላይ ብዙም የማይታዩት ለምንድነው? የሆነ ሰዓት ላይ ሚዲያው ከነሱ ውጭ አይኔ አይይ ይልና፣
ጋዜጠኛው ሁሉ ሲያስነጥሳቸው ሁሉ ካልዘገብኩ ይለንና ልክ ሲያገቡ አልያም በተለያየ ምክንያት ከሚዲያው ፊት ዞር ሲሉ አልፎ አልፎ
ለዛውም አዲስ ስራ ከሰሩ አልያም ለበዓል ካልሆነ ድራሻቸውን ያጠፋብናል ! ምንም ይሁን ምን ብዙዎቹ በዚህ አዝግ እና መከራ
በማያጣው ኑሯችን የህይዎት ቅመም ረጭተውበታል! እየወቀስናቸውም እየዘለፍናቸውም ጭምር! የሆነ ሆኖ ኢንዳስትሪው ፣ ሚዲያው
እንደአጉል ጎረምሳ ያላገባች ሴት የሚያሳድድበት ምክንያት ምንድነው?
@AlexAberham
ሴት ልጅ ራሷ የፈጣሪ ጽሁፍ ናት !
(አሌክስ አብርሃም)
@AlexAberham
--------//------
አንድ ታዋቂ ገጣሚ ጋር እያወራን ነው ! ብስጭት ብሎ <<ምናይነት ሴሰኛና ሴት ወዳድ ማህበረሰብ ነው ያለን >>
<<ምናደረገን ደግሞ >> ልጁ ብዙም ወቀሳ የማያበዛ ገና ከፌስቡክ በፊት ሳውቀው ጀምሮ አርፎ ከመጻፍ ውጭ ስለማንም ግድ የሌለው
ስለነበር በአባባሉ መደንገጤ አልቀረም!
<<ሴት ይወዳል ፣ወንዱ የተማረው ያልተማረው ሴት ይወዳል ! ያገባው ያላገባው ሴት ይወዳል፣ ሃይማኖተኛው ከፈጣሪው በላይ ቆንጆ
ሴት ያመልካል! በድግሪ የተመረቀች ሴት ፎቶ ላይ ላይክ ከሚያደርገው መቶ ሰው ሰማኒያው ጋውኗን ወጥሮ ለሚታየው ጡቷ ነው! አስሩ
ለከንፈሯ አምስቱ ለፈገግተዋ አራቱ ላፍንጫዋ ነው ላይክ የሚያደርገው ! አንዱ ብቻ ነው ጋውኗን ላይክ የሚያደርገው እሱም ጋውን አከራይ
ይሆናል ! ሴሰኛ ነጋዴ ሁሉ !ታዘብ ከፈለክ አንድ እንኳን ሰው በምን ተመረቅሽ የሚል የለም! ኮንግራ እያለ መንጫጫት ብቻ የተረገመ ሁሉ!
<<በደፈናው ጨፈጨፍከን>>
ምን በደፈናው ትላለህ ሴት ሲያይ ዳፍንታም እውር የሚሆን ወንድኮነው ፌስቡክን የወረረው <<አገሬ ፣ሶሻሊዝም፣ ሊበራሊዝም ትግሬ
ኦሮሞ አማራ ቤኒሻንጉል እያለ የሚደሰኩረው ሁሉ በውስጥ መስመር በየሴቱ አካውንት ሲልከሰከስና <እንትን > ሲለምን የሚውል ሴሰኛ
ነው!(እግዞ ) አይቸዋለሁ በሴት ስም የውሸት አካውንት ከፍቸ አዳሜን አይቸዋለሁ! አኦን ላይን ስሆን ሰጋውም ልቡም ኦን የሚሆንበት
አምስት ሺህ ጓደኛ ! ከውጭ በለው በጓንዴ ይልና በውስጥ መጥቶ <<ውዴ ሆዴ>> ሆዳም! ልጋጉን እያዝረበረበ ሃሳብሽ ምጡቅ ነው
ይላል አንድ መስመር እንኳን ሳልጽፍ! ሴሰኛ ሁሉ ! እዚህ ፌስቡክ ላይ አንዲት ነብስ ያለው ጽሁፍ የምትጽፍ ሴት አለች? ማናት እስቲ ?
እዚች አገር ላይ አንድ ነብስ ያላት ገጣሚ ሴት ጥራ እስቲ !
አንድ አምስት ጠራሁለት
ዱቄት ሁሉ! ሴት ስለምትወድ እንጂ አሁን እነዚህ ምናቸው ነው ገጣሚ ? ውዴ ደረትህ አገሬ አበባሽ . . . የትኛው ደረት ነው? ቅዠታም
ሁሉ ! ፊዴራል እንዳርጋው በዳሶ በጭንቅላቱ ሲያቆመው ደረቱን እንደከበሮ ሲደልቀው ያላየች ለመመስል ያገሯን ወንድ ካላጀገንኩ የምትል
አጨብጭቢ ! ደግሞ በያካውንቱ እየዞረች በየስሙ ላይ የ እየጨመረች የወንዱን ጩኽት ተከትላ ከማላዘን በስተቀር ማን አለች እስቲ ?
ሱሪ በገዛችና ጸጉሯን በተሰራች ቁጥር ፎቶ እየለጠፈች የላይክ ምጽዋት የምትለምን ደባሪ ሁሉ ! (እግዞ)
አረ በህግ ?
ህግ ? ህግ አስከባሪው ራሱ የሴት ቂ. እያሳዩ ኤርታሌ ቢወስዱት አገር ረስቶ ዘሎ ይገባል! የሳትራት ! ህግ አስከብር በተባለበት ሽጉጥ
በየመሸታ ቤቱ በሴት ሲጨፋጨፍበት ስንቱን አላየንም?
ሆ !
ሆ ምንድነው ? ሆ ብሎ ማጀብ ሆ ብሎ መደገፍ ሆ ብሎ መርገም ሆዳም ሁሉ !
ፌስቡክ ላይ መጻፍ ከጀመኩ አስር ዓመቴ በፖለቲካው ብትል በማህበራዊ ጉዳዩ ያልጻፍኩት ግጥም የለም ከመቶ ቢበዛ ከመቶ ሃምሳ ሰው
በላይ ላይክ አድርጎኝ ያውቃል? አያውቅም ! በተለይ ታዋቂ ነን የምትሉትማ ብትሞቱ የሚጽፍ ሰው አታበረታቱም! አንዲት ሴት ግን ምንም
ሳትናገር እየተስለመለመች የግማሽ ደይቃ ቪዲዮ ብትለቅ አምስት ሺህ ኮሜንት አስር ሃያ ሺህ ተመልካች ሲንጋጋ ታያለህ ! ጨዋ
ለመምሰል <<አለባበሰሽ ኢትዮጲያዊ አይደለም >> እያለ በሆዱ ጡቷን እንዳትሸፍነው ይሳላል !<<ምንድነው እንዲህ መገልፈጥ እያለ
ልቡን ገልፍጦ ቪዲዮውን ሰላሳ ጊዜ ደጋግሞ ያያል! ልጆቹ የሚላምጠ ምግብ አጥተው ሁዳቸው እየጮኽ እሱ በውድ ኢን ምራቁን
ይውጣል ቲሽ ምናገባው ስለባህል ? የኔ ማር እያለ አካውንቷ ላይ ይርመሰመሳል ቁጫጭ ሁሉ !
ሴቶቹም ይችን ለምደው የለት ላይካቸውን ለማገኘት የማይለጥፉት ነገር የለም አንዳንዶቹማ የቤተሰባቸውን ፎቶ ያሉትንም የሞቱትንም
ለጥፈው ፣ ልብሳቸውን ጫማቸውን ለጥፈው ፣ የቤት እቃቸውን ለጥፈው ፣ያባትና የናታቸውን የፍች ወረቀት ሁሉ ለጥፈው ፣የመስሪያ
ቤታቸው ሰው የተናገረውን ሁሉ ጽፈው ጨርሰው ባላቸው ጋር <<እንትን የሚያደርጉበትን>> ፐሮግራም ሁሉ መለጠፍ ነው የቀራቸው !
ሱሰኛ ሁሉ የላይክ ልክፍታም ሁሉ ! ትዳር እጅ እጅ ሲላት እዚህ እየመጣች ዛሬም መፈለጓን በጅ አዙር ተፈትሽእለች(እግዞ)
እና አንተ ላይክ ፈልገህ አይደህ ይሄ ሁሉ. . .?
<<ሰርቸ ነዋ! አይኔ እስኪጠፋ አንብቤ ፣በየጫት ቤትና መጠጥ ቤቱ ዙሬ መሰለህ ? ራሴ እስኪዞር አውርጀና አውጥቸ ተጠብቤ ነዋ !
የማንንም እንቶፈንቶ ለጥፌ ነው እንዴ . .አንገቴን ደፍቸ ተምሬ . . .አስተምሬም ! ለነገሩ አንተም ያው ነህ !! አንድ ቀን ላይክ አድርገህልኝ
ታውቃለህ? እስካሁን ቆንጆ ሴት ብሆን አብርሽየ እጅህ ይባረክ ምናምን ብልህ ኮሜንቴ ስር ሳይቀር ሪፕለይ ታደርግ ነበር >>
ምናልኩት ? ሃቅ ነው!! ትንሽ ላበሳጨው ብየ ደግሞ << አትድከም ሴት የግዜር ጽሁፍ ናት ! አሳምሮ ጽፎ ምድር ላይ ፖስት ያደረጋት አይኖቿ
የፍቅር ግጥም ፣ ፈገግተዋ አጭር የፍቅር ልብወለድ፣ ለቅሶዋ ትራጂየዲ ፣ ድምጿ የመድረክ ቲያትር ሙሉ ፓኬጅ ምን እናድርግ እኛ? !
እንደውም በዚህ የፈረንጆች አዲስ አመት አንድ ሺህ ወንድ ከነድንፋታው ፣ከነድራፍት ብርጭቆው ፣ከነግጥሙ ፣ ከነፍልስፍናው ፣ ከነ
ፖለቲካው ፣ ከነለዛ ቢስ ነቆራው አባርሬ በምትካቸው የሚስለመለሙ ቆንጆ ሴቶችን ጓደኞቸ እንዲሆኑ የመጋበዝ እቅድ አለኝ ! ሴት ልጅ ራሷ
የፈጣሪ ጽሁፍ ናት!! ስትወለድ መግቢያ ስታድግ ምስጋና ፣ስታፈቅራት ገጽ አንድ ስታገባት ገጽ ሁለት ፣ስትወልድ ገጽ ሶስት ፣ ስትዘንጥ ውብ
የመጽሃፍ ገጽ ልብሷን ስታወልቅ ታሪክ ስትተኛ ጥሞና ስትነቃ ንጋት . . . >>
ዝጋ ! አለኝ ቦግ ብሎ !
ዘጋሁ !!ድሮውንም ወንድ ጋር ማውራት እስካሁን ሴት በትሆን የኔ ማር ወሬ እንቀይር ነበር የምትለው አገር በሚያስቀይር ውብ ፈገግታ!
@AlexAberham
ራሳችን ላይ ለምን ሰነፍን ?
(አሌክስ አብርሃም)
@AlexAberham
--------//---------
የኢትዮጲያ 80% ህዝብ በገጠር የሚኖር አርሶ አደር ነው ! ታዝባችሁ ከሆነ ግን ፊልሞቻችንም ሆኑ የመድረክ ቲያትሮቻችን ላይ የገጠሬ
ገጸባህሪ ተላብሰው የሚጫዎቱ ተዋናዮቻችን የገጠሬ ገጸባህሪ ተላብሰው መጫዎት በጣም ይከብዳቸዋል! ይግረማችሁና ከገጠር
መጥተው ከተማ የተማሩ ተዋናያን ሳይቀሩ የገጠር ገጸባህሪ ተላብሶ መጫወት አይሆንላቸውም! እስቲ የትኛዋ ሴት ናት የተሞረደ ጥፍርና
ለስላሳ ጣቶች ያሏት? የት ገጠር ነው ቅንድቧ የተቀነደበ የገጠር ሴት ያለችው ? የትኛዋ የገጠር ሴት ናት ንግግሯ ላይ ክ የምትጨምረው ?
ወንዱንማ ተውት ወይ ይጋነናል ፣ ወይ ጅላጅል ያደርጉታል ወይ ዘበኛ ይሆናል አልያም ነብሰ ገዳይ ፣ አልያም የከተሜ ባህሪ ይጫነዋል!!
የገጠርን ነብስ በገጠር ልሳን ሳይሆን በገጠር ልሳን የካሳንችስ ነብስ ! እንዴት ራሳችንን ሁኖ መተወን አቃተን? ጥሩ የገጠር ገጸባህሪ
ተላብሶ የተጫወተ ተዋናይ ሳስብ ወደአእምሮየ የሚመጣው አብርሃም አስመላሽ ብቻ ነው!!
ሌላው አስገራሚ ነገር ህዝባችን 100% በሚባል ሁኔታ ደሃ ነው! እንደውም ከድህነት ወለል በታች ነው! ፊልሞቻችንን ተመልከቱ ድሃ ሁኖ
ከመተወን ይልቅ ሃብታምና የሃብታም ልጅ ሁኖ መተወን ባንጻራዊነት ይዋጣላቸዋል! በተለይ ሴቶቻችን የሃብታም ልጅ ሁኖ መተወን
ሲችሉበት ! ከአማርኛ ፊልሞች ከግማሽ በላዩ የሃብታም ልጅ ሴቶች ያሉበት ነው! አቤት መኪና አነዳድ ፣ አቤት መሪ አያያዝ ፣ አቤት
አበላል ? የእውነት የሃብታም ልጆችን አይተን ሰለማናውቅ እንጅ መናልባትም ይበልጧቸው ሁሉ ይሆናልኮ ! ያልሆነውን መተወን ግን እንዴት
ተሳካልን?
ሶስተኛ ልጨምር የአገራችን ሴቶች ብዙዎቹ ያን ያህል ወጣ ያለ ባህሪ የላቸውም ! እሷ ቀውጢ ነች የምትባለው እንኳን ያን ያህል የባህሪ
ችግር አይታይባትም ! ጨዋ ማለት በገሃዱ ዓለም አርፋ ትምህርቷን የምትማር፣ የማትጠጣ፣ መጥፎ ጓድኞች ጋር የማትገጥም ፣ ሜካፕ
የማታበዛ (ሃሃ) አጉል ልታይ ልታይ የማትል ፣ ትዳሯን የምታከብር ህብረተሰቡ ያስቀመጣቸውን የሞራል ህጎች የምትከተል፣ ቀሚስ
የምትለብስ ነጠላም ጣል የምታደርግ ወዘተ አይነት ነው ! ብዙዎቹም እንደዛ ናቸው! ፊልሞቻችን ላይ ጨዋ ሴቶች ሲሳሉ በጣም ቆንጆና
ሜካፕ እንደጉድ የተለሰነባቸው (ተኝተው ሲነሱ ራሱ ኩላቸው ዝንፍ የማይል ብቻቸውን ቢተኙ እንኳን እሽ፣ እንዴት ወንድ ጋር ተኝተው
ሜካፓቸው ነክች አይልም?) አይናቸውን የሚያስለመልሙ ፣ ሲናገሩ የሚፈላሰፉ አለ አይደል <<ፍቅር የነብስ እውነት እንጅ ከገበያ የሚገዛ
ሸቀጥ መናምን >> የሚሉ ፣ ሲያፈቅሩ ትራስ የሚያቅፉ ፣ በጣም ዝግይት ከማለታቸው ብዛት ጨዋ ሳይሆን የእምሮ እድገት ውሱንነት
ያለባቸው የሚመስሉ የሚሆኑት ለምንድነው ?
@AlexAberham
----------//---------
እኒህ ሰውየ !
(አሌክስ አብርሃም)
@AlexAberham
----------//----------
አለመገጣጠም ይሁን ሌላ ምክንያት እንጃ ብቻ መጋቢ ሓዲስ እሸቱን በአካል አይቻቸው አላውቅም ፣ ግን ሁልጊዜ የሚገርመኝ ነገር አንድ
ቀን ስልክ ተደወለልኝ! እሳቸው ነበሩ <<ግሩም መጽሓፍ ነው የጻፍከው በርታ >> አሉኝ ! እሱ ሲገርምኝ እንደገና ደውለው እንደገና
ስለጻፍኩት ሌላ መጽሃፍም ጭራሽ አንድ ርእስ ሁሉ መዘው እንደወደዱትና መልእክቱን እንዳደነቁ ፣ወጣት ጸሃፊ ይብዛልን ከሚል ማሳረጊያ
ጋር ነገሩኝ ! ሌላ ጊዜ ለሶስተኛ ጊዜ ደውለው ተመሳሳይ ነገር ነገሩኝ ! ለብዙ ሰው ይሄ ምንም የማያስገርም ነገር ሊመስል ይችላል !ነገሩ
ወዲህ ነው! ይች አንድ ሁለት ተብሎ ቢቆጠር ደርዘን እንኳን የሚሞላ በሕይዎት ያለ ነብስ ያለው ጸሃፊ በማይገኝባት ሚስኪን አገር ያሉትም
እርስ በርስ ከመደጋገፍና ከመማማር ይልቅ የጥላቻ የመቀናናትና የመናናቅ አዙሪት ውስጥ ሁነው አንዱ ያንዱን ውድቀትና ድክመት ከቡና
ጋር ሲያወራርድ ነው የሚውለው!
ችግርና በሽታ ከሚገድለው ደራሲ በላይ እንደጅብ እርስ በእርስ ተበላልቶ በቁሙ ከነመክሊቱ የሚሞተው ይበዛል! ከእያንዳኑዱ የህትመት
ብርሃን ካየና ከተደነቀ መጽሃፍ ኋላ በክፋታችን ሕይዎቱን ያጨለምነው ደራሲ አለ ! ዛሬ ላይ ብቻ ሳይሆን ትላንትም ታሪካችን እንዲሁ ነበር
(ስንዱ አበበ አለች ለጉድ ያቆማት፣ ብትመሰክር ስንት ጉድ አለ) በነገራችን ላይ እዚህ ፌስቡክ ላይ << ማንበብ ይሞላል ፣ማንበብ
ያጎድላል >> እያለ እንደቁራ ሲጮህ የሚውለው ብዙሃኑ ከማንበብም ከሚያነብ ሰውም የተጣላ ፣ ሲመቸው የውሽት አካውንት እየከፈተ
ሊጽፍ የሞከረውን ሁሉ ሲቀብር የሚውል ቀባሪ ነው! ወደተነሳሁበት ሃሳብ ስመለስ እኒህ ሰው የእድሜ ይሁን የሃይማኖት የፖለቲካ ይሁን
ሌላ የልዩነትን ግንብ፣ ጥሰው የሰራን ማበረታታት መክሊታቸው የሆነ ድንቅ ሰው ናቸው! ት ል ቅ ሰው መጋቢ ሓዲስ !!
@AlexAberham
👇👇👇👇👇👇👇👇👇👇
ገናን 😂😂
@AlexAberham
------//
#1 ነገረኛ ገዢ የሞባይል ካርድ ገዝቶ በፔስታል አርግልኝ ይላል😃😀😃
😁😁😁😁😁😁😁😁😁😁😁😁😁😁😁😁😁😁😁😁😁😁

#2 የገና በግ ታክሲ ውስጥ ሲጫን

ተሳፋሪ በቁጣ: - "

እንዴት ከበግ ጋር ትጭነናለህ!" ብሎ ቀወጠው።

ረዳቱም :-
" ዋጋውን ብትሰማ ኖሮ
ወንበር ትለቅለት ነበር።"
😁😁😁😁😁😁😁😁😁😁😁😁😁😁😁😁😁😁😁😁😁😁
@AlexAberham
<<ካልበላችሁ እንደኢትዮጲያዊያን ትሆናላችሁ>>
(አሌክስ አብርሃም)
@AlexAberham
----------//----------
አንድ አስተማሪ ረባሽ ተማሪውን ወላጅ አምጣ ይለዋል ! በቀጣዩ ቀን የልጁ አባት በተንፈላሰሰ መኪና ልጁን ይዞ ትምህርት ቤት ይገኝና
መምህሩን <<ልጀ ምን አጠፋ >> ይላል?
ልጅዎት በትምህርት ሰዓት ያወራል
በዛ ላይ የተሰጠውን የክፍልም ይሁን የቤት ስራ አይሰራም>> እያለ በጨዋ ደንብ ልጁን እንዲመክሩት ያሳስባል ! አባት ራሱን ኣየነቀነቀ
መምህሩን ሲሰማ ከቆየ በኋላ ወደልጁ ዞር አለና
<<አስተማሪህን ተመልከተው >> አለ በቁጣ ! ልጅ ወደአስተማሪው ዙሮ ከራስ ጸጉሩ እሰከእግር ጫማው ተመለከተው ፣ ያው ሚስኪን
አስተማሪ ተራ ቆዳ ጫማ ፣ በመታጠብ ብዛት የነጣች ጅንስ ሱሪ ኮሌታዋ ብን ያለች ሸሚዝ ለብሷል ! አባት ወደመምህሩ ዞር ብሎ
<<መምህር መኪና አለዎት ?>> ሲል ጠየቀ
<<አይ የለኝም>> አለ መምህሩ ጥያቄው ግራ ገብቶት
<<አሃ ! ታክሲ ሰልፍ ላይ ተጋፍተው ነዋ ወደስራ የሚመጡትና የሚሄዱት ፣የራስዎ ቤትስ አለዎት ? >>
<<አይ ተከራይቸ ነው የምኖረው>> አለ መምህሩ ተሳቆ
አባት ወደልጁ ዙሮ <<ሰማህ አይደል አንተ?! እየው ትምህርትህን በስርዓት ካልተማርክ እንደዚህ መምህር ነው የምትሆነው!!>>
እና ምን ለማለት ነው?ምንም ለማለት አይደለም!
በሌሎች ሰቆቃ ፣ያውም ህጻን ልጅ አቅፈው ፣የሞቀ የደመቀ ሕይዎታቸውን በጦርነት ተነጥቀው አስጠጉን ብለው በመጡ ሚስኪኖች ላይ
<<ማስተማር >> በሚል ያፈጀ ሰበብ እየተጠቋቆሙ እንደነሱ ነው የምትሆኑት አይነት ብሔራዊ ማላገጥ አሳፋሪ ነው!! ጭራሽ ለቀረጻው
ተገቢው ክፍያ ተከፍሏቸዋል ይልሃል ! ጉዳዩ የክፍያ ነው? ይህን ድራማ ተሰደው ከነዚህ ሶሪያዊያን በባሰ ሕይዎት ውስጥ ሁነው የሚያዩ
ሚሊየን ኢትዮጲያዊያን መኖራቸውን የረሳ ዝንጉነት! ግርምኮነው የሚለው ለመሆኑ ማንን ነው ስለጦርነት አስከፊነት የምናስተምረው?
የጦርነትን አስከፊነት ለኛ ለኢትዮጲያዊያን ለማስተማር ይሄን ያህል ያስኬድ ነበር ? ሽዎች አባቶቻቸውን በርስበርስ ጦርነት ገብረው ያላባት
የሚኖሩባት አገር ላይ ኮነን ፣ከዚህ በላይ ምን እንማር ? እንዲሁ በየሰፈራችን የጦርነት በትር ያረፈበት የሚያነክስ አይኑ የጣፋ ዜጋ
የሞላባት አገር በየመንገዱ የሚለምን አካል ጉዳተኛ ያለባት አገር ናትኮ ከዚህ ወዲያ ምን እንማር ? ዛሬ ዲያስፖራ ከምንለው የሚበዛው
በቀይ ሽብር ፣ በዘር ግጭት ፣ በአንባገነን አገዛዝ በጦርነት ተሰዶ ፣ከሚወዳት አገሩ ርቆ ወጣትነቱን የገበረ አይደልም እንዴ? እውነት
ማስተማር ነው ወይስ በሌሎች ችግር የማትረፍ ኢ- ሰበዊነት ?
ይታያችሁ የዛሬ ስንት አመት የተራቡ ህጻናቶቻችን እና ሴቶቻችን ከሲታ ምስል በመላው አለም <<ለእርዳታ>> በሚል ሰበብ በየቴሌቪዥኑና
ጋዜጣው ተሰራጭቶ ነበር ርሃቡ አለፈ፣ ዘለፋውና ታሪካችንን እየመዘዙ ማሳቀቁ ግን ዛሬም ኢትዮጲያዊያንን በየሄድንበት ይከተለናል !
ኢንተርኔቱ ሚዲያው ኢትዮጲያ ስትለው ከላሊበላና አክሱም ቀድሞ ፣ከእንግዳ ተቀባይነታችንና ከአድዋ ድላችን አስቀድሞ ያንን የሰቆቃ
እርቃን ፎቶ አውጥቶ መዘርጋት ይቀለዋል! ያ ክፉ ዘመናችን ቁስላችን ነው ! የሰለጠኑቱ አገራት እናቶች ሳይቀሩ ምግብ አልበላም የሚሉ
ህጻናት ልጆቻቸውን ፎቷችንን እያሳዩ <<ካልበላችሁ እንደኢትዮጲያዊያን ትሆናላችሁ>> እስከማለት ተዘልፈናል ፣ እየተዘለፍን ነው
እንዘለፋለንም! ደግሞ የሚገርሙት አታካብዱ የሚሉት ! እንኳን ያለውን ሁሉ ተነጥቆ ሊለምንህ የመጣን ጊዜ የጣለው ሚስኪን ቀርቶ
ቸግሮት ሊበደርህ የሚመጣ ጎረቤትህን ገመና ከባድ ሚስጥር ነበር ባገራችን !! ማክበድ ያለብንን ስናቃልል ነው ከባድ የማንነት ቀውስ
ውስጥ የገባነው !
እንደው ግን አዲስ አበባ ብቻ ያላችሁ ሃብታሞች ነገ ይሄ ቀን አልፎ በስሜታዊነት በምንሰራው ነገር እንደሐገር ከመተዛዘብ ምናለ ለነዚህ
ሚስኪን ስደተኞች አገራቸው እስኪረጋጋ መጠጊያ ነገር ሰጥታችሁ በሰው ፊት ከመገረፍ ብትታደጓቸው? ምን በሰው ፊት በቻ በካሜራም
ፊት እንጂ!! <<እግዚአብሔር ይመስገን ሶሪያዊያን ወደአገራችን ተሰደው መጡ እንትን አካባቢ እየለመኑ ነው >> ከሚለው የፌስቡክ ለጣፊ
እስከምናከብራቸው አርቲስቶቻችን በሌሎች ችግር የደቆሰው ትከሻ ላይ ቁመው ከፍ ሊሉ ሲንጠራሩ ማየት እንደአገር እንደህዝብ
የሚያሳቅቅ እንጂ ምንም የሚያኮራም የሚያስተምርም አይደለም ! ብንማርማ በራሳችን ሚሊየን ልጆች ስደትና መንከራተት በተማርን ነበር !
ባጠቃላይ ይሄ የድራማ ትእይንት <<ካልበላችሁ እንደኢትዮጲያዊያን ትሆናላችሁ >> ስድባችን በአማርኛ ተተርጉሞ ራሳችን ላይ
ያላገጥንበት ድንዛዜ ነው !
@AlexAberham
👇👇👇👇👇👇👇
👆👆👆👆👆👆👆
@AlexAberham
Share
👇👇👇
@AlexAberham
@AlexAberham
" የዕለት "ነገራችንን" አትንሳን! "
( በአሌክስ አብርሃም)
በቅርብ ቀን
የህይወት ስንክሳራችንን በየዕለት ትዝብት የምናይበት
👇👇👇👇👇
የለት "ነገራችንን" አትንሳን!
( አሌክስ አብርሃም)
👉 @AlexAberham